ሰዎች በክርስቶስ ቦታ የቤተክርስቲያን ራስ ሆነው ተሾሙ



ፓስተሮች ብዙውን ጊዜ ከሰው ንግግር በተወሰደ ጥቅስ ጉባኤያቸውን ይቆጣጠራሉ። ይህ ግን እውነት ነውን?

First published on the 25th of May 2022 — Last updated on the 25th of May 2022

እውነት የሚረጋገጠው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምስክር የሚሆን ጥቅስ በማምጣት ነው

 

ፓስተሮች ብዙ ጊዜ በሰው ንግግር ጥቅስ ወይም ለዚህ ጥቅስ በሚሰጡት ትርጓሜ ቤተክርስቲያኖቻቸውን ይቆጣጠራሉ። ይህ ግን እውነት ነውን?

56-0902 ግድግዳው ላያ ያለው የእጅ ጽሕፈት

እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ሥራውን መስራት የጀመረ ጊዜ አሕዛብ በትዕቢት ተሞልተው ሕዝብ ሁሉ የአንድን ቅዱስ ሰው ምስል እንዲያመልኩ ማስገደዳቸውን እንድታስተውሉ እፈልጋለሁ።

የአሕዛብ ዘመን የተጀመረው በዚያ መልክ ነው፤ በመጨረሻው እንደዚያው ነው የሚጠናቀቀው።

ባቢሎን ሰዎች ሁሉ ለዳንኤል ምስል እንዲሰግዱ አስገደደች፤ ዳንኤል ቅዱስ ሰው ነበረ።

ሐዋርያው ዮሐንስ ራዕዮቹን የገለጠለት ነብይ እግር ስር ሊሰግድ ተደፋ።

ራዕይ 19፡10 ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ።

አስቀድሞ እንዳያደርገው ተነግሮት ነበረ ነገር ግን ወዲያ በድጋሚ ተመሳሳይ ስሕተት ሰራ።

ራዕይ 22፡8 ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ። በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ።

9 እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ።

በዘመን መጨረሻ ሰዎች ወንድም ብራንሐምን የእግዚአብሔር ድምጽ ነው፣ የሰው ልጅ እርሱ ነው ብለው እንዲያመልኩ የሚያስገድድ መንፈስ ተለቋል። እርሱ ፍጹም ነው፤ አይሳሳትም ይላሉ።

ይህ መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ምዕራፍ ውስጥ ተገልጧል። እኛም በዘመን መጨረሻ ላይ ነው የምንገኘው፤ ስለዚህ ወደዚህ ወጥመድ ውስጥ እንዳትወድቁ።

የወንድም ብራንሐም ንግግር ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስን ሊገልጡ ይችላሉ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ሊተኩ አይችሉም።

ወንድም ብራንሐም ከተናገራቸው ንግግሮች የተወሰኑቱ እርስ በርሳቸው ይጋጫሉ።

ስለዚህ የትኛው ንግግሩ ትክክል መሆኑን በምን ታውቃላችሁ?

የትኛው ንግግሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚስማማ በመፈተሽ ብቻ ነው ማወቅ የሚቻለው።

ለምሳሌ፡-

“የዳንኤል ሰባተኛ ሱባኤ” ኦገስት 6 ቀን 1961

መሲሁ ኢየሱስ በሆሳዕና ዕለት ነጭ በቅሎ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በድል ገባ፤ የገባበት ቀን አፕሪል 2 ቀን 30 ዓ.ም ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው የሆሳዕና ዕለት በ30 ዓ.ም ነው።

 

ኢየሱስ በዚያ ሳምንት መጨረሻ አካባቢ ሐሙስ ዕለት ነው የተሰቀለው።

ዘጸአት 12፡3 ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም፦ በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ።

6 በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት።

ዘጸአት ምዕራፍ 12 ውስጥ በተጻፈው መሰረት የፋሲካ በግ በ10ኛው ቀን ተመርጦ በ14ኛው ቀን ነው የሚታረደው።

ኢየሱስ የተመረጠው የሆሳዕና ዕለት እሑድ ነው፤ ያም ዕለት ከወሩ 10ኛው ቀን ነበረ። ስለዚህ የሚገደለው በ14ኛ ቀን ማለትም ሐሙስ ነው። ሐሙስ ከተገደለ ብቻ ነው መቃብር ውስጥ ሶስት ሌሊት ቆይቶ እሑድ ጠዋት ሊነሳ የሚችለው።

ሶስቱ ሌሊቶች ሐሙስ ሌሊት፣ አርብ ሌሊት፣ እና ቅዳሜ ሌሊት ናቸው።

ማቴዎስ 12፡40 ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።

 

“የማይገለጥ ድምጽ” ጁላይ 14 ቀን 1962

የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው ኢየሩሳሌም ውስጥ በ33 ዓ.ም የበዓለ ሃምሳ ዕለት ነው።

እኛም መመለስ ያለብን ወደዚያ ቀን ነው። እኔ ወደዚያ ልመለስ እየሞከርኩ ነኝ። ነገር ግን ሰዎች ወደ መጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ትክክለኛ እምነት ሊመለሱ ሲሞክሩ እንዳይመለሱ የሚገዳደራቸው የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ይታያችኋልን?

 

በዓለ ሃምሳ ከትንሳኤ 50 ቀናት በኋላ ነው።

ኢየሱስ የተሰቀለው በ30 ዓ.ም ነው ወይስ በ33? አንዱን ጥቅስ ከተቀበላችሁ ሌላኛውን መጣል ያስፈልጋችኋል።

ይህንን ጉዳይ ለመፍታት ቀኖቹን በመጽሐፍ ቅዱስ መመርመር ያስፈልጋችኋል። ከነዚህ ቀናት አንዱ ብቻ ነው ተፈትኖ የሚያልፈው።

ትክክለኛው ቀን 33 ዓ.ም ነው ምክንያቱም ኢየሱስ በ29 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ሲጠመቅ ዕድሜው 30 ዓመት ነበረ፤ አገልግሎቱም ከዳንኤል 70ኛ ሱባኤ የመጀመሪያ አጋማሽ ጋር ይገጥም ዘንድ ለ3.5 ዓመታት ነው የዘለቀው።

ሉቃስ 3፡21 ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥

23 ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር

ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንይ፡-

“ይህ መልከጼዴቅ ማነው?” ፌብሩዋሪ 21 ቀን 1965

ሙሴ የተባለ ነብይ ነበረ። እግዚአብሔር አንድ ቀን ጠራውና ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ከለከለው፤ ከዚያም ሙሴ በዓለት ላይ ሞተ። መላእክትም ወሰዱትና ቀበሩት።

ሌላ ሰው ደግሞ ነበረ፤ ይህኛው ሰው ንስር ነው፤ መሞትም አላስፈለገውም። ይህኛው ሰው ዮርዳኖስ ወንዝ ላይ ተዳምዶ አለፈና እግዚአብሔረ ከሰማይ ሰረገላ ላለከለት፤ እርሱም የስጋውን ልብስ አውልቆ ዘላለማዊውን ሽልማቱን ሊቀበል ወደ ሰማይ ተነጠቀ።

ከስምነት መቶ ዓመታት በኋላ፤ ከስምነት መቶ ዓመታት በኋላ በመገለጥ ተራራ ላይ እነዚያ ሁለት ሰዎች ቆሙ። የሙሴ ስጋ ለብዙ መቶ ዓመታት በስብሷል ግን በመገለጥ ተራራ ላይ ሲታይ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ እና ዮሐንስ እስኪያውቁት ድረስ በንጹህ አካል ነበር የተገለጠው።

 

ጥያቄዎችና መልሶች በዕብራውያን 3 ላይ ኦከቶበር 6 ቀን 1957

ሙሴ እንኳ በጭራሽ … አይ ስጋው አልተገኘም። መላእክት ወስደውታል፤ ስጋው አልፈረሰም፤ አልበሰበሰም።

ሙሴ ፍጹሙ የክርስቶስ ጥላ ነበረ። ሙሴ ሲሞት ስጋውን መላእከት ወሰዱት፤ ስለዚህ ሰይጣን እንኳ ሙሴ የት እንደተቀበረ አያውቅም፤ ሰይጣን ከመላእከት አለቃ ሚካኤል ጋር ስለ ሙሴ ቀብር ሊከራከር ሞክሮ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ይነግረናል። እግዚአብሔር በንጥቀት ወደ ሰማይ ወስዶታል።

 

የሙሴ ስጋ በስብሶ ይሁን አይሁን ከሰው ንግግር ጥቅስ ወስደን ብቻ ልናረጋግጥ አንችልም።

ስለዚህ የሰው ጥቅሶች ብቻቸውን የእውነት ቁልፍ አይሆኑም።

አንዳንድ የሰው ጥቅሶች ስሕተት አለባቸው።

የሰው ንግግር ጥቅሶችን ሳትመረምሩ የምትቀበሉ ከሆነ የእባቡ ዘር የሚለው መልእክት መጀመሪያ አካባቢ አምስት የተሳሳቱ ዓረፍተ ነገሮች ስለምታገኙ ችግር ውስጥ ትገባላችሁ።

የተስተካከሉት ዓረፍተ ነገሮች በአራት ማዕዘን ቅንፍ [] ውስጥ ተቀምጠዋል።

 

“የእባቡ ዘር” ሴፕቴምበር 28 ቀን 1958

የመጀመሪያዋ ዲኖሚኔሽናዊ ቤተክርስቲያን … ዛሬ ከሰዓት በኋላ በነበረን ፕሮግራም “የኒቅያ አባቶች” የተባሉትን ሰዎች በኒቅያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተመልክተናል። ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የኒቅያ አባቶች መጡ፤ እነርሱም ከሶስት መቶ ሃያ አምስት ዓ.ም በኋላ ወደ ኒቅያ ፈረንሳይ መጡ [ኒቅያ በታናሹ እስያ ውስጥ ከጴርጋሞን በስተ ሰሜን የምትገኝ ከተማ ናት] በዚያም ታላቁን የኒቅያ ጉባኤ አደረጉ። በዚያ ጉባኤ ከተሰበሰቡ በኋላ ብዙ ሐይማኖታዊ መግለጫዎችን አጸደቁ፤ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እስከ ዛሬ ድረስ የዛኔ ያጸደቁትን የሐይማኖት መግለጫ ነው የምትከተለው፤ ፕሮቴስታንቶችም ይህንኑ ተቀብለዋል።

ዛሬ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ሳስተምር እንደተናገርኩት እስከ ተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን ዘመን ድረስ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመን [የተሰሎንቄ የቤተክርስቲያን ዘመን የሚባል የለም። የትያጥሮን ቤተክርስቲያን ዘመን ሲጠናቀቅ የጨለማው ዘመን ያበቃው የዛኔ ነው] አንድ ሺ አምስት መቶ ዓመታት የፈጀው የጨለማው ዘመን [የጨለማው ዘመን የቆየው ለ1,200 ዓመታት ያህል ነው። የጨለማው ዘመን በኒቅያ ጉባኤ በ325 ዓ.ም አካባቢ ተጀመረ፤ የጨለማው ዘመን የጀመረው ሰላሴ የሚባል ትምሕርት ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ እውነትን ሲጋርድ ነው፤ የጨለማው ዘመን የተጠናቀቀው ጀርመኒ ውስጥ በ1520 ዓ.ም ፖፑን ያወገዘ ጊዜ ነው] የዛኔ ጌታ የተናገረው “እስካሁን ስሜን አልካድክም” ብሎ ነው።

[በሁለተኛው ዘመን ማለትም በሰምርኔስ ቤተክርስቲያን ዘመን “ስም” አልተጠቀሰም]

ከዚያ ጊዜ ወዲህ እንደ ካቶሊክ፣ ሉተራን፣ ዌስሊ፣ ባፕቲስት፣ ፕሬስቢተሪያን፣ ፔንቲኮስታል እና ሌሎችንም ዲኖሚኔሽናዊ ስሞች ይዘው የተነሱ ቤተክርስቲያኖች በክርስቶስ አይደሉም። ነገር ግን ልክ ከዘመኑ መጠናቀቅ በፊት እንዲህ ብሎ ተናገረ፡- “በፊትህ የተከፈተ በር ሰጥቼሃለው”። አያችሁ? አሁን የምንኖርበት ዘመን ያ የተከፈተ በር ያለበት ዘመን ነው፤ ማለትም የመጨረሻዋ የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን የምትወጣበት የተከፈተ በር ነው።

እስከ ሎዶቅያውያን ጉባኤ ድረስ ያፉት ዓመታት ሶስት መቶ ሃያ አምስት ናቸው።

[ሎዶቅያ ሳይሆን የኒቅያ ጉባኤ ነው በ325 ዓ.ም የተደረገው]

 

የሎዶቅያ ጉባኤ ተደርጎ ነበረ ነገር ግን የተደረገው ከ363-364 ዓ.ም ነው። ይህ ጉባኤ ሰንበት ከቅዳሜ ወደ እሑድ እንዲለወጥ አድርጓል፤ በተጨማሪ ደግሞ የዮሐንስ ራዕይ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲወጣ አድርጓል። ይህን ያደረገው በዋነኝነት የዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 17 የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ስለሚያጋልጥ ነው።

“የዳንኤል ሰባተኛ ሱባኤ” ኦገስት 6 ቀን 1961

… ከዚያ በኋላ ድርጅት መመስረት የሚፈልጉት ኒቆላውያን መጡ። የከበሩ ታላላቅ ሰዎች ወደ ድርጅቱ ገቡ። ይህም የሆነው የኒቅያ ጉባኤ ባደረጉ ጊዜ ኒቅያ ሮም ውስጥ ነው። በዚያ ጉባኤ ምን አደረጉ? ቤተክርስቲያንን በደምብ አድርገው አደራጁዋትና ከዚያ በኋላ ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖችን ማሳደድ ጀመረች። በቀጣዩ የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የሆነው ክርስትና ሙሉ በሙሉ ጠፋ።

 

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ወንድም ብራንሐም ኒቅያ ሮም ብሎ ይናገራል። ምን ማለቱ ነው?

ኒቅያ ትንሹ እስያ ውስጥ የምትገኝ ከተማ ናት እንጂ ሮም ውስጥ አይደለችም።

ነገር ግን ንጉስ ኮንስታንቲን የኒቅያን ጉባኤ በመጠቀም ፖለቲካዊ ስልጣን ወደ ሮም ጳጳስ ወደ ሲልቬስተር እንዲተላለፍ አድርጓል። ይህንን ያደረገው የሮማ መንግስት ምክር ቤት አባላትን ለመቋቋም ፈልጎ ነው፤ ምክንያቱም እነርሱ በብዛት አረማውያን ሲሆኑ ኮንስታንቲንን የማስወገድ ፍላጎትም ነበራቸው። ኮንስታንቲን ክርስቲያን ነኝ በማለት የቤተክርስቲያንን አመራር በራሱ እጅ አደረገ። አረማውያን የምክር ቤት አባላትን ከመታገል ይልቅ ቤተክርስቲያንን መቆጣጠር ፈቃዱን ለመፈጸም እንደሚያመቸው አሰበ።

ኮንስታንቲን ለሮማ ጳጳስ የላተራንን ቤተመንግስት በስጦታ አበርክቶለት ነበር፤ የላተራን ቤተመንግስት አውሮፓ ውስጥ ከነበሩ ቤተመንግስቶች ሁሉ በውበት አንደኛ ነበረ። በዚህ ላይ ጨምሮ የብዙ ገንዘብ ስጦታም ሰጥቶታል። ይህም ስጦታ ለሮም ጳጳስ ትልቅ ክብርና ተሰሚነትን አጎናጽፎታል። ንጉሱም አዲቷን ከተማ ኮንስታንቲኖፕልን ለመገንባት ወደ ምስራቅ በሄደ ጊዜ የሮም ጳጳስ በምዕራብ በኩሉ ለንጉሱ ጠንካራ ደጀን ሆኖለታል።

ክርስትናን በመቀበል ኮንስታንቲን የአረማውያን ቤተመቅደሶች ውስጥ የነበሩትን ሃብቶች ሁሉ መውረስ ቻለ። ቤተክርስቲያን ከዚያ በፊት 10 ከባድ ስደቶች ውስጥ አልፋ ስለነበረ ምንም ሕንጻ አልነበራትም። ክርስቲያኖች ሲሰደዱ እና ሲጨቆኑ ነበር ያሳለፉት። ኮንስታንቲን ለክርስቲያኖች ስደትን በማስቆም እና ሃብት በመስጠት የእርሱ ደጋፊዎች እንዲሆኑ አደረገ። ከዚያ ወዲያ ወደ ቤተክርስቲያን ሕንጻ ለውጠው ይጠቀሙባቸው ዘንድ የአረማውያንን ቤተመቅደሶች ስለሰጣቸው ቤተክርስቲያንን እንደ ልቡ መቆጣጠር ቻለ።

የኒቅያ ጉባኤ ፖለቲካዊውን ንጉስ የበላይ ጠባቂ በማድረግ በቤተክርስቲያን እና በመንግስት መካከል ጋብቻ አደረገ። ቤተክርስቲያን ውስጥ ሹመትና እድገት ማግኘት በፖለቲካ በኩል ትክክለኛነትን የሚጠይቅ ነገር ሆነ። ኮንስታንቲን ለጳጳሳቱ የሐይማኖት መግለጫ ሰጣቸው፤ ከዚህም የተነሳ ጳጳሶቹ ስላሴ የቤተክርስቲያን ይፋዊ የእምነት አቋም ነው ብለው እንዲቀበሉ አስገደዳቸው። የባቢሎን ሚስጥራት ሮም ውስጥ በሚገኘው የላተራን ቤተመንግስት አማካኝነት ስር ሰደዱ። የሮም ጳጳስ የዓለም ሁሉ ቤተክርስቲያኖች ራስ የመሆን የስልጣን ጥም ስለነበረው የባቢሎን ሚስጥራት በእርሱ በኩል ተስፋፉ።

ስለዚህ “ኒቅያ ሮም” ብላችሁ እንደ ገደል ማሚቶ አትድገሙ፤ ምክንያቱም ይህ ምንም ትርጉም የሌለው ስያሜ ነው። ታሪክን መርምሩና ወንድም ብራንሐም ምን ሊያስተላልፍ እየሞከረ እንደነበር በትክክል ተረዱ።

ዛሬ በሜሴጅ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ በራስ መመካትና ራስን ማሞገስ በዝቷል፤ ነገር ግን መረጃዎችን መመርመርና ማጣራት ቀርቷል።

 

የሰው ንግግር ጥቅስ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ማለትም 2 ምስክር ያስፈልገናል

 

 

የሰው ንግግር ጥቅስ ምስክር መሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው። ስለዚህ ሁለት ምስክሮች ያስፈልጓችኋል።

ሁለት ምስክሮች ለማግኘት የሰው ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አመሳክራችሁ ማረጋገጥ አለባችሁ።

ደግሞም እውነትን ማግኘት ከፈለግን ጥቅሶችን ከታሪክም አንጻር መፈተሽና መመርመር አለብን።

ያለ ምንም ማስተዋል ጥቅሶችን ብቻ የምትደግሙ ከሆናችሁ ከገደል ማሚቶ ብዙም አትለዩም።

2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡2 ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም።

ዘዳግም 17፡6 በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ሞት የሚገባው ይገደል፤ በአንድ ምስክር አፍ አይገደል

ዘዳግም 19፡15 ስለ በደል ሁሉ፥ ክፉ በማድረግም ስለ ሠራት ኃጢአት ሁሉ በማንም ላይ አንድ ምስክር አይቁም፤ በሁለት ምስክሮች ወይም በሦስት ምስክሮች አፍ ነገር ሁሉ ይጸናል።

 

በተለይ ደግሞ ሁለት ጥቅሶች በአንድ ርዕስ ላይ የተለያየ ነገር ሲነግሩዋችሁ እውነትን ማረጋገጥ አትችሉም።

61-0808 ቤትህ

አሁን ደግሞ ታይተስ በ70 ዓ.ም የኢየሩሳሌምን ከተማ የከበበበትንና ቅጥሮቿን የፈራረሰበትን ጊዜ እንመለከታለን።

54-0515 ጥያቄዎችና መልሶች

ታይተስ በ96 ዓ.ም የኢየሩሳሌምን ቅጥር ከበበና ከተማይቱን አቃጠለ።

ሮማዊው ጀነራል ታይተስ ኢየሩሳሌምን ያፈራረሳት በ70 ዓ.ም ነው ወይስ በ90 ዓ.ም? ታሪክ የሚነግረን በ70 ዓ.ም እንደሆነ ነው።

በሌላ አነጋገር እውነትን ለማረጋገጥ ታሪክን እንደ ተጨማሪ ምስክር እንጠቀማለን ማለት ነው።

ጥቅሶች አንድ ሃሳብ ሊሰጡዋችሁ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሃሳቡ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መመርመር አስፈላጊ ነው።

62-0318 በድምጽ የተነገረው ቃል የመጀመሪያው ዘር ነው - 2

አሁን እነዚህ የተናገርኳቸው ነገሮች በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙ ከሆኑ ወይም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይገጥሙ ከሆኑ በሙሉ ስሕተት ናቸው።

65-0801 የዚህ ክፉ ዘመን አምላክ

ስለዚህ ጌታ ለዚህ ሰዓት የሰጠኝን መልእክት ያመኑ ሕዝብ ምን እየተደረገ እንዳለ ያውቁ ዘንድ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኙት ዘንድ ነው

63-1110 በእናንተ ውስጥ ያለው

መልእክቱን በሙሉ እመኑ። እመኑት። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካልተጻፈ ግን አትመኑት።

 

ይህም የ2,000 ዓመታቱን የወንጌል ብርሃን በ7 ልዩ ልዩ ዘመናት ከፋፍሎ “የቤተክርስቲያን ዘመናት” ብሎ ማጥናት ትክክል መሆኑን ያስረዳል።

ሌላ ጥላ እንይ።

የስንዴ ዘር ከተተከለ (በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን 12ቱ ሐዋርያት ተክለዋል) መጀመሪያ ይሞታል (በጨለማው ዘመን ውስጥ) ከዚያ በኋላ በተለያዩ ደረጃዎች እያደገ ይሄዳል። መጀመሪያ ቅጠል ያወጣል (የተሃድሶ መሪዎች)፤ ከዚያም አበባ ያብባል (ዓለም አቀፉ የወንጌል ስርጭት ዘመን)። ወደ መጨረሻው አካባቢ የመጀመሪያውን ዘር የሚመስል እሸት ይመጣል (ፔንቲኮስታሎች ኃይል በመግለጥ መልካም ነበሩ ነገር ግን በአዲስ ኪዳን የተገለጠውን የመጀመሪያ እውነት በከፊል አላገኙትም ነበር። የጌታ እራት ሲወስዱ ማታ ማታ አይወስዱም፤ እግር የማጠብ አገልግሎትን አያደርጉም። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ የጥንቷ ቤተክርስቲያን “ስላሴ” የሚል ቃል ተጠቅማ አታውቅም። ፔንቲኮስታሎች በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አያጠምቁም፤ ወዘተ.)።

በስተመጨረሻም የተተከለው የመጀመሪያው ዘር እሸት ሆኖ ይጀምርና በቅጠሉ ውስጥ ፀሃይ እያገኘ ለመታጨድ ይደርሳል።

የበቆሎን ዘር አስቡ።

በስተመጨረሻ በመከር የሚታጨደው የበቆሎ ዘር መጀመሪያ ከተዘራው ዘር ጋር አንድ ዓይነት ነው።

 

 

ስለዚህ ዛሬ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የምናገኛትን የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን ተመልክተን እንደ ሞዴላችን አይተን እምነታችንን እና አደራረጋችንን ወደ አዲስ ኪዳን መመለስ አለብን።

2ኛ ቆሮንቶስ 13፡1 ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ሁሉ ነገር በሁለትና በሦስት ምስክር አፍ ይጸናል።

 

የሰው ንግግር ጥቅስ ሰምታችሁ ዝም አትበሉ። የእግዚአብሔር ቃል እና በፍጥረት ውስጥ የሚገኙ ጥላዎች ይደግፉት እንደሆን አረጋግጡ።

 

 

የአጥቢያ ሽማግሌዎች የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ናቸው

 

 

በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከአጥቢያይቱ ሽማግሌ በላይ በስልጣን የሚበልጥ ሰው ካለ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ።

ይህ ከወንድም ብራንሐም ንግግር የተወሰደ ጥቅስ ነው።

ሐዋርያው ያዕቆብ በአሕዛብ አማኞች ላይ የጫነባቸው መመሪያ በጣም ጥቂት መሆኑን ልብ በሉ።

የሐዋርያት ሥራ 15፡13 እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ ወንድሞች ሆይ፥ ስሙኝ።

14 እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል።

20 ነገር ግን ከጣዖት ርኵሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቈርጣለሁ።

 

ቲቶ 1፡5 ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤

 

የጥንቷ ቤተክርስቲያን በየስፍራው ሁሉ እየሰበኩና እያስተማሩ በዞሩ ሰዎች አማካኝነት እውነትን ለብዙዎች አድርሳለች።

በዚያ ዘመን አማኞች እውነተን ከሐዋርያት ሰሙ፤ ነገር ግን ሐዋርያት ሕዝቡ ላይ ጌታ አልሆኑባቸውም። ሐዋርያት በአንድ ቦታ ብዙ ተቀምጠው አያውቁም፤ ደግሞም ብዙዎቹ ተገደሉ። አንዳንድ ሐዋርያት ወደ ሩቅ ቦታ ሄዱ። ቶማስ ወደ ሕንድ ሄዶ ነበር፤ በዚያም ተገደለ።

በየአጥቢያው ጉባኤውን ይመሩ የነበሩት የአጥቢያው ሽማግሌዎች ናቸው።

ይህንን አሰራር ዛሬም ልንከተል ይገባናል።

“ዕብራውያን ምዕራፍ አምስት እና ስድስት” ሴፕቴምበር 8 ቀን 1957

የአጥቢያ ጉባኤ ሙሉ ስልጣን አለው ብዬ አምናለሁ።

አዎ። እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን ነጻ ሆና ራሷን ታስተዳድር፤ የራሷ ፓስተሮች፣ የራሷን ዲያቆናት፣ የራሷን አገልጋዮች እየመረጠች ትሹም። በዚህ መንገድ ከተንቀሳቀሰች በውስጧ ያሉ ሰዎች በላያቸው ጳጳስ አይነግስባቸውም

ለዚያች ቤተክርስቲያን መንፈስ ቅዱስ እራሱ ሲፈልግ ይናገራታል እንጂ ይህን ወይም ያን ማድረግ ይችሉ እንደሆን ማንንም መጠየቅ አያስፈልጋቸውም

እያንዳንዱ ሰው በግሉ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ይገናኛል።

በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከአጥቢያዋ ሽማግሌ የሚበልጥ ማን እንዳለ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ።

እውነቴን ነው ወገኖች፤ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ነጻ መሆን አለባት፤ እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን ራሷን ታስተዳድር። ወንድማማችነት መልካም ነው። ቤተክርስቲያኖች ሁሉ በወንድማማችነት መንፈስ መተያየትና መደጋገፍ አለባቸው። ሆኖም ግን አጥቢያ ቤተክርስቲያን ራሷን በራሷ ማስተዳደር አለባት።

 

“ዕብራውያን ምዕራፍ ሰባት” ሴፕቴምበር 22 ቀን 1957

መላው ጉባኤ በአንድነት ሙሉ ስልጣን አለው።

ደግሞ … በዚህች ቤተክርስቲያን ውስጥ የዲያቆናት ቦርድ የፖሊስ ዓይነት ሥራ ነው የሚሰራው፤ ስርዓት ያስጠብቃል።

ደምብ ማርቀቅ ላይ ግን ቤተክርስቲያኒቱ በሙሉ ትሳተፋለች። ይህች ቤተክርስቲያን በአጥቢያ ቤተክርስቲያን ሉዓላዊነት ላይ ነው የተመሰረተችው።

ስለዚህ ይህንን ፓስተር በመሾምም ሆነ ያኛውን በማስገባት ላይ ምንም የግል መብት የለኝም። ንብረቱ የእኔ ነበር፤ ነገር ግን ለቤተክርስቲያን ተሰጥቷል።

ሁላችሁ በአንድነት ቤተክስቲያን ናችሁ። የቤተክርስቲያንን ጉዳይ የምትቆጣጠሩ እናንተው ናችሁ።

እናንተ ራሳችሁ ቤተክርስቲያን ናችሁ።

ጉባኤው ድምጽ ከሰጠ እና “ይቅር በሉት፤ በአገልግሎቱ ይቀጥል” ካለ እንደዚያው ነው የሚሆነው። አያችሁ? ቤተክርስቲያንን ለማስተዳደር ይህ ዓይነቱ አሰራር መልካም አይደለምን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ይህንኑ ነው።

እኛ ጳጳሳትና ተቆጣጣሪዎች፤ ይህንን ግባ ያንን ውጣ የሚሉ ብዙ ስልጣን የተሸከሙ ሰዎች የሉንም።

በዚህ ጉባኤ ውስጥ ከመንፈስ ቅዱስ በቀር ሌላ ማንም ስልጣን የለውም።

እርሱ ነው ሁሉን ነገር የሚያንቀሳቅሰው።

እኛም መንፈስ ቅዱስ የተናገረንን እንቀበለዋለን፤ ሕዝቡም በሙሉ በእርሱ ምሪት ይንቀሳቀሳል።

 

የሕዝቡ አጠቃላይ ፈቀድ ነው የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያመለክተው እንጂ የፓስተሩ የግል አመለካከት አይደለም።

ፓስተሮች ሁልጊዜም ቢሆን ጉባኤው ከእነርሱ ሃሳብ ጋር እንዲስማማ ጉባኤውን በግድ ያሳምኑታል። ይህም የፓስተሩ ፈቃድ እንጂ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። አዲስ ኪዳን ውስጥ ፓስተር ቤተክርስቲያንን እንደሚያስተዳድር ወይም እንደሚገዛ አንድም ጊዜ አልተጻፈም።

“ኩነኔ በውክልና” ኖቬምበር 13 ቀን 1960

ይህ ከመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሃሳብ አልነበረም። እንዳቸውንም ወደ አገልግሎት አልላካቸውም። እርሱ የላካቸው መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ለአገልግሎት እስኪቀባቸው ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲጠብቁ ነው። ነገር ግን ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ እንድትመራ ከማድረግ ይልቅ የስነ መለኮት ትምሕርት መቀላቀል ጳጳሳት፣ የአውራጃ አስተዳዳሪዎች እንዲፈለፈሉ አድርገው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትክክለኛ መሪ መንፈስ ቅዱስን ወደ ጎን ተወት አደረጉት

እነርሱ ግን ልክ ዶሮዎችን እንዳዳቀሉ፤ በቅሎንም እንዳዳቀሉ ሁሉንም ነገር አዳቀሉ …

 

“የጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ዘመን” ዲሴምበር 7 ቀን 1960

ማርቲን ሉተር የተነሳው ለእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ዕድል ለመስጠት ነው፤ ዌስሊ ወደ ጴንጤቆስጤ ሊያስገባት፤ ነገር ግን ሁላቸውም ተመልሰው ቤተክርስቲያንን በመሪዎች ስር ወደ ማደራጀት ወደ ኒቆላውያን ሃሳብ ሄዱ፤ ሌላውም ነገር ሁሉ …

 

ሰዎች ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን በድርጅት መልክ ማዋቀር ይፈልጋሉ።

ሁልጊዜም ቢሆን ድርጅት አዋቅረው አለቃ ሆነው መግዛትና ባዋቀሩት ድርጅት በኩል ገንዘብ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ።

በሩ ላይ የተለጠፈው ስም ክርስቲያን የሚል ነው። ከውስጥ የሚገኘው ስራ ግን ሽንገላ ነው።

 

“የጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ዘመን” የቤተክርስቲያን ዘመናት መጽሐፍ ምዕራፍ 5

ስለ ኤፌሶን ዘመን ሳስተምር ኒቆላውያን የሚለው ቃል ከሁለት የግሪክ ቃላት የመጣ መሆኑን እንዳብራራሁላችሁ ታስታውሳላችሁ ብዬ አምናለው፡ ኒቆ ማለት ማሸነፍ መግዛት ሲሆን ላዎ ማት ደግሞ ምዕመናን ማለት ነው።

ኒቆላውያን ማለት ምዕመናኑን መግዛት ማለት ነው።

ይህ ለምንድነው እንደ ክፉ ነገር የሚቆጠረው? ክፉ ተደርጎ የሚታየው እግዚአብሔር የራሱን ቤተክርስቲያን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች እጅ አሳልፎ ስላልሰጠ ነው።

እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን አደራ የሰጠው እግዚአብሔር ለሾማቸው፣ በመንፈስ ቅዱስ ለተሞሉ፣ ቃሉን በማድረግ ለሚኖሩ እና ሕዝቡንም የእግዚአብሔርን ቃል እየመገቡ ለሚመሩ ሰዎች ነው።

እግዚአብሔር ብዙሃኑ ሕዝብ በቅዱሳን ካሕናት ይመሩ ዘንድ ሕዝቡን በመደብ አልከፋፈለም።

መሪዎች ቅዱስ መሆን እንዳለባቸው እሙን ነው፤ ነገር ግን ጉባኤውም በሙሉ ቅዱስ መሆን አለበት።

በተጨማሪ ካሕናት ወይም አገልጋዮች በእግዚአብሔር እና በሕዝቡ መካከል ገብተው ሁለቱን ያቀራርቡ የሚል ቃሉ ውስጥ የትም ቦታ አልተጻፈም፤ ደግሞም ለእግዚአብሔር በሚያቀርቡትም አምልኮ በተለያየ ጎራ እንዲከፋፈሉ የሚል ትዕዛዝ የትም ቦታ አልተጻፈም። እግዚአብሔር ሁሉም ሰው በአንድነት እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት ይፈልጋል።

ኒቆላዊነት እነዚህን እወነቶች በማጥፋት አገልጋዮችን ከሕዝቡ ይነጥላል፤ መሪዎችንም አገልጋዮች ሳይሆኑ ጌቶች ያደርጋቸዋል።

ይህ አስተምሕሮ በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ በወጣ ደምብ ነው የተጀመረው። ችግሩ ያለው በሁለት ቃላት ውስጥ ነው፡- እነርሱም “ሽማግሌዎች” (ፕሬስቢተርስ) እና “ጠባቂዎች” (ቢሾፕስ) ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ በቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሽማግሌዎች እንዳሉ ቢያሳይም አንዳንዶች (ከእነርሱም መካከል ኢግናሺየስ አንዱ ነው) ቢሾፕ ወይም ጳጳስ ከፍ ያለ ከሽማግሌዎችም በላይ የሆነ ሥልጣን ያለው አገልጋይ ነው ብለው ማስተማር ጀመሩ

እውነታው ግን ምን መሰላችሁ፤ “ሽማግሌ” የሚለው ቃል ሰውየውን የሚያመለክት ሲሆን ቢሾፕ ወይም ጳጳስ የሚለው ቃል ግን የዚህኑ ሽማግሌ የአገልግሎት ክፍል ወይም ዘርፍ የሚያመለክት ቃል ነው።

ሽማግሌው ሰውየው ነው። ቢሾፕ የሰውየው የአገልግሎት ዘርፍ ነው።

“ሽማግሌ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሰውየው በጌታ ሆኖ ያሳለፋቸውን ዓመታት ብዛት ነው። የዚህ ቃል ትርጉሙ በፊትም ሁልጊዜም እንደዚሁ ነው።

ሰውየው ሽማግሌ የሆነው ስለተመረጠ ወይም ስለተቀባ አይደለም፤ ነገር ግን በጌታ ሆኖ ከሌሎች በላይ እድሜ የገፋ ስለሆነ ነው።

ይህ ሰው ከሌሎች ይልቅ የበሰለ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በደምብ የተማረ፣ ሊታመን የሚችል፣ ጀማሪ ወይም አዲስ ክርስቲያን ያልሆነ ነው፤ ልምድ ያለው እና በረጅም ዓመታት የክርስትና ሕይወቱ የተመሰከረለት ሰው ነው።

ነገር ግን ጳጳሳቱ የጳውሎስን መልእክቶች መከተል አቁመዋል፤ መልእክቱን ትተው ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ውስጥ ሽማግሌዎችን ከኤፌሶን ወደ ሚሊጢን ያስጠራበት ታሪክ ላይ ብቻ አተኮሩበት። ቁጥር 17 “ሽማግሌዎች” መጠራታቸውን ይናገርና እነዚሁ ሽማግሌዎች ደግሞ በቁጥር 28 ጠባቂዎች (ጳጳሳት) ተብለው መጠራታቸውን ያሳያል።

እነዚህ ጳጳሳት (ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተሞሉ እና የሥልጣን ጥማት እንደነበራቸው አያጠራጥርም) ጳውሎስ “ጠባቂዎች” ወይም ጳጳሳት ለሚለው ቃል የአንድ ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ብቻ ከሚለው ትርጉም የበለጠ ትርጉም ሰጥቷል ብለው በመከራከር የጳጳሳት ሥልጣን ከአንድ ቤተክርስቲያን የሚያልፍ ነው አሉ።

ስለዚህ በእነርሱ አስተሳሰብ ጳጳስ ማለት ከአንድ ቤተክርስቲያን አልፎ በብዙ አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች ላይ ስልጣን ያለው ሰው ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በታሪክ አይታወቅም፤ ሆኖም ግን እንደ ፖሊካርፕ ያለ አስተዋይ ሰው እንኳ ሳይቀር በዚህ የድርጅታዊነት አስተሳሰብ ተሳበ።

ስለዚህ በመጀመመሪያው ዘመን እንደ አገልግሎት ሆኖ የተጀመረው ኋላ አስተምሕሮ ሆኖ ቀጠለ።

ጳጳሶች ዛሬም ድረስ በሰዎች ላይ ስልጣን አለን ይላሉ፤ ሰዎችንም እንደፈሉ ያደርጓቸዋል፤ በአገልግሎት ውስጥ የፈለጉበት ቦታ ይመድቧቸዋል። ይህም አሰራር “ጳውሎስንና በርናባስን ለጠራኋቸው አገልግሎት ለዩልኝ” ያለውን መንፈስ ቅዱስን የሚቃወም አሰራር ነው። ይህ አሰራር የቃሉ ተቃዋሚ ነው፤ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።

 

“መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቤተክርስቲያን ውስት ብዙ ሽማግሌዎች እንደሚያገለግሉ ያሳያል”።

የጥንቷ ቤተክርስቲያን ስኬት ሚስጥሩ ይህ ነው።

በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ አስተዳድሮ አያውቅም። ጉባኤውን የሚያገለግለው የሽማግሌዎች ሕብረት ነው።

ይህም አሰራር ከዓመታት በኋላ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተጀመረው የአንድ ሰው አምባገነን አገዛዝ በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳይነሳ ተከላክሏል።

አንድ ሰው ብቻውን ገዥ የሚሆንበት አሰራር ድክመቱ ሰዎች ጥቅስ ወስደው እንደየቅዠታቸው መተርጎማቸው ነው።

ሰዎች ደግሞ በተደጋጋሚ ያለፉበትን ውድቀት አለማስተዋል ልማዳቸው ነው።

በሰዎች ላይ ስልጣን ስንይዝ የራሳችን ግብዝነትና ትዕቢት ያሳውረናል።

ዛሬ ፕሮቴስታንቶች የካቶሊክ እናታቸውን ምሳሌነት በመከተል ቤተክርስቲያንን “አንድ ሰው ብቻ መሪ” ሆኖ ያስተዳድር ይላሉ።

ማቴዎስ 20፡25 ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፡- የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።

26 በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥

27 ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤

28 እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።

 

“ሊያገለግል” የሚለው ቃል ዝቅ ማለትን እንጂ አለቃ ወይም ፓስተር መሆንን አያመለክትም።

መሪ መሆን ለሰዎች ነጻነት መስጠት እንጂ ማፈንና መቆጣጠር አይደለም።

 

“የዘመናቱ ታሪክ” የቤተክርስቲያን ዘመናት መጽሐፍ ምዕራፍ 10

የሚያሳዝነው ነገር እውነተኛው ወይን እንኳ ከዚህ ትምሕርት ተጽእኖ ነጻ አልነበረም። ይህንን ስል የኒቆላውያንን ሃሳብ ወይም አስተምሕሮ ያመጠው እውነተኛው ወይን ነው ማለቴ አይደለም። በፍጹም። ነገር ግን ያ ትንሽዬ የሞት ትል እውነተኛውን ወይን ይሞታል ብሎ ተስፋ በማድረግ ከስሩ ይበላው ነበር።

በእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንኳ ሳይቀር እግዚአብሔር ጳጳሳት እንዲሆኑ የተራቸው ሰዎች ይህንን ማዕረግ ተጠቅመው ከአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን በላይ በሌሎችም ላይ ስልጣን አለን ለማለት ይጠቀሙበት ነበር።

ነገር ግን በዚያ ዘመን በነበረችዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት መረዳት አልነበረውም። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፡- “ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።” ጳውሎስ ምንም ዓይነት ስልጣን የነበረው ቢሆንም እንኳ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ብቻ እንዲመለከቱ ያደርግ ነበር፤ ምክንያቱም የስልጣን ሁሉ ምንጭ እግዚአብሔር ነው።

ቀሳውስት ግን ሁልጊዜ መለኮታዊ አመራር ሲደመር የሰው አመራር ነበር የሚፈልጉት፤ ስለዚህ ክብር ለማይገባው ክብር እየሰጡ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በሰዎች እድፈት እንድትቆሽሽ አደረጓት

ኒቆላዊነት ከተመሰረተ በኋላ-- በሐዋርያት ቦታ የተተኩ ሰዎች ፓስተሮችን በድምጽ ብልጫ እየመረጡ በመሾም ሲቀጥሉ ሐሰተኛዋ ቤተክርስቲያን በዚህ አካሄድ የበለዓምን መንገድ ለመከተል አንድ እርምጃ ብቻ ነበር የቀራት። ቀጣዩ ወይም ሁለተኛው ደረጃ ወደ “ሰይጣን ጥልቅ ነገር” መግባት ነው።

 

ሰዎች በተመደቡበት አጥቢያ ውስጥ ተረጋግተው መቀመጥ ይከብዳቸዋል።

ሰዎች ታላቅ መሆንና ስልጣናቸውን በብዙዎች ላይ ማስፋፋት ይፈልጋሉ።

ይህ በካቶሊኮች እና በፕሮቴስታንቶች መካከል ብዙ ጊዜ የሚታይ ችግር ነው።

 

“ዕብራውያን ምዕራፍ ሰባት” ሴፕቴምበር 15 ቀን 1957

“ጦርነቶች ሁሉ” የሚደረጉት “ለመርሆች ተብሎ” ነው። በቤተክርስቲያናችሁ ውስጥ ትንሽዬ ጦርነት ካላችሁ ለትክክለኛው መርህ ሊሆን ይችላል። ለትክክለኛው ነገር ነው መዋጋት ያለባችሁ። እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን አባልም ይህንኑ ማድረግ አለበት …

ቤተክርስቲያንን ምንም ነገር እንዲያደናቅፋት አትፍቀዱ። አንድ ነገር ቤተክርስቲያንን ቢያደናቅፋት ተጠያቂዎቹ እናንተው እያንዳንዳችሁ ናቸው። እናንተ በተለያዩ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ ስትሆኑ በቤተክርስቲያናችሁ ውስጥ የተበላሸ ነገር ቢኖር ተጠያቂ እናንተው ናችሁ፤ ምክንያቱም የዚያች ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ናችሁ

ኃላፊነቱ የፓስተሩ አይደለም፤ የዲያቆናት ቦርድም አይደለም። ያንን ግለሰብ በግል አግኝታችሁ ማስታረቅ ኃላፊነቱ የናንተ ነው፤ የግለሰቦች ነው …

 

በአጥቢያ ሕብረት ውስጥ መንፈሳዊ ስልጣን በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ ነው የሚገኘው። ቤተክርስቲያን የምትመሰረተው ለአምልኮ በሚሰበሰቡና ሕብረት በሚያደርጉ አማኞች ነው። አንዴ በእምነት ካደጉ በኋላ እያንዳንዱ አማኝ ጉባኤውን የመከታተልና ጉባኤው በእውነት ጸንቶ እንዲቆም የመከታተል ኃላፊነት አለበት።

 

“ፍጹሙ” እሑድ ጃንዋሪ 27 ቀን 1963

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከአጥቢይቱ የበለጠ ስልጣን ያለው ማንም የለም።

አንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን በሌላ ቤተክርስቲያን አትተዳደርም ነጻ ናት፤ መንፈስ ቅዱስም በወደደበት መንገድ ይሰራል። እርሱ በሕዝቡ መካከል ነው የሚኖረው።

እኛ ግን ሌላ ፍጹም የሆነ መሪ አለን፤ የሁላችንም የበላይ የሆነ መሪ ምን ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል።

እነርሱ ከሚያስቡት ነገር ጋር ካልተስማማላቸው ወይም ከፍላጎታቸው ጋር አብሮ ካልሄደ “ይውጣልን። ይህ ከጌታ አይደለም” ይለሉ።

ይገርማል! በጣም አሳዛኝ ነገር ነው! ምን ዓይነት የተጣመመ ነገር ውስጥ ገባን! ስለዚህ እስከ ዛሬ ለመነቃቃት እያለቀስን መቆየታችን አያስደንቅም። ሰማይ በአስደናቂ ፔንቲኮስታል ኃይል ተሞልቷል እኛ ግን እንዴት አድርገን እንደምንወስደው አላወቅንም። ይህ እውነት ነው። ይህ ሁሉ የሆነው የእግዚአብሔርን ፍጹሙን መመሪያ አንቀበልም ስላልን ነው።

“በዚህ ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁ፤ የገሃነም ደጆች አይችሏትም” የሚለው የክርስቶስ መገለጥ፤ ፍጹሙ እውነት ይህ ነው።

የእግዚአብሔር ቃል ፍጹሙ መመሪያችን ነው።

“ይህን ስጋና ደም አልገለጠልህም፤ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ የገለጠልህ። በዚህም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁ።” አያችሁ? ቃሉ ፍጹም ነው።

 

ጉባኤው ትንሽም ይሁን ትልቅ በእምነቱ የበሰለ አማኝ በጉባኤው መካከል ሽማግሌ ነው።

ከእርሱ በላይ ሌላ ስልጣን የለም፤ ከአማኙ በላይ ካሕን የለም።

ይህ እውነት ነው። ሰዎች የተለያዩ አገልግሎት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፤ ነገር ግን አገልግሎት ውስጥ መግባታቸው ከሰዎች በላይ ከፍ ሊያደርጋቸው አይችልም።

ሁላችንም እኩል ነን። በአገልግሎታችን እንለያያለን እንጂ እኩል ነን። ሽማግሌዎች በሕብረት ሆነው ቤተክርስቲያንን ይንከባከባሉ። ሽማግሌዎች በሕብረት ሆነው ያላቸው ጥበብ አንድ ግለሰብ ብቻውን ከሚኖረው እውቀት በጣም የተሻለ ነው።

1ኛ ጴጥሮስ 2፡9 እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤

 

ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ አማኝ የአዲሱ የመልከጼዴቅ ክሕነት አካል ነው።

ከእናንተ በላይ ሊቀ ካሕኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንጂ ሌላ ማንም የለም።

ሌዋውያን በሕዝቡ እና በእግዚአብሔር መካከል ቆመው ሲያገለግሉ የነበሩበት የአሮን ክሕነት ተሽሯል።

 

አምስቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገልግሎቶች በአንድነት ሆነው ክሕነት አይሆኑም

 

 

የአሮንን ክሕነት በአምስቱ አገልግሎቶች ክሕነት አትተኩት።

የትኛውንም ሰው ከራሳችሁ በላይ አትሹሙ። ወደ ላይ ብትመለከቱ የምታዮች አንዱን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ መሆን አለበት።

1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡5 አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤

 

ከእናንተ በላይ ያለው ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌላ ማንም ሰው የለም። ማንም አገልጋይ ወይም አገልግሎት ከእናንተ በላይ አይደለም። አገልጋይ ባሪያ ነው። አምስቱ አገልግሎቶች እናንተ በክርስቶስ እንድታድጉ እና በክርስቶስ ውስጥ ስፍራችሁን እንድታገኙ ሊያግዙ የተሰጡ ናቸው። እነርሱ አገልጋዮች እንጂ ጌቶች አይደሉም።

 

“እግዚአብሔር ቃሉን ይጠብቃል” ጃንዋሪ 15 ቀን 1957

ቃሉ ምን ይላል? …

“ታላላቅ ጳጳሳት ይኖራሉ፤ ስለዚህ ስልጣን አለ ከተባለ እንኳ ስልጣኑ የእነርሱ ነው፤ ፈቃድ የሚሰጡ እነርሱ ናቸው …” በፍጹም አይደሉም።

“እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ የሚመሩት በእግዚአብሔር መንፈስ ነው።” ስለ መለኮታዊ ፈውስ ምን ይላል? “እርሱ ስለ በደላችን ቆሰለ፤ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።” ያለቀ ጉዳይ ነው።

አንድ ሰው መዳን ቢፈልግስ? ማነው መዳንን ሊሰጠው የሚችለው? ፖፑ ነውን? ጳጳሱ ነውን? ወይስ ካርዲናሉ ነውን? አይደለም፤ በጭራሽ አይደለም። የሮም ፖፕ ይህን ማድረግ አይችልም። የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳሳት የሰውን ነፍስ ማዳን አይችልም። ማናቸውም ቢሆኑ አንዳች ነገር ሊያደርጉ አይችሉም።

እያንዳንዳችሁ በቀራንዮ መስቀል ክርስቶስ ባጠናቀቀው ሥራ ላይ ያላችሁ እምነት ነው ለመዳን የሚያበቃችሁ። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረው ይህንን ነው።

 

“አትፍሩ፤ እኔ ነኝ” አፕሪል 14 ቀን

ኢየሱስ በእናንተ ቦታ እንደሞተላችሁ እስካላመናችሁና የግል አዳኝ አድርጋችሁ እስካልተቀበላችሁ ድረስ አትድኑም። እዚህ ያሉ አገልጋዮች ሁሉ በዚህ ለተሰበሰቡ ሕመምተኞች እጃቸውን ጭነው ከአሁን ጀመሮ እስከ ነገ ወዲያ ምሽት ድረስ ሊጸልዩላቸው ይችላሉ። ኢየሱስ ያደረገላችሁን ካልተቀበላችሁ በቀር አንዳች የሚሆንላችሁ ነገር የለም። ስለዚህ መዳንም ሆነ ፈውስ ከአገልጋዩ የተነሳ አይደለም የሚሆነው፤ እኛ እያንዳንዳቸው በቀራንዮ መስቀል በተጠናቀቀው የክርስቶስ ሥራ ላይ በግል ያመንነው እምነት ነው የሚሰራው

 

እምነታችሁ እናንተን በቀጥታ ከኢየሱስ ጋር ነው የሚያገናኛችሁ።

በእናንተ እና በኢየሱስ መካከል አንድም ሰው የለም።

 

“የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ዘመን” የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ ምዕራፍ 3

ያን ጊዜ ምን እንደተፈጸመ ተመልከቱ።

ያ ሐሰተኛ የወይን ተክል ስር እየሰደደ ነበር፤ እንዲሁም የሰው አገዛዝ ትክክል ነው ብሎ እያስተማረ ነበር። ቤተክርስቲያን በሰው አገዛዝ መተዳደር አለባት ብሎ እያስተማረ ነበረ

ሰዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግን አስተማረ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር መንገድ ከማድረግ ይልቅ ስልጣንን ሁሉ መንፈሳዊ ስልጣንን ሁሉ በራሳቸው እጅ አድርገው በእግዚአብሔር እና በሰዎች መካከል ገብተው የሚቆሙ ቅዱሳን ካሕናትን ሾሙ

ወደ ጥንቱ ወደ አሮን ክሕነት ተመልሰው ሄዱ።

የክርስቶስን መካከለኛነት አስወግደው እራሳቸውን ስለተኩበት የክርስቶስ ተቃዋሚ ሆነዋል። እግዚአብሔርም እንዲህ ማድረጋቸውን ጠላ።

የኤፌሶን ሰዎች ይህንን ሥራ ጠልተዋል፤ ስለዚህ ማንኛውም እውነተኛ አማኝ ሁሉ ይጠላዋል።

ይህ ነገር በዘመናት ውስጥ ሁሉ ሲሰራ ማየት ካቃተን ታውረናል ማለት ነው፤ አሁንማ በዘመን መጨረሻ ላይ ክፋቱ እየጨመረ ሄዷል።

የኒቆላውያን ስራ ድርጅታዊነት ነው።

ይህ አሰራር ሕዝቡን ያለያያል። የእግዚአብሔር ሕዝብ አንድ መሆን አለባቸው። ሁላቸውም በአንድ መንፈስ ወደ አንድ አካል ውስጥ ተጠምቀዋል፤ ስለዚህ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ መስራት አለበት፤ ሁሉም በመንፈስ ሆነው እግዚአብሔርን ያመልካሉ

ሰዎች ግን ታላቅነትን ስለፈለጉ በህዝቡ ላይ ተቆጣጣሪ ሆኑ፤ ጳጳሳትም ሊቀ ጳጳሳት ሆኑ፤ ከዚያም ለራሳቸው የሚያስፈራ ማዕረግ ስም ከሰጡ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል ትተው የራሳቸውን አስተምሕሮ ለሰዎች አስተማሩ።

ሕዝቡ እንዲታዘዙዋቸው አደረጉ፤ ሙሉ በሙሉ ለውጠዋቸው የአምልኮ ስርዓታቸው እንኳ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የምታመልክበትን አምልኮ እስከማይመስል ድረስ ለወጡ

እነዚህ ድርጊቶች በሙሉ የሐዋርያዊ መተካካት መጀመሪያዎች ነበሩ።

ከሐዋርያዊ መተካካት በኋላ የመዳን ጸጋ የሚገኝበት መንገድ “የቤተክርስቲያን አባልነት” ነው ብሎ ለማስተማር አንድ እርምጃ ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

ቃሉ ወደ ሐይማኖት መግለጫነት ደረጃ ዝቅ አለ። የክርስቶስ ተቃዋሚ በመንፈሱ ቤተክርስቲያንን ተቆጣጠራት።

 

ሕዝቡ እንዲታዘዙዋቸው አደረጉ፤ ሙሉ በሙሉ ለውጠዋቸው የአምልኮ ስርዓታቸው እንኳ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የምታመልክበትን አምልኮ እስከማይመስል ድረስ ለወጡ።”

የጥንቷ ቤተክርስቲያን በድምጽ መቅጃ ቴፕ አማካኝነት አልነበረም ስብከቶቿን የምታቀርበው።

ስብከቶችን በቴፕ ብቻ የምናዳምጥ ከሆነ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ቤተክርስቲያን ያገለገለችውን አገልግሎት እየተከተልን አይደለንም።

 

“የፊልደልፊያ ቤተክርስቲያን ዘመን” የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ ምዕራፍ 8

ነገር ግን ሰዎች ይህንን እውነት ልብ ብለውታል። በቤተክርስቲያን ላይ ሙሉ ስልጣን ያለውን ጌታ አክብረውታልን? አኔ እንዲህ እላለሁ፡- “አላከበሩትም”።

በየዘመናቱ ቤተክርስቲያን ስትተዳደር የኖረችው በሰው ሰራሽ የስልጣን ተዋረድ ነው -- ካሕናት -- በፈለጉት ሰዎች ላይ የምሕረትን በር የሚዘጉና ለፈለጉት ደግሞ የሚከፍቱ የሐዋርያት ተተኪዎች ነን የሚሉ ሰዎች ለቤተክርስቲያን ያለባቸውን ኃላፊነትና ፍቅር ትተው በገንዘብ ፍቅር አብደው ቤተክርስቲያንን ሲዘርፉና ሲያጠፉ ኖረዋል።

ካሕናቱ በድሎትና በቅንጦት ሲኖሩ ድሃዋ ቤተክርስቲያን ግን በፍርፋሪ ትኖራለች።

በየትኛውም ዘመን መልካም አድርገው አያውቁም።

ሁሉም ራሳቸውን ከድርጅት ጋር አቆራኝተው ስልጣንን ወይም መንግስትን ለሰዎች በመስጠት ቤተክርስቲያንን ለሰዎች ስልጣን እንድትንበረከክ አደረጓት።

ሰዎች ደፍረው በተቃውሞ በተነሱ ጊዜ ሁሉ ተቀጥቅጠው ከቤተክርስቲያን ተባርረዋል።

ሁሉም ዲኖሚኔሽኖች አንድ መንፈስ ነው ያላቸው።

እያንዳንዱ ዲኖሚኔሽን የቤተክርስቲያን መንግስት ቁልፍ ተሰጥቶኛል ይላል።

እያንዳንዱ ዲኖሚኔሽን በሩን የምከፍተው እኔ ነኝ ይላል። ይህ ግን እውነት አይደለም። ኢየሱስ ብቻ ነው በሩ። ብልቶችን በአካሉ ውስጥ የሚተክላቸውም ኢየሱስ ነው።

ለእያንዳንዱ የአገልግሎት ስጦታ የሚሰጥ ኢየሱስ ነው።

እርሱ ስጦታዎችን ለቤተክርስቲያን ይሰጣል። ጌታ ቤተክርስቲያንን ይንከባከባታል፤ ይመራታል። ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ብቻ ናት፤ እርሱም ከእርሷ ሌላ ማንም የለውም።

 

የፓስተሩ ፍልስፍና እንዲህ የሚል ነው፡- “ሁሉም ሰው የእኔን አመለካከት የመከተል መብት አለው”።

የሚያሳዝነው ነገር ስልጣን ሰዎችን ማበላሸቱ ነው።

ልክ ፓስተሮች በጉባኤያቸው ላይ ጌታ ሊሆኑ እንደሚፈልጉ ሁሉ አንዳንድ ተለቅ ያሉ ፓስተሮች ደግሞ ከእነርሱ በታች ያሉ ታናናሽ ፓስቶች ላይ ጌታ መሆን ይፈልጋሉ። ሁልጊዜ አንድ ሰው መሪ እንዲሆንና ለሌሎች ማድረግ የሚገባቸውን እንዲነግራቸው ይጠበቃል።

ይህ ዓይነቱ መንፈስ መጨረሻው የት ነው? መጨረሻው ዓለምን ሁሉ የሚቆጣጠር አንድ ሰው ተነስቶ ለሁሉም ሰው ምን ማድረግ እንደሚችሉና እንደማይችሉ ሲነግራቸው ነው።

ሰዎች ላይ አለቃ መሆን ለዲኖሚኔሽናዊ ቤተክርስቲያኖች መፈጠር መንስኤ ነው።

እግዚአብሔር በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለሰዎች የመስበክ እና የማስተማር አገልግሎት ሰጠ። ዛሬም የሚያደርገው ይህንኑ ነው። ሞዴላችን የጥንቷ ቤተክርስቲያን ናት። ማንም ቢሆን ሰዎች እንዳይሰብኩና እንዳያስተምሩ መከልከል የለበትም። ሰዎች መንፈስ ቅዱስን የመከተል መብታቸውን ማንም ሊወስድባቸው አይችልም። ፖፑ ግን በአንድ ሰው ስብከት ደስተኛ ካልሆነ እንዳይሰብክ መከልከል እችላለሁ ይላል። ፖፑ እንዲህ ዓይነቱን ስልጣን ለራሱ ወስዷል። ፕሮቴስታንቶች ፖፑን መኮረጅ የለባቸውም።

ፓስተሮች “የምሕረትን በር መዝጋት” እንችላለን በማለት ሰዎች ላይ አለቃ ይሆኑባቸዋል። ይህ አነጋገር በራሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። ወንድም ብራንሐም እንዲህ ብሎ አያውቅም። አንድ አማኝ ወደ ሐጥያት ቢመለስና ለዓለም እንኳ አስጸያፊ ሕይወት ውስጥ ቢገባ ስጋው ብቻ እንዲጠፋ ለሰይጣን ተላልፎ መሰጠት ይችላል። በዚህ ዓይነት የሐጥያት ጥልቀት ውስጥ የሚመላለስ ሰው ከዚያ በኋላ ይታመምና ምስክርነቱን በምድር ላይ እንዳያበላሽ እግዚአብሔር ይወስደዋል ወይም ሰውየው ከልቡ ንሰሃ ይገባና ከበሽታው ይድናል። ይህ ባልሆነበት ጊዜ ፓስተሩ እንዲሁ ያልተሰጠውን ስልጣን ይወስዳል። ነገር ግን አዲስ ኪዳን ውስጥ ስናነብብ አንድም ፓስተር እንዲህ እንዳደረገ ተጽፎ አናገኝም።

ፓስተሮች የእነርሱን አመለካከት የማይቀበሉ ሰዎችን ለመጨፍለቅ ይህንን ቴክኒክ ይጠቀማሉ። ይህ አሰራራቸው መንፈሳዊ ጉልቤ ያደርጋቸዋል። ፖፑ የእርሱን አመለካከት የማይቀበሉ ሰዎችን እንዲያወግዝ ያነሳሳው ይህ መንፈስ ነው።

አንዳንድ ነገሮች በዘመናት እንኳ አይለወጡም።

“ፓስተር” የሚለው ቃል አዲስ ኪዳን ውስጥ በሚከተለው ጥቅስ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተጻፈው።

ኤፌሶን 4፡11 እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤

ከአምስት አገልግሎቶች ውስጥ ፓስተሮች አራተኛ ደረጃ ላይ ነው የተመዘገቡት። ይህም ትልቅ ደረጃ አይደለም። ስለዚህ ፓስተር የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እንዲሆን ስልጣን የሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የለም።

ኤፌሶን ውስጥ የሚገኘው ይህ ጥቅስ አገልግሎቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚሩበትን ቅደም ተከተል ያሳያል። ሐዋርያት በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጻፉት ቃል ከሁሉ የሚበልጥ መመሪያችን ነው። ቤተክርስቲያንን የሚመራት ነብይ ሐዋርያት አዲስ ኪዳን ውስጥ የጻፉዋቸውን ሚስጥራት በመግለጥ ወደ አዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ሊመልሰን ይገባል። ነብዩ ወደ ሐዋርያት መሰረት ነው የሚመልሰን። የወንጌላዊው አገልግሎት በየስፍራው እየሄደ አንደ ደማሚት ቦምብ በሚፈነዳ ኃይል ሰዎች ከአለማመን እያነቃ እየፈነቃቀለ ወደ መዳን እንዲመጡ ማድረግ ነው። የፓስተሩ አገልግሎት ሰዎች በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት እንዲያድጉ ማበረታታትና በሕወት፣ በስራ፣ እንዲሁም በቤተሰብ ውስጥ በሚገጥማቸው ችግሮች ዙርያ ማማከር ነው።

ፓስተሩ ወንጌላዊው ያመጣቸውን አዳዲስ ሰዎች ተቀብሎ በዓለም ከነበራቸው ልማድና እውቀት እያላቀቀ ቅርጽ አልባ ድንጋዮች የነበሩትን የብሎኬት ቅርጽ እንዲይዙ ማድረግ ነው።

ከዚያም የአስተማሪው ስራ እነዚህን ድንጋዮች ተቀብሎ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥልቅ ሚስጥራት በመግለጥ በክርስቶስ ውስጥ ያላቸው ስፍራ ላይ እንዲቀመጡ ማድረግ ነው። አንድ ሰው የሚያምነውን እምነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ ሲችል በቃሉ ማለትም በክርስቶስ ውስጥ የተመደበለትን ስፍራ አግኝቷል ማለት ነው።

 

63-0724 እግዚአብሔር ሰውን አስቀድሞ ሳያስጠነቅቅ ወደ ፍርድ አያመጣውም

ገር ግን አያችሁ በቤተክርስቲያን ውስጥ ፓስተሩ አለ፤ ፓስተሩም ልዩ ሰው ነው። የሰዎችን ጭንቀት መሸከም እንዲችል የተዘጋጀ ሰው ነው። ሸክም ተሸካሚ ሰው ነው፤ የሕዝቡን ቀምበር መሸከም የሚችል በሬ ነው። ፓስተሩ ሰው ከሰው ጋር ወይም አንድ ቤተሰብ ከሌላ ቤተሰብ ጋር ተጣልቶ ሳለ (ለማናቸውም ሳይወግን) ከሁለታቸውም ጋር አብሮ መቀመጥና ሁለቱንም አነጋግሮ ወደ እርቅ ማምጣት የሚችል ሰው ነው። አያችሁ? እርሱ ፓስተር ነው፤ እንዴት ችግር መፍታት እንደሚችል ያውቃል።

ወንጌላዊው ልዩ ሰው ነው። ወንጌላዊው ልዩ ሰው ነው። እንደ እሳት ኳስ የሚነድድ ሰው ነው። ወንጌላዊው ወደ ከተማ ገብቶ መልእክቱን ይሰብካል፤ ከዚያም ይወጣና ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳል። ወንጌላዊው ልዩ ሰው ነው።

አስተማሪ ልዩ ሰው ነው። ቁጭ ብሎ የመንፈስ ቅዱስን ቅባት እየተቀበለ ቃሉን ይወስድና በመንፈስ ቅዱስ እያገናኘ ስለሚያስተምር ወንጌላዊም ይሁን ፓስተሩ ከአስተማሪ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም

 

አስተማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማገናኘትና ጠለቅ ያለ ሚስጥር መግለጥ ይችላል፤ በዚህም ወንጌላዊ እና ፓስተር ሊወዳደሩት እንኳ አይችሉም።

1ኛ ቆሮንቶስ 12፡28 እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።

 

እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን በስርዓት ሲያዋቅራት ፓስተሮችን አልጠቀሰም።

ዋናው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምሕርት ነው። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን እንደተጻፈ ቢያውቁና በቃሉ ቢጸኑ ኖሮ ቤተክርስቲያን አትወድቅም ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ናችሁ የሚባለው ሌላ ሰው ከእናንተ ተምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ሲያምን ነው።

 

 

የአጥቢያ ሽማግሌዎች አጥቢያ ቤተክርስቲያንን ማስተዳደር አለባቸው

 

 

እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምሕርት በሚሰጥበት ስፍራ አጥቢያ ቤተክርስቲያንን የሚያስተዳድሯት የአጥቢያው ሽማግሌዎች ናቸው።

ጳውሎስ የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን እንዲመሩ ኃላፊነት የሰጠው ለኤፌሶን አጥቢያ ሽማግሌዎች ነው።

ኤፌሶን ለሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ሁሉ መሰረት የሆነች ቤተክርስቲያን ናት።

የሐዋርያት ሥራ 20፡17 ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤

የሐዋርያት ሥራ 20፡28 በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

 

 

ጴጥሮስም ከጳውሎስ ጋር በመስማማት አጥቢያ ቤተክርስቲያንን የሚያስተዳድሯት የአጥቢያይቱ ሽማግሌዎች መሆናቸውን ጽፏል።

በዚህ አሰራር ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁሉም ሰው እኩል ይሆናል።

የትኛውም አገልግሎት ከየትኛውም በላይ ከፍ ስለማይደረግ የኒቆላውያን አሰራር ቦታ አያገኝም፤ ኒቆላውያን በጉባኤው ወይም በምዕመናን ላይ ራሳቸውን ከፍ በማድረግ ይነግሱባቸዋል።

1ኛ ጴጥሮስ 5፡1 እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤

2 በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤

3 ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤

የዳኑ ክርስቲያኖች በሙሉ የንጉስ ካሕናት ናቸው ማለትም እያንዳንዱ የዳነ ክርስቲያን ካሕን ነው።

1ኛ ጴጥሮስ 2፡9 እናንተ ግን … የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ … ናችሁ፤

አንድ ካሕን ከሌላ ካሕን አይበልጥም።

ሊቀ ካሕኑ ኢየሱስ ብቻ ነው ከካሕናት ሁሉ በላይ ከፍ ያለው።

1ኛ ጢሞቴዎስ 5፡17 በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል።

አንዳንድ ሽማግሌዎች የአምስቱ አገልግሎቶች አካል ስለሆኑ ይሰብካሉ። ሌሎች ሽማግሌዎች ደግሞ አይሰብኩም። ነገር ግን ሁሉም ሽማግሌዎች እኩል ናቸው፤ በአጥቢያ ቤተክርስቲያን አስተዳደርም ውስጥ እኩል ሚና ይጫወታሉ። አገልግሎት ያለው ሽማግሌ አገልግሎት ከሌለው ሽማግሌ በምንም አይበልጥም።

ዛሬ ፓስተሮች ቤተክርስቲያኖቻቸውን በኃይል ይገዛሉ። ፓስተሮች እንዴት ነው ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ ያልሰጣቸውን ስልጣን ወደመያዝ የመጡት?

“የፓስተር” አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተጠቀሰው፤ ዛሬ ግን ቤተክርስቲያኖች ላይ ገዥ ሆኗል።

የሆነ ነገር ከስፍራው ለቋል።

 

“ሶስተኛው ማሕተም” ማርች 20 ቀን 1963

ከመካከላቸው የሆነ ሰው ከሮም ቤተክርስቲያን ጋር የማይስማማ ሁሉ እንደ መናፍቅ ተቆጥሮ መገደል አለበት የሚለውን መገለጥ የተቀበለ ጊዜ … ይህ በቃ የፈለጉትን ማድረጊያ ሆናቸው። ከዚያም እንደ ልብ ደም ማፍሰስ ቀጠሉ።

 

በ400 ዓ.ም አካባቢ ኦጋስተን የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የሚቃወሙ ሰዎችን ሁሉ መግደልና ማጥፋት ትክክል ነው ብሎ ወሰነ። ከዚያ ወዲያ ከ50 ዓመታት በኋላ ታለቁ ፖፕ ሊዮ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የሚቃወሙ ሰዎችን ማጥፋት ሕግ አድርጎ ደነገገ።

በዚህ ዘመን ደግሞ የፕሮቴስታንት ፓስተሮች የሚቃወሙቸውን ሰዎች ስም የማጠፋት ዘመቻ ጀምረዋል። ከእግዚአብሔር ቃል ጠቅሳችሁ እነርሱ ስሕተት መሆናቸውን ስታሳዩዋቸው ስለ እናንተ ምን ብለው እንደሚያወሩ ታያላችሁ።

 

“የትያጥሮን ቤተክርስቲያን ዘመን” የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ ምዕራፍ 6

ቶማስ አክዊናስ እና አልቨረስ ፕላጊየስ እንዲህ ብለው ነበር፡- “በመንፈሳዊ ዓይን ለሚመለከቱት ሰዎች ፖፑ ሰው ሳይሆን አምላክ ነው የሚመስለው። ለስልጣኑ ምንም ገደብ የለውም። የፈለገውን ነገር ትክክል ነው ወይም እውነት ነው ብሎ ማወጅ ይችላል፤ የፈለገውንም ሰው መብት መንፈግ ይችላል። ይህንን ስልጣን መጠራጠር መዳንን ያሳጣል። የቤተክርስቲያን ታላላቅ ጠላቶች የመታዘዝን ቀንበር የማይሸከሙ ሰዎች ናቸው።”

 

እግዚአብሔር በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሰውን አስተማሪ አድርጎ የመሾም መብት አለው።

ወይም በኢንተርኔት እንዲያስተምር የማድረግ መብትም አለው።

ድሮ ድሮ የካቶሊክ ፖፕ ብዙ አስተማሪዎችን ከማስተማር አግዷቸዋል። የካቶሊክ መንፈስ እየተስፋፋ ስለሚሄድ የፕሮቴስታንት መሪዎችም ሰዎች እንዳያስተምሩ ሲከላከሉ ብታዩ አትደነቁ።

ፖፑ እንዳታስተምር ብሎ የጻፈለትን ትዕዛዝ ሉተር በእሳት አቃጠለው፤ እኛም የሉተርን አርአያ መከተል አለብን።

 

“መልእክት የማይገልጠው ድምጽ” ጁላይ 14 ቀን 1962

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወይም ዲኖሚኔሽናዊ ቤተክርስቲያን የተጀመረችው ሮም ውስጥ ነው። ዲኖሚኔሽኖች የተጀመሩት ሮም ውስጥ ነው፤ ስለዚህ ወደዚያው ነው የሚመለሱት። የጥንቷ ጋለሞታ የጋለሞታዎች እናት እና ልጆቿም ጋለሞታዎች ናቸው። ስለዚህ ወደዚያ ይመለሳሉ።

 

ፕሮቴስታንት የሆነ ሰው በምንም ዓይነት መንገድ ካቶሊኮችን መከተል የለበትም። የጋለሞታይቱ ልጅ መሆን የሚፈልግ ማነው?

 

 

ከሰው ትምሕርት የተወሰዱ ጥቅሶች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው ቃል ጋር መስማማት አለባቸው

 

 

የሐዋርያት ሥራ 17፡10-11 ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤

እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።

 

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የተናገረውን ሁሉ ዝም ብለው አያምኑም ነበር፤ የጳውሎስ ትምሕርት ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚስማማ መሆኑን ለማጣራት ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ይመረምሩ ነበር።

ዛሬም እንደ እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር አለብን።

 

“በእናንተ ውስጥ ያለው” ኖቬምበር 10 ቀን 1963

መልእክቱን በሙሉ እመኑ።

መልእክቱን እመኑ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኝ ከሆነ አትመኑት።

 

“ዕብራውያን ምዕራፍ ሁለት” ኦገስት 25 ቀን 1957

በብሉይ ኪዳን ዘመን የአንድ ነብይ ቃል ከመፈጸሙ በፊት ይመረመራል፤ ይፈተሻል።

እኛ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ግዴለሾች ነን፤ እነርሱ ግን ግዴለሽ አልነበሩም

 

“ሶስተኛው ማሕተም” ማርች 20 ቀን 1963

ያ የእግዚአብሔር መልአክ አንድ እንኳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ነገር ቢነግረኝ አላምነውም

 

“በድምጽ የተነገረው ቃል የመጀመሪያው ዘር ነው” ማርች 18 ቀን 1962

አሁን እነዚህ የተናገርኳቸው ነገሮች በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙ ከሆኑ ወይም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይገጥሙ ከሆኑ በሙሉ ስሕተት ናቸው።

 

“በዘመን መጨረሻ ላይ የተቀቡ ሰዎች” ጁላይ 25 ቀን 1965

ማንም ይሁን ማን ጉዳዬ አይደለም፤ እኔም ልሁን ወይም ሌላ ሰው፤ “እንደ ሕጉ እና እንደ ነብያቱ ካልተናገረ በውስጡ ብርሃን ስለሌለው ነው።” አያችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረው ይህንን ነው። “የሰው ሁሉ ቃል ሐሰት ይሁን የእኔ ብቻ እውነት ይሁን” ማንም ይሁን ማን።

 

“ስድስተኛው ማሕተም” ማርች 23 ቀን 1963

እኛ ለሞኝነት ቅርብ ነን፤ ለብዙ ነገር ቅርብ ነን፤ እምነታችን እራሱ በግምሽ ልብ የሆነ እምነት ነው።

መጀመሪያ ማየት አለብኝ።

ያየሁትም ጊዜ ያየሁት ነገር ቃሉ ውስጥ መመገኘት አለበት

እንግዲህ እስካሁን ድረስ በእግዚአብሔር ጸጋ በፍጹምነት … ሙሉ በሙሉ መርምሬ አይቸዋለሁ፤ እንደምታውቁት ከቃሉ ጋር በፍጹም የሚስማማ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

እግዚብሔር እንዲህ ይላል የሚል መሆን አለበት፤ ምክንያቱም እኔ ስላወቅሁ ወይም ስለገባኝ የምናገረው ነገር ብቻ መሆን የለበትም፤ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት መሰረት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል የሚል መሆን አለበት።

ቃሉ ይኸው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይኸው፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አመሳክራችሁ በማየት እግዚአብሔር በቃሉ የተናገረው እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ትችላላችሁ። አያችሁ?

 

ወንድም ብራንሐም ራዕይ ካየ በኋላ ያየውን ራዕይ በመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ይመረምረዋል፤ ይህን የሚያደርገው ራዕዩ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጣላ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው።

 

“የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት” ሴፕቴምበር 28 ቀን 1958

አንድ ሰው ከጌታ ዘንድ የሆነ መገለጥ አገኘሁ ቢል እና መገለጡ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራዕይ ድረስ ሙሉ በሙሉ ባይገጥም አስተምሕሮ አድርገው ቢያቀርቡትም እንኳ አንቀበለውም። አያችሁ?

ከመጽሐፍ ቅዱስ መምጣት አለበት። ዝም ብሎ አንድ ሰው መገለጥ ተቀብያለሁ ስላለ ብቻ ልናምነው አንችልም።

መገለጥ ከቃሉ ጋር የሚስማማ ከሆነ ችግር የለውም፤ እንቀበለዋለን።

 

ጥቅሶች መነሻ ሃሳብ ይሰጡናል።

የሰውን ጥቅስ ከማመናችሁ በፊት ሃሳቡን በመጽሐፍ ቅዱስ መርምሩትና የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ ብቻ በመጠቀም እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ትችሉ እንደሆን እዩ።

ሃሳቡን ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ልታረጋግጡ ካልቻላችሁ ስሕተት ሰርታችኋል ማለት ነው።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በአንድ መሪ የሚተዳደር ማዕከላዊ አሰራር የሚከተል ድርጅት አቋቋመች። ካሕናት ወይም ቀሳውስት በምዕመናን ማለትም በጉባኤው ላይ ገዥዎች ሆኑ። አንድ ቄስ የእያንዳንዱ ጉባኤ አለቃ ሆኖ ተሰየመ። ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ቄሶች ጳጳሳት ሆኑና በሌሎች ቄሶች ላይ ገዥዎች ሆኑ። የበላይ ተቆጣጣሪ ማለት አንድ ሰው ብዙ ጉባኤዎችን መቀጣጠር እንዲችል የሚያደርግ አሰራር ነው። በዚህ መንገድ የስልጣን ተዋረድ ተዋቀረና አንድ ሰው ማለትም ፖፑ የሐይማኖት ድርጅቱን ሁሉ እስመቆጣጠር እንዲደርስ ተደረገ።

ማንኛውም ተቃውሞ ወዲያው ይታፈናል። ውግዘት ተቃዋሚዎችን ማስወገጃ መንገድ ሆነ።

ሮም ውስጥ ወደምትገኘው ወደዚህች ማዕከላዊ ድርጅት ብዙ ገንዘብ እየጎረፈ ገባ፤ ይህም ሃብታም እና ኃይለኛ አደረጋት።

ይህ ሐሰተኛው የወይን ተክል ነው።

 

 

የቤተክርስቲያን ራስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ እርሷም አካሉ ናት

 

 

የትኛውም ሟች ሰው ወይም የትኛውም ፓስተር የቤተክርስቲያን ራስ መሆን አይችልም።

ኤፌሶን 5፡23 ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና።

 

የአካሉ ራስ የአካሉ አዳኝም ነው። የትኛውም ሟች ሰው ቤተክርስቲያንን ማዳን አይችልም፤ ኢየሱስ ብቻ ነው የሚችለው።

ቆላስይስ 1፡18 እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው።

 

የቤተክርስቲያን ራስ ከሙታን በኩር ሆኖ የተነሳው ነው። ሞቶ ከሙታን የተነሳውና በማይበሰብስ አዲስ አካል ተመልሶ የመጣው ኢየሱስ ብቻ ነው።

ሌላ ማንም ሰው ይህን ሊያደርግ አይችልም።

ኢየሱስ ከሁሉ የበላይ ሊሆን ይገባዋል። ነገር ግን የበላይ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፤ ደግሞም የቤተክርስቲያን ራስ ነኝ ይላሉ።

አንዳንድ ፓስተሮች የቤተክርስቲያን ራስ ነኝ የሚሉት ራሳቸውን ከጉባኤው በላይ ከፍ ሊያደርጉ ፈልገው ነው። ነገር ግን አዲስ ኪዳን የትም ቦታ ፓስተሩ የቤተክርስቲያን ራስ ነው ብሎ አይናገርም።

 

ይህንን ቁልፍ እውነት አትርሱ።

የቤተክርስቲያን ራስ ኢየሱስ ብቻ ነው።

እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል በነርቭ ስርዓት ከራስ ጋር ይገናኛል። ስለዚህ ራስ እያንዳንዱን የሰውነት ክፍል በቀጥታ ይቆጣጠራል። እምነታችሁ በእናንተ እና በኢየሱስ መካከል በቀጥታ ያገናኛል። ኢየሱስ ብቻ ነው ሕይወታችሁን መቆጣጠር ያለበት ምክንያቱም ለሕይወታችሁ ያለውን ፈቃዱን የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው። ሌሎች ሰዎች ሊመሩዋችሁና ሊያግዟችሁ ይችላሉ ነገር ግን እርሱ ብቻ ነው ሊቆጣጠራችሁ የሚገባው።

ኢየሱስ ቃሉ ስለሆነ የምታምኑት ነገር በሙሉ እንደ እግዚአብሔር ቃል መሆን አለበት።

ልትከተሉ የሚገባችሁ ሞዴል የጥንቷ ቤተክርስቲያን ናት። ከጥንቷ ቤተክርስቲያን የተለያችሁ አትሁኑ።

ከሰው ንግግር ጥቅስ ውስጥ የተማራችሁት ነገር ካለ ሙሉ በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ መርምረችሁ አረጋግጡ።

 

አጠራጣሪው ድምጽ ጁላይ 14 ቀን 1962

የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የተጀመረችው ኢየሩሳሌም ውስጥ በ33 ዓ.ም የበዓለ ሃምሳ ዕለት ነው። ወደዚያ ነው መመለስ ያለብን። እኔ ወደዚያ ጊዜ ልመለስ እየሞከርኩ ነኝ።

ነገር ግን እውነተኛው የእግዚአብሔር መንፈስ ሰዎችን ወደ መጀመሪያው እምነት ሊመልሳቸው ሲሞክር የክርስቶስ ተቃዋሚ እንቅስቃሴ ደግሞ ሰዎችን ወደ ሌላ መንገድ ሲወስዳቸው ታያላችሁ?

 

የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን እውነተኛ እምነት ለመከተል ዓላማ ይዛችሁ ብትነሱ ብዙም ለስሕተት አትጋለጡም።

 

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23