ዮሐንስ የበላው መጽሐፍ ለምንድነው “ታናሽ” የሆነው?



ቤተክርስቲያኖች በመታወራቸው ምክንያት የሚቃረኑዋቸውንና ትተው የሚያልፏቸውን ትንንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መረዳት የሚችሉ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው።

First published on the 4th of December 2021 — Last updated on the 4th of December 2021

ራዕይ 10፡2 የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥

በዚህ ትንቢት ዘመን ውስጥ ቤተክርስቲያኖች በተቃረኑዋቸው ወይም ቸል ብለው ባለፉቸው በትንንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን።

በትንንሽ ቁጥሮችና በትንንሽ ሕብረቶች ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን። በትልልቅ ቤተክርስቲያኖች ላይ አይደለም ትኩረት ማድረግ ያለብን።

ዕዝራ 9፡8 አሁንም ቅሬታ ይተውልን ዘንድ፥ በተቀደሰውም ስፍራው ችንካርን ይሰጠን ዘንድ፥ አምላካችንም ዓይናችንን ያበራ ዘንድ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ ለጥቂት ጊዜ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ሞገስ ተሰጥቶናል።

እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ሥራውን የሚሰራው ከጥቂት ቅሬታዎች ጋር ነው። ስለዚህ በሰው ዘንድ መገፋትን እንጂ ተቀባይነትን አትተብቁ።

ኢሳይያስ 1፡9 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር።

ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ዘመን ለመናገር ሎጥ የሰዶም ከተማ ላይ እሳት ከመውደቁ በፊት ከሁለት ሴቶች ልጆቹ ጋር ለጥቂት ያመለጠበትን ታሪክ እንደ ምሳሌ ተጠቀመ። ሁለት ትልልቅ ከተሞች በእሳት ተቃጥለው ሲጠፉ ሶሶት ሰዎች ብቻ አመለጡ። እግዚአብሔር የቁጥር ብዛት አያስገርመውም። ከሙሽራይቱ የሚፈልገው ብዛት ሳይሆን ጥራት ነው።

ሉቃስ 17፡28 እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤

አድገው ትልቅ ጥፋት የሚያስከትሉት ትንንሽ ስሕተቶች ናቸው።

መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 2፡15 ወይናችን አብቦአልና የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮች፥ ጥቃቅኑን ቀበሮች አጥምዳችሁ ያዙልን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ተመርምረው ለማጋለጥ የሚያስቸግሩ ትንንሽ ስሕተቶች ሾልከው ይገባሉ። ስሕተት ልክ እንደ በሽታ አምጪ ሕዋስ ወይም እንደ ጀርም ነው፤ ምክንያቱም ስሕተት እየተባዛ ይሄዳል። ስሕተት ውስጥ ስንገባ ትምሕርታችንን ለማረጋገጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የመጠቀም ልማዳችን እየቀነሰ ይሄዳል። ከዚህም የተነሳ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየራቅን እንሄዳለን።

ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተገለጡ ሚስጥራትን የመተርጎም መብት ያላቸው ይመስላቸዋል። ይህ ስሕተት ነው።

2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡2 ቃሉን ስበክ

ማቴዎስ 4፡4 እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው።

ቃሉ ውስጥ የተጻፈውን ብቻ ነው ማመን ያለብን።

ሰዎች ሰባተኛውን ማሕተም እናውቃለን ይላሉ። ሰባተኛው ማሕተም ግን ዝምታ ነው። ዝምታን ማንም መተርጎም አይችልም። ይህ ስሕተት እየተባዛ ነው።

ስለዚህ ሰባቱ ነጎድጓዶች ምን እንደተናገሩ እናውቃለን በማለት አሁንም ሰዎች ያልተጻፈውን የመተርጉም መብት አለን ይላሉ። ከዚህም የተነሳ የተለያዩ የነጎድጓድ ትርጉሞች ተፈልፍለዋል። ስለዚህ ዳንኤል በራዕዩ ያየው የአሕዛብ ምስል እግር ላይ እንዳሉት ጣቶች ስሕተቶችም ተባዝተዋል።

ከዚያም ቀጥለው ደግሞ የኢየሱስን አዲስ ስም እናውቃለን ይላሉ። ይህም ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም። ስለዚህ ይህ አስተምሕሮ መጽሐፍ ቅዱስን በግልጽ ይቃረናል።

ራዕይ 19፡12 ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤

በዚህ ቃል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን አዲስ ስም ማንም ሰው እንደማያውቀው በግልጽ ተናግሯል። ይህንን ስም አውቀዋለው የሚል ማንኛውም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እየተቃረነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን መቃረን ጥሩ አይደለም።

 

ኢሳይያስ 28፡13 ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል።

ስለዚህ እውነትን መረዳት የምንችልበትን ፍንጭ እንድናገኝ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ መመርመር አለብን።

እያንዳንዱ ትንንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሁሉ በቦታው መጋጠም አለበት እንጂ ቸል መባል የለበትም።

ኢየሱስ ለምንድነው ሁለት ጊዜ በምድር ላይ በጣቱ የጻፈው?

ሰባኪዎች ይህንን ትምሕርት ቸል ይሉታል። ነገር ግን ይህ መልእክት ለአይሁዳውያን የሙሴ ሕግ እነርሱን ለመለወጥና የተሻሉ ሰዎች ለማድረግ አቅም እንዳልነበረው የሚያሳይ ትምሕርት ነው።

ኢየሱስ አምስት ሺዎቹን እና አራት ሺዎቹን ባበላ ጊዜ ቀጥሎ ከምግቡ በተረፉ መሶቦች ቁጥር ላይ ትኩረት አደረገ። እነዚህም ሰዎቹ ያልበሏቸው የምግብ ቁርስራሽ ናቸው። ለምን?

ማቴዎስ 16፡9 ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?

10 ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?

ሰዎቹ አንበላም ያሉት ምግብ ትኩረቱን ስቦታል።

12 መሶቦች እና 7 መሶቦች ነበሩ። የነዚህ ሁለት ቁጥሮች ትርጉም ምንድነው?

ቤተመቅደሱ ውስጥ 12 ሕብስት እና ሰባት ቅርንጫፍ ያለው መቅረዝ ነበሩ። እነዚህ ቁጥሮች ለምን ተደገሙ?

ጭንቅላታችሁ ከአካላችሁ ጋር የተጋጠመው በጀርባ አጥንታችሁ ነው። ሰባት የአንገት አጥንቶች እና ጎድኖቻችሁን የሚሸከሙ አስራ ሁለት የጀርባ አጥንቶች።

እነዚህ ጥቅሶች የሚገጥሙበት ሃሳብ ብቅ እያለ ነው። ኢየሱስ ምን ሊነግረን ነው የፈለገው?

ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ ነው (የቤተክርስቲያን ራስ ፖፑ ወይም ፓስተሩ አይደለም)።

 

 

እርሱ ከአካሉ ከቤተክርስቲያን ጋር በሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ተጋጥሟል። የመጀመሪያው ልክ እንደ ባለ ሰባት መብራቱ መቅረዝ የእግዚአብሔርን ብርሃን ለማብራት በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የምትኖረዋ ቤተክርስቲያን ናት።

ሁለተኛው ቡድን ደግሞ 144,000 ሆነው በታላቁ መከራ ዘመን ውስጥ ጌታ ኢየሱስን ለመቀበል የሚመለሱት 12 የእስራኤል ነገዶች ናቸው።

እነዚህ አስራ ሁለት ነገዶች በቤተመቅደሱ በቅድስት ስፍራ ውስጥ ባለው 12 ሕብስት ተወክለዋል። ስለዚህ አይሁዶች ጌታን ለማግኘት ዛሬ ወደ እስራኤል መመለስ አለባቸው። እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ትልቁ ትኩረቱ አይሁዶችን ወደ እስራኤል መመለስ ነው።

ወደ ምግብ ቅርጫቶቹ ተዓምራት እንመለስ።

ኢየሱስ ጥቂት ምግብን በማብዛት ሕዝቡን ሁለት ጊዜ መገበ፤ ሕዝቡ ግን አብዛኛውን ምግብ ጥለው ደቀመዛሙርቱ ቁርስራሾችን ሰበሰቡ። እንጀራ እና ስጋ የአስተምሕሮ ተምሳሌት ናቸው።

ሰዎቹ አንበላም ብለው የተዉት ቁርስራሽ ምግብ በዚያ ዘመን አይሁዶች የኢየሱስን ወንጌል አንቀበልም ማለታቸውንና ኢየሱስን መስቀላቸውን ይወክላል።

ይህን አይሁዶች አንቀበልም ያሉትን ወንጌል ኋላ ሐዋርያት የሆኑነት ደቀመዛሙርት ለሁለት ወገኖች ያቀርባሉ። ሐዋርያት አዲስ ኪንን ጻፉ፤ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍም በ2,000 ታሪክ ውስጥ ለቤተክርስቲያን ተሰጠ። ከዚያም በኋላ በታላቁ መከራ ውስጥ 144,000ዎቹ አይሁዶች ከ2,000 ዓመታት በፊት አይሁዶች አንቀበልም ብለው የገፉትን ወንጌል ይቀበሉታል።

ሚስጥራቱ ከተገለጡ እንደ ሩት እኛም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ትንንሽ ጥቅሶች ላይ ጠለቅ ያለ የመረዳት ቃርሚያ መቃረም እንችላለን (ቃርሚያ ማለት አጫጆች ሳይሰበስቡ የተዉት ፍሬ ነው) ማለትም ቤተክርስቲያኖች ተሰቷቸው ሳይቀበሉ ቸል ብለው የጣሉት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው። ምክንያቱም የተጻፈው ቃል ውስጥ ያለውን ጠለቅ ያለ ሚስጥር ማየት አልቻሉም።

በ7 ቁጥር እና በ12 ቁጥር የተወከሉት ጠለቅ ያሉ ሚስጥራት አካልን ከራስ ጋር የሚያጋጥሙ አጥንቶች ቁጥር ጋር አንድ መሆናቸው ነው።

ኤፌሶን 5፡23 ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና።

ቤተክርስቲያን ክርስቶስ ራሷ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ በመደገፍ ሕይወቷን ጀመረች።

አማኞች የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ብቻ ነበር የሚከተሉትና የሚያምኑት።

የሰዎችን እምነት ለማበላሸት የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ሰውን በክርስቶስ ቦታ የቤተክርስቲያን ራስ አደረገ። ፓስተሩን ከፍ አድርገውን የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አደረጉት (ይህን ያደረጉት “ፓስተር” የሚለው ቃል አዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ተጠቅሶ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ስድስት ጊዜ መወገዙን እያወቁ ነው)፤ በስተመጨረሻም ፖፑ የቤተክርስቲያኖች ሁሉ አለቃ ሆነ።

“ስልጣን ያባልጋል” የሚለውን ምሳሌያዊ አባባል አትርሱ።

የትኛውም አንድ ግለሰብ የቤተክርስቲያን አለቃ ተደርጎ በተሾመ ጊዜ ስልጣን ስለሚያባልገው አምባገነን ሆኖ ይለወጣል።

መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ጊዜ ፓስተር የቤተክርስቲያን ራስ ነው አይልም። ይህ ባቢሎናዊ አስተሳሰብ ነው።

“የተከፈተ” መጽሐፍ ማለት በራዕይ ውስጥ የተጠቀሰው ብርቱ መልአክ ወደ ምድር ከመውረዱ በፊት አንድ ሰው የክርስቶስ ተቃዋሚውን ሚስጥር ገልጦ አስተምሯል ማለት ነው።

የክርስቶስ ተቃዋሚ እንዴት ወደ ስልጣን እንደወጣ የማናውቅ ከሆነ በተገለጠ ጊዜ ስለማናስተውለው ያስተናል።

“ናዚ” የሚለው ቃል አብረውት የተያያዙ ሁለት ሃሳቦች አሉ። አንደኛው የጨካኝ ነፍሰ ገዳዮች ቡድን ነው። ሁለተኛው ደግሞ የዚህ ስርዓት ራስ የሆነው ሒትለር የተባለው ሰው ነው። ሒትለር ትዕዛዙን የሚፈጽሙለት ናዚዎች ያስፈልጉት ነበር። ናዚዎች ደግሞ ድርጊታቸውን ሕጋዊ ለማድረግ የሒትለር ስልጣን ያስፈልጋቸው ነበር። በሁለት መንገድ የሚሰራ ሒደት ነው።

ሒትለር በ1945 እንደሞተ ወዲያው የናዚ እንቅስቃሴ ተቋረጠ። ናዚዎቹ የሚከተሉትና የሚያገለግሉት ራስ አልነበራቸውም።

የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስም በሰው እና በአንድ ሥርዓት አማካኝነት ነው የሚሰራው። ሥርዓቱ ሰው ሰራሽ እምነቶችና መመሪያዎች ያሉት የተደራጀ ዲኖሚኔሽናዊ ሐይማኖት ነው። የዚህ ስርዓት ራስ ደግሞ ሥርዓቱን የሚመራውና የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ነኝ በማለት ለራሱ ሕጋዊነትን የተጎናጸፈው ፖፑ ነው።

ስለዚህ ፖፑ ወደ ስልጣን የወጣበት አወጣጥ ቀስ በቀስ ነው።

ኮንስታንቲን በ312 ዓ.ም ወደ ንጉስ በሆነ ጊዜ የሮም ጳጳስ እየተንገዳገደ ነበር። ኮንስታንቲን ለሮም ጳጳስ ብዙ ሃብትና ገንዘብ ከሰጠው በኋላ የምዕራባዊቱ ቤተክርስቲያን ራስ እንዲሆን ስልጣን ሰጠው። ስለዚህ ኮንስታንቲን ወደ ምሥራቅ ወደ ኮንስታንቲኖፕል በሄደ ጊዜ የሮም ጳጳው በምዕራቡ ዓለም ውስጥ አምባ ገነን የቤተክርስቲያን መሪ ሆነ።

ነገር ግን ከዚያ ወዲያ ባርቤሪያውያን ምዕራባዊውን የሮማ ግዛት አፈራረሱት፤ ይህም ዛሬ ምዕራብ አውሮፓ ነው።

ዳንኤል 7፡8 ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፥ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፥ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ እነሆም፥ በዚያ ቀንድ እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት።

ቀንድ የስልጣን ምሳሌ ነው። ቫቲካን ስፋቷ አንድ ካሬ ኪሎሜትር ብቻ ሲሆን በምድር ላይ ከሁሉ ታናሽዋ መንግስት ናት።

ይህ ካርታ ኮንስታንቲኖፕል ውስጥ ተቀምጦ በነበረው በምስራቃዊው የሮማ ገዥ ይተዳደር የነበረውን የምስራቁን የቤዛንታይን ግዛት ያሳያል።

 

 

የሔሩሊ ነገድ ራስ የነረበው ኦዶዋሰር በ476 ዓ.ም ኢጣልያ ውስጥ ምዕራባዊውን የሮማ ገዥ ገለበጠውና ኢጣልያ ውስጥ ገዥ ሆነ። ኦዶዋሰር በስላሴ አያምንም ነበር፤ ስለዚህ ሮም ውስጥ የነበረው ፖፕ አልወደደውም። ኢጣልያ አጠገብ ይኖሩ የነበሩት ቴዎዶሪክ እና ኦስትሮጎቶች ወደ ኢጣልያ ገብተው ሔሩሊዎችን እንዲያጠፏቸው ኮንስታንቲኖፕል ውስጥ የተቀመጠው የምስራቃዊ ሮማ መንግስት ገዥ ጠየቃቸው። እነርሱም እንደተጠየቁት አደረጉ። ነገር ግን ቴዎዶሪክ እና ኦስትሮጎቶችም በስላሴ አያምኑም ነበር፤ ስለዚህ ፖፑ ደስ አልወደዳቸውም። ኮንስታንቲኖፕል ውስጥ ተቀምጦ የነበረው በስላሴ የሚያምነው ገዥ ሰሜን አፍሪካ ውስጥ የሚኖሩትና ከባሕር ኃይላቸው የተነሳ ለሮም ስጋት የነበሩትን ቫንዳሎችን እንዲያጠፋለት አንድ ሰራዊት ላከ (ቫንዳሎችም በስላሴ አያምኑም ነበር)። ይህም ለዚያ ሰራዊት ሰሜን አፍሪካ ውስጥ ምቹ የሆነ የጦር ሰፈር አስገኘላቸው፤ ከዚያ ተነስተው ኢጣልያን ለመውረር ያመቻቸዋል። (ይህም ልክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካ የእንግሊዝና የራሺያ ጥምር ጦር ኃይሎች አስቀድመው ሰሜን አፍሪካን ተቆጣጥረው ከዚያ በመነሳት ኢጣልያን እንደወረሩት ማለት ነው)። ይህ ከኮንስታንቲኖፕል የመጣው ሰራዊት ወደ ኢጣልያ ዘምቶ ኦስትሮጎቶችን ለማጥፋት ሃያ ዓመታት ፈጀበት። ስለዚህ በስላሴ የማያምኑ የነበሩት እና ለሮማ መንግስት መፈራረስ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሶስት ባርቤሪያውያን ነገዶች በሙሉ ጠፉ። ሔሩሊዎች፣ ቫንዳሎች፣ እና ኦስትሮጎቶች ሶስት ቀንዶች (ወይም የነገድ ኃይሎች) ነበሩ፤ እነርሱም በሙሉ ተደምስሰው በመጥፋታቸው ፖፑ አውሮፓ ላይ በስልጣን በወጣ ጊዜ የስላሴ ትምሕርት ያለ ምንም ተቃውሞ መደላደል ቻለ። ስለዚህ ምዕራባዊውን የአውሮፓ ግዛት ከአረማዊው የሮማ መንግስት ነጥቀው የተቆጣጠሩ ቀሪ ባርቤሪያውያን ነገዶች መካከል ፖፑ በስልጣን ከፍ ከፍ ማለት ቻለ። በምዕራብ አውሮፓ የነበሩ እነዚህ ሁሉ ባርቤሪያውያን ነገዶች ስላሴን ተቀበሉ፤ ስለዚህ ቀጥለውም ፖፑን የቤተክርስቲያን ራስ አድርገው ተቀበሉ። ስለዚህ የሮም ቤተክርስቲያን በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተብላ ታወቀች። ካቶሊክ ማለት ዓለም አቀፍ ማለት ነው። በ1200 ዓ.ም ፖፑ አውሮፓ ውስጥ ከነገሰ ከማንኛውም ንጉስ እኩል ኃይለኛ ነበረ።

ዳንኤል 7፡8 ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፥ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፥ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ እነሆም፥ በዚያ ቀንድ እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት።

ፖፑ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ነኝ በማለት በባርቤሪያውያን ላይ ስልጣኑን አጠናከረ። ኢየሱስ ለጴጥሮስ የመንግስተ ሰማያትን ቁልፎች ሰጠው። ጴጥሮስ ሰዎች ንሰሃ እንዲገቡና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ በነገራቸው ጊዜ የመንግስተ ሰማያትን በር ከፈተ።

የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

39 የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው።

ይህ የመንግስተ ሰማያት ቁልፍ ነው። ዛሬም እኛን ጨምሮ ለሁሉም ሰው ይሰራል። ጴጥሮስ እንደሰበከው የመንግስተ ሰማያት ቁልፍ ንሰሃ መግባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ነው። ይህም በእናንተ እና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የሚደረግ የግል ሕብረት ነው።

ፖፑ ግን ለባርቤሪያውያን የነገራቸው ጴጥሮስ የመንግስተ ሰማያትን በር የሚከፍተው ፖፑ ለረዱ እና ለፖፑ ለሚናገረው ቃል ለሚታዘዙ ሰዎች ብቻ እንደሆነ አድርጎ ነው። ስለዚህ ጴጥሮስ ሰው ሆኖ ሳለ ከኢየሱስ በላይ ከፍ ከፍ ተደረገ። ኢየሱስ የመንግስተ ሰማያት በር ነው። ፖፑ ግን የበሩ መክፈቻ ቁልፍ ያለው በጴጥሮስ እጅ ነው በማለት ማን ወደ መንግስተ ሰማያት እንደሚገባ እና እንደማይገባ የሚወስነው ጴጥሮስ ነው ብሎ አስተማረ። ወደ መንግስተ ሰማያት መግቢያውን በር የሚቆጣጠረው ጴጥሮስ ነው የሚለውን ትምሕርት በመፍራትና ጴጥሮስን ለማስደሰት በመጨነቅ ባርቤሪያውያን ለፖፑ መታዘዝ ጀመሩ። ለፖፑ ካልታዘዙ እና ፖፑን ካልረዱት በቀር ጴጥሮስ የመንግስተ ሰማያትን በር እንደማይከፍትላቸው አመኑ።

ስለዚህ ፖፑ ጴጥሮስ በኢየሱስ ማለትም በእግዚአብሔር ልጅ ቦታ ቆሟል ብሎ አስተማረ።

“የኮንስታንቲን ስጦታ” በ700 ዓ.ም አካባቢ በሐሰት የተፈጠረ ሰነድ ነው፤ ይህም ሐሰተኛ ሰነድ የተዘጋጀው የፖፑን ስልጣን ከፍ ለማድረግ ታስቦ ነው። (ሰነዱ ሐሰተኛ መሆኑ የታለጠው በ1440 ነው። እስከዚያ ድረስ አስር ፖፖች ስልጣናቸውን ለማረጋገጥ ተጠቅመውበታል)። ይህ ሰነድ የተዘጋጀው የባርቤሪያውያንን ድጋፍ ለማግኘት ተብሎ ነው፤ በተለይም ከባርቤሪያውያን መካከል ኃይለኛ የሆኑትን የፍራንኮችን ድጋፍ ለማግኘት ነው፤ ፍራንኮች ከምስራቃዊው የሮማ ገዥ ፖፑ ላይ ሊሰነዘርበት ከሚችለው ጥቃትም ጥበቃ ያደርጉለት ነበር። ይህ ሰነድ ጴጥሮስ VICARIVS FILII DEI (ወይም “በእግዚአብሔር ልጅ ምትክ”) የሚል ማዕረግ እንደነበረው ይናገራል። በሌላ አነጋገር የመንግስተ ሰማያት በር ይከፈትላችሁ እንደሆን የሚወስነው ኢየሱስ ሳይሆን ጴጥሮስ ነው ማለት ነው። የተወሰኑ የላቲን ፊደሎች የቁጥር ዋጋ አላቸው። የጴጥሮስ ማዕረግ ነው በተባለው የላቲን ቃል ውስጥ ያሉት ፊደሎች ዋጋቸው ሲደመር 666 ነው።

(I = 1, V = 5, L = 50, C = 100, D = 500)

ሮማውያን ብዙውን ጊዜ በ U ፈንታ V ይጠቀሙ ነበር ምክንያቱም ድንጋይ ላይ ለመቅረጽ ቀጥ ያሉ መስመሮች ቀለል ይላሉ። የእንግሊዝኛውን w ደብልዩ እንለዋለን ምክንያቱም ይህን ፊደል ለመጻፍ UU እንደ VV ወይም W ተደርጎ ስለሚጻፍ ነው።

ይህ VICARIVS FILII DEI ወይም “በእግዚአብሔር ልጅ ምትክ” የሚለው ማዕረግ የተለጠፈበት ብቸኛው ሰው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው። ነገር ግን ይህ ማዕረግ አውሮፓ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ባርቤሪያውያን ለፖፑ እንዲታዘዙ አደረገ ምክንያቱም ፖፑ የጴጥሮስ ተተኪ እንደሆነ እና ለፖፑ ካልታዘዙ በቀር ጴጥሮስ የመንግስተ ሰማያትን በር እንደማይከፍትላቸው አምነው ነበር።

“ታላላቅ ነገሮችን መናገር” ማለት ወደ መንግስተ ሰማያት እንዴት እንደምንገባ መናገር ነው።

“ዓይኖች” ጥበበኝነትን ይወክላሉ። የሰው ጥበብ። ሰዎች መሪ ሆነው በቤተክርስቲያን ላይ ይሰለጥኑ ዘንድ ከፍ መደረጋቸውን ያሳየናል። ዛሬ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይልቅ ለፓስተራቸው አብልጠው ይታዘዛሉ። ቤተክርስቲያንን እየገዟት ያሉት ክርስቲያናዊ ልማዶችና የፓስተሩ አመለካከቶች ናቸው፤ እነዚህም ቤተክርስቲያንን ወደ 45,000 ዓይነት ልዩ ልዩ ዲኖሚኔሽናዊ ቤተክርስቲያኖች እንድትሰነጣጠቅ አብቅተዋታል።

ክሪስማስ። የክሪስማስ ዛፍ። ዲሴምበር 25። ሊቀ ጳጳሳት። ኩዳዴ ጾም። ዲኖሚኔሽን። ካተኪዝም። ኮንፈርሜሽን።

ቀጥተኛ ተቆጣጣሪ። ስላሴ። አንድ አምላክ በሶስት አካላት። የመጀመሪያው ሐጥያት የዛፍ ፍሬ መብላት ነው፤ ሔዋንም በዚህ ምክንያት ነው ስትወልድ በጭንቅ የምትወልደው።

እነዚህ ቃላት እና አባባሎች ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ናቸው፤ ሆኖም ግን ብዙ ክርስቲያኖች ናቸው እንደ እውነት የሚያምኑዋቸው። ስለዚህ ሮም ውስጥ የተጀመሩ የቤተክርስቲያን ልማዶች ወደ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ተሰራጭተዋል።

 

የክርስቶስ ተቃዋሚውን የሚወክለው ታናሽ ቀንድ ማለትም ትንሽዋ የቫቲካን መንግስት አድጋ ተጽእኖዋን በዓለም ዙርያ ሁሉ አሰራጭታለች።

 

ዛሬ ክርስቲያኖች በሰው ጥበብ የተፈጠሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ቃላትን በደስታ ተቀብለው ያምናሉ።

በዚህም መንገድ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተነስቶ ወደ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች ተሰራጨ።

ዳንኤል ቀጥሎ ሌላ ራዕይ አየ፤ በዚህም ራዕይ ውስጥ የታላቁ አሌግዛንደር የግሪክ መንግስት ወደ አራት ትናንሽ መንግስታት ሲከፋፈል ተመለከተ።

ዳንኤል 8፡8 አውራውም ፍየል ራሱን እጅግ ታላቅ አደረገ፤ በበረታም ጊዜ ታላቁ ቀንዱ ተሰበረ፥ ወደ አራቱም የሰማይ ነፋሳት የሚመለከቱ አራት ቀንዶች ከበታቹ ወጡ።

አራቱ የሰማይ ነፋሳት ማለት እነዚህ ክስተቶች መንፈሳዊ ትርጉም አላቸው ማለት ነው።

ከእነዚህ አራት መንግስታት መካከል ከሁሉም ትንሽ የሆነው መንግስት በጀነራል ላይሲማከስ የተመራው የጴርጋሞን መንግስት ነበር። ሊቀ ካሕናቱ ወይም የባቢሎን ሚስጥራት ፖንቲፍ በ539 ዓመተ ዓለም ቂሮስ ባቢሎንን ባሸነፈ ጊዜ ወደ ጴርጋሞን ሸሽቶ ነበር። በ133 ዓመተ ዓለም ካሕን-ንጉስ አታለስ 3ኛው ሲሞት ይገዛው የነበረውን የጴርጋሞን መንግስት ለሮም ሰጠ። ዩልየስ ቄሳር በ63 ዓ.ም ጉቦ ከፍሎ የባቢሎን ሚስጥራት ፖንቲፍ የሚለውን ማዕረግ ለራሱ ወሰደ። የሮማ ነገስታት ሁሉ ይህን ፖንቲፍ የሚለውን ማዕረግ ይጠቀሙበት ነበር፤ በስተመጨረሻ ግን ቴዎዶሲየስ በ378 ዓ.ም አልፈልገውም አለ። በ400 ዓ.ም የሮም ጳጳስ ፖንቲፍ የሚለውን ማዕረግ ለራሱ ወሰደ። በባቢሎናውያን ሕግ መሰረት ፖንቲፉ ራሱን መሸፈን አለበት። ለዚህ ነው ፖፑ ሁልጊዜ በራሱ ላይ ቆብ የሚያደርገው።

የግሪክ መንግስታት በሮም በተሸነፉ ጊዜ የባቢሎን ሚስጥራት ሮም ውስጥ ስር ሰደዱ።

የሮማ መንግስት በባርቤሪያውያን እጅ በፈራረሰ ጊዜ የባቢሎን ሚስጥራት በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስር ሰደዱ።

ዳንኤል 8፡9 ከእነርሱም ከአንደኛው አንድ ታናሽ ቀንድ ወጣ፥ ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም ወደ መልካሚቱም ምድር እጅግ ከፍ አለ።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምስራቅ ሁልጊዜ የሚያመለክተው አጋንንታዊ አሰራርን ነው። ቃየን ከመጀመሪያው ከኤደን ተነስቶ ወደ ምስራቅ ሄደ።

ሐውልቶች። ጣኦታት። ለሙታን መጸለይ። ፑርጋቶሪ፤ ሙታን ከፖርጋቶሪ እንዲወጡ ገንዘብ መክፈል። ወደ ማርያም መጸለይ። ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ መጸለይ። ወደ ቅዱሳን መጸለይ። ይህ ሁሉ አጋንንታዊ አሰራር ነው፤ የሞቱትንም ቅዱሳን ወደ ጠንቋይነት ደረጃ ዝቅ ያደርጋቸዋል።

ዳንኤል 8፡10 እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፤ ከሠራዊትና ከከዋክብትም አያሌዎችን ወደ ምድር ጣለ፥ ረገጣቸውም።

ዳንኤል የክርስቶስ ተቃዋሚውን አመጣጥ በብሉይ ኪዳን ዘመን ውስጥ ተከታትሎ ጴርጋሞን ውስጥ የሚሰወረው የባቢሎናውያን ሚስጥር መሆኑን ደርሶበታል፤ ይህም ትንሽ ሆኖ ሰው ሳያስተውለው ይቆይና በስተመጨረሻ ወደ ሮም ግዛት ይሸጋገራል። የሮም ግዛት ውስጥ ከገቡ በኋላም ማንም ሳያስተውላቸው ተደብቀው ቆይተው ዩልየስ ቄሳር ዓለምን ሊገዛ ወደ ስልጣን በወጣ ጊዜ ታዋቂነትና ገናናነትን ተጎናጸፉ። ንጉስ ቴዎዶሲየስ ፖንቲፍ የሚባለውን ማዕረግ አልቀበልም ባለ ጊዜ ይህ ማዕረግ ማንም ሳያስተውለው ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሾልኮ ገባ። ስለዚሀ የሮማ ፖንቲፍ ወይም ፖፕ የባቢሎን ሚስጥራት ተጽእኖ በዓለም ዙርያ በተሰራጩ ጊዜ ነው ወደ ስልጣን የወጣው።

የባቢሎን ሚስጥራት ወደ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖችም ውስጥ ሾልከው ገብተዋል፤ ነገር ግን ማንም ልብ አላላቸውም።

ከትንሽ ጅማሬ ተነስተው ዛሬ ዓለምን ሁሉ ለመውረስ ተቃርበዋል።

ነገር ግን ኢየሱስም ጅማሬው ታናሽ ነበረ።

ሚክያስ 5፡2 አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።

ቤተልሔም ታናሽ ከተማ ነበረች።

ነገር ግን ኢየሱስ በቤተልሔም ነው የተወለደው። ኢየሱስ አገልግሎቱንም ከታናሽ ከተማ ጀመረ፤ በአገልግሎቱ መጨረሻም መንፈስ ቅዱስን ሊቀበሉ የተሰበሰቡ 120 ተከታዮች ብቻ ነበሩት። ስለዚህ በመጀመሪያው ምጻቱ ኢየሱስ አገልግሎቱን ያጠናቀቀው ጥቂት ተከታዮች ብቻ በማፍራት ነው።

በዳግም ምጻቱም ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ነው የሚሆነው።

ማቴዎስ 10፡42 ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።

ትንንሽ የደግነት ስራዎች ማንም ሰው አያስተውላቸውም።

ሕጻናት የሚለው በዘመን መጨረሻ የሚኖሩ ልጆችን ያመለክታል ምክንያቱም እነዚህ ልጆች ወደ ሐዋርያዊ አባቶቻቸው መመለስ አለባቸው። አንድ ጽዋ ውሃ የእውነተኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሕሮ ተምሳሌት ነው።

ኢየሱስ ሰው ሰራሽ አስተምሕሮ ሳይሆን እውነትን ለሰዎች እንድናካፍል ነው የሚጠብቅብን።

ማቴዎስ 18፡4 እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው።

ትሕትና ውበት አለው። የበለጠ ትሁት ስንሆን እና ስለ ራሳችን ማሰብ ስንቀንስ እግዚአብሔር ይበልጥ ይጠቀምብናል።

1ኛ ዮሐንስ 2፡13 አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።

አባቶች ማለት ወደ እምነታቸው ልንመለስ የሚገባን የጥንት ቤተክርስቲያን አማኞች ናቸው። ወጣቶቹ በጨለማው ዘመን የሚፈጸሙ ግፎችን እና በካቶሊክና በፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች መካከል የተደረጉ ሐይማኖታዊ ጦርነቶችን ተቋቁመው ለማለፍ የበረቱ ነበሩ። ከዚያም በታላቁ የወንጌል ስርጭት ዘመን ከባሕር ማዶ ሰይጣንን ድል ነሱት።

እኛ በዘመኑ መጨረሻ ወደ ጥንታዊቷ ቤተከርስቲያን አባቶች እምነት መመለስ ያለብን ትንንሽ ልጆች ወይም ሕጻናት ነን።

አብ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ በአካል የኖረው እግዚአብሔር መሆኑን እናውቃለን። ስለዚህ የእግዚአብሔር አብ ሰብዓዊ ስሙ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እናውቃለን።

ስሙን ካላወቃችሁ በቀር እግዚአብሔር አብን ልታውቁት አትችሉም።

ስለ ክርስቶስ ሲናገር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-

ቆላስይስ 2፡9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤

ማቴዎስ 19፡14 ነገር ግን ኢየሱስ፦ ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና አለ፤

ኢየሱስ ሕጻናት (ማለትም በመጨረሻ ዘመን የምንኖር ክርስቲያኖች) ወደ እርሱ ማለትም ወደ ቃሉ እንድንመለስ ይፈልጋል። የሆነ የቤተክርስቲያን አስተምሕሮ ወይም የሆነ የቤተክርስቲያን መሪ ንግግር ጥቅሶችን እንድናምን አይፈልግም።

“ሕጻናትን አትከልክሏቸው” ሲል በመጨረሻው ዘመን ሕጻናት ማለትም እውነተኛ ክርስቲያኖች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለመመለስ በሚያደርጉበት ጥረት ውስጥ በብዙ መገፋት እና መከራ ውስጥ እንደሚያልፉ ማመልከቱ ነው።

1ኛ ዮሐንስ 4፡4 ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና።

በውስጣችን የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ የዘመናችንን ስሕተቶችን ሁሉ አሸንፈን የምናልፍበት እና በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ ማመን የምንችልበት ብቸኛ መንገድ ነው።

1ኛ ዮሐንስ 5፡21 ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።

ሰይጣን ከፈጠራቸው አስተምሕሮዎች መካከል ከሁሉም በላይ ስኬታማ የሆነው አስተምሕሮ ሶስት አካላት ያሉበትና እያንዳንዳቸውም አምላክ የሆኑበት የስላሴ አስተምሕሮ ነው። ይህ አስተምሕሮ ባቢሎን ውስጥ የጀመረ ሲሆን አሁን በያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስር የሰደደ እምነት ሆኗል።

ሰውን አምላክ አታድርጉት። አንድን ሰው ከሕዝብ በላይ አታድርጉት። መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ በመከተል ጽኑ።

ያዕቆብ 2፡1 ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ።

ስለዚህ “ትንሽ” የሚለው ቃል በዘመን መጨረሻ ላይ ልዩ ልዩ ትርጉሞች አሉት።

ትንሽ የአማኞች ሕብረት ይኖራል።

እኛ ወደ ጴንጤቆስጤያዊ አባቶች የምንመለስ ትንሽ የሕጻናት ሕብረት ነን።

ስለ ራሳችን ትንሽ ብቻ ነው ማሰብ ያለብን። የግል አመለካከቶቻችን ብዙም አስፈላጊ አይደሉም። ማመን ያለብን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነው።

 

ራዕይ 3፡8 ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና።

የፊልደልፊያ የወንጌል ስርጭት ዘመን (ፊልደልፊያ ማለት የወንድማማች መዋደድ ነው) ብዙ ጀብዱ የተፈጸመበት ቢሆንም እንኳ ካመኗቸው ስሕተቶች የተነሳ ብዙም ብርታት አልነበራቸውም። ነገር ግን ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን በታማኝነት ተጠቅመዋል፤ ደግሞም ወዳላመኑ ሰዎች ሃገር በሄዱ ጊዜ ሁሉ መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መሆኑን በታማኝነት ሰብከዋል። ትኩረታቸውን የወንጌል አገልግሎት ላይ አድርገው ስለነበረ ነው እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስ መረዳታቸው ላይ የነበራቸውን ስሕተት ብዙም ያልቆጠረባቸው።

ስለዚህ ዛሬ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እምነት መያዛችንን ማረጋገጥ አለብን።

በንስር ዘመን ስለምንኖር እውነትን አጥርተን እንድናይ ይጠበቅብናል።

እስቲ የወደፊቱን ዘመን እንመልከት።

ራዕይ 6፡11 ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።

እነዚህ በብሉይ ኪዳናዊ እምነታቸው ምክንያት በቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የተገደሉ አይሁዶች ናቸው። ታላቁ መከራ ተጀምሯል፤ ሙሽራይቱም ሰማይ ውስጥ ስለሆነች እነርሱ ወደ ምድር ወርደው ብዙዎቻቸውን የገደለችውን ዲኖሚኔሽናዊቷን የሮማ ቤተክርስቲያን ማጥፋት ይፈልጋሉ። ነገር ግን ለጥቂት ጊዜ እንዲታገሱ ተነገራቸው። ታላቁ መከራ የሚቆየው ለሶስት ዓመት ከግማሽ ብቻ ነው። 144,000ዎቹ አይሁዶች እና አብረዋቸው የሚያገለግሉ ሰዎች ኢየሱስን መቀበልና መገደል ይጠብቃቸዋል። ከዚያ በኋላ ነው ሁሉም ለአርማጌዶን ጦርነት መሄድ የሚችሉት።

ፖፕ አርባን 2ኛው አይሁዶች ወደ ፓለስታይን በሚሄዱበት መንገድ የመስቀል ዘመቻ ጦርነት አዘጋጅቶ ዘረፋቸው፤ ደግሞም ገደላቸው። ፖፕ ፓየስ 11ኛው ሒትለር ወደ ስልጣን እንዲወጣ ድጋፍ አድርጎለታል። ፖፕ ፓየስ 12ኛው ሒትለር ስድስት ሚሊዮን አይሁዶችን የገደለበትን ሆሎኮውስት የተባለውን ጭፍጨፋ አላወገዘም። እነዚህ ሁሉ የተገደሉ አይሁዶች ወደ ምድር ወርደው የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን እና እያዩ ዝም ያሉትን የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች መበቀል ይፈልጋሉ።

እኛ ሰዎች ሁልጊዜ እንቸኩላለን።

ከዚህ ቃል ግን ጥቂት መታገስ እንዳለብን እንማራለን። እግዚአብሔር ከእኛ የግል ጉዳዮች የሚበልጡ ትልልቅ እቅዶች አሉት። ስለዚህ ስለ ራሳችን ብዙ አለማሰብ መልመድ አለብን።

ራዕይ 10፡2 የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥ እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።

64-0119 ሻሎም

ነገር ግን አስታውሱ የሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ ብንገባ ኢየሱስ “ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ እኔ በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለው” ብሎ ቃል ገብቶልናል። ታላቁ ንጉስ መሪ ሲመጣ በትሩንም ሲሰነዝር ከዚያ በኋላ “ጊዜ የሚባል ነገር አይኖርም።” ያ የራዕይ ምዕራፍ 10 መልአክ አንድ እግሩን በምድር አንድ እግሩን በባሕር ሲያደርገውና በራሱ ላይ ቀስተደመና ሲወጣ እንዲህ ብሎ ምሏል፡- “ወደፊት አይዘገይም”። ያ ጊዜ ሲደርስ ከሙታን መካከል ትነሳላችሁ። ሌሎቹ እዚያው ሲቀሩ እናንተ ግን ትገባላችሁ።

ሙታን ባሕር ውስጥ ወይም ምድር ውስጥ ነው የሚቀበሩት።

ብርቱው መልአክ ለታላቅ ሥራ ነው የሚመጣው፤ ይህም ሙታንን ማስነሳት ነው።

የተከፈተው መጽሐፍ “ትንሽ” መጽሐፍ ተብሎ ነው የተገለጸው።

በመጨረሻ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያምኑ ሰዎች “ጥቂቶች” ናቸው።

ራዕይ 10፡11 በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደ ገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል ተባለልኝ።

ዮሐንስ የጻፋቸው አምስት መጻሕፍት በ2,000 ዓመታቱ የቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሁሉ ይናገራሉ።

በቤተክርስቲያን ዘመናት መጀመሪያ ላይ ዮሐንስ መጽሐፉን በላና ከመጽሐፉ ጋር አንድ ሆነ።

ዮሐንስ በትንሳኤ ጊዜ ሲነሳም መጽሐፍ ቅዱስን እንዳመነ ይቀጥላል። ከዚያም ከሙታን ካስነሳው ከብርቱው መልአክ ጋር በምድር ላይ አብሮ ይቆማል።

ራዕይ ምዕራፍ 10 የሚናገረው ስለ ትንሳኤ እና ሙሽራይቱ ወደ ሰማይ ለመነጠቅ ስለምታደርገው ዝግጅት ነው። ሰባቱ ነጎድጓዶች ቃላቸውን በሚናገሩ ጊዜ በሕይወት ያሉት የሙሽራይቱ አካላት እና ከሙታን የተነሱ ቅዱሳን የተገለጠውን የተጻፈውን መጽሐፍ በመጠቀም ያልተጻፉትን የነጎድጓዶቹን ንግግር እየተረዱ ይከተላሉ።

ስለዚህ ዮሐንስ በመጨረሻ ይህንኑ የተገለጠ መጽሐፍ ይበላል (ያላምጣል ያምናል)።

ስለዚህ የቤተክርስቲያን ዘመናት መጀመሪያ እና መጨረሻ አንድ ዓይነት ይሆናል።

ሙሴ እና ኤልያስም የሰባተኛውን ማሕተም (የጌታን ምጻት) እንዲሁም ለጌታ ምጻት የሚያዘጋጁንን የሰባቱን ነጎድጓዶች ሚስጥራት በሙሉ ለማወቅ መጽሐፉን ይበላሉ። ከዚያ በኋላ ሙሴ እና ኤልያስ 144,000ዎቹን አይሁዶች ለመጠበቅ እና ለመምራት የታላቁ መከራ ሚስጥራት ላይ ትኩረት ማድረግ ይችላሉ።

63-0321 አራተኛው ማሕተም

ሰባቱ ነጎድጓዶች ድምጻቸውን መስማት የሚችል ሕዝብ ሲመጣ እስኪያሰሙ ድረስ ጠብቁ። የእግዚአብሔር ቃል ስለታም ሰይፍ ነው፤ ይቆርጣል። እነርሱም ሰማያትን መዝጋት ይችላሉ፤ የፈለጉትን መዝጋር የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን።

እርሱም ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ይገደላል፤ ይህም ቃል በሁለት ወገን ከተሳለ ሰይፍ ይልቅ ስለታም ነው። እነርሱ ከፈለጉ መቶ ቢሊዮን ዝንቦችን መጥራት ይችላሉ። አሜን። እነርሱ የሚናገሩት ነገር ሁሉ ይፈጸማል፤ ምክንያቱም ቃላቸው ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣ የእግዚአብሔር ቃል ነው። አሜን።

ይህ ማለት በታላቁ መከራ ዘመን ውስጥ ሰባቱ ነጎድጓዶች ሁለቱን ነብያት ለሥራ ሲያስነሷቸው ማለት ነው፤ ይህም የሚሆነው እነዚሁ ሰባት ነጎድጓዶች ለሙሽራይቱ አካላት ከምድር ላይ ተነጥቀው ጌታን በአየር ላይ የሚቀበሉበትን እምነት ከሰጧቸው በኋላ ነው።

ትንሹ መጽሐፍ።

ሰባቱ ነጎድጓዶች በሚናገሩ ጊዜ ጥቂቶች ብቻ ማለትም ታንሽ መንጋ ብቻ ናቸው የነጎድጓዶቹን ንግግር መረዳት የሚችሉት። ስለዚህ ለመነጠቅ የሚያስፈልገውን እምነት በውስጣቸው ገንብተው ወደ ሰማይ የሚነጠቁት እነዚህ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። እነዚህ ጥቂት ሰዎች በአሁኑ ሰዓት ጊዜያቸውን ሰጥተው የወንድም ብራንሐምን ንግግር ጥቅሶች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እየወሰዱ በመመርመር መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት የቻሉ ሰዎች ናቸው።

የሜሴጅ ተከታዮች ነጎድጓዶቹ ተናግረዋል፤ የተናገሩትንም እናውቃለን ብለው ያስባሉ። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች እስከ ዛሬ በምድር ላይ መቅረታቸው በራሱ “እውቀታቸው” ወይም ብልህ መገለጣቸው ለመነጠቅ የሚሆን እምነት እንዳልሰጣቸው ያሳያል።

ብልህ እንድንሆን አልተጠየቅንም።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንድንጣበቅ ብቻ ነው የተጠየቅነው።

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ስለ ነጎድጓዶቹ የተሰበኩ ብዙ አስተምሕሮዎች አሉ። ሁላቸውንም ሁለት የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ።

የትኛውም የነጎድጓዶች አስተምሕሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመጠቀስ ሊሰበክ አይችልም፤ ምክንያቱም ነጎድጓዶቹ የተናገሩት ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም።

ሁለተኛ ደግሞ፤ የትኛውም የነጎድጓዶች አስተምሕሮ ተፈላጊውን ውጤት አላስገኘም፤ ማለትም የሚያምኑትን ሰውች ወደ ሰማይ አልነጠቃቸውም።

ብዙ ማስታወቂያ እና ግርግር ብቻ ነው የፈጠሩት እንጂ አንዳችም ውጤት አላመጡም፤ ምክንያቱም ከትምሕርታቸው በኋላ አንድም ሰው ወደ ሰማይ አልተነጠቀም።

በጣም የሚያሳዝነው አንዳንዶቹ የነጎድጓድ አስተማሪዎች ወደ ላይ በመነጠቅ ፈንታ መቃብሮቻቸው ውስጥ አግድም ተኝተዋል።

ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተጣብቀው የሚቆዩ ጥቂቶች ይኖራሉ፤ እነዚህም ከሙታን ትንሳኤ በኋላ ሰባቱ ነጎድጓዶች ቃላቸውን የሚናገሩበትን ጊዜ ይጠብቃሉ።

ማቴዎስ 7፡14 ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።

15 የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።

ሉቃስ 12፡32 አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።

ስለ መጨረሻው ዘመን ሲናገር ስለ ትልቅ ቡድን አይደለም የሚናገረው።

ሉቃስ 18፡8 እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?

ኢየሱስ በዘመን መጨረሻ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አላየም።

ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።

እምነታችሁን መገንባት የምትችሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንጂ በሰው ንግግር ጥቅሶች ላይ አይደለም።

ጌታ በሚመለስበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ቃል የሚያምኑ ሰዎች በጣም ጥቂት ነው የሚሆኑት። መጽሐፍ ቅዱስን ትተው የሰው ንግግር ጥቅስ እና የዚህኑ ትርጓሜ በማሳደድ ይጠመዳሉ።

1ኛ ሳሙኤል 15፡17 ሳሙኤልም አለ፦ በዓይንህ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባህ።

እግዚአብሔርን በጣም የሚያስገርመው ትሕትና ነው። ትሕትና ማለት ስለ ራሳችን ዝቅ አድርገን ማሰብ ነው።

አመለካከቶቻችን እና ትርጓሜዎቻችን መጽሐፍ ቅዱስን መተካት አይችሉም።

ራሳችንንም ሆነ ሌላ ሰውን ከፍ ከፍ ማድረግ ምንም አይጠቅመንም።

ሉቃስ 19፡17 እርሱም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ባሪያ፥ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው።

እምነታችንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማድረግ ለቃሉ ታማኝነታችንን የምናረጋግጥበት መንገድ ነው፤ ቃሉም እግዚአብሔር ነው።

1ኛ ቆሮንቶስ 5፡6 መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን?

አንድ የተሳሳተ መገለጥ ስንከተል ያ ስሕተት ወደ ሌሎች ስሕተቶች እየመራን በስተመጨረሻ ፈጽመን ከእውነት ርቀን እንሄዳለን።

ያዕቆብ 3፡5 እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።

ጥቂት የተሳሳቱ ቃላት አእምሮዋችን ውስጥ የተሳሰቱ ምስሎችን ይፈጥራሉ።

ሃሳቦችን መረዳት የምንችለው አእምሮዋችን ውስጥ ምስሎችን በመፍጠር ነው።

አንድ ጊዜ አእምሮዋችን ውስጥ የተሳሳተ ምስል ከገባ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ ምስል ጋር እንዲገጥም ማድረግ አንችልም፤ ስለዚህ እምነታችንን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መተርጎም እናቆማለን። ከዚያ በኋላ እምነታችን በአሸዋ ላይ የተመሰረተ ይሆንና ወደ አለማመን ይለወጣል።

ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ

ኢየሱስ መልእክቱን በፊልደልፊያ እና በሌሎች ከተሞች ላለችዋ ቤተክርስቲያን እንዳጻፈው በሎዶቅያ ላለችው ቤተክርስቲያን አላጻፈም።

ያጻፈው ለሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ነው። ቤተክርስቲያኒቱ የእግዚአብሔር ሳትሆን የእነርሱ ናት።

ለራሳቸው ሰዎችን መሪዎች አድርገው ሹመዋል፤ እነርሱም ቤተክርስቲያኖችን የሚገዙ ፓስተሮች ናቸው።

በወደዱት የሰው ንግግር ጥቅሶች ላይ የተመሰረቱ የራሳቸው አስተምሕሮዎች አሏቸው።

ብልህ መስለው ለመታየት የፈለጓቸውን ጥቅሶች ይገጣጥማሉ የፈለጉትን ይሰነጣጥቃሉ።

ቤተክርስቲያናቸው በድራም እና በዲስኮ ሙዚቃ ቅልጥ ያለ አስገራሚ ቤተክርስቲያን ነው። ቤተክርስቲያናቸው ውስጥ የሚያቀርቡት መዝናኛ እና ንግድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን የትም ቦታ ድራም የሚባል የሙዚቃ መሳሪያ አልተጠቀሰም።

የሎዶቅያውያን ቤተክስቲያን ውስጥ ቃሉ የለም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን በር ውጭ ነው የቆመው። ነገር ግን እርሱ በመካከላቸው አለመገኘቱን እንኳ አላወቁም (“ስለማታውቅ”) ያላወቁት እርስ በራሳቸውን በማስደነቅ ሃሳብ ስለተጠመዱ ነው።

በዚህ ዘመን ውድድር በበዛበት ዘመናዊ ክርስትና ውስጥ እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን እኔ ከሁሉ የተሻልኩ ነኝ ይላል።

ማቴዎስ 18፡20 ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።

እግዚአብሔር ጥቂት ሰዎች በሕብረት በሚቀመጡ ጊዜ ተገኝቶ ሊባርካቸው ቃል ገብቷል። ትልልቅ ቡድኖችና አላለም።

ሮሜ 16፡5 በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ።

የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን የተጀመረው በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ በሚሰባሰቡ ትንንሽ ቡድኖች ነው። ቤተክርስቲያን ትንሽ ቡድን ስትሆን ማንም ግለሰብ ታላቅ መሆን አይችልም። ማንም ደግሞ ያለ ቅጥ ሃብታም መሆንም አይችልም።

ኢየሱስ ገንዘብ ለዋጮችን ከቤተመቅደሱ እንዳባረራቸው ልብ በሉ።

አሁን ግን ሃብታሞቹ ፓስተሮች ኢየሱስን ማለትም የተጻፈውን ቃል ከቤተክርስቲያናቸው ያባርራሉ።

2ኛ ተሰሎንቄ 2፡3 ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና።

የመጨረሻው ቀን ከመምጣቱ በፊት ብዙዎች ከእውነት መንገድ ይስታሉ። ስለዚህ በታላላቅ ቤተክርስቲያኖች ብዙም አትመሰጡ።

 

ኢየሱስ ታላቅ ድግስ አዘጋጅቶ ብዙ ሰዎችን ስለ ጋበዘ አንድ ሰው ምሳሌ ተናገረ።

እግዚአብሔር ብዙ የዳኑ ክርስቲያኖችን ወደ በጉ የሰርግ እራት ይጋብዛቸዋል። ነገር ግን የጋበዛቸውን ሁሉ ይቀበላቸዋል?

ምሳሌው አይቀበላቸውም ይላል።

ሉቃስ 14፡16 እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤

17 በእራትም ሰዓት የታደሙትን፦ አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ።

18 ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው፦ መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።

እግዚአብሔር ወደ ራሱ የሚጋብዘን ወደ እርሱ ለመቅረብ የመጽሐፍ ቅዱስን መንገድ ስንከተል ብቻ ነው።

በራሳችን መንገድ ወደ እርሱ ልንቀርብ አንችልም።

ከነዚህ ከዳኑ ክርስቲያኖች መካከል ማናቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተጣብቀው አይቆዩም። ሁላቸውም በየራሳቸው ሃሳብና ፍላጎት ተጠምደዋል። ሁላቸውም የፈቀዱትን ማድረግ ይመርጣሉ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ባለመከተላችን ይቅርታ አድርጉልን፤ ግን ከተወሰኑ የሰው ንግግር ጥቅሶች ተነስተን ያዘጋጀናቸው ብልህ ሃሳቦች አሉን።

እግዚአብሔርን ለማገልገል በራሳቸው ባዘጋጁት “ብልህ” መንገድ እግዚአብሔር የሚገረም ይመስላቸዋል።

ለነገሩ የራሳቸው ቤተክርስቲያን ማለትም የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ውስጥ አይደሉ። ስለዚህ እንደፈለጉት ማድረግ ይችላሉ። ምክንያቱም ቤተክርስቲያኒቱ የእነርሱ እንጂ የእግዚአብሔር አይደለችም።

ሉቃስ 14፡24 እላችኋለሁና፥ ከታደሙት ከእነዚያ ሰዎች አንድ ስንኳ እራቴን አይቀምስም አለው።

ይህ አስደንጋጭ መልስ ነው።

እግዚአብሔር በዘመናዊ ቤተክርስቲያኖች እና በታላላቅ ፓስተሮቻቸው ምንም አይገረምም። እነርሱ ሙሽራይቱ ውስጥ እንዲሆኑ አይፈልግም።

ማቴዎስ 7፡22 በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።

23 የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።

መጽሐፍ ቅዱስን ካልታዘዝን ታላላቅ ስኬቶች ምንም ትርጉም የላቸውም።

ስለዚህ የተዘጋጀውን እራት የሚበላ ሰው መገኘት ነበረበት።

ሉቃስ 14፡23 ጌታውም ባሪያውን፦ ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው፤

መጥፎ ሰዎች እና ወንበዴዎች ማሕበረሰቡ ያገለላቸው ሰዎች የሚኖሩት በመንገድ እና በቅጥር ነው።

መልካሞቹ የዳኑ ክርስቲያኖች ከኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ዲኖሚኔሽናዊ ትምሕርቶችን ይመርጣሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር እነርሱን ትቶ በመንገድ እና በቅጥር ያሉትን ይጠራቸዋል።

ዛሬ በዓለም ዙርያ ራሳቸውን እንደ ፈሪሳውያን ጻድቅ አድርገው የሚቆጥሩ ክርስቲያኖች ፕሬዚዳንት ትራምፕን ይቃወሙታል፤ የሚቃወሙትም እንደ ግለሰብ ጥሩ ታሪክ ስለሌለው ነው። ብዙ ፉክክር ባለበት ምርጫ ውስጥ ቢያሸንፍም እንኳ ክርስቲያኖች ስለ እርሱ አስተሳሰባቸውን ሊቀይሩ አልቻሉም። ምርጫውን ማሸነፍ አልነበረበትም ይላሉ።

ለምንድነው ያሸነፈው?

ምክንያቱም በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ትሁን የሚል ሃሳብ ሲቀርብና 128 ሃገሮች ይህንን ሃሳብ ሲቃወሙ ከደገፉ 9 ሃገሮች ውስጥ በመደገፍ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ስለሆነ ነው። ሌሎቹ የክርስቲያን ሃገሮች ሁሉ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ የመሆኗን ሃሳብ ተቃውመዋል። ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ቡሽ፣ እና ኦባማ ሁላቸውም ጥሩ ሰዎች ናቸው፤ ነገር ግን ሙስሊም ሃገሮችን ለመጋፈጥ የሚበቃ ወኔ አልነበራቸውም። ኢየሱስን ከመፍራት ይልቅ አላህን ፈርተዋል።

128 ሃገሮች እግዚአብሔርን በመቃወም ድምጽ ሰጡ። ዘጠኝ ሃገሮች እግዚአብሔርን ደግፈው ድምጽ ሰጡ። ይህም በስተመጨረሻ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ምን ያህል ጥቂት እንደሚሆኑ ያሳያል።

ስለዚህ ይህ የዘመን መጨረሻ ምሳሌ ነው።

መልካሞቹ ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ለማገልገል እምቢ ካሉ ክፉዎቹ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማገልገል ጥሪ ይቀርብላቸዋል።

ክፉዎቹ ሰዎች ከመልካሞቹ ሰዎች የበለጠ ወኔ እንዳላቸው እናያለን። ፕሬዚዳንት ትራምፕ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መመለሳቸው ሁለት ሺ ዓመት ያስቆጠረ ትንቢት እንዲፈጸም አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው። ልክ የፋርስ ንጉስ ቂሮስ አይሁዶች ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ እንዳደረገው ማለት ነው።

ለብቻ መቆም፤ በመጨረሻ ጥቂት ሆኖ ታማኝ መሆን። ይህ ትልቅ ወኔ ይጠይቃል።

1965 የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ዘመን - የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ ምዕራፍ 3

እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ምን ትመስል እንደነበረ እንዴት አድርገን እንደምንመዝን አሁን ገብቷችኋል (የበዓለ ሃምሳ ዕለት ምን ትመስል እንደነበረ እና በቃሉ ውስጥ በሐዋርያት ሥራ በተጻፈው መሰረት ምን እንደምትመስል) ስለዚህ ይህንኑ መመዘኛ በመጠቀም ቤተክርስቲያን እንዴት እንደ ወደቀች ማሳየት እንችላለን። ወደ መጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሾልከው የገቡትና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እና በዮሐንስ ራዕይ እንዲሁም በመልእክቶች ውስጥ የተገለጡት መሰረታዊ ስሕተቶች በቀጣዩ የቤተክርስቲያን ዘመን ይበልጥ ጎልተው ይወጣሉ፤ በስተመጨረሻም በመጨረሻው በሎዶቅያውያን ዘመን እውነት ሙሉ በሙሉ በጨለማ ትዋጣለች

በዚህ ከጌታ በተቀበልነው ቁልፍ አማካኝነት ሌላ አስደናቂ እውነት እናገኛለን። እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ሁልጊዜም ቢሆን በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደነበረችዋ ቤተክርስቲያን ለመሆን ትሞክራለች። ትክክለኛ ቤተክርስቲያን እንደዚህ ነው የምትሆነው። ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ቀናት ጌታ ከመገለጡ በፊት እውነት ሙሉ በሙሉ በስሕተት ተውጣ እንደምትጠፋም ከቃሉ ውስጥ አይተናል።

ማቴዎስ 22፡14 የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።

ምሳሌ 30፡24 በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፤ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፤

25 ገብረ ጕንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ።

ጉንዳኖች ሁልጊዜ በሥራ እንደተጠመዱ ናቸው። በበጋ ወቅት ለክረምት ምግብ ያከማቻሉ። እኛም ጥቅሶችን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እየወሰድን መርምረን ትምሕርቱን ማመን አለብን፤ የምናምነውም ወንድም ብራንሐም ስለተናገረ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ስለተናገረ ነው። ይህ የፊተኛው ዝናብ ማለትም የትምሕርት ዝናብ ወቅት ነው። ስለዚህ አሁን የምንማርበት ጊዜ አግኝተናል።

የኋለኛው ዝናብ ፍሬው ከተክሉ ላይ የሚታጨድበት የመከር ዝናብ ነው። ሙታን ከመቃብራቸው ላይ እንደ መከር እህል ታጭደው ይወሰዳሉ፤ ሙሽራይቱም ከምድር ተወስዳ ወደ ሰማይ ትሄዳለች። ብርቱው መልአክ ወደ ምድር የሚወርደው ይህን ለማድረግ ነው። ስለ ወንድም ብራንሐም ትምሕርቶች እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከነዚህ ትምሕርቶች የተነሳ የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ የተከፈተ መጽሐፍ ሆኖልናል። መጽሐፍ ቅዱስ የተከፈተ መጽሐፍ ከሆነላችሁ የመጨረሻው መከር አካል አትሆኑም።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፉት የሰባቱ ነጎጓዶች ቃላት ነጎድጓዶቹ በሚናገሩ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሆነ ቦታ ተሰውረው ልታገኙዋቸው ይገባችኋል። ስለዚህ የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስ በደምብ ማወቃችሁን እርግጠኛ ሁኑ።

ይህ ዌብሳይት የተዘጋጀው ሰው ሁሉ ይህንን እውነት መርምሮ እንዲያገኝ ለመርዳት ነው።

ታናሽ ቡድን ይህን ሚስጥር ይደርስበታል።

በወንድም ብራንሐም ንግግር ጥቅሶች በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መተርጎም እንዳለብን የምንማርበት ጊዜ አሁን ነው።

ምሳሌ 30፡26 ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፣ ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ።

ሽኮኮዎች ዓለት ውስጥ የሚኖሩ ጥንቸሎች ናቸው። እኛም ልክ እንደ እነርሱ ደካሞች ነን፤ ነገር ግን በዓለቱ በክርስቶስ ውስጥ መደበቅን መማር አለብን፤ በክርስቶስ ውስጥ ማለት በተገለጠው ቃሉ ውስጥ ማለት ነው።

 

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23