ማርቆስ 2 የናዝሬት ሰዎች ኢየሱስን አንቀበልም አሉ



ኢየሱስ ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት ጭምር ተቃውሞ ገጥሞታል። ኃይሉን ይወዱታል ትምሕርቱን ግን ይቃወሙታል።

First published on the 3rd of March 2023 — Last updated on the 3rd of March 2023

ነብዩ ወደ ቃሉ ሊጠቁማችሁ እንጂ ወደ ራሱ ሊጠቁማችሁ አይገባም

 

መጥምቁ ዮሐንስ ሕዝቡን ወደ ኢየሱስ እንዲመራ አስቀድሞ የተላከ መንገድ ጠራጊ ነበረ።

ዮሐንስ 1፡6 ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤

በሌላ አነጋገር ሕዝቡ የቃሉን ብርሃን መረዳት እስኪችሉ ድረስ ዮሐንስ በተናገረው ንግግር ብርሃንነት ተጠቅመው መንገዳቸውን ማየት ነበረባቸው ማለት ነው።

ዮሐንስ 1፡7 ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።

ሰዎች ኢየሱስ ማን መሆኑን ለመረዳት የዮሐንስን ንግግር እንደ መነጽር መጠቀም አለባቸው።

ለመረዳት ከባድ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን መረዳት እንድንችል የዊልያም ብራንሐምን ንግግሮች እንደ መነጽር መጠቀም አለብን።

ብዙ ሰዎች ያልተገነዘቡት ዋናው ነገር ዮሐንስ ብርሃን መሆኑን ነገር ግን እውነተኛው ብርሃን አለመሆኑን ነው።

ዮሐንስ ከሰው ልጆች አንዱ (ነብይ) ነበረ እንጂ ዋናው የሰው ልጅ አልነበረም።

ዮሐንስ መሲህ (የተቀባ ሰው) ነበረ፤ ነገር ግን መሲሁ አልነበረም።

ኢየሱስ ብቻ ነው የሰው ልጅ።

ዮሐንስ ኢየሱስን እንደ ሰው ለአይሁድ ሕዝብ ገለጠላቸው።

ወንድም ብራንሐም ኢየሱስን መረዳት እንድንችል እንደ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ (እንደ ቃሉ) ገለጠልን።

65-0725 በዘመን መጨረሻ ላይ የተቀቡት

ይህ ምንድነው? መልአኩ የሰው ልጅ አይደለም፤ ነገር ግን መልእክተኛው የሰውን ልጅ እየገለጠው ነው። አሁን ለይታችሁ ማየት ቻላችሁ? ለእናንተ ከባድ የሚመስላችሁ ይህ ነው፤ አያችሁ።

የሰው ልጅ እራሱ ሳይሆን ሰባተኛው መልአክ፤ ሰባተኛው መልእክተኛ ነው የሰው ልጅን ለሕዝብ የሚገልጠው ፤

ዮሐንስ 1፡8 ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።

የነብዩ ንግግሮች “የእግዚአብሔር ድምጽ” አይደሉም። የነብዩ ንግግሮች የእግዚአብሔር ድምጽ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ያብራራሉ።

65-0801 የዚህ ክፉ ዘመን አምላክ

…ጌታ ኢየሱስ ለዚህ ዘመን የሰጠኝን መልእክት ያመኑ ሰዎች አሁን ምን እየተፈጸመ እንዳለ ያውቁ ዘንድ እንዲሁም ከቃሉ ውስጥ የትጋ እንደተጻፈ ማሳየት ይችሉ ዘንድ ነው።

 

መልእክቱ እውነት መሆኑን ከኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ አለባችሁ።

64-0614 ልዩ መልእክት

መልአኩ እንዲህ ብሎ ነው የተናገረኝ፡- “ሕዝቡ እንዲያምኑህ አድርግ።”

እኔም የእግዚአብሔር ቃል ስናገር “ቃሉን እመኑ” ማለቴ እንጂ “እኔን እመኑ” ማለቴ አይደለም።

63-0630 ሶስተኛው ፍልሰት

…የእግዚአብሔር ድምጽ በቃሉ በኩል ሲጠራቸው በግልጽ ሊሰሙ ይችላሉና … መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን አዳምጡ፣ ዛሬ የሚጠራችሁ የእግዚአብሔር ድምጽ መጽሐፍ ቅዱስ ነው

 

ናዝሬት ውስጥ ሕዝቡ ኢየሱስን አንቀበልም አሉ፤ እርሱም መጥምቁ ዮሐንስ እስር ቤት ከገባ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ፈቀቅ አለ።

የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት በመጥምቁ ዮሐንስ ንግግር በጣም ከመመሰጣቸው የተነሳ ኢየሱስ እያገለገለ መሆኑን እንኳ ልብ አላሉም።

ሉቃስ 12፡48 ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥

የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት ከሌሎች ሰዎች ቀደም ብለው እውነትን የማወቅ ዕድል አግኝተው ነበር። ከዚህም የተነሳ እግዚአብሔር ከእነርሱ ብዙ ነው የጠበቀው። እነርሱ ግን ከዮሐንስ በኋላ ኢየሱስን ማለትም ቃሉን ለመከተል እምቢ አሉ።

የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት ኢየሱስን ለመቀበል እምቢ በማለታቸው ለኢየሱስ አገልግሎት እንቅፋት ነበሩ። እነርሱ ዮሐንስን ከልባቸው ከመከተላቸውና በዮሐንስ አገልግሎት ድምቀት እጅግ ከመደነቃቸው የተነሳ የኢየሱስን አገልግሎትና ታላቅነት ማየት እስከማይችሉ ድረስ ታውረው ነበር

በመጥምቁ ዮሐንስ ንግግር በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ኢየሱስን ቸል አሉ።

ወንድም ብራንሐም ኢየሱስን እንደ ሰው አይደለም ጠቁሞ የሚያሳየን፤ ነገር ግን ኢየሱስን መረዳት እንደምንችለው የተገለጠ ቃል አድርጎ ነው የሚያሳየን።

ወንድም ብራንሐም የእግዚአብሔር ድምጽ ነው ደግሞም አይሳሳትም ብለው በማስተማር የሜሴጅ ሰዎች የተገለጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንዳይሰራጭ እንቅፋት እየሆኑ ናቸው፤ ምክንያቱም የሜሴጅ ተከታዮች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ትተዋል።

62-1007 የበሩ መክፈቻ

ሰዎች ሚስታቸውን ትተው ትክክለኛዋን አጥንታቸውን ፍለጋ መውጣት አለባቸው እያሉ ይሰብካሉ፤ በተጨማሪ ደግሞ እኔ ልሳሳት እንደማልችል አድርገው ያወራሉ። … ከዚህም የባሱ አንዳንድ አስደንጋጭ ነገሮችን ይናገራሉ።

“የሰው ንግግር ጥቅስ አለኝ” የሚለው አባባል “ተብሎ ተጽፏል” የሚለውን ተክቶታል።

የሰው ንግግር ጥቅስ ለመከተል ብለው ቃሉን ቸል የሚሉ ሁሉ ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል።

ዮሐንስ ከመንገድ ተወግዶ ወኅኒ ቤት ሲገባ ብቻ ነው ኢየሱስ በይፋ ተገልጦ ማገልገል የቻለው።

ማቴዎስ 4፡12 ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ።

ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።

መንገድ ጠራጊውን ካወቃችሁ በኋላ ወዲያው ዓይናችሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ልታነሱ ትችላላችሁ። መንገድ ጠራጊው ራሱ ግን የመጣው ዓይናችሁን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንድታደርጉ መጽሐፍ ቅዱስን ሊያብራራላችሁ ነው።

ዊልያም ብራንሐምን የሚከተሉ እና እምነታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማሳየት የማይችሉ የሜሴጅ አማኞች ትልቅ ችግር ይገጥማቸዋል። ብዙ ተሰጥቷቸው ነበር ነገር ግን ዓይናቸውን ዋናው ግብ ከሆነውና ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ከሚመልሰን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥር ላይ አንስተው ሌላ ቦታ አደረጉ።

64-0823 ጥያቄዎችና መልሶች

ቃሉን በሙላት መቀበል የሚችሉ ግን እኔ ስለሰበክሁ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ስለተናገረ ይቀበላሉ። የሚቀበሉ ሁሉ ለመቀበል ነጻ ናቸው ምክንያቱም ቃሉ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል።

 

ኢየሱስ አገልግሎቱ እንዲስፋፋና ወደ ገሊላ መግባት እንዲችል ዮሐንስ ከመንገድ መወገድ ነበረበት።

 

 

ኢየሱስ ገሊላ ውስጥ ማገልገልን መረጠ ምክንያቱም ገሊላ በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ውስጥ ያሉ ካሕናት ለእርሱ ካላቸው ጥላቻ ራቅ ያለ ሥፍራ ነው። ኢየሱስ ለገቢ ምንጫቸው ስጋት ሆኖባቸዋል። የሐይማኖት መሪዎች ልባቸው ገንዘብ ማሳደድ ላይ ነው።

ቤተመቅደሱ ዛሬ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍሎች የሚጠሉ የቤተክርስቲያን ድርጅቶች ምሳሌ ነው። ለዚህ ነው በመጨረሻው የሎዶቅያውያን የቤተክርስቲያን ዘመን ሰዎች ቃሉን አንቀበልም ሲሉ ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን በር ውጭ የሚቆመው።

 

የናዝሬት ሰዎች ኢየሱስን ተቃወሙት፤ ሊገድሉትም ሞከሩ

 

ኢየሱስ ቀጥሎ የደረሰበት ነገር ከሁሉ ይበልጥ የሚያውቁት ሰዎች እርሱን መግፋታቸው ነው፤ በተለይም ናዝሬት ውስጥ የሚኖሩ አይሁዶች አልተቀበሉትም።

ሉቃስ 4፡16 ወዳደገበቱም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ።

ቃሉን ሰበከላቸው፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ፈለጉ። ቸልተኛ የሆኑ ሰዎች ቤተክርስቲያን ሲመላለሱ የሚሆነው ይህ ነው። ኢየሱስ በነብዩ ኤልያስ አማካኝነት ከለምጸ ስለተፈወሰው ስለ አሕዛቡ ንዕማን ተናገረ። ንዕማን እንደታዘዘው ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ብሎ ነው የተፈወሰው። ከዚያም ቀጥሎ ደግሞ ኤልያስ በ3 ዓመት ተኩሉ የረሃብ ዘመን ምግብ እንዲበላ የተላከው ወደ አንዲት አሕዛብ ሴት መሆኑንም አነሳላቸው። ሊነግራቸው የፈለገው ግልጽ ነበር። እግዚአብሔር ፊቱን ከአይሁድ መልሶ ወደ አሕዛብ ዘወር እንደሚል እያመለከታቸው ነበር።

የአይሁዶችም ምላሽ እውነቱን የነገራቸው ሰው ላይ የግድያ ሙከራ ማድረግ ነበር።

ዛሬም እንዲሁ ነው። ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ስሕተታቸውን ሊያርማቸው የተነሳ ሰውን በፍጥነት ይገፉታል፤ ምክንያቱም ቤተክርስቲያኖች መሳሳታቸውን መቀበል አይወዱም።

ሉቃስ 4፡29 ይጥሉትም ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት፤

ሉቃስ 4፡30 እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።

በቁጣ ገንፍለው ከከበቡት አይሁዶች መካከል እንዴት አልፎ ሊሄድ ቻለ?

እኛ በሶስት ዳይሜንሽኖች ውስጥ ነው የምንንቀሳቀሰው፤ እነዚህም ርዝመት፣ ስፋት፣ እና ከፍታ ናቸው።

ጊዜ ደግሞ የአራተኛው ዳይሜንሽን አካል ሲሆን እርሱም የመልካምና የክፉ መንፈሳዊ ዳይሜንሽን ወይም ቀጠና ነው። በዚህ በአራተኛው የጊዜ ዳይሜንሽን ውስጥ የሚኖሩ አጋንንትና ሰይጣን ጊዜያቸው ሲያበቃ የእሳት ባሕር ውስጥ ይገባሉ። እኛ በጊዜ ውስጥ እንቅስቃሴያችን ከትናንት ወደ ነገ ብቻ ስለሆነ እንደፈለግን በነጻነት መንቀሳቀስ አንችልም። የመልካም እና የክፉ ቅልቅል የሆነው የሰው መንፈስ ከዚህ ከአራተኛው ዳይሜንሽን ጋር ለመገናኘት ውስብስብ የሆነውን አንጎላችንን ይጠቀማል።

ኢየሱስ ግን ከፍ ባለው መንፈሳዊ በሆነው በስድስተኛው የሰማይ ዳይሜንሽን ውስጥም መንቀሳቀስ ይችል ነበር።

ዮሐንስ 3፡13 ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።

 

በስድስተኛው ዳይሜንሽን ውስጥ ገብቶ በሚንቀሳቀስ ጊዜ ማንም ሰው ሊነካው አይችልም ነበር።

 

ለዚህ ነው ከትንሳኤው በኋላ በሮች የተዘጉበት ቤት ውስጥ በር ሳይከፍት ይገባ የነበረው።

ኢየሱስ ያደገው ናዝሬት ውስጥ ነው። ነገር ግን በዚያ ከተማ በደምብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች እግዚአብሔር ወደ አሕዛብ ዘወር እንደሚል ሲሰብክ አልተቀበሉትም። ይህ ማለት እግዚአብሔር ከአይሁድ ዘወር እያለ መሆኑ ገብቷቸዋል። ሐይማኖተኛ ሰዎች ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል እንደሆኑ ይመስላቸዋል። ስለዚህ በናዝሬት የሚኖሩ አይሁዶች ኢየሱስ በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኞች አለመሆናቸውን ስለነገራቸው ሊገድሉት ፈለጉ።

ልክ እንደዚሁ ወንድም ብራንሐምን በደምብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች እውነትን ከኪንግ ጄምስ ቨርዥነ መጽሐፍ ቅዱስ በመግለጥ ከሌሎች ሰዎች ሊበልጡ አይችሉም።

የሰውን ንግግር ጥቅሶች ማንበብ ብቻ ይበቃል በሚል ሐሰተኛ ትምሕርት የተታለሉ የሜሴጅ አማኞች ጥቅሶቹ የተለያየ ነገር በሚናገሩ ጊዜ እንዴት አድርገው መተርጎም እንዳለባቸው አያውቁም። ቀጥለው ደግሞ እግዚአብሔር ሊተዋቸው እንደሆነ ሲረዱ ይፈራሉ፤ ስለዚህ ልክ እንደ ጥንቶቹ አይሁዳውያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ተመሳክረው ትክክል መሆናቸው የተረጋገጠላቸውን ጥቅሶች ብቻ የሚያምኑ ሰዎችን ስም ያጠፋሉ። ምክንያቱም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው።

በመጨረሻም ቃሉ ኢየሱስ መልእክተኛ ሆኖ ከመጣው ነብይ ይበልጣል።

 

ናዝሬት ማለት የቅርንጫፉ ቦታ ነው

 

ኔትዘር የተባለው የዕብራይስጥ ቃል ቅርንጫፍ ማለት ነው።

ኔትዘሬት ማለት የቅርንጫፉ ቦታ ነው።

በግሪኩ አዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው ናዝሬት የሚለው ቃል የመጣው ኔትዘሬት ከተባለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።

ኢሳይያስ 11፡1 ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል።

ዘካርያስ 3፡8 ታላቁ ካህን ኢያሱ ሆይ፥ ስማ በፊትህም የሚቀመጡት ባልንጀሮችህ ለምልክት የሚሆኑ ሰዎች ናቸውና ይስሙ፤ እነሆ፥ እኔ ባሪያዬን ቍጥቋጥ አወጣለሁ።

9 በኢያሱ ፊት ያኖርሁት ድንጋይ እነሆ አለ፤ በአንዱ ድንጋይ ላይ ሰባት ዓይኖች አሉ፤

ለሰባት ዓይኖች ብርሃን የሚሰጡ ሰባት መብራቶች፤ እነዚህ እግዚአብሔር ለሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት የላካቸው ሰባት መልእክተኞች ናቸው።

ይህም የሚገልጸው ባለ ሰባት ቅርንጫፉን መቅረዝ ነው። ስድስት መብራቶች በመቅረዙ መካከል ካለው መካከለኛ መብራት የሚወጡ ቅርንጫፎች ናቸው።

ዘጸአት 25፡31 መቅረዝንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ፤ መቅረዙ ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀጠቀጠ ሥራ ይደረግ፤ ጽዋዎቹም ጕብጕቦቹም አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት።

32 በስተጎኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስትም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ።

 

 

ባለ ሰባት ቅርንጫፉ መቅረዝ ውስጥ መካከለኛው ቅርንጫፍ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ሐዋርያትን ተጠቅሞ የአዲስ ኪዳን እውነት መሰረትና አምድ የሆነችዋን የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን በመጀመሪያው ዘመን ውስጥ መሰረተ።

በቀጣዮቹ 2,000 ዓመተት ውስጥ የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ታሪክ እንደ ቅርንጫፍ ሆኖ የወጣው ከክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ነው።

አሕዛቡ ንዕማን ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማለቱ በሰባቱ የአሕዛብ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ እያንዳንዱ ግለሰብ በቃሉ ውሃ አማካኝነት ታጥቦ ከልቡ ውስጥ አለማመን እንደሚወገድለት የሚያስረዳ ተምሳሌት ነው።

አሕዛብ እንደ ቤተክርስቲያን በሕብረት አይደለም የሚድኑት፤ አሕዛብ በየግላቸው ነው የሚድኑት።

ልክ ጋራዥ ውስጥ መግባት ወደ መኪናነት እንደማይለውጣችሁ ሁሉ ቤተክርስቲያን መሄድም ክርስቲያን አያደርጋችሁም።

 

 

ሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የጀመረው በ170 ዓ.ም የአጥቢያ ሽማግሌዎች ቤተክርስቲያንን ማስተዳደራቸው ቀርቶ አንድ ጳጳስ የቤተክርስቲያን ራስ ነኝ ያለ ጊዜ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በእያንዳንዷ ቤተክርስቲያን አንድ ሰው ራስ ሆኖ ተሾመባት። በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያ የቤተክርስቲያን ዘመን ይህ ተደርጎ አያውቅም። ከዚያም ልክ ናዝሬት ውስጥ አይሁዶች ኢየሱስን ሊገድሉ በሞከሩበት መንገድ እነዚህ ጳጳሳት የሮማ ንጉስ በ325 ዓ.ም በተደረገው የኒቅያ ጉባኤ የኮንስታንቲንን ፖለቲካዊ ተጽእኖ ተቀብለዋል (በዚህም አካሄዳቸው ብዙ ገንዘብ አግኝተዋል)። ኮንስታንቲን አብ እና ወልድ አንድ ባህሪ ናቸው በማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውን የስላሴ ትምሕርት ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ አስገባ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይገኙ ቃላትን በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምሕርቶችን አስፋፋ።

ይህም ድርጊት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ፍቅር ከሰዎች ልብ ውስጥ አጠፋ፤ ቤተክርስቲያንም በብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ትምሕርቶች እንድትሞላ በር ከፈተ። ክሪስማስ። ዲሴምበር 25። የገና ዛፍ። የስቅለት አርብ። የፋሲካ ሰኞ። ኩዳዴ። የፋሲካ እንቁላሎች። የፋሲካ ጥንቸሎች፣ ወዘተ።

ከዚያም በረጅሙ የአራተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ በዘለቀው የጨለማ ዘመን ከአስር ሚሊዮን በላይ ክርስቲያኖች እንደ በሬ ታርደው ሞተዋል።

 

 

ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዲሁም ብዙ ክርስቲያኖች ሞቱ።

ኋለኞቹ ቤተክርስቲያኖች የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የነበራትን እምነት ትተው መሄዳቸው ክፋት ነው።

ናዝሬት ውስጥ ሰዎች ኢየሱስን ለመግደል እንደሞከሩት ልክ እንደዛው በ325 ዓ.ም በተደረገው የኒቅያ ጉባኤ እና በ1520 በተጠናቀቀው የጨለማ ዘመን መካከል ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመግደል ሙከራ አድርገዋል። ኢየሱስ ቃሉ ነው። እርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው።

 

ናዝሬት ሰው ዞር ብሎም የማያያት እንቅልፋም ከተማ ነበረች

 

በጨለማው ዘመን ውስጥ ብዙ እውነተኛ አማኞች የአልፕስ ተራሮች ውስጥ ሊሸሸጉ በሄዱበት ጠፍተው ቀርተዋል። በ1620 አውሮፓ ውስጥ በእምነታቸው የተነሳ ስደት የበዛባቸው ሰዎች ወደ አሜሪካ ሸሽተው ሄዱ።

ናዝሬት ከዋናው መንገድ ተገንጥሎ በሚገባው መንገድ ላይ የምትገኝ ማንም ዞር ብሎ የማማያት ከተማ ናት።

በብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም ይሁን በሌሎች ጥንታውያን ጽሑፎች ውስጥ ከመንገድ ወጣ ብላ የምትገኘዋ ታናሽዋ የናዝሬት ከተማ ተጠቅሳ አታውቅም።

ናዝሬት ማንም የማደንቃት በሰዎች ሁሉ የተረሳች ትንሽ ከተማ ናት። ገሊላ አውራጃ ውስጥ እንኳ ታዋቂ አይደለችም። ከአዲስ ኪዳን ውጭ ናዝሬት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰችው በአንድ የታሪክ ምሑር ጽሑፍ ውስጥ በ200 ዓ.ም ነው።

ከኢየሩሳሌም መውጣት ቁልቁል መውረድ ነው፤ ይህም ከአካባቢው መልክዓ ምድር አንጻር ብቻ ሳይሆን ከማሕበረሰብ አንጻርም ነው። ሆኖም ግን እግዚአብሔር ራሱን ባዶ የማድረግ ምሳሌነቱን እያሳየ ስጋ ለብሶ ሰው ሆኖ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ በተገለጠ ጊዜ “ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ”።

ኢየሱስ በዚህች ተራ መናኛ ከተማ ውስጥ ነው ያደገው።

ሉቃስ 2፡51 ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥

ኢየሱስ ከናዝሬት ተገፍቶ ከወጣ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ሄደ፤ የቅፍርናሆም ከተማም የአገልግሎቱ ዋና ማዕከል ሆነች።

 

 

ቅፍርናሆን ሞቅ ያለችና ብዙ እንቅስቃሴ ያለባት ከተማ ናት

 

ሉቃስ 4፡31 ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤

ቅፍርናሆም (የስሟ ትርጉም የምቾት መንደር ነው) ለተወሰነ ጊዜ የኢየሱስ አገልግሎት ማዕከል ሆነች። የቅፍርናሆም ሕዝብ ኢየሱስ ሲሰብክ ሰሙ፤ አስደናቂ ኃይሉንና ፍቅሩንም አዩ። ነገር ግን እርሱን አልተቀበሉትም። የኑሮዋቸው ምቾት መንፈሳዊ ቅናትን ከውስጣቸው አጥፍቶባቸዋል።

ድሎት የጋለ ፍላጎትንና ቅናትን ይገድልና በቀብሩ ላይ እየሳቀ ይሄዳል (ኦማር ካያም)።

 

 

የመጨረሻውና ሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በገንዘብና በንብረት ሃብታም የሆነ ዘመን ነው።

ራዕይ 3፡17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥

የገንዘብ ፍቅር መንፈሳዊነትን አይቀበልም።

በዕለት ተለት ኑሮ ትግል ውስጥ ስንመላለስ ከባድ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ትርጉም መረዳት የሚያስፈልገን አይመስለንም። የሕይወት ዋና ግባችን ጊዜያዊ የሆነውን የኑሮ ችግር መፍታት ሆኗል።

ማቴዎስ 4፡13 ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ።

የዛብሎን ነገድ እና የንፍታሌም ነገድ አዋሳኞች የሚገናኙት በቅፍርናሆም ከተማ ነው።

ዘፍጥረት 49፡13 ዛብሎን በባሕር ዳር ይቀመጣል፤ እርሱም ለመርከቦች ወደብ ይሆናል፤ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ድረስ ነው።

ያዕቆብ ወደፊት ኢየሱስ በቅፍርናሆም ከተማ ስለሚኖርበት ጊዜ ትንቢት እየተናገረ ነበር፤ ይህም ስፍራ በዛብሎን እና በንፍታሌም ድንበር መካከል ነው።

 

 

ወደብ ማለት መርከቦች ሲመጡ የሚቆሙበት ቦታ ወይም ከአውሎ ነፋስ የሚጠለሉበት ማለት ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደመሆኑ መጠን መጠለያችን ማረፊያችን ነው። አንዴ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ከቻላችሁ በኋላ ወደ ትክክለኛው እውነት ጉዞ ጀምራችኋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መገለጥ ለሰዎች ነፍስ መጠለያ ነው።

ወደ መጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ሊመልሰን የሚችለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መረዳት እኛ ከምንገምተው በላይ አስፈላጊ ነው። በዚህ የምድር ሕይወታችን ውስጥ በሚያጋጥሙን ጉዳዮች ተጠምደን የሕይወት ዋናው ነገር እነርሱ ይመስሉናል። ከዚህም የተነሳ ሞኞች ሆነን ከሰነፎቹ ቆነጃጅት ጎራ እንቀላቀላለን።

ዘፍጥረት 49፡21 ንፍታሌም የተፈታ ሚዳቋ ነው፤ መልካም ቃልን ይሰጣል።

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ ስዚህ የመልካም ቃላት ምንጭ እርሱ ነው። ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት በላይ የሚጠቅመን ቃል የለም።

ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ ሕዝቡ በመጥምቁ ዮሐንስ ተጽእኖ ስር ስለነበሩ በደምብ አያደምጡትም ነበር። ብዙዎቹ ለዮሐንስ ባላቸው ታማኝነት የተነሳ ታውረው ኢየሱስን መከተል አልቻሉም።

ዮሐንስ 3፡22 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።

ኢየሱስ ከራሱ ደቀመዛሙርት ጋር ሕብረት ፈጥሮ ሳለ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት ደግሞ የራሳቸውን ሌላ ሕብረት ፈጠሩ።

የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ግን ይከተሉ የነበሩት ዮሐንስን እንጂ ኢየሱስን አልነበረም።

ዮሐንስ 3፡23 ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥ እየመጡም ይጠመቁ ነበር

ዮሐንስ ወደ እስር ቤት ከመግባቱ በፊት በአግልግሎት ላይ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር መቆየትን መረጡ፤ ከዚህም የተነሳ የዮሐንስን ንግግር ያዳምጡ ስለነበረ ከሌላው ሰው ይልቅ ወደ እውነት የቀረቡ መሰላቸው። ወደ ዮሐንስ አብዝተው በመቅረብ ኢየሱስን ማለትም ቃሉ ቸል ብለው ቀሩ።

ዮሐንስ 3፡24 ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና።

25 ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ።

የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ኢየሱስን ሳያማክሩ የአይሁዶችን ጥያቄዎች ሊመልሱ ሞከሩ። ዛሬም የሜሴጅ ተከታዮች አንዳንድ የሰው ንግግር ጥቅሶችን ሲተረጉሙ መጽሐፍ ቅዱስን አያማክሩም። ከዚህም የተነሳ የ2016ቱን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሒላሪ ክሊንተን ታሸንፋለች ብለው ትንቢት ተናግረው ነበር። ነገር ግን አላሸነፈችም።

ዮሐንስ 5፡35 እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ።

ዮሐንስ አገልግሎቱ ታላቅ ነበረ፤ የዮሐንስ ደቀመዛሙርቱም ዮሐንስ የማይሳሳት ፍጹም ሰው ነው ብለው እስኪያምኑ ደርሰው ነበር።

ዮሐንስ 5፡36 እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤

የዊልያም ብራንሐም ንግግሮች መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለመረዳት ይጠቅሙናል፤ ነገር ግን የንግግሮቹን እውነተኛነት በመጽሐፍ ቅዱስ መዝነን ማጣራታችን አስፈላጊ ነው።

“ተብሎ ተጽፏል” ማለት “እከሌ እንዲህ ብሏል” ከሚለው አነጋገር የሚበልጥ ስልጣን አለው።

ዮሐንስ 3፡30 እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል።

እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ለራሳችሁ ማረጋገጥ የሰውን ንግግር እንደ ገደል ማሚቶ ከመድገም ይሻላል፤ ወንድም ብራንሐም ያለው ይህንን ነው።

የሰባቱ ቤተክርስቲያን ዘመናት ማብራሪያ - ምዕራፍ 9 - የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ዘመን

…እውነተኛ ነብይ ሁልጊዜ ሰዎችን ወደ ቃሉ ነው የሚመራቸው፤ ሁልጊዜ ሰዎችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው የሚያስተሳስራቸው፤ ሕዝቡ ነብዩን ወይም ነብዩ የተናገረውን ቃል እንዲፈሩ አያስተምርም፤ ቃሉ የተናገረውን እንዲፈሩ ነው የሚያስተምራቸው።

አብዝተው ዮሐንስ ላይ በመደገፍ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት የዮሐንስን ትልቅ ስሕተት ደገሙ። ለዚህም ችግር የተጋለጡት ነብዩን ማረም አይቻልም የሚል አስተምሕሮ በመፍጠራቸው ነው።

ሉቃስ 7፡19 ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ወደ እርሱ ጠርቶ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ።

እነዚህ ሁለት የዮሐንስ ደቀመዛሙርት በዮሐንስ ተጽእኖ ስር ሆነው ለረጅም ጊዜ ከመቆየታቸው የተነሳ ዮሐንስ ኢየሱስ መሲሁ መሆኑን በተጠራጠረ ጊዜ ዮሐንስ የሰራውን ስሕተት ተከትለው ሄደዋል። ስለነዚህ ሁለት ደቀመዛሙርት ከዚህ ጥቅስ ወዲያ ሁለተኛ አልተጻፈም።

ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስን አልነቀፈውም። ዮሐንስ ሰው ነው፤ ሰዎች ደግሞ ይሳሳታሉ። የተሳሳቱት የዮሐንስ ደቀመዛርት ናቸው። የዮሐንስን ስሕተት እንደ ትክክለኛነት አድርገው ቆጠሩ። ነገር ግን ይህን ለማድረግ የሚያበቃ አንዳችም አጥጋቢ ምክንያት አልነበራቸውም።

ከዮሐንስ ደቀመዛሙርት መካከል ወጥቶ ከ12ቱ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት አንዱ ለመሆን የበቃው እንድርያስ ብቻ ነው።

ዮሐንስ 1፡35 በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥

[ከነዚያ ሁለት የዮሐንስ ደቀመዛሙርት አንዱ እንድርያስ ነበር]።

36 ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ፦ እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ።

ነብዩ ዮሐንስ እራሱን ሊያስተዋውቅ አይደለም የተላከው፤ እርሱ የተላከው ኢየሱስ በምድር ላይ እንደ ሰው በሚመላለስበት ጊዜ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ እንዲጠቁም ነው።

ነብዩ ዊልያም ብራንሐም እራሱን ሊያስተዋውቅ አይደለም የተላከው። እርሱ የተላከው በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ የሚመላለሰውን ኢየሱስን ለሰዎች ለማሳየት ነው።

ዮሐንስ 1፡37 ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።

ሁለቱ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ዮሐንስ ኢየሱስን ካሳያቸው በኋላ የኢየሱስ ተከታዮች ሆነው ቀሩ።

የመንገድ ጠራጊውን ነብይ አገልግሎት የምንቀበልበት ትክክለኛው አቀባበል ይህ ነው። መጀመሪያ በቃሉ የተገለጠውን ኢየሱስን ልብ ብላችሁ ተመልከቱት፤ ከዚያ ወዲያ የተጻፈውን ቃል በማመን እና በማድረግ ኑሩበት።

ነብዩ ዊልያም ብራንሐም የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መገለጥ ሲያስተምራችሁ አድምጡት፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከትምሕርቱ ጋር የተያያዙ ጥቅሶችን በራሳችን አገናኝታችሁ ያመናችሁት እውነት መሆኑን እስክታረጋግጡ ድረስ በደምብ ተማሩ። ከዚያ መጽሐፍ ቅዱስን ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል ተከተሉ።

ስሕተት ቁ. 1 - የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ከኢየሱስ ይልቅ ዮሐንስን መረጡ።

ስሕተት ቁ. 2 - ኢየሱስ ናዝሬት ውስጥ በማደጉ ምክንያት ከሌሎች ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኢየሱስን በደምብ ያውቁ የነበሩ የናዝሬት ሰዎች እግዚአብሔር ወደ አሕዛብ ዘወር እንደሚል ሲነግራቸው ኢየሱስን ሊገድሉት ፈለጉ።

ስሕተት ቁ. 3 - ብዙ ተዓምራት የተደረገባት የቅፍርናሆም ከተማ ኢየሱስን አልተቀበለችውም፤ በመጨረሻም ፈርሳ ለብዙ ዘመናት ባዶ ሆና ቀረች።

ይህ ማስጠንቀቂያ ነው። ወንድም ብራንሐምን በደምብ ማወቅና ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይልቅ የእርሱን ንግግር ጥቅሶች መምረጥ፣ እንዲሁም በአስደናቂ አገልግሎቱ ውስጥ በሚገለጠው ኃይል መደሰት በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናችሁን አያሳይም።

 

አራት ሰዎች በዙፋኑ ዙርያ ያሉትን 4ቱን ሕያዋን ፍጥረታት ይወክላሉ

 

ማርቆስ 2፡1 ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ።

“ከጥቂት ቀን በኋላ”። እንዲህ ዓይነቱ መዘግየት የተለመደ አይደለም። ሰዎች ለእውነት የሚሰጡት የተሳሳተ ምላሽ እውነት በፍጥነት እንዳትሰራጭ እንቅፋት ይሆናል።

ማርቆስ 2፡2 በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር።

የሕዝብ ብዛት ለአገልግሎት አይመችም። ትልልቅ ቤተክርስቲያኖች የመጽፍ ቅዱስ እውነት ከመካከላቸው ደብዝዞ እስኪጠፋ ድረስ ነው የራሳቸውን ልማዶችና አመለካከቶች ለሕዝብ የሚያስተምሩት። ሰባኪዎቹ ሕዝቡ የሚፈልጉትን ስብከት እየመረጡ በመስበክ በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተወዳጅነት ያስጠብቃሉ። ስለዚህ ሕዝብ በበዛበት ወደ ኢየሱስ መጠጋት አስቸጋሪ ነው። ሰዎች በዙርያቸው የሚገኙ ሰዎችን አመለካከት ይከተላሉ። ከዚህም የተነሳ እውነተኛ የሆነውን የቃሉን መገለጥ አያገኙም።

አንድን ሰው ወደ ኢየሱስ ፊት ማቅረብ ብዙ ጥረት ይጠይቃል።

58-1005 እግዚአብሔር ሰውን ጠራ

ሰዎች እየተጋፉ ሲገቡ ስናይ፤ በበሩ አካባቢ ሲቆሙ፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሕዝብ ከትንሽዋን ቤተክርስቲያን ትተው ሲሄዱ ስናይ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው መሆኑን ያስታውሰናል። ጌታ ወደ ምድር መጥቶ በስጋ ተገልጦ የጎበኘን ጊዜ እርሱን ፍለጋ የሚመጡ ሰዎች ብዛት እጅግ ታላቅ ስለነበረ አንድ በሽተኛ ይዘው ሲመጡ ወደ እርሱ አጠገብ መድረስ ባለመቻላቸው በቤቱ ጣራ በኩል መግባት ግድ ሆኖባቸዋል። ዛሬም ደግሞ ልክ እንደዚህ ሰው ተጋፍቶ ለሚገባ ሰው ሁሉ እግዚአብሔር ዋጋውን እንዲከፍለው እንጸልያለን።

ኢየሱስ በመጀመሪያው ምጻቱ እንደ ሰው ተገለጠ።

በዳግም ምጻቱ የሚታየው እንደተገለጠው ቃል፤ መረዳት እንደምንችለው ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ሆኖ ነው።

ማርቆስ 2፡3 አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት።

አንድን ሽባ ሰው አራት ሰዎች ተሸክመውት የቤት ጣራ ላይ ወጡ። ጣራውንም ቀደው ወደ ቤቱ ውስጥ በገመድ አወረዱት።

ማርቆስ 2፡4 ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፥ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ።

ይህም ሽባ ሰው በአሕዛብ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት መካከል የሚኖሩትን በእምነታቸው ሽባ የሆኑ ሰዎችን ይወክላል። አራቱ ሰዎች ጀእግዚአብሔር ዙፋን ዙርያ ያሉትንና ቤተክርስቲያንን የሚመራ መንፈሳዊ መገለጥ የሚያመጡትን አራት ሕያዋን ፍጥረታት ይወክላሉ። ይህም በአረማዊ ልማዶቻቸው የተነሳ እምነታቸው ሽባ የሆነባቸውን አሕዛቦች ወደ ኢየሱስ እና ወደተገለጠው ቃሉ በማምጣት ከወደቁበት ያነሳቸዋል። የምንድነው የቤተክርስቲያን አባል በመሆን ሳይሆን ከኢየሱስ ጋር የግል ሕብረት በማድረግ ነው።

 

 

ራዕይ 4፡7 ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል።

ራሳችንን ከዝናብ እና ከፀሃይ ለመከላከል ብለን የምንሰራው ጣራ ወደ ሰማይ ማየት እና እምነታችንን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ እንዳንችል ይከለክለናል። ዓይናችን ከስጋዊ ምቾታችን እና ከስጋዊ ንብረቶቻችን ውጭ አልፎ ማየት አይችልም። ጸሎታችን እንኳ ሳይቀር ጤንነታችንን፣ ገንዘባችንን፣ ሥራችንን፣ ቤተሰቦቻችንን፣ እና ጓደኞቻችንን በተመለከተ ናቸው። የእምነታችን ልክ የሚወሰነው ብዙውን ጊዜ የባንክ ሒሳባችን ውስጥ ባለው የገንዘብ መጠን ነው። እኛም ገቢ እስካስገኘልን ድረስ የምናደርገውን ማንኛውንም ዓይነት ድርጊት ትክክል እንደደሆነ እናስባለን።

መጀመሪያ የምንድነው ጌታ ኢየሱስን በግል በማወቅ ነው፤ ይህም መልካም ነው፤ ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ የቤተክርስቲያን አስተሳሰቦች ጣራ እንሰራለን፤ በነዚህም አስተሳሰቦች በራሳችንና በመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት መካከል ግድግዳ እናቆማለን። እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን የራሷን የሆነ ሰው ሰራሽ አስተሳሰቦች ታዘጋጅና አባል ሁሉ ይህን መከተል ግዴታው ነው ትላለች። አንድ የቤተክርስቲያን አባል እንኳ ቤተክርስቲያን ካዘጋጀችለት ስርዓትና አስተምሕሮ ውጭ መውጣት አይፈቀድለትም። ይህም ያስከተለው ውጤት የ45,000 ዓይነት የተለያዩ ዲኖሚኔሽኖች እና ቤተክርስቲያኖች መፈጠር ነው።

ቁሳቁስና ገንዘብ በሚያሳድደው ቤተክርስቲያናዊ አመለካከት ጣራ ላይ ቀዳዳ መከፈት አለበት፤ በዚህመ ቀዳዳ በኩል ወደ እግዚአብሔር መመልከትና ፈቃዱን ለመፈጸም እንዲሁም የቃሉን ሚስጥራት ለመረዳት የሚያስፈልገንን እምነት ከእርሱ እንቀበላለን። በሰማይ በዙፋኑ ዙርያ የሚገኙት አንበሳው፣ ጥጃው፣ ሰውየው፣ እና ንስሩ ሥራቸው ቤተክርስቲያን በ2,000 ዓመታት ታሪኳ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንድትሆን ማድረግ ነው።

እነዚህ አራት ሕያዋን ፍጥረታት በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ቤተክርስቲያንን ሲመራት የነበረውን የክርስቶስ መንፈስ ባህርያት ይገልጣሉ።

ሰዎቹ ጣራውን ገንጥለው ሽባውን ሰውዬ ወደ ኢየሱስ ፊት አወረዱት።

ሰማያዊ ከሆነው ከመንፈስ ቅዱስ የሚመጣ ምሪት ሁሉ ትኩቱ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ፊት በማቅረብ ላይ ነው፤ እርሱም ሰዎች ሊሰሙ የሚችሉት የተገለጠው ቃል ነው። 7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት የተጎናጸፉት ስኬት ይህ ነው። ይህም ስኬት የቤተክርስቲያን አባል በቤተክርስቲያን አስተምሕሮ መሞላቱ ሳይሆን ግለሰቦች ወደ ኢየሱስ ፊት ቀርበው በቤተክርስቲያን አስተሳሰቦችና በዓለማዊ ስኬት ምክንያት ሽባ ሆኖ የነበረው እምነታቸው ከክርስቶስ ጋር በግል ወደሚሆን ሕያው ሕብረት መለወጡ ነው።

ወደዚህ ዓይነት ሕብረት ውስጥ የገባ ሰው የዘመን መጨረሻ ላይ የተላከው ነብይ ባስተማረው ትምሕርት መሰረት የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት አንብቦ ለራሱ መረዳት እና በእግሮቹ መቆም የሚችል ሰው ነው።

እነዚህ የተገለጡ ሚስጥራት ወደ አንበሳው ማለትም ወደ ጥንታዊው የሐዋርያት ዘመን ቤተክርስቲያን እምነት ይወስዱናል። በሬው ለመታረድ የተዘጋጀ እንስሳ ነው፤ በጨለማው ዘመን ውስጥ ጥጃው ወደ በሬነት እያደገ በነበረበት ጊዜ ከአስር ሚሊዮን የሚበልጡ ክርስቲያኖች ስለ እምነታቸው ተገድለዋል። ሰውየው የማርቲን ሉተርን ምሑርነት የሚወክል ሲሆን ማርቲን ሉተር ጀርመኒ ውስጥ እግዚአብሔር አእምሮውን ሲያበራለት መዳን በእምነት ብቻ ነው የሚለውን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ አምጥቷል። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር የሰዎችን አእምሮ ሲባርክ ከ1604 – 1769 ዓ.ም ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉሞ ታርሞ ፍጹም ስሕተት የሌለው የእግዚአብሔር ቃል ሆኖ ታትሟል።

እንግሊዝ ውስጥ ጆን ዌስሊ ቅድስና እና የወንጌል ስርጭትን ወደ ቤተክርስቲያን መለሰ፤ ከዚህም የተነሳ ታላቁ የወንጌል ስርጭት ዘመን ተጀመረ። ከአስር ሺ የሚበልጡ ወንጌል ሰባኪዎች ከእንግሊዝ ወጥተው በኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ወንጌልን በዓለም ዙርያ አሰራጭተዋል።

ማርቆስ 2፡5 ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፦ አንተ ልጅ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው።

በዚህ ክፍል ኢየሱስ ዋናውን ነገር ተናገረ።

ዋናው ችግር በሽታ አይደለም። ምድርን ያስጨነቃት ትልቁ ችግር ሐጥያት ነው።

ሐጥያት ወደ ኤድን ገነት ባይገባ ኖሮ በሽታ ምድር ላይ ባልሰለጠነ ነበር። ማንኛውም ሰውን የሚያስጨንቅ ችግር መነሻው ሐጥያት ነው።

ነገር ግን አሁን በድርጊት የምናያቸው ሐጥያቶች ከእነርሱም ይበልጥ ጥልቅ የሆነ ችግር መገለጫዎች ናቸው።

የሐጥያታችን ምንጩ አለማመን ነው።

የምንዋሸው ስለማናምን ነው። አለማመኔ ሲወገድ መዋሸት አቆማለሁ።

ዮሐንስ 16፡9 ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤

በኢየሱስ ማመን አለብን፤ ምክንያቱን እርሱ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ማመን አለብን።

ኢየሱስ አንድን ሽባ ሰው የፈወሰው ኃይሉን ለማሳየት ብቻ ብሎ አይደለም። ይህንን ሰው እንደ ምሳሌ በመጠቀም ኢየሱስን እንደ አዳኝ አድርገው ከመቀበላቸው በፊት ብዙ ሚሊዮን ሰዎች በአለማመናቸው ምክንያት እንዴት ሽባ ሆነው እንደነበት እያሳየ ነው። እነዚህም ሰዎች በቀጣዮቹ 2,000 ዓመታት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን እየተማሩ በማመን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን የሚሆኑ ናቸው።

እያንዳንዱ ሰው በግሉ ወደ ኢየሱስ ካልመጣ በቀር ሕይወቱ ምንም ትርጉም አይኖረውም።

የምንድነው በቤተክርስቲያን አይደለም። በመልካም ሥራ መዳን አንችልም። የምንድነው በግላችን ንሰሃ በመግባት ኢየሱስን ስንቀበለው ብቻ ነው።

ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦

ራዕይ 3፡16 እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።

ሴት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት። ሰባተኛዋ ወይም የመጨረሻዋ ቤተክርስቲያን ፍጻሜዋ በታላቁ መከራ ውስጥ ነው።

እግዚአብሔር የመጨረሻዋን የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ከአፉ እንደሚተፋት ተናግሯል።

ራዕይ 3፡20 እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።

ነገር ግን ድምጹን ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን የሚሰማውን ግለሰብ እግዚአብሔር ከአፉ አይተፋውም።

ማንም የሚለው ቃል ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኝን ግለሰብ ማለት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን መከተል የሚፈልግ ግለሰብ ተስፋ አለው።

63-0630 ሶስተኛው ፍልሰት

… የእግዚአብሔር ድምጽ በቃሉ በኩል ሲጠራቸው በግልጽ ሊሰሙ ይችላሉና … መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን አዳምጡ፣ ዛሬ የሚጠራችሁ የእግዚአብሔር ድምጽ መጽሐፍ ቅዱስ ነው

 

ማርቆስ 2፡6 ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም፦

7 ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው አሰቡ።

8 ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው፦ በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ?

ኢየሱስ የልባቸውን ሃሳብ ያውቃል። ይህን ሲያዩ እርሱ እግዚአብሔር መሆኑን መረዳት ነበረባቸው፤ ምክንያቱም የሰውን የልብ ሃሳብ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

1ኛ ነገሥት 8፡39 በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለውና ስጠው።

 

ማርቆስ 2፡9 ሽባውን፦ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ፦ ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?

በሽታ የሐጥያት ውጤት ነው።

ስለዚህ ኢየሱስ እውነትን በተግባር ገልጦ ሊያስረዳቸው ነው።

ኢየሱስ እግዚአብሔር ከሆነ የሰዎችን ልብ ያውቃል፤ ሐጥያታቸውንም ያስተሰርያል። ስለዚህ በፊቱ በሽታም መቆም አይችልም።

ማርቆስ 2፡10 ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤

ማርቆስ 2፡11 ሽባውን፦ አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው።

ይህ ተግባራዊ ማሳያ ነው። ሐጥያት ይቅር ከተባለ በኋላ በሽታ ለቆ ሄደ። ይህም ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን ያስረዳል።

ማርቆስ 2፡12 ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፥ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና፦ እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ።

 

ማርቆስ 2፡13 ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው።

የባሕር ዳርቻ በባሕር እና በደረቁ ምድር መካከል የሚከፍል መስመር ነው። ባሕር ሰላም የሌላቸውን ያልዳኑ ሕዝቦችን ይወክላል። ምድሩ ደግሞ ዳግም የተወለዱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ የሚፈልጉ ጻድቃን አማኞችን ይወክላል።

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደመሆኑ መጠን ሰላም በሌላቸው ባልዳኑት ሕዝቦች፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚያልፉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ሃሳቦች እንዲሁም ፋሽኖች እና በእውነተኛ አማኞች መካከል የሚከፍል መስመር ነው።

የኢየሱስ ትምሕርቶች በእውነትና በስሕተት መካከል ግልጽ የሆነ መስመር አስምረዋል። የባሕር ዳርቻ ግልጽ የሆነና ምንም የማያሻማ መስመር ነው።

 

ኢየሱስ አስተሳሰቡ ከሕዝቡ ይለይ ነበር

 

ማርቆስ 2፡14 ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና፦ ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው።

ማርቆስ ክርስቶስን እንደ ታላቅ አገልጋይ ነው የገለጠው።

አገልጋዮች የሚሰሩና ግብር የሚከፍሉ ሰዎች ናቸው።

ስለዚህ ማርቆስ እንደ አገልጋይ ግብር መክፈል ስሕተት አለመሆኑን እያሳየ ነው። ግብር የሚከፈልበት ገንዘብ አንዲት ሃገር መንገዶች፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ወደቦች፣ ትምሕርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የፖሊስ አገልግሎትና ጦርሰራዊት፣ ወዘተ. እንዲኖሩዋት ይረዳሉ።

ነገር ግን ግብር ሰብሳቢዎች በሕዝብ ዘንድ የተጠሉ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ በሰዎች ዘንድ የተጠላውን ሰው ኢየሱስ ደቀመዝሙሩ አድርጎ መረጠው።

ማርቆስ 2፡15 በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ ይከተሉትም ነበር።

ኢየሱስ ከሐጥያተኞች ጋር በመብላት ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው የሚቆጥሩ አይሁዶችን አስቆጣቸው።

ማርቆስ 2፡16 ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ፦ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው? አሉ።

ማርቆስ 2፡17 ኢየሱስም ሰምቶ፦ ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።

የወንጌል ሥራ የሚሰራ ሰው መዳን ከሚያስፈልጋቸው ሐጥያተኞች መካከል መገኘት አለበት።

ማርቆስ 2፡18 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጦሙ ነበር። መጥተውም፦ የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጦሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት።

ተቺዎች ማነጻጸርና መተቸት ይወዳሉ። የዮሐንስ ደቀመዛሙርት የሚጾሙትና የኢየሱስ ደቀመዛሙርት የማይጾሙት ለምንድነው?

ኢየሱስ የሙሽራይቱ ቤተክርስቲያን ባል ነኝ በማለት እርሱ ሙሽራው በምድ ሳለ ጾም እንደማያስፈልግ አስረዳቸው። ይህም ምን መደረግ እንዳለበት የሚያውቀው እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው።

ማርቆስ 2፡19 ኢየሱስም አላቸው፦ ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጦሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጦሙ አይችሉም።

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ግን ቤተክርስቲያን በጾም ምሪትን መፈለግ ይጠበቅባታል።

ማርቆስ 2፡20 ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ወራትም ይጦማሉ።

የበዓለ ሃምሳ ዕለት ነገሮች ሁሉ ተለውጠዋል። ነገር ግን ከኢየሱስ ሞት በፊት ደቀመዛሙርቱ ይህን ሁሉ አስቀድመው ሊያውቁ የሚችሉበት መንገድ አልነበረም። ኢየሱስ እንደሚሞት እንኳ አያውቁም ነበር።

ማርቆስ 2፡21 በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።

አሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ጨርቅ ሲሰፋበት አዲሱ ጨርቅ አሮጌውን ልብስ ይቀደዋል። ስለዚህ የበዓለ ሃምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው አዲስ በሆነችዋ ቤተክርስቲያን ላይ ነው። የአይሁዶች አሮጌ ሐይማኖታዊ ጉባኤ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም የአዲስ ኪዳን ትምሕርቶች ከስጋዊ ጉዳዮች ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ነው የሚያተኩሩት።

ማርቆስ 2፡22 በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ።

የሕግ ጠባቂዎች የወንጌሉን የጸጋ መልእክት መረዳት አይችሉም። ከአእምሮዋቸው በላይ ነው።

 

ሰንበት ከሥራ እረፍት ሳይሆን ከሐጥያት እረፍት ሆነ

 

ማርቆስ 2፡23 በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር።

ሰንበት ሰባተኛው ቀን ሲሆን እርሱም መከር የሚሰበሰብበትን ሰባተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን ይወክላል። መከር የሚሆነው ከሰብሉ ላይ ፍሬው ታጭዶ በሚወሰድበት ገዜ ነው። ይህም ሙሽራይቱ ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ወደ ሰማይ የምትነጠቅበት ጊዜ ነው።

ማርቆስ 2፡24 ፈሪሳውያንም፦ እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ? አሉት።

አይሁዶች ለቁርስ ጥቂት እሸት መቅጠፍን የአንድ ቀን ሥራ አድርገው ሊቆጥሩ ፈለጉ።

ሥራ ምንድነው፣ ሥራ ምን አይደለም በሚል ርዕስ ማለቂያ የሌለው ክርክር ያደርጋሉ።

ማርቆስ 2፡25 እርሱም፦ ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥

ዳዊት ሕጉን ተላለፈ። የራበው ጊዜ ቤተመቅደስ ውስጥ ገብቶ ለካሕናት ብቻ የተፈቀደውን የመስዋእት እንጀራ በላ። ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎችም አብረውት በሉ። ዳዊት ይህን አድርጎ ያልተቀጣው እንዴት ነው?

ማርቆስ 2፡26 ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው።

ጠለቅ ብለው ማስተዋል ያስፈልጋቸዋል።

ኢየሱስ የዳዊት ልጅ ነው። ስለዚህ ዳዊት የኢየሱስን አገልግሎ በራሱ ሕይወት ገልጦታል። ግዙፉን ጎልያድ መግደል የቻለው ዳዊት ብቻ ነበር። ዳዊት 5 ጠጠሮች ከወንዝ ለቅሞ ወሰደ። ይህም በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን እግዚአብሔርን እና በዙፋኑ ዙርያ የሚገኙትን አራት ሕያዋን ፍጥረታት ይወክላል።

ዳዊት አንድ ጠጠር አነጣጥሮ በግዙፉ የጎልያድ ግምባር ላይ ወረወረ። ይህም አንድን የቤተክርስቲያን ግዙፍ የስነ መለኮት ምሑር አንድ ጥያቄ እንደ መጠየቅ ነው።

“የአብ፣ የወልድ፣ እና የመንፈስ ቅዱስ ስም ማነው?” ለዚህ ጥያቄ መልስ የላቸውም። ስላሴያዊው አምላክ አንድ ስም የለውም። የማንኛውም ሰው ግምባር ማለትም አንጎሉ ያለበት ሥፍራ መልስ ማግኘት አይችልም። ይህ ጥየቄ ቤተክርስቲያኖች ላይ እንደ ግዙፉ ጎልያድ ሆኖ ይገዛቸው የነበረውን የስላሴ አስተምሕሮ ይገድለዋል።

ዳዊት የአይሁድን ሰራዊት ሊያሸንፉት ከማይችሉት ከጎልያድ ታደጋቸው።

ኢየሱስ በቀራንዮ መስቀል በተሰቀለ ጊዜ ሞት የተባለውን ግዙፉን ጠላታችንን ገጠመውና ስለ ሐጥያታችን በመሞት መውጊያውን ነቀለው። የሞት መውጊያ ሐጥያት ነው ምክንያቱም ስንሞት ለሐጥያታችን ዋጋ እንከፍላለን። ኢየሱስ ስለ ሐጥያታችን ዋጋ ከፍሏል። ስለዚህ ከአሁን በኋላ ሞት እኛን ሊያጠፋን አይችልም።

ዳዊት የኢየሱስን ሕይወት በከፊል ኖሮታል።

ዳዊት ንጉስ እንዲሆን ተቀብቶ ነበር፤ ነገር ግን ጠላቱ ሳኦል እስኪሞት ድረስ ሊነግስ አልቻለም።

ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ ንጉስ እንዲሆን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ነበር። ነገር ግን ጠላቱ ማለትም የመጨረሻው ፖፕ በአርማጌዶን ጦርነት ውስጥ እስኪሞት ድረስ ኢየሱስ በ1,000 ዓመት መንግስት ውስጥ መንገስ አይችልም።

እስከ ጊዜው ድረስ ኢየሱስ በመልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካሕናት ሆኖ እያገለገለ ይቆያል።

ዳዊት ንጉስ እንዲሆን ከተቀባ በኋላ ዙፋን ላይ ከመቀመጡ በፊት ለካሕናቱ ብቻ የተፈቀደውን እንጀራ በመብላት እንደ ካሕን እንዲያገለግል ተፈቅዶለት ነበር። ዳዊት ይህን ያደረገው በራሱ ሕይወት የክርስቶስን አገልግሎት በከፊል ማሳየት ስለነበረበት ነው።

ማርቆስ 2፡27 ደግሞ፦ ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤

ሰንበት ምን መስራት እንደማንችል የሚከለክለን የሕግ ዓይነት አይደለም።

ከሐጥያት እና ከአለማመን የምናገኘው እረፍት የሐጥያት ሥራችንን እየሰራን መቀጠል አንችልም ማለት ነው።

ይህን እረፍት ልናገኝ የምንችለው ኢየሱስ ወደ ውስጣችን ሲገባ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ሐጥያት የመስራት ፍላጎት የሚለቀን የዛኔ ብቻ ነው።

ማርቆስ 2፡28 እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።

ኢየሱስ የእውነተኛው ሰንበት ጌታ ነው፤ ምክንያቱም በውስጣችን ያደረው የኢየሱስ መንፈስ ነው ከሐጥያታችን የሚያሳርፈን። ከሐጥያት እና ከጭንቀት እውነተኛውን እረፍት የሚሰጠን በውስጣችን የሚኖረው የክርስቶስ መንፈስ ነው።

 

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23