ዘፍጥረት 1 - አዳም ሊወድቅ የማይችል መንፈስ ነው



እግዚአብሔር መናፍስትን ለዘላለም እንዲኖሩ ነው የፈጠራቸው። የፍራፍሬ ዛፎቹ በሙሉ መልካም ነበሩ። ከመጀመሪያው ስለ ሐጥያት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ አልነበረም።

First published on the 22nd of October 2022 — Last updated on the 22nd of October 2022

ሳይንቲስቶች ስለ ዓለማችን ብዙም አያውቁም

 

 

ገሃዱ ዓለም በጣም የተወሳሰበ ነው።

አፖሎ 11 የተባለችዋ መንኩራኩር ከጨረቃ ስትመለስ ያመጣችው የጨረቃ ድንጋይና የጨረቃ አቧራ ብዙ ነገሮችን አወሳስቧል።

ላቦራቶሪ ውስጥ የተደረጉ ሙከራዎች እንዳሳዩት አንዳንዱ የጨረቃ ድንጋይ በዕድሜ ከመሬት ይበልጣል።

ስለዚህ ጨረቃ ከመሬት በዕድሜ ትበልጣለች። ይህም እንዴት ሊሆን እንደቻለ ሳይንስ ማብራራት አይችልም።

ደግሞ ከዚህም የባሰ አለ። አንዳንዱ የጨረቃ አቧራ ዕድሜው ከጨረቃ ድንጋይ በቢሊዮን ዓመታት ይበልጣል።

ድንጋዮች ተሰባብረው ነው አቧራ የሚሆኑት። ስለዚህ ድንጋዮች ከአቧራው በዕድሜ መብለጥ ነበረባቸው።

ጨረቃ ላይ እውነታው ግን በተቃራኒ ነው። ሳይንስ በዚህ ግራ ተጋብቷል፤ ስለዚህ መልስ የለውም።

ከዓለማችን 95 በመቶ የሚሆነው የተሰራው ከዳርክ ኤነርጂ እና ከዳርክ ማተር ነው።

“ዳርክ” የሚለው ቃል ስለ ጉዳዩ ምንም እውቀት የለንም ለማለት የሚያገለግል ለዘብ ያለ አነጋገር ነው።

የቢግ ባንግ ቲዎሪም ቢሆን ስለ ዳርክ ኤነርጂ እና ስለ ዳርክ ማተር ምንም አያብራራም። ስለዚህ የቢግ ባንግ ቲዎሪ ስለ ዓለማችን 95 በመቶ ማብራራት አይችልም። እና የቢግ ባንግ ቲዎሪ ጥቅሙ ምንድነው? ብዙም አይደለም።

በተጨማሪ በጨጓራችንና በአንጀታችን ውስጥ ያለው ከ45 – 50 በመቶ የሚሆነው የዘረመል ወይም ጄኔቲክ መረጃ ከምንም ነገር ጋር ከእጽዋት፣ ከእንስሳት፣ ከፈንገስ፣ ከቫይረስ፣ ከባክቴሪያ ጋር አይመሳሰልም። ይህንንም ሳይንቲስቶች ባዮሎጂካል ዳርክ ማተር ይሉታል።

ስለዚህ ብዙ ያልገባን ነገር አለ ማለት ነው።

1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡20 ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤

21 ይህ እውቀት አለን ብለው፥ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና። ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን።

የሳይንስ ቲዎሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወሙ ከሆነ እውነተኛ ሳይንስ ሳይሆኑ ከንቱ ቀባጣሪዎች ናቸው።

ሳይንስ የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት መካድ ይፈልጋል፤ ነገር ግን ሳይንስ የተፈጥሮን እውነታዎች መግለጥ አልቻለም።

ሳይንስ ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን እየካዱ ዘመናቸውንና ዘላለማቸውን ያለ ምንም ዓላማ እንዲንከራተቱ፣ ተጨባጭ ተስፋ እንዳይኖራቸው አድርጓል።

 

ሰዎች ብዙ ሐጥያቶችን ይፈጽማሉ

 

 

ዛሬ ዓለም ያለባት ችግር ምንድነው?

ምድራችን በውስጧ የሚገኘው ሃብት ውስን ነው፤ ይህንንም ውስን ሃብቷን ለመጠቀም የሚሻሙ ሰዎች በዝተውባታል።

ውስን የሆነው የምድር ሃብት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እየተከፋፈለ አይደለም፤ ሃብታሞች በስግብግብነታቸው አብዝተው እየወሰዱ ደግሞም ብዙ እያባከኑ ናቸው። ምንም ጥቅም የሌላቸው ብዙ ምርቶችን ለማምረትና ብዙ የጦር መሳሪያዎችን ለማምረት ብለን አካባቢያችንን እንበክለዋለን እንመርዘዋለን። የዓለማችን ትልቁ ንግድ የጦር መሳሪያ፣ ጥይት፣ ወንጀል፣ አደንዛዥ ዕጽ፣ መጠጥ እና ሲጋራ ናቸው። ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር፣ ስግብግብነት፣ እና የብቃት ማነስ በዓለማችን ላይ ድህነት፣ ኢፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል እና የተፈጥሮ ግብዓቶች ብክነት እንዲፈጠር ያደርጋል።

ከዓለማችን ሕዝብ ግማሹ የውሸት በሚያብረቀርቁ ከተሞቻችን ውስጥ ነው የሚኖረው። የሚያሳፍረው ነገር በነዚህም ከተሞች ውስጥ ከትላልቆቹ ሕንጻዎች ጋር የቆሻሻ መጣያ የሚመስሉ የላስቲክ ቤቶችና የድሆች መኖሪያዎች አብረው ይገኛሉ።

ለብዙዎች ይህ ዓይነቱ ሕይወት አዲሱ ባቢሎን ነው፤ ሰዎች ከዋነኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተገልለው ግማሽ ሕይወት እና ግማሽ ሞት ውስጥ ይኖራሉ። እነዚህ የላስቲክ ከተሞች ትርፍ ለሆነው የሰው ቁጥር ማራገፊያዎች ናቸው። ከሶርያ እንዳየነው ከስደተኞች እንኳ መቀበል የሚቻለው የተወሰኑትን ብቻ ነው። የስደተኛ መጠለያዎችም በቀላሉ የላስቲክ ከተሞች ወደመሆን ይለወጣሉ። የአፍሪካ የላስቲክ ከተሞች ከትክክለኛ ከተሞቿ በሁለት እጥፍ እያደጉ ናቸው። የላስቲክ መንደሮች ውስጥ ለሚኖሩ ለብዙዎቹ ሰዎች ከተሞች መተዳደሪያ የሞሆን ስራ ሊሰጡዋቸው አይችሉም።

በአሰራራቸው ብልሹ የሆኑ ባለ ስልጣኖች ገንዘብ ከድሆች ወደ ሃብታሞች እንዲሸጋገር ስለሚያደርጉ በሃብታም እና በድሃ መካከል ያለው ክፍተት ሁልጊዜ እየሰፋ ነው የሚሄደው። በ2008 ዓ.ም የተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ በ1029 ከተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ወዲህ ታላቅ የኢኮኖሚ ቀውስ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ወቅት መንግስት የግብር ከፋዮችን ገንዘብ እያወጣ ለሃብታሞች መልሶ መቋቋሚያ እያደለ ነበር። መንግስት ሃብታም ሰዎች በገንዘብ አያያዛቸው ብኩን እንደነበሩ እያወቀ እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ አድርጎላቸዋል።

በዚሁ ወቅት ከልክ በላይ ያሻቀበው የቤቶች መግዣ ዋጋ አዳዲስ ሙሽሮች በከባድ እዳ እንዲዘፈቁ አድርጓል።

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦቻችን ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ የኑሮ ሁኔታዎች ውስጥ ራሳቸውን ችለው ለመቆም ይፍጨረጨራሉ። ለእነርሱ ሕይወት ብዙም አስደሳች አይደለችም።

 

በወሲባዊ ግንኙነት መዋለድ ዓለማችን በሕዝብ ብዛት እንድትጨናነቅ እያደረገ ነው

 

 

በምድር ላይ ሕዝብ መብዛቱ ብዙዎቹ ሰዎች በስቃይና በችግር እንዲኖሩ ዳርጎዋቸዋል።

የዓለም ሕዝብ ቁጥር ከ1960 እስከ 2000 ዓ.ም በ40 ዓመታት ውስጥ ከ 3ቢሊዮን በእጥፍ ወደ 6ቢሊዮን አድጓል። ይህ ዓይነቱ የሕዝብ ቁጥር እድገት ወደፊት ሊቀጥል አይችልም። በ2020 ዓ.ም የዓለም ሕዝብ ቁጥር 7.8 ቢሊዮን ደርሷል።

ይህ ወሲባዊ ግንኙነት የፈጠረብን የሕዝብ ቁጥር ቦምብ ነው። ምድር የአሁኑን የሕዝብ ብዛት መሸከም አልቻለችም። ሁሉም ሰው ተመችቶት ይኑር ብለን ካሰብን በዚህ የሕዝብ ብዛት የሚቻል አይደለም፤ ደግሞም ለወደፊቱ አያዛልቅም። በአሁኑ ሰዓት ከዓለም ሕዝብ 20 በመቶ የሚሆነው ሥራ አጥ ነው ወይም ከሚገባው በታች እየተከፈለው ነው የሚሰራው፤ ስለዚህ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ይኖራል። ለዚህ ሁሉ መንስኤው “የነጮቹ በሽታ” የሚሉት የገንዘብ ፍቅር ነው።

ክርስቲያኖች የሚያመልኩት እግዚአብሔር እውነተኛው ፈጣሪ ከሆነ በወሲባዊ ግንኙነት አማካኝነት መዋለድ የሚያዋጣ አይደለም፤ ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት ከዓለም ሕዝብ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት በእርሱ አያምኑም።

ከወሲብ ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮችንም አስቡ፡- ዝሙት፣ በሐጥያት መኖር፣ የወጣት ሴቶች እርግዝና፣ ኤድስ፣ የአባለዘር በሽታዎች፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ ሳይታሰቡ የተወለዱ ልጆች፣ ፍቺ፣ ወላጅ አልባ ልጆች፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን።

በሰዶም ዘመን እንደነበረው የግብረ ሰዶማዊነት መስፋፋት።

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ በእርግዝና ወቅት የሚመጣ ሕመም፣ ጠዋት ጠዋት ማቅለሽለሽ፣ ከመውለድ ጋር የተያያዙ ሕመሞች፣ እንዲሁም ብዙ አደጋዎች።

በአወንታዊ ጎኑ ስናየው ወሲብ በባል እና በሚስት መካከል የሚያስደስት ድርጊት ነው። ልጅ የመውለድ ሕመም ካለፈ በኋላ በተወለደው ሕጻን ምክንያት የሚገኝ ደስታ አለ።

ስለዚህ ወሲብ የመልካም እና ክፉ እውቀት ዛፍ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው።

በሰው ሕይወት ውስጥ ከሚያልፉ ልምምዶች ሁሉ ልዩ ቦታ ያለው ሲሆን መልካምም ክፉም ገጽታዎች አሉት።

ወሲብ በትዳር ውስጥ መልካም ነው፤ ከትዳር ውጭ ግን ክፉ ነው።

ስለ መዋለድ የምናውቀው ብቸኛ መንገድ ነው ነገር ግን መጨረሻው ብዙ አስከፊ ውጤትን ሊያስከትል የሚችል ከልክ በላይ የሆነ የሕዝብ መባዛት ነው። ስለዚህ ብዙም የሚያዛልቅ አማራጭ አይደለም።

 

ወሲብ ዘላለማዊ ሕይወትን ሊያመጣ አይችልም

 

 

ወሲብን በመልካምም ሆነ በክፉ መንገድ ቢጠቀሙበት አንድ የማይለወጥ ነገር አለ፤ እርሱም ወላጆች ዘላለማዊ ሕይወት ቢኖራቸውም እንኳ ዘላለማዊ ሕይወታቸውን ወደ ልጆቻቸው ማስተላለፍ አይችሉም።

በእርግጥ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ከዚህ የተሻለ እቅድ ነበረው።

ዘፍጥረት 1፡12 ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

ፍሬያማ ዛፍ ለምሳሌ አፕል በዛፉ ፍሬ ውስጥ ያለውን ሕይወት የሚሸከም ዘር ያፈራል።

 

 

እያንዳንዱ ዘር የራሱን አካል ያፈራል።

1ኛ ቆሮንቶስ 15፡38 እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል።

ይህ በእግዚአብሔር የመጀመሪያ እቅድ ውስጥ ልዩ የሆነ ቦታ ያለው ሃሳቡ ነው።

እኛ ያልገባን ነገር ስጋ የለበሱ እንስሳት ሁሉ በወሲባዊ ግንኙነት እየተባዙ እንዴት ምድርን ሊያጨናንቁ እንደማይችሉ ነው።

ዘፍጥረት 1፡21 እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

ዘፍጥረት 1፡22 እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው፦ ብዙ፥ ተባዙም፥ የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።

 

እንስሳት የራሳቸው ነጻ ፈቃድ የላቸውም።

እንስሳት ሲፈጠሩ በውስጣቸው በነበረው ደመነፍስ እየተመሩ ነው የሚኖሩት። ለምሳሌ እያንዳንዱ የሸረሪት ዝርያ የሚሰራው የሚገርም የሸረሪት ድር ዓይነት አለ፤ ነገር ግን ሌላ ዓይነት ድር መስራት አይችልም። እንስሳት የሚራቡት በወሲባዊ ግንኙነት ነው፤ ይህም የእንስቷ የወሲብ ፍላጎት በየዓመቱ የሚነሳሳበት ወቅት አለ፤ ያ ወቅት ሲያልፍ ፍላጎቷ ተመልሶ ይጠፋል። በምድር ላይ በቂ የእንስሳት ቁጥር ከተባዛ በኋላ እግዚአብሔር የሁሉንም እንስሳት ወሲባዊ ፍላጎት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያጠፋል፤ ከዚያ በኋላ ስለማይዋለዱ ምድር አትጨናነቅም።

ዘፍጥረት 1፡21 እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

 

ዓሳዎች እና ወፎች ልዩ ፍጠረታት ናቸው። አካላቸው የምድር አፈር ውስጥ በሚገኙ ንጥረ ነገሮች ነው የተሰራው። ባሕር ውስጥ ለሚኖሩ ፍጥረቶች ግን እግዚአብሔር በውሃ ግፊት ውስጥ መኖር የሚችል ለየት ያለ የሕይወት መንፈስ አዘጋጅቶላቸዋል። አካላቸው ከምድር አፈር ንጥረ ነገሮች የተሰራ ቢሆንም ከምድር አፈር በተለየ መኖሪያ ውስጥ መኖር እንዲችል ተደርጎ ነው የተሰራው።

የዮሐንስ ራዕይ ውስጥ ሰባት ራስ ያለው አውሬ ከባሕር ውስጥ እንደሚነሳ ተጽፏል፤ ይህንንም ስንረዳው የገንዘብ፣ የፖለቲካዊ ሙስና፣ እና ዲኖሚኔሽናዊ ጫናዎች ሁሉ በአንድነት የሚሰሩበት ዓለም እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱ ስፍራ ለክፉ መናፍስት ምቹ የሆነ መራቢያ ቦታ ነው። ይሁዳን ጠይቁት። እግዚአብሔርንና ገንዘብን ማገልገል አንችልም።

ወፎችንም ደግሞ እግዚአብሔር ከምድር በላይ ከፍ ብሎ ባለው አየር ውስጥ ዝቅተኛ ግፊትና ዝቅተኛ የኦክስጅን ክምችት ባለበት ስፍራ መኖር እንዲችሉ አድርጎ ነው የፈጠራቸው።

ዘፍጥረት 1፡25 እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥

የምድር አራዊት አካል የተሰራው ከሚኖሩበት ምድር ውስጥ በተገኙ ንጥረ ነገሮች ነው።

የእንስሳትን ሕይወት እግዚአብሔር እንዲሁ ነው የፈጠረው። እነዚህ ሁሉ ፍጥረታት አንጎላቸው ውስጥ በደመ ነፍስ እየተመሩ የመኖር ዝንባሌ ተሰጥቷቸው ነው የተፈጠሩት፤ ስለዚህ አኗኗራቸው አስቀድሞ ሲፈጠሩ በተወሰነላቸው መንገድ ብቻ ነው። በደመ ነፍሳቸው ከመኖር በቀር ሌላ አማራጭ የላቸውም።

ሰውን ግን እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ነው የፈጠረው።

 

እግዚአብሔር ሰውን በደምብ አስቦ ነው የፈጠው

 

 

ዘፍጥረት 1፡26 እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤

እግዚአብሔር ሰውን እንዲሁ ዝም ብሎ አልፈጠረውም። እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር በቁም ነገር አስቦ መፍጠሩ ለሰው ልዩ ክብርን አጎናጽፎታል። ሰው እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጡራን ሁሉ ከፍተኛው ፍጡር ስለሆነ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯል። የእግዚአብሔርም የመጨረሻ ሃሳቡ በሰው ውስጥ መኖር ነው። ሰይጣን እንስሳትም ውስጥ ቢሆን ቢኖር ደስ ይለዋል፤ ለምሳሌ በገደራ የነበሩ አሳማዎች ውስጥ፤ እግዚአብሔር ግን መኖር የሚፈልገው ሰው ውስጥ ብቻ ነው።

ዮሐንስ 4፡24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው።

ስለዚህ የእግዚአብሔር አምሳል ታናሽ መንፈስ ነው።

ይህም የተፈጠረው ከምንም ነው፤ ምክንያቱም መንፈስ ከምድር አፈር ሊፈጠር አይችልም።

መንፈስ ሆኖ የተፈጠረው ሰው እግዚአብሔርን ይመስላል፤ ስለዚህ ሰው ሲፈጠር ነጻ ፈቃድ ነበረው። እግዚአብሔር ሰው ለእርሱ በግዳጅ እንዲታዘዝ አልፈለገም። እግዚአብሔር ሰው በራሱ ነጻ ፍላጎትና ፈቃድ እግዚአብሔር እንዲያገለግል ነው የፈለገው።

ስለዚህ ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ውስጥ እግዚአብሔር በዓይን የማይታይ መንፈስ የሆነ ሰውን ፈጠረ። ሰውን ከምድር አፈር አልፈጠረውም። ስለዚህ አሁን እየተነጋገርን ያለነው ከምድር አፈር ስለተበጀው ስጋ ስለለበሰው ሰው አይደለም። እንስሳት ሁሉ ስጋ ለብሰው ነው የተፈጠሩት። ስለዚህ እንስሳት በወሲባዊ ግንኙነት እንዲዋለዱ ተወስኖላቸዋል።

እግዚአብሔር ግን ለሰው ነጻ ፈቃድ ለመስጠትና ምድርን በሕዝብ ብዛት ከመጨናነቅ ለመከላከል ስለ ሰዎች መባዛት የተለየ ሃሳብ ነበረው። ሰዎች ነጻ ፈቃድ ቢኖራቸውና የፈለጉትን ያህል ብዙ ልጆች ቢወልዱ፤ ይህም ደግሞ ለዘላለም ቢቀጥል ብላችሁ አስቡ። እንደ ምድር ባለች ውስን ፕላኔት ላይ የሕዝቡ ያለልክ መብዛት ኑሮን ከባድ ያደርገው ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ደግሞ በእንስሳት ውስጥ እንደሚያደርገው በሰዎች ውስጥ ያለውን የወሲብ ፍላጎት ቢያጠፋው ሰዎች ነጻ ፈቃድ አይኖራቸውም።

ስለዚህ ከእንስሳት በተለየ እግዚአብሔር ለሰዎች ነጻ ፈቃድ የሚሰጥ ከሆነ ሰውን በተለያዩ አማራጮች መካከል መምረጥ የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ማኖር አለበት። ሰው የሚያማርጥባቸው የተሳሳቱ አማራጮች ከሌሉት ሰው የመምረጥ ነጻ ፈቃድ አይኖረውም ማለት ነው። ነጻ ፈቃድን ለመምረጥ እግዚአብሔር ለሰው አጓጊ የሆነ ሌላ አማራጭ ማቅረብ ነበረበት፤ ከዚያም ሰው እግዚአብሔርን ከልቡ ስለሚወድ ትክክለኛ ወዳልሆነው አማራጭ አይሄድም ብሎ ተስፋ ማድረግ ነው።

 

አንድ ሰው እና አንዲት ሴት በሰማይ የሚኖሩ የ3 ሰዎች አምሳል ሊሆኑ አይችሉም

 

 

እግዚአብሔር በመጀመሪያ የፈጠረውን መንፈሳዊ ሰው እንመልከት።

ዘፍጥረት 1፡26 እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።

“እንፍጠር” የሚለውን በብዙ ቁጥር የተጻፈውን ግስ ብዙ ሰዎች ሶስት አካላት ያሉበትን ስላሴ ለማመልከት ነው ይላሉ፡ እነርሱም አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ። ነገር ግን ከነዚህ ከሶሱቱ አንዱም እንኳ ሴት አይደለም።

ስለዚህ እግዚአብሔር በምድር ላይ ሁለት ወንድ እና ሴት ሲፈጥር ችግር ይፈጠራል።

ዘፍጥረት 1፡27 እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።

በምድር ላይ ሁለት ሰዎች ከእነርሱም አንዷ ሴት ስትሆን በሰማያት የሚኖሩ የሶስት ሰዎች አምሳል ሊሆኑ አይችሉም፤ ደግሞ ከሶሱቱ አንዳቸውም እንኳ ሴት አይደሉም።

 

 

ይህ ምስል ስሕተት እንዳለበት ግልጽ ነው። ለምን? ምክንያቱም በሰማይ የሚኖሩ ሶስት መንፈሶችንና በምድር ስጋ ለብሰው የሚኖሩ ሁለት ሰዎችን ያሳያል።

የሰው ስጋ የእግዚአብሔር አምሳል አይደለም።

የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ አምሳል ነው።

ዘፍጥረት ምዕራፍ 1ን ከመንፈስ አንጻር ብቻ እንመልከተው።

“እንፍጠር” የሚለው ቃል ከስጋ አንጻር ስንመለከተው ከአንድ ሰው በላይ የሆነ ቁጥርን ያመለክታል።

እየተነጋገርን ያለነው ግን ስለ መንፈስ ነው። የሰው መንፈስ ውስብስብ ፍጥረት ነው።

አንድ ሰው ከራሱ ሕሊና ጋር መከራከር ይችላል፤ ነገር ግን መከራከር መቻሉ ሁለት ሰው አያደርገውም።

ነህምያ 5፡7 በልቤም አሰብሁ፥

ነህምያ ከሌላ ሰው ጋር እየተማከረ አልነበረም። ዳዊትም ከሌላ ሰው ጋር እየተጫወተ አልነበረም።

መዝሙር 77፡6 … ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ …

ሳይንቲስቶች ሁላችንም ለብዙ ሰዓት ከራሳችን ጋር እንደምናወራ አረጋግጠዋል፤ ይህም የተጠላለፉ ሃሳቦቻችንን አጥርተን መመልከት እንድንችል ይረዳናል።

ዘፍጥረት ውስጥ ያለው አነጋገር በተጨማሪ ደግሞ ነገስታት “እኛ” እያሉ የሚናገሩበት ዓይነት ነው።

ነገስታት፣ ጳጳሳት “እኔ” ብለው በመናገር ፈንታ ብዙውን ጊዜ “እኛ” እያሉ ነው የሚናገሩት።

“እኛ” የሚለው ቃል የስልጣንና የግርማዊነታቸውን ሙላት ይገልጣል፤ “እኔ” ብለው ቢናገሩ የስልጣናቸውን ታላቅነት አይገልጽም።

ለንጉስ አርጤክስስ በግሉ ደብዳቤ ተጻፈለት። “ለንጉሡ” የሚለው ነጠላ ቃል ደብዳቤው የተጻፈው ለንጉሡ እና ለአማካሪዎቹ አለመሆኑን ያመለክታል። ደብዳቤው የተጻፈው ለንጉሡ ብቻ ነው።

ዕዝራ 4፡11 ለንጉሡ ለአርጤክስስ የላኩት የደብዳቤ ግልባጭ ይህ ነው፦

የንጉሡን መልስ ልብ በሉ።

ዕዝራ 4፡18 ሰላም አሁንም ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነበበ።

“በፊቴ” የሚለው ቃል ንጉሡ አንድ ግለሰብ መሆኑን ይጠቁማል። “እኛ” የሚለው ቃል ደግሞ ነገስታት ስለ ራሳቸው ሲናገሩ የሚጠቀሙት ክብራቸውንና ስልጣናቸውን የሚገልጽ አነጋገር ነው።

 

የእግዚአብሔር ልጆች ሰዎች እንጂ መላእክት አይደሉም

 

 

እግዚአብሔር የትኛውንም መልአክ ልጄ ነህ ብሎ አያውቅም።

ዕብራውያን 1፡5 ከመላእክትስ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው?

የእግዚአብሔር ልጆች ማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው።

ሮሜ 8፡14 በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።

እግዚአብሔር ለፈጠረው ዓለም ሁሉ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ስለ ራሱ “እኛ” ብሎ መናገር ይገባዋል፤ ከዚያም በላይ ማለት ይገባዋል።

 

 

ዘፍጥረት 1፡27 እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።

የእግዚአብሔር መንፈስ የራሱን ወሰን የሌለው መንፈስ እንዲመስል አድርጎ የሰውን መንፈስ ፈጠረ።

ሰውን ሰው ያደረጉ ባህርያት የተገኙት ከየት ነው?

ኢዮብ 38፡4 ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ?

ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር።

ኢዮብ 38፡7 … የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥

ምድር በተፈጠረች ጊዜ የሰው ልጆች በሙሉ ነበሩ።

ይህ ሊሆን የሚችለው በመጀመሪያ በእግዚአብሔር አእምሮ ውስጥ የነበርን ከሆነ ነው።

አእምሮ ማለት አንጎላችን ወይም ጭንቅላታችንን የሚጠቀም መንፈስ ነው።

አዳም በመጀመሪያ በስጋ አካል ውስጥ መኖር ከመጀመሩ በፊት አእምሮው ንጹህ መንፈስ ነበረ።

ስለዚህ የሰዎች ባህርያት በእግዚአብሔር አእምሮ ውስጥ ነበረ፤ ከዚያ በኋላ ነው ተነጥለው በስጋዊ አካል ውስጥ መኖር የጀመሩት።

በተመሳሳይ መንገድ ከአዳም የምትገኘዋ ሴትም ከመፈጠሯ በፊት ባህሪዎቿ የአዳም አእምሮ ውስጥ ሆነው ለብቻ በስጋዊ አካል ውስጥ እስክትኖር ድረስ እየጠበቀች ነበር። ሴቲቱ በአዳም አእምሮ ውስጥ ስለነበረችበት ጊዜ ምንም አታስታውስም። ዓለም ሲፈጠር በእግዚአብሔር አእምሮ ውስጥ ስለነበርንበት ጊዜ ምንም አናስታውስም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ሆነን ወደፊት እንድንኖርበት የተዘጋጀልንን መኖሪያ አይተን ተደሰትን። አባታችሁ ወጣት ሳለ በእርሱ ውስጥ የነበራችሁበትን ጊዜ አታውቁትም ነገር ግን በውስጡ እስፐርም ሴል ነበራችሁ። ከዚያም እናታችሁ የራሳችሁ የሆነ አካል በማሕጸኗ ውስጥ እስክታበጅላችሁ ድረስ ስትጠባበቁ ነበር።

 

 

በዚህ ጊዜ አዳም በውስጡ የሴት ባህርያትን ጨምሮ የያዘ ወንድ መንፈስ ነበረ። በውስጡ የነበረችዋ የሴት ባህርይ ይደረግ ስለነበረው ነገር ምንም አታውቅም። በዚህ ጊዜ ነበረ እግዚአብሔር ሰዎች መባዛት እንዳለባቸው የተናገረው። ነገር ግን ይህን የተናገረው ስለ መንፈሳዊ መባዛት ነው ምክንያቱም በዚያ ሰዓት የሰው ስጋ ገና አልተፈጠረም።

ስለዚህ እግዚአብሔር የሰዎችን መባዛት ከወሲባዊ ግንኙነት ጋር አያይዞ አልነበረም ያሰበው።

 

ፍሬያማ ማለት በውስጡ ዘር ያለው ፍሬ ወይም ሕጻን ነው

 

 

ዘፍጥረት 1፡28 እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።

 

እግዚአብሔር መንፈስ የነበረውን ሰው በሚያናግርበት ጊዜ ይህ ሰው እንዴት ባለ መንገድ እንዲባዛ ነበር ያሰበለት? ፍንጩን የምናገኘው “ተባዙ” በሚለው ቃል መንፈሳዊ ትርጉም ውስጥ ነው።

ዘፍጥረት 1፡12 … ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

 

ይህ ምን ማለት ነው?

ኤልሳቤጥ ነፍሰጡር የነበረችዋን ማርያም አናገረቻት።

ሉቃስ 1፡42 በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው

 

የማሕጸን ፍሬ ሕጻን ልጅ ነው።

ሉቃስ 8፡11 ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው

 

ይህም የሚገልጸው እግዚአብሔር ሴቲቱ እንድትወልድ የፈለገውን በድንግልና የሚወለደውን ሕጻን ነው።

እግዚአብሔር አዳምና ሚስቱ በድንግልና የሚወለደውንና በውስጡ የእግዚአብሔር ቃል ሙላት የሚኖረውን ሕጻን ልጅ እንዲወልድ ፈለገ።

ይህም ሕጻን የዘላለም ሕይወት ዘር ይሆናል።

ይህ ሕጻን አድጎ ትልቅ ሰው ሲሆን ነጻ ፈቃድ ያለው በሙሉ ልቡ እግዚአብሔርን መታዘዝና የሚወድና ሐጥያት የማይሰራ ሰው ይሆናል። በዚህ መንገድ ሞት ወደ ኤድን ገነት ሳይገባ ይቀር ነበር።

ይህም ሰው ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ቅዱሳኑን በሙሉ ከምድር አፈር ይጠራቸውና ምድርን ለመሙላት የሚበቃ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከፈጠረ በኋላ በራሱ ውስጥ ካለው ቅዱስ መንፈስ እያካፈለ በእያንዳንዳቸው ውስጥ እፍ ይልባቸዋል። ከዚያ ወዲያ ሰዎችን መፍጠር ያቆማል።

የሰዎችም መንፈሳዊ መባዛት ያበቃል።

ሲኦል ገብተው የሚቃጠሉ ክፉ ሰዎችም አይፈጠሩም።

ወሲብ ሳይጀመር ይቀር ነበር። ሞትም አይታወቅም ነበር።

ሊሞቱ የሚችሉት በወሲባዊ ግንኙነት አማካኝነት የሚራቡ ፍጡራን ብቻ ናቸው።

መንፈስ የነበረው ሰው አዳም ይህንን ልጅ ሊወልድ እንደማይችል ተረድቷል፤ ስለዚህ ማድረግ እግዚአብሔር በራሱ መንገድ ይህ ልጅ እንዲወለድ እስኪያደርግ ደረስ መጠበቅ ነበር።

የሰው የመጀመሪያ ፈተናው ይህ ነበር። ከሰው ይጠበቅ የነበረው ነገር እግዚአብሔር ቃሉን እስኪፈጽም ድረስ ለመጠበቅ በቂ ትዕግስት ማሳየት ነው።

እግዚአብሔር የተለያዩ ተክሎችን ፈጠረና በውስጣቸው የእጽዋት ሕይወት አኖረ፤ እንስሳትን ፈጠረና በውስጣቸው የእንስሳ ሕይወት አኖረ። እንስሳትና እጽዋት ሐጥያት ሊሰሩ አይችሉም፤ ስለዚህ እንስሳትና እጽዋት የሚሞቱበት ምክንያት አልነበረም። ነገር ግን እንስሳትና እጽዋት አኗኗራቸው በተፈጥሮዋቸው ውስጥ በተደረገባቸው ፕሮግራም መሰረት እንጂ የራሳቸው ምርጫ የላቸውም።

እግዚአብሔርም ለየት ያለ ነገር ፈለገ። እግዚአብሔር በሰዎች ልብ ውስጥ መኖር ይችል ዘንድ ከሰዎች ልብ የተዘጋጀ ድንኳን ለራሱ ፈለገ። እግዚአብሔር ከእንስሳት በላይ ከፍ ያሉ ሰብዓዊ ሕይወት ያላቸው ሰዎችን መፍጠር ብቻ አይደለም የፈለገው። እግዚአብሔር ሰዎች ነጻ ፈቃድ እንዲኖራቸውና በራሳቸው ፍላጎት እንዲታዘዙትና እንዲያገለግሉት ነው። ይህም አደጋ ያለበት ውሳኔ ነው ምክንያቱም ነጻ ፈቃድ ለሰዎች መስጠት ማለት አማራጭ የሆኑ ክፉ መንገዶችን መምረጥ እንዲችሉ መፍቀድ ነው። ስሕተት መስራት ሐጥያት ነው፤ ሐጥያትም ደግሞ ሞትን ያስከትላል። ነጻ ምርጫ እንዲኖራቸው እግዚአብሔር በፊታቸው መልካሙንም ክፉውንም አስቀመጠላቸው።

ይህን ከማድረጉ በፊት መጀመሪያ እግዚአብሔር ምንም ፈተና በሌለበት ቦታ አዳምን አስተማረው፤ አዳምም ከእግዚአብሔር እውነትን ተምሮ መልካሙን ከክፉው መለየት ቻለ።

 

ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ውስጥ ሁሉም የፍራፍሬ ዛፍ መልካም ነበረ

 

 

ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ውስጥ መልካም እና ክፉውን የምታሳውቀዋ ዛፍ አለመጠቀሷን ልብ በሉ።

አዳም መንፈስ በነበረ ሰዓት ሰይጣን ምንም ሊያደርገው አልቻለም፤ ምክንያቱም አዳም መናፍስትን ማየት ይችል ነበረ፤ ስለዚህ ክፉ መንፈስ ሲመጣ ወዲያው አይቶ መለየት ይችል ነበር።

ዘፍጥረት 1፡29 እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤

እግዚአብሔር ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን ወደ ፊት እንዲበሉ ነው የፈጠረላቸው። ቁጥር 19 “መብል ይሆናችሁ ዘንድ” ሲል እንደ ትንቢት ስለ ወደፊት ነው የሚናገረው።

ከዚያ በኋላ ዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ውስጥ እግዚአብሔር በስጋዊ አካል ውስጥ ያኖራቸዋል፤ የዚያን ጊዜ ምግብ መብላት ያስፈልጋቸዋል። ምግባቸውም ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎች ላይ ሆኖ ተዘጋጅቶላቸዋል።

“የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤”

ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ ሁሉ መልካም ነበረ።

ከየትኛውም ፍሬ ከሚያፈራ ዛፍ ቀጥፎ መብላት ጉዳት አልነበረውም። አዳም የአፕል ፍሬዎችን አትብላ አልተባለም ምክንያቱም ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎች በሙሉ መልካም ነበሩ።

ዘፍጥረት 1፡30 ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ

አረንጓዴ ተክሎች ምግብ እንደሚሆኑ የተነገረ ትንቢት የለም። “ይሁንላቸው” ስለሚል ቀድሞውኑ ሆኗል።

እንስሳት ሁሉ ከመጀመሪያው ስጋዊ አካል ለብሰው ነበር። ምግባቸውም አረንጓዴ ተክሎችና ቅጠላቅጠል ነበሩ። አንበሶችም በጎችም ቅጠል እንዲበሉ ነበር የታዘዙት። በዚያ ጊዜ የዱር አራዊት ሥጋ አይበሉም ነበር።

ዘፍጥረት 1፡31 እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን።

አዳም መንፈስ ነበረ። ሊጎዳው የሚችል ምንም ነገር አልነበረም። ግኡዙ ፍጥረት፣ የፍራፍሬ ዛፎች ሁሉ መልካም ነበሩ። ግኡዝ ፍጥረታት የአዳምን መንፈስ ሊጎዱ አይችሉም። ደግሞም መልካም እና ክፉውን የሚያሳውቅ ዛፍ የሚባል ፍጥረታዊ ዛፍም አልነበረም፤ ምክንያቱም የተፈጠሩት ነገሮች በሙሉ መልካም ነበሩ።

ፍራፍሬም ይሁን የትኛውም ምግብ ሰው በልቶ ሊረክስ አይችልም። ምክንያቱም ክፉ የሚመጣው ከሰው ልብ ውስጥ ካለው ምኞች ነው።

ማርቆስ 7፡18 እርሱም፦ እናንተ ደግሞ እንደዚህ የማታስተውሉ ናችሁን? ከውጭ ወደ ሰው የሚገባ ሊያረክሰው ምንም እንዳይችል አትመለከቱምን?

ማርቆስ 7፡19 ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና፤ መብልን ሁሉ እያጠራ አላቸው።

ማርቆስ 7፡20 እርሱም አለ፦ ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው።

ከሰው ልብ ውስጥ የሚወጣው ሃሳብና ክፋት ነው ሰውን የሚያረክሰው።

 

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23