ራዕይ 5፡6፤ 7 ቀንዶች 7 ዓይኖች
We update studies as the Lord Jesus leads us. You can find the latest update of this study at ChurchAges.net
ቤተመቅደሱ በውስጡ ባለ 7 ቅርጫፍ መቅረዝ እና 12 ሕብስቶች አሉት። 7ቱ መብራቶች 7ቱን የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላሉ።
- ኢየሱስ ብዙ ከባድ አገልግሎቶችን ብቻውን ያከናውናል
- ልብ አራት ክፍሎች እንዳሉት ቤተክርስቲያንም አራት ደረጃዎች አሏት
- ቀጣዩ ጥቅስ በዘመን ውስጥ የሚደረግ ጉዞ ነው
- እግዚአብሔር ለ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናትና ለ12ቱ የእስራኤል ነገዶች እቅድ አለው
- ሰባት መናፍስት
- ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች
ኢየሱስ ብዙ ከባድ አገልግሎቶችን ብቻውን ያከናውናል
ራዕይ 5፡6 በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፥ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።
በጉ ኢየሱስ በዙፋኑ መካከል ነው።
ነገር ግን ቀደም ባለው ምዕራፍ ውስጥ ስንመለከት ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የነበረ አንድ እንዳለ እናያለን።
ራዕይ 4፡2 ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤
በአንድ ዙፋን መካከል ሁለት ሰዎች በአንድ ጊዜ ሊቀመጡ አይችሉም።
ስለዚህ ምዕራፍ 4 ውስጥ እንደተጻፈው ዙፋኑ ላይ ያለው እግዚአብሔር ምዕራፍ 5 ውስጥ በዙፋኑ መካከል የቆመው በጉ እራሱ ነው።
ይህ ሰውኛ ዘይቤ ይባላል።
በጉ የኢየሱስን የማዳን እና ዓለምን የመቤዠት አገልግሎት ይወክላል።
መጽሐፉን ማለትም የፍጥረት ባለቤትነት ማረጋገጫውን ይዞ ዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ኢየሱስን እንደ ፈጣሪ ይወክላል።
እነዚህን የፈጣሪነትና የቤዛነት ሥራዎችን በአንድነት አጣምሮ መያዝ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ይህን ሊያደርግ የሚችል ሌላ ማንም የለም።
ኢሳይያስ 43፡1 አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ።
ሌሎች ሐይማኖቶች አንድ አምላክ ብቻውን እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ሊሰራ ይችላል ብለው አያምኑም።
ለራሳቸው ብዙ አማልክትን ፈጥረዋል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ አምላክ አንድ ልዩ አገልግሎት ያከናውናል።
ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሾልከው ከገቡ ትልልቅ ስሕተቶች አንዱ ይህንኑ የአረማውያን አስተሳሰብ በመቀበል እነዚህን ከባድና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚያከናውኑ ስላሴዎች ያስፈልጋሉ ብሎ ማሰብ ነው።
ነገር ግን በዙፋኑ መካከል የቆመው በግ ዙፋኑ ላይ የተቀመጠው እራሱ ነው።
ይህም በተለያዩ መንገዶች የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ራሱን የሚገልጥ አንድ አካል ነው።
የሚያሳዝነው ነገር ቤተክርስቲያን ሶስት አካላት የሚለውን ሃሳብ መቀበሏና ይህም እምነት ሶስት መንፈሶች አሉ የሚለው ሃሳብ ያስከትል ይን አይሁን ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች እርግጠኛ አለመሆናቸው ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ እንደተናገረው አንድ መንፈስ ብቻ ነው ያለው።
ስላሴ የሚለው ትምሕርት ሲመጣ አብሮት አንድ ነው ወይስ ሶስት ነው? የሚል ጥያቄ አስከተለ። እስከ ዛሬ ይህንን እንቆቅልሽ ማንም አልፈታውም።
ታዋቂ የሆነው ወንጌላዊ ቢሊ ግራሐም እና የቴሌቪዥን ወንጌላዊ ዶ/ር ዴቪድ ሬገን ሁለቱም ስለሴን በደምብ መረዳት እንዳልቻሉ በግልጽ ተናግረዋል።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ 7 መናፍስት ሲናገር ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች እጥፍ ድርብ ግራ ይጋባሉ። የስላሴ ትምሕርት እንኳ ስለ ሰባት መናፍስት አይናገርም።
ታድያ በዚህ ጥቅስ እግዚአብሔር ሊያስተምረን ያሰበው ምንድነው?
7 ቀንዶች። 7 ዓይኖች። 7 መናፍስት?
የተወሰነ መነሻ ሃሳብ ያስፈልገናል።
ልብ አራት ክፍሎች እንዳሉት ቤተክርስቲያንም አራት ደረጃዎች አሏት
ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር የማዳን እቅድ ውስጥ ዋነኛዋ ጉዳይ ናት። ኢየሱስ ለቤተክርስቲያን ነው የሞተው። ከዚያም ከሙታን ተነሳ።
ልክ እንደዚሁ ቤተክርስቲያንም በመልካም ጅማሬ ከጀመረች በኋላ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ደረጃዎች ውስጥ ምድር ላይ እንደተተከ ዘር ትሞታለች።
ከዚያም በመጨረሻዎቹ ሁለት ደረጃዎች ውስጥ ቤተክርስቲያን ከምድር ውስጥ እንደሚበቅል ቡቃያ ተመልሳ ታብባለች።
በስተመጨረሻ የሚታጨደው ዘር በመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ዘመን ከተተከለው ዘር ጋር ፍጹም ተመሳሳይ መሆን አለበት።
እግዚአብሔር ይህንን እቅድ እንዴት ነው ሊያከናውነው የሚችለው?
ምዕራፍ 4 ውስጥ እግዚአብሐየር በዙፋኑ ላይ ይቀመጣል፤ ነገር ግን ከዙፋነኑ መካከል የሚወጣው መንፈሱ በአራት የተለያዩ መንገዶች ይገለጣል።
ራዕይ 4፡6 በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ። በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ፥ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ።
ዓይኖች የማስተዋል ተምሳሌት ናቸው። “በፊት” ማለት ያለፈውን ያውቃሉ ማለት ነው። “በኋላ” ማለት የጥንቱንም ያውቃሉ ማለት ነው።
እነዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ባለፉት 2,000 ዓመታት የቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ቤተክርስቲያንን እየመራ ሳለ የተገለጠባቸው መንገዶች ናቸው።
እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ነው የሚሰራው ምክንያቱም የምድር ታሪክ በየዘመናቱ የመለዋወጡን ያህል የቤተክርስቲያንም ሁኔታ በየጊዜው ይለዋወጣል።
ሰይጣን ቤተክርስቲያንን ለማታለል የተጠቀመበት ሶስት ሽንገላዎች አሉት፤ እነዚህንም ሽንገላዎች በታሪክ ውስጥ በተለያዩ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ያለውን ተጽእኖ ለማጣጣል ተጠቅሞበታል።
የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ክርስቲያኖችን ለማሳት የሚጠቀምባቸው ዋነኞቹ ሶስት መንገዶች ሐይማኖታዊ ሽንገላ፣ ፖለቲካዊ ኃይል፣ እና በገንዘብ ፍቅር የሚሰራ አጋንንታዊ አሰራር ናቸው። ከዚያም ሰይጣን በዘመን መጨረሻ ላይ ያለችዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሾልኮ ለመግባት ሶስቱን አጣምሮ አንድ ሐመር መልክ ያለው ፈረስ እየጋለበ በመምጣት ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ ሞትን ያስገባል።
እግዚአብሔር ቅዱስ መንፈሱን በመጠቀም ይህንን ክፋት በአራት መንገድ ተዋግቷል።
ራዕይ 4፡7 ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል።
በእግዚአብሔር ዙፋን ዙርያ አራት ሕያዋን ፍጥረታት እና 24 ሽማግሌዎች አሉ።
ራዕይ 4፡4 በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።
ከዋክብቱ 24ቱን ሽማግሌዎች ይወክላሉ። እነርሱም ከብሉይ ኪዳን 12 አባቶች እና ከአዲስ ኪዳን ደግሞ 12 ሐዋርያት ናቸው።
የእግዚአብሔር ታላቅ እቅድ ቤተክርስቲያንንም እስራኤልንም ያካተተ ነው።
ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች ተነስተን እግዚአብሔር በሰማይ በዙፋኑ ላይ በ4 እንስሶች (መንፈስ ቅዱስ የሚገለጥባቸው 4 ልዩ ልዩ መንገዶች) እና በ24 የብሉይ ኪዳን እና የአዲስ ኪዳን ሽማግሌዎች ተከብቦ እንደሚኖር ማየት እንችላለን።
መንፈስ የሚገለጥባቸው የተለያዩ መንገዶች የተለያዩ መንፈሶች ማለት አይደለም።
አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ልጅ፣ አባት፣ እና አያት መሆን ይችላል። እያንዳንዱ ሚና መንፈሱን በተለየ መንገድ ይገልጠዋል፤ እርሱ ግን አንድ መንፈስ ብቻ ነው ያለው።
እግዚአብሔር የሚኖርበት እንዲህ ያለ ስፍራ በምድር የት ነው ያለው?
ዳግመኛ በተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልብ ውስጥ ነው።
በልባችን ውስጥ ያሉት አራት ክፍሎች በዙርያቸው 24 የጎድን አጥንቶች አሉ።
ንሰሃ በገባና በሚያምን ልብ ውስጥ ኢየሱስ የሚኖር ከሆነ አራቱ ክፍሎችና ሃያ አራቱ አጥንቶች 4ቱን እንስሳት እና 24ቱን ሽማግሌዎች ይወክላሉ።
አራቱ እንስሳት አራቱን የኢየሱስ አገልግሎቶች ይወክላሉ፤ እነዚህም አራት አገልግሎቶች እርስ በራሳቸው የሚቃረኑ ይመስላሉ።
ነገር ግን አንድ ሆኖ እነዚህን አራት ተቃራኒ አገልግሎቶች አጣምሮ መያዝ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው።
አራቱ ወንጌሎች የኢየሱስን አራት ታላላቅ አገልግሎቶች ይተርካሉ።
እንደ አንበሳ እርሱ ንጉስ ነው። እንደ ጥጃው ወይም በሬው ደግሞ ሸክማችንን የሚሸከም አገልጋይ ነው።
ስለዚህ ለእኛ አገልጋይም የሆነ ንጉስ ነው።
እንዲሁም ፍጹም ሰው እና የሚበርረው ንስር ወይም እግዚአብሔር እራሱ ነው።
ማለትም ሰው ሆኖ እግዚአብሔርም የሆነ ብቸኛው ሰው ነው።
በምድር ላይ ሰው ሆኖ እየኖረ በዚያው ጊዜ ደግሞ በሰማይ ይኖር ነበር። የማይቻል ነገር ማድረግ ለእርሱ የተለመደ ነው።
ዮሐንስ 3፡13 ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።
ኢየሱስ ምድር ላይ ተቀምጦ ኒቆዲሞስን እያናገረ በነበረበት በዚያው ሰዓት በሰማይም ነበረ።
ኢየሱስ በአንድ ጊዜ የፍጥረታዊው እንዲሁም የልዕለ ተፈጥሮአዊው ዓለም ገዥ ነው። ይህ ለእኛ የሚቻል ነገር አይደለም።
ለእርሱ ግን ምንም አስቸጋሪ አይደለም።
ልባችን ውስጡ መስቀል እንዳለው አድርገን ማሰብ እንችላለን።
አራት ክፍሎች ሲኖሩት ደም ወደ ቁጥር 1 እና ቁጥር 3 ውስጥ ይፈስሳል።
የኢየሱስ ዘር ሐረግ ማቴዎች ምዕራፍ 1 ውስጥ ተመዝግቧል፤ ይህም የዘር ሐረግ ከንጉስ ዳዊት ይጀምርና ኢየሱስ አንበሳ ማለትም ንጉስ መሆኑን ያሳያል። ቀጥሎ ደግሞ ከመልከጼዴቅ ጋር ፊት ለፊት የተገናኘውን አብርሃምን ይጠቅሰዋል። መልከጼዴቅ እግዚአብሔር ራሱን በጊዜያዊነት ለመግለጥ የተጠቀመበት አካል ነው።
ሌላኛው የኢየሱስ ዘር ሐረግ የተጻፈው ሉቃስ ምዕራፍ 3 ውስጥ ብቻ ሲሆን ይህም ምዕራፍ ሐጥያት ከመስራቱ በፊት የመጀመሪያው ፍጹም ሰው ከነበረው ከአዳም ይጀምራል።
ኢየሱስም የመጀመሪያው አዳም ያበላሸውን ነገር ሁሉ ሊያስተካክል የመጨረስ አዳም ወይም ፍጹም ሰው ሆኖ መጣ።
4ቱ ወንጌሎች የመስቀሉን ታሪክ ይነግሩናል።
ማቴዎስ ኢየሱስን አንበሳ፣ የአይሁድ ንጉስ፣ የዳዊት ልጅ አድርጎ ያሳየናል። የሁለት ዓመት ሕጻን እያለ ጠቢባን ከሩቅ መጥተው ጎብኝተውታል።
ማቴዎስ ስለ ግርግም አይናገርም ምክንያቱም ነገስታት ግርግም ውስጥ አይወለዱም።
ማርቆስ ኢየሱስን እንደ በሬ ማለትም ታታሪ ሰራተኛ እና ስለ ሐጥያታችን የታረደልን መስዋእት፤ ሐጥያታችንን በሰይጣን ላይ ለማራገፍ ተሸክሞ ወደ ሲኦል የሄደለን ትጉ አገልጋይ አድርጎ ያሳየናል።
ሉቃስ ኢየሱስን ፍጹም ሰው አድርጎ ያሳየናል። ደሃ ሆኖ በሚሸት ግርግም ውስጥ ተወለደ። ሉቃስ ከቤቱ ጠፍቶ ከጋለሞታዎች ጋር ገንዘቡን ስላባከነው ነገር ግን ኋላ ይቅር ስለተባለው ልጅ እንዲሁም ልክ ከመሞቱ በፊት ይቅር ስለተባለው ሌባ ይነግረናል።
ዮሐንስ ደግሞ ከፍ ብሎ የሚበርር ንስር፤ ከእኛ ሁሉ በላይ የሆነው እግዚአብሔር አድርጎ ያሳየናል። የመጀመሪያ ተዓምሩ ሰርግ ቤት ውሃን ወደ ወይን ጠጅ መለወጥ ነው። የመጨረሻው ተዓምሩ ደግሞ ሕያው የሆነችዋን ሙሽራ በሰማይ ወደተዘጋጀው ወደ በጉ ሰርግ እንድትታደም የማትሞት አድርጎ መለወጥ ነው።
አራቱ እንስሳት በተጨማሪ በ2,000 ዓመታት ውስጥ ያለፈውን የቤተክርስቲያን ታሪክ ይናገራሉ።
አንበሳው ቤተክርስቲያንን የመሰረቷትና የእውነትን መሰረት የተከሉ ሐዋርያት የነበሩበትን የመጀመሪያውን የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ዘመን ይገልጻል።
ከዚያ በኋላ በ325 ዓ.ም የኒቅያ ጉባኤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውን “ስላሴ” የተባለ ቃል በቤተክርስቲያን ላይ በጫነባት ጊዜ እውነት ሞተች። ቤተክርስቲያንም ፖለቲካዊ ስልጣን አግኝታ የሚቃወሟትን ማለትም የቤተክርስቲያን መሪዎች የሚሉትን የማይቀበሉ ሰዎችን መግደል ጀመረች። የስላሴን ትምሕርት የተቃወሙ ሰዎች ተገደሉ። ከዚያ በኋላ ረጅሙ የጨለማ ዘመን ተጀመረ፤ በዚህም ረጅም ዘመን ውስጥ ጥጃው ብርቱ በሬ እስኪሆን ድረስ ለማደግ ጊዜ አገኘ፤ ይህም ለስራ እና ለመታረድ የተፈጠረ እንስሳ ነው። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ተቃውማችኋል ተብለው ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተገደሉ።
በ1517 ዓ.ም አካባቢ አእምሮውን እግዚአብሔር የባረከለት ማርቲን ሉተር ጻድቅ የሚኖረው በእምነት ብቻ ነው ብሎ አስተማረ። ትክክለኛው የመዳን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሶ ገባ።
እግዚአብሔር የሰዎችን አእምሮ እና ጥበብ ስለባረከ እግዚአብሔር የቀባቸው 47 ምሑራን ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን ተረጎሙ። ከተረጎሙት በኋላ ለቀጣዮቹ 150 ዓመታት በተደጋጋሚ ሲፈተሽና ሲመረመር ቆይቶ በ1769 የተስተካከለው ትርጉም ወጣ።
ከዚያ በኋላ ጆን ዌስሊ ውስጥ የነበረው ሰብዓዊ ጥበብ በእግዚአብሔር መንፈስ ተቀብቶ የወንጌል ስርጭትን እና ቅድስናን ሰበከ፤ ከዚህም የተነሳ በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ታላቁ የወንጌል ስብከት ዘመን ተጀመረ።
የሰዎች ጥበብ በእግዚአብሔር ተባርኮ ነበር፤ ሰይጣን ግን የእግዚአብሔርን ቃል ለሽያጭ በማቅረብ ቤተክርስቲያንን ወደ ንግድ ማዕከል ለወጣት። በዚያ ጊዜ ሐጥያታችሁን ለማስተስረይ የስርየት ወረቀት በሽያጭ ይቀርብላችሁ ነበር። ከዚህ ሽያጭ በተሰበሰበው ገንዘብ ቫቲካን ውስጥ ሲስቲን ቻፕል እና የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ሕንጻዎች ተሰርተውበታል። ወንጌሉ ለካቶሊኮችም ለፕሮቴስታንቶችም ትልቅ ንግድ ሆነ።
የታላቁ ንስር የፕሮቴስታንት መነቃቃት በ1906 ሎሳንጀለስ ውስጥ አዙዛ እስትሪት በተባለ ቦታ ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል አሜሪካ ውስጥ ወደ ቤተክርስያን መመለስ ጀመረ። ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መረዳትና ወደ መጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ እምነት መመለስ ይችሉ ዘንድ ከ1947 እስከ 1965 ዊልያም ብራንሐም ጠለቅ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራትን በመግለጥ አስተማረ።
በመጨረሻ የሚታጨደው የእውነት ዘር በመጀመሪያ በሐዋርያት ከተተከለው የተጻፈ ዘር ጋር አንድ ዓይነት መሆን አለበት።
ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መገለጥ ለመገዳደር ሰይጣን ብዙ ልዩ ልዩ ሽንገላዎችን ይዞ ወደ ቤተክርስቲያን ገባ። ሐይማኖታዊ ሽንገላ 45,000 ዓይነት ልዩ ልዩ ዲኖሚኖሽኖችን ከመፍጠር አልፎ ከ100 በላይ የተለያዩ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዲዘጋጁ አደረገ። በዚህ ሁሉ ግርግር መካከል እውነትን ለማግኘት መሞከር ተስፋ ያስቆርጣል። ከሁሉ ይበልጥ ጥቃት የተሰነዘረበትና እስካሁንም የሚሰነዘርበት መጽሐፍ ቅዱስ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ነው።
ፖለቲካ ትኩረቱን ተቃዋሚዎችን መጥላት ነው፤ ቤተክርስቲያን ደግሞ ፖለቲካ ውስጥ ገባች። ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚለውን ትዕዛዝ ጣለችው።
ትልቅ ንግድ ሃብታም ወደ ሆነችዋ ቤተክርስቲያን ኢንቨስትመንት እና ንብረቶችን ይዞ ገባ። ትልልቅ ቤተክርስቲያኖች ብዙ ትርፍ አጋበሱ። የብልጽግና ወንጌል ትኩረቱ ቁሳዊ ሃብት መሰብሰብ ላይ ሆነ።
የቴሌቪዥን ሰባኪዎች ያላቸው ግማሽ ሰዓት ብቻ ቢሆንም በዚያችም ውስጥ የሚሸጡ መጻሕፍት እና ቪዲዮዎችን ለማስተዋወቅ ጊዜ አላቸው፤ ሲያስተዋውቁም የዓለማዊ ንግድ ቴክኒኮችን ሁሉ ነው የሚጠቀሙት።
ቀጣዩ ጥቅስ በዘመን ውስጥ የሚደረግ ጉዞ ነው
ብዙ የቤተክርስቲያን ሰዎች በመረዳት የሚሳሳቱት የበጉን እንቅስቃሴ በተመለከተ ነው።
ራዕይ 5፡7 መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው።
በጉ ዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከእግዚአብሔር እጅ መጽሐፉን ለመቀበል ወደ ዙፋኑ ፊት የሚሄድ ሌላ አካል አድርገው ነው የሚያዩት።
ይህ ዓይነቱ መረዳት ግን ስሕተት ነው።
ራዕይ 5፡6 በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፥
በጉ ሁልጊዜም በዙፋኑ መካከል ስለነበረ ከቦታ ወደ ቦታ አልተንቀሳቀሰም።
ታዲያ ወዴት ነው የተንቀሳቀሰው?
አይንሽታይንን ጠይቁት። የአይንሽታይን ቲዎሪ በስፍራ እና በጊዜ አራት ቀጠናዎች ውስጥ ነው የምንኖረው ይላል።
ስፍራ ከጊዜ ጋር የተጠላለፈ ነገር ነው።
በስፍራ እንደምንንቀሳቀስ በደምብ እናውቀዋለን፤ ነገር ግን በጊዜም ውስጥ ከጥንቱ ወደ ዛሬና ወደ ወደፊቱ እንደምንንቀሳቀስ አናስተውልም።
በጊዜ ውስጥ ወደ ፊት ብቻ ነው መንቀሳቀስ የምንችለው።
ኢየሱስ ግን እኛ የማንችለውን ማድረግ ይችላል። በጊዜ ውስጥ ወደ ፊትም ወደ ኋላም መንቀሳቀስ ይችላል።
በጉ ዙፋኑ መካከል ሆኖ በስፍራ አልተንቀሳቀሰም፤ ነገር ግን በጊዜ ወደ ኋላ ሄዶ እስከ ቀራንዮ ደርሷል። ከዚያም በጊዜ ውስጥ ወደ ፊት በመንቀሳቀስ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ መጥቶ ያቀደው የማዳን እቅድ በተሳካ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አረጋግጧል።
ይህንን ጥቅስ መረዳት ያለብን በዚህ መንገድ ነው።
ይህ እንቅስቃሴ በ2,000 ዓመታት የቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የተደረገ ጉዞ ነው። ይህም የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቀስተደመና ነው።
7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት በ4 ክፍሎች ይከፈላሉ፤ እነዚህም በእግዚአብሔር ዙፋን ዙርያ ባሉት በአራቱ እንስሳት ይመራሉ።
የመጀመሪያዎቹ አራቱ ማሕተሞች እያንዳንዳቸው በሁለት ጥቅስ ነው የተገለጡት።
የመጀመሪያዎቹ ሰባት ቁጥሮች 7ቱን የቤተክርስቲያን ዘመናት ይገልጻሉ። የመጀመሪያዎቹ ሶስት ማሕተሞች እያንዳንዳቸው ሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናትን ይገልጻሉ።
የንስሩ 4ኛው ማሕተም በቁጥር 7 ውስጥ 7ኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን ብቻ ይገልጻል።
ቀጣዩ ቁጥር ማለትም ቁጥር 8 የታላቁን መከራ 3.5 ዓመታት ይገልጻል፤ ይህም የሚሆነው ሙሽራይቱ ከጌታ ጋር ለመሆን ልክ እንደ ንስር ወደ ሰማይ ከተነጠቀች በኋላ ነው።
ይህን ሁሉ በራዕይ ምዕራፍ 6 የመጀመሪያ 8 ቁጥሮች ውስጥ ማንበብ ትችላላችሁ።
ራዕይ 6፡1 በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።
ራዕይ 6፡2 አየሁም፥ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት።
የመጀመሪያው ማሕተም ሁለት የመጀመሪያ ቁጥሮች የመጀመሪያዎቹን ሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላሉ።
እነዚህ ሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናት ሰው የቤተክርስቲያን ራስ እንዲሆን በመፍቀድ ሐይማኖታዊ ሽንገላ ስር እንዲሰድድ ፈቅደዋል።
ቤተክርስቲያኖች አንድ ሰው የአንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ራስ እንዲሆን ከፈቀዱ በኋላ ይህ ሽንገላ እየተስፋፋ መሪውን ከፍ በማድረግ ቤተክርስቲያንን እስከ 7ኛው የቤተክስቲያን ዘመን መጨረሻ ድረስ ሲያታልላት ሊቆይ ችሏል።
የመጀመሪያው እንስሳ የይሁዳ ነገድ አንበሳ ሲሆን እርሱም በመጀመሪያው ዘመን የተገለጠውን ሐዋርያዊ እውነት ይወክላል።
ሰይጣን የክርስቶስ ተቃዋሚውን በነጭ ፈረስ (ሐይማኖታዊ ሽንገላ) ላይ አስቀምጦ በመላክ ምላሽ ሰጠ፤ ይህም ፈረሰኛ ደጋን አለው ቀስት ግን የለውም፤ ይህም ሽንገላ ነው።
ቀስት የለውም ማለት የእግዚአብሔር ቃል የለውም ማለት ነው። ፓስተሩ የቤተክርስቲያን ራስ ነው የሚል አንድ ቃል አዲስ ኪዳን ውስጥ የለም። ዛሬ ግን ፓስተሩ ወይም ሪቨረንድ ወይም ቄስ የቤተክስቲያን ራስ ሆኖ ያልተቀመጠበት አንድም ቤተክርሰቲያን የለም። ነገር ግን ፓስተር የሚለው ቃል አዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተጠቀሰው። ይህም ሰውን ከፍ የማድረግ ልማድ ቀጥሎ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካርዲናሎች፣ የአውራጃ አስተዳዳሪዎች ወደሚባሉ ማዕረጎች ሁሉ ተስፋፍቷል።
ይህ አንድን ሰው የቤተክስቲያን መሪ የማድረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ የተሳሳተ ልማድ ቤተክርስቲያንን ሙሉ በሙሉ አታልሏታል።
ይህ ቤተክርስቲያን ውስጥ አንድን ሰው ከሕዝቡ በላይ ከፍ የማድረግ ስሕተት በመጀመሪያዎቹ ሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ስር ከሰደደ በኋላ በ860 ዓ.ም ፖፕ ኒኮላስ ከነገስታት ጋር እኩል ይሆን ዘንድ ዘውድ እስከጫነበት ጊዜ ድረስ ዘልቋል። ይህም ከፍታ አልበቃ ብሏቸው በ1316 ፖፑ ከነገስታት በላይ ከፍ ይል ዘንድ ባለ ሶስት ድርብ ዘውድ ጫኑለት።
“ድል እየነሳ” ማለት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዲኖሚኔሽናዊ እምነቶች መሪን የቤተክርስቲያን ራስ ይሆን ዘንድ ከፍ ከማድረግ ልማዳቸው ጋር የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖችንም ድል ይነሳሉ ማለት ነው።
ራዕይ 6፡3 ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።
በረጅሙ የጨለማው ዘመን ውስጥ ጥጃው ትልቅ ብርቱ በሬ ሆኖ አደገና ታረደ። በዚያ ዘመን የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ከተቃወሙ እንደሚሞቱ ሁልጊዜ ዛቻ ይደርስባቸው የነበሩ ክርስቲያኖች እጅግ እየበረቱ ሄደዋል።
ራዕይ 6፡4 ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፥ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።
ቁጥር 4 እና 5 ሶስተኛውን እና አራተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላሉ።
ይህ ቁጥር ስለ ሌላ ፈረስ ቢናገርም ሌላ ፈረሰኛ አልጠቀሰም። ስለዚህ ያው አንዱ የክርስቶስ ተቃዋሚ በሁለተኛ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ነው ማለት ነው፤ ይህም ፖለቲካዊ ኃይልን ይወክላል።
ሐይማኖት እና ፖለቲካ ተያይዘው አደገኛ ዳንስ ይደንሳሉ።
ሐይማኖት ሰዎች ተከፋፍለው እንዲጠላሉ ያደርጋል። ፖለቲካ ደግሞ እርስ በራሳቸውን የሚገዳደሉበት ኃይል ይሰጣቸዋል።
በ325 ዓ.ም በተደረገው የኒቅያ ጉባኤ ፖለቲከኛው ሮማዊ ገዥ ኮንስታንቲን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለውን “ስላሴ” የተባለ ቃል ቤተክርስቲያኖች እንዲቀበሉ አስገደደ። ይህም ድርጊት ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ብዙ ቃላት ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲገቡ በር በመክፈት እውነትን ገደለ።
ፕሮቴስታንቶች ከሚያምኑባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ አንዳንድ የካቶሊክ አስተምሕሮዎች መካክ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡- ስላሴ፣ የውሃ ጥምቀት በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ማጥመቅ (እነዚህ ማዕረግ እንጂ ስም ስላልሆኑ ስላሴያዊው አምላክ ስም የለውም)፣ ክሪስማስ፣ ዲሴምበር 25፣ የገና ዛፍ፣ የስቅለት አርብ፣ የፋሲካ ሰኞ፣ የኩዳዴ ጾም፣ ሰው የቤተክርስቲያን ራስ ነው እና የመሳሰሉት።
በ476 ዓ.ም ባርቤሪያውያን የሮማ መንግስትን ባፈራረሱ ጊዜ ሞቶ የነበረው አረማዊው የሮማ መንፈስ ከሮማ መንግስት ውድቀት አልፎ በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አማካኝነት እንደገና ነፍስ ዘርቶ ተነሳ።
የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እጅግ ትልቅ ፖለቲካዊ ኃይል በመላበስ ጠላቶቿን እየጨፈጨፈች በጨለማው ዘመን ውስጥ ብቻ ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተቃዋሚዎቿን ገደለች።
እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ አስተምሕሮዎች ቤተክርስቲያን ላይ በግድ የተጫኑባት ስለነበሩ ከተሃድሶ በኋላ ፕሮቴስታንቶች እንኳ ሳይቀሩ በነዚህ አስተምሕሮዎች ማመናቸውን ቀጥለዋል። በስላሴ ጉዳይ ብዙ ሚሊዮኖች ስለተገደሉ ማንም ሰው ስላሴን የመቃወም ድፍረት የለውም። ዛሬ እንኳ በስላሴ የሚያምኑ ፕሮቴስታንቶች በስላሴ ከማያምኑ ጋር ምንም ሕብረት ማድረግ አይፈልጉም።
አሁን ወደ ማርቲን ሉተር ተሃድሶ ደርሰናል።
ራዕይ 6፡5 ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ጕራቻ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ።
6 በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ፦ አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ ሲል ሰማሁ።
ቁጥር 5 እና 6 አምስተኛውንና 6ኛውን የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላሉ።
ስንዴ እና ገብስ ዳቦ ለመጋገር ይጠቅማሉ። ዳቦ ወይም እንጀራ የእግዚአብሔርን ቃል ይወክላል ምክንያቱም ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ ነው።
የቤተክርስቲያን መሪዎችን ሃብታም ለማድረግ ለማበልጸግ ተብሎ የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሸቀጥ እየተሸጠ ነው።
በትልልቅ ንግድ ውስጥ የሚራው የአጋንንት አሰራር ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብቷል። የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ሕንጻን ለመስራት ተብሎ ይሸጥ የነበረው የስርየት ወረቀት ማርቲን ሉተር በተቃውሞ ለተሃድሶ እንዲነሳ ቀሰቀሰው። ፖፑ ይል እንደነበረው ይህን ወረቀት መግዛት ለሐጥያት ስርየት ያስገኛል።
ዘይት መንፈስ ቅዱስን ይወክላል። ወይን ደግሞ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ሲጀምሩ የሚያገኙት የመገለጥ መነቃቃት ነው።
እግዚአብሔር በጨለማው ዘመን ውስጥ ጠፍቶ የነበረውን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን መመለስ ጀመረ።
የእውነት ተሃድሶ ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት ሲጀምር ሰይጣን ለበቀል የቤተክርስቲያን መሪዎችን በገንዘብ እና በሃብት ፍቅር በማማለል ቤተክርስቲያንን ወደ ንግድ ማዕከልነት ለወጣት። ነገር ግን በየዘመናቱ እግዚአብሔር አእምሮዋቸውን የባረከላቸው ሰዎች ስለነበሩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ ለማምጣት ጥረት አድርገዋል።
ጀርመኒ ውስጥ ማርቲን ሉተር መዳን በእምነት ነው የሚለውን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ አመጣ። የእንግሊዝ ምሑራን ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን ተረጎሙ። እንግሊዝ ውስጥ ጆን ዌስሊ የወንጌል ስርጭትን እና ቅድስናን ስላስተማረ ታላቁ የወንጌል ስብከት ዘመን ተጀመረ።
ነገር ግን የሰው ጥበብ ጠለቅ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መግለጥ አልቻለም።
ጠለቅ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መገለጥ እንደ ንስር አጥርቶ አድርጎ ማየት የሚችል የነብይ እይታ ይጠይቃል።
ራዕይ 6፡7 አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።
ቁጥር 7 የመጨረሻውን ሰባተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን ይወክላል።
ሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የሚጠናቀቀው በ3.5 ዓመታት ታላቅ መከራ ነው።
7ኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን የከፈተው የጴንጤቆስጤ መነቃቃት አሜሪካ ውስጥ በአዙዛ እስትሪት ሎሳንጀለስ ከተማ ካሊፎርኒያ ውስጥ ተጀመረ።
የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እና ስጦታዎች ተመልሰው ወደ ቤተክርስቲያን መጡ። የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት ግን ሳይገለጡ ቀሩ።
በ1947 እና 1965 መካከል እግዚአብሔር አሜሪካ ውስጥ ዊልያም ብራንሐም የተባለ ሰውን በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት ገለጠ፤ ይህንንም ያደረገው ሐዋርያት በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ያምኑ ወደነበረው እምነት መመለስ እንድንችል ነው።
ማቴዎስ ምዕራፍ 25 ውስጥ የተጠቀሱት ልባሞቹ ቆነጃጅት የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት ተረድተው ለጌታ ዳግም ምጻት ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ።
ዳንኤል 12፡10 ብዙ ሰዎች ሰውነታቸውን ያጠራሉ ያነጡማል ይነጥሩማል፤ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፤ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፥ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ።
የዳኑት ሰነፍ ቆነጃጅት በቤተክርስቲያን ልማዶች እና እምነቶች ስለሚታለሉ በታላቁ መከራ ውስጥ ይገደላሉ፤ ይህም ታላቅ መከራ ራዕይ ምዕራፍ 6 ቁጥር 8 ውስጥ ተገልጧል።
መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ነው። መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያንን ወደ ጌታ ነጥቆ ሲወስዳት ሕይወት ከምድር ለቆ ይሄዳል።
ሕይወት ማለት ቃሉ ነው።የእግዚአብሔር ቃል በሌለበት ሞት ይነግሳል።
ሕይወት ለቆ ሲወጣ ሞት ሰተት ብሎ ይገባል።
ራዕይ 6፡8 አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።
የክርስቶስ ተቃዋሚ የሆነው ፈረሰኛ እንደ ሞት ሆኖ ነው የተገለጠው።
0.8 ቢሊዮን ፕሮቴስታንቶችን እና 1.4 ቢሊዮን ካቶሊኮችን ብንደምር የምድር ሕዝብ አንድ አራተኛው ክርስቲያን መሆኑን እናየለን።
የ3.5 ዓመቱ ታላቅ መከራ ሲጀምር ሰይጣን የመጀመሪያ ኢላማውን የሚያደርገው ክርስቲያኖች ላይ ነው።
ሰይጣን ኢላማውን የሚያነጣጥርበት ሌላ ቡድን የአይሁድ ሕዝብ ነው።
ሰይጣን በ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ አይሁዶችን ሲገድል እና ሲያሳድድ ቆይቷል። ይህም በ5ኛው ማሕተም ውስጥ ተገልጧል።
በ6ኛው ማሕተም ውስጥ እንደተገለጠው ኢየሱስ የታላቁን መከራ ዘመን ተጠቅሞ ከ12ቱ የእስራኤል ነገዶች መካከል 144,000 አይሁዶችን ለይቶ ያወጣል።
እግዚአብሔር በቀራንዮ ከአይሁዶች በተለየ ጊዜ ወደ አሕዛብ ዘወር አለ።
ኢየሱስ ሙሽራይቱን ወደ ሰማይ ነጥቆ ከወሰደ በኋላ ወዲያው በቤተክርስቲያን መሪዎቻቸው የተሸነገሉ ሰነፍ ቆነጃጅት ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ይገባሉ።
ከዚያም ኢየሱስ ወደ አይሁዶች ይመለስና 144,000 አይሁዶች የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ይቀበላሉ።
እግዚአብሔር ለ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናትና ለ12ቱ የእስራኤል ነገዶች እቅድ አለው
በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረውን የአይሁደች ቤተመቅደስ ብንመለከት በአምልኮ ስርዓታቸው ውስጥ የሚጠቀሙባቸው ሁለት ዋነኛ እቃዎችን እናያለን። እነርሱም ባለ 7 ቅርንጫፍ መቅረዝ እና 12 ዳቦዎች ያሉበት የገጹ ሕብስት የተቀመጠበት ጠረጴዛ ናቸው። እነዚህን 12 ዳቦዎች በየሳምንቱ በሰንበት ነው የሚበሏቸው፤ ከበሉም በኋላ በ12 ዳቦዎች ይተኩዋቸዋል።
12 ዳቦዎች በግልጽ የሚወክሉት እግዚአብሔር 12ቱን የእስራኤል ነገዶች እያስተዳደራቸው እንደሆነ ነው።
ዛሬ አይሁደች ወደ እስራኤል ተመልሰው በመሄድ እየተሰበሰቡ መሆናቸውን እናያለን፤ ይህም እግዚአብሔር በታላቁ መከራ ዘመን ወደ እነርሱ ይመለስ ዘንድ ነው። ይህ ሁሉ ጊዜው መቃረቡን ለእኛ ለአሕዛብ የሚጠቁም ማስጠንቀቂያ ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ብሎ እውቅና ሰጠ፤ ይህም ወደ ዘመን መጨረሻ በጣም መጠጋታችንን ያሳያል።
ኢየሱስ ወደ አይሁዶች ዘወር ከማለቱ በፊት ቤተክርስቲያን ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል መነጠቅ አለባት። በ2020 ዓ.ም ለአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ በሚደረግበት ጊዜ በርኒ ሳንደርስ ጆ ባይደንን በብዙ ነጥብ እየመራው ነበር፤ ኋላ ግን የእስራኤል ዋና ከተማ ወደ ቴል አቪቭ መመለስ አለበት ሲል ነው እራሱ ወደ ኋላ የቀረው። ከሳምንት በኋላ የበርኒ ሳንደርስ ቅሰቀሳ ተቋረጠ። እግዚአብሔር እስራኤል ከ2,000 ዓመታት በፊት ወደነበረችበት እንድትመለስ ይፈልጋል።
ሰባት መናፍስት
ባለ ሰባት ቅርንጫፉ መቅረዝ በ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ሲያበራ የነበረውን የወንጌሉን ብርሃን ይወክላል።
7 ቁጥር በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ መስራት የሚጀመረው ከዚህ ነው።
በእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመን እግዚአብሔር በዚያ ዘመን ውስጥ ሰይጣንን ለመዋጋት እና እውነትን ለማስፈን ለዚያ ዘመን ልዩ እቅድ ነበረው።
ስለዚህ በእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ እግዚአብሔር ከተለያዩ ሁኔታዎች ጋር ነበር ትግል የገጠመው።
እግዚአብሔር 7 መንፈሶች የሉትም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ከየዘመናቱ ሁኔታ አንጻር በ7 የተለያዩ መንገዶች ይሰራ ነበር።
ስለዚህ እያንዳንዱ ዘመን ልዩ ስለነበረ 7ቱ መናፍስት የሚለው እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ዘመን በተለየ መንገድ ይሰራ እንደነበረ ያመለክታል።
ከ33 ዓ.ም እስከ 170 ዓ.ም ድረስ የነበረው የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን (ይህም ሽማግሌዎች ወይም ጳጳሳት የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበሩበት ጊዜ ነው) ሐዋርያት የተንቀሳቀሱበትና 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የጻፉበት ዘመን ነው። ዋናው ጸሐፊ እና የአሕዛብ ሐዋርያ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ነው። አልፎ አልፎ ለረጅም ጊዜ ቁጭ ብሎ መልእክቶችን እንዲጽፍ እግዚአብሔር ጳውሎስን በእስር ቤት ያስቀምጠው ነበር። እግዚአብሔር ሐዋርያውን ዮሐንስን በፍጥሞ ደሴት ወደምትገኝ እስር ቤት የላከው በዚያ ተረጋግቶ ተቀምጦ ታላቁን የራዕይ መጽሐፍ እንዲጽፍ ነው።
ከ170 ዓ.ም እስከ 312 ዓ.ም በሁለተኘው የቤተክስቲያን ዘመን ውስጥ ቤተክርስቲያን ብዙ ስደት ደርሶባታል፤ አማኞችም ተበታትነዋል፤ ይህም የሆነው በሰዎችና በመሪዎች ተጽእኖ ስር እንዳይወድቁ ነው። እስከ 312 ዓ.ም ድረስ በነበሩ ዓመታት ውስጥ 3 ሚሊዮን የሚያህሉ ክርስቲያኖች በሮማ መንግስት ተገድለዋል።
በ3ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ከ312-606 ዓ.ም ፖለቲካኛው መሪ ንጉስ ኮንስታንቲን ቤተክርስቲያንን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ በ325 ዓ.ም በኒቅያ ጉባኤ ሰብስቦ ቤተክርስቲያን የስላሴን አስተምሕሮ በግድ እንድትቀበል አደረጋት። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ብዙ ትምሕርቶች ለምሳሌ በ325 ዓ.ም የስቅለት አርብ፣ በ350 ዓ.ም ክሪስማስ፣ በ382 የሮም ጳጳስ ፖንቲፍ ወይም የባቢሎናውያን ሚስጥራት ሊቀካሕነው ነው፣ እንዲሁም በ450 ደግሞ መናፍቃንን መግደል የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው የሚሉ ትምሕርቶች ወደ ቤተክርስቲያን ሾልከው ሲገቡ እውነት ከቤተክርስቲያን ወጥታ ጠፋች።
ቅዱስ ፓትሪክ እና ኮሉምባ የተባሉ ታዋቂ ክርስቲያኖች በሮማ ግዛት ምዕራባዊ ጥግ አየርላንድ እንዲሁም ከእንግሊዝ እና ከእስኮትላንድ ድንበር ራቅ ብለው የሚገኙ ደሴቶች ውስጥ ተሸሸገው ነው ከግድያ የተረፉት።
ከ606 – 1520 ዓ.ም የዘለቀው 4ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ፖፑ በዓለም ዙርያ የቤተክርስቲያኖች ሁሉ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ። ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳያነብብ ተከለከለ። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በመቃወማቸው የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከአስር ሚሊዮን አለፈ።
ብዙ ክርስቲያኖች ወደ ምድረበዳ ተሰድደው እንደ አልፕስ የመሳሰሉ ተራሮች ውስጥ ተደበቁ።
እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን በሚመልስበት ጊዜ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በደምብ ተጠቅሞባቸዋል።
ከ1520 – 1750 የዘለቀው 5ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በማርቲን ሉተር ተሃድሶ ምክንያነት በጣም ዝነኛ ነው። የሕትመት ቴክኖሎጂ በዚያ ጊዜ ገና እየተጀመረ ነበር፤ ሉተርም የማተሚያ ማሽኖችን በብልሃት በመጠቀም ትራክቶችና ትንንሽ መጽሐፎችን በብዙ ሺ ቅጂዎች አባዝቶ አሰራጨ። እነዚህም ሕትመቶች መልእክቱን ወደ ብዙ ቦታዎች አደረሱለት። ሉተር ከእርሱ በኋላ የመጡ 17 የተሃድሶ መሪዎች ከጻፏቸው በራሪ ወረቀቶች በላይ ብዙ በራሪ ወረቀቶችን ጻፈ።
በ1750 ዓ.ም አካባቢ በእንፋሎት ኃይል የሚሰራው ሞተር መርከቦችን ማንቀሳቀስ በመቻሉ ብዙ የወንጌል ሰባኪዎች በመርከብ እየተሳፈሩ በዓለም ዙርያ ወንጌልን ይዘው ሄደዋል፤ እንዲሁም በእንፋሎት ኃይል የሚንቀሳቀስ ሞተር ያላቸው ባቡሮች ወንጌል ሰባኪዎች በ6ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ከ1750 – 1906 በምድር ላይ ብዙ ቦታ አድርሰዋቸዋል።
በ7ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቴፕ ሪኮርደር ተፈለሰፈና በ1947 ዓ.ም ገበያ ላይ ለሕዝብ ቀረበ። ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ በዚያ ዓመትስብከቶች በድምጽ ተቀርጸው እንዲቀመጡ በዊልያም ብራንሐም መጠቀም የጀመረው ለዚህ ነው። ካደረጋቸው ብዙ ድንቆችና ምልክቶች መካከል ዋነኛው አገልግሎቱ የተጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥረት መግለጥ ነው፤ የዚህም አገልግሎት ዓላማ ሙሽራይቱ መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ተረድታ በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ሐዋርያት ያምኑ ወደነበረው እምነት መመለስ እንትችል ነው።
ኢንተርኔት የተፈጠረው በ1989 ዓ.ም ሲሆን አሁን የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት ለሕዝብ ሁሉ ለማሰራጨት ያገለግላል።
በ2016 ዓ.ም ጉግል ትኩረቱን በሞባይል ስልኮች ላይ አደረገ፤ ስለዚህ በ2021 ዓ.ም ከዓለም ሕዝብ ሁለት ሶስተኛው ባለ ሞባይል ሆኗል።
ስለዚህ ኢንተርኔት በዓለም ዙርያ ዋነኛው መገናኛ ዘዴ በመሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መገለጥ በቀላሉ ወደ አራቱ የምድር ማዕዘናት መድረስ ይችላል።
ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች
በእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጎልቶ የወጣ አንድ የእግዚአብሔር እውነት አለ።
ቀንድ የእንስሳ ብርታት ነው። እግዚአብሔር በእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ምን ዓይነት ብርታት ነው የገለጠው?
ዓይናችን የምናይበት የሰውነት ክፍል ነው። በሕይወት እንድንኖርና እንዳንጠፋ በዘመናችን ሰይጣን ምን እየሰራ እንዳለ ማየትና ከዚያ መጠንቀቅ አለብን።
ከዚህም ይበልጥ ከባድ የሆነው ነገር ደግሞ እግዚአብሔር ምን እየሰራ እንዳለ ማወቅና በዚያ የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ነው።
እግዚአብሔር አሰራሩን በሚለውጥ ጊዜ ሰዎች ከቤተክርስቲያናቸው ልማድ ተላቅቀው እግዚአብሔርን መከተል በጣም ይከብዳቸዋል።
ዮሐንስ 7ቱን የቤተክርስቲያን ዘመናት እንደ 7 መቅረዞች አየ፤ ነገር ግን በመካከለኛው መቅረዝ ውስጥ ብቻ ነው ኢየሱስን ያየው።
ይህም ማለት የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ብቻ ነው ሙሉው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይታወቅ የነበረው።
ራዕይ 1፡13 በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፥ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።
ታላቁ ሐዋርያ ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር አልተከራከረም። እንደ ሞተ ሰው ሆኖ ወደቀ። ኢየሱስ ቃሉ ነው። ከቃሉ ጋር በፍጹም አትከራከሩ ወይም ልትለውጡት አትሞክሩ።
ራዕይ 1፡17 ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ
የመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ከመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ጋር አንድ ዓይነት መሆን አለበት።
በመከር ጊዜ የሚታጨደው ዘር መጀመሪያ ከተዘራው ዘር ጋር አንድ ዓይነት ነው።
የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የነበረው ብርታት እና ኃይል ሐዋርያት የጻፉት እውነት ነው።
በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ጳውሎስ የአሕዛብ መልእክተኛ ሆነ። ጳውሎስ ቤተክርስቲያን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበረች ማየት የሚችል ዓይነ ነበረው፤ ስለዚህ አማኞችን በትክክለኛው መንገድ ለመምራት ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ግማሹን የጻፈው እርሱ ነው።
ራዕይ 1፡18 ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።
የቤተክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ።
ቤተክርስቲያን የሕይወትን ቃል ዘር ከአዲስ ኪዳን ሐዋርያት ተቀበለች። ከዚያ በኋላ በ325 ዓ.ም የኒቅያ ጉባኤ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቀውን “ስላሴ” የሚባል ቃል ወደ ቤተክርስቲያን በማስገባት እውነተን መግደል ጀመሩ። ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ የስሕተት ትምሕርቶች ወደ ቤተክርስቲያን ገቡና በስተመጨረሻ በጨለማ ዘመን ውስጥ እውነት ሞተች። ነገር ግን የተሃድሶው ዘመን ቅጠሎች ለምልመው እንደ አበባ አበቡና የወንጌል ስርጭት ዘመን ወንጌልን ወደ ዓለም ሁሉ አዳረሰ። ቀጥሎ የጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ ዘር ሲበቅል ሐዋርያት በመጀመሪያው ዘመን ያምኑ የነበሩትን እውነቶች እና የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መልሶ ወደ ቤተክርስቲያን ያመጣ ዘንድ ለዊልያም ብራንሐም በር ከፈተለት።
የመጨረሻው ዘመን ላይ ዝግጁ የሆነችዋ ሙሽራ ለኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ አክብሮት አላት፤ ፍጹም ስሕተት የሌለው ትክክለኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ትቀበላለች።
መንፈስ ቅዱስ በ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ እንዴት እራሱን እንደገለጠ ለማየት 7ቱን ቀንዶች እና 7ቱን ዓይኖች እንመልከት።
ይህች በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን የነበረችዋ የመጀመሪያዋ የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ናት።
እግዚአብሔር ቤተክርስያንን እራሱ በሚፈልገው መንገድ ተከላት።
በመጨረሻው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን መጀመሪያ ሲተክላት እንደነበረችው ሆና ሊያገኛት ይፈልጋል።
የዚህች ቤተክርስቲያን ቀንድ ወይም ኃይሏ አማኞች ለእግዚአብሔር ቃል የነበራቸው ፍቅር ነው።
የእግዚአብሔር ዓይን ማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ነው፤ እርሱም በእግዚአብሔር እውነት ውስጥ እጅግ የተለቀ መረዳት ነበረው፤ በተጨማሪም እጅግ ብርቱ ሰው ስለነበረ ከሰይጣን የተሰነዘረበትነ ብዙ ዱላ ምንም ሳይነጫነጭ በትዕግስት ችሎ አልፏል።
በሁለተኛ የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ሰዎች በቤተክርስቲያን ላይ ገዥ ሲሆኑ እውነት ከቤተክርስቲያን ቀስ በቀስ ወጥታ ጠፋች።
ሌላው የእግዚአብሔር ዓይን ደግሞ አይሬንየስ ነው፤ እርሱም ሊዮንስ በተባለች የፈረንሳይ ከተማ ውስጥ ሐዋርያት ያስተማሩት እውነት ሳይጠፋ እንዲቆይ አድርጓል።
የእግዚአብሔር ቀንድ ወይም ኃይል በአረማዊው የሮማ መንግስት አማካኝነት ቤተክርስቲያን ድሃ ሆና እንድትቆይ ወይም እንድትሰደድ ማድረግ ነበረ። ሲበታተኑ እና ከስደት ሲሸሹ ወንጌልን በየስፍራው መስበክ ቻሉ፤ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ አንድ ሰው ገዥ ከሚሆንበት የስሕተት አሰራር ተጠብቀዋል።
በሶስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በ325 ዓ.ም የኒቅያ ጉባኤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለውን “ስላሴ” የተባለ ቃል በግዴታ ቤተክርስቲያን ላይ ጫነ። እውነት ሞተች።
የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቃዋሚዎቿን ማሳደድ ጀመረች።
የእግዚአብሔር ኃይል የተገለጠው አማኞችን ጠንካራ በማድረግ ነው። መከራን ታግሰው ብዙዎቹ ሞቱ። አልፎ አልፎ ትልቅ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል ይገለጥ ነበረ።
የእግዚአብሔር ዓይን ቱርስ በተባለች የፈረንሳይ ከተማ ውስጥ ማርቲን። ቤተክርስቲያኖች ሰው ሰራሽ አስተምሕሮዎችን ተከትለው በወደቁበት ሰዓት ማርቲን ሐዋርያዊ አስተምሕሮዎች ላይ ትኩረት አደረገ።
አራተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የጨለማው ዘመን ነው። በዚያ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ተከለከለ። አጉል እምነቶች ተስፋፉ።
የእግዚአብሔር ቀንድ ብዙ እንክብካቤ የማያስፈልጋቸው ብርቱ ሰዎችን ማስነሳት ነበር። ብዙዎች እያረጀች በመጣችዋ የሮማ መንግስት ዳርቻ ላይ ይኖሩ ነበር። ሌሎች ወደ አልፕስ ተራሮች ምድረበዳ ሸሹ። እውነት ሳትጠፋ እንድትቆይ ለመጠበቅ እግዚአብሔር የገዳሞችን ፈታኝና አስቸጋሪ ሕይወት ተጠቀመ።
ለ1,000 ዓመታት ያለማቋረጥ ሞትን በየዕለቱ ሲጋፈጡ በመኖር ሁልጊዜ በኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነት እየኖሩ እምነታቸውን ጠብቀው ሞቱ።
እነዚህ አማኞች በሁሉ አቅጣጫ ተስፋ በሌለበት ሰዓት እንኳ እጅ አንሰጥም በማለት ጸንተው ቆሙ።
የእግዚአብሔር ዓይን አየርላንዳዊው ኮሉምባ ነበረ፤ እርሱም በአየርላንድ እንዲሁም ከስኮትላንድ ምዕራባዊ ጠረፍ ራቅ ብላ በምትገኘው ሀይ ወይም አዮና ይኖር ነበር።
ኮሉምባ እውነትን በእስኮትላንድ ጎሳዎች መካከል አሰራጨ።
ኮሉምባ ከሞተ በኋላ እውነት በጨለማው ዘመን ውስጥ ሞተች።
ቤተክርስቲያንም በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ከነበረው እውነት እየራቀች ሄደች።
ቤተክርስቲያን ወደ አዲስ ኪዳን ትምሕርትና ምሳሌ መመለስ ጀመረች።
ይህም ወደ እውነት የመመለስ ጉዞ የተጀመረው ጀርመኒ ውስጥ በ1520 ማርቲን ሉተር በጀመረው ተሃድሶ ነው።
በ5ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የእግዚአብሔር ቀንድ የማርቲን ሉተር አስደናቂ ድፍረትና ቆራጥነት ነበር፤ ማርቲን ሉተር ከካቶሊክ ቤተክስቲያን ልማዶች ይልቅ ለመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ቦታ ልንሰጥ ይገባናል ብሎ ተከራከረ። የሕትመት ማሽን በተፈጠረ ጊዜ የጻፋቸው በራሪ ወረቀቶች በፍጥነት በመሰራጨታቸው የሉተር ትምሕርቶች በስፋት ሊዳረሱ ችለዋል። ሉተር ያነደደውን እሳት ፖፑ ሊያጠፋው አልቻለም፤ ስለዚህ ሰዎች በክርስቶስ ብቻ በማመን እየዳኑ ሲሄዱ ተሃድሶው በብዙ ሃገሮች ተሰራጨ።
ማርቲን ሉተር የእግዚአብሔር ዓይን ነበረ፤ ስለዚህ ጽድቅ በስራ ሳይሆን በእምነት ብቻ መሆኑን ማየት ችሏል።
በ6ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የእግዚአብሔር ቀንድ ጆን ዌስሊ ነበረ፤ እርሱም መዳን በእምነት ብቻ ነው ብሎ እያስተማረ የመዳን ውጤት ደግሞ በቅድስና የመኖር መልካም ስራ መሆኑን ሳይታክት አስተማረ። የብዙ ሰዎች ሕሊና ተነቃቅቶ ሰዎች የቅድስና ሕይወት ለመኖር ተነሳሱ። በቅድስና መኖር ለቤተክርስቲያን ትልቅ ብርታት ሰጣት፤ ከዚህም የተነሳ ሰዎች በቁጥር በዝተው የቤተክርስቲያናቸውን አዳራሽ ሞልተው ሲተርፉ በታላቁ የወንጌል ስርጭት ዘመን መዳንን እና በቅድስና መመላለስን በዓለም ሁሉ ላይ አስፋፉ።
ጆን ዌስሊ የእግዚአብሔር ዓይን ነበረ፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያን ከፖለቲካ መራቅ እንዳለባት አይቶ እንግሊዝ የፈረንሳይን አብዮት ከመኮረጅ እንድትተርፍ አደረገ። ዊልያም ዊልበር ፎርስ በወንጌል ከዳነ በኋላ ዕድሜውን ሁሉ ባርነትን ለማጥፋት ሲታገል ኖረ። ሰዎች በከፍተኛ የስነ ምግባር ስርዓት ይኖሩ ስለነበረ ሰይጣን እንደ ልቡ መስራት አልቻለም።
በእንፋሎት ኃይል የሚሰሩ ሞተሮች ሲፈጠሩ በዚያው የባቡር መንገዶችም ተዘረጉ፤ ይህም የብዙ ሃገሮች ውስጠኛ ክፍሎች ለወንጌል ሰባኪዎች ተደራሽ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ አድርጓልቨ በእንፋሎት ኃይል የሚሰሩ መርከቦች የወንጌል ሰባኪዎችን ወደ እሩቅ ሃገሮች ሁሉ አደረሷቸው።
ያ ዘመን የወንድማማች መዋደድ ዘመን ነበረ፤ ይህም ከሁሉ ይበልጥ ብርቱ የሆነ ቀንድ ወይም ኃይ ነው፤ ስለዚህ ወንጌል ሰባኪዎች በሌሎች በሩቅ ሃገሮች የሚኖሩ ሰዎችን እንደ ወንድሞቻቸው በመቁጠር የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ማዳን ይካፈሉ ዘንድ ሄደው የወንጌሉን መሰከሩላቸው።
የ7ኛው ቤተክርስቲያን ዘመን ቀንድ የእግዚአብሔር ቃል ፍቅር እና የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት ሲገለጡ በመስማት የሚገኘው ታላቅ ደስታ ነው። የሙሽራይቱ አካላት ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን ከየትኛዋም ቤተክርስቲያን ወይም የቤተክርስቲያን መሪ የበለጠ ያከብራሉ። ትልቁ ፍላጎታቸው የቤተክርስቲያኖችን ስሕተት ትተው እውነትን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደተናገረ መረዳት ነው። ትምሕርታቸው ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ የሚፈልጉት ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፤ ይህንንም የሚያደርጉት ወሳኝ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እርስ በርሳቸው አገናኝተው በማየት ነው።
እግዚአብሔር ኢንተርኔትን ይጠቀማል ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የሚያብራሩ ዌብሳይቶች በዓለም ዙርያ ሁሉ ደርሰው ይታያሉ። ከእንግዲህ ማንም ቢሆን በቤተክርስቲያን መሪው አስተምሕሮ ተገድቦ ሊቀር አይችልም።
በዚህ በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የእግዚአብሔር ዓይን የነበረው ሰው ዊልያም ብራንሐም ነው፤ እርሱም የቤተክርስቲያን መሪዎች ግራ የተጋቡባቸውን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት በመግለጥ ከ1,000 በላይ ስብከቶችን በድምጽ ቀድቶ አስቀምጧል። ዊልያም ብራንሐም ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መመራት አስፈላጊ መሆኑን ተረድቷል። የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ከነበሩ አማኞች ጋር እምነታችን አንድ ዓይነት እንዲሆን የመጽፍ ቅዱስ ሚስጥራትን መረዳት እንዳለብን በአጽንኦት ይናገር ነበር።
ዛሬ ትልቁ አሳሳቢ ነገር የመጽሐፍ ቅዱን ሚስጥራት መገለጥ ለሕዝብ ሁሉ ማሰራጨት ነው።
የንስሩ ዓይን መጽሐፍ ቅዱስ መናገር የፈለገውን ሚስጥር አጥርቶ ማየት ይችላል። እየመጣ ካለው ታላቅ መከራ ሊያድነን የሚችለው እውነትን መረዳት ብቻ ነው።
63-0630 ሶስተኛው ፍልሰት
የእግዚአብሔር ድምጽ በቃሉ ውስጥ ሲጠራቸው በደምብ መስማት ይችላሉ።
… ዛሬ በዚህ ዘመን የሚራችሁ የእግዚአብሔር ድምጽ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በደምብ አድምጡ።
64-0823 ጥያቄዎችና መልሶች - 1
ቃሉን በሙላት የሚቀበሉት ሰዎች የሚያቀበሉት መጽሐፍ ቅዱስ እራሱ ስለተናገረ እንጂ እኔ ስለሰበክሁ አይደለም። የሚቀበሉ ሁሉ ለመቀበል ነጻ ናቸው ምክንያቱም ቃሉ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል።