ማርቆስ 10 ፍቺ እና እንደገና ማግባት ዝሙት ነው



ሕጋዊ የሆነ የጋብቻ መሃላ የሚፈታው በሞት ብቻ ነው። የኤድን ገነት ውስጥ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ባለትዳሮች አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ነበሩ። ወደ መጀመሪያው መመለስ አለብን።

First published on the 2nd of December 2022 — Last updated on the 17th of December 2022

ፈታችሁ ሌላ ሰው ማግባት አትችሉም

 

እግዚአብሔርን ሰው በሆነው በኢየሱስ አይተነዋል።

ሴት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት።

ስለዚህ ጋብቻ እግዚአብሔር ከእውነተኛዋ የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ጋር ያለውን ሕብረት ይወክላል።

ከዚህም የተነሳ ኢየሱስ ለአሕዛብ የጋብቻን መመሪያ ለውጧል።

የጋብቻ ቃልኪዳናችሁን ለዘላለም መጠበቅ አለባችሁ። እናንተ ወይም የትዳር አጋራችሁ እስኪሞቱ ድረስ መፍረስ የለበትም። ቃላችሁን መጠበቅ አለባችሁ።

የእግዚአብሔር ሙሽራ አካል እንደመሆናችሁ የእግዚአብሔርንም ቃል መጠበቅ አለባችሁ።

ዛሬ ከኤድን ገነት ጋር የምንገናኝበት ብቸኛ መንገድ ጋብቻ ነው። ኤድን ገነት ውስጥ ከነበሩ ነገሮች በእኛ ዘንድ ሳይጠፋ እስከ ዛሬ የቀረው ጋብቻ ብቻ ነው። ስለዚህ ለጋብቻ እግዚአብሔር በኤድን ገነት ውስጥ ወደ መሰረታቸው የመጀመሪያ ሁኔታዎች መመለስ አለብን።

በሌላ አነጋገር ጋብቻን ጠበቅ አድርገን ነው መያዝ ያለብን።

ማርቆስ 10፡1 ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ ደግሞም ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ እንደ ልማዱም ደግሞ ያስተምራቸው ነበር።

ከዮርዳኖስ ማዶ ያለው ምድር ከዮርዳኖስ ወንዝ በቀኝ በኩል የሚገኘው ሃገር ነው።

አቅጣጫዎች የሚወሰኑት ከኢየሩሳሌም አንጻር ነው።

ይህ አካባቢ የአሕዛብ መኖሪያ ነው።

ወደ ዮርዳኖስ ከቀኝ በኩል በመምጣት ኢየሱስ ወደፊት በ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ስለሚያደርገው አገልግሎት አጽንኦት እየሰጠ ነው።

 

 

ማርቆስ 10፡2 ፈሪሳውያንም ቀርበው፦ ሰው ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት።

ብሉይ ኪዳን ውስጥ “ፈሪሳውያን” የሚል ቃል የለም። ፈሪሳውያን በአይሁድ ሕዝብ ላይ በመሪነት ለያዙት ስልጣናቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ስለሌላቸው ከኢየሱስ የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ፈርተዋል፤ ምክንያቱም እውነተኛው ራስ ኢየሱስ ነው።

የአይሁድ መሪዎች እውነትን አይፈልጉም። እነርሱ የሚፈልጉት ኢየሱስን በነገር ማጥመድ ነው። ፈሪሳውያን ሐሰተኛ የሐይማኖት መሪዎች ስለሆኑ ሁልጊዜ ኢያሱስን ማሳጣትና ሐሰተኛ ማስባል ነው ጥረታቸው፤ እርሱ ግን እውነተኛው መሪ እና የአይሁዶች ራስ ነው።

ልክ እንደዚሁ ፓስተርም አዲስ ኪዳን ውስጥ የቤተክርስቲያን መሪ እንዲሆን ስልጣን አልተሰጠውም፤ ደግሞም የመንጋው እረኛ ተብሎም አያውቅም። ስለዚህ ፓስተሮች ስለ ስልጣናቸው ስጋት ይሰማቸዋል፤ ከዚህም የተነሳ የሽማግሌዎች ሕብረት ቤተክርስቲያንን በኃላፊነት እንደሚመሩ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መቀበል አይፈልጉም።

የሐዋርያት ሥራ 20፡17 ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤

የሐዋርያት ሥራ 20፡28 በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

 

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ስለዚህ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ የዛሬዋ ቤተክርስቲያን እውነተኛ ራስ ነው።

ከጥንትም ጀምሮ የእግዚአብሔር ዓላማ ከአሕዛብ የሆነችዋን ቤተክርስቲያን ማግባት ነው፤ እርሷንም ሙሽራ ብሎ ይጠራታል።

ይህም የጋብቻና የፍቺ ጥያቄ አስነሳ።

ማርቆስ 10፡3 እርሱ ግን መልሶ፦ ሙሴ ምን አዘዛችሁ? አላቸው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሙሴ ምን ብሎ ነበር?

ማርቆስ 10፡4 እነርሱም፦ ሙሴስ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ አሉ።

የፍች ወረቀት ፈርሞ ማባረር ብቻ ነው።

ማርቆስ 10፡5 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ።

ኢየሱስ ሲመልስላቸው ፍቺ የተፈቀደው በልብ ድንዳኔ ምክንያት ነው አለ።

ማርቆስ 10፡6 ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤

እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ጀምሮ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ተጋብተው የክርስቶስ እና የሙሽራይቱ ምሳሌ እንዲሆኑ ነው ዓላማው። እግዚአብሔር በመጀመሪያ የፈጠረው አዳምንና ሔዋንን ነው።

የኤድን ገነት ውስጥ ሐጥያት ከገባ ወዲህ ግን በጋብቻ ጸንቶ መኖር በጣም አስቸጋሪ ነገር እየሆነ መጥቷል።

ስለዚህ እናት እና አባታችሁ በትዳራችሁ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ ከወላጆቻችሁ ቤት ውጡ። ወላጆቼ ጣልቃ መግባትና የልጃቸውን ትዳር መምራት ይወዳሉ። የቤት ራስ ባል ነው እንጂ የባልየው አባት ወይም እናት አይደሉም።

ነገር ግን አንዳንድ ወላጆች የልጆቻቸውን ጋብቻ መቆጣጠር ይፈልጋሉ።

ማርቆስ 10፡7 ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥

አንድ ሰው የቤተሰቡ ራስ መሆኑን ለማረጋገጥ ከቤቱ መውጣት አለበት።

ከዚያም ሰው በመከራም ሆነ በደስታ ጊዜ ከሚስቱ ጋር መሆን አለበት። በመልካም ጊዜም ይሁን በሃዘን ጊዜ፤ በጤናም ይሁን በሕመም ጊዜ ሁሉ ከሚስቱ መለየት የለበትም።

ማርቆስ 10፡8 ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም።

አካልን የሚቆጣጠረው አእምሮ ነው። ሰው ሁልጊዜ ለአካሉ መልካም የሆነ ነገርን እየመረጠ ነው የሚያደርገው። ልክ እንደዚሁ አንድ ሰው እና ሚስቱ በአንድ ልብ ተስማምተው አንዳቸው ለሌላው የሚጠቅመውን እያሰቡ አብረው መኖር አለባቸው። የትዳር አጋራቸውን የራሳቸው አካል እንደሆኑ አድርገው ነው ማየት ያለባቸው።

ማርቆስ 10፡9 እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።

ሕጋዊ የሆነ የጋብቻ መሃላ በሞት ካልሆነ በቀር ሊሻር አይችልም።

ፍቺ መልካም አማራጭ አይደለም። አብረው ሊኖሩ ካልቻሉ መለያየት ነው ያለባቸው፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ለመታረቅ መፈለግ አለባቸው።

ሔዋን ሐጥያት ሰራች፤ እግዚአብሔርም ሊገድላት ይፈቅድ ነበር፤ በዚህም የጋብቻ ቃልኪዳኗ ይሻራል።

ሮሜ 6፡23 የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤

አዳም ግን በጣም ይወዳት ስለነበረ አብሯት ሐጥያት መስራትና ከእርሷ ጋር መሆንን መረጠ፤ ይህንንም ያደረገው እግዚአብሔር በሆነ መንገድ ሊያድናቸው እንደሚችል በማመን ነው። እግዚአብሔርም እነርሱን ከኤድን ገነት በማባረርና አንድ እንስሳ ገድሎ በደሙ እና በእንስሳው ቆዳ አማካኝነት አዳናቸው። እነርሱ ለሰሩት ሐጥያት ንጹሃን እንስሳት ዋጋ ከፈሉ።

ቤተክርስቲያን ሐጥያት ሰራች፤ ኢየሱስ ግን በጣም ስለወደደን ስለ እኛ ሐጥያት ሆኖ ሐጥያታችንን ተሸክሞ በቀራንዮ መስቀል ሞተ። ንሰሃ ስንገባ ሐጥያታችን ከእኛ ወደ እርሱ ይሻገራል፤ የእርሱ ንጽሕና ደግሞ ከእርሱ ወደ እኛ ይሻገራል።

እርሱ ስለ እኛ ሞተና እኛ ከእርሱ ጋር እንኖር ዘንድ ሐጥያታችንን ከእኛ አራቀ።

በክርስቶስ እና ከአሕዛብ በሆነችው ቤተክርስቲያን መካከል የተደረገው የጋብቻ ቃልኪዳን አይሻርም።

እግዚአብሔር ሰዎችም ከሚስታቸው ጋር ያደረጉትን የጋብቻ ቃልኪዳን እንዲያከብሩ ይጠብቃል። አንድ ወንድ ከአንዲት ሚስት ጋር ለዘላለም።

ማርቆስ 10፡10 በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር ጠየቁት።

የጥንቷ ቤተክርስቲያን አባላት በሰው ቤቶች ውስጥ እየተሰባሰቡ ጉዳዮቻቸውን በነጻነት ይወያዩ ነበር።

የቤተክርስቲያን ሕንጻ በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው በ220 ዓ.ም ነው። የጥንቷ ቤተክርስቲያን ቤተመቅደሱ እና የኢየሩሳሌም ከተማ ከመደምሰሳቸው በፊት እስከ 70 ዓ.ም ድረስ ኢየሩሳሌም ውስጥ በሰዎች ቤት ወይም ቤተመቅደሱ ውስጥ ነበር መሰብሰቢያዋ። ሌሎች ከተሞች ውስጥ የነበሩ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ በሰዎች ቤት እና በክፍት ሥፍራዎች ነበር የሚሰበሰቡት። በሮም የነበሩ ክርስቲያኖች በዋሻዎችም ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር።

ማርቆስ 10፡11 እርሱም፦ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤

ኢየሱስ በጥብቅ ነው የተናገረው። በአንድ ሰው እና በአንዲት ሴት መካከል የተደረገ የጋብቻ ቃልኪዳን በደስታ ጊዜም ይሁን በሐዘን ሊፈርስ አይችልም፤ የሚፈርሰው ከሁለት አንዳቸው ሲሞቱ ብቻ ነው።

አንድ ሰው በሕግ ያገባትን ሚስቱን ቢፈታ ሌላ ሴት ማግባት አይችልም። ይህ ዝሙት ነው።

ማርቆስ 10፡12 እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።

ልክ እንደዚሁ ሴትም ባሏን ብትፈታ ሌላ ሰው ማግባት አትችልም፤ ሌላ ሰው ካገባች ዝሙት ነው።

 

ሕጻናት ልጆች የመጨረሻውን ዘመን አማኞች ይወክላሉ

 

በስተመጨረሻ መንፈሳዊ ልጆች ቃሉን ወደጻፉ ወደ ሐዋርያዊ አባቶች እምነት መመለስ አለባቸው።

ማርቆስ 10፡13 እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው።

ሐዋርያት እንኳ ሕጻናትን ወደ ኢየሱስ ማለትም ወደ ቃሉ የማምጣትን አስፈላጊነት ሊረዱ አልቻሉም።

በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን አማኞች የእምነታቸውን ትክክለኛነት ከእግዚአብሔር ቃል ማለትም ከኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያረጋግጡ ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን አያውቁም።

የቤተክርስቲያን አባቶች የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ዘመን ሐዋርያት ናቸው።

ወጣቶቹ ደግሞ ከጨለማው ዘመን በኋላ ጽድቅ በእምነት የመሆኑን እውነት በ5ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ወደ ቤተክርስቲያን መልሰው ያመጡ የተሃድሶ መሪዎች እና ቅድስና እና የወንጌል አገልግሎትን በ6ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን መልሰው ያመጡ የተሃድሶ መሪዎች ናቸው።

 

 

ከዚያ በኋላ ጴንጤቆስጤያዊ ልጆች በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን መልሰው አመጡ።

ከዚያ በኋላ ዊልያም ብራንሐም የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት ይችሉ ዘንድ ለሕጻናት የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት ገለጠ።

ለዚህ ነው እጁን ጭኖ ይዳስሳቸውና ይባርካቸው ዘንድ ሕጻናትን ወደ ኢየሱስ ያመጧቸው።

በመጨረሻው ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መገለጥ የሚዳሰሱትና የሚባረኩት ሕጻናት ናቸው። በመጨረሻው በንስር ዘመን ወደ መጀመሪያው ወደ አንበሳው የቤተክርስቲያን ዘመን ወደ አባቶች የሚመለሱት ሕጻናት ብቻ ናቸው።

 

 

ማርቆስ 10፡14 ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና፦ ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና።

ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን አባቶች እምነት የሚመለሱ ሕጻናት የዘመን መጨረሻ ቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቅ አትኩሮት የሚደረገው በእነርሱ ላይ ነው።

ማርቆስ 10፡15 እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው።

የእግዚአብሔር መንግስት ማለት መንፈስ ቅዱስ በውስጣችሁ መኖሩ ነው።

ሉቃስ 17፡21 ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው

በእያንዳንዱ ዘመን ሰዎች ለዚያ ዘመን መንፈስ ቅዱስን መታዘዝ አለባቸው።

በ5ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በሉተር የቤተክርስቲያን ዘመን ሰዎች በእምነት ለመዳን መታዘዝ ነበረባቸው።

በ6ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በዌስሊ ዘመን ሰዎች በቅድስና ለመኖርና ወንጌልን ለመስበክ መታዘዝ ነበረባቸው።

በ7ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቅ ምልክት የሆኑት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሰው መጡ።

በ7ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ማብቂያ አካባቢ በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቃችሁ ማስረጃ እንዲሆን የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መረዳት አለባችሁ።

ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤

ማርቆስ 10፡16 አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው።

እውነትን መረዳት ለቤተክርስቲያን አልተሰጣትም። በመጨረሻው ዘመን ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን ደጅ ውጭ ቆሞ ነው ያለው።

ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦

ራዕይ 3፡20 እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤

እያንዳንዱ ልጅ ኢየሱስን በግሉ ማግኘት አለበት።

የእውነትን መገለጥ ማግኘትና ከኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማረጋገጥ አለባችሁ ምክንያቱም ኢየሱስ ቃሉ ነው። እያንዳንዱ ሕጻን ኢየሱሰን ያቅፋል። ይህ የቤተክርስቲያን ልምምድ አይደለም። ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን መውደድና የሚለውን መቀበል አለባችሁ። የእግዚአብሔርን ቃል ከሰዎች አመለካከት ሁሉ በላይ መቀበል አለባችሁ። ደቀመዛሙርት ሕጻናትን ወደ ኢየሱስ እንዲያመጡ ተነገራቸው። የሜሴጅ ሰባኪዎች ከሰው ንግግር የወሰዷቸውን ጥቅሶቻቸውን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ አምጥተው እምነታቸውን ከእግዚአብሔር ቃል ማረጋገጥ አለባቸው። ዛሬ ኢየሱስን የምናየው እንደ ተገለጠው ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

 

ለ10ቱ ትዕዛዛት የተሰጠ አዲስ አተረጓጎም

 

ማርቆስ 10፡17 እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው።

ኢየሱስን “ቸር መምሕር” ብሎ በመጥራት ሰውየው ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን እየመሰከረ ነው።

ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን ማመኑ ሰውየው በአንድ አምላክ ብቻ ማመኑን ያስረዳል፤ ይህም የመጀመሪያው ትዕዛዝ ነው።

ይህ ሰው “ሮጦ” መጣ። ሰውየው በሰው እጅ ወደተሰራ ወደተቀረጸ ምስል አልመጣም፤ ይህ በሁለተኛው ትዕዛዝ ተከልክሏል። በቀጥታ ወደ ዋናው ምንጭ ወደ እግዚአብሔር መጥቶ ነው የተንበረከከው።

ይህ ሰው የእግዚአብሔር ስም ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አውቋል። የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ የሚለው ሶስተኛው ትዕዛዝ ትርጉሙ ይህ ነው። ቤተክርስቲያኖች አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ የተባሉ ሶስት ማዕረጎች የእግዚአብሔር ስም ናቸው በማለት የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ ይጠራሉ።

የመጀመሪያዎቹ ሶስት ትዕዛዛት ከመለኮት ጋር የተያያዙ ናቸው።

ሰውየው መለኮትን በተመለከተ በትክክል ስለተረዳ ኢየሱስ ስለ መጀመሪያዎቹ ሶስት ትዕዛዛት አላነሳለትም።

ማርቆስ 10፡18 ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።

“ቸር” የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ “ጉድ” ነው። ዛሬ በእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሃገሮች ውስጥ ክርስቲያኖች “እንዴት ነህ/ሽ?” ተብለው ሲጠየቁ “አይ አም ጉድ” ይላሉ።

ይህም ኢየሱስ ሲናገር ማንም ቸር የለም ካለው ጋር ይቃረናል። ስለዚህ ማሕበረሰቡ ያመጣውን አዲስ የአነጋገር ፋሽን ተከትለን ልንስት እንችላለን።

4ኛው ትዕዛዝ የሰንበት እረፍትን በተመለከተ ነው። ብሉይ ኪዳን ውስጥ ይህ ቅዳሜ ዕለት ከስራ የሚደረግ እረፍት ነው።

በአዲስ ኪዳን ይህ እረፍት ከሐጥያት በሚደረግ እረፍት ተለውጧል፤ እረፍቱም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው።

ኢሳይያስ 28፡11 በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ እርሱም፦ ዕረፍት ይህች ናት፥

የበዓለ ሃምሳ ዕለት ደቀመዛሙርት በሌሎች ልሳናት ተናገሩ። ይህም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው።

ኢሳይያስ 28፡12 የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም ማረፊያ ናት አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ።

እግዚአብሔር የፍጥረትን ሥራ ከጨረሰ በኋላ አረፈ። ከዚያ በኋላ ሁለተኛ ወደ መፍጠር ሥራ አልተመለሰም።

ዕብራውያን 4፡10 ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።

አይሁዶች ሥራ ሰርተው በሰንበት ዕለት ያርፉ ነበር፤ ከዚያም እሁድ ዕለት ወደ ሥራ ይመለሳሉ። እግዚአብሔር ግን ከእረፍቱ በኋላ ወደ ሥራ አልተመለሰም፤ ስለዚህ የአይሁዶች ሰንበት እንከን ነበረው።

ወደዚህ እውነተኛ እረፍት ልንገባ የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካኝነት ብቻ ነው። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የሐጥያትን ሥራ ከመስራት ያሳርፈንና ሐጥያት የመስራት ፍላጎትን ከእኛ ላይ ያነሳዋል። በዚህም ምክንያት ሐጥያት ወደ መስራት አንመለስም።

አይሁዳዊው ሰውዬ ይህን መረዳት አይችልም፤ ስለዚህ ኢየሱስ ስለ አራተኛው ትዕዛዝ አልተናገረም።

ቀሪዎቹ ስድስት ትዕዛዛት የሚከተሉት ናቸው፡-

ዘጸአት 20፡12 (6) አባትህንና እናትህን አክብር፤

(6) አትግደል።

(7) አታመንዝር።

(8) አትስረቅ።

(9) በሐሰት አትመስክር።

(10) አትመኝ፤

እነዚህ ትዕዛዛት ለቤተክርስቲያን ጠቀል ያለ ትርጉም አላቸው።

(5) መንፈሳዊ አባቶቻችን ሐዋርያት ሲሆኑ እናት ቤተክርስቲያናችን የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ቤተክርስቲያን ናት። አባቶቻችን ያምኑ የነበሩትን ወደ ማመን በመመለስና ከእነርሱ ጋር ባለመቃረን እናከብራቸዋለን።

(6) በ325 ዓ.ም በኒቅያ ጉባኤ እንደ ስላሴ፣ አብ እና ወልድ አንድ ባህሪ ናቸው፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ የመለኮት ሁለተኛው አካል፣ አንድ አምላክ በሶስት አካላት፣ እና የስቅለት አርብ የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኙ ቃላትን በማስገባት የእውነትን ፍቅር ገደሉ።

(7) የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጨለማው ዘመን አውሮፓን ስትገዛ ቆየችና ራሷን እናት ቤተክርስቲያን ብላ ጠራች። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምታስተምራቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምሕርቶች ማመን ከእርሷ ጋር ዝሙት መፈጸም ነው።

(8) ማርቲን ሉተር መዳን በእምነት ብቻ ነው ብሎ አስተማረና ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወጣ። ነገር ግን ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንደ ስላሴ፣ ሕጻናትን ውሃ በመርጨት ማጥመቅ፣ ማጽናት፣ ካተኪዝም፣ እና “በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ” እያሉ ማጥመቅ (ይህ መጠሪያ የእግዚአብሔር ስም ይመስል) እና የመሳሰሉ ሃሳቦችን ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሰርቆ ወጣ። ሉተር የእግዚአብሔር ስም ማን እንደሆነ አብራርቶ አያውቅም።

(9) ጆን ዌስሊ ቅድስና ወይም መልካም ሥራን ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ አመጣ። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰዎች መዳናቸው በእምነት እና በመልካም ሥራ ላይ የተመሰረተ መሰላቸው። ይህም ሐሰተኛ ምስክር ነው። መልካም ሥራዎች ማንንም ማዳን አይችሉም። ሆኖም መልካም ሥራ መስራት ይጠበቅብናል።

(10) የማንንም ሰው ንብረት አትመኝ።

ከዚህም ጠለቅ ባለ መልኩ የማንንም አገልግሎት አትመኝ።

መጽሐፍ ቅዱስን ከአንተ የተሻለ ማስተማር የሚችለው ሰውን አገልግሎት ቀምተህ ብትወስድ ሕዝቡን ትበድላቸዋለህ ምክንያቱም መማር የሚገባቸውን እውነት መማር አይችሉም።

ፓስተሮች በጉባኤው ወይም በምዕመናን ላይ ያላቸውን ስልጣን ላለማስነካት ብለው የማስተማር አገልግሎት ውስጥ ለመግባት ይመኛሉ። ከዚያ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት ከእነርሱ በላይ መረዳት የሚችሉ አስተማሪዎችን ዝም ያሰኛሉ። ፓስተሮች ከእነርሱ ጋር ለማይስማሙ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች መድረካቸውን ይከለክላሉ። ነገር ግን ፓስተሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት በአግባቡ መግለጥ አይችሉም። ፓስተሮች የቤተክርስቲያን ራስ እና አስተማሪዎች ለመሆን ራሳቸውን ከፍ ከፍ ስለሚያደርጉ ኒቆላውያን ናቸው። ፓስተሮች አስራት እየሰበሰቡ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ያላመነችባቸውን ሰው ሰራሽ ትምሕርቶች በማስተማር ሕዝቡን ያጭበረብራሉ

ራዕይ ምዕራፍ 4 ውስጥ በዙፋኑ ዙርያ አራት እንስሳት እንደቆሙ ተጽፏል።

 

 

እነዚህ 4ቱን ወንጌሎች ይወክላሉ።

ራዕይ 4፡6 በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ። በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ፥ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ።

7 ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል።

በምድር ላይ የእግዚአብሔር ዙፋን የሰው ልብ ነው። ኢየሱስ የሚኖረው በሰው ልብ ውስጥ ነው።

ኤፌሶን 3፡17 ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር

 

 

በሰው ልብ ውስጥ የሚገኙት አራቱ ክፍሎች በእግዚአብሔር ዙፋን ዙርያ ያሉትን አራቱን እንስሳት እንዲሁም በአንድ ላይ የክርስቶስን ሕይወት የሚገልጡትን 4ቱን ወንጌሎች ይወክላሉ።

 

 

ማርቆስ ኢየሱስን የገለጠው እንደ ጥጃ ወይም በሬ አድርጎ ነው፤ ይህም ሸክማችንን የሚሸከም በሬ ወይም ታላቅ አገልጋይ ማለት ነው።

እግዚአብሔርን እንዴት በትክክል ማገልገል እንደምንችል ማርቆስ ብዙ ፍንጮችን ይሰጠናል።

ማርቆስ 10፡19 ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው።

እግዚአብሔርን ማገልገል የምትፈልጉ ከሆነ የመጀመሪያው ስሕተታችሁ ሰው ሰራሽ ትምሕርቶችን የምትማሩበት ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል መሆናችሁ ነው። መጀመሪያ ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልማዶችና ከዲኖሚኔሽናዊ አስተሳሰቦች መራቅ አለባችሁ። ይህ መንፈሳዊ ዝሙት ነው። እግዚአብሔርን ማገልገል የሚፈልጉ ፕሮቴስታንቶች መጀመሪያ ኮሌጅ ይገባሉ (ይህ የካቶሊክ ሃሳብ ነው)፤ ኮሌጅም ውስጥ የአንድ ቤተክርስቲያን ልማዳዊ ትምሕርቶችን ይማራሉ። ከነዚህ ልማዳዊ ትምሕርቶች ውስጥ ስላሴ ይገኝበታል። ስለዚህ እግዚአብሔርን እናገለግላለን ብለው ቢነሱም ከመጀመሪያው ተበላሽተው ነው የሚጀምሩት።

ፕሮቴስታንቶች እግዚአብሔርን ማገልገል ሲፈልጉ መጀመሪያ የቤተክርስቲያን አባል ይሆናሉ። ከዚያም ስለ ስላሴ ይማራሉ። ከዚያ በኋላ ሕይወታቸውን ሁሉ በተሳሳተ መንገድ ይመላለሳሉ።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመሆንን ፍቅር ከገደሉ እንደ “ስላሴ” እንዲሁም “የስቅለት አርብ” የመሳሰሉ የኒቅያ ጉባኤ ካመጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌሉ ቃላት ራቁ።

ኤቮልዩሽን፣ ቢግ ባንግ፣ ኩዳዴ፣ ወይም የሰባት ዓመት መከራ እና የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቃቸውን ቃላት ከሌላ ቦታ ሰርቃችሁ አትጠቀሙ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ብቻ በታማኝነት ተጠቀሙ።

ወደ ራሳችሁ ወይም ወደ መልካም ሥራችሁ በማመልከት ሐሰተኛ ምስክር አትስጡ፤ ምክንያቱም መልካም ሥራችሁ ሰዎችን ሊያድን አይችልም።

ፓስተሮች የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ነን በማለት ሕዝቡን ማጭበርበር የለባቸውም። ፓስተሮች አስተማሪ ነን ካሉ ሕዝቡ ስለተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው ይቀራሉ።

63-0724 እግዚአብሔር ሰውን አስቀድሞ ሳያስጠነቅቀው ወደ ፍርድ አያመጣውም

አስተማሪ ልዩ ሰው ነው። የመንፈስ ቅዱስን ቅባት ተቀብሎ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን ማገጣጠም ይችላል፤ በዚህም ችሎታው ፓስተር እና ወንጌላዊ ሊወዳደሩት አይችሉም።

በስተመጨረሻ እናት እና አባትህን አክብር።

አባቶች የመጀመሪያውን የቤተክርስቲያን ዘመን ማለትም እናት ቤተክርስቲያንን የመሰረቱ ሐዋርያት ናቸው። እግዚአብሔርን በትክክል ማገልገል ከፈለግን የመጨረሻውን የቤተክርስቲያን ዘመን ወደ መጀመሪያው የቤተከርስቲያን ዘመን መመለስ አለብን።

ጠቃሚ አገልጋዮች መሆን ከፈለግን ከላይ የተጻፉትን ማሟላት ይጠበቅብናል።

 

ኢየሱስ በ10ቱ ትዕዛዛት ላይ ባልንጀራህን ውደድ የሚል ትዕዛዝ ጨመረ

 

ማቴዎስ ኢየሱስ በ7ቱ ዘመናት ውስጥ ላለችዋ የአሕዛብ ቤተክርስቲያን እንዲሁም በ3.5 ዓመቱ ታላቅ መከራ ውስጥ ለሚወጡት ለ144,000ዎቹ አይሁዶችም ንጉስ መሆኑን ገልጦ ነው የጻፈው።

ማቴዎስ 19፡18 እርሱም፦ የትኞችን? አለው። ኢየሱስም፦ አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥

19 አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።

ማቴዎስ ስለ 144,000ዎቹ አይዶችም ጭምር ስለ ጻፈ በስላሴ አስተምሕሮ አማካኝነት የእውነት ፍቅር ስለ መገደሉ በመናገር ነው የሚጀምረው። አይሁዶች እንደ ሕዝብ ስላሴን አይቀበሉም (አንዳንድ አይሁዶች የሆነ ቤተክርስቲያን አባል መሆን ስለሚፈልጉ ስላሴን ይቀበላሉ)። 144,000ዎቹ ግን ይህንን ትልቅ ስሕተት አይቀበሉም።

144,000ዎቹ አይሁዶች ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዲኖሚኔሽናዊ ሕብረት መራቅ አለባቸው፤ ምክንያቱም ይህ ሕብረት መንፈሳዊ ዝሙት ነው።

ስለ 144,000ዎቹ እንዲህ ተጽፏል፡-

ራዕይ 14፡4 ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና።

ሴት ቤተክርስቲያን ናት። 144,000ዎቹ እውነት የገባቸው ስለሆኑ የትኞቹም ቤተክርስቲያኖች ውስጥ አባል ሆነው አልገቡም። ስለዚህ ሁለቱ ነብያቶቻቸው እውነትን ያስተምሯቸዋል። የትኛውንም የቤተክርስቲያን ልማድ አይሰርቁም፤ የትኛውንም ዲኖሚኔሽናዊ ሃሳብ አይሰርቁም።

የታላቁ መከራ ግፍ እና ሰቆቃ ሐሰተኛ ምስክር ሆነው እራሳቸውን ማዳን እንደማይችሉ ያሳውቃል። ስለዚህ በራሳቸው ሥራ ሳይሆን ለሁለቱ ነብያት በተሰጣቸው ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል ይታመናሉ።

ሙሴ እና ኤልያስ ወደ መጀመሪያዎቹ ሐዋርያዊ አባቶች ትምሕርት እና ወደ መጀመሪያው ዘመን እናት ቤተክርስቲያን ምሳሌ ይመሩዋቸዋል።

በመቀጠል ኢየሱስ 10ቱ ትዕዛዛት ከእኛ የሚጠብቁትን የመልካም ሥራዎች አገልግሎት ጠቅለል አድርጎ ይናገራል።

“ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ማለት አይሁዶች ከአሕዛብ የሆኑ ክርስቲያኖችን እምነት ይቀበላሉ፤ ከዚያ ወዲያ ሁላችንም ባልንጀሮች እንሆናለን።

አይሁድ እና አሕዛብ ሁለት የተለያዩ ወገኖች ሆነው መታየታቸው ይቀራል። 144,000ዎቹ እምነታቸው ልክ እንደ እኛ እምነት ይሆናል፤ ደግሞም 144,000ዎቹ የአሕዛብ ቤተክርስቲያንን ይወዳሉ። እንደውም ለአሕዛብ ቤተክርስቲያን ጠባቂዎች ተደርገው ነው ተለይተው የሚወጡት።

መኃይለ መኃልይ 4፡12 እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት።

የክርስቶስ ሙሽራ በዙርያዋ አጥር እንዳላት እንደተቆለፈ ገነት ናት። ይህም አጥር ማለት 144,000ዎቹ የተመረጡ አይሁዶች ናቸው።

ኢየሱስ ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን አድርገን ስለ መውደድ ከመናገሩ ጋር ጠለቅ ያለ ሃሳብ እየገለጠ ነው። ይህ እውነት የሆኑ መልካም መመሪያዎችን በመታዘዝ እራስን ስለ መውደድና እራስን እንደ ጥሩ ክርስቲያን ስለ መቁጠር አይደለም።

ትክክለኛ ትርጉሙ እነዚያን መመሪያዎች በመከተል ከቤተክርስቲያን ስሕተቶች መራቅና ለሌሎች ሰዎች ጠቃሚ አገልጋይ ለመሆን ሌሎች ሰዎችን ስለ መውደድ ነው። እግዚአብሔር ክርስቲያን እንድንሆን የፈለገው መልካም የሆነ ኑሮ ኖረን ከዚያም መንግስተ ሰማይ እንድንገባ አይደለም። ክርስቲያኖች እንዲህ እያሉ ያስባሉ፡- “አቤት ታድዬ፤ መንግስተ ሰማይ እገባለው እኮ”።

ይህ ትክክለኛው አስተሳሰብ አይደለም።

እግዚአብሔር ክርስቲያን እንድንሆን የፈለገው ሌሎችን አገልግለን ወደ መንግስተ ሰማያት እንዲገቡ እንድንረዳቸው ሊጠቀምብን አስቦ ነው።

 

የገንዘብ ፍቅር እምነታችንን ያጣጥላል

 

ቀጥሎ ሉቃስን እንመለከታለን፤ ሉቃስ ኢየሱስን እንደ እውነተኛ ሰው ነው የገለጠልን።

ክርስቶስ ሃብታሙን ሰው አናገረው።

ሉቃስ 10፡26 እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው።

27 እርሱም መልሶ፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።

አስርቱ ትዕዛዛት በሁለት ፍጹም በሆኑ ሃሳቦች ተጠቅልለዋል። መጀመሪያ ዓይናችሁን በኢየሱስ ማለትም በተጻፈው ቃል ላይ አድርጉ።

የመጀመሪዎቹ አራት ትዕዛዛት እንዴት እግዚአብሔርን እንደምንወድ እና እንደምናገለግል ይነግሩናል። አንድ አምላክ ብቻ አለ፤ እርሱን የሚመስል ሰውም ሆነ የተቀረጸ ምስል የለም። ፖፑ ቪካሪየስ ክሪስቲ ነኝ፤ በክርስቶስ ቦታ ነኝ ይላል። ይህ ውሸት ነው። ማንም ሰው በክርስቶስ ቦታ መሆን አይችልም።

የሜሴጅ ተከታዮች ዊልያም ብራንሐም የእግዚአብሔር ድምጽ ነው ይላሉ። ውሸት። ዊልያም ብራንሐም የሰባተኛው መልአክ ድምጽ ነው። የእግዚአብሔር ድምጽ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት የቻላችሁ ጊዜ ባልንጀራችሁን መውደድና ባልንጀራችሁ ጌታ ሲመጣ ለመቀበል እንዴት መዘጋጀት እንደሚችል ልታስተምሩትና ልትረዱት ትችላላችሁ።

የመጨረሻዎቹ 6 ትዕዛዛት ሰውን እንዴት እንደምንወድና እንደምናገለግል ይነግሩናል።

አራተኛው ትዕዛዝ ከእግዚአብሔር እቅድ ጋር ያጣብቀናል። እውነተኛው የሰንበት እረፍት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ሲሆን ይህም ከሐጥያት ሥራ እና ከአለማመን ያሳርፈናል። ከዚያ በኋላ ብቻ ነው የእግዚአብሔር ዕቅድ ምን እንደሆነ መርምረን የምናውቀውና እግዚአብሔርን ሌሎችን ለመርዳት ሊጠቀምብን የሚችለው።

ለእግዚአብሔር እና ለገንዘብ መገዛት አንችልም። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ የመገኘቱ ሚስጥር ሲሆን ይህም ከገንዘብ ፍቅር ነጻ ያወጣናል።

ማርቆስ 10፡20 እርሱም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው።

ይህ ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ ትዕዛዛትን ጠብቋል።

ነገር ግን ከሁሉ አብልጦ የሚወደው ገንዘብን ነው።

ማርቆስ 10፡21 ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና፦ አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው።

የመጨረሻው የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ዘመን ትልቅ ድክመት እንዲህ የሚለው ንግግሯ ነው፡-

ራዕይ 3፡17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥

ሃብት እምነታችንን ያራክሰዋል። ስንት ቢልየነሮች ናቸው ኢየሱስን እንደ አዳኛቸው አድርገው የሚያውቁ? ስንት ቢሊየነሮች ናቸው ትዳራቸውን እንኳ እንዳይፈርስ መጠበቅ የሚችሉ?

ማርቆስ 10፡22 ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ።

ንብረቱ ሰውየውን ገዛው።

ሃብቱ ኢየሱስን እንዳይከተል አደረገው።

በ2020 ዓ.ም የተነሳው የኮሮና ወረርሽኝ የዓለምን ኢኮኖሚ አናግቷል።

በ2022 ዓ.ም ዩክሬይን ላይ የተደረገው ወረራ የኑሮ ውድነት እንዲጨምር አድርጓል።

ሁላችንም በኢኮኖሚያዊ ጫና እየተፈተንን ነን።

ማርቆስ 10፡23 ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን፦ ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው።

ሃብታም ሰዎች እምነታቸው ባንክ ባስቀመጡት ገንዘብ ላይ የተመሰረተ ነው።

ማርቆስ 10፡24 ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ፦ ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው።

 

ኢየሱስ ስለ ሃብት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ደገመው

 

ገንዘብ የመንግስተ ሰማያት ቁልፍ አይደለም። ኢየሱስ ገንዘብ በረከት ሳይሆን እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል በግልጽ አስጠንቅቋል።

ማርቆስ 10፡25 ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው።

ሰዎች ሃብታሞች በእግዚአብሔር የተባረኩ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ሃብታም ሰዎች ሃብት ከሰጣው ከእግዚአብሔር ይልቅ ሃብታቸውን መውደድ ይጀምራሉ። እግዚአብሔር በሃብት ሲባርከን ወዲያ ሃሳባችን ይለወጥና ሃብት ከመጀመሪያውም የሚገባን ስለነበረ ይመስለናል።

ከገንዘብ ጋር የሚመጣው ችግር ገንዘብ ለብዙ ነገሮች በር መክፈቱ ነው። ከነዚህም በሮች መካከል አብዛኞቹ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የሚያስወጡን ናቸው። ከብዙ ዕድሎች መካከል የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈልጎ ማግኘት ቀላል አይደለም። ገንዘብ ደግሞ በተጨማሪ አልባሌ የሆኑ ሰዎች እንደ ጓደኛ እንዲቀርቡንም ያደርጋል።

ራሳችንን መካድ ሲገባን ገንዘብ ስለ ራሳችን ያለን ግምት ያለ ልክ ከፍ እንዲል ያደርጋል።

ገንዘብ ሲኖረን በተጋነነ ተድላ በመኖር ያለንን እንድናሳይና እንድንመካበት ይፈትነናል።

ሃብት ገንብን ወደ ማባከንና ስለ ገንዘብ በመጨነቅ ተጨማሪ ሃብትን በትጋት ወደ ማሳደድ ይመራል። በተለይ ሁልጊዜ የማይጠፋው ጭንቀት ገንዘብ ሊጠፋ ይችላል ወይም ገቢ ሊቀንስ ይችላል የሚለው ጭንቀት ነው። ይህም ሰዎች በሥራቸው ውስጥ ገንዘብን የመጨርና ገቢ የማሳደግ ሱስ ይፈጥርባቸዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱት ገንዘብ በራሱ ወደ አለመርካት ሊያመራ አይችልም - ደስታን ወደ ማጣት የሚመራው ገንዘብና ቁሳቁስ ለመሰብሰብ የሚደረገው የማያቋርጥ ሩጫ ነው። ለገንዘብ ቅድሚያ መስጠት በቤተሰብና በጓደኝነት ውስጥም ዝቅተኛ ደስታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ብዙ ጥናቶች እንዳመለከቱት ብዙውን ጊዜ አደንዛዥ እጾችን ለመጠቀም የሚጋለጡት የሃብታም ልጆች ናቸው፤ ይህም የሚሆነው የሃብታም ልጆች በትምሕርት ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ ስለሚጠበቅባቸውና ከወላጆቻቸው ጋር ጊዜ የማሳለፍ ዕድል ስለሌላቸው ከነዚህ ሁሉ በሚመጣባቸው ጫና ምክንያት ነው።

ልጆች በተለያየ ምክንያት በብቸኝነት ስሜት ሊጎዱ ይችላሉ። አንደኛ ሃብታም ወላጆች በሥራ ውጥረት ምክንያት ብዙውን ጊዜ እቤት ስለማይገኙ ለልጆቻቸው ጊዜ አይኖራቸውም። ልጆች ደግሞ ከትምሕርት ቤት በሚሰጣቸው ብዙ የቤት ሥራ ምክንያት ሊጨነቁ ይችላሉ።

በሃብታም ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ሁሉ የሞላላቸው ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሁሉ የሞላላቸው ልጆች የሚከፍሉት ዋጋ ብዙ ነው። ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች ከተወለዱ ልጆች ይልቅ የሃብታም ልጆች ጭንቀት ይበዛባቸዋል። ስለዚህ የሃብታም ልጆች ለጭንቀት፣ ለድብርት፣ ለዕጽ ሱስ፣ ለስርቆት ለማጭበርበር የተጋለጡ ናቸው። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በብዛት ወደ ጠጪነት እና ማሪዋና የተባለ ዕጽ ተጠቃሚነት የሚያዘነብሉት የሃብታም ልጆች ናቸው።

በሃብት እያደጉ በሚሄዱ ማሕበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ትምሕርት ቤት ውስጥ ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ እና ከትምሕርት ጋር ተጓዳኝ በሆኑ እንቅስቃሴዎችም ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጫና ይመጣባቸዋል፤ ይህም ለከፍተኛ ጭንቀት ያጋልጣቸዋል። የሃብታም ልጆች ከሚጠበቅባቸው ከፍተኛ ውጤት የተነሳ በነጻነት መኖር አይችሉም።

ከመንፈሳዊ ሕይወት አንጻር ሚልክያስ ምዕራፍ 4 ውስጥ እንደተጻፈው ልጆች ናቸው ወደ ሐዋርያዊ አባቶች መመለስ ያለባቸው።

ትዳር ውስጥ ወንድ የሴት ራስ ነው። ሴት ቤተክርስቲያንን የምትወክል ከሆነች ወንድ ደግሞ የቤተክርስቲያን ራስን ይወክላል። እርሱም ኢየሱስ ነው። ዛሬ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ባይደግፈውም እንኳ ፓስተሩ የቤተክርስቲያን ራስ እንደሆነ እየተቆጠረ ነው።

ስለዚህ ሃብታሙ ሰውዬ የሃብታም ቤተክርስቲያኖችን ሃብታም ፓስተሮች ይወክላል። ሃብት እና ስልጣናቸውን አስጠብቀው ይኖራሉ፤ ይህም ስልጣን የሰዎችን ገንዘብ የመሰብሰብ ስልጣን ነው። ራሳቸውን ከፍ ከፍ ያደረጉ የቤተክርስቲያን ራሶች የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ስላልሆኑ የተገለጡትን የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መረዳት ለእነርሱ በጣም ከባድ ነው። እምነታቸው ትክክል መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ተጠቅመው ማስረዳት አይችሉም። ለዚህ ነው ብዙ ሺ ዓይነት ቤተክርስቲያኖችና ዲኖሚኔሽኖች የተከፈቱት። ስለዚህ የሚከሏቸው ሰዎችም በብዙ ዓይነት የስሕተት ሽንገላዎች ይታለላሉ።

እነዚህ ሁሉ አሉታዊ ነገሮች ሲደማመሩ ከስሕተት የሚያመልጡ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

ማርቆስ 10፡26 እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው፦ እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ።

እውነታውን ስንጋፈጥ ሰዎች ራሳቸውን ማዳን እንደማይችሉ እንገነዘባለን።

ክርስቲያኖች ሃብትን የሚነቅፍ ማንኛውም ትምሕርት መስማት አይፈልጉም። ምክንያቱም ውስጥ ውስጡን ከልብ የምንፈልገው ነገር ሃብት ነው።

ማርቆስ 10፡27 ኢየሱስም ተመለከታቸውና፦ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ።

እግዚአብሔር ብቻ ነው እውነተኛው አዳኝ። እኛም የምንድነው ኢየሱስ ሐጥያታችንን ስለተሸከመ ብቻ ነው። ከዚያም ኢየሱስ ዓይናችንን እንዲያበራ መፍቀድ አለብን። የዚያን ጊዜ ራሳችንን ስንመለከት በምናየው ነገር ደስ አይለንም፤ ስለዚህ ንሰሃ ለመግባት እንቀናለን። እያንዳንዳችን ንሰሃ የምንገባበት ብዙ ነገር አለን። ሊያስተካክለን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ደግሞም የምንወዳቸው እምነቶቻችንም ከተጻፈው ቃል ምን ያህል ርቀው እንደሄዱ ማየትም አንፈልግም።

 

እውነተኛው ሽልማት ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት ውስጥ ነው

 

ማርቆስ 10፡28 ጴጥሮስም፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ይለው ጀመር።

ቀጥሎ ጴጥሮስ እርሱ እና ሌሎቹ ደቀመዛሙርት ኢየሱስን ለመከተል ብለው ቤታቸውንና ቤተሰባቸውን ትተው በመምጣታቸው ስለከፈሉት መስዋእትነት ያነሳል።

ማርቆስ 10፡29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥

30 አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።

እግዚአብሔር እያንዳንዱን መስዋእት መዝግቦ ይዟል። ሰዎች ስለ ከፈሉት መስዋእትነት ሁሉ በጊዜው ሽልማታቸውን ይቀበላሉ። ቆም ብለን የተቀበልነውን በረከት መቁጠር ብንጀምር በዚህ በምድር ሕይወት መከራ ቢበዛም እንኳ ብዙ ሽልማቶችንም ከጌታ እንዳገኘን እናስተውላለን። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ለመረዳት በምናደርገው ጉዞ ውስጥ የሚገጥመን አንዱ ከባድ ፈተና ብቸኝነት ነው።

ትልቁ ነገር ትኩታችንን በሚመጣው ሕይወት ላይ ማድረግ ነው እንጂ በአሁኑ ሕይወት ላይ አይደለም። የአሁኑ ሕይወት ከመከራውና ከችግሮቹ ሁሉ ጋር ጊዜያዊ ነው። ቀጣዩ ሕይወታችን ግን በብዙ ሽልማቶች የተሞላ ስለሆነ በዚህ ምድር ሳለን ያጣነውን ሁሉ ይክሰናል።

ማርቆስ 10፡31 ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።

ኢየሱስ ንግግሩን ሲጨርስ በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን እና በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን መካከል ምንም ልዩነት መኖር እንደሌለበት ያስገነዝባል። ስለዚህ በዘመን መጨረሻ የምንገኝ ክርስቲያኖች ትኩረታችን ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን እምነቶች በመመለስ ላይ መሆን አለበት። እግዚአብሔር ለዘመናችን ያለው ሃሳብ ይህ ነው። ዛሬ ከሁሉ የሚበልጠው እውነት ይህ ነው።

ማርቆስ 10፡32 ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፥ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም አሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር።

ኢየሱስ እየመራ ደቀመዛሙርቱ ይከተሉ ነበር። ይህም ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን መከተል እንዳለብን ያሳስበናል።

ኢየሱስ ቃሉ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምንማረው ነገር በጣም ያስደንቀናል ምክንያቱም ቤተክርስቲያኖች ከአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ምን ያህል ርቀው እንደሄዱ እናያለን። እኛም ደግሞ ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን እምነት ስንመለስ ከሰዎች ዘንድ የሚገጥመንን ጥላቻና ስደት የተነሳ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆንብን ስናስበው ያስፈራናል። ነገር ግን እግዚብሔር በዚህ በመዘን መጨረሻ ለእኛ ያለው ሃሳቡ ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን እምነት እንድንመለስ ነው።

ማርቆስ 10፡33 እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፥ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፥

ኢየሱስ ለቤተክርስቲያን ድልን ሊያጎናጽፋት ስለፈለገ መሞትን መረጠ። የኢየሱስ ስኬት የተመሰረተው ያለውን ሁሉ በማጣት ነው።

በዚህ ምድር የመበልጸግን ወንጌል አልሰበከም።

ዋነኞቹ የሐይማኖት መሪዎች ወይም የቤተክርስቲያን መሪዎች ግን የእግዚአብሔርን ቃል እውነር ማውገዝ ብቻ ነው ሃሳባቸው። የቤተክርስቲያን ዓለም የስሕተት ወጥመድ ሆኗል፤ ቤተክርስቲያኖች በሙሉ በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን እውነት እየካዱ ናቸው።

ማርቆስ 10፡34 ይዘብቱበትማል ይተፉበትማል ይገርፉትማል ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።

ይህ በኢየሱስ ላይ ደርሶበታል፤ ስለዚህ አካሉ በሆነችው በቤተክርስቲያንም ላይ ይደርስባታል።

መጽሐፍ ቅዱስን የሚጠቅሱ እውነተኛ አማኞች ይቀለድባቸዋል፤ ይዋረዳሉ፤ ይሰደዳሉ።

ኢየሱስ በ3 ቀናት በኋላ ከሞት እንደተነሳ ሁሉ እውነትም በመጨረሻዎቹ ሶስት የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ በሉተር፣ በዌስሊ፣ እና በሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ከሞት ትነሳለች። ይህም በሎዶቅያ የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን የምትመለስ ሙሽራ ትኖራለች ማለት ነው፤ ምክንያቱም ዊልያም ብራንሐም ብዙ ክርስቲያኖችን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲመለሱ ያስተምራቸዋል። ከዚያ በኋላ የአዲስ ኪን ቤተክርስቲያን ትንሳኤ ይሆናል፤ ከሙሽራይቱ አካላት በምድር በሕይት ያሉ ሰዎችም አካላቸው ይለወጣል። ከዚያም ጌታን በአየር ላይ ሊቀበሉ ይነጠቁና ወደ ሰማይ ይሄዳሉ።

 

ቤተክርስቲያን ውስጥ የግል እና የቤተሰብ አጀንዳ ማራመድ ስሕተት ነው

 

ማርቆስ 10፡35 የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው፦ መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት።

የሚያሳዝነው ነገር በኢየሱስ ትንሳኤ ላይ ትኩረት በማድረግ ፈንታ ያዕቆብና ዮሐንስ ሃሳባቸው ከሰዎች ሁሉ በላይ ራሳቸውን በስልጣን ከፍ ማድረግ ላይ ነበር (ይህንንም ሊደርሱበት የፈለጉበት መንገድ በዝምድና ነው)። በቤተክርስቲያን ውስጥ ካሉ ስሕተቶች ሁሉ ትልቁ ስሕተት ለዘመዶች ማድላት ነው። የፓስተሩ ስልጣን ከአባት ወደ ልጅ ይተላለፋል። ለምን? ገንዘብ ከቤተሰብ እንዳይወጣ ነዋ። በሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቁ እርግማን ገንዘብ ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን ቤተክርስቲያን ገንዘብን በማሳደድ ተጠምዳለች።

ማርቆስ 10፡36 እርሱም፦ ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው።

ኢየሱስ ምን ላድርግላችሁ አላቸው።

ማርቆስ 10፡37 እነርሱም፦ በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት።

እነርሱ የሚፈልጉት ክብርን ለማግኘት የሚያስፈልገውን መከራ እና ሞት ኢየሱስ ከተቀበለው በኋላ ለራሳቸው በሰማይ ሁለት ትልልቅ የስልጣን ሥፍራዎችን መያዝ ነው።

የመከራውን ጽዋ በሙሉ ኢየሱስ ይጠጣውና ከዚያ ሽልማቱን እኔና ወንድሜ እንቀበላለን።

ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ማስቀደማቸውን ተመልከቱ።

ማርቆስ 10፡38 ኢየሱስ ግን፦ የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አላቸው።

ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ምን እየተናገሩ እንደሆነ እንኳ እንደማያውቁ ነገራቸው። የቤተክርስቲያን ትልቅ ድካም አገልጋዮች አፋቸውን ሞልተው እየሰበኩ ስላሉት ነገር አለማወቃቸው ነው። ሰባቱ ነጎድጓዶች የተናገሩትን ቃል እናውቃለን የሚሉትን የሜሴጅ ሰባኪዎች ተመልከቱ። ሰባቱ ነጎድጓዶች ምን ብለው እንደተናገሩ የተጻፈ ነገር የለም፤ ስለዚህ የሜሴጅ ሰባኪዎች ለሕዝቡ የሚያስተምሩት በማስረጃ ያልተደገፈ ግምታቸውን ነው። እንዲህም አድርገው ገንዘብ ይከፈላቸዋል።

ኢየሱስ በተያዘ ጊዜ ዮሐንስ እና ያዕቆብ ከአካባቢው ሸሽተው ሄደዋል። ኢየሱስን በተከተሉ ሰዎች ሁሉ ላይ ኢየሱስ በተያዘ ጊዜ ስለሚመጣባቸው ከባድ የፍርሃት መንፈስ ማንም አላወቀም ነበር። ያንን አስፈሪ ሌሊት ሊጋፈጥ የቻለው ኢየሱስ ብቻ ነበር።

ማርቆስ 10፡39 እነርሱም፦ እንችላለን አሉት። ኢየሱስም፦ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤

ኢየሱስ የሚቀበለውን መከራ ሁሉ እንቀበላለን ብለው ተናግረው ነበር። ስለዚህ መጀመሪያ የተገደለው ሐዋርያ ያዕቆብ ሲሆን ዮሐንስ ደግሞ በዘይት ተቀቅሏል፤ እንዲሁም ሁለት ጊዜ በፍጥሞ ደሴት ላይ ታስሯል።

ማርቆስ 10፡40 በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው።

እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰነውና የሚፈጽመው እቅድ አለው። ይህም እቅዱ በሰዎች ጥረት ላይ የተደገፈ አይደለም።

 

 

ከኢየሱስ ቀኝ እና ግራ በኩል መቀመጥ ኢየሱስ በአብ ቀኝ በተቀመጠበት ሥፍራ ሶስት ሰዎች የተቀመጡበት ስላሴ አለመኖሩን ያረጋግጣል። እግዚአብሔር ከኢሱስ በግራ በኩል ስለሆነ የተቀመጠው ከኢየሱስ በግራ በኩል ሰው የሚቀመጥበት ክፍት ቦታ የለም።

 

 

ማርቆስ 10፡41 አሥሩም ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ይቈጡ ጀመር።

የሁለቱ ደቀመዛሙርት የስልጣን ጥማት በደቀመዛሙርት መካከል መከፋፈልን ፈጠረ። የሰዎች የስልጣን ጥማት ቤተክርስቲያንን ስለሚገነጣጥላት ክርስትናን እንደ መተዳደሪያ ሙያ መያዝ ጥሩ አይደለም።

ማርቆስ 10፡42 ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።

ኢየሱስ ስለወደፊቷ ቤተክርስቲያን እያሰበ ነው የተናገረው። አሕዛብ ከሰዎች ሁሉ በላይ ከፍ ያለ ባለስልጣን መሆንና ሰው ሁሉ ያለ ምንም ማንገራገር እንዲታዘዛቸው ይፈልጋሉ።

ማርቆስ 10፡43 በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥

መሪ አገልጋይ ነው። የአሕዛብ ቤተክርስቲያን በሞኝነቷ አገልጋይን ወይም ፓስተርን የቤተክርስቲያን ራስ ነው ብላ ከፍ አደረገችው። አገልጋይ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሁሉ ታናሽ እንዲሆን ራሱን ዝቅ ያደርጋል እንጂ ራስ አይሆንም።

ማርቆስ 10፡44 ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን።

ወደ ላይ ለመውጣት መንገዱ ወደ ታች መውረድ ነው። ስለዚህ አገልጋይ ለመሆን ትጉ እንጂ የቤተክርስቲያን ራስ ለመሆን አትሽቀዳደሙ።

ማርቆስ 10፡45 እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።

ኢየሱስ ሰዎች እንዲያገለግሉት ብሎ አልመጣም። እርሱ የመጣው ሊያገለግል ነው። እርሱ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ ነው።

የኢየሱስ አገልግሎት በአጭሩ ሲገለጽ እንደሚከተለው ነው፡- “ስጦታው ሰጠ”።

 

የተሳሳቱ መረዳቶች የቃሉን የመስራት ሃይል ያዳክማሉ

 

ማርቆስ 10፡46 ወደ ኢያሪኮም መጡ። ከደቀ መዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጣ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስ እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር።

በርጠሜዎስ ኢያሪኮ ውስጥ የሚኖር ዓይነ ስውር ነበር።

በርጠሜዎስ በሎዶቅያ የቤተክርስቲያን ዘመን የሚኖሩ እውነትን እንዳያዩ በቤተክርስቲያን መሪዎች ዓይናቸው የታወረባቸውን ሰዎች ይወክላል።

ስለዚህ በርጠሜዎች ዓይኑ እንዲበራ ከፈለገ ከቤተክርስቲያን መውጣት እንዳለበት ገብቶታል (ቤተክርስቲያንን የምትወክለው የኢያሪኮ ከተማ ናት)።

ከኢያሪኮ ውጭ ማለት ልክ ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን ውጭ እንደቆመበት እንደ ሎዶቅያውያን የመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ነው

ማርቆስ 10፡47 የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ፦ የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ይጮኽ ጀመር።

የናዝሬቱ ኢየሱስ። ናዝሬት ሰባተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን ትወክላለች። ናዝሬት የግሪክ ቃል ነው እንጂ የዕብራይስጥ ቃል አይደለም ምክንያቱም ናዝሬት የሚል ስም ብሉይ ኪዳን ውስጥ አልተጠቀሰም።

ናዝሬት ከሁለት ቃላት የተገኘ ስም ነው።

ኔትዘር ማለት በዕብራይስጥ ቅርንጫፍ ሲሆን ኔትዘሬት ማለት ቅርንጫፍ የሚወጣበት ቦታ ነው።

ናዛራ ማለት እውነት ማለት ነው።

ናዛራ እና ኔትዘሬት አንድ ላይ ሲሆኑ እውነት የሚወጣበት ቅርንጫፍ የሚል ትርጉም ይሰጡናል።

ወደ ግሪክ ሲተረጎም ናዝሬት የሚለውን ቃል ይሰጠናል።

ዮሐንስ ኢየሱስን በመቅረዞቹ መካከል አየው፤ መቅረዙም እውነት እንደ ቅርንጫፍ ተከፋፍሎ የተሰራጨበትን 7ቱን የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላል።

የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ብቻ ነው እውነቱ የሚገኘው፤ ስለዚህ ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን መመለስ አለብን።

 

 

ታላቁ ሐዋርያና ነብይ ዮሐንስ በኢየሱስ እግር ስር እንደ ሞተ ሰው ሆኖ ወደቀ። ከኢየሱስ ጋር ሊወዳደር የሚችል ነብይ የለም።

ራዕይ 1፡13 በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፥

በመቅረዞቹ መካከል ማለት እውነትን ያገኘው የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ብቻ ነው ማለት ነው።

“የዳዊት ልጅ” የሚለው መጠሪያ ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ዘመን የሚጠራበት ስም አይደለም። ኢየሱስ የዳዊል ልጅ ተብሎ የሚጠራው በሺ ዓመት መንግስቱ ሲነግስ ብቻ ነው።

ማርቆስ 10፡48 ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፦ የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ።

በርጠሜዎስ እውነትን ማወቅ ፈለገ ምክንያቱም እውነት ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ቃሉ ነው። እውነትን ፍለጋ ከተነሳን በኋል ልክ እንደ በርጠሜዎስ ሌሎች ሰዎች የሚሉትን ሁሉ ጥለን ማለፍ አለብን። ጌታ በመገለጥ ኩል ዓይናችንን እንዲያበራልን ዘወትር መለመን አለብን።

ማርቆስ 10፡49 ኢየሱስም ቆመና፦ ጥሩት አለ። ዕውሩንም፦ አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል ብለው ጠሩት።

ኢየሱስን የዳዊል ልጅ ሆይ ብሎ መጥራት ወደፊት ስለሚመጣው የሺህ ዓመት መንግስቱ መናገር ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ዝም ሊል አልቻለም፤ ሰውየውን ቆሞ ጠበቀው።

ኢየሱስ እውሮቹን የሎዶቅያ ቤተክርስቲያኖች የተገለጠው ቃሉ ውስጥ ያሉትን ሚጥራት እንዲያገኙ ሊረዳቸው አይችልም። ከሲኦል መዳን ይችላሉ ነገር ግን ከሚመጣው ከታላቁ መከራ መዳንና ለዳግም ምጻት መዘጋጀት አይችሉም።

ማርቆስ 10፡50 እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ።

ከቤተክርስቲያን መሪዎች የተማረውን የቤተክርስቲያን ስነመለኮት እና ቲዎሪ የደረበለትን ልብስ አውልቆ ጥሎ መጣ።

ቤተክርስቲያኖች ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን እምነት መመለስ እንዳለብን አያውቁም። ስለዚህ ቤተክርስቲያኖች ለኢየሱስ ዳግም ምጻት የምንዘጋጅበትን መንገድ ሊመሩን አይችሉም።

ማርቆስ 10፡51 ኢየሱስም መልሶ፦ ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? አለው። ዕውሩም፦ መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ አለው።

ኢየሱስን “ጌታ” ብሎ ጠራው።

ይህም ትክክል ነው ምክንያቱም ኢየሱስ ጌታ ነው። አንድ አምላክ ብቻ አለ እርሱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ማርቆስ 10፡52 ኢየሱስም፦ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው።

ኢየሱስን እንደ መለኮት ሙላት፣ እንደ ሁሉን ቻይ አምላክ ማየቱ ዓይኖቹ እንዲበሩ አደረገለት።

ኢየሱስን በመከተል ብቻ ነው በርጠሜዎስ እግዚአብሔርን የሚያገለግልበትን ትክክለኛ መንገድ ማግኘት የሚችለው። ኢየሱስን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መከተል አለብን፤ እርሱም እየመራን ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ይወስደናል። ኢየሱስ የሚታየው ከመቅረዙ መካከል ብቻ ነው። የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ብቻ ነው እውነቱ የሚገኘው።

 

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23