ማርቆስ 3 - እግዚአብሔርን የምናገለግለው በፈቃዱ ውስጥ ስንሆን ብቻ ነው



የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማናውቅና የማንታዘዝ ከሆነ አምልኮዋችንም ሆነ አገልግሎታችን ብዙም ዋጋ የለውም።

First published on the 31st of December 2022 — Last updated on the 31st of December 2022

መፈወስ የሚችለውን ብቸኛውን አገልጋይ ሊገድሉ ይፈልጋሉ

 

ማርቆስ 3፡1 ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፥ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤

ማርቆስ ኢየሱስን እንደ ታላቅ አገልጋይ ነው የገለጠው።

ይህ ሰው እጁ የሰለለ በመሆኑ ለማንም አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ በዚህም ምክንያት የብዙ ሰዎችን ትኩረት ስቧል።

ማርቆስ 3፡2 ሊከሱትም፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር።

አይሁዶች ስለ ሕጉ የነበራቸው መረዳት ለራሳቸው የማይጠቅም ነበር። የሰለለው እጁ ሳይፈወስ በፊት በጣም ጥሩ አይሁድ እንደሆነ ይቆጥሩታል ምክንያቱም በየትኛውም ቀን ምንም ሥራ ስለማይሰራ በሰንበትም ቀን ሥራ መስራት አይችልም።

ኢየሱስ ቢፈውሰውና በሰዎች ምጽዋት በመኖር ፈንታ የቀን ሥራ መስራት የሚችለው ሰው ቢያደርገው አይሁዶች ኢየሱስን ያወግዙታል። ይህን ሰው ከዚህ ስቃይ ሊፈውሰው የሚችለውን ብቸኛውን ሰው ኢየሱስን ሊያወግዙት ይፈልጋሉ።

ማርቆስ 3፡3 እጁ የሰለለችውንም ሰው፦ ተነሥተህ ወደ መካከል ና አለው።

ኢየሱስም ሰውየውን ወደፊት በመጥራት ጠላቶቹን ፊት ለፊት ተጋፈጣቸው።

ማርቆስ 3፡4 በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ።

ኢየሱስ ለሰዎቹ ግልጽ ይሆን ዘንድ ጉድጓድ ውስጥ ስለወደቀ እንስሳ አነሳላቸው።

ማቴዎስ 12፡11 እርሱ ግን፦ ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?

አይሁዶች በሰንበት በግ ማዳን ደስ ይላቸዋል፤ ሰውን ማዳን ግን ደስ አይላቸውም።

ይህም ግብዝነት ኢየሱስን አስቆጣው።

ማርቆስ 3፡5 ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፥ ሰውየውንም፦ እጅህን ዘርጋ አለው።

ታላቁ አገልጋይ ኢየሱስ ሥራ መስራት የማይችል የማይጠቅም የነበረውን ሰውዬ ሰርቶ መኖር የሚችል ጠቃሚ አገልጋይ አደረገው።

ማርቆስ 3፡6 ዘረጋትም፥ እጁም ዳነች። ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ከሄሮድስ ወገን ጋር ተማከሩበት።

ነገር ግን ይህ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል ቢገለጥም ፈሪሳውያን ኢየሱስ ማን እንደሆነ ማየት አልቻሉም። ኢየሱስ ያደረገው ተዓምር እነርሱ ማድረግ የማይችሉት ስለሆነ ንዴት እና ጥላቻ ሞልቶባቸዋል።

ስለዚህ ሐይማኖትን ከፖለቲካ ጋር ሊያጣምሩ ፈልገው ከአይሁድ መካከል ፖለቲከኞች ወደሆኑት ወደ ሔሮድስ ወገኖች ዞር አሉ (በራዕይ ምዕራፍ ስድስት ሁለተኛው ማሕተም ውስጥ እንዳለው ቀይ ፈረስ)። ወታደራዊ ኃይልን በሚቆጣጠረው የፖለቲካ ስልጣን ሰይፍ ተጠቅመው ኢየሱስን ሊያጠፉት ፈልገዋል።

ማርቆስ 3፡7 ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤

ኢየሱስ በፖለቲካዊ ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት አሳይቶ አያውቅም። ስለዚህ ወደ ገሊላ ባሕር ፈቀቅ አለ።

ይህ ለተከታዮቹ ጥሩ ፍንጭ ነው። ፖለቲካዊ ተሳትፎ የእግዚአብሔርን መንግስት ለማስፋፋት ምንም ስለማይጠቅም አትግቡበት ማለቱ ነው። ፖለቲካ እና ሐይማኖት ሲቀላቀሉ ሞትን የሚያመጣ መርዝ ይሆናሉ።

 

ስሞች የእግዚአብሔርን ዓላማ ይገልጣሉ

 

ማርቆስ 3፡8 እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገው ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ።

 

 

እነዚህ ከተሞችና ግዛቶች ሁሉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሊማሩ የሚገባቸውን ነገር ይገልጣሉ።

የኢየሩሳሌም መሪዎች ሐይማኖታዊ ተጽእኖዋቸውንና ስልጣናቸውን በመጠቀም ደካማው ሮማዊ ገዥ ጴንጤናዊ ጲላጦስ ቃል የሆነውን ኢየሱስን እንዲገድል ያስገድዱታል። ከዚያም በ70 ዓ.ም ሮማውያን ተመልሰው መጡና ቤተመቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ አፍርሰው ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አይሁዶችን ገደሉ። ከሮም ወይም ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነት ካላችሁ ራሳችሁን ብዙ ትጎዳላችሁ።

ኤዶምያስ ከይሁዳ በስተደቡብ የሚገኝ ሃገር ስለሆነ የተስፋይቱ ምድር አካል አይደለም። አይሁዶች በመቃዕብያን አመራር ስር በነበሩ ጊዜ ለጥቂት ዘመን ነጻነታቸውን አግኝተው ነበር። የዚያን ጊዜ ያገኙትን ኃይል ተጠቅመው ኤዶምያስን አንበረከኩና ኤዶማውያንን በግዳጅ አይሁድ አደረጓቸው። ይህም ለአይሁድ ትልቅ አደጋ አስከትሎባቸዋል፤ ምክንያቱም ሔሮድስ ኤዶማዊ ነበር፤ ሮማውያንም ንጉስ አድርገው በአይሁዶች ላይ ሾሙት። እርሱም በአይሁዶች ላይ ከነገሱ ሰዎች ሁሉ አንደኛ ጨካኝ ንጉስ ነበረ፤ ስልጣኑንም ጠብቆ ያቆየው ብዙ አይሁዶችን በመግደል ነው። ይህም ለአይሁዶች ከተስፋይቱ ምድር ውጭ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ መስፋፋት እንዳያደርጉ ከበድ ያለ ትምሕርት ሰጥቷቸዋል።

ከዮርዳኖስ ማዶ ማለት ከኢየሩሳሌም በስተ ምስራቅ ከወንዙ ተሻግሮ ያለው አካባቢ ነው። ያም የአሕዛብ ሃገር ነው።

ጢሮስ እና ሲዶናም የአሕዛብ ከተሞች ናቸው።

ይህም ወደፊት ወንጌል ወደ አሕዛብ ሊመጣ እንደነበረ የሚያሳይ ምልክት ነበር።

 

እግዚአብሔር ስሕተትን ከሚከተሉ ሰዎች አንዳችም ምስጋና አይፈልግም

 

ማርቆስ 3፡9 ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤

ኢየሱስ እንደ ሰው ይኖር ስለነበረ እጅግ ብዙ ሕዝብ የእርሱን እርዳታ ፈልገው ሲያጋፉት ይቸገር ነበር።

ከባሕር አጠገብ ሆኖ ካስተማረና ከፈወሰ አገልግሎቱን ሲያበቃ ከሕዝቡ የሚያመልጥበት ጀልባ ማግኘት ይችላል ማለት ነው።

ማርቆስ 3፡10 ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር።

ሰዎች ሲፈወሱ የበለጠ ብዙ ሰዎች ፈውስ ፍለጋ ከሕዝቡ መካከል እየተጋፉ ይመጣሉ። ሐኪሞች ሊያድኑ ባልቻሉዋቸው በሽታዎች ሁሉ ላይ ኢየሱስ ኃይል ነበረው።

የኢየሱስ አገልግሎት በአስደናቂ መለኮታዊ ኃይል የተሞላ ነበረ።

ማርቆስ 3፡11 ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው፦ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ።

ክፉ መናፍስት ለኢየሱስ እውቅና ይሰጡ ነበር።

ኢየሱስ ግን የክፉ መናፍስትንና ስሕተት የሚያምኑ ሰዎችን ምስጋና አይፈልግም።

እርኩሳን መናፍስት እውነተን ሲያዩ ለይተው ያውቋታል።

ስለዚህ ተራ ሰዎች ስለ ኢየሱስ እውነቱን ማወቅ ባይችሉ ምንም ማመካኛ የላቸውም።

ማርቆስ 3፡12 እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው።

ኢየሱስ ግን ከእርኩሳን መናፍስት ዘንድ የሚገኘውን እውቅና አልፈለገውም።

ኢየሱስ ስሕተትን ከሚከተሉ ሰዎች ዘንድ ምስጋና አይፈልግም።

ማቴዎስ 7፡21 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።

ሁለት ጊዜ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለው ንግግር የእርሱን ጌትነት ለማጉላት ነው።

የኢየሱስን ጌትነት በከንፈራቸው በደምብ ይመሰክራሉ ልባቸው ግን ከእርሱ በጣም እሩቅ ነው ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን የእውነት ቃል ለማመን ፈቃደኞች አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ሃሳብ ይገልጥልናል። ሰዎች ግን የራሳቸውን ሃሳብ መከተል ስለሚመርጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆነው የቤተክርስቲያናቸው አስተምሕሮ እና ልማድ ተጠምደው ይቀራሉ።

በነዚህ ዓይነት ሰዎች ምስጋናና አድናቆት ጌታ ምንም አይደሰትም።

ማቴዎስ 7፡22 በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።

ትንቢት ትልቅ ስጦታ ነው። አጋንንትን ማስወጣትም ትልቅ ስጦታ ነው። ትንቢት መናገርና አጋንንት ማስወጣት ድንቅ አገልግሎቶች ናቸው። እንደ ሰው ስንመለከተው እነዚህን ዓይነት ስጦታዎች ያሉዋቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር በጣም የተጠጉ ሰዎች ይመስሉናል።

ነገር ግን አይደሉም። ስጦታ ቢኖራቸውም እንኳ እግዚአብሔር ግን ከአጠገቡ ያባርራቸዋል።

ማቴዎስ 7፡23 የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።

“የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን”። እነዚህ ሎዶቅያውያን እራሳቸውን ደስ የሚያሰኛቸውን ትምሕርት ይከተላሉ፤ እግዚአብሔርንም እራሳቸው በፈለጉት መንገድ ያገለግላሉ። እግዚአብሔር እንዲያገለግሉት ፈቃዱ ሳይሆን ነው እነርሱ ከልባቸው የሚያገለግሉት። ነገር ግን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ማገልገል ጊዜ ማባከን ነው።

እውነትን ልታምኑ ካልቻላችሁ ተሸንግላችኋል፤ ከሰነፎቹ ቆነጃጅት መካከል ገብታችኋል ማለት ነው።

እውነትን የማታምኑ ከሆነ ኢየሱስ በእናንተ ምንም አይገረምም፤ ምክንያቱም ከመሞታችሁ በፊት ታላቁ መከራ ውስጥ ገብታችሁ ነው የምትስተካከሉት።

የመጨረሻው የሎዶቅያውያን (የሕዝቡ መብት) ቤተክርስቲያን ዘመን ትልቁ ስሕተት እራሳቸውን በሚያመቻቸው መንገድ እግዚአብሔርን ሊያገለግሉ መወሰናቸው ነው።

የእግዚአብሔር በረከት ማስረጃ አድርገው በዋነኛነት የሚቆጥሩት በሃብትና በንብረት መባረክን ነው። ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም አለማወቃቸውን እንኳ እንዳያስተውሉ አሳውሯቸዋል።

ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦

ራዕይ 3፡17 ብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ

የሚያሳዝነው ነገር የዛሬዎቹ ቤተክርስቲያኖች አለማወቃቸውን አለማወቃቸው ነው።

መሳሳታቸውን ስለማያውቁ ለመታረምና ወደ እውነቱ ለመመለስም ምንም ጥረት አያደርጉም።

ማቴዎስ 7፡23 የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።

ዓመፀኞች። የሚያደርጉት ነገር ስሕተት መሆኑን እያወቁ ያደርጋሉ። እንደ ስላሴ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እና “አብ እና ወልድ አንድ ባህርይ ናቸው” የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፉ ነገሮችን ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውቅና በሌለውና ስምም በሌለው በስሉስ አምላክ ያምናሉ፤ ደግሞም ንስሐ እንዲገቡና በኢየሱስ ስም እንዲጠመቁ የሚያዝዛቸውን የሐዋርያት ሥራ 2፡38 እና የመሳሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን አይቀበሉም።

ስለዚህ ሕይወታቸው የተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን በማመንና ሌሎች ሰው ሰራሽ ስሕተቶችን በማመን የተደባለቀ ነው። በውስጥ በልባቸው የሆነ ስሕተት እንዳለባቸው ያውቃሉ ነገር ግን ቤተክርስቲያናቸውን እንደተሳሳተች ማሰቡ ይጨንቃቸዋል። ነገር ግን የሞኝነታቸው ብዛት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተት አለ ብለው ማመናቸው ነው። በዚህም ድርጊታቸው ኢየሱስ ስሕተት አለበት እያሉ ነው ምክንያቱም እነርሱ የሚተቹት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ኢየሱስ እራሱ ነው። እርሱም ከአፉ አውጥቶ ሊተፋቸው መድረሱ አያስደንቅም።

መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም መሆኑን ማመን አለብን።

 

ኢየሱስ አገልጋዮቹ ወደ ከፍታ እንዲወጡ ይጠራቸዋል

 

ማርቆስ 3፡13 ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ።

ወደ ተራራ ወጣ። ተራራ መውጣት አድካሚ ሥራ ነው። ተራራ ሲወጣ ዳገት ስላለው መውጣቱ ቀላል አይደለም። ትግል የእድገት ሕግ ነው።

ኢየሱስ የጠራቸው ብቻ ናቸው ያንን ተራራ መውጣት የሚችሉት።

የተጠሩ ሰዎችን የምንለየው ለእግዚአብሔር ቃል በሚያሳዩት ታማኝነት ነው ምክንያቱም የሚጠራቸውና የሚያስደንቃቸው የእግዚአብሔር ቃል ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ መማር ይፈልጋሉ። ጠለቅ ያሉትን ሚስጥራት መረዳት ይፈልጋሉ።

ዓለም ሁሉ በጉን እየተዋጋው ነው። ከእርሱ ጋር የሆኑት የተጠሩ ናቸው ምክንያቱም እርሱ የመረጣቸው ናቸው። እነርሱ አልመረጡትም።

ራዕይ 17፡14 እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።

በኢየሱስ መጠራትና በኢየሱስ መመረጥ ትልቅ ነገር ነው ግን በቂ አይደለም።

ከእኛ በኩል መሟላት ያለበት ነገር አለ። ለተጠራንበት ጥሪ ታማኝ መሆን አለብን፤ ይህም ታማኝነት ማለት በምንም ዓይነት መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን አለመንቀፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም እና እንከን የሌለው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ማመን አለብን።

ደግሞም የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት የመረዳት ፍላጎት ሊኖረን ይገባል፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ሃሳብ ጠለቅ ብልን እንድንገባ የሚረዱን ሚስጥራቱ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ መረዳታችን እያደገ ሲመጣ የእግዚአብሔርን ሃሳብ ማለትም ፈቃዱን ይበልጥ እያወቅን እንሄዳለን።

 

ከ12ቱ ደቀመዛሙርት መካከል ሁለቱ ታላላቅ ነጎድጓድ አማኞች ናቸው

 

ማርቆስ 3፡14 ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤

12ቱ ደቀመዛሙርት ከኢየሱስ ጋር አብረው መቆየት ይፈልጋሉ። ስለዚህ ኢየሱስን መቃረን ወይም ከእርሱ ጋር መከራከር የለባቸውም። ከዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን አይቃረኑም።

ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ እነርሱ ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያሳዩ ዘንድ ልኳቸዋል።

የእምነታችን መሰረት መሆን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።

ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።

ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን ተከራከረና በመጨረሻም ካደው። የአስቆሮቱ ይሁዳ ኢየሱስን በገንዘብ ሸጠው። ለተጻፈው ቃል ታማኝ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው።

ማርቆስ 3፡15 ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ

ደቀመዛሙርቱ በአጋንንት እና በበሽታ ላይ መለኮታዊ ኃይል ተሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን እነዚህ ትልልቅ ስጦታዎች ጴጥሮስን እና ይሁዳን በተሳሳተ መንገድ ከመሄድ አላተረፏቸውም።

ለተጻፈው ቃል ታማኝ መሆን አስደናቂ መለኮታዊ ስጦታዎችን ከመቀበል ይበልጣል።

ማርቆስ 3፡16 ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤

ጴጥሮስ ስሙን ኢየሱስ ነው ያወጣለት።

ካቶሊኮች በዚህ ተሳስተዋል ምክንያቱም ለራሳቸው አዲስ የክርስትና ስም ያወጣሉ።

የጥንት አረማውያን (ፒተር የሚባል) ታዋቂ ተርጓሚ እንደሚመጣና የአማልክትን ሚስጥራት እንደሚገልጥ ያምኑ ነበር። “ሮማ” የሚለው ቃል ትርጉሙ ዝነኛ ማለት ነው።

ፒተር ሮማ ዝነኛ ተርጓሚ ነበር። ይህም ስም በቀላሉ የሮማው ጴጥሮስ ሆነ።

የሮማ ቤተክርስቲያንም ይህንን ተጠቅማ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሮም ውስጥ ነበር ብላ የሽንገላ ዘመቻ አደረገች። በስተመጨረሻ በ383 ዓ.ም ዳማሰስ የተባለው የሮማ ጳጳስ ጴጥሮስ የመጀመሪያው የሮማ ጳጳስ ነበረ የሚለውን እና የሮማ ጳጳሳት የጴጥሮስ ተተኪዎች ናቸው የሚለውን አስተምሕሮ ተቀበለ። ከ400 ዓ.ም ጀምሮ የሮማ ጳጳስ እራሱን ፖፕ ብሎ ጠራ።

ፔተር ሮማ ፒተር የሚለው ስሙ የመጀመሪያ ስሙ እንጂ ኋለኛ ስሙ አይደለም። ካቶሊኮች ጴጥሮስ የጴጥሮስ የመጀመሪያ ስሙ ነው ብለው ብዙ ትኩረት ስላረጉበት ፕሮቴስታንቶችም የመጀመሪያ ስሙ ነው ብለው ያምናሉ።

ማርቆስ 3፡17 የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤

ያዕቆብ እና ዮሐንስ ከደቀመዛሙርት መካከል ዋነኞቹ ናቸው። ነገር ግን ከደቀ መዛሙርት ዋነኞች መሆናቸው እንኳ ጠላቶቻቸውን ማጥፋት እንዲፈልጉ ከሚያደርጋቸው የስሕተት መንፈስ አላዳናቸውም።

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ በነበረ ሰዓት የሳምራውያን መንደር ሰዎች ሊቀበሉት አልፈለጉም።

ሉቃስ 9፡51 የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥

52 በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤

53 ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም።

ሳምራውያኑ ኢየሱስን አለመቀበላቸው ዮሐንስንና ያዕቆብን እጅግ አስቆጥቷቸዋል፤ ስለዚህ ሳምራውያንን ሊገድሏቸው ፈለጉ።

ሉቃስ 9፡54 ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው፦ ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት።

“የነጎድጓድ ልጆች” ተቃዋሚዎቻቸውን ሁሉ ቢያጠፉ ደስታቸው ነው።

ሉቃስ 9፡55 እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፦ ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤

ነገር ግን በውስጣቸው የነበረው መንፈስ ትክክለኛ አልነበረም። ኢየሱስ የመጣው ሰዎችን ለማዳን ስለሆነ የሚቃወሙትን ሰዎች አልገደለም።

ሉቃስ 9፡56 የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።

ይህ ዓይነቱ ጨካኝ መንፈስ ሰባቱ ነጎድጓዶች ምን እንደተናገሩ እናውቃለን በሚሉ የዊልያም ብራንሐም ተከታዮችም ዘንድ አለ፤ ነጎድጓዶቹ ምን ብለው እንደተናገሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈ አስተምሕሮ በመስበክ ፖፑ የወደቀበት ተመሳሳይ ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ ፖፑም መጽሐፍ ቅዱስ ያልተጻፉ ብዙ አስተምሕሮዎችን ያስተምራል። ስለዚህ የነጎድጓድ አማኞችን ብትቃወሙ ጉዳችሁ ፈላ።

ማርቆስ 3፡18 እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥

19 አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን።

የአስቆሮቱ ይሁዳ የቤተክርስቲያን መሪና ሐዋርያ ሆኖ የሰለጠነ ሰው ነበር። ግን ይህ ሁሉ እንኳ ከሰይጣን ሽንገላ ሊያድነው አልቻለም። ልክ እንደ ሌሎች ብዙ የቤተክርስቲያን መሪዎች የውድቀቱ ምክንያት ለገንዘብ መስገብገቡ ነው።

 

ኢየሱስ በሰውነቱ የሕዝብ ብዛት ይከብደው ነበር

 

ማርቆስ 3፡20 ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ።

እጅግ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ እንዲፈውሳቸው አጠገቡ ለመድረስና እርሱን ለመንካት ይጋፉ ነበር።

እንዲፈውሳቸው ጥያቄ ስላበዙበት ኢየሱስ ለራሱ እረፍት የሚያደርግበት ጊዜ አልነበረውም። ምግብ የሚበላበት ጊዜ እንኳን አጣ። ሕዝቡ ስለ እርሱ ረሃብና ድካም ግድ አልነበራቸውም፤ ሁላቸውም የራሳቸው መፈወስ ብቻ ነበር የሚያሳስባቸው።

ማርቆስ 3፡21 ዘመዶቹም ሰምተው፦ አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ።

የሕዝቡ ብዛትና ጥያቄያቸው እንዲሁም ግፊያቸው ማንኛውንም ሰው ሊያደክም የሚችል ስለነበረ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ኢየሱስን ከሕዝቡ መሃል ጎትተው ሊያስወጡት ወሰኑ። አንድ ሰው ብዙ ሺ ሕዝብ ብቻውን ለማገልገል ያለው አቅም ውስን ነው።

ብዙ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ማስተናገድ በጣም ከባድ ነው።

ለዚህ ነው ኢየሱስ ሞቶ ወደ ሰማይ ያረገውና የራሱን መንፈስ እንደ መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር የላከው።

ዮሐንስ 14፡16 እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤

የስላሴ አማኞች “ሌላ አጽናኝ” የሚለው ቃል መንፈስ ቅዱስ የሚባል ሌላ አካል ይመስላቸዋል።

ቀጣዩ ቁጥር ግን እንደዚያ አይደለም የሚለው።

ዮሐንስ 14፡17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።

እግዚአብሔር እንደ ኢየሱስ ተገልጦ ከሰው ዘንድ ይኖር ነበር።

ከዚያ ወዲያ የኢየሱስ መንፈስ ተመልሶ ይመጣና በሰዎች ልብ ውስጥ እንደ መንፈስ ቅዱስ ይኖራል።

እግዚአብሔር በመጀመሪያ እንደ ሰው ሆኖ ራሱን አሳየ ወይም ገለጠ፤ ይህም የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ያደረበት ኢየሱስ የተባለ ሰው ሲሆን በአይሁዶች ዘንድ ኖረ። ከዚያ ወዲያ እግዚአብሔር መንፈሱን አከፋፍሎ በቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ውስጥ እየገባ ይኖራል። እግዚአብሔር ራሱን አከፋፍሎ በእያንዳንዱ ግለሰብ ውስጥ ኖረ።

1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥

መንፈስ ቅዱስ በዓለም ዙርያ ሁሉ በአንድ ጊዜ መንቀሳቀስና መስራት ይችላል፤ ስለዚህ እጅግ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት መካከል አንድ ሰው ብቻ ያለ እስኪመስል ድረስ የእያንዳንዱን ሰው ጥያቄ በነፍስ ወከፍ ማስተናገድ ይችላል።

 

ኢየሱስ ዲያብሎስን አስሮ አጋንንትን ያስወጣቸዋል

 

ማርቆስ 3፡22 ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም፦ ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ፦ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ።

ኢየሩሳሌም የምትገኝበት ሥፍራ ከቅፍርናሆም ከፍ ያለ ቦታ ነው። ስለዚህ የኢየሩሳሌም ጻፎች ወደ ቅፍርናሆም ሲመጡ ከተራራ ወርደው ነው የሚመጡት። በዚህ ውስጥ ግን የተሰወረ ሚስጥርም አለ። የኢየሩሳሌም ጻፎች እራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የተሻሉና የሚበልጡ አድርገው ነው የሚመለከቱት፤ ስለዚህ ኢየሱስ የተባለውን ተዓምር ሰሪ ሊመረምሩ ወደ ቅፍርናሆም ሲወርዱ ዝቅ እንዳሉ አድርገው ይቆጥራሉ።

ወዲያውም ኢየሱስን የአጋንንት አለቃ ብለው አወገዙት። ይህ ልክ ዛሬ ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች ዓይነት ባህርይ ነው። እነርሱን ከተቃወማችኋቸው ሰይጣን ናችሁ ይሏችኋል።

ማርቆስ 3፡23 እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው፦ ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል?

ኢየሱስ ግን ሲመልስላቸው የሰይጣን መንግስት በራሱ ላይ ጥቃት የሚሰነዝር ከሆነ ብዙም እንደማይቆይ ነገራቸው።

ማርቆስ 3፡24 መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤

የሶቪየት መንግስት የፈራረሰው በውስጡ የነበሩ 15 መንግስታት ነጻነታቸውን በጠየቁ ጊዜ ነው። የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶችም ነጻነታቸውን በጠየቁ ጊዜ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ መንግስት ፈረሰ።

ውስጣዊ ተቃውሞ መንግስት እንዲፈርስ ያደርጋል።

ማርቆስ 3፡25 ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም።

አንድ ቤተሰብ ተስማምቶ በአንድ ቤት ውስጥ ካልኖረ የቤተሰቡ ዓባላት ይበታተኑና ቤተሰቡ ይፈርሳል።

አንድ ቤተሰብ አንድ ሆኖ የሚዘልቀው በግጭት ሳይሆን በስምምነትና በትብብር ነው።

ማርቆስ 3፡26 ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም።

የአጋንንት መንግስት እስካሁን ድረስ ጸንቶ መኖሩ አጋንንት እርስ በራሳቸው እንደማይቀዋወሙ ይመሰክራል።

ኢየሱስ የሰይጣንን ኃይል ተጠቅሞ አጋንንትን ማስወጣት አይችልም፤ ምክንያቱም አጋንንት ሰው ውስጥ የሚገቡት የሰይጣንን ኃይል በመጠቀም ስለሆነ የራሱን ኃይል ማፍረስ ይሆንበታል።

ማርቆስ 3፡27 ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፥ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።

ኢየሱስ የሰይጣንን ኃይል ተጠቅሞ አጋንንትን ማስወጣት የማይችልበት ሌላ ምክንያት አጋንንትን ለማስወጣት የሰይጣንን ኃይል ማሰር ስላለበት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ አጋንንትን በሚያስወጣት ሰዓት ሰይጣን ስለሚታሰር ሰይጣን በዚያ ሰዓት ምንም ኃይል የለውም።

በሺ ዓመት መንግስት ወቅት ሰይጣን ለ1,000 ዓመታት ይታሰራል። ከዚያ ኢየሱስ ዓለምን በሙሉ ይገዛል።

ይህም ኢየሱስ ከሰይጣን በላይ ኃይለኛ መሆኑን ያሳያል።

ዕብራውያን 13፡8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።

ኢየሱስ ወደፊት በሚመጣው የሺ ዓመት መንግስት ሰይጣንን ማሰር ከቻለ በማንኛውም ጊዜ በፊትም ሆነ ወደ ፊት ሰይጣንን ማሰር ይችላል።

ኢየሱስ ሰይጣንን ማሰር ከቻለ ማንኛውንም አጋንንት ማሰር ይችላል ምክንያቱም ሰይጣን ከአጋንንት ሁሉ ትልቁ ጋኔን ነው።

በፍጹም መንፈስ ቅዱስ ሰይጣን ነው አትበሉ።

ማርቆስ 3፡28 እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤

እግዚአብሔር ሐጥያትን ሁሉ ይቅር ይላል፤ ነገር ግን ይቅር የማይለው አንድ ሐጥያት ብቻ አለ።

የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሰይጣን ሥራ ነው የምትሉ ከሆነ

ማርቆስ 3፡29 በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።

አይሁዶች ኢየሱስን የአጋንንት አለቃ አሉት። ይህን ስድባቸውን እግዚአብሔር ይቅር ብሏቸዋል።

ነገር ግን ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሰይጣን ሥራ ብለው ከተናገሩ በጭራሽ ይቅር አይባልላቸውም።

ማርቆስ 3፡30 ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና።

ይህ በፍጹም በጭራሽ ማለት የሌለብን ነገር ነው።

 

የኢየሱስ ቤተሰቦች የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው

 

ማርቆስ 3፡31 እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት።

ኢየሱስ ከዮሴፍ እና ከማርያም የተወለዱ አራት ወንድሞች ነበሩት።

ማቴዎስ 13፡55 ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን?

ማርቆስ 3፡32 ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና፦ እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት።

ኢየሱስ እናቱና አራት ወንድሞቹ እየፈለጉት እንደነበረ ሲሰማ የተናገረው ንግግር በስጋ ቤተሰቡ የሆኑ ሰዎች በዝምድናቸው የተነሳ ከሌላው ሰው የተለየ ጥቅም ሊያገኙ እንደማይችሉ ያሳያል።

በሌላ አነጋገር የተወለድንበት ቤተሰብ እግዚአብሔርን አያስደንቀውም።

ማርቆስ 3፡33 መልሶም፦ እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው።

ማርቆስ 3፡34 በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና፦ እነሆ እናቴ ወንድሞቼም።

ከዚያም በዚያ ሥፍራ ተሰብስበው ቃሉን ወደሚያዳምጡ ሰዎች አመለከተ።

ቃሉን በማመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ የእርሱ እውነተኛ ቤተሰቦች መሆናቸውን በግልጽ አስረዳቸው። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምታደርግ ማንኛዋም ሴት እሕቱ ናት። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ቤተሰብ ከእናቱ እና ከአራት ወንድሞቹ የሚበልጥ ትልቅ ቤተሰብ ነው።

ማርቆስ 3፡35 የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።

ማርቆስ ስለ ኢየሱስ አገልጋይነት አጉልቶ ነው የጻፈው።

እንደ አገልጋይነቱ የአገልግሎቱ ዋነኛ ቁም ነገር የላከውን ፈቃድ ማድረግ ነው።

ባርያ ለጌታው መታዘዝ አለበት። ባርያ ወይም አገልጋይ የፈለገውን ማድረግ አይችልም።

ሉቃስ ኢየሱስን ፍጹም ሰው አድርጎ ይገልጸዋል።

የሉቃስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ከእኛ ከሰዎች ምን እንደሚጠብቅ ይነግረናል።

ሉቃስ 8፡21 እርሱም መልሶ፦ እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አላቸው።

የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና መታዘዝ አለብን።

ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይነግረናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈ ማንኛውም ነገር እግዚአብሔርን ሊያስደስተው አይችልም።

ኤፌሶን 3፡14 ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤

“እግዚአብሔር አብ” ሙሉ በሙሉ “በእግዚአብሔር ልጅ” ውስጥ ኖረ። (መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ወልድ የሚል ቃል የለም)።

ኤፌሶን 3፡15 ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት

በውሃ ጥምቀት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም የተቀበሉ ሁሉ በ2,000 ዓመታት ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ የሰማያዊ ቤተሰብ አባላት ናቸው።

 

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23