ማርቆስ 6 - የትንሹ ልጅ ምሳ 5,000 ሰዎችን አጠገበ



እውነት በቤተሰብ ውስጥ ተቀባይነት አጣች። ከሕጋዊ ጋብቻ በኋላ ፍቺ፣ እና እንደገና ጋብቻ አይቻልም። መከራ ኢየሱስን እንድንከተል ያደርገናል

First published on the 19th of December 2022 — Last updated on the 19th of December 2022

ኢየሱስ ወደ ናዝሬት በሄደበት የራሱ ቤተሰቦች አንቀበልህም አሉት

 

ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ውስጥ እያገለገለ ነበረ።

ማርቆስ 6፡1 ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።

ከዚያም ወዳደገበት ከተማ ወደ ናዝሬት ሄደ።

 

 

ማርቆስ 6፡2 ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና፦ እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው?

ሰዎች የተላመዱትን ነገር እንደ ብርቅ አያዩትም። ከዚህም የተነሳ በመካከላቸው ተወልዶ ያደገ ሰው ዝነኛ ሲሆን ብዙም አይደነቁም።

ሰዎቹ በኢየሱስ ትምሕርትና በሚያደርጋቸው ተዓምራት በጣም ተገርመው ነበር። ነገር ግን ይህን አስደናቂ ኃይል ከየት እንዳመጣው አላወቁም።

ማርቆስ 6፡3 ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር።

የናዝሬት ሰዎች ግራ ተጋቡ። በኢየሱስ ቤተሰብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ እንደማንኛውም ሰው ተራ ሰዎች ነበሩ። ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ዮሴፍና ማርያም አራት ወንዶች ልጆችና ሴትች ልጆች ወልደዋል። ነገር ግን እነዚህ ልጆች የኢየሱስ ተከታዮች አልነበሩም።

ጌታን ስትቀበሉ ቤተሰቦቻችሁ ራሳቸው ይነሱባችኋል።

ማርቆስ 6፡4 ኢየሱስም፦ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው።

ነብይን ቤተሰቡና ዘመዶቹ እንዲሁም የሃገሩ ሕዝብ አይቀበሉትም። በቅርበት የምናውቀውን ሰው በድንገት እግዚአብሔር ሊጠቀምበት ሲጀምር ለማመን እንቸገራለን። ኢየሱስን ይቀበሉት የነበሩት ሌሎች ሰዎች የሌላ ሃገር ሕዝብ ነበሩ።

ማርቆስ 6፡5 በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም።

ባደገበት በናዝሬት ከተማ ኢየሱስ ብዙም ሊሳካለት አልቻለም።

ማርቆስ 6፡6 ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር።

ባለማመናቸው ኢየሱስ ተደነቀ። እነዚህ ሰዎች ከዘመናዊ ክርስቲያኖች ጋር ይመሳሰላሉ፤ የዘመናችን ክርስቲያኖች የጌታን ልደት እንዲያከብሩ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይጠይቃቸው ያከብራሉ። ስለዚህ ክሪስማስ ብለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ቃል ፈጠሩ። ዲሴምበር 25ም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም፤ ስለዚህ ክሪስማስ በዓመቱ ውስጥ ታላቁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ በዓል ነው። አለማመን ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈ ነገር ስታምኑ ነው። “የስቅለት አርብ፣” “የፋሲካ ሰኞ፣” ኩዳዴ ጾም፣ የፋሲካ እንቁላሎች፣ የፋሲካ ጥንቸሎች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉም።

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው።

ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ይዘው መዞር ከመልመዳቸው የተነሳ የሚያምኑት ነገር አብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ መሆኑን አያውቁም። የቤተክርስቲያን ልማዶች መጽሐፍ ቅዱስን ተክተዋል። ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተት የመሰላቸውን ይተቻሉ፤ ነገር ግን የሚሄዱበትን ቤተክርስቲያን አይተቹም። ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይልቅ አክብረው የሚቀበሉት የቤተክርስቲያናቸውን ልማዶች ነው። አይሁዶችም ከኢየሱስ ይልቅ ፈሪሳውያን መሪዎቻቸውን ይሰሙ ነበር።

ማርቆስ 6፡7 አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥

ኢየሱስ 12 ሐዋርያትን መረጠና ሁለት ሁለት እያደረገ ላካቸው።

 

ሰባኪዎች እግዚአብሔርን መታመን መለማመድ አለባቸው

 

ማርቆስ 6፡8 ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው።

ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር እንዲተማመኑና ለራሳቸው ምንም ነገር፣ ምግብም ይሁን ገንዘብ እንዳያዘጋጁ ነው የተነገራቸው።

ደቀመዛሙርቱ ለግል ትርፋቸው ሳያስቡ እንዲያገለግሉ ነው የተነገራቸው።

ከረጢት እረኞች ከቤት ሲወጡ የሚይዙት ትንሽዬ ቦርሳ ነው። ደቀመዛሙርቱ ከረጢት ሳይይዙ ከወጡ ለራሳቸው ምቾት የሚሆን ነገር ይዘው መሄድ አይችሉም።

ዳዊት እረኛ በነበረ ጊዜ ይዞ በሚዞረው ከረጢት ውስጥ ነው ለወንጭፉ የሚሆኑ ጠጠሮችን የያዘው።

1ኛ ሳሙኤል 17፡40 በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ።

 

በትር ረጅም መንገድ ለሚሄዱ ሰዎች ድጋፍ ይሰጣል። እግዚአብሔር ለሥራ የተዘጋጁ ሰዎችን ይፈልጋል።

ማርቆስ 6፡9 በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ።

የግድ የሚያስፈልጋቸውን ብቻ ነው መያዝ ያለባቸው።

ጫማዎቻቸው እየተመላለሱ እንዲሰብኩ ያስችሏቸዋል። እጀ ጠባብ ወይም ጃኬት ምቾታቸውን ይጨምረዋል፤ ስለዚህ ኢየሱስ ከአንድ በላይ አትያዙ አላቸው። ወንጌልን መስበክ ገንዘብ ለማግኘት ወይም ለምቾት አይደለም። ከባድና ብዙ አደጋዎች ያሉበት ሥራ ነው።

ዳንኤል ባየው ምስል ውስጥ ያሉት እግሮች ሰባቱን የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላሉ። የወርቁ ራስ የባቢሎንን ሃብት ይወክላል።

ትኩረቱ ግን እግሮቹ ላይ ነው፤ እነዚህም እግሮች በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ወንጌልን ለመስበክ የሚመላለሱ እግሮች ናቸው። የዛሬ ክርስቲያኖች የተጸናወታቸው የገንዘብ ሃሳብ ቢሆንም በዚህ ምስል ውስጥ ግን ገንዘብን ስለሚያስበው ራስ ምንም ትኩረት አልተደረገም። የዘመናችን ቤተክርስቲያን ሰዎች “ተመልከቱ ያለኝን የገንዘብ ብዛት፤ እግዚአብሔር እየባረከኝ ነው” ማለት ይወዳሉ።

 

 

ማርቆስ 6፡10 በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ።

ደቀመዛሙርቱ ለስብከት ሲሄዱ የተቀበሏቸውን ቤቶች ቤቶች መባረክ ይችላሉ።

የጥንቷ ቤተክርስቲያን አባላት የሚሰበሰቡት በመኖሪያ ቤቶች ነበር። በአንድ ቤት ውስጥ ጥቂት ሰዎች ሲሰበሰቡ አንድን ሰው ከቤተክርስቲያን በላይ ከፍ ከፍ ለማድረግ አያመችም። አንድን ሰው የቤተክርስቲያን ራስ አድርጎ መሾም ነው የጥንቷን ቤተክርስቲያን ወደ ስሕተት መንገድ ያስገባት። “የቤተክርስቲያን ሕንጻ” (ይህ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም) ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው ሕንጻ በ220 ዓ.ም አካባቢ ነበር። ስለዚህ የዛሬዎቹ የቤተክርስቲያን ሕንጻዎች አጀማመራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም።

ብቸኛው ታዋቂ ሕንጻ ኢየሩሳሌም ውስጥ የነበረው ቤተመቅደስ ነው። ኢየሩሳሌም ደግሞ ዋነኛዋ ቤተክርስቲያን ተደርጋ ትቆጠር ነበር። እግዚአብሔር ግን በ70 ዓ.ም ቤተመቅደሱንና ኢየሩሳሌምን አፈራረሳቸው። ከዚያ ወዲያ እግዚአብሔር ትኩረቱን ያደረገው ወንጌልን ከቤት ወደ ቤት በማስፋፋት ላይ ነው። ስልጣን ወዳድ የሆኑ ሰዎች ከክርስቲያኑ ሕዝብ በላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግና ገንዘብ በማከማቸት ላይ ትኩረት አደረጉ። የቤተክርስቲያን መሪዎች ስልጣንን የፈለጉት የሕዝቡን ገንዘብ ለመውሰድ ነው። (ትክክለኛ ቤተክርስቲያን የሚባሉት ሕዝቡ ናቸው ምክንያቱም ሕንጻው ቤተክርስቲያን አይደለም)። ጳጳሳት ትልልቅና ውብ በሆኑ ቤቶች ውስጥ መኖር ጀመሩ። ለሰባኪዎችም ክርስትና ጥሩ ክፍያ የሚያስገኝ ሙያ ሆነ።

ማርቆስ 6፡11 ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው።

ሕዝቡ ደቀመዛሙርቱን ካልተቀበሉዋቸው፤ ደቀመዛሙርቱ ትተዋቸው ያልፋሉ።

አማኞች በአሕዛብ ምስሉ እግር ውስጥ ባለው ሸክላ (አማኞች) እና በብረቱ (በድርጅታዊ አስተዳደር ብቃት በተካነ አንድ የቤተክርስቲያን ራስ የሆነ ሰውን የሚከተሉ ዲኖሚኔሽናዊ ክርስቲያኖች) ነው የተወከሉት። ቃሉን የማይቀበሉ የማያምኑ ሰዎች ደግሞ ከእግሮቹ በታች ባለው አፈር ነው የተወከሉት፤ ስለዚህ እነርሱ በእግሩ ውስጥ ያለው ሸክላ አካል አይሆኑም።

ብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጻፉት በሰዶም እና ገሞራ ይኖሩ የነበሩ የማያምኑ ሰዎች በዘመናቸው የመጣውን እወነት አንቀበልም በማለታቸው በእሳት ተቃጥለው ጠፉ። አሁን ግን መሲሁ ራሱ መጥቷል። መሲሁን አለመቀበል በጣም የከፋ ሐጥያት ነው።

ማርቆስ 6፡12 ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥

ንሰሐ ሰበኩ ምክንያቱም ንሰሐ ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቂያ የመጀመሪያ እርምጃ ነው።

ማርቆስ 6፡13 ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።

ደቀመዛሙርት የእግዚአብሔርን ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል ገለጡ።

 

ከጋብቻ ወዲያ ፍቺ እና እንደገና ጋብቻ አይፈቀድም

 

ማንኛውም ሰው ወይም ሴት አግብተው ሲፈቱ የመጀመሪው የትዳር አጋራቸው በሕይወት ባለበት ጊዜ ሁሉ ድጋሚ ማግባት አይችሉም። የጋብቻ ቃልኪዳን ሞት እስኪለየን ድረስ የሚል ነው።

ሕጋዊ ጋብቻ ሊፈርስ የሚችልበት ሌላ ምንም መንገድ የለም።

ማርቆስ 6፡14 ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።

ንጉስ ሔሮድስ ስለ ኢየሱስ ሲሰማ መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት የተነሳ መሰለው።

ማርቆስ 6፡15 ሌሎችም፦ ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም፦ ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ።

መሲሁ እንደ ሰው ሆኖ መምጣቱን ማንም ሊያስተውል አልቻለም።

ሁላቸውም ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከነበሩ ነብያት አንዱ መስሏቸዋል።

ዛሬ የምናውቀው እውነታ የበፊቱ ተቃራኒ ነው። ኢየሱስ ዛሬ እንደ ሰው ሆኖ አልመጣም፤ የመጣው እንደ ተገለጠው ቃል ሆኖ ነው። ብዙ የሜሴጅ ሰባኪዎች የመጨረሻው ዘመን ነብይ ኢየሱስ ነው በማለታቸው ተሳስተዋል።

ማርቆስ 6፡16 ሄሮድስ ግን ሰምቶ፦ እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ።

መጥምቁ ዮሐንስ የተገደለበት ምክንያት ስለ ጋብቻ እና ፍቺ በድፍረት በመናገሩ ነው።

ማርቆስ 6፡17 ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤

የፊሊጶስ ሚስት ሔሮድስን ለማግባት ብላ ፊሊጶስን ፈታዋለች።

ማርቆስ 6፡18 ዮሐንስ ሄሮድስን፦ የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና።

መጥምቁ ዮሐንስ ለመናገር ፍርሃት አልነበረውም። ማንም ሰው ፈቶ ማግባት አይችልም።

ይህም እምነቱ ሕይወቱን አሳጥቶታል።

ብዙ ቤተክርስቲያኖች ዛሬ ፍቺ እና እንደገና ጋብቻ የሚፈቅዱት ለዚህ ነው። ይህ በሰዎች ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አስተምሕሮ ነው። ፓስተሮች ፍቺ እና እንደገና ጋብቻ አንፈቅድም ቢሉ ሕዝቡ ቤተክርስቲያንን ጥለው ይሄዳሉ።

የቤተክርስቲያን መሪዎች ደግሞ ተወዳጅ መሆንና ሰዎችን ወደ ቤተክርስቲያናቸው መሳብ ይፈልጋሉ፤ ስለዚህ ሰዎች የፈለጉትን እንዲያምኑ ይፈቅዱላቸዋል።

ፍቺ እና እንደገና ጋብቻ ዝሙት ነው። በባልና በሚስት መካከል የተደረገው የመጀመሪያው የጋብቻ ቃልኪዳን ብቻ ነው ዋጋ ያለው። ይህም ቃልኪዳን አንዳቸው እስኪሞቱ ድረስ የጸና ነው። የመጀመሪያው የትዳር አጋር በሕይወት ሳለ ሁለተኛው የጋብቻ ቃልኪዳን ተቀባይነት የለውም።

ማርቆስ 10፡11 እርሱም፦ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤

12 እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።

ሄሮድያዳ መጥምቁ ዮሐንስን አጥብቃ ትጠላዋለች ምክንያቱም “ሕጋዊ ሽፋን” የሰጠችውን ዝሙቷን አጋልጦባታል።

ማርቆስ 6፡19 ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤

ሄሮድያዳ ሴት እንደመሆኗ ቤተክርስቲያንን ትወክላለች። የቤተክርስቲያን ሰዎች ምንም የማያመቻምቸውን የኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መስማት አይፈልጉም። ዊልያም ብራንሐም የዘመን መጨረሻ ነብይ መሆኑን መቀበልም ሆነ እርሱን ማዳመጥ አይፈልጉም።

ቤተክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ደስ ባላቸው መንገድ ማገልገል ይፈልጋሉ፤ ይህም የፈለጉትን ለማድረግ እንዲመቻቸው ነው። ይህ ምቾትን ማዕከል ያደረገ ሐይማኖት ነው። የብልጽግና ወንጌል። ክርስቲያኖች አክሊል ይፈልጋሉ ነገር ግን መስቀሉን አይቀበሉም።

ማርቆስ 6፡20 ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤

ሔሮድስ ለመጥምቁ ዮሐንስ አክብሮት ነበረው፤ ስብከቱንም መስማት ይወድ ነበር። ነገር ግን ስብከቱን ሰምቶ ሕይወቱን ማስተካከል አይፈልግም ነበር።

ነገር ግን ሔሮድስ በሴት ልጁ (ሴት ቤተክርስቲያንን ትወክላለች) እና በመጥምቁ ዮሐንስ መካከል ምርጫ ሲቀርብለት ሴቲቱን መረጠና ነብዩን ገደለው።

የሜሴጅ ተከታዮች የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በሚፈልጉበት መንገድ ሊተረጉሙ ሲፈልጉ መጽሐፍ ቅዱስን እና ወንድም ብራንሐም የተናገራቸውን ቃላት አይቀበሉም።

የሜሴጅ አማኞች ወንድም ብራንሐም በፍጹም የማይሳሳተው የሰው ልጅ ነው ይላሉ።

እርሱ ግን የማልሳሳት ነኝ አላለም፤ ደግሞም የሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን መልአክ ወይም መልእክተኛ እንደመሆኑ መጠን እርሱ የሰው ልጅ አይደለም።

62-1007 የበሩ መክፈቻ

ሰዎች ሚስታቸውን ትተው ትክክለኛዋን አጥንታቸውን ፍለጋ መውጣት አለባቸው እያሉ ይሰብካሉ፤ በተጨማሪ ደግሞ እኔ ልሳሳት እንደማልችል አድርገው ያወራሉ። … ከዚህም የባሱ አንዳንድ አስደንጋጭ ነገሮችን ይናገራሉ።

65-0725 በዘመን መጨረሻ የተቀቡ ሰዎች

… “የሰባተኛው መልአክ መልእክት፤ የማሕተሞቹ መፈታት።” ምን ይሆን?

መልአኩ የሰው ልጅ አይደለም፤ ነገር ግን መልአኩ ወይም መልእክተኛው የሰው ልጅን ይገልጠዋል። አሁን ልዩነቱ ገባችሁ?

ማርቆስ 6፡21 በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና

እኛ ሰዎች ልደት የማክበር አባዜ ተጸናውቶናል። የልደት ቀን ትልቅ ድግስ ለመደገስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከሆነው መንገድ ለመውጣት የሚያመች ቀን ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የየትኛውም ጻድቅ ሰው የልደት ቀን አልተጠቀሰም።

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን የልደት ቀን እንድናከብር አልጠየቀንም።

የልደት ቀን ከአራት መቶ ዓመታት ጸጥታ በኋላ እስራኤል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠው ነብይ እንዲገደል ምክንያት ሆኗል።

ከዚያ በኋላ አይሁዶች ኢየሱስን እራሱን ሊገድሉ ተነስተዋል። ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ ነው።

ዮሴፍ ግብጽ ውስጥ ከዳቦ ጋጋሪ እና ከጠጅ አሳላፊ ጋር በእስር ቤት በነበረ ጊዜ (ይህ በመጨረሻው እራት ላይ የቀረበው እንጀራና ወይን ነው) ዳቦ ጋጋሪው በፈርዖን የልደት ቀን ተገደለ።

እንጀራው የኢየሱስ ሞት ምሳሌ እንዲሆን በመጨረሻው እራት ላይ ተቆርሷል።

ስለዚህ ፈርዖንም በልደት ቀኑ ሰው ገድሏል፤ ይህም የኢየሱስን ሞት ያመለክታል።

ስለዚህ እግዚአብሔር እውነት ስለ ልደት ቀን ግድ ይለዋል?

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ልደት ቀን አክብሩ ብሎ አላዘዘንም።

ማርቆስ 6፡22 የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን፦ የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤

ልጅቷ በዘፈኗ ሔሮድስን አዝናናችው። የሴቶች ውበት እንዲህ ነው ሰውን ለጊዜው የሚያዝናናው።

ማርቆስ 6፡23 የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት።

ይህ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ነው። አንድ ሰው እንዴት ለአንዲት ወጣት ዘፋኝ ያልታወቀ ነገር ቃል ይገባላታል?

ሴት ቤተክርስቲያንን ትወክላለች።

ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን የምትነግራቸውን ሁሉ ለማመንና ለማድረግ ቃል በመግባታቸው ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ያደርጋሉ።

ማርቆስ 6፡24 ወጥታም ለእናትዋ፦ ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች።

ልጅቱ እናቷን ጠየቀች፤ እናትየውም ቃል የሚያመጣው ነብይ ይገደልልኝ ብላ ጠየቀች።

ልጅየው ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖችን ትወክላለች። እናትየው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ትወክላለች። ስለዚህ በዘመን መጨረሻ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች ወደ እናታቸው ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እምነት ይመለሳሉ፤ በአንድነትም ነብዩ ያመጣውን የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛ መገለጥ ለማጥፋት ይስማማሉ።

ማርቆስ 6፡25 ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው።

በመጨረሻው ዘመን ስሕተት በግልጽ ይሰራል።

“ወዲያውም ፈጥና” የሚለው ቃል ሰይጣን በመጨረሻው ዘመን በነብዩ የተገለጡትን የእግዚአብሔር ቃል ሚስጥራት ለማበላሸት ምን ያህል እንደሚጓጓ ያሳያል።

ቤተክርስቲያኖች ለዊልያም ብራንሐም ጆሮ ዳባ ልበስ ይላሉ ወይ ደግሞ ዊልያም ብራንሐም እንደ እግዚአብሔር ድምጽ ሆኖ የሚናገረው የማይሳሳተው የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብለው ከፍ ከፍ ያደርጉታል። ከዚህም የተነሳ የዊልያም ብራንሐም ንግግሮች መጽሐፍ ቅዱስን ከመግለጥ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ይተካሉ።

አዲስ ኪዳን ውስጥ “የእግዚአብሔር ድምጽ” ተብሎ አልተጻፈም።

ማርቆስ 6፡26 ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም።

ሔሮድስ ነብዩን ሊገድል አልፈለገም ነበር።

ነገር ግን ቤተክርስቲያንን የሚወክሉት ሴቶች ካልተገደለልን አሉ። የሜሴጅ ቤተክርስቲያኖች የሰውን ንግግር ጥቅሶች በራሳቸው ፍላጎት ተርጉመው እንደፈለጉት ጠምዝዘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን እውነት የሚቃረን አስተምሕሮ ያዘጋጃሉ። የሜሴጅ ቤተክርስቲያን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ትተዋል። እምነታቸው ትክክል መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ ትተዋል።

ማርቆስ 6፡27 ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥

በድጋሚ በልደት ቀን የነፍ ግድያ ተፈጸመ። እግዚአብሔር በዚህ ሁሉ ምን እየነገረን ነው?

የዮሐንስ እሬሳ የአይሁድ ሕዝብ የነበሩበትን ሁኔታ ይወክላል። ከአይሁድ ሕዝብ ላይ ራስ ተቆርጦ ተነስቷል። እነርሱ ያላወቁት የእነርሱ ራስ ኢየሱስ ነበር። የፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያን እና የካሕናቱ ስብከት ሕዝቡ ከኢየሱስ እንዲለዩ የሚያደርግ ነበር።

በዘመናችን የሜሴጅ ሰባኪዎች አሳስተው የተረጎሙት የዊልያም ብራንሐም ንግግር ጥቅስ የሜሴጅ አማኞችን ከኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ለይቷቸዋል (እነርሱም ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ትተዋል)። መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ትልቅ ችግር ሆኗል።

ማርቆስ 6፡28 ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች።

እናት እና ልጅ ተባብረው ዘግናኝ ጥፋት ፈጽመዋል። ኢየሱስ እንደ ሰው በተገለጠ ጊዜ ያስተዋወቃቸውን ነብይ ገድለዋል።

ቤተክርስቲያኖች የሚያስተምሩት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ትምሕርት የወንድም ብራንሐምን ተጽእኖ እየገደለ ነው። ወንድም ብራንሐም ያመጣቸውን መገለጦች ትክክለኛነት አማኞች ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ፈትሸው እንዲያረጋግጡ ሲመክራቸው ነበረ።

ወንድም ብራንሐም ኢየሱስን እንደ ተገለጠው ቃል አድርጎ ነው ያስተዋወቀን።

ማርቆስ 6፡29 ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት።

ከዮሐንስ ደቀመዛሙርት መካከል ወጥቶ ከኢየሱስ አሥራ ሁለት ደቀመዛሙርት አንዱ ለመሆን የበቃው እንድሪያስ ብቻ ነው። መጥምቁ ዮሐንስ የተባለውን ነብይ የተከተሉ ሁሉ የቃሉ ተከታዮች ሆነዋል ማለት አይደለም።

ሕዝቡ በመጥምቁ ዮሐንስ በጣም ከመገረማቸው የተነሳ ለኢየሱስ ትኩረት ለመስጠት ተቸግረው ነበር።

ኢየሱስ በአገልግሎቱ ጠለቅ ብሎ ከመግባቱ በፊት እግዚአብሔር ዮሐንስን ከመንገድ ማስወገድ ነበረበት።

የነብዩ ንግግር ሁልጊዜ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንድንመለከት ነው የሚያሳስበን።

ማርቆስ 6፡30 ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት።

 

ደግስ በምድረ በዳ

 

ማርቆስ 6፡31 እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ።

ይህች ዓለም ለኑሮ አስቸጋሪ ልትሆን ትችላለች። የሰዎች ፍላጎት ብዙ ነው፤ ነገር ግን ብዙ ነገር ደግሞ ይበላሻል።

ስለዚህ ሰዎች ሁልጊዜ ወደ ኢየሱስ ይመጡ ነበር፤ ምክንያቱም ሊፈውሳቸው እንደሚችል አውቀዋል።

በስተመጨረሻ ኢየሱስን ፍለጋ የመጣው ሕዝብ የምግብ መብያ ፋታ እንኳ አሳጣው።

ከዚያም ኢየሱስ ከቤተሳይዳ በስተደቡብ በረሃማ ቦታ ይዟቸው ሊሄድ ወሰነ።

ቦታው ከታች ባለው ካርታ ላይ አረንጓዴ ሞላላ ቅርጽ ያለበት ነው። ይህ ኢየሱስ 5,000 ሰዎችን ያበላበት ቦታ ነው።

ኢየሱስ ከመያዙ በፊት ካደረጋቸው ተዓምራት መካከል በአራቱም ወንጌሎች ውስጥ የተመዘገበው ብቸኛው ተዓምር ይህ ነው።

 

 

ማርቆስ 6፡32 በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ።

ለብቻቸው ሆነው በመርከብ ሄዱ፤ ነገር ግን ሕዝቡ ደግሞ በውሃው ዳር ዳር እየሮጡ ተከተሏቸው።

ማርቆስ 6፡33 ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ።

ሕዝቡ ኢየሱስን ለማግኘት በጣም ፈልገዋል።

ማርቆስ 6፡34 ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።

ከሐይማኖት መሪዎቻቸው እውነትን ተምረው የማያውቁት ሕዝብ ኢየሱስ ሲያስተምር ለማዳመጥ በጣም ይጓጉ ነበር።

ማርቆስ 6፡35 በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤

ማርቆስ 6፡36 የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው አሉት።

37 እርሱ ግን መልሶ፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት።

38 እርሱም፦ ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ አላቸው። ባወቁም ጊዜ፦ አምስት፥ ሁለትም ዓሣ አሉት።

ሁለት ዓሣ ሲደመር አምስት እንጀራ ይሆናል ሰባት፡ ይህም ሰባቱን የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላል።

ሐዋርያት የአዲስ ኪዳንን ቤተክርስቲያን መስርተዋል፤ እርሷም ለሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ሁሉ የእውነት መሰረት ናት።

እንጀራ የእግዚአብሔር ቃል ምሳሌ ነው።

በእግዚአብሔር ቃል አምስት የቤተክርስቲያን ዘመናት ይመሰረታሉ።

ዓሣ ው ውስጥ ሰምጦ በመዋኘት ከእይታ መሰወር ይችላል።

ሁለቱ ዓሣዎች የሚወክሉት እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን በሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ እንደምትሰደድ ነው። በሶስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በኒቅያ ጉባኤ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውን የስላሴ ትምሕርት ለመቀበል በተገደደች ጊዜ እውነት ጠፍታ ነበር።

ከዚያም በአራተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ማለትም በጨለማው ዘመን ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተቃዋሚዎች በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እጅ ተገድለዋል። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የተቃወሙ ሰዎች ሁሉ ሸሽተው ምድረ በዳ ውስጥ ይደበቁ ነበር። ከአውሮፓ ብዙ ክርስቲያኖች ተሰድደው ወደ አሜሪካ ሄደዋል።

ማርቆስ 6፡39 ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው።

ሕዝቡ ሁሉ በተለያየ ቡድን እየሆኑ ተቀመጡና ደቀመዛሙርቱ እንጀራ እና የዓሣ ስጋ አቀረቡላቸው። እንጀራና የዓሣ ስጋ ሁለቱም የእግዚአብሔር ቃል ምሳሌዎች ናቸው። በሌላ አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያት ቤተክርስቲያንን የመሰረቱበትን አስተምሕሮ ይመግበናል።

ማርቆስ 6፡40 መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ።

እያንዳንዱ ክርስቲያን በሆነ ዘመን የሆነ ቦታ ተወልዶ የሐዋርያትን አስተምሕሮ በመቀበልና በማመን እግዚአብሔርን ያገለግላል።

ማርቆስ 6፡41 አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት መካከል ተከፋፍለዋል። እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመን የተለያየ ተግዳሮት ነው የገጠመው። የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን እውነትን ይዞ ነበር።

ከዚያም ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ እውነትን ለቀቅ ማድረግ ጀመሩ ምክንያቱም ጳጳሳትን የቤተክርስቲያን ራስ ናቸው ብለው ከፍ በማድረጋቸው ነው። በቀጣዮቹ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ቀስ በቀስ ብዙ ሐዋርያዊ እውነቶች ከቤተክርስቲያን እየጠፉ ሄዱ።

ሶስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በጣም የከፋ ችግር የተፈጠረበት ጊዜ ነበር ምክንያቱም በኒቅያ ጉባኤ አማካኝነት ስላሴ እና የስቅለት አርብ የተባሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምሕርቶች ገቡና መጽሐፍ ቅዱስን የመማር ፍላጎት ገደሉ። ከዚያም የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስላሴን የማይቀበሉ ሰዎችን ማሳደድ ጀመረች፤ ስላሴን የማያምኑ ሰዎችም ልክ ዓሣ ውሃ ውስጥ እንደሚሰወረው ተሰውረው መኖር ጀመሩ።

 

 

ካቶሊክ ባልሆኑ ክርስቲያኖች ላይ የተነሳው ስደት በ4ኛው ክፍለ ዘመን እየተባባሰ ሄደ። ይህም በተሰወረ ዓሣ የተመሰለው ሁለተኛው ዘመን ነው፤ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከአስር ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎችን በምትገድልበት ዘመን ዓሣው ፈጽሞ ከእይታ እስኪጠፋ ድረስ ይሰወራል።

ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር በአምስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ በማርቲን ሉተር ተሃድሶ አማካኝነት ነገሮችን መለወጥ ጀመረ፤ በዚህም ተሃድሶ ጻድቅ በእምነቱ በሕይወት ይኖራል ተብሎ እንደተጻፈው በእምነት የመጽደቅ ትምሕርት ወደ ቤተክርስቲያን ተመለሰ።

በስድስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን እንግሊዝ ውስጥ ጆን ዌስሊ ስለ የቅድስና እውነትን ወደ ቤተክርስቲያን በመመለስ የመቀደስን ትምሕርት አመጣ።

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በሁለት ደረጃ ነበር ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሶ የመጣው። ፔንቲኮስታሎች ተዓምራዊ ስጦታዎችን መልሰው ሲያመጡ ወንድም ብራንሐም ደግሞ አሜሪካ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት ገለጠ። ስለዚህ የመጨረሻው ዘመን ላይ የምትገኘዋ ቤተክርስቲያን ወደ ጥንቶቹ ሐዋርያት እምነት ለመመለስ ተዘጋጅታለች።

 

 

ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤

በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቃችን ማስረጃው የተጻፈውን ቃል ሚስጥራት መረዳት መቻላችን ነው።

ማርቆስ 6፡42 ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤

የአሕዛብ ቤተክርስቲያኖች በየዘመናቸው በተላከላቸው መልእክተኛ አማካኝነት በተቀበሉት እውነት አማካኝነት ነው ጸንተው ያለፉት። እያንዳንዱ መልእክተኛ በተላከበት ዘመን የምትገኘዋን ቤተክርስቲያን ወደ ተጻፈው ወደ እግዚአብሔር ቃል ሊመልሳት የተቻለውን ያህል ሁሉ ጥረት አድርገዋል።

ፍጥረታውያን የነበሩት አይሁዶች ሆዳቸው እስኪሞላ ድረስ ፍጥረታዊውን እንጀራ በልተዋል። ከዚያ በኋላ መብላት ያልፈለጉትን ብዙ የእንጀራ ቁርስራሽ ጥለዋል።

እነዚህ የተጣሉት የእንጀራ ቁርስራሾች አይሁዶች መንፈሳዊውን የወንጌል እንጀራ ማለትም ኢየሱስ ይዞ የመጣላቸውን ትምሕርት አለመቀበላቸውን ያሳያሉ።

ማርቆስ 6፡43 ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ።

ሰዎቹ አንበላም ብለው የተረፋቸው 12 መሶብ የእንጀራ ቁርስራሽ ትርጉም አለው።

ማቴዎስ 16፡9 ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?

ሰዎቹ አንበላም ብለው ከተረፋቸው 12 መሶብ የእንጀራ ቁርስራሽ ምን መረዳት እንችላለን?

አይሁዶች በቀራንዮ መስቀል ወንጌልን አለመቀበላቸውን አሳይተዋል። ደቀመዛሙርቱም ሕዝቡ አንቀበልም ያሉትን ወንጌል ሰብስበው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አድርገው ጻፉ።

ከዚያም ሰባቱ የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ዘመናት (በሰባቱ ማለትም አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ የተመሰሉት) ሲጠናቀቁ የአሕዛብ ቤተክርስቲያኖችም የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የነበሩ አማኞች የተቀበሏቸውን የአዲስ ኪዳን የተገለጡ ትምሕርቶች አንቀበልም ይላሉ። ሕዝቡ አንቀበልም ያሉት 12 መሶብ ቁርስራሽ አሕዛብ በ7ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን መጨረሻ ላይ አንቀበልም ብለው የሚጥሉት እውነት በ3.5 ዓመቱ ታላቅ መከራ ውስጥ ተመልሶ ወደ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች እንደሚሄድ ያመለክታል። ይህም አሕዛብ አንቀበልም ያሉት ወንጌል በዚያ ጊዜ 144,000ዎቹ አይሁዶች ይቀበሉታል።

ማርቆስ 6፡44 እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ።

ሴት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት።

ማርቆስ ወንዶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መጻፉ ቤተክርስቲያንን ሳይሆን አይሁዶችን ለማለት መፈለጉን ያሳያል።

5,000 ምን ይወክላል?

ከአዳም ውድቀት ጀምሮ እስከ ኢየሱስ ድረስ ያለፉት ዓመታት 4,000 ናቸው።

ከዚያም አይሁዶ ኢየሱስን ለመቀበል እምቢ አሉና ከእግዚአብሔር ፈቃድ ወጡ።

አይሁዶች በታላቁ መከራ ዘመን ተመልሰው ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመጣሉ። ዛሬ በሕይወት ካሉት 18 ሚሊዮን አይሁዶ መካከል ሁለት ሶስተኛዎቹ ይሞታሉ፤ አንድ ሶስተኛዎቹ ደግሞ በታላቁ መከራ ውስጥ ሳይሞቱ አልፈው ለ1,000 ዓመት በሰላም ወደሚገዛው ወደ ሺ ዓመት መንግስት ይገባሉ።

እነርሱ እና ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውም ለ1,000 ዓመታት እግዚአብሔርን ያገለግላሉ።

በሕይወት የሚተርፉት አንድ ሶስተኛ አይሁዶች ክርስቶስን ከሚቀበሉት ከ144,000ዎቹ ጋር የሚቆጠሩ አይደሉም። 144,000ዎቹ ለበጉ ሚስት ለሙሽራይቱ ጥበቃ የሚያደርጉ አይሁዶች ናቸው።

ስለዚህ አይሁዶች እግዚአብሔርን የሚያገለግሉበት ዓመት በሙሉ ሲደመር 4,000 + 1,000 = 5,000 ነው።

ይህንንም እውነት እንደ ምሳሌ የሚገልጠው እንጀራና ዓሣ የበሉ አይሁዶች ብዛት 5,000 መሆኑ ነው።

ዘካርያስ 13፡8 በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ክፍል ተቈርጠው ይሞታሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሦስተኛውም ክፍል በእርስዋ ውስጥ ይቀራል።

9 ሦስተኛውንም ክፍል ወደ እሳት አገባለሁ፥ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፥ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፤ እኔም፦ ይህ ሕዝቤ ነው እላለሁ፤ እርሱም፦ እግዚአብሔር አምላኬ ነው ይላል።

ወደ ሺ ዓመቱ መንግስት የሚገቡት 6 ሚሊዮን አይሁዶች ለተጨማሪ 1,000 ዓመት እግዚአብሔርን አይሁዶች ያገለግሉ ዘንድ ያስችሏቸዋል። እነርሱም ያልዳኑና ወንጌልን ሰምተው የማያውቁ ከአርማጌዶን ጦርነት የተረፉ አሕዛቦች መካከል ይኖራሉ።

 

 

2ኛ ጴጥሮስ 3፡8 እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።

በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የሚያልፉት 2,000 ዓመታት ለአይሁዶች አይቆጠሩላቸውም፤ ምክንያቱም እነርሱ በቀራንዮ መስቀል እውነትን አንቀበልም ብለው ጥለዋል። ስለዚህ የብሉይ ኪዳን 4,000 ዓመታት ብቻ ናቸው የሚቆጠሩላቸው።

የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን 2,000 ዓመታትም አይቆጠሩላቸውም።

ነገር ግን በሕይወት የተረፉ አይሁዶች ወደ 7ኛው ቀን ማለትም የ1,000 ዓመቱ የሰላም መንግስት ውስጥ ይገባሉ።

 

ኢየሱስን ቀድሞ መሄድ ስሕተት ነው

 

ማርቆስ 6፡45 ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው።

ኢየሱስ “ወደ ቤተሳይዳ” አላለም። እንደዚያ ቢል ኖሮ በቀጥታ ወደ ቤተሳይዳ መቅዘፍ ማለት ይሆናል።

“እንዲቀድሙት” የሚለው “ከፊት ለፊት” ማለት ነው።

“ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት” ነው ኢየሱስ ያለው።

 

 

ወደ ማዶ መሻገር አለባቸው ነገር ግን የጴጥሮስ፣ የእንድሪያስ፣ እና የፊሊጶስ ሃገር ወደ ሆነችው ወደ ቤተሳይዳ አይደለም። ከቤተሳይዳ ፊትለፊት አልፈው መሄድ አለባቸው፤ ቤተሳይዳ ቢሄዱ አጭርና ቀላል መንገድ ይሆንላቸው ነበር። ክርስትና አልጋ በአልጋ የሆነ ሕወት አይደለም። ጉዞዋቸው በሃገራቸው በኩል አሳልፎ ይወስዳቸዋል፤ ነገር ግን ወደ ቤታቸው ወደ ቤተሳይዳ ከመግባታቸው በፊት የጀመሩትን ጉዞ መጨረስ አለባቸው።

ቤተሳይዳ ማለት የዓሣ ቤት ነው።

ወደ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት ኢየሱስ ሰውን አጥማጅ መሆን ሊያስተምራቸው ነው።

ከዚህ መማር የምንችለው ትልቅ ትምሕርት ጥሩ ነው ብለን በምናስበው ነገር ላይ የተመሰረተ ውሳኔያችን ስሕተት እንደሚሆን ነው።

ከዚያም ለብዙ ሰዓታት እንደክማለን እንጂ የትም አንደርስም። ከዚያም ትክክለኛውን አቅጣጫችንን የምናገኘው ነፋስ ከያዝነው መንገድ ገፍቶ ሲያወጣን ነው። ይህ የሚሆነው ኢየሱስን ወደ መርከባችን ውስጥ ስናስገባ ብቻ ነው።

የሚያስፈልጋቸውን ትምሕርት ይማሩ ዘንድ ኢየሱስ ለጊዜው ብቻቸውን ተዋቸው።

ደቀመዛሙርቱም ከኢየሱስ በተለዩ ጊዜ የተሳሳተ ውሳኔ አደረጉ።

ማርቆስ 6፡46 ካሰናበታቸውም በኋላ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።

በራሳቸው መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነበር። ስለዚህ የተሳሳተ ውሳኔ አደረጉ። በቤተሳይዳ ፊት ቀድመው አልፈው ወደ ማዶ መሻገር አለባቸው። ቅርቡና ከሁሉም የሚመቸው መዳረሻ ቅፍርናሆም ነው። ቅፍርናሆም ለመድረስ ረጅም ጊዜ አይፈጅም፤ በዚያም ሳሉ ምግብ እና ጥቂት እንቅልፍ ማግኘት ይችላሉ። እኛ ሰዎች ሁልጊዜ ለራሳችን ቀላልና ምቹ የሆነውን መንገድ ነው የምንመርጠው።

ማቴዎስ 14፡22 ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው።

ሰዎች ወደ ትክክለኛው መዳረሻቸው መድረስ ከፈለጉ ከእግዚአብሔር ቀድመው መሄድ የለባቸውም።

ጉዞዋቸው ጌንሰሬጥ ሲደርሱ ተጠናቀቀ። ይህም ረዘም ያለውና አስቸጋሪ የሆነው ነገር ግን ኢየሱስ ደግሞ እንዲሄዱበት የፈለገው ጉዞ ነበር።

ማርቆስ 6፡53 ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ።

እነርሱ ደግሞ በጣም አጭር የሆነውን መንገድ ይዘው ወደ ቅፍርናሆም መሄድ ፈልገው ነበር። ሰዎች የእግዚአብሔርን እቅድ መረዳት በጣም ይከብዳቸዋል።

 

 

ዮሐንስ 6፡16 በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፥

17 በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር። አሁንም ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፤

በራሳቸው ተነስተው ሲሄዱ ወደ ቅፍርናሆም ለመድረስ ነው ያሰቡት። ቅፍርናሆም ግን ኢየሱስ ከረገማቸው ሶስት ከተሞች አንዷ ናት። ስለዚህ እኛ ሰዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ በቅጡ አንረዳም።

ኢየሱስ አብሯቸው አልነበረም። ምን ማድረግ እንዳለባቸው በራሳቸው ወሰኑ። ከዚህም የተነሳ መሄድ ወደሌለባቸው ቦታ ለመሄድ መንገድ ጀመሩ። ወደ ጌንሰሬጥ የሚወስደውን ረጅሙን መንገድ ትተው ወደ ቅፍርናሆም ለመሄድ ተነሱ።

ኢየሱስም ቀድመውት እንዲሄዱ ፈቀደላቸው። እነርሱም ከዚህ የሚያገኙት ትምሕርት ያስፈልጋቸው ነበር።

ኢየሱስን መከተል አለብን እንጂ ቀድመነው መሄድ የለብንም።

ኃይለኛ ማዕበል መነሳቱ ደቀመዛሙርቱ ከኢየሱስ ቀድመው የመሄዳቸው ውጤት ነው።

ስለዚህ ደቀመዛሙርቱ በመከራ ውስጥ በማለፋቸው ኢየሱስ መቅደም እንዳለበት ተማሩ።

ከኢየሱስ ትንሳኤ በኋላ እንዲህ ሆነ።

ማርቆስ 16፡1 ሰንበትም ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም የያዕቆብም እናት ማርያም ሰሎሜም መጥተው ሊቀቡት ሽቱ ገዙ።

የማርቆስ ወንጌል የሚያበቃው ሶስት ሴቶች ወደ ባዶው መቃብር መጥተው መልአክ ሲያዩና መልአኩም እንዲህ ብሎ ሲናገራቸው በመግለጽ ነው፡

ማርቆስ 16፡7 ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም፦ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው።

አሁን ደቀመዛሙርቱ ኢየሱስ ቀድሟቸው ሊሄድ እነርሱም ሊከተሉት እንደሚገባቸው ተረዱ።

ይህም ዊልያም ብራንሐም እውነተኛውን የእግዚአብሔር ቃል ከጨለማው ዘመን ሞት ውስጥ አውጥቶ ወደ ቤተክርስቲያን መመለሱን የሚያሳይ ምሳሌ ነው። በሶስት የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ያለፈችዋ ሙሽራ እውነትን መልሳ መቀበል ትጀምራለች።

ሙሽራይቱ እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን መከተል እስክትጀምር ድረስ ሶስት የቤተክርስቲያን ዘመናት ያልፋሉ። የዚያን ጊዜ ሙሽራይቱ ወደ መጀሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን እምነት ትመለሳለች።

 

 

ጀርመኒ ውስጥ ማርቲን ሉተር በእምነት ብቻ የመዳንን እና የመጽደቅን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ አመጣ። ይህም 5ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ነው።

እንግሊዝ ውስጥ ጆን ዌስሊ የቅድስና እና የመቀደስን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ አመጣ። ይህም 6ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ነው።

ሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በሁለት የተከፈለ ነው። ከ1906 ዓ.ም ጀምሮ አሜሪካ ውስጥ የነበሩ ፕንቲኮስታሎች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ወደ ቤተክርስቲያን መልሰው አመጡ። ይህ የተሃድሶስ ሶስተኛ ደረጃ ነበር።

ከዚያም ዊልያም ብራንሐም አሜሪካ ውስጥ በአራተኛው ደረጃ የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መረዳት ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ አመጣ።

ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤

በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቃችን ማስረጃው የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መረዳት መቻላችን ነው።

63-0318 የመጀመሪያው ማሕተም

… የእግዚአብሔር ሚስጥር የሰባተኛው መልአክ አገልግሎት ነው።

 

መከራና ችግር በእውነተኛው መንገድ እንድንሄድ ያደርጉናል

 

ማርቆስ 6፡47 በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ።

በመሸም ጊዜ። ይህ የሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ማብቂያ ነው።

ማርቆስ 6፡48 ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር።

የሚሄዱበት መንገድ የተሳሳተ ስለነበረ እግዚአብሔር ኃይለኛ ነፋስ አስነስቶ መለሳቸው። ነፋሱ እየገፋቸው ይሄዱ ከነበሩበት መንገድ መለሳቸው (ያልተቆራረጠውን ቀስት ተመልከቱ) ከዚያም ወደ ትክክለኛው መንገድ መራቸው (ነጠብጣቡ መስመር)፤ ወደዚህ መንገድም የተመለሱት ኢየሱስ ወደ መርከባቸው ከገባ በኋላ ነው።

 

 

የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንደመሆናችን ታላቅ ትምሕርት እናገኛለን።

መከራና ችግር ከግል ሩጫችን ይመልሱንና ወደ ኢየሱስ እንድንሮጥ ያደርጉናል። ኢየሱሰን በልባችን እንደ የእግዚአብሔር ቃል መቀበል እውነተኛ ምሪት ለማግኘት ይረዳናል።

በመንገዳችን የሚያሰናክሉን ማዕበሎች የሚመጡብን ለበጎ ነው።

በራሳችን አቅም እግዚአብሔርን ለማገልገል ስንሞክር ብዙ እንለፋለን እንጂ ጊዜ ከማባከን በቀር ምንም ቁም ነገር አንሰራም። ልክ እንደ ቫቲካን በሰዎች ፊት የሚያስደንቅ ነገር ልንሰራ እንችላለን፤ ነገር ግን ይህም ቢሆን እውነትን ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ ከማምጣት አንጻር ምንም ጥቅም የለውም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት እንደገና የሚገለጡበት አራተኛው ደረጃ የሙሽራይቱ አካላት የሆኑ ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት ለራሳቸው መረዳት ሲችሉ ነው። የዚያን ጊዜ ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ ሲመላለስ ያዩታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልገቡንን ጥቅሶች ቸል ብለናቸው የምናልፍ ከሆነ ወይም ከቀየርናቸው ኢየሱስም አልፎን ይሄዳል።

ተግተን መጸለይና የነዚያን ከባድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ትርጉም መፈለግ አለብን። የመጽሐፍ ቅዱስን ጥልቅ ሚስጥራት መረዳት ከፈለግን አብዝተን ወደ ጌታ መጮህና የሚመጡልንን አዳዲስ ሃሳቦች በልባችን መቀበል አለብን።

የሌሊቱ አራተኛ ክፍል እውነት ወደ ቤተክርስቲያን የምትመለስበትን አራተኛ ደረጃ ያመለክታል። ይህም ግለሰቦች የእምነታቸውን ትክክለኝነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር በማመሳከር ብቻ ማረጋገጥ የሚችሉበት ደረጃ ነው።

ማርቆስ 6፡49 እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥

“ጮኹ”። የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መገለጥ ሲመጣልን ከጠበቅነው እጅግ በጣም የተለየ ስለሚሆን በመደነቅ እንድንጮህ ያደርገናል።

ባሕር እረፍት የሌለው በሁከት የሚኖር ሕዝብ ማለት ነው። በሰዎች ፖለቲካዊ ዓለም ውስጥ ነውጥ ቢበዛም እንኳ ኢየሱስ ከሁሉ በላይ መሆኑንና በዓለም ውስጥ የሚከሰቱ ነገሮች ሁሉ በእርሱ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ማስተዋል አለብን። ነገር ግን ዘመኑ ሁከት የበዛበትና ያለ ፍርሃት መኖር ከባድ የሆነበት ጊዜ ነው።

ማርቆስ 6፡50 ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና፦ አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው።

እምነታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አማካኝነት ይናገረን ዘንድ የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መረዳት አለብን።

ማርቆስ 6፡51 ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤

በስተመጨረሻ ኢየሱስን ወደ መርከባቸው ውስጥ አስገቡት። የክርስቲያን ስኬት ሚስጥሩ ይህ ነው።

ክርስቶስ በውስጣችሁ ሲሆን ውስጣዊ ሰላም ስለሚሰጣችሁ በውጭ ያለው ሁከት አይረብሻችሁም።

ፊልጵስዩስ 4፡11 ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና።

ሮሜ 8፡28 እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።

በራሳቸው ጥረት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም ነበር፤ ነገር ግን ክርስቶስን ወደ መርከባቸው ውስጥ ሲቀበሉ ሰላም እና እረፍት ሆነላቸው።

ዛሬ በዓለም ሕዝቦች መካከል ግፍ፣ ጭካኔ፣ ሌብነት፣ ስግብግብነት፣ ጥላቻና ራስ ወዳድነት ቢበዛም እንኳ ኢየሱስ በዚህ ሁሉ ውስጥ ዛሬም የራሱን ፈቃድ ማድረግ በመቻሉ እንደነቃለን።

ማርቆስ 6፡52 ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።

አይሁዶቹ አንበላም ብለው የጣሉት አስራ ሁለት መሶብ ቁርስራሽ እንጀራ እምቢ አንቀበልም ያሉትን ወንጌል እና በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ከእግዚአብሔር መለየታቸውን ያመለክታል። ከዚያም በመጨረሻው ዘመን ተጥለው የነበሩት አይሁዶች ወደ እስራኤል ይሰበሰባሉ፤ በታላቁ መከራ ዘመንም ጌታን ይቀበላሉ።

አይሁዶች ባለፉት 2,000 ዓመታት ውስጥ አቅጣጫ ጠፍቶባቸዋል፤ ነገር ግን በታላቁ መከራ ኃይለኛና ነውጠኛ አውሎ ነፋስ አማካኝነት ተገፍተው ወደ ትክክለኛው መንገድ በመመለስ ጌታን ያገኛሉ።

 

ጌንሰሬጥ ሰላም የሰፈነበትን የሺ ዓመት መንግስት ይወክላል

 

ማርቆስ 6፡53 ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ።

ጌንሰሬጥ ማለት የንጉሱ ገነት ነው።

የኤድን ገነት የተበላሸችው በሰባተኛው ቀን ሐጥያት ሲገባ ነው።

የዳዊት ልጅ የሆነው ኢየሱስ በሺ ዓመት መንግስት ጊዜ ለ1,000 ዓመታት ምድርን በሰላም ይገዛል። የዚያን ጊዜ የእውነትም የሰላም አለቃ ሆኖ ይገለጣል፤ ምድር ሁሉ የእርሱ ገነት ትሆናለች።

ስለዚህ በሺ ዓመት መንግስት ጊዜ ምድር ሁሉ ጌንሰሬጥ ትሆናለች። ጌንሰሬጥ ማለት የንጉሴ ገነት ነው። በዚህም ሰይጣን የኤድን ገነት ውስጥ አበላሽቶት የነበረው ሰባተኛ ቀን ይጠናቀቃል ምክንያቱም በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ቀን 1,000 ዓመታት ነው።

2ኛ ጴጥሮስ 3፡8 እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።

 

 

ለስድስት ቀናት (6,000 ዓመታት) እግዚአብሔር ምድርን ለሰው ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ሲያዘጋጃትና የኤድን ገነት አድርጎ ሲያበጃት ነበር። በ7ኛው ቀን ወይም 1,000 ዓመት ውስጥ ሐጥያት ወደ ኤድን ገነት ገባ።

ሰይጣን ምድርን መግዛት ከጀመረ 6,000 ዓመታት አልፈዋል። ኢየሱስ በአርማጌዶን ጦርነት የክፉውን ሰራዊት ሁሉ ካጠፋ በኋላ በ7ኛው ቀን ማለትም ለ1,000 ዓመታት ዓለምን በሙሉ ይገዛል። ምድር በሙሉ የንጉሱ ገነት ትሆናለች። ጌንሰሬጥ። ለዚህ ነው ኢየሱስ ጌንሰሬጥን የጉዞው መጨረሻ አድርጎ የመረጠው።

ማርቆስ 6፡54 ከታንኳይቱም ሲወጡ ወዲያው አውቀውት

የአርማጌዶን ጦርነት ሲያበቃ ዓለም ሁሉ በኢየሱስ አገዛዝ ስር ይሆናል

ፊልጵስዩስ 2፡10 ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥

ኢየሱስ ጠላቶቹን ሁሉ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ ካጠፋቸው በኋላ ሁሉም ሰው በታላቅ ድምጽ የኢየሱስን ስም ይጠራል፤ ሰውም ሁሉ ኢየሱስን ያውቃል።

ማርቆስ 6፡55 በዚያች አገር ሁሉ ዙሪያ ሮጡና እርሱ እንዳለ ወደ ሰሙበት ስፍራ ሕመምተኞችን በአልጋ ላይ ያመጡ ጀመር።

ከአርማጌዶን ጦርነት የተረፉ ሰዎች ሁሉ የኢየሱስ ሰላም እና ፈውስ ያገኛቸዋል።

ማርቆስ 6፡56 በገባበትም ስፍራ ሁሉ፥ መንደርም ከተማም ገጠርም ቢሆን፥ በገበያ ድውዮችን ያኖሩ ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

የታመሙ ሰዎች መፈወስ እጅግ አስደናቂ ነገር ቢሆንም ግን ጉዳዩ የሕመምተኞች ፈውስ ብቻ አይደለም። የሕዝቦች ሁሉ ፈውስ ጭምር ነው የሚሆነው። ዘረኝነትና ጎሰኝነት ይወገዳሉ።

ሰዎችም እግዚአብሔር በአንድ ዘር ያውም በሰው ዘር ብቻ ደስ እንደሚለው ወደ መረዳት ይመጣሉ።

ከዚያም ሰዎች ሁሉ አንድ ትልቅ ቤተሰብ ይሆናሉ።

ኢየሱስ አንድ ጊዜ ብቻ የነካው ሰው ጤናውም ሆነ አመለካከቱ ይለወጣል።

 

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23