ማርቆስ 14 - ክፍል 2 - ክርስቶስ ብቻ ነው ዋጋውን መክፈል የሚችለው
We update studies as the Lord Jesus leads us. You can find the latest update of this study at ChurchAges.net
ጴጥሮስ የሰነፎቹ ቆነጃጅት ቤተክርስቲያን መሪ ምሳሌ ነው። ጴጥሮስ ኢየሱስን ማለትም ቃሉን በርቀት ይከተለዋል፤ ግን ደግሞም ቃሉን ይክደዋል።
- በኤድን ገነት የተሰራ ሐጥያት በጌቴሴማኒ አታክልት ቦታ ተወገደ
- የሐጥያታችንን እድፈት ብዛት ኢየሱስ በፍርሃት እንዲንቀጠቀጥ አደረገ
- ለንግስና የተመረጠው ነገድ ይሁዳ ነው
- ማርቆስ እግዚአብሔርን ማገልገል ከመልመዱ በፊት ወድቋል
- ጴጥሮስ የሰነፍ ቤተክርስቲያን መሪ ምሳሌ ነው
- የሰነፎቹ ቆነጃጅት መሪ የሆነው ጴጥሮስ ቃሉን ጊዜ ካደ
- አስተምሕሮ ማዘጋጀት የአስተማሪ ሥራ ነው
በኤድን ገነት የተሰራ ሐጥያት በጌቴሴማኒ አታክልት ቦታ ተወገደ
ማርቆስ 14፡32 ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው።
“ተቀመጡ”። ወሳኝና ፈታኝ ሰዓት ላይ ስለደረሱ ደቀመዛሙርቱ ምን ማድረግ የሚችሉት ነገር አልነበረም።
የአቅማቸው መጨረሻ ላይ ደርሰዋል።
በሞት እና በሕይወት መካከል በሚደረግ ትግል ውስጥ ጦርነቱን ማሸነፍ የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው።
ጌቴሴማኒ ማለት “የዘይት መጭመቂያ” ማለት ነው።
የማዳን ሥራ ሂደቱ የተጀመረው በጌቴሴማኒ ነው። ኢየሱስ የሐጥያታችንን ሸክም ተሸከመ።
ከመጣበት ከባድ ጫና የተነሳ ከጸሎት በቀር ሌላ ምንም መሸሸጊያ አልነበረውም።
ኢየሱስ ከነበረበት ጫና የተነሳ የደረሰበት ጭንቀት መንፈስ ቅዱስ ከውስጡ ተጨምቆ እንደሚወጣ ይመስል ነበር። ከዚያም ከትንሳኤው በኋላ በእርሱ ውስጥ የነበረው መንፈስ ቅዱስ ተመልሶ መጥቶ በኢየሱስ በሚያምኑ ሰዎች ልብ ውስጥ አደረ፤ እነርሱም ተሰብስበው ቤተክርስቲያን ሆኑ።
አረንጓዴ የወይራ ፍሬዎች ሲበስሉ ቀለማቸው መጀመሪያ ቀይ ከዚያም ወደ ጥቁር ይለወጣል። ከዚያም ተፈጭተውና ተወቅጠው ከውስጣቸው ዘይት ይወጣል።
ዮሐንስ 19፡1 በዚያን ጊዜም ጲላጦስ ኢየሱስን ይዞ ገረፈው።
2 ወታደሮችም ከእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አኖሩ ቀይ ልብስም አለበሱት፤
ኢየሱስን ለጥቂት ጊዜ ቀይ ልብስ አልብሰውት ነበር፤ ከዚያም ስለ ሐጥያታችን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ቅጣት ከተቀበለ በኋላ ቀኑ ለሶስት ሰዓታት በጨለም ጠቆረ። ይህ ክስተት የፀሃይ ግርዶች አልነበረም፤ ምክንያቱም የፀሃይ ግርዶች የሚቆየው ለ7 ደቂቃዎች ብቻ ነው።
ማርቆስ 15፡33 ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።
ጌቴሴማኒ ውስጥ ኢየሱስ ሊመጣበት ካለው አስፈሪና አስጨናቂ መከራ እየተዘጋጀ ነበር።
ደቀመዛሙርቱ ብርቱ ሰዎች ነበሩ። ስለዚህ እንዲሸሹ ያደረጋቸው በዚያ ሰዓት የመጣው የፍርሃት መንፈስ በጣም ኃይለኛ ስለነበረ ነው።
ማርቆስ 14፡33 ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና።
ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ እና ዮሐንስ እንደ እምነት፣ ተስፋ፣ እና ፍቅር ናቸው።
በኢየሱስ ላይ ያለን እምነት በእርሱ ውስጥ በአካል ይኖር ከነበረው ከእግዚአብሔር ጋር የተሻለ ሕብረት ውስጥ እንድንሆን ተስፋ ይሰጠናል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ስለ እኛ ሊሞትልን እንደሚገባው እስኪያስብ ድረስ ነው የወደደን።
ቆላስይስ 2፡9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤
የኤድን ገነት ውስጥ አዳም እና ሔዋንን ከሐጥያታቸው እንዴት እንደሚያድናቸው መላ ሊቀይስ እግዚአብሔር እራሱ መጣ። የማዳኑን ሥራ ለማንም በአደራ ሊሰጥ አልፈለገም ምክንያቱም ማንም ፍጹም የሆነ ሥራ ሊሰራ አይችልም።
ስለዚህ በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ውስጥ በድጋሚ እግዚአብሔር እራሱ ነው ሰው በሆን በኢየሱስ ውስጥ ሆኖ ከሐጥያታችን ሊያድነን የመጣው።
የሐጥያታችንን እድፈት ብዛት ኢየሱስ በፍርሃት እንዲንቀጠቀጥ አደረገ
ነገር ግን ኢየሱስ ስለ ሐጢያታችን ሊከፍል የመጣው ዋጋ ከአስጨናቂም በላይ አስጨናቂ ነበር።
ኢየሱስ ሐጥያታችንን በተሸከመ ጊዜ በውስጡ ይኖር የነበረው የእግዚአብሔር መንፈስ ከኢየሱስ “ፊቱን ሰወረበት” ሊያናግረውም አልፈቀደም። ስለዚህ ኢየሱስ እንደተጣለ ሐጥያተኛ ተሰማው። ኢየሱስ የሐጥያታችንን ዋጋ በሰብዓዊ አቅሙ ብቻ ከፈለው እንጂ ምንም ዓይነት መለኮታዊ አቅም አልተጠቀመም።
ኢሳይያስ 59፡2 ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።
ማርቆስ 14፡34 ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ትጉም አላቸው።
በውስጡ ይኖር የነበረው የእግዚአብሔር መንፈስ ከኢየሱስ ፊቱን ሰወረ።
ስቃይን የምንቀበለው በአእምሮዋችን ውስጥ ሲሆን እሱም መንፈሳችን ወይም ሕይወታችን ነው።
ስንሞት መንፈስ ከአካላችን ተለይቶ ይወጣል።
ነፍሳችን ግን በመንፈሳችን ውስጥ ነው ያለችው።
1ኛ ሳሙኤል 25፡29 ያሳድድህ ዘንድ ነፍስህንም ይሻ ዘንድ ሰው ቢነሣ፥ የጌታዬ ነፍስ በሕያዋን ወገን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የታሰረች ትሆናለች፤
ሮሜ 8፡10 … መንፈሳችሁ ግን … ሕያው ነው።
ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ውስጥ ይጣላል፤ ስለዚህ በሲኦል ለሚገቡ ከበድ ያለ ስቃይ ይጠብቃቸዋል፤ ይህም ስቃይ የነፍስ ከመንፈስ መለየት ነው። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።
ራዕይ 20፡14 ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።
ኢየሱስ በነፍሱ መከራን መቀበል ጀመረ።
ይህም ማለት በስጋው መቀበል የጀመረው የሲኦል ስቃይ መስቀሉ ላይ በተሰቀለ ጊዜ እየባሰበት ይሄዳል። ሰይጣን ኢየሱስን ለማጥፋት ባደረገው ሙከራ ከሲኦል ጉድጓድ ውስጥ ያጠራቀመውን ያለ የሌለ ኃይሉን ሁሉ ተጠቅሞ ኢየሱስ ላይ የመከራ ዓይነት ሁሉ አወረደበት።
የዚህ ዓለም ሰዎች ማየት በማይችሉበት መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ሞት እና ሕይወት ታላቅ ፍልሚያ ገጠሙ።
ማርቆስ 14፡35 ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና፦
የጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ኢየሱስ ሐጥያታችንን ከነእድፉ ለመሸከም እሺ አለ። እንከን የሌለው ንጹሕ ሕይወቱ በእኛ እርኩስ ሃሳቦችና አስጸያፊ ድርጊቶች ጎደፈ። የሐጥያተኛ ሕይወታችን ሙሉ እድፈትና ቆሻሻ በእርሱ ላይ ተጫነ።
ኢየሱስ በሐጥያታችን ብዛት ነፍሱ ተጨነቀች።
ይህ ማንም ሊሸከመው የማይችለው ሸክም ነው።
ማርቆስ 14፡36 አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ።
ማርቆስ ግን በወንጌሉ ኢየሱስን ወደ በሬነት እንዳደገ ጥጃ አድርጎ ያሳየናል።
የሐጥያታችንን ዋጋ ለመክፈል ሐጥያታችንን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ መሄድ፤ የኢየሱስ አገልግሎት ይህ ነበር።
መከራውን ሸሽቶ ለማምለጥ በጣም ተፈትኖ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ፈተና ለብቻው ተጋፍጦ ማሸነፍ እንዳለበትም ተረድቶ ነበር።
በእርሱ እና በሰው ልጆች መካከል ልውውጥ ተደርጓል።
ሐጥያታችን ወደ እርሱ ተላለፈ፤ የእርሱ ጽድቅ ደግሞ በእምነት ወደ እኛ ተላለፈ።
ማርቆስ 14፡37 መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም፦ ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን?
በመጀመሪያ ምጻቱ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ላይ የታየባቸው ድክመት ተግተው መጸለይ አለመቻላቸው ነው።
በመጨረሻው ዘመን የቤተክርስቲያኖች ድክመት ደግሞ ሾልከው እየገቡና እየተቆጣጠሩን ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሃሳቦችና ልማዶች ነቅተን በመጠበቅ መቆጣጠርና መከላከል አለመቻላችን ነው።
የሲኦል ሰራዊት ሁሉ ተነቃቃ። ሰይጣን ወሳኝ ሰዓት መድረሱን ተገንዝቦ አጋንንቱን በመላክ ደቀመዛሙርቱ ላይ ስውር በሆነ መንገድ ጥቃት እንዲሰነዝሩባቸው አደረገ። አጋንንቱም ደቀመዛሙርት ላይ እንቅልፍ ጣሉባቸው።
በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት መጨረሻ አካባቢ አስር ቆነጃጅት ማለትም ንጹሐን ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ የዳኑ ክርስቲያኖችን ይወክላሉ።
የጌታን ምጻት እየተጠባበቁ ሳለ ሁላቸውም እንቅልፍ ይወስዳቸዋል። ይህም የሰይጣን ተንኮል ነው።
ማቴዎስ 25፡5 ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
የጨለማው ዘመን ካበቃ በኋላ እውነት እንዴት ወደ ቤተክርስቲያን እንደተመለሰች ተመልከቱ።
ማርቲን ሉተር ጻድቅ በእምነቱ በሕይወት ይኖራል በሚለው የአምስተኛ የቤተክርስቲያን ዘመን ተሃድሶ አማካኝነት ቤተክርስቲያንን ከእንቅልፏ አነቃት። ከዚያም እርሱ ከሞተ በኋላ ሉተራኖች እንቅልፋቸውን ተኝተው ቀሩ፤ አንድም እርምጃ ወደፊት ፈቀቅ አላሉም።
ስለ ቅድስና በሰበከው በጆን ዌስሊ አማካኝነት ሁለተኛ ዙር የማንቂያ ጥሪ መጣ። ጆን ዊስሊ ከሞተ በኋላ ሜተዲስቶች እንቅልፋቸውን ተኝተው ቀሩ፤ አንድም እርምጃ ወደፊት ፈቀቅ አላሉም።
ከዚያ ቀጥሎ የመጣው የጴንጤቆስጤ መነቃቃት እና ወንድም ብራንሐም የተቀበለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መገለጥ ለቤተክርስቲያን ሶስተኛ የማንቂያ ጥሪ ነበረ።
ማርቆስ 14፡38 ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።
ሉተራኖች ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሲወጡ ብዙ ስሕተቶችን ይዘው ወጥተው ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን እውነት ለይተን እናውቅ ዘንድ መጸለይ እና መንቃት አለብን። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ እምነቶች የቤተክርስቲያን ልማዶች ሆነው ይቀጥላሉ።
ከስጋችን ድካም የተነሳ ሳናውቀውና ሳናስተውለው ወዲያው ወደ ስሕተት እንወድቃለን።
ደቀመዛሙርቱ ከእነርሱ በኋላ በየዘመናቱ እንደሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ተመሳሳይ ድካም ስላለባቸው ኢየሱስ ይህን አስቀድሞ በማወቅ አስጠንቅቋቸው ነበር። ኢየሱስ ድካማቸውን አይቶ እንዲተጉ እና ለብርታት እንዲጸልዩ መከራቸው ምክንያቱም እነርሱም ፈተና መጥቶባቸው ነበር። ራሳቸውን ለማዳን ብለው ኢየሱስን እንዲክዱ የሚያደርግ ፈተና ይመጣባቸዋል።
ማርቆስ 14፡39 ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ።
በስድስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በሜተዲስቶች የቅድስና መነቃቃት ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ነው የጠፈጠረው። ዌስሊ ከሞተ በኋላ ሜተዲስቶች እንቅልፍ ተኙና አንድ እርምጃ እንኳ ወደፊት አንራመድም አሉ።
ማርቆስ 14፡40 ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም።
በመጨረሻው ወይም በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ማብቂያ አካባቢም ቤተክርስቲያን እንደገና አንቀላፍታለች።
ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
17 … ስለማታውቅ፥ …
የመጨረሻዋ ቤተክርስቲያን እንቅልፍ ውስጥ ናት፤ ስለዚህ ምን እየተደረገ እንዳለ እንኳ አታውቅም ምክንያቱም በ45,000 ዓይነት ቤተክርስቲያኖችና ዲኖሚኔሽኖች ተከፋፍላለች። እነዚህ ቤተክርስቲያኖች በሙሉ በትምሕርታቸው የተለያዩ ናቸው ነገር ግን እያንዳንዱ ትክክለኛ እኔ ነኝ ብለው ያስባሉ።
ደቀመዛሙርቱ ሊቋቋሙ የማይችሏቸው ሰይጣናዊ ኃይሎች ተለቀው ነበር። ደቀመዛሙርቱም እንቅልፍ በመተኛታቸው በዙርያቸው እየሆነ የነበረውን ነገር አላወቁም።
ዛሬም በመጨረሻው ዘመን ተመሳሳይ ነገር እየሆነ ነው ያለው። ክርስቲያኖች በቸልተኝነት እንቅልፋቸውን ተኝተዋል ምክንያቱም እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን በትምሕርቷ ከሌሎቹ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ የተለየች ብትሆንም እንኳ ሁሉም ትክክለኞች እኛ ነን ብለው አምነዋል።
ማርቆስ 14፡41 ሦስተኛም መጥቶ፦ እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል።
ደቀመዛሙርቱ እንቅልፍ ተኝተው ሳለ ኢየሱስ የሐጥያታችንን ብዛት እንዳይሸከም የመጣበትን ፈተና ታግሎ አሸነፈ።
ሐጥያት የኤድን አትክልት ቦታ ውስጥ ተጀመረ። ኢየሱስ ደግሞ በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ውስጥ የሐጥያትን ኃይል መስበር ጀመረ።
የሐጥያት ቀጣዩ እርምጃው አሳልፎ መስጠት ነበር።
ኢየሱስ በመጀመሪያው ምጻቱ የቤተክርስቲያን መሪ በነበረው በይሁዳ እንደ ሰው ተላልፎ ተሰጠ።
ዳግም ምጻቱ እየቀረበ ባለበት በአሁኔ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ተላልፎ የተሰጠው እንደተገለጠው የእግዚአብሔር ቃል ነው። የኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን መገለጦች ለማደናቀፍ ብዙ ሐሰተኛ አስተምሕሮዎች ይፈጠራሉ። በእንግሊዝኛ ብቻ ከ100 በላይ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተዘጋጅተዋል። እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን ራስ ሆኖ የተሾመባት ሰው አለ፤ የዚህም ሰው አመለካከቶች እንደ እውነት ይቆጠራሉ። ይህ ከባድ መንፈሳዊ ዝቅጠት ነው። በአሁኑ ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ፍላጎት እየተተረጎመና እየተጠመዘዘ ነው። በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሰዎች አመለካከት መተካቱ እውነት ተላልፋ እየተሰጠች መሆኑን ያመለክታል።
ለንግስና የተመረጠው ነገድ ይሁዳ ነው
ማርቆስ 14፡42 ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።
ኢየሱስ ተላልፎ የሚሰጥበት ሰዓት ደረሰ።
እኛም በዛሬዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለንበት ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ሰዎች የቤተክርስቲያናቸውን ልማዶችና አመለካከቶች በመምረጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አሳልፈው እየሰጡ ናቸው።
ማርቆስ 14፡43 ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ።
የሚያሳዝነው ነገር አሳልፎ ሰጭው የቤተክርስቲያን መሪ መሆኑ ነው። ይህም ተዓምራት አድርጎ የሚያውቅ ሰው ነው።
አንድን ሰው ለመያዝ ብዙ ሕዝብ ሰይፍ ይዘው መጡ።
ዛሬም የራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይዘው የተነሱ ብዙ ሰባኪዎች አሉ። የራሳቸውን አመለካከት ይዘው መጥተዋል። ሁላቸውም ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት ያለበት ትርጉም ነው በማለት ስለሚያወግዙ የየራሳቸውን አመለካከት ይዘው ተነስተዋል።
ማርቆስ 14፡44 አሳልፎ የሚሰጠውም፦ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።
አሳልፎ ሰጭው አታላይ ሰው ነው። መሳም የፍቅር ምልክት ነበረ ነገር ግን ዕድሜ ለይሁዳ አሁን የክሕደትና አሳልፎ የመስጠት ምልክትም ሆኗል።
ማርቆስ 14፡45 መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና፦ መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤
ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት አለበት፣ እንከን አለበት እያሉ ሊቃወሙትና ሊለውጡት ወይም ሊነቅፉት የሚፈልጉ ሰዎች ፈጥነው ይነቅፉታል።
በመጨረሻው ዘመን የተገለጠውን እውነት ሊነቅፉ የሚፈልጉ ሰዎችም ፈጥነው ይነቅፉታል።
ማርቆስ 14፡46 እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት።
ሕዝብ ተሰብስበው ኢየሱስን ያዙት። ዛሬም የሐይማኖት መሪዎች የእውነትን መገለጥ ለመቃወም ይሰበሰባሉ። እንደ ስላሴ፣ ክሪስማስ እና የሰባት ዓመት መከራ የመሳሰሉ የቤተክርስቲያን ልማዳዊ ትምሕርቶች ተቀባይነት አግኝተዋል፤ ስለዚህ እነዚህን ስሕተቶች የተቃወመ ወዮለት።
ማርቆስ 14፡47 በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ።
ጴጥሮስ ስሕተት በሰራ ጊዜ ማርቆስ ሲጽፍ ጴጥሮስን በስም አልጠቀሰውም። ስለዚህ ማርቆስ እግዚአብሔርን ስናገለግል የራሳችንን ስም ለማስጠራት ብለን መሆን እንደሌለበት ይመክረናል። ስማችንን እና የራሳችንን ክብር መተው አለብን።
ማርቆስ ጴጥሮስን በስም ባይጠቅሰውም እንኳ የጴጥሮስን ውድቀት ጠቅሷል።
አገልጋዮች ስሕተታቸውን ለመግለጥ መፍራት የለባቸውም፤ ምክንያቱም ከስሕተታቸው ሁላችንም መማር እንችላለን።
በዚህ ክፍል የተጠቀሰው ተምሳሌት የቃሉ ሰይፍ ሲሆን እርሱም ቃሉን ሊያስሩ የሚፈልጉ ሰዎችን ጆሮዋቸውን ይቆርጣል። ይህም የማያምነውን ሰው መንፈሳዊ ጆሮ ስለሚደፍነው የማያምን ሰው የተገለጠውን እውነት መረዳት አይችልም።
ማርቆስ 14፡48 ኢየሱስም መልሶ፦ ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን?
ሊይዙት ሲመጡ በሚስጥር በጨለማ ነው የመጡት። ልክ አለመሆናቸውን አውቀውታል ግን ብዙ በመሆናቸው ተማምነው ነው ሊይዙት የመጡት።
ሰይጣን የሚተማመነው ብዙሃኑን በመቆጣጠር ነው።
ማርቆስ 14፡49 በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው።
ኢየሱስ ቤተመቅደሱ ውስጥ በየቀኑ ያስተምር ነበር፤ ሕዝቡም እርሱ ከቤተክርስቲያን መሪዎች የተለየ መሆኑን አውቀዋል። ስለዚህ ሕዝቡ ኢየሱስ የሚያስተምረውን ትምሕርት መስማት ይፈልጉ ነበር። በዚህ ምክንያት የአይሁድ ሕዝብ መሪዎች ኢየሱስን ቤተመቅደስ ውስጥ መያዝ ፈርተዋል፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ለእርሱ ሊያግዙ ይችላሉ ብለው አስበዋል። ስለዚህ ከመሸ በኋላ በሚስጥር መጥተው ያዙት ምክንያቱም ሰዎች ሐጥያት ሲሰሩ ማንም ሊያያቸው በማይችልበት ጨለማ ውስጥ ተሸሽገው መስራት ይወዳሉ።
“መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።”
የይሁዳ ክሕደት
መዝሙር 41፡9 ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።
ኢየሱስን ሲይዙት በሚስጥርና በተንኮል በተሞላ መንገድ ነው የያዙት።
ሰቆቃ 4፡20 ስለ እርሱ፦ በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን ያልነው በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጕድጓዳቸው ተያዘ።
የተቀባው ማለትም ክርስቶስ የመንፈሳዊ ሕይወታችን እስትንፋስ ነው። አይሁዶች ወጥመድ ሊያጠምዱበት ጉድጓድ ቆፈሩለት። በሌሊት መጥተው ያዙትና በእርሱ ላይ ይደገፉ ከነበሩ ደቀመዛሙርቱ ለይተው ወሰዱት።
“ጥላ” ከስደት እና ከተቃውሞ ሐሩር ከለላ የሚሆን የጥበቃ ተምሳሌት ነው።
እርሱ ግን ሁልጊዜ የዋህ እና ትሑት ነበር፤ ሲይዙትና ሲያንገላቱት በሐሰትም ሲከስሱት እንኳ አልዛተባቸውም።
ኢሳይያስ 53፡7 ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
ሊቀ ካሕናቱ ኢየሱስን በሐሰት ቢያሲዘውና ቢከስሰውም በሮማውያን ሕግ መሰረት የሚያስገድለው አንድም ጥፋት አላገኘበትም። ወደ ሔሮድስ ላኩት፤ ሔሮድስም አንዳች ጥፋት አላገኘበትም። ወደ ጲላጦስ መልሰው ሲያመጡት ጲላጦስም አንዳች ጥፋት አላገኘበትም፤ ነገር ግን አይሁዶች ዓመጽ እንዳያስነሱበት ብሎ እንዲገድሉት የሞት ፍርድ ፈረደበት።
እርሱ ግን የሞተው በእርግጥ ስለ ሐጥያታችን ዋጋ ለመክፈል ነው።
ኢሳይያስ 53፡8 በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?
እረኛው በግፍ በተያዘ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ በሙሉ በፍርሃት ሸሹ።
ዘካርያስ 13፡7 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገዴ ብትሄድ ትእዛዜንም ብትጠብቅ፥ በቤቴ ላይ ትፈርዳለህ፥ አደባባዮቼንም ትጠብቃለህ፥ በዚህም ከቆሙት ከእነዚህ ጋር መግባትን እሰጣለሁ።
ማርቆስ 14፡50 ሁሉም ትተውት ሸሹ።
ኢየሱስ በተያዘ ጊዜ በደቀመዛሙርቱ ላይ ኃይለኛ የፍርሃት መንፈስ ወድቆባቸው ነበር። እነርሱም እንዳይያዙ ብለው ተበታተኑ።
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙን ሰዎች በተፈጥሮዋችን ራሳችንን ለማዳን ነው የምንሯሯጠው።
ክርስቶስ ታላቁ አገልጋይ መሆኑን ገልጦ የጻፈው ማርቆስ እኛ ሰዎች እግዚአብሔርን ስናገለግል ምን ያህል ጉድለት እንዳለብን ያሳያል። ደቀመዛሙርቱ በሙሉ የራሳቸውን ነፍስ ለማዳን ብለው ከቃሉ (ከኢየሱስ) ሸሹ።
ዛሬም እኛ ይህንኑ ነው የምናደርገው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ከመቆም ይልቅ በብዙሃኑ የቤተክርስቲያን አመለካከት እንማረካለን።
መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን ልደት እንድናከብር ያልጠየቀን ለምንድነው ብለን ለመጠየቅ እንኳ ድፍረት የለንም።
ክሪስማስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ቃል መሆኑን ለመጥቀስ እና “እንኳን ለገና በዓል አደረሳችሁ” የሚለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ አባባል መሆኑን ለመናገር ድፍረት የለንም።
ዲሴምበር 25 አረማውያን ሮማውያን የሚያመልኩት የፀሃይ አምላክ ልደት ቀን መሆኑንና ቀኑም በ274 ዓ.ም ያወጀው ዲሴምበር 22 ቀን የሮማ ጳጳስን የገደለው ሮማዊ ንጉስ ኦሬልያን መሆኑን እያወቅን ዝም እንላለን።
ከዚያ በኋላ በ350 ዓ.ም አካባቢ ፖፕ ዩልየስ ቀዳማዊ ዲሴምበር 25 ቀንን ኮርጆ በመጠቀም የእግዚአብሔር ልጅ ልደት ነው ብሎ አወጀ። የካቶሊክ ስርዓት ቅዳሴ ማስ ይባላል። ስለዚህ በዓሉ ክራይስትስ-ማስ ተብሎ ይጠራ ነበር፤ ኋላም ክሪስማስ ተባለ።
ይህም አረማዊ በዓል ቀስ ብሎ ወደ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖ ገባ።
አረማውያን በዓሉ ከክርስቶስ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር እንደሌለ ያውቁ ነበር፤ ስለዚህ የክርስቶስን ስም ሰርዘው ኤክስማስ አሉት።
ቤተክርስቲያኖችም ቀስ በቀስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እየራቁ ሄዱ።
ማርቆስ እግዚአብሔርን ማገልገል ከመልመዱ በፊት ወድቋል
ማርቆስ 14፡51 ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥ ጎበዛዝቱም ያዙት፤
ማርቆስ ስለዚህ በስም ስላልተጠቀሰው ሰው ሲናገር የራሱን ውድቀትና ፍርሃት እየገለጸ ነው።
ማርቆስ 14፡52 እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።
ሲይዙት እራሱን ከሰዎች እጅ መንጭቆ በማውጣት ማርቆስ የለበሰውን ነጠላ በእጃቸው ላይ ጥሎ ሮጠ። ከቃሉ ከኢየሱስ ጋር ከመቆም ይልቅ ራቁቱን ሆኖ መሮጥ መረጠ።
እግዚአብሔርን ማገልገል የምንጀምረው ከውድቀት ነው።
የመጨረሻዋ የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያንም “ራቁት” ተብላ ተገልጻለች ምክንያቱም ቤተክርስቲያኖቻችን እንደልብስ ሆኖላቸው የነረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አውልቀዋል።
ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
ራዕይ 3፡17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥
ከዚያ በኋላ ማርቆስ ከሳውል እና ከበርናባስ ጋር ማገልገል ጀመረ።
የሐዋርያት ሥራ 12፡25 በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ።
ከዚያ ወዲያ ማርቆስ አገልግሎቱን ገና በመጀመር ላይ ከነበረውና ስሙ ገና ወደ ጳውሎስ ካልተለወጠው ሳውል ጋር ተባበረ። ነገር ግን ማረቆስ መከራ እየበዛ ሲሄድ ጵንፍልያ ከተማ ውስጥ ትቷቸው ሄደ።
ከሳውል ኋላም ጳውሎስ ተብሎ ከተሰየመው ሰው ጋር ሆኖ እግዚአብሔርን ማገልገል በጣም ትልቅ ትጋትና መሰጠት ይጠይቃል። ጳውሎስ ሁልጊዜ ስደት ይደርስበት ነበር።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በርናባስ እንደገና ማርቆስን ይዞ መሄድ ፈለገ፤ ነገር ግን ጳውሎስ ይህን ሃሳብ ተቃወመ።
የሐዋርያት ሥራ 15፡37 በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤
በቀጣዩ ጉዞዋቸው በርናባስ ማርቆስ አብሯቸው እንዲመጣ ፈለገ፤ ጳውሎስ ግን ማርቆስን አልፈለገም።
የሐዋርያት ሥራ 15፡38 ጳውሎስ ግን ይህን ከእነርሱ ጋር ሊወስድ አልፈቀደም፥ ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፥ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና።
ጳውሎስ እና በርናባስ መካከል ክርር ያለ ክርክር ተፈጠረ፤ ከዚያም በርናባስና ማርቆስ ጳውሎስን ትተው ሄዱ።
ማርቆስ እግዚአብሔርን ለማገልገል እየሞከረ ነበር፤ ነገር ግን የጳውሎስን መስፈርት አላሟላም።
የሐዋርያት ሥራ 15፡39 ስለዚህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፥ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ።
በመጨረሻም ማርቆስ በአገልግሎቱ እየተሻሻለ መጣ፤ ጳውሎስም አብሮት እንዲያገለግል ተቀበለው።
2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡11 ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ። ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው።
ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ማርቆስን ተጠቅሞ ሁለተኛው ወንጌል እንዲጻፍ አደረገ፤ ይህም ወንጌል ጥጃው አድጎ ሸክም መሸከም የሚችል በሬ እንደሚሆን ያሳያል። ከዚህም የምንማረው እግዚአብሔርን ለማገልገል ብቁ እስክንሆን ድረስ መማር እንደሚያስፈልገንና ጊዜም እንደሚጠይቅ ነው። አንድን ሰው እግዚአብሔር ሊጠቀምበት ከመቻሉ በፊት ያ ሰው በአገልግሎት ማደግ እና በውድቀት ውስጥ ማለፍ ያስፈልገዋል።
ማርቆስ 14፡53 ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ።
የሐይማኖት መሪዎች የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን ኢየሱስን ሊፈርዱበት ወጡ።
ዛሬም የቤተክርስቲያን መሪዎች በዊልያም ብራንሐም አማካኝነት የተሰጠንን የተገለጠውን ቃል ሊያወግዙ ሊያጣጥሉ ተነስተዋል።
የዛሬ ቤተክርስቲያኖች በቤተክርስቲያን ልማዶች ተተብትበው ቀርተዋል፤ እነዚህም ልማዶች ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን የመጡ ሲሆኑ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ደግሞ ከባዕድ አምልኮ የተቀበለቻቸው ናቸው። የሮማ ካቶሊኮች የሰሩት ስሕተት የባዕድ እምነት ልማዶችን በክርስቲያናዊ ስያሜዎች መጥራታቸው ነው። ይህን በማድረጋቸው ምክንያት አረማውያን “ክርስቲያን” ሲቀበሉ ምንም መለወጥ እንዳያስፈልጋቸው አደረጉ። በዚህ መንገድ የሮማ ካቶሊክ ተከታዮች ቁጥር አደገ።
ጴጥሮስ የሰነፍ ቤተክርስቲያን መሪ ምሳሌ ነው
ማርቆስ 14፡54 ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር።
ስለ መዳን፣ ቅድስና፣ እና ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል በተመለከተ እውነቱን ይዘዋል። ነገር ግን ጠለቅ ስላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት ሲጠየቁ መመለስ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫል፣ አፈታሪኮች አሉበት ወይም ስሕተት አለበት ይላሉ። በዚህ መንገድ በብዙ ርዕሶች ላይ መሃይምነታቸውን ይሸፋፍናሉ፤ ደስ ያላቸው ቦታ ደግሞ የራሳቸውን አስተሳሰብ ለመደገፍ ብለው ቃሉን ይለውጡታል።
ጴጥሮስ ራሱን ከቃሉ እንዳራቀ አስተውሉ።
የቤተክርስቲያን መሪዎች እምነታቸው ትክክል መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማሳየት አይችሉም።
ማርቆስ 14፡55 የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤
ዛሬ ኢየሱስ በኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እንደ እግዚአብሔር ቃል ከእኛ ጋር አለ። ቤተክርስቲያኖች ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት እንዳለበትና ብዙ ቦታ በትክክል እንዳልተተረጎመ ለማሳየት ይፍጨረጨራሉ።
ስለዚህ የራሳቸውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጅተዋል።
ማርቆስ 14፡56 ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም።
ቤተክርስቲያኖች ከ100 በላይ የተለያዩ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አዘጋጅተዋል።
እነዚህ የተለያዩ ትርጉሞች እርስ በራሳቸው አይስማሙም።
ስለዚህ ቤተክርስቲያኖች ፍጹም ትክክል የሆነ ምንም እንከን የሌለው መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት አይቻልም ብለው ደምድመዋል።
ከዚህም የተነሳ እምነታቸው የተተከለበት የማይናወጥ መሰረት የላቸውም ምክንያቱም እምነት የሚመሰረተው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ነው።
ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።
ማርቆስ 14፡57-58 ሰዎችም ተነሥተው፦ እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት።
ሰዎቹ የተናገሩት ቃል ውሸት ነበር።
የቤተክርስቲያን መሪዎች የሚተቻቸውን ሰው ስም ሲያጠፉ የሚያቀርቡበትን ክስ አሳማኝ ለማድረግ የሰውየውን ንግግር ጠምዝዘው ያቀርባሉ። ሐሰተኛ ምስክሮች ሰው የተናገረውን በትክክል ደግመው አይናገሩም።
ኢየሱስ የተናገረው እርሱን ቢገድሉት በሶስት ቀን ተመልሶ እንደሚነሳ ነበር።
ዮሐንስ 2፡19 ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።
ኢየሱስ ቤተመቅደስ ብሎ የተናገረው የተናገረው ስለ ራሱ ስጋ ነው።
ማርቆስ 14፡59 ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም።
እነዚህ ምስክሮች ውሸታሞች ስለነበሩ ምስክርነታቸው እርስ በርሱ የሚጋጭ ነበረ።
ዘመናዊ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም ተመሳሳይ ችግር አለባቸው። ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ቃል አዲሶቹ ትርጉሞች በተለያየ ቦታ ለውጠውታል፤ ስለዚህ ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች በተለያየ ክፍል እርስ በርሳቸው ይጋጫሉ።
በዚህ ዘመን በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ቤተክርስቲያኖች እርስ በራሳቸው ሊስማሙ አልቻሉም።
አንዳንዶች ውርጃን ሲደግፉ ሌሎች ደግሞ ይቃወማሉ።
አንዳንዶች ሴት ሰባኪዎችን ይቀበላሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ አይቀበሉም።
አንዳንዶች የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ሲቀበሉ ሌሎች አይቀበሉም።
የራሺያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ኪሪል ፕሬዚደንት ፑቲን በ2022 ዩክሬይን ላይ የፈጸመውን ክፉ ወረራ በመደገፍ ቃለ ቡራኬውን ሰጥቷል። አንግሊካዊው የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ደግሞ ወረራውን አውግዞታል።
ማርቆስ 14፡60 ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ፦ አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው።
ኢየሱስ ምንም አልመለሰም። በሐሰት ሲከስሱት ዝም አለ።
ማርቆስ 14፡61 እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና፦ የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው።
ከዚያም ኢየሱስ እርሱ የሰው ልጅ መሆኑን በግልጽ ነገራቸው።
ማርቆስ 14፡62 ኢየሱስም፦ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ።
ሊቀ ካሕናቱ በፍጥነት ውሳኔ ማድረግ አስፈልጎት ነበር። ኢየሱስን እንደ መሲሁ እና ፍጹሙ የእግዚአብሔር ቃል መቀበል ወይ ደግሞ ኢየሱስን ለቤተመቅደሱ፣ ለሊቀ ካሕናቱ ስልጣን እና ገንዘብ ስጋት እንደሆነ አስቦ መግደል።
ልክ እንደ አብዛኞቹ የሐይማኖት መሪዎች ሊቀ ካሕናቱ የተጨነቀው በቤተመቅደሱ በኩል ስለሚያገኘው ገቢ እና ስለ ስልጣኑ ብቻ ነበር።
የሚያሳዝነው ነገር ከ37 ዓመታት በኋላ በ70 ዓ.ም የሊቀ ካሕናቱን የገቢ ምንጭ ቤተመቅደስ ሮማውያን አፈራረሱት። ቤተመቅደሱ ውስጥ የነበረውን ወርቅና ሃብት በሙሉ ወደ ሮም ይዘው ሄዱ፤ እርሱንም ተጠቅመውበት ኮሎሲየም የተባለውን እስታዲየም ሰሩበት፤ በዚያም እስታዲየም ውስጥ ክርስቲያኖችን ለአንበሶች እራት አድርገው ጣሉዋቸው። ሮማዊው ጀነራል ታይተስ 1,1,00,000 አይሁዶችን በጨፈጨፈ ጊዜ ከአሮን ቤት የሆኑት ሊዋውያን ካሕናት በሙሉ አልቀዋል። ሊቀ ካሕናቱ እና የቤተመቅደሱ ሃብትም አብረው ጠፍተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስን የሚቃወም ሁሉ የመጨረሻ ዕድል ፈንታው ይህ ነው።
ማርቆስ 14፡63 ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፦ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል?
አጋንንት የእግዚአብሔርን ቃል ይቃወማሉ። ሊቀ ካሕናቱ አጋንንታዊ ድርጊት ፈጸመ። ልብሱን ቀደደ። ይህ ድርጊት የሙሴን ሕግ የሚተላለፍ ድርጊት ነበረ።
ስለዚህ እንደ ሊቀ ካሕናት ቀያፋ በስልጣኑ ሕጉ እንዲያበቃ አደረገ።
ዘሌዋውያን 10፡6 ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን፦ እንዳትሞቱ በማኅበሩም ሁሉ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ራሳችሁን አትንጩ፥ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ እግዚአብሔር ስላቃጠለው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ።
አሮን የመጀመሪያው ሊቀ ካሕናት ነበረ። ይህ ስልጣን ለአሮን የልጅ ልጆች በየትውልዳቸው ተላልፏል።
ሊቀ ካሕናቱ ልብሱን እንዳይቀድ ሕግ በጥብቅ ከልክሎታል።
ማርቆስ 14፡64 ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ፦ ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።
ቀያፋ ልብሱን በመቅደድ ሕጉን ተሳደበ።
ኢየሱስ ተሳድቧል በማለት የራሱን ሐጥያት ሸፈነ። ለእውነት ሳይሆን ለደሞዛቸውና ለስልጣናቸው ብለው ከቀያፋ ጋር የሚስማሙ ሰዎች ሁሉ ወዲያ ቀያፋ ባቀረበው ክስ ተስማሙ።
የእግዚአብሔር ቃል ከሆነው ከኢየሱስ ይልቅ የሐይማኖት መሪያቸውን በመምረጣቸው የተነሳ ሁላቸውም በሰማይ የነበራቸውን ቦታ አጥተዋል።
ኢየሱስ በመጀመሪያ ምጻቱ በመጣበት ጊዜ የዘመኑ ፋሽን እርሱን ማጥላላት ነበረ።
አሁን ከዳግም ምጻቱ በፊት ደግሞ የተጀመረው ፋሽን ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥላላትና መተቸት ነው። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ስማቸው ከሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተደምስሷል ምክንያቱም ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወሙ የቤተክርስቲያን መሪዎቻቸውን ያምናሉ። ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በመካከላችን ነው።
ዘዳግም 12፡32 እኔ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፥ ከእርሱም ምንም አታጕድል።
በሌላ አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስን እንደተጻፈ ሳትለውጡ ተቀበሉት። ምንም ነገር መቀየር አይፈቀድም።
የተሰራው ጥፋት ቀያፋ ሕጉን መሻሩ ብቻ አይደለም። ኢየሱስን በጨለማ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከያዙት በኋላ ሕገወጥ በሆነ ችሎት የፈረዱበት ሰዎች የሚያደርጉት ነገር በሙሉ ሕገወጥ ነበረ።
ማርቆስ 14፡65 አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና፦ ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።
ለኢየሱስ ያላቸውን ንቀት ለማሳየት ፊቱ ላይ ተፉበት፤ ከዚያም መቱት።
ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ ነው።
እንጀራ ወደ ሆዳችን ከመውረዱ እና ጨጓራችን ውስጥ ከመፈጨቱ በፊት አፋችን ውስጥ በምራቅ መሸፈን አለበት።
የማያምኑ ሰዎች ቃሉ ላይ ምራቃቸውን ተፍተውበታል፤ ስለዚህ አማኞች ቃሉን መዋጥና ከሰውነታቸው ጋር ማዋሃድ እንዲሁም ሚስጥራቱን መረዳት ይችላሉ።
እያፌዙበት ዓይኖቹን በጨርቅ አስረው እየመቱት ማን እንደመታህ ትንቢት ተናገር አሉት። ፊቱን በጥፊ መምታትም ቀጠሉ።
የሰነፎቹ ቆነጃጅት መሪ የሆነው ጴጥሮስ ቃሉን ጊዜ ካደ
ኢየሱስ ቃሉ ነው።
ኢየሱስን በመካዱ ጴጥሮስ ቃሉን መካዱ ነበር።
ዛሬም የቤተክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔር ቃል የማይሳሳትና የማይለወጥ መሆኑን ይክዳሉ። ስለዚህ ኢየሱስ የማይሳሳት መሆኑን ይክዳሉ ማለት ነው። ኢየሱስን ዛሬ በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ መልክ ብቻ ነው የምናየው። ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን ስንተች ኢየሱስን እየተቸነው ነው። ይህም ከሰነፎቹ ቆነጃጃት አንዳቸውን እንድንሆን ያደርገናል።
ማርቆስ 14፡66 ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥
ቆነጃጅት ማለት በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚኖሩ የዳኑ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ጠለቅ ያሉ ሚስጥራት መረዳት ባለመቻላቸው የተነሳ የተታለሉ ክርስቲያኖች ናቸው።
እነዚህ ክርስቲያኖች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን ይታዘዛሉ ነገር ግን ብዙዎቹንም ደግሞ ይክዳሉ።
ጴጥሮስ ኢየሱስን ተቃረነ። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ከመቃረን ጋር አንድ ነው። ኢየሱስ ጴጥሮስ እንደሚክደው ተናገረ፤ ጴጥሮስ ግን የለም አልክድህም በማለት ኢየሱስን ተቃረነ። ሰነፎቹ ቆነጃጅትም የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን ይቃረናሉ፤ ደግሞም አይቀበሉዋቸውም።
ኢየሱስ የጴጥሮስን ድካም ገልጦ ተናገረ፤ ጴጥሮስ ግን የኢየሱስን ንግግር ተቃወመ። ጴጥሮስ ኢየሱስን በፍጹም እንደማይክድ በትዕቢት ተናገረ። የዳኑት ሰነፍ ቆነጃጅትም ዛሬ የቆምነው ለኢየሱስ ነው ብለው ያወራሉ ነገር ግን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን ከመካዳቸውም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን መከተል የሚፈልጉ ሰዎችን ያወግዛሉ።
ሰነፎቹ ቆነጃጅት ቤተክርስቲያናቸውን ወይም የቤተክርስቲያን መሪዎቻቸውን መተቸት አይችሉም። ነገር ግን የእነርሱን ስሕተት የሚገልጡ ወይም የማይመቿቸውን የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን መተቸት ደስ ይላቸዋል። ሰነፎቹ ቆነጃጅት ትኩረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን ቤተክርስቲያናቸው እና የቤተክርስቲያን መሪዎቻቸው ላይ ነው።
ሴት በተለይም ድንግል ሴት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት። በዚህ ዘመን ሰዎች ከቤተክርስቲያናቸው ጋር በሃሳብ አለመስማማት በጣም ያስፈራቸዋል።
ጴጥሮስም ከኢየሱስ ማለትም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አብሮ ነበር መባልን ፈራ። ዛሬ ኢየሱስን በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ነው የምናየው፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ሃሳብ ይነግረናል።
ራዕይ ምዕራፍ 3 የመጨረሻዋ የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ለብ እንዳለ ውሃ እንደሆነችና ብዙም ዋጋ እንደሌላት ይነግረናል።
ሰነፎቹ ቆነጃጅት ሶስት የተሃድሶ ደረጃዎችን ይቃወማሉ።
ማርቆስ 14፡67 ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና፦ አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው።
እሳት ሲሞቅ ማለት ጴጥሮስ እሳቱ ዳር ተቀምጦ ሳለ ፊቱ ሁሉ ይሞቃል ነገር ግን ለምሽቱ ቀዝቃዛ አየር የተጋለጠው ጀርባው ሙቀት ስለማይደርሰው ይበርዳል። ይህ የሙቀት እና የቅዝቃዜ ድብልቅ ነው ለብ ያለ አማኝን የሚወክለው። ለብ ያለ አማኝ ማለት መጽሐፍ ቅዱስን በከፊል የሚያምን በከፊል ደግሞ የማያምን ሰው ማለት ነው።
ሴቲቱ ጴጥሮስን ከኢየሱስ ጋር ነበርክ ማለትም ከቃሉ ጋር ቆመሃል ብላ ከሰሰችው። ጴጥሮስ ግን ካደ። የሰነፎቹ ቆነጃጅት መሪዎች ለዘመናቸው የተገለተውን አንዳንዱን ቃል ብቻ ነው የሚያምኑት፤ ከዚያ በኋላ ቃሉ ወደ ቀጣዩ ዘመን ሲሸጋገር እነርሱ ማመናቸውን ያቆማሉ።
የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚለው መጠሪያ የኢየሱስን መነሻ ማለትም የት እንዳደገ ያመለክታል። የቤተክርስቲያን መነሻ ሐዋርያት የአዲስ ኪዳንን እምነት የመሰረቱበት የመጀመሪያ የቤተክርስቲያን ዘመን ነው። ይህም የመጀመሪያ መብራት በመቅረዙ ላይ ወደ ሰባት የቤተክርስቲያን ዘመናት ቅርንጫፍ ያወጣል።
ኔትዘር የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ቅርጫፍ ማለት ነው።
ኔትዘሬት ማለት ቅርንጫፍ የሚከፈልበት ቦታ ነው።
ናዛራ ማለት እውነት ነው።
ኔትዘሬት እና ናዛራ የሚሉት ቃላት በአንድ ላይ “እውነት እንደ ቅርንጫፍ የምታቆጠቁጥበት ቦታ” የሚል ትርጉም ይሰጡናል።
እነዚህ ቃላት ተጣምረው በብሉይ ኪዳን ዕብራይስጥ መጻሕፍት ውስጥ አይገኙም።
ናዝሬት የሚለው የግሪክ ቃል ኔትዘሬት እና ናዛራ የሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት ጥምረት ውጤት ነው።
ከዚያም በመጨረሻ የመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን እምነት መመለስ አለበት። ዋስትና ያለው የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ብቻ ነው ምክንያቱም ባለ ራዕዩ ዮሐንስ ኢየሱስን ቆሞ ያየው በዚያ ዘመን ቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ ነው።
የሐዋርያቱ የመጀመሪያ የቤተክርስቲያን ዘመን ብቻ ነው እውነቱን የተቀበለው። ስለዚህ እውነትን ማግኘት ከፈለግን ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን መመለስ አለብን።
የዘመን መጨረሻ ላይ ያለው የንስር እይታ ከሐዋርያቱ የመጀመሪያ የአንበሳ እምነት ጋር መስማማት አለበት።
ማርቆስ 14፡68 እርሱ ግን፦ የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ።
ጴጥሮስ ሴትየዋ ስትጠይቀው ስለ ማን እንደምታወሪ አልገባኝም አለ።
ዛሬም የቤተክርስቲያን መሪዎች ያለባቸው ትልቅ ችግር የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት አለመረዳታቸው ነው።
የቤተክርስቲያን መሪዎች ለማብራራት ከባድ ስለሆኑ ጥቅሶች ሲጠየቁ ምንም የማይጠቅሙ ዝርዝር ጉዳዮች ናቸው ብለው ያጣጥሉዋቸዋል።
ነገር ግን እነርሱ እንደሚሉት የማይጠቅሙ ዝርዝሮች ከሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምን እንደበዙ ማብራራት አይችሉም።
ስለዚህ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሶችን በተመለከተ አለማወቃቸውን ለመሸፋፈን ብለው እየዋሹ ናቸው።
ጴጥሮስ ከዚያ ቤት ውስጥ ወጥቶ ሄደ። የቤተክርስቲያን መሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነ አስተምሕሮ ይገነባሉ ምክንያቱም አስተምሕሮዎቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ብቻ በመጠቀም ሊረጋገጡ አይችሉም።
በዚህ መንገድ የዘመናችን ቤተክርስቲያን መሪዎች ሐዋርያት ከመሰረቱት ከመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን እምነት ወጥተው ርቀው ሄደዋል። ሐዋርያት ስላሴ የሚል ቃል ተጠቅመው አያውቁም፤ ሲያጠምቁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው ያጠመቁት (የሐዋርያት ሥራ 2፡38)።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም የአብ፣ የወልድ፣ እና የመንፈስ ቅዱስ ስም መሆኑን ተረድተዋል።
ይህ መሰረታዊ እውነት የምንድነው በጸጋ አማካኝነት በእምነት መሆኑን በተሰበከበት በአምስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በነበረው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ወቅት ተረስቶ ስለነበረ ማንም አልተቀበለውም።
ሰርቬተስ ጠንካራ የስላሴ ተቃዋሚ ነበረ፤ ጆን ካልቪን የተባለው ታላቅ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ መሪ ሰርቬተስን በአደባባይ በእሳት እንዲቃጠል አድርጓል። ዙሪክ ውስጥ የነበረው ታዋቂ የተሃድሶ መሪ ዝዊንግሊ የአናባፕቲስቶች መሪ የነበረውን ፈሊክስ ማንዝ የተባለ ሰው ውሃ ውስጥ ሰምጦ እንዲሞት አድርጓል ምክንያቱም ደግሞ ፈሊክስ ማንዝ በውሃ ውስጥ በመጥለቅ መጠመቅን በማመኑ ነው። ዝዊንግሊ ሕጻናትን ውሃ በመርጨት በማጥመቅ ነበር የሚያምነው። ከሰው ጋር በሃሳብ አለመስማማታችንን ለመግለጽ እነዚህን ድርጊቶች መፈጸም የለየለት ጭካኔ ነው።
ማርቆስ 14፡69 ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት፦ ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር።
ከዚያም ጴጥሮስ ለሁለተኛ ጊዜ ካደ።
በዓለም አቀፉ የወንጌል ስርጭት ዘመን ሰባኪዎች መዳን የሚቻለው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በማመን ብቻ እንደሆነ አስተምረዋል። ትኩረታቸውን በሙሉ በኢየሱስ ላይ አድርገዋል፤ ሆኖም ግን ኢየሱስ ሁሉን ቻይ ጌታ እግዚአብሔር መሆኑን ክደዋል። የዚያ ዘመን ሰባኪዎች በስላሴ ቢያምኑም እንኳ በስላሴ የማያምኑ ክርስቲያኖች ላይ ጥላቻ አልነበራቸውም።
“የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ” ኢየሱስ ሁሉን ቻይ መሆኑን ይገልጣል።
ራዕይ 1፡8 ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፦ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።
የጴጥሮስ ሁለተኛ ክሕደት በጣም ለአጭር ጊዜ ነበር። በስድስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የተነሱት የወንጌል ሰባኪዎች በስላሴ በማያምኑ ክርስቲያኖች ላይ ብዙም ጥላቻ አልነበራቸውም።
ማርቆስ 14፡70 እርሱም ደግሞ ካደ።
ጆን ዌስሊ ካስተማረው የወንድማማች መዋደድ ትምሕርት ተጽእኖ የተነሳ ክርስቲያኖች ከማይስማሟቸው ሰዎች ጋር ሲገጥሙ ለጥላቻና ለግፍ አይነሳሱም ነበር።
ከዚያ በኋላ ወደ መጨረሻው ወይም ሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን እንመጣለን።
ማርቆስ 14፡70 ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን፦ የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት።
የጴጥሮስ ሶስተኛ ክሕደት የመጨረሻውን የሎዶቅያውያንን የቤተክርስቲያን ዘመን ይወክላል (ሎዶቅያ ማለት የሕዝቡ መብት ማለት ነው)። ዛሬ ሙሽራዋ ማለትም ልባሞቹ ቆነጃጅት የሚናገሩት ስሕተትና እንከን በሌለው ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጡት ሚስጥራት ቋንቋ በመጠቀም ነው። እነዚህ ልባም አማኞች ወሳኝ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በማገናኘት እምነታቸው ትክክለኛ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣሉ።
ዊልያም ብራንሐም የሚለውን ስም ከጠቀሳችሁ በኋላ ብዙ ሰዎች በቁጣ ጸጉራቸው ይቆማል፤ የዘመናችን ክርስቲያኖችም በስላሴ የማያምኑ ሰዎችን እና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚያጠምቁ ሰዎችን ሲቃወሙ አንደበታቸውን መቆጣጠር እንኳ አይችሉም።
ማርቆስ 14፡71 እርሱ ግን፦ ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ።
በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን ውስጥ የስላሴ ትምሕርትን ብትቃወሙ ሰነፎቹ ቆነጃጅቶች በጣም ይናደዱና ከቤተክርስቲያናቸው ያስወጡዋችኋል።
ቄስ ወይም አገልጋይ ወይም ሪቨረንድ ወይም ፓስተር የቤተክርስቲያን ራስ አይደለም አትበሉ። በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ማንም ሰው የቤተክርስቲያን ራስ ተብሎ ተጠርቶ አያውቅም። የዛሬዎቹ ቤተክርስቲያኖች ግን እንዲህ ዓይነቱን ንግግር አይቀበሉም።
አስተምሕሮ ማዘጋጀት የአስተማሪ ሥራ ነው
63-0724 እግዚአብሔር ሰውን አስቀድሞ ሳያስጠነቅቀው ወደ ፍርድ አያቀርበውም
አስተማሪ የተለየ ሰው ነው። አስተማሪ ተቀምጦ በመንፈስ ቅዱስ ቅባት ከረሰረሰ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት ወስዶ ይገጣጥምና ያስተምራል፤ በዚህ አገልግሎት ፓስተርም ሆነ ወንጌላዊ ከአስተማሪ ጋር አይተካከልም።
ሰነፎቹ ቆነጃጅት እንዲህ ዓይነቱን ንግግር መቀበል አይችሉም።
1ኛ ቆሮንቶስ 12፡28 እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ሲመሰርታት ሐዋርያትን (የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን የጻፉትን) እና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን የጻፉትን ነብያት እንዲሁም ለአሕዛብ ቤተክርስቲያን የተላከውን የዘመን መጨረሻ ነብይ ተጠቅሟል፤ ይህም ነብይ ወደ ሐዋርያቱ የመጀመሪያ ቤተክርስቲያን ዘመን እምነት ይመልሰናል።
ማቴዎስ 17፡11 ኢየሱስም መልሶ፦ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤
ከዚያም ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የወንድም ብራንሐምን ንግግሮች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ወስደው እርሱ የተናገረውን ከብሉይ ኪዳን እና ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንዲያረጋግጡ እግዚአብሔር አስተማሪዎችን ይጠቀማል። ለራሳችሁ የምታመሰኩ ከሆናችሁና የአስተምሕሮውን ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ውስጥ ማየት ከቻላችሁ የነብያትና የሐዋርያት ትምርት ሸሆናው የተሰነጠቀ እና ለመብላት ንጹሕ እንደሆነ እንስሳ (አስተምሕሮ) ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እምነቱ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ የሚችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።
64-0823M ጥያቄዎችና መልሶች 1
ቃሉን በሙላት መቀበል የሚችሉ ግን እኔ ስለሰበክሁ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ስለተናገረ ይቀበላሉ። የሚቀበሉ ሁሉ ለመቀበል ነጻ ናቸው ምክንያቱም ቃሉ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል።
የ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ማብራሪያ - ምዕራፍ 9 - የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ዘመን
…እውነተኛ ነብይ ሁልጊዜ ሰዎችን ወደ ቃሉ በመምራት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያስተሳስራቸዋል እንጂ ለሕዝቡ እኔን ፍሩኝ አይልም ወይም ንግግሬን ፍሩ አይልም፤ ቃሉ የሚናገረውን ብቻ እንዲፈሩ ነው የሚያስተምራቸው።
62-0318 የተነገረው ቃል የመጀመሪያው ትክክለኛ ዘር ነው - 2
አሁን እነዚህ የተናገርኳቸው ነገሮች በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙ ከሆኑ ወይም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይገጥሙ ከሆኑ በሙሉ ስሕተት ናቸው።
65-0801 የዚህ ክፉ ዘመን አምላክ
... ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ለዚህ ሰዓት የሰጠኝን መልእክት ያመኑ ሰዎች በአሁኑ ሰዓት ምን እየተፈጸመ እንዳለ ያውቁ ዘንድ እና በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ይረዱ ዘንድ።
አስተምሕሮ እውነት የሚሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ መርምራችሁ ስታረጋግጡት ብቻ ነው እንጂ የሰውን ንግግር ስትተረጉሙ አይደለም።
የፓስተር አገልግሎት በቤተክርስቲያን ውስጥ የሰዎችን የግል ችግሮች እና በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት ነው።
63-0724
ነገር ግን አያችሁ በቤተክርስቲያን ውስጥ ፓስተሩ አለ፤ ፓስተሩም ልዩ ሰው ነው። የሰዎችን ጭንቀት መሸከም እንዲችል የተዘጋጀ ሰው ነው። ሸክም ተሸካሚ ሰው ነው፤ የሕዝቡን ቀምበር መሸከም የሚችል በሬ ነው። ፓስተሩ ሰው ከሰው ጋር ወይም አንድ ቤተሰብ ከሌላ ቤተሰብ ጋር ተጣልቶ ሳለ (ለማናቸውም ሳይወግን) ከሁለታቸውም ጋር አብሮ መቀመጥና ሁለቱንም አነጋግሮ ወደ እርቅ ማምጣት የሚችል ሰው ነው። አያችሁ? እርሱ ፓስተር ነው፤ እንዴት ችግር መፍታት እንደሚችል ያውቃል።
የሰዎችን የግል ችግሮች አዳምጦ መፍታት የፓስተሮች አገልግሎት ነው።
ማርቆስ 14፡72 ጴጥሮስንም ኢየሱስ፦ ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።
ዶሮው ሁለተኛ ጊዜ መጮሁ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለሁለተኛ ጊዜ ተገልጠው ሰባተኛዋን ቤተክርስቲያን በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ወደነበረው ሐዋርያዊ ትምሕርቶች እንደሚመልሷት ያመለክታል።
በእያንዳንዱ ጥያቄ ውስጥ “የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ይህንን ታምን ነበር?” እያልን መጠየቅ አለብን።
ሰነፎቹ ቆነጃጅት ሁልጊዜ እየተገለጠ የመጣውን እውነት እየካዱ ይኖራሉ።
በመጀመሪያ ተምረውት የነበረውን ብቻ ይዘው ወደ ፊት መራመድን እምቢ ይላሉ። እያንዳንዱ ሰው እሱ የሚሄድባት ቤተክርስቲያን ብቻ እውነቱን እንደያዘች ያምናል።
እምነታቸውን ከኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማረጋገጥ እንዳለባቸው ማመን ትተዋል።
ከዚህም የተነሳ ወደ ታላቁ ውስጥ ይገባሉ፤ በዚያም ብዙ ለቅሶ ይሆናል።
ማቴዎስ 8፡12 የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
ይህ ሁሉ ቤተክርስቲያንን እና የቤተክርስቲያን መሪን ከእግዚአብሔር ቃል የማስቀደም አሳዛኝ ውጤት ነው።