ማርቆስ 9 - ኢየሱስን ብቻ እመኑ እንጂ ሌላ ሰው አትመኑ
We update studies as the Lord Jesus leads us. You can find the latest update of this study at ChurchAges.net
ኢየሱስ ሲገለጥ ነብያት አስፈላጊነታቸው ያበቃል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ የሚፈልጉትን ሕጻናት አትውቀሷቸው፤ አትፍረዱባቸው።
- ጌታ በመጨረሻው ዘመን እንዴት እንደሚመጣ የሚያሳይ ቅድመ እይታ
- በስተመጨረሻ የቤተክርስቲያን መሪዎች ስሕተት መሆናቸው ይገለጣል
- የኤልያስ ድርብ ምጻት
- ቃሉን የማንሰማ ከሆንን ዲዳዎች ነን ማለት ነው
- የትንሳኤው ሰዓት ግራ የሚያጋባ ሰዓት ነው
- የስልጣን ወዳድ የቤተክርስቲያን መሪዎች እርግማን
- በመጨረሻው ዘመን ሕጻናትን አታሳስቱ
ጌታ በመጨረሻው ዘመን እንዴት እንደሚመጣ የሚያሳይ ቅድመ እይታ
ማርቆስ 9፡1 እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ፥ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ አላቸው።
“ሞትን የማይቀምሱ”። ይህ ቃል ትኩረቱን ያደረገው በመጨረሻው ዘመን በሕይወት ስለሚኖሩ የሙሽራይቱ አካላት ነው።
ኢየሱስ በዘመን መጨረሻ ስለሚሆነው ነገር ከደቀመዛሙርቱ መካከል ለሶስቱ በጥቂቱ ሊያሳያቸው አሰበ።
ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ሶስቱን ይዞ ሊሄድ ተነሳ (እነዚህ ሶስት ደቀመዛሙርት 5ኛውን፣ 6ኛውን፣ እና 7ኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን መልእክተኞችን ይወክላሉ፤ በነዚህ ሶስት የመጨረሻ ዘመናት መልእክተኞቹ በጨለማው ዘመን ጠፍቶ የነበረውን የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን ዘመን እውነት መልሰው ወደ ቤተክርስቲያን በተሃድሶ ያመጣሉ)።
የመጀመሪያው እርምጃ የሚመጣው ድምጽ ነው፤ ማለትም ሙሽራይቱ በእምነቷ አጥብቃ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ እንድትከተል የምትማርበት ነው። ድምጹ ማለት ወንድም ብራንሐም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ መልእክቶቹን ሲሰብክ አይደለም። ድምጹ ማለት ሙሽራይቱ የተማርችውን እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ መርምራ ስታረጋግጥ ነው።
65-1127 ሰምቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየች
እግዚአብሔር ሆይ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ልክ እንደዚህ ዓይነት ሰዓት ይመጣል የነጎድጓድ ድምጽ የሚሰማበት ሰዓት፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ልጅ በታላቅ ድምጽ ከሰማያት ይወርዳል፤ በመላእክት አለቃ ድምጽ፣ በእግዚአብሔር መለከት ይመጣል፤ በክርስቶስም ሆነው የሞቱት ይነሳሉ።
ወንድም ብራንሐም ከመሞቱ አንድ ወር በፊት ድረስ ድምጹ ገና ወደ ፊት ይመጣል ብሎ ሲጠባበቅ ነበር። ወንድም ብራንሐም ሚስጥራቱን በመግለጥ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፤ አሁን የእኛ ድርሻ እርሱ ያስተማረንን መገለጦች በመጽሐፍ ቅዱስ እየመዘንን ለራሳችን ማረጋገጥ ነው፤ የዛኔ ድምጹ ይፈጸማል።
ያ ድምጽ ከተፈጸመ በኋላ በ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የሞቱትን ቅዱሳን ከሙታን የሚያስነሳው የመላእክት አለቃ ድምጽ ይመጣል።
ሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት በሚፈጸሙ ጊዜ በቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የሞቱ ቅዱሳን ከሙታን ሲነሱ የሚሆነው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ኢየሱስ ቀድሞ አሳያቸው። ከተነሱ በኋላ አንድ አስደናቂ ነገር ይሆናል፤ ይህም የአካላቸው ወደ ትንሳኤ አካል መለወጥ ነው። ይህም ኃይለኛው ነገር ግን ሚስጥራዊው የሰባቱ ነጎድጓዶች አገልግሎት ነው። በሕይወት ያለችዋ ሙሽራ ከአሕዛብ ወገን በሆነው ነብይ ዊልያም ብራንሐም አማካኝነት የተጻፈውን ቃል ሚስጥር ከተማረች በኋላ ትኩረቷ የነጎድጓዶቹ ቃል ላይ ነው የሚሆነው። ከዚያ የሙሽራይቱ አካላት በሙሉ ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ። ከዚያም ቀጥሎ በ3.5 ዓመቱ የታላቅ መከራ ዘመን ውስጥ እግዚአብሔር በሁለቱ አይሁዳዊ ነብያት አማካኝነት ወደ አይሁዶች ይመለሳል።
የዚህ ምዕራፍ ትልቁ ትኩረት የሙሽራይቱ አካል በታላቅ ክብር ስለ መለወጡ ነው። ይህም በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ስፍራ የተሰጠው ጉዳይ ነው። በተፈጸመ ጊዜ በምድር ላይ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጥ ይሆናል።
ማርቆስ 9፡2 ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤
ኢየሱስ ወደ ተራራ “አወጣቸው” የሚለው ቃል በዘመን መጨረሻ የሚኖሩ ደቀመዛሙርት የተጻፈውን ቃል ብቻ መከተል ይለምዳሉ ማለት ነው። ደቀመዛሙርቱ የተከተሉት ማንኛውንም ሰው ወይም አንድን ቡድን ሳይሆን ኢየሱስን ብቻ ነው።
ዛሬ ኢየሱስን የምናያው በእግዚአብሔር ቃል ነው።
ስለ ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ የምትናገሩት ነገር በሙሉ ስለ ኢየሱስ መናገራችሁ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን በማንኛውም መንገድ ብትነቅፉ ኢየሱስን መንቀፋችሁ ነው።
ስለዚህ ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ እንከን የሌለበት ፍጹሙ እውነት መሆኑን ማመን አለባችሁ።
“ረጅም ተራራ” ማለት የተገለጠው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብልህ ሰዎች ሊመረምሩት ከሚችሉት በላይ ነው ማለት ነው። እውነቱን ማየት እንድንችል ከዓይናችን ላይ ቅርፊቱን የሚያነሳልን ኢየሱስ ብቻ ነው። ሶስቱ ደቀመዛሙርት ለመጨረሻዎቹ ሶስት የቤተክርስቲያን ዘመናት የተላኩትን መልእክተኞች ይወክላሉ። እነርሱ ቃሉን እንደተከተሉት እኛም እነርሱን መከተል አለብን። እነርሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምሯችሁን ብቻ እመኑ።
“ከስድስት ቀንም በኋላ” ሰባተኛው ቀን ይመጣል፤ ይህም የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ሰባተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን ይወክላል። ሰባተኛውም ዘመን የሚጠናቀቀው በሕይወት ያሉት የሙሽራይቱ አካላት ወደ ከበረው አካላቸው ተለውጠው ወደ ሰማይ ሲነጠቁ ነው።
“ተለወጠ” የሚለው ቃል በሕይወት ያለችዋ ሙሽራ አካላት ወደ ከበረው አካላቸው መለወጣቸውን ይወክላል። ይህም በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የሚኖሩ ቅዱሳን ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚመለሱበት የሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ፍጻሜ ነው።
“ረጅም ተራራ” ማለት ብዙ ተግዳሮትና ትግል፣ ስደት እና መገፋት ያለበትን ሂደት ነው የሚያመለክተው። ነገር ግን ከተራራ ጫፍ ላይ ሆነው የሚያዩት እይታ መጽሐፍ ቅዱስን ለሚወዱ ሰዎች መከራውን በደስታ እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል።
“ብቻቸውን”። የተገለጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት የሙሽራይቱ እምነት ከቤተክርስቲያንና በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ካለው ከሰነፎቹ ቆነጃጅት እምነት የተለየ እንዲሆን ያደርጋሉ።
1ኛ ቆሮንቶስ 15፡52 የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።
መጀመሪያ ሙሽራይቱ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ መከተል ስትለምድ “ድምጹ” ይመጣል። ከዚያ በኋላ የሚመጣው ሙታንን የሚያስነሳው የመላእክት አለቃ ድምጽ ነው። ይህን ተከትሎ የሙሽራይቱ አካላት የሆንን ሁሉ አካላችን ወደ ማይሞተው የክብር አካል ይለወጣል። የክርስትና ሕይወታችሁ ታላቅና ክብር የሞላው ፍጻሜ ይህ ነው፤ በዚያን ጊዜ ሐጥያት በሌለበት አካል ውስጥ ትኖራላችሁ።
1ኛ ተሰሎንቄ 4፡16 ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤
17 ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።
ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ኢየሱስ ፊቱ ያበራበት ተራራ ታቦር ተራራ ነው ይላሉ። ግን ይህ ግምት ብቻ ነው። ተራራው የትኛው እንደሆነ ስሙ ባለመጠቀሱ ሚስጥር ሆኖ ቀርቷል። የዚህ ተራራ ስም ሚስጥር መሆኑ አግባብ ነው ምክንያቱም የጌታ ዳግም ምጻት የዓለማችን ታላቁ ሚስጥር ነው።
ከአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ትንሳኤ በኋላ ድምጻቸውን የሚያሰሙት የሰባቱ ነጎጓዶችም ነገር ታላቅ ሚስጥር ነው፤ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም። በሕይወት የሚኖሩ ቅዱሳንና ከሙታን የተነሱት ቅዱሳን አካላቸው የሚለወጠው በነጎድጓዶቹ አማካኝነት ነው። ይህም ጥልቅ ሚስጥር ሲሆን የሚገለጠው በሚፈጸምበት ሰዓት ብቻ ነው።
ማርቆስ 9፡3 ልብሱም አንጸባረቀ፤ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ።
ነጭ ቀለም የሚገኘው በቀስተ ደመና ውስጥ ከሚገኙ ሰባት ዋነኛ ቀለሞች ድብልቅ ነው።
ነጭ ማለት ሰባቱም የቤተክርስቲያን ዘመናት በሙሉ በአንድነት ሆነው የሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውህደት የሆነችዋን ሙሉዋን ሙሽራ ይገልጣሉ ማለት ነው። ይህም እግዚአብሔር ሙሽራይቱን የሚቤዥበት ታላቅ እቅዱ ነው።
በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ፍጻሜ የሙሽራይቱ ነጭ ልብስ፣ የሰርግ ቀሚስ ይዘጋጃል።
7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ተሟልተው እንዲጠናቀቁ የመጨረሻው ዘመን ወደ መጀመሪያው ዘመን እምነት መመለስ አለበት።
የሰባተኛው ንስር የተገለጠው ቃል በሐዋርያት ዘመን በአንበሳው ዘመን ከተጻፈው ቃል ጋር ተመሳሳይ መሆን አለበት።
ማርቆስ 9፡4 ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፥ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር።
ለሙሽራይቱ
ኤልያስ የመጨረሻውን ዘመን ነብይ ዊልያም ብራንሐምን ይወክላል፤ ዊልያም ብራንሐም በ7ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የሚኖሩ ልጆችን ወደ መጀመሪያው ዘመን ወደ ሐዋርያዊ አባቶች እምነት ለመመለስ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራትን ገልጦ አስተምሯል።
በተጨማሪ ኤልያስ በኢየሱስ ዳግም ምጻት ሰዓት የምትኖረዋል ሙሽራ ይወክላል። ኤልያስ በሰረገላ ወደ ሰማይ ተነጥቆ ስለሄደ አልሞተም። በዚህም ምክንያት ኤልያስ አካላቸው ወደማይሞት አካል የሚለወጥላቸውን ቅዱሳን ይወክላል። እነዚህ ሰዎች በሰው ታሪክ ውስጥ ብቸኞቹ የማይሞቱ ሰዎች ይሆናሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ ሰማይ ተነጥቀው ጌታን በአየር ላይ ይቀበሉታል።
ሙሴ እንደ በክርስቶስ ዳግም ምጻት ወቅት አንድ ሰው ከ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ከሙታን የተነሱትን ቅዱሳን የሙሽራይቱ አካላት ይወክላል።
ለአይሁዶች
ኤልያስ እና ሙሴ በ3.5 ዓመቱ ታላቅ መከራ ወቅት 144,000ዎቹን ለማዳን ወንጌልን የሚሰብኩትን ሁለቱን ነብያት ይወክላሉ።
በስተመጨረሻ የቤተክርስቲያን መሪዎች ስሕተት መሆናቸው ይገለጣል
ማርቆስ 9፡5 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦ መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው።
ጴጥሮስ ወዲያው የሰራው ስሕተት ዛሬ ቤተክርስቲያን የምትሰራው ዓይነት ስሕተት ነው፤ ሶስት ሰዎችን ሲያይ እንደ ስላሴ ዓይነት እምነት በልቡ ጀመረና ሶስት የማምለኪያ ስፍራዎች ሊያዘጋጅ ተነሳ።
በተራራው ላይ ያያቸው የዘመን ፍጻሜ ምልክቶች ጴጥሮስን ግራ አጋብተውታል። ባለማስተዋል (ልክ እንደ ሰነፎቹ ቆነጃጅት) ያልተረዳውን ሁሉ ሊተረጉም ሞከረ።
ጴጥሮስ ልክ በዚህ ዘመን ብዙዎቹ የሜሴጅ ተከታዮች የሚሰሩትን ትልቅ ስሕተት ሰራ። ስሕተቱም ነብዩን ከኢየሱስ እኩል ከፍ ማድረጉ ነው። ጴጥሮስ ነብዩ ኤልያስን ሊያመልክ ዳስ መስራት ፈለገ። የሜሴጅ አማኞች ዊልያም ብራንሐምን የሰው ልጅ፣ የእግዚአብሔር ድምጽ እያሉ ይጠሩታል፤ ከዚህም የተነሳ የእርሱን ንግግሮች ከተጻፈው ቃል በላይ ከፍ አድርገዋል። ስለዚህ ወንድም ብራንሐምን ወደ መለኮትነት ደረጃ ከፍ በማድረጋቸው በጣም ተሳስተዋል።
በእነርሱ አእምሮ ውስጥ “የብራንሐም ንግግር ጥቅስ አለኝ” የሚለው አባባል “ተጽፏል” የሚለውን ተክቶታል።
“የወንድም ብራንሐምን መጻፎች እስካነበብኩና በቴፕ የተቀረጹ መልእክቶቹን እስካዳመጥኩ ድረስ ምንም አልሆንም ምክንያቱም የሱ መልእክቶ ፍጹሙ የእግዚብሔር ቃል ናቸው” ይላሉ አንዳንዶች።
ልክ እንደ ጴጥሮስ እነርሱም ዊልያም ብራንሐምን ወደ መለኮትነት ደረጃ ከፍ ያደርጉታል።
ምሳሌ 29፡18 ራእይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተመሰገነ ነው።
ሰባቱ ነጎድጓዶች በተገለጡ ጊዜ መልእክታቸውን መረዳት እንድንችል ወደ ፊት ስለሚፈጸሙ ክስተቶች እውቀት ሊኖረን ይገባል።
መጽሐፍ ቅዱስን በወንድም ብራንሐም ትምሕርት መሰረት መተርጎምን እምቢ የሚሉ ሰዎች ሰባቱ ነጎድጓዶች ልክ ከትንሳኤ በኋላ ቃላቸውን በሚያሰሙ ጊዜ የነጎድጓዶቹን ሚስጥራዊ መልእክት መረዳት የሚችሉበት በቂ እውቀት አይኖራቸውም። ስለዚህ በጣም ግራ የሚያጋባ ጊዜ ይሆንባቸዋል።
63-0318 የመጀመሪያው ማሕተም
ነገር ግን አስቡ፤ አሁን ይህንን እየጻፈ ነበር፤ ነገር ግን ሌሎቹን ማለትም ሰባቱን ነጎድጓዶች ሊጽፍ ሲያስብ “አታጻፍ” አለው። ያየውን ሁሉ እንዲጽፍ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። ነገር ግን እነዚህ ሰባት ነጎድጓዶች ራዕይ ምዕራፍ 10 ውስጥ በተናገሩ ጊዜ “እንዳትጽፍ” ተብሎ ተነገረው። ሚስጥሮች ናቸው። ምን እንደሆኑ እስከ አሁን ድረስ አናውቅም፤ ነገር ግን ኋላ በጊዜያቸው ይገለጣሉ ብዬ አምናለው።
ሲገለጡም ቤተክርስቲያን ከዚህ ዓለም የምትወጣበት ተነጥቃ የምትሄድበትን እምነት እና ጸጋ ይሰጧታል።
እስከዚያው ድረስ በተገለጠልን እን በተረዳነው እንመላለሳለን፤ ባለፉት ዘመናት ውስጥ ሁሉን አይተናል። የእግዚአብሔርን ሚስጥራት አይተናል። በመጨረሻው ዘመን ሙሽራይቱ እንዴት ባለ ታላቅ ክብር እንደምትሰበሰብ ተመልክተናል። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን እስካሁንም ድረስ ልናውቅ የማንችለው ነገር አለ። ሌላ ነገር አለ።
ነገር ግን እነዚህ ሚስጥራት መገለጥ ሲጀምሩ … እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡- “ቆይ፤ አሁን አትጻፋቸው። ጥቂት ጠብቅ። በዚያ ቀን እኔ እገልጠዋለው፤ ስለዚህ አሁን አትጻፈው፤ ምክንያቱም የሚያነቡት ይንገዳገዱበታል። ተወው፤ አትጻፈው። (አያችሁ?)
ነገር ግን በዚያ ቀን ሊገለጥ በሚያስፈልግበት ጊዜ እኔ እገልጠዋለው።”
ሰባቱ ነጎድጓዶች ድምጻቸውን ሲያሰሙ መልእክታቸው ሁላችንንም ያንገዳግደናል። መልእክታቸው ልናስብ ከምንችለው ነገር ሁሉ በጣም የተለየ ይሆናል።
አሁን በለበስነው አካላችን ውስጥ ሆነን መነጠቅ አንችልም። መነጠቅ የምንችልበትን እምነት የምናገኘው አካላችን ወደ አዲስ የማይሞት የክብር አካል ሆኖ ከተለወጠ በኋላ ብቻ ነው።
ሆሴዕ 4፡6 ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤
የተገለጠውን የእግዚአብሔር ቃል መማር አለብን፤ አለበለዚያ እግዚአብሔር ሊሰራ ያሰበውን አናውቅም።
ወንድም ብራንሐም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገለጣቸውን ሚስጥራት መረዳት አለብን።
ጴጥሮስ በተሳሳተ ጊዜ አብረውት የነበሩ ደቀመዛሙርቱ በታላቅ ፍርሃት ውስጥ ነበሩ።
ጴጥሮስ የነበረበት ፍርሃት የስሕተት ቃል እንዲናገር አድርጎታል። ፍርሃት ውስጥ በነበረ ጊዜ በራሱ የመሰለውን ከሚናገር እግዚአብሔር እስኪናገር በጸጥታ ቢጠብቅ ይሻለው ነበር።
ማርቆስ 9፡6 እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር።
በሚያዩት ነገር በጣም ፈርተው ነበር፤ ደግሞም ግራ ገብቷቸዋል። ቤተክርስቲያን የሰራችው ሌላ ስሕተት ደግሞ ስለ ምን እንደምትናገር ሳታውቅ በማታቀው ባልተረዳችው ነገር ላይ አስተምሕሮ ማበጀቷ ነው።
ስለ ሰባቱ ነጎድጓዶችም ሆነ ስለ ጌታ ምጻት ምንም አናውቅም፤ አዲሱን የኢየሱስን ስምም አናውቅም ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፉም። መማር ያለብን የተጻፉትን ሚስጥራት ነው። ሰዎች ግን ያልተጻፉትን እናውቃለን በማለት እራሳቸውንም ሌሎችንም ያታልላሉ።
ማርቆስ 9፡7 ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም፦ የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።
ጴጥሮስ ከሰራው ትልቅ ስሕተት የተነሳ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር በደመና ውሰጥ ሰወረና ኢየሱስን ብቻ እንዲሰሙ አዘዛቸው። እርሱ ቃሉ ነው። ቃሉ ውስጥ የተጻፈውን ብቻ እመኑ።
በትንሳኤ እና በሰባቱ ነጎድጓዶች መገለጥ ወቅት ከሚኖረው ብዙ ሁካታና ግራ መጋባት የተነሳ ብዙ ነገር ምን እንደሆነ እነኳ ለአንዳንዶች ግልጽ አይሆንም። ስለዚህ ሙሉ በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ መከተል አለባችሁ ምክንያቱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ሊታመን የሚችል ምንም ነገር የለም።
ማርቆስ 9፡8 ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም።
ይህ ቁልፍ የሆነ ሰዓት ነበረ። ኢየሱስን ብቻ አዩ። ሁለት ትልልቅ ነብያት ሙሴ እና ኤልያስ ወደ ኢየሱስ ሊጠቁሙን ይችላሉ፤ እኛ ግን ኢየሱስን ብቻ ነው ማመን ያለብን። እርሱ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ከእርሱ ጋር ሲነጻጸር ሌላው ሰው ሁሉ ምንም ነው። ታላላቆቹ ነብያት ሙሴ እና ኤልያስ ሲሰወሩ ኢየሱስ ብቻ ተገለጠ።
እምነታችንን በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ማድረግ አለብን።
ዮሐንስ 1፡35 በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥
36 ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ፦ እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ።
37 ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።
መጥምቁ ዮሐንስ ታላቅ ሰው ነበረ፤ በድንቅ አገልግሎቱም ደቀመዛሙርትን አስከተለ። ነገር ግን ደቀመዛሙርቱን ወደ ኢየሱስ ያመለከታቸው ጊዜ እነዚያ ደቀመዛሙርት ኢየሱስን ተከተሉት እንጂ ዮሐንስን አልተከተሉም።
የዊልያም ብራንሐም ንግግሮች ደቀመዛሙርቱን ወደ ኢየሱስ የሚጠቁሙ ነበሩ ምክንያቱም ትምሕርቱ ኢየሱስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን የሚያሳይ ነበረ። ዊልያም ብራንሐም የተናገረውን ከተረዳነው መከተል ያለብን የተገለጠውን ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ ዊልያም ብራንሐምን አይደለም። እነዚህ የተገለጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ወደ ነበሩ የሐዋርያት እምነቶች ይመልሱናል። የምንመላለስበትን መንፈሳዊ ምሪት የምናገኘው በዚህ መንገድ ነው።
የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን አማኞች የሚያምኑትን ነው የምናምነው፤ እነርሱ የሚያደርጉትን ነው የምናደርገው?
ማርቆስ 9፡9 ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው።
ደቀመዛሙርቱ በተራራው ላይ ያዩት ነገር ሰባቱን የቤተክርስቲያን ዘመናት የሚመለከት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ እስከ ትንሳኤው ድረስ ያዩትን እንዳያወሩ አስጠነቀቃቸው ምክንያቱም ያዩት ነገር በዚያ ዘመን የነበሩትን አይሁዶች አይመለከትም። ቢነገራቸውን አያስተውሉትም። ቤተክርስቲያን የበዓለ ሃምሳ ዕለት ከተመሰረተች በኋላ ነው የኢየሱስ ሞት፣ ቀብር፣ እና ትንሳኤ ለሰዎች ትርጉም የሚሰጣቸው።
ማርቆስ 9፡10 ቃሉንም ይዘው፦ ከሙታን መነሣት ምንድር ነው? እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።
ትንሳኤ የሚለው ሃሳብ ከአእምሮዋቸው በላይ ሆነባቸው።
ይህ በተጨማሪ ሙሽራይቱ በመጨረሻ ምን እንደምትመስል የሚያሳይ ነው። የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ትንሳኤ ብዙ ጥያቄ የሚፈጥር ሚስጥራዊ ዘመን ነው የሚሆነው።
የኤልያስ ድርብ ምጻት
ማርቆስ 9፡11 እነርሱም፦ ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ እንዲገባው ጻፎች ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት።
ኢየሱስ መሲሁ መሆኑን ተረዱ። ነገር ግን ለምንድነው ቅዱሳት መጻሕፍት ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ነብዩ ኤልያስ ቀድሞ ይመጣል የሚሉት?
ማርቆስ 9፡12 እርሱም መልሶ፦ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናናል፤ ስለ ሰው ልጅም እንዴት ተብሎ ተጽፎአል? ብዙ መከራ እንዲቀበል እንዲናቅም።
ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ ከአእምሮዋቸው በላይ ነው።
ኢየሱስ የተናገረው ኤልያስ ሁሉን ነገር ሊያስተካክል ወደ ፊት ስለመምጣቱ ነው።
መጥምቁ ዮሐንስ ግን ሁሉንም ነገር አላቀናም። የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት የአዲስ ኪዳን ወንጌል መጀመሪያ ነበር።
ማርቆስ 1፡1 የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።
ማርቆስ 1፡4 ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።
በተጨማሪ ዮሐንስ አይሁዶችን ከመሲሁ ጋር አስተዋወቀ። አይሁዶች ከዚያ በፊት መሲህ ኖሯቸው አያውቅም፤ ስለዚህ ይህ ነገሮችን ወደነበሩበት የመመለስ አገልግሎት አይደለም። ይህ ፍጹም አዲስ አገልግሎት ነው።
ዮሐንስ የንሰሃ ጥምቀትን አስተዋወቀ። አይሁዶች ከዚያ በፊት ተጠምቀው አያውቁም። ሙሴ ቀይ ባሕር ውስጥ ባሳለፋቸው ጊዜ ምሳሌያዊ ጥምቀት ተጠምቀዋል ግን ውሃ አልነካቸውም። የአይሁድ ግለሰቦች ዮሐንስ ከመምጣቱ በፊት ውሃ ውስጥ በመጥለቅ ተጠምቀው አያውቁም።
መጥምቁ ዮሐንስ አይሁዶች በመቅደስ ያደርጉት የነበረው አምልኮ ተምልሶ እንዲመጣ አላደረገም ምክንያቱም አገልግሎቱን ከቤተመቅደሱ እሩቅ በሆነ ቦታ ነበረ ያከናወነው፤ የሐይማኖት መሪዎችንም ሁሉ የእፉኝት ልጆች ወይም መርዛማ እባቦች ብሎ አውግዟቸዋል።
ስለዚህ ሁሉን ሊያቀና ይመጣል የተባለለት ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ አይደለም።
ማርቆስ 9፡13 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ደግሞ መጥቶአል፥ ስለ እርሱም እንደ ተጸፈ የወደዱትን ሁሉ አደረጉበት አላቸው።
ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ኤልያስማ አስቀድሞ መጥቷል ከዚያም ገደሉት በማለት የተናገረው ስለ ዮሐንስ ነው።
ስለዚህ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላም ሚስጥር አለ።
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የጌታ ምጻት ሚስጥር ተገልጧል፤ በዚያ ሚስጥርም ውስጥ ተከትሎ የተገለጠው ሚስጥር የእኛ አካል በትንሳኤ ወደማይሞት አካል መለወጡ ነው። ይህንም ተከትሎ የተገለጠው የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ትንሳኤ ሚስጥር ሲሆን እርሱም የሚሆነው የጥንቷ ቤተክርስቲያን የነበራትን የእውነት አስተምሕሮ በሙሉ መልሶ የሚያመጣው የኤልያስ ሚስጥር ነው።
የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ሐዋርያት ያስተማሩት ሙሉ እውነት ነበረ።
ሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የተሰራው ስሕተት በእያንዳንዱ ከተማ ላይ ጳጳሳትን መሾም ነው። ይህ የኒቆላውያን ሥራ ነው። የኒቆላውያን ሥራ አንድን ሰው በምዕመናን ላይ ራስ አድርጎ መሾም ነው።
በ325 የተደረገው የኒቅያ ጉባኤ ቤተክርስቲያን ለመጽሐፍ ቅዱስ የነበራትን ፍቅር ገድሎ በሶስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ቤተክርስቲያን እንደ ስላሴ እና የስቅለት አርብ የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ የማይደግፋቸውን ትምሕርቶች እንድትቀበል አስገደዳት። ከዚያ በኋላ የመጣው የጨለማ ዘመን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በአራተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ተቀብሮ ጠፋ።
በ5ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ማርቲን ሉተር መዳን በእምነት ብቻ ነው የሚለውን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ አመጣ። ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉሙ ለ160 ዓመታት የትርጉሙ ትክክለኛነት ሲመረመር ቆየ።
በ6ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ጆን ዌስሊ ቅድስና እና የወንጌል አገልግሎትን ወደ ቤተክርስቲየን መለሰ። ይህም ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ሁሉ ወደተሰራጨበት ወደ ታላቁ የወንጌል ስርጭት ዘመን አመራ።
በ7ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሶ መጣ። ከዚያ በኋላ ዊልያም ብራንሐም የኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት በመግለጥ የመጀመሪያውን የቤተክርስቲያን ዘመን እውነት መልሶ አመጣ።
ወደፊት ይመጣል ብሎ ኢየሱስ የተናገረለት ኤልያስ ዊልያም ብራንሐም ነው። የዊልያም ብራንሐም አገልግሎት ኢየሱስን እንደተገለጠው የእግዚአብሔር ቃል ማስተዋወቅ ነው።
መጥምቁ ዮሐንስ መጥቶ እንዳለፈ ኢየሱስ የተናገረለት ኤልያስ ነው። እርሱም ኢየሱስን እንደ ሰው አስተዋወቀ።
ቃሉን የማንሰማ ከሆንን ዲዳዎች ነን ማለት ነው
መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው እውነት። ከእግዚአብሔር ቃል ከመናገራችን በፊት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን መስማት አለብን።
ራዕይ 1፡3 ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።
“የሚሰሙ” የሚለው በማስተዋል የሚሰሙ ማለት ነው። “የሚጠብቁ” የሚለውም በማስተዋል የሚጠብቁ ማለት ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የማንጠቅስ ከሆንን ከእውነት አንጻር ዲዳዎች ነን ማለት ነው።
በቤተክርስቲያኖች ውስጥ ያለው ትልቅ ችግር መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ነው።
በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ፈንታ ከ100 በላይ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ተዘጋጅተዋል። ሰይጣን ሰዎች ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን እንዳይሰሙ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው።
በተጨማሪ ሰይጣን ሰዎች የትኛውም መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም አይደለም ብሎ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል።
ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች እምነታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማረጋገጥ ትተዋል።
ከዚህም የተነሳ 45,000 ዓይነት ቤተክርስቲያኖች እና ዲኖሚኔሽኖች የተፈጠሩ ሲሆኑ ሁሉም እርስ በራሳቸው ይቃረናሉ። ቤተክርስቲያኖች የብዙ ዓይነት ልዩ ልዩ የአመለካከቶች ገበያ ከመሆናቸውም በላይ እያንዳንዱ ትክክለኛው እኔ ነኝ ማለታቸው በጣም ግራ የሚያጋባ ነገር ነው።
ማርቆስ 9፡14 ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ሲከብቡአቸው ጻፎችም ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አየ።
ጻፎቹ የአይሁድ መሪዎች ሲሆኑ ከደቀመዛሙርቱ ጋር አጋንንት ማውጣት ያቃታችሁ ለምንድነው እያሉ ሲያፋጥጧቸው ነበር።
ማርቆስ 9፡15 ወዲያውም ሕዝቡ ሁሉ ባዩት ጊዜ ደነገጡ፥ ወደ እርሱም ሮጠው እጅ ነሡት።
ሕዝቡ ኢየሱስን ባዩ ጊዜ እርሱ ግን ምንም እንደማይሳነው ወዲያው አወቁ።
ማርቆስ 9፡16 ጻፎችንም፦ ስለ ምን ከእነርሱ ጋር ትከራከራላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው።
ኢየሱስ ጻፎችን ስለ ምን እየተከራከሩ እንደነበር ጠየቃቸው። ጻፎች ግን ጸጥ አሉ። ከኢየሱስ ጋር ለመከራከር መሞከር እንደማያዋጣቸው ገብቷቸዋል። ደግሞም ጻፎች ደቀመዛሙርትን ለምን አጋንንት ማስወጣት አልቻላችሁም ብለው መጠየቃቸው ስሕተት መሆኑንም አውቀዋል። ጥያቄያቸውን ለኢየሱስ ቢደግሙለት እርሱ ደግሞ እናንተስ እራሳችሁ አጋንንትን ማስወጣት ያልቻላችሁት ለምንድነው ብሎ ይጠይቃቸው ነበር።
ቀጥሎ በአጋንንት የተያዘው ልጅ አባት ተናገረ።
የዚህ ልጅ አባት ሙሉውን እውነት ያውቁ የነበረበትን የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን አባቶች ይወክላል። በአጋንንት የተያዘው ልጅ እግዚአብሔር አንዳችም መልካም ነገር ያልመሰከረለት ሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ወደ አባቶች እምነት መመለስ ያለባቸውን ልጆች ይክላል።
ይህ አጋንንት ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳናነብብ እና እውነትን ከኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀስን መናገር እንዳንችል የሚያደርገን ስለሆን እግዚአብሔር ከዘመናችን ላይ ነቅሎ ይጥለዋል። ስለዚህ እውነትን በተመለከተ ደንቆሮና ዲዳ ሆነናል።
ማርቆስ 9፡17 ከሕዝቡ አንዱ መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤
ልጄ ዲዳ ነው። ልጅየው በመጨረሻው የቤተክርስቲን ዘመን ያሉትን እምነታቸውን ከኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ የማይችሉትን ልጆች ይወክላል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታ የተጻፉ ጥቅሶች ትርጉማቸው ምን እንደሆነ ስለማያውቁ ከቃሉ ብቻ እየጠቀሱ መናገር አይችሉም።
ማርቆስ 9፡18 በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፥ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፥ አልቻሉምም አለው።
ደቀመዛሙርቱ ይህንን ግትር አጋንንት የሚያስወጡበት አቅም አልነበራቸውም።
ዛሬም በዘመናችን ላይ የተለቀቀ ጠንካራ የአለማመን መንፈስ መኖሩን መገንዘብ አለብን።
ማርቆስ 9፡19 እርሱም መልሶ፦ የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው።
ኢየሱስ እኛ ሰዎች ያለብንን የእምነት ጉድለት ሲያይ ያዝናል። እምነት እንደጎደለው ትውልድ ነው የሚያየን። ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ስንገባ ወዲያው ተጠራጣሪዎች ነው የምንሆነው።
ማርቆስ 9፡20 ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ።
ጋኔኑ ኢየሱስ እንደሚያስወጣው አውቋል፤ ስለዚህ ከመውጣቱ በፊት የቻለውን ያህል ልጁን ለመጉዳት አንፈራገጠው። ብዙውን ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ኢየሱስ ችግራችንን ከመፍታቱ በፊት ችግራችን በጣም ይባባሳል። የችግራችን መባባስ የእምነታችን ፈተና ነው። ችግሮች እየተባባሱ በሚሄዱ ሰዓት እምነታችንን አጥብቀን ይዘን እንቀጥላለን? ነገሮች ሰላም በሆኑበት ሰዓት ማንም ሰው ማመን ይችላል።
ማርቆስ 9፡21 አባቱንም፦ ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤
ጋኔኑ ልጁ ውስጥ ገብቷል።
በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የምንገኝ ልጆች ወደ መጀመሪያው ዘመን ሐዋርያዊ አባቶች መመለስ አለብን። ከዚህም የተነሳ በዘመናችን የተገለጡትን የኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት ሰዎች እንዳያምኑ ለማድረግ ብዙ አጋንንት በሥራ ላይ ተሰማርተዋል። ዓላማቸውም የአሁኗ ቤተክርስቲያን እምነቷ እንደ መጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን አባቶች እምነት እንዳይሆን ለማድረግ ነው።
በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት አጋንንት የፈላጭ ቆራጭነትን መንፈስ በዓለም ላይ ለቀቁ። እንደ እስታሊን እና ሒትለር የመሳሰሉ ፍጥረታዊ ፈላጭ ቆራጮች ደግሞ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በተጀመረው ጭፍጨፋ ጊዜ በእስራኤል ላይ የነፍሰ ገዳይነት እና የጥፋት መናፍስትን ለቀቁ። ከዚህም የተነሳ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች አለቁ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እነዚህ የተለቀቁ አጋንንት የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖችን ማለትም መንፈሳዊ እስራኤልን ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ወደ አንድ ሕብረት ውስጥ ለማሰባሰብ የዓለም ቤተክርስቲያናት ምክር ቤት ውስጥ ገቡ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና የተደራጁ ዲኒሚኔሽናዊ ሐይማኖቶችን አስተምሕሮ ማመን የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች ሞት ነው፤ እነርሱም ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን ማመን ትተዋል።
ማርቆስ 9፡22 ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው።
ይህ ልጅ ሰባተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን የሚወክል ምሳሌ ነው።
የሁለት የዓለም ጦርነቶች እሳት። ለነጻነት ብለው ብዙ ጦርነቶችን የተዋጉ የብዙ ሕዝቦች ሁካታ የሞላበት ባሕር። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የመጣው የዘረኝነት ነውጥ እና የእርስ በርስ ጦርነት። በ2022 ዓ.ም ብቻ አፍሪካ ውስጥ ጦርነት የሚደረግባቸው 40 አካባቢዎች ነበሩ። በዚያ ላይ ተጨምሮ ደግሞ የሽብርተኝነት ሞገድ ዓለምን ሁሉ እያስጨነቀ ነው።
በዓለም ላይ ታላቅ የሆነችዋን ራሺያ የተባለች ሃገር የሚመራው ፑቲን የተባለ ፈላጭ ቆራጭ በአውሮፓ ውስጥ ታላቅ የሆነችዋን ዩክሬይን የተባለች ሃገር በ2022 መግዛት አለብኝ ብሎ ያስባል። የሰው ስግብግብነት ገደብ የለውም። ፑቲን ዩክሬይን ላይ ወረራ በመጀመር ሃገሪቱን እያወደመ ነው፤ በዓለም ኢኮኖሚም ላይ ኪሳራ እያስከተለ ነው።
ብዙ ድሆች የሚኖሩባትና በግፍ የተሞላችው ዓለማችን የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ እየጨመረባት ከመሆኑ የተነሳ የኑሮ ውድነት ችግር ገጥሟታል። እንደ ሐዋርያዊ አባቶቻቸው መሆን የሚፈልጉ የዚህ ዘመን ልጀች ብዙ ከባድ ፈተናዎች ውስጥ ያልፋሉ።
የእግዚአብሔር ርህራሄ እና እርዳታ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው።
ማርቆስ 9፡23 ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው።
እምነታችን የተመሰረተው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው። ስለዚህ ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በሙሉ ማመን አለብን።
መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው የእግዚአብሔርን እቅድ ሊገልጥልን የሚችለው።
ማርቆስ 9፡24 ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ።
አባትየው በአንድ አምላክ ብቻ ነው የሚያምነው፤ ለእርዳታ የጮኸውም ወደ ኢየሱስ ብቻ ነው። የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን አባቶች አማኞች ነበሩ ምክንያቱም አለማመናቸውን እንዲያስወግድላቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኸዋል።
ስለዚህ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ቃል እየመረመሩ የተጻፈውን በሙሉ አመኑ።
የሐዋርያት ሥራ 17፡10 ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤
11 እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።
ልጆች የሚኖሩበት የመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን በጣም አሳሳች ነው። 45,000 የተለያዩ ቤተክርስቲያኖ አሉ፤ ሁሉም ግን ትክክለኛዋ ቤተክርስቲያን እኔ ነኝ ይላሉ። ደግሞም ከ100 በላይ የተለያዩ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ። ከዚህም ሌላ ከ100 በላይ የተለያዩ የዊልያም ብራንሐም መልእክቶች አሉ። ከዚህም የተነሳ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹሙ እንከን የሌለበት የእግዚአብሔር ቃል ነው ብሎ የሚያምን ብዙም ሰው የለም። ከዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያኖች ውስጥ ያለው የአለማመን ችግር እየተባባሰ ነው ምክንያቱም መጨረሻው እየተቃረበ ሲመጣ ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን በር ውጭ ቆሞ ነው ያለው።
ማርቆስ 9፡25 ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና፦ አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፥ ከእርሱ ውጣ እንግዲህም አትግባበት አለው።
ችግሩ ምን እንደሆነ ኢየሱስ በትክክል ያውቃል። ልጅየው ደንቆሮ ስለሆነ መስማት አይችልም። መናገርም ያልቻለው መስማት ስለማይችል ነው።
ልጅየው የዘመን መጨረሻ ክርስቲያኖችን ይወክላል። አባትየው የመጀመሪያውን የቤተክርስቲያን ዘመን አባቶች ይወክላል። ኤልያስ ልጆችን ወደ አባቶች መመለስ አለበት።
የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል የማንሰማ ከሆንን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰን ልንናገር አንችልም።
ሰይጣን ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን እንድትሰሙ አይፈልጉም።
ስለዚህ የኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን ትርጉም በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በመተካትና የሰዎችን አእምሮ እንደ ስላሴ፣ ክሪስማስ፣ ዲሴምበር 25፣ የስቅለት አርብ፣ እና በመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ቃላት በመሙላት ቤተክርስቲያኖች ሰዎች እውነትን መስማት እንዳይችሉ ያደርጋሉ። እውነትን መስማት ካልቻሉ ደግሞ እውነተን መናገር አይችሉም፤ ስለዚህ እውነትን በተመለከተ ዲዳዎች ናቸው። በዚህ ዘመን ያሉትን ቤተክርስቲያኖች በሰው ሰራሽ ልማዶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ የስሕተት ትምሕርቶች አስሮ የያዘው በጣም ጠንካራ ጋኔን ነው። ለዚህ ነው የቤተክርስቲያን ሰዎች ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ውሃ ጥምቀት እና ስለ 7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት እውነቱን መናገር የማይችሉት።
ሕዝቡ ሰብሰብ ብለው መምጣታቸው ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ተሰባስበው አንዲት ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን እንደሚመሰርቱ ያመለክታል። ይህም የመጽፍ ቅዱስን ቃል የማይሰማውና የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል መናገር የማይችለው ጋኔን ልጅየውን (ማለትም እውነተኛ አማኞችን) ለቆ የሚወጣበት ጊዜ ነው።
ማርቆስ 9፡26 ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም፦ ሞተ እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ።
የአለማመንን መንፈስ ማስወጣት ልጅየው ላይ ከባድ ነገር ነበር። ብዙ ስሜታዊ ሕመም አስከትሎበታል። ጋኔኑ በወጣለት ሰዓት የሞተ ይመስል ነበር። የቤተክርስቲያን ሰዎች ልጁ የሞተ መሰላቸው ምክንያቱም የእነርሱን ቤተክርስቲያናዊ ትምሕርት አልቀበልም ብሏቸዋል። ብዙም ነገር የተሳካለት አይመስልም ነበር። እውነትን ማግኘት የሚቻለው በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ከማለፍ ጋር ነው።
ማርቆስ 9፡27 ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው ቆመም።
እውነትን የማግኛ መንገድ ከኢየሱስ ጋር የግል ሕብረት ማድረግ ነው።
በቤተክርስቲያን ልምምድ ላይ መደገፍ የለብንም። ዛሬ ሰዎች ትኩረታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በመስማማት ላይ ሳይሆን ከቤተክርስቲያን ጋር በመስማማት ላይ ነው። ብዙ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ብዙ ቤተክርስቲያኖችም አሉ። እንዲህ ከሆነ ታዲያ እውነት የሚገኘው እንዴት ነው?
ኢየሱስ የቆመው ከቤተክርስቲያን በር ውጭ መሆኑን ማሰብ አለብን። እውነት ያለው በእርሱ ዘንድ ብቻ ነው። አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት ይችል ዘንድ ዓይኑን ሊያበራለት የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው።
ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
ራዕይ 3፡20 እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ …
ኢየሱስ ቤተክርስቲያንን እንደ ቡድን ተሰብስባ እየፈለጋት አይደለም። አሁን ሰዎች በየግል እያገኘ ሊያበረታቸው ነው የሚፈልገው።
ግለሰቦች የኢየሱስን እርዳት በማግኘት የተገለጡትን የእግዚአብሔር ቃል ሚስጥራት እየተቀበሉ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያድጋሉ፤ የተገለጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራትም የእምነታቸው መሰረት ናቸው።
ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።
እምነታችን ጠንካራ እንዲሆን ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም እንከን የሌለበት እውነት መሆኑን ማመን አለብን።
ማርቆስ 9፡28 ወደ ቤትም ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ፦ እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምንድር ነው? ብለው ብቻውን ጠየቁት።
ደቀመዛሙርቱ በእምነታቸው ደክመው ነበር።
ማርቆስ 9፡29 ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም አላቸው።
ሰዎች ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳይሰሙ እና ከኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይጠቅሱ የሚያደርጋቸው ጋኔን ኃይለኛ ክፉ መንፈስ ነው። ጸሎት እና ጾም ራስን መግዛት የሚጠይቅ መንፈሳዊ ልምምድ ነው።
የትንሳኤው ሰዓት ግራ የሚያጋባ ሰዓት ነው
ማርቆስ 9፡30 ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ያስተምር ስለ ነበር ማንም ያውቅ ዘንድ አልወደደም፤
ኢየሱስ በገሊላ አለፈ፤ ነገር ግን ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም።
ማርቆስ 9፡31 ለእነርሱም፦ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጣል፥ ይገድሉትማል፥ ተገድሎም በሦስተኛው ቀን ይነሣል ይላቸው ነበር።
ማርቆስ 9፡32 እነርሱም ነገሩን አላስተዋሉም፥ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።
በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የሞቱት ቅዱሳን ከሙታን ሲነሱ የሚፈጠረውን ሁኔታ አናውቀውም።
ሙታን ተነስተው በሚናገሩ ጊዜ ሰዎች እንደማይሰሙዋቸውና እና እንደማያምኑዋቸው ኢየሱስ በአላዛር እና በሃብታሙ ሰውዬ ምሳሌ አማካኝነት አስጠንቅቋል። ከሙታን የተነሱ ሰዎች ሲናገሩ ማንም የማያምናቸው ለምንድነው?
ምክንያቱም ከሙታን የተነሱ ሰዎች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ብቻ ነው የሚናገሩት፤ ቤተክርስቲያኖች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማመን ትተዋል።
ስለዚህ ዛሬ ወደ ቤተክርስቲያን የሚመላለሱና የቤተክርስቲያናቸውን አስተምሕሮ ደግፈው መከራከር ብቻ የሚችሉ ሰዎች ከሙታን ከተነሱ ቅዱሳን ጋር ይከራከራሉ፤ ደግሞም የሚናገሩትንም አይቀበሏቸውም።
ሉቃስ 16፡31 ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።
ትንሳኤው በክሪስማስ ወቅት ቢፈጸም ብላችሁ አስቡ። የጌታን ልደት አክብሩ ተብለን አልታዘዝንም። “እንኳን ለገና በዓል አደረሳችሁ” የሚለው አነጋገር፣ ክሪስማስ፣ እና ዲሴምበር 25 መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደሉም። በመጀመሪያዎቹ ሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ክሪስማስ የሚባል በዓል በጭራሽም አልነበረም። ክሪስማስ ወደ ቤተክርስቲያን በ350 ዓ.ም እንዲገባ ያደረገው ፖፕ ዩልየስ ቀዳማዊ ነው። ከሙታን የተነሱ ቅዱሳን ቤተክርስቲያኖች በሳንታ ክሎስ እና በቀይ ኮፍያቸው ምን ምን ማለታቸው እንደሆነ አይገባቸውም። ከሙታን የተነሱ ቅዱሳን ክሪስማስን እና ሌሎች ልማዶችን አይቀበሉም፤ ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች ደግሞ ከሙታን የተነሱትን ቅዱሳን ይቃወሟቸዋል። ይህም በዚህ ዘመን የሚኖሩ ቤተክርስቲያን ተመላላሾች ወደ ሐዋርያዊ አባቶች አለመመለሳቸውን ያረጋግጣል። “Jingle bells” የሚለው የክሪስማስ መዝሙር አንዳችም መጽሐፍ ቅዱሳዉ መሰረት የለውም።
ልክ እንደ ዛሬዎቹ ክርስቲያኖች “አለስተዋሉም”። ከኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ የማይረዱት ነገር አለ፤ ነገር ግን ከራሳቸው ቤተክርስቲያን ውጭ ሌላ ሰው እንዲያስረዳቸው ለመጠየቅ በጣም ይፈራሉ፤ ምክንያቱም የራሳቸው ቤተክርስቲያን መሃይምነት ይጋለጥባቸዋል። የተለያዩ አመለካከቶች ያሉዋቸው 45,000 ዓይነት ቤተክርስቲያኖች ቢኖሩም እንኳ የእነርሱ ቤተክርስቲያን ትክክለኛዋ ቤተክርስቲያን እንደሆነች አጥብቀው ይሟገታሉ።
የስልጣን ወዳድ የቤተክርስቲያን መሪዎች እርግማን
ማርቆስ 9፡33 ወደ ቅፍርናሆምም መጣ። በቤትም ሆኖ፦ በመንገድ እርስ በርሳችሁ ምን ተነጋገራችሁ? ብሎ ጠየቃቸው።
ቅፍርናሆም ማለት “የምቾት ከተማ” ማለት ነው።
ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች ብዙ ጥረት የማይጠይቅና ብዙውን ጊዜ የሚያርፉበት የምቾት እምነት ነው የሚፈልጉት። የዛሬ ክርስቲያኖች መስቀሉን ሳይሸከሙ አክሊል ሊቀበሉ ይፈልጋሉ።
ለዚህ ነው የዚህ ዘመን ቤተክርስቲያኖች በሙሉ ማቴዎስ ምዕራፍ 25 ውስጥ በተጻፈው በ10ሩ ቆነጃጅት ምሳሌ የተገለጹት። ሴት ቤተክርስቲያንን ትወክላለች። ድንግል ሴት ንጹህ ሴት ናት፤ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ የዳኑ ክርስቲያኖችን ትወክላለች። ነገር ግን አምስቱ ሰነፎች ናቸው ምክንያቱም ድነዋል ግን በሰው ሰራሽ የቤተክርስቲያን ስሕተቶች ተታልለዋል።
ሰነፎቹም ልባሞቹም ቆነጃጅት አንቀላፍተው ተነሱ የሚለውን ጥሪ እየተጠባበቁ ናቸው። ይህም ዛሬ በቤተክርስቲያን ያሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ የሚገልጽ ምሳሌ ነው። ሁሉም አንቀላፍተዋል።
ከእንቅልፍ የሚቀሰቅሳቸው ጥሪ ሲመጣ ከቤተክርስቲያናቸው እንዲወጡ ይነግራቸዋል።
ቤተክርስቲያን መጠለያ ቦታ መሆን ይገባት ነበር፤ ነገር ግን የሽንገላ ወጥመድ ሆናለች።
ማቴዎስ 25፡5 ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
6 እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ።
ይህ ምሳሌ በየትኛውም ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ሰው ጌታ ሲመጣ ለመቀበል ዝግጁ እንዳልሆነ ያሳያል። ይህም የሆነበት ምክንያት ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን በር ውጭ ስለቆመ ነው።
ደቀመዛሙርቱ “እኔ እበልጣለው፤ እኔ እበልጣለው” በሚል የፉክክር ክርስትና ውስጥ ነበሩ። “እኔ ካንተ እሻላለሁ።” “የእኔ ቤተክርስቲያን ካንተ ቤተክርስቲያን ትሻላለች።”
ቤተክርስቲያኖች ውስጥ ራስን ማመስገን በዝቷል።
ደቀመዛሙርቱ ግን ራሳቸውን ከፍ ማድረጋቸውን ለኢየሱስ ገልጠው ለመናገር አፍረዋል። በመጨረሻው በሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ዘመን ኢየሱስ ስለ ቤተክርስቲያን አንዳችም መልካም ነገር አልተናገረም፤ እንደውም የዛሬዋን ቤተክርስቲያን ከሃዲ፣ ዕውር፣ መሃይም፣ ለብያለች፣ እና እግዚአብሔር ከአፉ ሊተፋት የቀረበች ስለመሆኗ ይነቅፋታል።
ማርቆስ 9፡34 እነርሱ ግን በመንገድ፦ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? ተባብለው ነበርና ዝም አሉ።
ሊናገሩ አልቻሉም፤ ምክንያቱም በልባቸው የሚያፍሩበት ነገር አስበዋል። እያንዳንዱ የራሱን ክብር እየፈለገ ነበር።
ጥማታቸው መክበርና ከፍ ብሎ መታየት ነበር።
ቤተክርስቲያኖ ስልጣን አላቸው። የስልጣን ጥም ያለባቸው ሰዎች ስልጣን እና ገንዘብ ያሳድዳሉ።
ስልጣን የሚፈልጉት ገንዘባችሁን ለመውሰድ ነው።
የቤተክርስቲያኖች እርግማን የኒቆላውያን ሥራ ነው። የኒቆላውያን ሥራ ማለት አንድን ሰው በምዕመናን ወይም በጉባኤው ላይ ከፍ ማድረግ ነው።
የፉክክር ክርስትና ውስጥ ማነው ከሁሉ ታላቅ የሚለው ጥያቄ ነው የሁሉን አእምሮ የሚቆጣጠረው።
ማርቆስ 9፡35 ተቀምጦም አሥራ ሁለቱን ጠርቶ፦ ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን አላቸው።
እራሳችሁን ከሁሉ የምትበልጡ አድርጋችሁ አትመልከቱ። ከዚያ ይልቅ ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ ሌሎችን ብታገለግሉ ይሻላችኋል። የሰው ዓይን ውስጥ ለመግባት የምትጥሩ ከሆነ ከእግዚአብሔ ፈቃድ ውጭ ሆናችኋል።
ማርቆስ 9፡36 ሕፃንም ይዞ በመካከላቸው አቆመው አቅፎም፦
ልጅ የሚወክለው በዘመን መጨረሻ የሚገኙ አማኞችን ነው። ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን አባቶች መመለስ ያለባቸውን ልጆች ይወክላል።
ልጆች በዚህ እንግዳ በሆነ ዓለም ግራ ይጋባሉ፤ ስለዚህ እንግዳ ዓለም ብዙ ጥያቄ አለባቸው፤ ስለዚህ መረዳት ይፈልጋሉ።
መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ልክ እንደ ልጆች መሆን አለብን። ተጨማሪ እውቀት እናገኝ ዘንድ ለመማር የተዘጋጀንና ብዙ ጥያቄ የምንጠይቅ መሆን አለብን።
ማርቆስ 9፡37 እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው።
በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነትን ፍለጋ ለመፈተሸ እርስ በራሳችንን ማበረታታት አለብን። መመለስ የማንችላቸውን ከባድ ጥያቄዎችን መቀበል አለብን፤ ምክንያቱም መቀበላችን ቤተክርስቲያን ዓይናችን ላይ የጋረደችብንን ጥቁር ጨርቅ ያስወግድልናል።
ማቴዎስ 7፡7 ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።
ማርቆስ 9፡38 ዮሐንስ መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ስለማይከተለንም ከለከልነው አለው።
ቤተክርስቲያን የተሸከመችው ሌላ እርግማን ደግሞ መለያየት ነው። ያ ሰውዬ የቤተክርስቲያኔ አባል ካልሆነ እግዚአብሔር ሊጠቀምበት አይችልም የሚል አመለካከት።
“ከለከልነው”። ከእኛ አንዱ ስላልሆነ ቤተክርስቲያኑን ዘጋንበት።
ኢየሱስ ግን ያደረጉትን አልተቀበላቸውም።
ማርቆስ 9፡39 ኢየሱስ ግን አለ፦ በስሜ ተአምር ሠርቶ በቶሎ በእኔ ላይ ክፉ መናገር የሚችል ማንም የለምና አትከልክሉት፤
40 የማይቃወመን እርሱ ከእኛ ጋር ነውና።
የፉክክር ክርስትና አደገኛ ወጥመድ ነው። እግዚአብሔር በሁሉም ሥፍራ የፈለገውን ሰው ይጠቀማል።
1ኛ ቆሮንቶስ 1፡12 ይህንም እላለሁ፦ እያንዳንዳችሁ፦ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ።
እያንዳንዱ ቡድን ከሌላ የተሻለ እንደሆነ ያስባል።
ማርቆስ 9፡41 የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ።
ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች በሃሳብ ከእነርሱ ጋር የማይስማሙ ሰዎችን በቀላሉ ያወግዛሉ።
ደግነት ግን የራሱ ሽልማት አለው።
በሰብዓዊ ርሕራሄ ብቻ ለሙሽራይቱ ቸር የሆኑ ሰዎች ሽልማት ይጠብቃቸዋል።
ስለዚህ ከአንድ ሰው ጋር በአስተምሕሮው ስላልተስማማህ ብቻ አታውግዘው። አስተምሕሮውን ልታወግዘው ትችላለህ፤ ነገር ግን ሰውየውን አታውግዘው። ይልቁንም ለሰውየው ቸር ሁንለት።
በሃሳቡ ያልተስማማኸው ሰው እኮ ድንገት ትክክል ሊሆንም ይችላል።
ለሰውየው ደግ ከሆን የፍርድ ቀን የሚገጥምህን ዕጣ ፈንታ ታሳምረዋለህ።
ሰውየው ስሕተት ውስጥ ቢሆን እንኳ ለእርሱ ደግ በመሆንም በራስህ ላይ የምታመጣው ምንም ጉዳት የለም፤ እንደውም ሰውየው ሃሳቡን እንዲለውጥ ምክንያት ልትሆነውም ትችላለህ።
በመጨረሻው ዘመን ሕጻናትን አታሳስቱ
ማርቆስ 9፡42 በእኔም ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር።
በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ ከእነርሱ ጋር የማይስማማውን ሁሉ ያወግዛሉ። ነገር ግን በዘመን መጨረሻ ስለምትገኘው ቤተክርስቲያን የሚናገር ትንቢትም ይሁን ምሳሌ ስለ ቤተክርስቲያን አንዳችም መልካም ነገር አይናገርም።
የምትፈርድበት ሰው ወደ ሐዋርያዊ አባቶች እየተመለሱ ካሉ ልጆች መካከል አንዱ ሊሆንም ይችላል። ነገሩ እንዲህ ከሆነ በራስህ ላይ እየፈረድክ ነህ ማለት ነው።
የወፍጮ ድንጋይ አገልግሎቱ እህል መፍጨት ነው፤ የተፈጨውንም እህል ትበሉታላችሁ። ጠለቅ ያሉትን የመጽፍ ቅዱስ ሚስጥራት መገለጥ በማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ለመረዳት ቀላል እንዲሆኑ ማድረግ አለብን። ነገር ግን ይህ ብዙ ትጋት የሚጠይቅ ከባድ ኃላፊነት ነው። መገለጦቹ ካገኘን በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለዘመን መጨረሻ ሕጻናት ማብራራት እንችላለን፤ እነርሱም የተገለቱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት በተረዱ ጊዜ ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ሐዋርያዊ አባቶች እምነት መመለስ ይችላሉ።
ሚልክያስ 1፡1 የእግዚአብሔር ቃል ሸክም
መጽሐፍ ቅዱስን ማብራራት ካልቻልን የዊልያም ብራንሐም አገልግሎት አልገባንም ማለት ነው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የያዝነው የተሳሳት መረዳት በሙሉ በአንገታችን ዙርያ እንደ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ ሆኖ ሰው ሰራሽ የሆኑ እምነቶችና ባዕድ ልማዶችን የሚከተሉ እረፍ የሌላቸው ቤተክርስቲያን ተመላላሾች የሞሉበት ባሕር ውስጥ ያሰጥመናል። እነዚህ ሰዎች አብዛኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማብራራት አይችሉም። ስለዚህ በዘመን መጨረሻ ስለሚገኙ ቤተክርስቲያኖች የተጻፉ አሉታዊ ትንቢቶችን እና ምሳሌዎችን በሙሉ ሳያነቡ ያልፋሉ። ራሳቸውን እያታለሉ ይኖራሉ።
ማርቆስ 9፡43 እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ … ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመሄድ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል።
መጽሐፍ ቅዱስን በተግባር እንዳትታዘዙ የሚያግዳችሁን በመንገዳችሁ የቆመ ነገርን በሙሉ አስወግዱ።
የትኛውም የቤተክርስቲያን አገልግሎት ሥራ ለጌታ ምጻት ሊያዘጋጃችሁ አይችልም።
በግላችሁ ጥቂት ነገር ብቻ ልትሰሩ ትችላላችሁ ግን ያ ጥቂት ነገር በቤተክርስቲያናችሁ ልማድ ውስጥ ሆናችሁ ከምትሰሩት ብዙ ነገር ይበልጣል። የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል መለወጥ የሚያስከትለው ቅጣት በጣም ከባድ ነው።
ማርቆስ 9፡44 ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት
ሲኦል ውስጥ ሳላችሁ የሲኦል እሳት ሊጠፋ አይችልም። የሲኦል እሳት የሚጠፋው ውስጡ የገቡ ሐጥያተኞች በሙሉ የቅጣት ዘመናቸውን ሲጨርሱ ነው። የሲኦል እሳት ዘላለማዊ አይደለም። ዘላለማዊ ቢሆን ኖሮ ውስጡ የሚገቡ ሰዎች ሲኦል ውስጥ ለመሆን የዘላለም ሕይወት ያስፈልጋቸዋል። የዘላለም ሕይወት ግን ከሲኦል እሳት የምትድኑበት ነው።
ማርቆስ 9፡45 እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ … ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመጣል አንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።
እንዴት መመላለስ እንዳለባችሁና የትኛውን መንገድ መከተል እንዳለባችሁ የሚያሳዩ ልማዶችን ቤተክርስቲያኖች ለየራሳቸው አበጅተዋል። ቤተክርስቲያኖች የሚሉትን ትታችሁ ሂዱ። ልንከተለው የሚገባን ብቸኛው መንገድ ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን የሚያደርሰንን ብቻ ነው። ፈጠን ፈጠን እያላችሁ በብልጽግና ወንጌል መንገድ ከምትሄዱ ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ብታዘግሙ ይሻላችኋል።
ማርቆስ 9፡46 ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት
ከሲኦል እሳት ውስጥ ማምለጫ መንገድ የለም።
ማርቆስ 9፡47 ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጣት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ … ወደ ገሃነመ እሳት ከመጣል አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል።
ዓይናችሁ የምታዩበት የአካላችሁ ክፍል ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆኑ የግል እይታዎቻችሁና አስተሳሰባችሁ ተለዩ። ነገሮችን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚገልጥበት መንገድ ውጭ እንድታዩ የሚያደርጋችሁን የግል አመለካከታችሁን ጣሉ።
ማርቆስ 9፡48 ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት
መጽሐፍ ቅዱስን ያለመከተል ውጤቱ በጣም ከባድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከማይደግፋቸው የግል አመለካከቶቻችሁም ሆነ ከቤተክርስቲያን አመለካከቶች ሽሹና አምልጡ።
ሁላችንም በፈተና እሳት ውስጥ ማለፍ ይገባናል።
ማርቆስ 9፡49 ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና፥ መሥዋዕትም ሁሉ በጨው ይቀመማል።
ጨው ስጋ እንዳይበላሽ ያደርጋል። የሚደርስብን መከራ የእውነት መጽሐፍ ቅዱስን እናምን እንደሆን ይፈትነናል። በአቋማችን ማመቻመች አልተፈቀደልንም። የእውነት የምናምነው ምን እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ማስመሰልና ስሕተት ሁሉ በመከራ እሳት ከላያችን ላይ ተቃጥሎ ይጠፋል።
ማርቆስ 9፡50 ጨው መልካም ነው፤ ጨው ግን አልጫ ቢሆን በምን ታጣፍጡታላችሁ? በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።
ለእግዚአብሔር ቃል እውነተኛ ፍቅር ሊኖራችሁ ይገባል፤ እንዲሁም በመንገዳችሁ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ወይም እንቅፋት ቢገጥማችሁ እንኳ ቃሉን ለመረዳት ቆርጣችሁ መነሳት ያስፈልጋችኋል።
ነገር ሁሉ ሲበላሽ እንኳ በእምነት ጸንታችሁ ትቆማላችሁ?
መንገዳችሁ ላይ ተግዳሮት ሲገጥማችሁ ተግዳሮቱን አልፋችሁ የምትሄዱበት አቅም ያስፈልጋችኋል።
መስቀሉን ለመሸከም ተዘጋጅተናልን?
ተዘጋጅታችሁ ከሆነ ከሌሎች ሰዎች እውነትን ከሚከተሉም ከማይከተሉትም ጋር ሰላም ሊኖራችሁ ይገባል። እነርሱ ቢከተሉ ባይከተሉ የራሳቸው ውሳኔ ነው። እውነትን እንዲያምኑ ልታደርጓቸው አትችሉም።