የዘፍጥረት ምዕራፍ 1 የመጀመሪያዎቹ አራት ቀኖች



ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ውስጥ ከተጻፈው አንጻር ስለ ፍጥረታዊው ዓለም እና ስለ መንፈሳዊው ዓለም ምን ልንማር እንችላለን?

First published on the 30th of July 2022 — Last updated on the 30th of July 2022

 

ዓለም መች እንደተፈጠረች ጊዜው አልተጠቀሰም

መፍጠር ማለት ምንም ጥሬ እቃ በሌለበት አንድ ነገር መስራት ነው።

ዘፍጥረት 1፡1 በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።

ፀሃይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ እና ፕላኔቶች በሙሉ በምዕራፍ አንድ የመጀመሪያ ቁጥር ውስጥ ነው የተፈጠሩት።
እግዚአብሔር ሰባቱን ቀኖች ከመዘርዘሩ በፊት ሁሉን ነገር ፈጥሮ ጨርሷል።

መፍጠር ማለት ያለ ምንም ጥሬ እቃ አዲስ ነገር መስራት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጀመሪያው ምዕራፍ የመጀመሪያ ቁጥር ውስጥ ምንም ዓይነት የጊዜ ርዝመት አልተጠቀሰም።
መሬት እና ሕዋ ሲፈጠሩ ምን ያህል ጊዜ ፈጁ ለሚለው ጥያቄ የፈለጋችሁትን ያህል ጊዜ ይሆናል ብላችሁ ማሰብ ትችላላችሁ። በፀሃይ ዙርያ ያሉትን ከዋክብትና ፕላኔቶች እንዲሁም ሌሎቹን ሁሉ ከዋክብት ለመፍጠር በጣም ብዙ ቢሊዮን ዓመታት ፈጅቶ ሊሆንም ይችላል።

ዓመታቱ እንዲህ በጣም ብዙ መሆናቸው ከምድር እጅግ ብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ ከዋክብት ብርሃናቸው ወደ ምድር እንዲደርስ በቂ ጊዜ ይሰጣቸዋል።
እግዚአብሔር ሲሰራ በችኮላ አልነበረም የሰራው። ደግሞም የሚኖረው የጊዜ ገደብ በሌለበት በዘላለማዊነት ውስጥ ነው። ስለዚህ በዘላለም ውስጥ የሚኖረው እግዚአብሔረ ለሰራው የፍጥረት ስራ የጊዜ ርዝመት መተመን ምንም ትርጉም የሌለው ድካም ነው። ዘላለም ማለት ከጊዜ ቀምበር ነጻ የምንወጣበት እንደሆነ አድርገን ማሰብ እንችላለን።

እግዚአብሔር ሕዋ፣ ፀሃይ፣ ጨረቃ፣ እና መሬትን ምንም ዓይነት ጥሬ እቃ ሳይጠቀም ፈጠራቸው። የጊዜው ርዝማኔ ስላልተጠቀሰ እግዚአብሔር ምድርን ለመፍጠር ምን ያህል ዘመን እንደፈጀበት አናውቅም። እግዚአብሔር ምድር ሕይወት ላላቸው ፍጥረታት ምቹ እንድትሆን አሰበ፤ ስለዚህ ምድርን በጥልቅ ውሃ ሸፈናት። ሕይወት ብዙ ውሃ ይፈልጋል። ነገር ግን ምድር ከፀሃይ በጣም እስከራቀች ድረስ በጣም ቀዝቃዛ ትሆናለች። ከዚህም የተነሳ በምድር ገጽ ላይ የሚገኘው ውሃ በረዶ ይሆናል። ይህም የመጀመሪያው የበረዶ ዘመን ነበር።

ከዚያም እግዚአብሔር በበረዶ ግግር የተሸፈነችዋን ምድር ወደ ፀሃይ ጠጋ አደረጋት፤ በረዶውም መቅለጥ ጀመረ። የቀለጡት የበረዶ ግግረች በምድር ገጽ ላይ ሲንቀሳቀሱ ለምድር ገጽ ቅርጽ ማበጀት ጀመሩ። እግዚአብሔርም የምድር ቅርጽ እርሱ እንዳሰበው ሆኖ እስከሚያይ ድረስ የበረዶ ግግሮችን ወዲያና ወዲህ አንቀሳቀሳቸው።

ከዚያ ወዲያ የበረዶ ግግሮቹ ሙሉ በሙሉ ቀልጠው የምድር ገጽ በሙሉ በጥልቅ ውሃ ተሸፈነ።
እግዚአብሔር ሌላ የበረዶ ዘመን እንዲመጣ ቢፈልግ ውሃ በሙሉ ቀዝቅዞ ወደ በረዶነት እንዲለወጥ ምድርን ከፀሃይ ፈቀቅ ያደርጋታል። ከዚያ በኋላ ምድርን መልሶ ወደ ፀሃይ በማስጠጋት ምድር ቅርጽዋ እንደገና የሚሞረድበት ሌላ የበረዶ ዘመን እንዲመጣ ያደርጋል። ይህንን ሂደት እግዚአብሔር ከፈለገ ብዙ ጊዜ ሊደጋግመው ይችላል።

ከመጨረሻው የበረዶ ዘመን በኋላ ምድር በሙሉ በጥልቅ ውሃ ተሸፈነች።
ውሃ ግን እየተነነ ደመና ይፈጥራል።

ስለዚህ ከምድር ገጽ በላይ ጥቅጥቅ ያሉ ደመናዎች ተፈጠሩ፤ እነዚህም ጥቅጥቅ ያሉ ደመናዎች የፀሃይን ብርሃን ሙሉ በሙሉ ጋረዱ። ከደመናዎቹ በላይ ፀሃይ እያበራች ነበር፤ ከደመናዎቹ በታች ግን ውሃው በሙሉ ጨለማ ውስጥ ተውጦ ነበር።

 

 

የደመናዎች ክምችት እየበዛ ሲሄድ ከበታቹ ጨለማ ፈጠረ።
እነዚህን ሁሉ ክስተቶች ሙሴ በራዕይ እየተመለከተ ነበር።
ሙሴ በራዕይ የምድርን ገጽ ሲመለከት ማየት የቻለው የውሃውን ገጽ ብቻ ነበር። ውሃ የራሱ የሆነ ቅርጽ የለውም። ውሃ ሁልጊዜ የፈሰሰበትን ስፍራ ቅርጽ ነው የሚይዘው። ውሃ በምድር ገጽ ላይ የተራራ ወይም የሸለቆ ቅርጽ ሊሰራ አይችልም፤ ስለዚህ ሙሴ ያየው የውሃው ገጽ ጠፍጣፋ እንደነበረ ብቻ ነው።

ዘፍጥረት 1፡2 ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤

(የውሃው ገጽ ጠፍጣፋ እና ባዶ ነበረ፤ ምንም ዓይነት ቅርጽ አልነበረውም። ስለዚህ ትልቅና ባዶ ስፍራ ብቻ ነበረ።)
ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤
(ከቀለጡት የበረዶ ግግሮች የተገኘው ውሃ በጨለማ ተሸፍኖ ነበረ። ይህም ከባሕር ላይ የሚነሳ ትነት ከምድር በላይ ጥቅጥቅ ያለ ደመና በመፍጠር የፀሃይ ጨረር ወደ ምድር እንዳይደር ከሚጋርድበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።)
የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።

 

 

ራሷን በራሷ ልትፈጥር የማትችለውን ምድር እግዚአብሔር ከፈጠራት በኋላ በምድር ላይ ሕያዋን ፍጥረታትን ለማኖር ወሰነ።
ከመጀመሪያው ሲሰራ የነበረው እግዚአብሔር ብቻ ነው።
እስከዚህ ድረስ ጊዜ አልተጠቀሰም፤ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ምን ያህል ጊዜ እንደፈጁ አናውቅም። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በውሃው ላይ በመንቀሳቀስ የሕይወትን ዘር እየዘራ በስራ ላይ ነበረ፤ የሕይወትን ዘር ከውሃው ስር በነበረው ምድር ላይ ነው የተከለው፤ ውሃውም ከደመናዎች በታች ነበረ።

እግዚአብሔር በተንቀሳቀሰ ጊዜ ሕይወት በሌለበት ስፍራ ሕይወት እንዲኖር ያደርጋል።

ስለዚህ እግዚአብሔር ደመናዎቹን እና በምድር ገጽ ላይ የነበረውን ውሃ ገለል በማድረግ ተዘርቶ የነበረው የሕይወት ዘር እንዲበቅል አደረገ።
በምስሉ ውስጥ ቢጫው ቅርጽ እግዚአብሔርን ይወክላል።

 

 

እግዚአብሔር ዘሮቹን ከውሃው በታች ከተከለ በኋላ ምድርን ሲመለከተታት አሁንም በውሃ እና በጨለማ ተሸፍናለች። እግዚአብሔር ምድርን በሕያዋን ፍጥረታት የሚሞላበት የራሱ አሰራርና ነበረው።
እስከዚህ ድረስ የፍጥረት ስራ ከጊዜ ርዝመት ጋር አልተያያዘም። ስለዚህ እግዚአብሔር ለስራው የተጠቀመው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ አናውቅም።

በዚህም ምክንያት ከዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ በመነሳት የምድር ዕድሜ ምን ያህል እንደሆን ማስላት አንችልም።
እግዚአብሔር ጊዜን መጥቀስ የጀመረው አስቀድሞ በፈጠራት ምድር ላይ ሕያዋን ፍጥረታትን ለማኖር ሲወስን ነው።

 

ቢግ ባንግ የተባለው የሥነ ፍጥረት ቲዎሪ ጥሩ ሳይንስ አይደለም

 

 

ሳይንቲስት ያልሆኑ ሰዎችን የሚያሸማቅቅ ታዋዊ የሆነ ሳይንሳዊ ቲዎሪ ቢግ ባንግ የሚባለው ነው፤ ይህ ቲዎሪ ዓለም የተፈጠረው በታላቅ ፍንዳታ ነው ስለሚል እውነት ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም በመጀመሪያ ምንም አልነበረም ተብሎ ቢጀመር የፈነዳው ነገር ምን እንደሆነ ሳይንቲስቶች ሊነግሩን አይችሉም። ስለዚህ የሚሉት ሲያጡ አንድ “ትልቅ እንቁላል” በተዓምር መጣና ፈነዳ ይላሉ።

ቲዎሪያቸውን ለመጀመር ይህ ተዓምር የግድ ያስፈልጋቸዋል ግን ተዓምር ብለው አይቆጥሩትም፤ ምክንያቱም ሳይንስ ስለ ተዓምራት አያጠናም።
ይህ የፈነዳው “ነገር” ከየት መጣ? ማንም አያውቅም።

ከምንም ነገር ተነስቶ እንዴት ወደ መኖር ሊመጣ ቻለ? ማንም አያውቅም።
መጀመሪያስ ምን ነበረ? ማንም አያውቅም።
የፈነዳው የሆነ ነገር ነው። ነገር ግን በመጀመሪያው “አንዳችም ነገር” አልነበረም፤ ቁስም ሆነ ኤነርጂ ወይም ኃይል አልነበሩም። ምንም ነገር ካልነበረ “ምንም” ሊፈነዳ አይችልም።

ሳይንቲስቶች “ምንም” ነገር አልነበረም ብለው አይጀምሩም። ሁልጊዜም የሆነ ዓይነት ኤነርጂ ወይም ኃይል ነበረ ይላሉ። ነገር ግን እያጭበረበሩ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ኃይል እንዴት ከምንም ነገር ሊመጣ እንደቻለ አያብራሩም።

የመጀመሪያው የፊዚክስ ሕግ ኃይል ሊፈጠር አይችልም ይላል።

ሳይንቲስቶች ግን በዓለም ውስጥ ያለው ኃይል በሙሉ ቢግ ባንግ በተባለው ታላቅ ፍንዳት የመጀመሪያ ሶስት ደቂቃዎች ውስጥ ነው የተፈጠረው በማለት ይህንን የፊዚክስ ሕግ ይጣረሳሉ።
ቢግ ባንግ ከተባለው ፍንዳታ በፊት ዓለም ምን ትመስል እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። ብዙ ቲዎሪዎች አሉ እንጂ አንድም ማስረጃ የለም። ትክክለኛ ሳይንስ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህ ፍጥረት ከምንም ነገር መጣ የሚለው ሃሳብ ትክክለኛ ሳይንስ አይደለም፤ ምክንያቱም አንዳችም ተጨባጭ ማስረጃ የለውም።

ሳይንቲስቶች ሕዋ የተፈጠረው ከታላቁ ፍንዳታ ነው ይላሉ። ይህም ከታላቁ ፍንዳት በፊት ሕዋ አልነበረም ማለት ነው። ስለዚህ ሕዋ ካልነበረ ያ ትልቅ እንቁላል ከመፈንዳቱ በፊት ያረፈበት ስፍራ አልነበረውም።
ከዚህ የተነሳ ቢግ ባንግ ጥሩ ቲዎሪ አይደለም ማለት ነው።

እንደ አላን ጉት እና የኖቤል ሽልማት አሸናፊው እስቲቨን ዋይንበርግ የመሳሰሉ ታላላቅ ሳይንቲስቶች ቢግ ባንግ የተባለውን ቲዎሪ ይደፉ ነበር፤ ግን ከጊዜ በኋላ ትተውታል። የዓለማችን 96 በመቶው ዳርክ ኤነርጂ እና ዳርክ ማተር የሚባል ነገር ነው፤ ነገር ግን ቢግ ባንግ የተባለው ቲዎሪ ዳርክ ኤነርጂ እና ዳርክ ማተር እንደሚገኙ አስቀድሞ አልተናገረም፤ ደግሞም ዳርክ ኤነርጂ እና ዳርክ ማተር ምን እንደሆኑ ማብራራትም አይችልም።

ታላቁ ሳይንቲስት ካርል ሳጋን “Cosmos” በሚል ርዕስ በጻፈው ታዋቂ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ቢግ ባንግ ቲዎሪ ሲናገር “… ዘመናዊውና ሳይንሳዊው አፈታሪካችን ቢግ ባንግ …” ብሏል። ደግሞም፡- “በአንድ የስነ ፍጥረት ተዎሪ መሰረት ዓለም እንዴት እንደሆነ ከአስር ወይም ከሃያ ቢሊዮን ዓመታት በፊት ተፈጠረችና ለዘላለም መስፋፋቷን ቀጠለች …” (ገጽ 258-259) ይላል። ካርል ሳጋን እራሱ በኤቮልዩሽን እና በቢግ ባንግ በጣም የሚያምን ሰው ነበር። “እንዴት እንደሆነ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ ስለ ዓለም አፈጣጠር ሳይንስ ያስቀመጠው ቲዎሪ ምንም ማስረጃ እንደሌለው ያመለክታል። ኦቮልዩሽኒስቶች ሁሉ ስለ ዓለም አፈጣጠር ሲናገሩ እንደ “ምናልባት፣” “የሆነ ቦታ፣” “በግምት” እና የመሳሰሉ እርግጠኝነትና ግለጽነት የጎደላቸው ቃላት በመጠቀም ነው የሚያስረዱት።

ካርል ሳጋን ሁለት ቢግ ባንጎች ነበሩ የሚለውን ሃሳብ ደጋፊ ነበረ፤ አንደኛው ለፍንዳታ አንደኛው ደግሞ ሲፈነዳ የተበታተነው ተመልሶ እንዲጣበቅ ለማድረግ።
ፍሬድ ሆይል ደግሞ ብዙ ትንንሽ ባንጎች ነበሩ ብሎ ሃሳብ ያቀርባል። ነገር ግን የዚህን መላ ምት ሒሳብ አስልቶ ማሳየት በራሱ በጣም ከባድ ነው።

ሳይንስ ስለ ዓለማችን አመጣጥ ሊያስረዳ ሲሞክር እርግጠኛ የሆነ መሰረት የለውም። ተጨባጭ ማስረጃዎችም የሉትም። ስለዚህ በግምቶች ብቻ የተሞላ ነው።
ጳውሎስ የሰጠውን የማስጠንቀቂያ ቃል እንመልከት፡-

1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡20 ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤

21 ይህ እውቀት አለን ብለው፥ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና። ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን።

 

ሳይንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከተቃረነ ስህተት የሚገኘው ሳይንስ ውስጥ ነው።
ሳይንስ የተጨባጭ እውነታ እና የመላ ምት ቅልቅል ነው፤ ስለዚህ ሳይንስ የተማሩ ሰዎች ግምት ነው። ሳይንስ በተጨባጭና በተረጋገጡ ነገሮች ላይ ሲናገር በጣም ትክክል ነው፤ ነገር ግን በቲዎሪዎች ላይ ሲናገር ትክክል ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ቲዎሪዎች ተቀባይነት የሚኖራቸው በማስረጃ ሲረጋገጡ ብቻ ነው። እንደዚያም ሆኖ ቲዎሪው አጠራጣሪ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ኋላ የተገኘ ማስረጃ ቲዎሪው ስሕተት መሆኑን ሊያሳይ ይችላል፤ ስለዚህ ቲዎሪው ኋላ የመጣውን ማስረጃ ሊያብራራው ካልቻለ ውድቅ ይሆናል። ሳይንሳዊ ቲዎሪዎች በግምቶች ላይ ነው የሚመሰረቱት ምክንያቱም ሳይቲስቶቹ በቦታው ላይ ተገኝተው ምን እንደተፈጠረ አላዩም። ለምሳሌ በ1958 ሳይንቲስቶች ምድር ላይ ሆነው ባደረጉት ጥናት መሰረት የቪነስ ሙቀት 18 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው፤ ፕላኔቷም በደመናዎች የተከበበች ስለሆነች በውሃ የተሞላች ናት ብለውን ነበር። እኛም ስንሰማ ይህ በትክክለኛ ሳይንሳዊ መለኪያዎች የተመሰረተ ግምት ነው ብለን ነበር። ነገር ግን ሮኬት ወደ ቪነስ ልከው ባዩ ጊዜ የፕላቷ ሙቀት 450 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሆኖ ተገኘ፤ ደመናዎቿም የሰልፈሪክ አሲድ ደመናዎች ሆነው ተገኙ። ስለዚህ ቪነስ ላይ ምንም ውሃ የለም። ደግሞ ልብ በሉ፤ ቪነስ ከሁሉም ቅርባችን የምትገኝ ፕላኔት ብትሆንም እንኳ ሳይንቲስቶች ስለ ቪነስ ተሳስተዋል።

አሜሪካ ጨረቃ ላይ ከመውጣቷ በፊት ሳይንቲስቶች የጨረቃ ከፍታዎች ልክ ምድር ላይ እንዳሉት እሳተ ገሞራዎች የቀለጠ ዓለት በሚተፉ እሳተ ገሞራዎች የተሰሩ ናቸው ብለውን ነበር። የጠፈር ተመራማሪዎች ጨረቃ ላይ በወጡ ጊዜ ግን እሳተ ገሞራ ስለመኖሩ አንዳችም ማስረጃ አላገኙም። ስለዚህ ጨረቃ ላይ ያሉ ነገሮች አፈጣጠራቸው ምድር ላይ ካሉ ነገሮች ጋር ተመሳሳይ አይደለም። ሳይንሳዊ ቲዎሪዎች ያለባቸው መሰረታዊ ችግር ይህ ነው - ምን ያህል ትክክል መሆናቸውን አናውቅም። ሳይንቲስቶች ቦታው ላይ ተገኝተው ነገሮችን እስኪለኩ ድረስ በቲዎሪዎቻቸው ስላስቀመጡት ድምዳሜ እርግጠኛ ሊሆኑ አይችሉም። ዓለም በተፈጠረች ጊዜ አንድም ሳይንቲስት አልነበረም። ፍጥረት ከመጀመሩ በፊት ዩኒቨርስ ምን ይመስል እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ቁሳዊ ማስረጃ የለንም። ስለዚህ ይህ ሳይንስ ሊደርስበትና ሊያጠናው የማይችለው ጉዳይ ነው።

ሳይንስ የተለየ ነገር ስለተናገረ ብላችሁ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን አትጣሉ። በፍጥረት መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር ብቻ ነው የነበረው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ምስክርነት ብቻ ነው ትክክለኛ ማስረጃ ሊሆን የሚችለው።

ፍርድ ቤት ውስጥ ምስክር ቀርቦ ሲናገር ዳኛ እንዲህ ብሎ ይጠይቀዋል፡- “ይህ ሲሆን በዓይንህ አይተሃል?” ለዚህ ጥያቄ፡- “አዎ” ብሎ መመለስ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

 

የእውነት ብርሃን እና የሰው አመለካከት ጨለማ ሲነጻጸሩ

 

 

የእግዚአብሔር የመጀመሪያ ቀን ብርሃንን ከጨለማ ለየ፤ ይህንንም ያደረገው ምድርን ለሕያዋን ፍጥረታት ምቹ ለማድረግ ነው።

ወደ ዘፍጥረት ተመልሰን ስንመለከት እግዚአብሔር አፈር ውስጥ ከውሃ በታች እና ከደመናዎች በታች ተዘርቶ የነበረውን ሕይወት ሊያበቅል ወሰነ።

ዘፍጥረት 1፡3 እግዚአብሔርም፦ ብርሃን ይሁን አለ፤ ብርሃንም ሆነ።

የፀሃይ ብርሃን ቀድሞ ነበረ፤ ነገር ግን ጥቅጥቅ ያለውን ደመና ሰንጥቆ ወደ ምድር ሊደርስ አልቻለም።

 

 

እግዚአብሔር፡- “ብርሃን ይሁን” ባለ ጊዜ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ደመናዎቹን መታቸውና በደመናዎቹ ውስጥ የነበሩትን የውሃ ሞሎክዩሎች ወደ ነበሩበት የሃይድሮጅን እና ኦክስጅን ጋዝ አተሞች መለሳቸው። እነዚህ ብርሃን አስተላላፊ ጋዞች በምድር ዙርያ ለምድር ከለላ የሚያደርግ ስስ መጋረጃ ሆነው ተለወጡ፤ ከዚህም የተነሳ የፀሃይ ብርሃን ወደ ምድር መድረስ ቻለ።

በዚህ መንገድ የፀሃይ ብርሃን ወደ ምድር ደረሰ።

 

 

ከፀሃይ ብርሃን የሚወጣው የሙቀት ሞገድ ከምድር ዙርያ ባለው በተለያዩ ጋዞች የተሰራ ከባቢ አየር ውስጥ ተበታትኖ ምድር ላይ ሲደርስ በእኩል ሙቀት ይሰራጫል። ስለዚህ ምድር ላይ በሁሉም ስፍራ እኩል ሙቀት ይደርሳል፤ ዝናብም አይዘንብም። ዝናብ የሚፈጠረው ሞቃት አየር እና ቀዝቃዛ አየር ሲገናኙ ነው። ለምሳሌ በቀዝቃዛ ቀን ከአፋችሁ የሚወጣው ሙቅ ትንፋሽ ቀዝቃዛ መስታወት ላይ ሲያርፍ ትንፋሻችሁ ውስጥ ያለው የውሃ ትነት መስታወቱን እንደ ጉም ድብዝዝ ያደርገዋል።

ሊኒየር የተባለ ተወርዋሪ ኮከብ በ2000 ዓ.ም ፀሃይ አጠገብ ሲፈነዳ በ3.3 ሚሊዮን ቶን የውሃ ሞለኪዩሎች መበታተን የተነሳ የሃይድሮጅን እና የኦክስጅን ደመና ፈጠረ። ይህም የሚያሳየን ውሃ በሕዋ ውስጥ ወደተሰራበት ሁለት ጋዞች ወደ ሃይድሮጅን እና ወደ ኦክስጅን ጋዞች በቀላሉ ሊበታተን እንደሚችል ነው።

ዘፍጥረት 1፡4 እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፥ እግዚአብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።

እግዚአብሔር የሰራው ነገር በሙሉ መልካም ነው። ወደ ፀሃይ የዞረው የምድር ግማሽ አካል በቀን ብርሃን ውስጥ ነበር። ለፀሃይ ጀርባውን የሰጠው የምድር ግማሽ አካል ደግሞ የሌሊት ጨለማ ውስጥ ነበረ።

ጨለማ የራሱ ሕልውና ኖሮት የተፈጠረ ነገር አይደለም፤ የብርሃን አለመኖር ውጤት ብቻ ነው እንጂ።

አለማመን ሐጥያት ነው፤ መንስኤውም የእግዚአብሔር ቃል አለመኖር ነው። የምናምነው ነገር በተጻፈው ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያልተመሰረተ ከሆነ አለማመን ወይም መንፈሳዊ ጨለማ ነው።

እንደ ስላሴ፣ ኩዳዴ፣ የስቅለት አርብ፣ የፋሲካ ሰኞ፣ መቁጠሪያ፣ ክሪስማስ፣ ዲሴምበር 25 የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌሉ ቃላት የዘመናችን ቤተክርስቲያኖች ጨለማ ውስጥ መሆናቸውን ያመለክታሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ልደት እንድናከብር አላዘዘንም። ለዚህ ነው ኢየሱስ የተወለደበት ቀን መች እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈው።

 

የእግዚአብሔር አንድ ቀን ከእኛ 1,000 ዓመታት ጋር እኩል ነው

 

 

ዘፍጥረት 1፡5 እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን።

ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በዚህ ቃል ውስጥ ነው።
በዚያ ሰዓት ሰዎች ገና ስላልተፈጠሩ እግዚአብሔር ጊዜን በሰዎች 24 ሰዓት መለካት አላስፈለገውም።
በዚያ ሰዓት የነበረው እግዚአብሔር ብቻ ስለነበር ጊዜውን የለካው “በእግዚአብሔር ቀኖች” ነው።
አንድ “የእግዚአብሔር ቀን” ምን ያህል ይረዝማል? የሰዎችን 1,000 ዓመታት ያህላል።

2ኛ ጴጥሮስ 3፡8 እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ።

 

በክርስትና ውስጥ የመጀመሪያው እርምጃ ከሐጥያታችን ንሰሃ መግባትና ኢየሱስን አዳኛችን አድርገን መቀበል ነው። በዚህ መንገድ ነው የምንድነው።
ባለ 1,000 ዓመቱ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ቀን “ብርሃንን የምናይበትን” የመዳንን የመጀመሪያ እርምጃ ይወክላል።

ልባችን ጥቅጥቅ ባለ የሐጥያት ወይም የአለማመን ደመና ተጋርዷል። ንሰሃ ስንገባ የእግዚአብሔር ቃል የሐጥያት እና የአለማመንን ግርዶች ይሰብረውና ሐጥያታችንን መታየት እስከማይችል ድረስ ይደመስሰዋል። ከሐጥያት ነጻ ወጥተን ስለ ሐጥያታችን በሞተልን በእግዚአብሔር ልጅ ብርሃን በኢየሱስ ክርስቶስ ደስ እንሰኛለን። ልብ በሉ እርሱ ሁልጊዜም ነበረ፤ ነገር ግን ንሰሃ በገባን ጊዜ ሐጥያታችን ስለተወገደልን ነው እርሱ እንዴት ውብና ድንቅ መሆኑን ማየት የቻልነው።

እግዚአብሔር የደመናውን ግርዶች እና ጨለማውን ለማስወገድ 1,000 ዓመታት መፍጀት የግድ አስፈልጎት አይደለም። ያን ያህል ጊዜ መቆየት ፈልጎ ነው። ስለዚህ 1,000 ዓመታት እስኪጠናቀቁ ድረስ ጠበቀ። ከዚያም “የመጀመሪያው ቀን” ወይም 1,000 ዓመት ተጠናቀቀና የሁለተኛው ቀን ስራ ተጀመረ።

በመጀመሪያው ቀን ምንም የተፈጠረ ነገር የለም። እግዚአብሔር አስቀድሞ የፈጠራትን ምድር ለሰዎች ምቹ እንድትሆን ማበጀት ጀመረ እንጂ።

ከባሕር ላይ በትነት በተነሳው እንፋሎት የተፈጠሩት ጥቅጥቅ ያሉ ደመናዎች ከእግዚአብሔር አፍ በወጣው ቃል በምድር ዙርያ በዓይን የማይታይ የሃይድሮጅን እና የኦክስጅን ጋዞች መጋረጃ ሆነው ተለወጡ። እግዚአብሔር ሲናገር ነገሮች ይሆናሉ። ይህ እውነተኛ ኃይል ነው።

እግዚአብሔረ ለነፍሳችን ሲናገርና እኛም ስንቀበለው መዳን ይሆንልናል፤ እኛም እንለወጣለን።
አስቀድሞ የነበረው የፀሃይ ብርሃን አሁን ወደ ምድር መድረስ ቻለ።

 

ውሃ ወደ ሃይድሮጅን እና ወደ ኦክስጅን ጋዞች ሊከፋፈል ይችላል

 

 

ከውሃ የተገኙ ለምድር ከለላ የሚያደርጉ ጋዞች ከባሕሩ በላይ ከነበረው ከከባቢ አየር በላይ ነበሩ።

ባሕር እረፍትና ሰላም የሌላቸውን ሕዝቦች ይወክላል። ከሰዎች ስግብግብነት፣ ራስ ወዳድነትና የስልጣን ሽኩቻ መዳን ከፈለግን ጥበብ፣ ምሪት፣ እና ጥበቃ ከላይ ማግኘት አለብን።

ዘፍጥረት 1፡6 እግዚአብሔርም። በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።

ለሕይወት የመጀመሪያው አስፈላጊ ነገር ብርሃን ነው።
ከዚያ ቀጥሎ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ለመተንፈስ አየር ያስፈልጋቸዋል።

በእምነት የመዳንን ብርሃን ካገኘን በኋላ የምንተነፍሰውን የቅድስና አየር ማግኘት አለብን።

ስለዚህ እግዚአብሔር በምድር ላይ ባሕርን በከደኑ ውሃዎች እና ከላይ ደግሞ ደመናው ውስጥ ባሉት ወደ ውሃ ጋዞች ወደ ሃይድሮጅን እና ኦክስጅን የበታተናቸው ውሃዎች መካከል ጠፈር አደረገ። [በኖህ ዘመን እግዚአብሔር ከጠፈር በላይ ያሉትን የውሃ ጋዞች መልሶ በመግጠም የጥፋት ውሃ ሆነው እንዲዘንቡ አደረገ። ስለዚህ ለምድር ከለላ ሆነው የተዘረጉት ጋዞች በዝናብ መልክ ምድር ላይ ወረዱ። ከምድር በላይ ምንም ከለላ የሚሆን ግርዶች በሌለበት ሰዓት የፀሃይ ብርሃን ውስጥ ያሉ ጎጂ የሆኑ ጨረሮች፣ ለምሳሌ አልትራቫዮሌት ጨረር፣ ምድር ላይ ደረሱና ከጥፋት ውሃ በኋላ ሰዎች በለጋ ዕድሜያቸው መሞት ጀመሩ።]

ዘፍጥረት 1፡7 እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ።

ሰው ሊተነፍሰው የሚችለው ጋዝ ያለበት ከባቢ አየር ጠፈር ተብሎ ተጠራ።
አየር ውስጥ ያሉት የጋዝ ዓይነቶች በትክክል መመጣጠን አለባቸው። የኦክስጅን መጠን ከ16 ፐርሰንት በታች ከወረደ እሳት መንደድ አይችልም፤ በሰውነታችን ሴሎችም ውስጥ ምግብ መቃጠል አይችልም፤ ስለዚህ ሰውነታችን ሙቀትና ኃይል አያገኝም። የኦክስጅን መጠን ከ21 ፐርሰንት በላይ ከሆነ ደግሞ እሳትን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይሆናል።

ዘፍጥረት 1፡8 እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን።

ሰማይ በከፍታ ላይ ያለ መንፈሳዊ ዓለም ስለሆነ ሰማይን ለማየት “ወደ ላይ” እንመለከታለን። ስለዚህ ከባቢ አየር የሰማይ ምሳሌ ነው።
ምድር የራሷ ከባቢ አየር ስላላት በአየሩ ውስጥ ያሉት ሞለኪዩሎች የፀሃይ ብርሃን ውስጥ ያለውን ሰማያዊ ቀለም በየአቅጣጫው ይበታትኑታል። ሰማያዊ ብርሃን አጭር ሞገድ ያለውና ብዙ ኃይል ያለው ነው።

ከሰማያዊው ብርሃን ከፊሉ ወደ ታች በመበታተን ወደ ምድር ይደርሳል። ወደ ላይ ቀና ስንል ሰማያዊው ብርሃን ወደ ታች ወደ እኛ ሲመጣ እናያለን። ለዚህ ነው ሰማይን ስንመለከት ሰማያዊ ቀለም የሚታየን።
ይህም የእግዚአብሔር ዙፋን ምሳሌ ነው።

ሕዝቅኤል 1፡26 በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ።

(ሰንፔር ሰማያዊ ድንጋይ ነው)።
እግዚአብሔር ከባቢ አየርን ለማበጀት 1,000 ዓመታት የጠበቀው ሕይወት ያላቸው ፍጡራን መተንፈስ እንዲችሉ ነው።
በክርስትና ሕይወታችን የመጀመሪያው እረምጃ ከሐጥያታችን ንሰሃ በመግባት መዳን ነው፤ ይህም “ብርሃንን ለማየት” ያስችለናል። ቀጣዩ እርምጃ የቅድስናን ከባቢ አየር ማበጀት ነው።

ዕብራውያን 12፡14 ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና

1ኛ ተሰሎንቄ 4፡3 ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ ከዝሙት እንድትርቁ፥

ሳይንቲስቶች በምድር ላይ እንደ አሞኒያ እና ሜቴን የመሳሰሉ መርዛማ ጋዞች በነበሩበት ሰዓት ላይ በሆነ ባልታወቀ መንገድ ምድር ላይ ሕይወት ተጀመረ ይላሉ። ነገር ግን ጥንታዊ በሆኑ ዓለቶች ውስጥ የነዚህን ጋዞች መኖር ማስረጃ ሊያገኙ አልቻሉም። መርዛማ በሆኑ ጋዞች መካከል ሕይወት ተጀመረ ማለት አሳማኝ ሃሳብ አይደለም።

ውሃ በዓይን ወደማይታዩ የሃይድሮጅን እና ኦክስጅን ጋዞች እንደሚበታተን የሚያሳይ ሳይንሳዊ ማስረጃ በዚህ ጥናት መጨረሻ አካባቢ ይገኛል።

 

3ኛው ቀን ላይ የብስ ከባሕር ተለየ

 

 

ምድርን ለሰው ሕይወት ምቹ እንድትሆን የማበጀት ስራ የተሰራበት ሶስተኛው ቀን ደረቁ መሬት ከባሕር እንዲለይ የተደረገበት ነው።

የእግዚአብሔር ቃል በጽድቅ መኖርን ይጠይቃል። ከሐጥያት እና ከአለማመን መለየት አለብን።
አሁን ለሶስተኛው ደረጃ ጊዜው ደረሰ፤ እርሱም 3ኛው ቀን ነው።

ዘፍጥረት 1፡9 እግዚአብሔርም። ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ።

ውሃዎቹ በአንድ ላይ ተሰበሰቡና ከምድር ተለዩ። ባሕር እረፍትና ሰላም የሌላቸውን ሕዝቦች ይወክላል።

ራዕይ 17፡15 አለኝም። ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው።

ክፉዎች እውነትን ለመቃወም በአንድነት እንደሚሰበሰቡ ሁሉ ጻድቃንን ለብቻቸው ይለዩዋቸዋል። ደረቁ ምድር ጻድቃንን ይወክላል። ሐጥያተኞች ከጻድቃን ፈቀቅ ይላሉ፤ ከብዙሃኑ ክፉዎች ጋር ለመቀላቀል ብለው ከጻድቃን ተለይተው ይሄዳሉ። ብዙሃኑን ተከትሎ መሄድ ሁልጊዜም መጨረሻው ገደል መግባት ነው።

እግዚአብሔርም ደረቁን ምድር ወደ ላይ ስለገፋው ከባሕር በላይ ከፍ ብሎ ወጣ። ይህም አንድ ታላቅ አህጉር ሆነ፤ ሳይንቲስቶች ፓንጌያ (ሙሉ ምድር) ይሉታል። በኖህ ዘመን በጥፋት ውሃ የመጣውን ኃይል በመጠቀም እግዚአብሔር ይህንን አንድ ብቻ የነበረውን ታላቅ ምድር ወደ ትናንሽ አሕጉሮች ከፋፈለው።

ዘፍጥረት 1፡10 እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

ደረቁ የብስ ምድር ተብሎ ተጠራ። ውሃው ስም አልተሰጠውም።

ውሃው የመከማቸቱ ሂደት ባሕር ተብሎ ተጠራ። በመጨረሻም ኢክዩሜኒካል በተባለ እንቅስቃሴ ቤተክርስቲያኖች የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አንቀበልም በማለት ወደ አንድነት ይመጣሉ። ቤተክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ፍጹም መመሪያቸው አድርገው መቀበል ትተዋል። የሰዎችን ፍላጎት ላለመጋፋት ተብሎ የቃላት ትርጉሞች ይለወጣሉ። ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተት አለ ይላሉ። በአሁኑ ዘመን ከ100 በላይ የተለያዩ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስን የምታምነዋ የክርስቶስ ሙሽራ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቃ በመያዟ ምክንያት ሌሎች ቤተክርስቲያኖች ገለል ስለሚያደርጓት ተለይታ ለብቻዋ ትቆማለች። “ቤተክርስቲያን” የሚለው ቃል የተገኘበት የግሪክ ቃል ትርጉሙ “ተጠርተው የወጡ” ወይም “የተለዩ” ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማመን አንድ ሰው በቤተክርስቲያኖች ውስጥ ተፈላጊነቱ እንዲቀንስ ያደርጋል።

ዘፍጥረት 1፡11 እግዚአብሔርም። ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ።

ደመናዎቹ ተወግደው የፀሃይ ብርሃን ወደ ምድር ሲደርስ እንዲሁም ለመተንፈስ ምቹ የሆነ ከባቢ አየርም ተዘጋጅቶ ደረቁ ምድር ከባሕር ከተለየ በኋላ እግዚአብሔር በምድር ላይ የተከላቸው የሕይወት ዘሮች የሚበቅሉበት ጊዜ ደረሰ። ተክሎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፤ ይህም የመጀመሪያው የሕይወት ተዓምር ነበረ።

ዘፍጥረት 1፡12 ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

እያንዳንዱ የእጽዋት ተክል እራሱን የመሰሉ እጽዋት የሚወልድና የሚያባዛ ዘር ያፈራል።

ዘፍጥረት 1፡13 ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን።

በሶስተኛው ቀን የተከናወነው የዕጽዋትን ሕይወት የመፍጠር ስራ የመንፈሳዊ ሕይወት ማለትም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ምሳሌ ነው።

የእግዚአብሔር መንፈስ ግለሰቡን ይቆጣጠረዋል፤ ከዚያም ያንን ሰው እግዚአብሔር ወዳዘጋጀለት ፍጹም ፈቃድ ይመራዋል። ከዚህ በፊት ሕይወታችንን በራሳችን ስንመራ ነበር፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ አማኞች ሕይወታቸውን እግዚአብሔር እንዲቆጣጠር ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ፤ ከዚያም ሕይወታቸውን እግዚአብሔር ይመራል።

 

እግዚአብሔር በምድር ላይ ፀሃይ የቀኑን ሰዓት እንድትቆጣጠር አደረጋት

 

 

ፀሃይ ፍጥረታዊ ብርሃናችን ናት፤ ስለዚህ መንፈሳዊው ብርሃናችን የሆነውን ኢየሱስን ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል ትወክላለች።

ስለዚህ በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን እንዴት እንደምንመላለስ እና በእግዚብሔር ቃል ውስጥ ቦታችንን እንድናገኝ የሚመራን መጽፍ ቅዱስ ነው እንጂ ቤተክርስቲያን አይደለችም።

አሁን እያንዳንዱ ምሳሌ እና ትንቢት ሁሉ የመጨረሻውን የቤተክርስቲያን ዘመን በሚያወግዝበት የመጨረሻ ዘመን ላይ እንደምንገኝ ማስተዋል አለብን። ስለዚህ ዋስትናችን እያንዳንዳችን በግል የጥንቷ ቤተክርስቲያን ወዳመነችው እምነት በመመለስ ነው። ይህም ጥልቅ የሆነ የእግዚአብሔር ሚስጥር ነው።

መንፈስ ቅዱስ ለዘመናችን ወደሚያስፈልገን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሁሉ ሊመራን ይገባል። መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው መጽሐፍ ቅዱስን ሊገልጥልን የሚችለው።

ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤

እግዚአብሔር ቀጣዩን ስራውን ከማከናወኑ በፊት ተጨማሪ 1,000 እንዲያልፉ አደረገ።

የእግዚአብሔር አራተኛ ቀን ላይ ፀሃይ ተሰራች፤ ይህም የሆነው ፀሃይ በመጀመሪያ ከተፈጠረች በኋላ ነው፤ ፀሃይም የቀኑን ሰዓት ብርሃን እና ሙቀት የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጣት።

ዘፍጥረት 1፡14 እግዚአብሔርም አለ። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤

እስከዚህ ድረስ ትኩረት ሁሉ በምድር ላይ ነበረ። ቀጥሎ ግን ምድር በሕዋ ውስጥ ከፀሃይ፣ ከጨረቃ፣ እና ከከዋክብት አንጻር ትክክለኛ ስፍራዋን የምትይዝበት ጊዜ ደረሰ።

በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከመጽቅ፣ ከመቀደስ፣ እና በመንፈስ ቅዱስ ከመጠመቅ በኋላ አራተኛው ደረጃ ግለሰቡ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ በክርስቶስ አካል ማለትም በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተመደበለትን ስፍራ ማገኘቱ ነው።

በሎዶቅያ ማለትም በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ወደ ጥንቷ ቤተክርስቲያን ትምሕርቶች መመለስ አለብን።

በመጨረሻ የሚሰበሰበው መከር በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ከተዘራው ዘር ጋር ተመሳሳይ ነው።

መከር የሚባለው ተክሎ በሚሞት ጊዜ ከላዩ ላይ የሚለቀመው ፍሬ ነው። ይህም ሙሽራይቱ ጌታ በአየር ላይ ለመቀበል ከምድር ተነጥቃ ስለመሄዷ የሚያስረዳ ውብ ምሳሌ ነው።

 

 

ቀንና ሌሊት እየተፈራረቁ እንዲገለጡ ፀሃይ ታስፈልገናለች፤ እንዲሁም መሬት ደግሞ በራሷ ዛቢያ ላይ መሽከርከር አለባት። ምድር በ24 ሰዓት ውስጥ አንድ ዙር መሽከርከር አለባት። ፍጥነቷን ቀንሳ ብትሽከረከር ቀኑ በጣም ስለሚረዝም ምድር ሙቀቷ ይጨምራል። ሰዎችም ደግሞ የስራ ሰዓታቸው በጣም ይረዝምና ይደክማቸዋል። ምድር ስትሽከረከር ፍጥነቷን ብትጨምር ደግሞ ቀኑ በጣም ስለሚያጥር ስራዎቻችንን ሰርተን ለመጨረስም ጊዜው አይበቃንም። ከዚያ ሌላ ደግሞ ቀኑ በቂ ሙቀት ስለማያገኝ ሰብሎች ከፀሃይ ብርሃን እና ከሙቀት የሚገኘውን ኃይል በበቂ መጠን ስለማያገኙ ፍሬ አያፈሩም።

ስለዚህ ቀኑ ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ ከምትሽከረከርበት ፍጥነት ጋር የተያያዘ ነው። በመሬት ላይ ያለው ሙቀትም የሚወሰነው ምድር ከፀሃይ ባላት ርቀት ነው። ከሚያስፈልግ በላይ ጠጋ ብንል በሙቀት እንቃጠላለን፤ በጣም ብንርቅ ደግሞ በብርድ እንቸገራለን። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በጣም ወሳኝ ናቸው።

ዓመቱ የሚወሰነው ምድር በፀሃይ ዙርያ በምሕዋሯ ላይ በምትዞርበት ፍጥነት ነው። ይህ ፍጥነት በጣም ከጨመረ ዓመቱ ስለሚያጥር ሰብሎች ለማደግ በቂ ጊዜ አያገኙም። ይህ ፍጥነት ቢቀንስ ደግሞ ዓመቱ ይረዝማል፤ የክረምቱም ወቅት ይረዝማል፤ በዚህም ምክንያት በበጋ ወቅት ያከማቸነው አዝመራ ረጅሙን ክረምት ለማሳለፍ አይበቃንም።

ግብጽ ውስጥ ከከዋክብት ሁሉ ደማቅ የሆነው ሲሪየስ የተባለው ኮከብ በየዓመቱ ከምስራቁ ሰማይ አድማስ በላይ ፀሃይ ከመውጣቷ በፊት በየዓመቱ በተመሳሳይ ቀን ነው የሚወጣው። ያ ቀን ሁልጊዜ የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን ተደርጎ ይቆጠራል። በዚያ ቀን ማታ የናይል ወንዝ ውሃ በዙርያው አጥለቅቆ የነበረውን ምድር ትቶ ሰብሰብ ይልና ለአዲሱ ዘር ለሚዘራበት ወቅት ለም መሬት ያዘጋጃል። ስለዚህ ግብጽ የመጀመሪያው ትክክለኛ ካላንደር ነበራት፤ ዩልየስ ቄሳርም የግብጽን ካላንደር ኮርጆ ለሮማ መንግስት ተጠቀመበት። እስከ ዛሬ ድረስ ያንኑ ካላንደር ነው የምንጠቀመው።

የጠፈር ተመራማሪዎች ወደ ጨረቃ ሄደው ለመመለስ መንገድ እንዳይጠፋባቸው ከዋክብትን ተጠቅመዋል።

ወቅቶች የዓመት ክፍል ናቸው። አንድን ዓመት ለመከፋፈል ቀላሉ ዘዴ ጨረቃን መጠቀም ነው። ጨረቃ ሙሉ ትሆንና ከዚያ በኋላ ምንም ጨረቃ እስከማናይ ድረስ ትጠፋለች። ከዚያ ከወር በኋላ እንደገና ሙሉ ጨረቃ ሆና ትመለሳለች። የጨረቃ ምሕዋር የአንድ ዓመት አንድ አስራ ሁለተኛ ያህል ነው። ስለዚህ ጨረቃ አንድ ዓመትን በ12 ወራት ያህል ተከፋፍላለች።

እያንዳንዱ ወቅት ሶስት ወር ይፈጃል። ወቅቶቹ መፈራረቃቸውን በትክክል የሚያሳዩን የከዋክብት ስብስቦች ናቸው።

ብዙ ከዋክብት በቡድን በቡድን ተሰባስበው ነው የሚወጡት። በዓለም ዙርያ በስፋት የሚታወቁ 88 የከዋክብት ስብስቦች አሉ። ፖላሪስ የተባለው ኮከብ ወደ ሰሜን ያመለክታል። አምስቱ የሳዘርን ክሮስ የተባሉ ከዋክብት ደቡብ ወዴት እንደሆነ ይጠቁሙናል። ከዚህ በፊት በነበሩ ክፍለ ዘመናት ከዋክብት በባሕር ላይ ለሚሄዱ መርከበኞች በጉዞዋቸው ወቅት አቅጣጫ እንዳይስቱ መሪ ሆነው አገልግለዋቸዋል። በአሁኑ ዘመን ግን ሰዎች ከከዋክብት ይልቅ ጂፒኤስ እየተጠቀሙ ናቸው።

በደቡባዊው ንፍቀ ክበብ ውስጥ አቅጣጫ ለማግኘት ዘሳዘርን ክሮስ የተባሉትን ከዋክብት እንጠቀማለን። ይህም ወደ መንግስተ ሰማይ ለመድረስ አቅጣጫ የሚጠቁመን የክርስቶስ መስቀል መሆኑን የሚያሳይ የመንፈሳዊ እውነት ምሳሌ ነው።

የሰሜን ኮከብ ሁልጊዜ ወደ ሰሜን ነው የሚጠቁመው። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና፣ ዛሬ፣ እስከ ለዘላለምም ያው መሆኑን ያመለክታል። እርሱ የማይለወጥ ጌታና አዳኝ ነው።

ዕብራውያን 13፡8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።

ምድር በፀሃይ ዙርያ በምትሄድበት ምሕዋርዋ ላይ እንደሆነች አስቡ፤ ይህም ሰዎች በተለያዩ ወቅቶች የሰማይን የተለያየ ክፍል እንዲያዩ ይረዳቸዋል። ከዋክብትን ማየት የምንችለው በሌሊት ብቻ ነው፤ ያውም ፀሃይ ወደሌለችበት አቅጣጫ ስንመለከት።

በእያንዳንዱ ወቅት ለሶስት ወራት ያህል በሌሊቱ ሰማይ ላይ የሚታዩ የተወሰኑ የከዋክብት ስብስቦች አሉ። እነዚያ ከዋክብት በሌሊት እስከታዩ ድረስ ሰዎች በየትኛው ወቅት ውስጥ እንደሆኑ ያውቃሉ። ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙት የጊዜ መቁጠሪያ ካላንደር የከዋክብት ስብስብ ነው። በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ውስጥ የሚገኙ ዋኘኞቹ የከዋክብት ስብስቦች በቀይ ቀለም የተጻፉት ናቸው።

 

 

ዘፍጥረት 1፡15 በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ።

እግዚአብሔር ምድርን ከፀሃይ እና ከጨረቃ በትክክለኛ ርቀት ላይ ነው ያስቀመጣት። ምድር ከፀሃይ በ159 ሚሊዮን ኪሎሜትር ርቅ ላይ መሆን አለባት። ምድር ከጨረቃ በ380,000 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው። ጨረቃ በባሕር ውሃ ላይ የምታደርገው ስበት ታላላቅ ማዕበሎችን ይፈጥራል። ይህም ባሕር ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች እንዲገላበጡ ስለሚያደርግ የባሕር ውሃ ረግረግ አይሆንም። ጨረቃ ትንሽ ቀረብ ብትል የባሕር ማዕበል ከሚያስፈልገው በላይ ከባድ ይሆን ነበር። ጨረቃ ትንሽ ራቅ ብትል ደግሞ የባሕር ማዕበሎች ደካማ ይሆኑ ነበር። ከዚህም የተነሳ ባሕር ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን በበቂ ሁኔታ ማገላበጥ አይቻልም ነበር።

ዘፍጥረት 1፡16 እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።

በዚህ ቀን እግዚአብሔር ፍጥረትን “የፈጠረው” ከምንም ነገር አይደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ “ፈጠረ” የሚለውን ቃል አይጠቀምም።

መጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀመው ቃል “አደረገ” የሚለውን ነው። “አደረገ” የሚለው ቃል ሁለት ትርጉሞች አሉት። አንድን ነገር ከተለያዩ ጥሬ እቃዎች ገጣጥሞ ማበጀት ወይም ሰውን ወይም አንድን ነገር የሆነ ነገር እንዲሰራ ማስገደድ ማለት ነው። ሰማይ እና ምድር አስቀድመው ያለ ጥሬ እቃ ከምንም ነገር ተፈጥረዋል። ስለዚህ ሰማይ እና ምድርን ከሆነ ነገር መስራት አላስፈለገም፤ ቀድመው ተፈጥረዋል።

አሁን የሆነ ነገር እንዲሰሩ እግዚአብሔር ፈለገ። ዋነኞቹ የብርሃን ምንጮች በመሆን ከምድር በላይ ባለው ሰማይ ላይ መሰልጠን አለባቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ “አደረገ” የሚለውን ቃል መጠቀሙ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ስራ እንዲያከናውኑ እንዳደረጋቸው የሚገልጽ ነው፤ ይህም የቀን እና የሌሊት ገዥዎች መሆን ነው።

እግዚብሔር ፀሃይ በቀን ላይ እንድትሰለጥን እና ጨረቃ ደግሞ በሌሊት እንድትሰለጥን አደረገ።

ይህን ያደረገው ጨረቃ እና ፀሃይ ከተፈጠሩ በኋላ ነው፤ ስለዚህ እነርሱን እንደገና መፍጠር አላስፈለገውም።

ፀሃይ እና ጨረቃ የሆነ ስራ እንዲሰሩ አደረገ። የተሰጣቸውን ሥራ እንዲያከናውኑ አደረገ

እያንዳንዱ የተሰጣቸውን ስራ እንዲሰሩ አደረገ

ብርሃናቸው በቀኑ እና በሌሊቱ ላይ መሰልጠን አለበት። ፀሃይ በቀኑ ላይ ትሰለጥንበታለች፤ ነገር ግን በሌሊት ላይ አትሰለጥንም። ስለዚህ ጨለማ ምድርን በሸፈናት ሰዓት ፀሃይ ብርሃኗን ወደ ምድር ለማድረስ ጨረቃ ታስፈልጋታለች። ከፀሃይ ተንጸባርቆ የመጣውን ብርሃን የጨረቃ ብርሃን እንለዋለን፤ ጨረቃዋም ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ በሌሊት ለመንቀሳቀስ በበቂ ሁኔታ ማየት እንድንችል ይረዳናል።

ኢየሱስ ማለትም የእግዚአብሔር ቃል ሕይወታችንን መቆጣጠር አለበት። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲወጣ ብርሃን ይህንን ዓለም ትቶ ሄደ። ከዚያ በኋላ ጨረቃ (ቤተክርስቲያን) መጣች፤ የቤተክርስቲያንም ተልዕኮ የእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ማንጸባረቅ ነው። ቤተክርስቲያን የሰራችው ስሐተት ደግሞ እስከ አሁንም ድረስ የምትሰራው ስሕተት የራሳችንን ብርሃን የራሳችንን አመለካከት ማንጸባረቃችን ነው። ወይም ደግሞ የአንድ ታዋቂ ሰው አመለካከት እናንጸባርቃለን። ወይም ደግሞ የቤተክርስቲያናችንን ልማዶች እናንጸባርቃለን። እነዚህ ሁሉ አመለካከቶች በእግዚአብሔር ቃል ላይ እስካልተመሰረቱ ድረስ በሙሉ ጨለማ ናቸው። ጨረቃ የራሷ ብርሃን የላትም። ጨረቃ ማታ ማታ በጨለማ ለተዋጠው ዓለም የምታበራው የፀሃይን ብርሃን በማንጸባረቅ ነው። ለእኛ የተሰጠን ተልዕኮ የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል ማንጸባረቅ ብቻ ነው። ሌላ ምንም ተልዕኮ የለንም። በራሳችን ምንም ብርሃን የለንም፤ ስለዚህ ለሰው ልንጠቅም የምንችለው የእግዚአብሔር ብርሃን የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ስናንጸባርቅ ብቻ ነው።

አንድ የማስጠንቀቂያ ሃሳብ እናካፍላችሁ። ዓለም በፀሃይ (እግዚአብሔር) እና በጨረቃ (ቤተክርስቲያን) መካከል ስትገባ የመሬት ጥላ ጨረቃን ያጨልማታል፤ የዛኔ የጨረቃ ግርዶሽ ተፈጠረ እንላለን። ስለዚህ ዓለማዊነት የክርስቲያኖችን ምስክርነት ያጨልመዋል፤ ክርስቲያኖች ግን በዓለማዊ ፋሽን እና ዓለማዊ ትርፍ ላይ ከማተኮር ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል ማንጸባረቅ አለባቸው።

 

 

ዘፍጥረት 1፡17 እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤

እግዚአብሔር ወደ መንግስተ ሰማያት የሚያስገባውን መንገድ ያሳየን ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን ብርሃን አድርጎ ሰጥቶናል። እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን የመሰረታት ክርስቲያኖች በንግግራቸውም ሆነ በአኗኗራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ብርሃን ለሌሎች እንዲያንጸባርቁ ነው።
እንደ አለመታደል ሆኖ ጨረቃ በወር ውስጥ የተወሰኑ ቀናት የምታንጸባርቀው ብርሃን ድምቀቱ እየቀነሰ እየደበዘዘ የሚሄድበት ወቅት አሉ። ችግሩ ከኢየሱስ አይደለም። የክርስትና ሕይወት ምስክርነታችን እየደበዘዘ ሲሄድ ተጠያቂዋ ቤተክርስቲያን ናት።

ማርቆስ 4፡16 እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥

17 ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ።

18 በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥

19 የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል።

 

ክርስቲያኖች ጊዜያዊ በሆነው በዚህ ምድር ሕይወት ጥቅመፐች ላይ ትኩረት ያበዛሉ፤ ከዚህም የተነሳ የዳኑ ጊዜ ለእግዚአብሔር የነበራቸውን የቀደመ ፍቅር ይጥላሉ። ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች ልባቸው ገንዘብ እና ብልጽግና ላይ ነው።

1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡5 አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ።

 

ሰዎች የስግብግብነት ወንጌል በቀላሉ ይማርካቸዋል። እርሱም የብልጽግን ወንጌል ነው።

ዘፍጥረት 1፡18 በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።

የእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛውን መንገድ ይነግረናል (መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው ቃል እንደ ፀሃይ ብርሃን ነው)፤ ደግሞም ትክክል ያልሆነውንም መንገድ ያሳየናል (መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈ ነገር ሁሉ ለሰዎች አሳማኝና ትክክለኛ ቢመስልም መንፈሳዊ ጨለማ ነው)።

ለምሳሌ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሮማ ካቶሊክ ተከታይ የሆነችዋን ፖላንድ ኮምዩኒዝም ተቆጣጥሯት ስለነበረ ሕዝቡ በድሕነት ተሰቃዩ፤ እንደዚያም ሆኖ ግን በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸው እምነት ጠንካራ ነበረ። አብዛኞቹ የፖላንድ ነዋሪዎች ካቶሊክ አማኞች ሲሆኑ ፖላንድ ፖላንድ ውስጥ የኮምዩኒስት መንግስትን በመገልበጥ ሂደት ውስጥ ፖፕ ጆን ዳግማዊ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። የኮምዪኒስት መንግስት በመውደቁ ለጊዜው ችግሮችን የተፈቱ ይመስል ነበር። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖችን ከኮምዩኒዝም ቀምበር ስላላቀቀቻቸው ለሕዝቡ ትልቅ ድል ይመስል ነበር። ኋላ ግን ወዲያው የፖላንድ ሕዝብ ከአሜሪካ የመጣውን ለገንዘብ የመሯሯጥ ሃሳብ ሰፍ ብለው ተንጋግተው ሲቀበሉ ባየች ጊዜ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታላቅ ድንጋጤ ነው የሆነባት። ሕዝቡ ለገንዘብ ሲስገበገቡ የብዙዎቻቸው እምነት ቀዘቀዘ። ስለዚህ አሁን ብዙዎቹ የፖላንድ ሕዝቦች መንፈሳዊ ሕይወታቸው ወርዷል፤ ከበፊቱም ይልቅ ከእግዚአብሔር ርቀዋል ብላ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትፈራለች።

ስለዚህ በጊዜው ፖለቲካ እና ሐይማኖትን መቀላቀል ለሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መልካማ መስሎ ታይቷት ነበር፤ ነገር ግን ኋላ ስታየው ምንም መልካም ውጤት አላስገኘም።

ምንጊዜም ቢሆን ፖለቲካ እና ሐይማኖት ሲቀላቀሉ የሚያስገኙት ውጤቱ ሞት ብቻ ነው።

ባለፈው ክፍለ ዘመን አየርላንድ ውስጥ ሲፈጸም የነበረውን የፕሮቴስታንት እና ካቶሊክ ግጭት ተመልከቱ።

የአይሲስ እና ሌሎች ሙስሊም ተዋጊዎች የሚፈጽሟቸውን ዘግናኝ ግፍ ተመልከቱ።

 

እግዚአብሔር ምንጊዜም በምድር ላይ የሕይወትን ዘር የሚያበቅልበትን ቀጣይ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት 1,000 ዓመታት ጠብቋል።

 

ስለ ቀን በተደረገው ገለጻ ውስጥ ሌሊት የሌለው ለምንድነው?

 

“ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ” የሚለው ቃል ሙሽራይቱ የታላቁ መከራ ጨለማ በምድር ላይ በሚያጠላበት ሌሊት ውስት አታልፍም ማለት ነው።

ዘፍጥረት 1፡19 ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።

ሌሊት አልተጠቀሰም። ስለዚህ ሌሊትን ባለመጥቀስ እግዚአብሔር ምን ሊነግረን እየሞከረ ነው?
የሌሊቱ ጨለማ በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን (በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን) መጠናቀቂያ ላይ ለሚመጣው የ3.5 ዓመታት ታላቅ መከራ ምሳሌ ነው። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ሙሽራይቱን ለሰርግ ግብዓ ወደ ሰማይ ይወስዳታል። ኢየሱስ ብርሃን ስለሆነ ብርሃን በምድር ላይ በሌለ ጊዜ ምድርን ጨለማ ይወርሳታል።

ዮሐንስ 9፡4 ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች።

ሕይወት ምድርን ለቆ ሲሄድ ሞት እንደ ፈረሰኛ እየጋለበ ወደ ታላቁ መከራ ይመጣል።
ቀን ብርሃንን ይወክላል። ሌሊት ሞትን ይወክላል።

ራዕይ 6፡8 አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።

ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ በሚለው ቃል ውስጥ ጠዋቱ ኢየሱስ ከሙሽራይቱ ጋር ሆኖ በምድር ላይ የሚገዛበትን የ1,000 ዓመት የሰላም መንግስት ነው። (ሒትለት የመሰረተው መንግስት ለ1,000 ዓመታት እንደሚገዛ ተናግሮ ነበር፤ ነገር ግን ከ12 ዓመታት በላይ አልዘለቀም። ስለ 1,000 ዓመት መንግስት ሲናገር ማንን እየኮረጀ እንደሆነ መገመት አያቅታችሁም።)

ማታ የሚለው ቃል የሚወክለው የሰባተኛውን ቤተክርስቲያን ዘመን ማለቂያ ማለትም ልክ ታላቁ መከራ ከሚጀምርበት ዘመን በፊት ያለውን ጊዜ ነው፤ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ሙሉ ብርሃን በምድር ላይ እንደገና በሙላት ያበራል። ማርቲን ሉተር የጽድቅ እና በእምነት የመዳን እውነት ተመልሶ እንዲመጣ አደረገ። ዌስሊ ከሐጥያት ተለይቶ የመኖርን የቅድስና ትምሕርት መልሶ አመጣ። ጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትንና መለኮታዊ ስጦታዎችን መቀበልን መልሶ አመጣ። ከዚያ በኋላ ያስፈለገን የእግዚብሔርን ቃል እውነት ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ የሚያመጣ ነብይ ነው።

ዛሬ በክርስትና ውስጥ 160 የተለያዩ ጎራዎች አሉ። ከነዚህ ጎራዎች ውስጥ የወጡ 45,000 ዓይነት የተለያዩ ዲኖሚኔሽናዊ እና ዲኖሚኔሽናዊ ያልሆኑ ቤተክርስቲያኖች አሉ፤ እነዚህ ሁሉ የየራሳቸው የተለያየ እምነት አላቸው።

በአሁኑ ሰዓት በእንግሊዝኛ ብቻ ከመቶ በላይ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ።

እያንዳንዱ ክርስቲያን በየራሱ ቤተክርስቲያን ተሸሽጎ ትክክለኛው እምነት ውስጥ እንደሆነ አድርጎ ያስባል። ነገር ግን አንዳቸው ከሌላቸው ልዩነት ያላቸው 45,000 ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ ከክርስቲያኖች መካከል ብዙዎቹ እምነታቸው የተሳሳተ መሆኑን ባለማወቃቸው የተሳ አንድ ቀን ማፈራቸው አይቀርም። ልዩ ልዩ አመለካከቶች እጅግ ከመብዛታቸው የተነሳ የትኛው ትክክል መሆኑን እንኳ ለይቶ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነገር ሆኗል። እውነትን ከእግዚአብሔ ቃል ገልጦ የሚያሳየን የዘመን መጨረሻ ነብይ ያስፈልገናል። ቤተክርስቲያኖች እንኳ እጅግ በጣም ከመከፋፈላቸው የተነሳ ይህንን ዓይነቱን እገዛ ሊያደርጉልን አይችሉም።

ወደ ሁለት እግሮች እና አስር ጣቶች እንደተከፋፈለው እንደ ዳንኤል ምስል የአሕዛብ ቤተክርስቲያን እምነቶች በልዩነታቸው ከቁጥር በላይ ተባዝተዋል።

እምነታቸው ትክክለኛ መሆኑን እንዴት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ እንደሚችሉ እርግጠኛ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ከእነርሱ ጋር የማይስማማ ሰውን ሁሉ መዝጋትና አለማናገር አለማዳመጥ ይመርጣሉ።

ዳንኤል በራዕይ ያየው የአሕዛብ ምስል የ2,000 ዓመታት የአሕዛብ ቤተክርስቲያንን ታሪክ ይወክላል።

 

 

ዋነኞቹ መንፈሳዊ ስጦታዎች ጥበብ እና እውቀት ናቸው። ዋነኛዎቹ ስጦታዎች አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ወይም ምሳሌ ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ እና በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ጥቅሶችን አንድ ሃሳብ እንዲገልጡ እንዲሁም ጠለቅ ያለ መረዳት እንዲያካፍሉ የማገናኘት ጥበብ ናቸው።

ስለዚህ ክርስቲያኖች አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ምን ማለት እንደሆነ የግል አመለካከታቸውን ከመናገር ይልቅ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አማካኝነት መፍታት ማብራራት መቻል አለባቸው።

1ኛ ቆሮንቶስ 12፡7 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል።

8 ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥

9 ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥

10 ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤

11 ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።

ተዓምራት አስደናቂ ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ከተዓምራትም በላይ ለጥበብ እና ለእውቀት ቅድሚያ ይሰጣል።

ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ከሁሉ በፊት ያስፈልገናል ብሎ የሚያስበው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፤ በተለይ ደግሞ በትንቢት ቃል ውስጥ ያሉት ምሳሌዎች ምን ማለት እንደሆኑ መረዳት። መጽሐፍ ቅዱስን የማናውቅ ከሆነ በቀላሉ እንታለላለን፤ በተለይም የዓለም ሁኔታ ነውጥ ሲበዛበት፣ ቤተክርስቲያኖች እና ፖለቲከኞች መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረን አመለካከት ይዘው ሲቆሙ መጽሐፍ ቅዱስን የማናውቅ ከሆነ በቀላሉ ይሸነግሉናል።

ስለዚህ ሙሽራይቱ የሐዋርያትን አስተምሕሮ ወደታዘዘችው ወደ መጀመሪያይቱ የቤተክርስቲያን ዘመን ትምሕርቶች ስትመለስ በማታ ብርሃን ይኖራል።

ዘካርያስ 14፡7 አንድ ቀንም ይሆናል፥ እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ይሆናል፤ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል

 

ራዕይ 10፡7 ወደ ፊት አይዘገይም፥ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥

 

ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል አለ።

ስለዚህ የእግዚአብሔር ሚስጥር የሚገለጠው በሰባተኛው ወይም በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ሙሽራይቱ በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ወደነበረው እምነት ስትመለስ ነው።

ይህ ማታ የተባለው ሰዓት የሚመጣው ልክ የታላቁ መከራ ጨለማ ከመምጣቱ በፊት ነው።

ከዚያም እግዚአብሔር ሌሊቱን (የ3.5 ዓመቱን ታላቅ መከራ) ሳይጠቅስ በቀጥታ ወደ ጥዋት ያልፋል (ይህም አዳም ሊገባበት ያልቻለው የ1,000 ዓመት የሰላም መንግስት ሲሆን በዚህ መንግስት ውስጥ ኢየሱስ በምድር ላይ ይነግሳል)።

ይህም እውነተኛዋ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን 3½ ዓመታት በሚፈጀው ታላቅ መከራ ውስጥ አታልፍም ማለት ነው። እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ጨለማውን አታየውም፤ ምክንያቱም በነዚያ 3½ ዓመታት ውስጥ በሰማይ ወደተዘጋጀው የሰርግ እራት ግብዣ ሄዳ በዚያ ትቆያለች፤ በዚያም ሌሊት የለም፤ ጨለማ የለም፤ ሐጥያትም የለም።

ስለዚህ የክርስቶስ ሙሽራ በአሰቃቂው ታላቅ መከራ ውስጥ አታልፍም።

እግዚአብሔር የፈጠረውን ሕይወት በምድር ላይ ለማኖር በወሰነ ጊዜ በ7-የእግዚብሔር ቀናት ውስጥ ማለትም በሰዎች አቆጣጠር በ7,000 ዓመታት ውስጥ ሊያከናውን ወሰነ። እስከ ስድስተኛው ቀን ድረስ ሰዎች አልነበሩም፤ ስለዚህ ሰዎች የሚቆጥሩትን ቀን መጠቀም አላስፈለገም።

ስለዚህ በ6,000 ዓመታት ውስጥ አንዳችም ሕይወት የሌለባትን ፕላኔት እግዚአብሔር ገነት አድርጎ ሰራት። ከዚያም 7ኛው ቀን የእግዚአብሔር ልጅ አዳም እና ሚስቱ ምድርን ለ1,000 ዓመታት እንዲገዙ ተብሎ የተዘጋጀ ቀን ነበረ። ነገር ግን 1,000 ዓመታት በሚፈጀው በሰባተኛው ቀን ውስጥ ሴቲቱ እግዚአብሔር ባዘጋጀው እቅድ በመሰላቸት እግዚአብሔር ከተናገረው የተለየ አጓጊ ትምሕርት ሰማች። ዓይኖቿን ከእግዚአብሔር ቃል ላይ አነሳች፤ ሐጥያትም ወደ ዓለም ገባ፤ ሰይጣን ዓለምን ተቆጣጠረ።

 

 

 

ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ካበላሸበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ምድርን ለ6,000 ዓመታት ገዝቷል፤ ውብ የሆነውን የኤደን ገነት ወደ ነፍስ ግድያ ቀጠና ለውጠታል፤ ባለፈው ክፍለ ዘመን ብቻ በሰዎች ጥላቻ የተፈጠሩ ጦርነቶች ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች እልቂት ምክንያት ሆነዋል። ዛሬ ሰዎች በቸልተኝነት የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል ምንም እንደማይጠቅም ሁሉ ጣል ጣል ያደርጉታል። ብናውቀውስ ምን ይጠቅመናል? ይላሉ። በራሳቸው ለሁሉ ነገር ብቁ የሆኑ ይመስል ምንም እንደማያስፈልጋቸው፣ ምንም ዓይነት እርማት እንደማያሻቸው ያስባሉ። ከዚህ ሁሉ ቅዠታቸው የሚነቁት እንደ ደራሽ ውሃ በድንገት የ3.5 ዓመቱ ታላቅ መከራ ሲመጣባቸውና ዓለምን እንደ መንፈሳዊ ሱናሚ እያናወጠ ሁሉን ነገር ሲደመስስ ነው። ዓለም ግን የምትጠፋው በኖህ ጊዜ እንደሆነው በውሃ ሳይሆን በዕሳት ማዕበል ነው።

 

2ኛ ጴጥሮስ 3፡10 የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።

 

ይህ የሰው ዘመን ነው። ስለዚህ የፈለጋችሁትን የማድረግ ነጻነት አላችሁ። እግዚአብሔርን ማመን ትችላላችሁ፤ እግዚአብሔርን ቸል ማለት ትችላላችሁ። ነጻ ፈቃድ ተሰጥቷችኋል።

የታላቁ መከራ ዘመን ደግሞ የእግዚአብሔር ቀን ስለሆነ በዚያ ጊዜ እግዚአብሔር ምድርን ለመጪው የሺ ዓመት መንግስት ለማንጻት በሐጥያተኞች ላይ እንደፈለገ ያደርጋል።

በታላቁ መከራ ዘመን ማለቂያ ኢየሱስ ክፋትን ሙሉ በሙሉ ይደመስሳል።

ከዚያ በኋላ የራሱን የሺ ዓመት መንግስት ይመሰርታል። ስለዚህ የእግዚአብሐየር ልጅ ኢየሱስ እና እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ማለትም የኢየሱስ ሙሽራ በምድር ላይ ለ1,000 ዓመታት ይነግሳሉ፤ በዚህም እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ያሰበው ሰባተኛ ቀን ይፈጸማል፤ ይህ ሰባተኛ ቀን በመጀመሪያው የእግዚአብሔር ልጅ በአዳም እና በሚስቱ አልተፈጸመም ነበር።

 

ራዕይ 20፡4 ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ

 

ከዚህ የምንማረው ትምሕርት ሰይጣን የእግዚአብሔርን እቅድ እንደሚያበላሽና ሊያዘገይ እንደሚችል ነው፤ ነገር ግን ሰይጣን እግዚአብሔር እቅዱን እንዳይፈጽም ሊከለክለው አይችልም። በስተመጨረሻ አሸናፊው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለዚህ ከኢየሱስ ጋር መቆም ያዋጣል። በስተመጨረሻ እንደ ሰይጣን የሚሸነፍ ተጫዋችን መደጀፍ የሚፈልግ ማነው? ሁልጊዜ ብርሃን ጨለማን ያሸንፋል። ብርሃን ጨለማን ማጥፋት ይችላል፤ ጨለማ ግን ትንሽዋን ብርሃን እንኳ ሊያጠፋት አይችልም።

 

ሬድዮአክቲቭ የተባለው የዘመን መተመኛ ስልት የተሳሰተ ውጤት ሊሰጥ ይችላል

 

 

አሁን ደግሞ ሳይንቲስቶች በሬድዮ አክቲቭ የዘመን መለኪያ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የምድር ዕድሜ ስንት ዓመት መሆኑን የሚገምቱበትን ግምት እንመልከት።

ሬድዮ አክቲቭ የዘመን መለኪያ በብዙ መላ ምቶች (ግምቶች) ላይ የተመሰረተ ዘዴ ነው፤ ምክንያቱም ጥንታዊ ክስተቶች በተከሰቱ ጊዜ ማንም በዚያ ተገኝቶ የተመለከታቸው የለም። ለጊዜው የሬድዮ አክቲቭ የዘመን ስሌት ውስጥ ያሉ ችግሮችን ትተን በሬድዮ አክቲቭ ስሌት የተገኙ ጥቂት ውጤቶችን ብቻ እንመልከት።

አሜሪካ ውስጥ አንድ ተማሪ ሼልፊች የተባለ ጠንካራ ቅርፊት ያለው ዓሳ አጠመደና በዚያኑ ዕለት የዓሳውን ቅርፊት የሬድዮ አክቲቭ የዘመን ስሌት ማሽን ውስጥ አስገባው። ማሽኑም ዓሳው ከሞተ 2,300 ዓመታት ሆኖታል የሚል መልስ ሰጠው። ((M S Keith and G M Anderson 16 August 1963 Radiocarbon dating: fictitious results with mollusk shells in Science, ገጽ 634)

በ1991 ኬፕታውን ውስጥ የምትኖረዋ ወይዘሮ ጆዋን አሕረንስ በሥነ ጥበብ የትምሕርት ክፍለ ጊዜዋ ጥቂት የድንጋይ ላይ ስዕሎች ሳለች። የድንጋይ ላይ ስዕሎችዋን የአትክልት ቦታ ውስጥ ባስቀመጠችበት ሌቦች ሰረቁባትና ከከተማ ውጭ ሜዳ ላይ ጣሉዋቸው። ይህም ሜዳ ላይ የተገኘ የሃገር በቀል ጎሳዎች የኮይ ሳን ጥንታዊ የድንጋይ ላይ ስዕል የመጀመሪያ ምሳሌ ሆነ። የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲት ሬድዮካርበን የዘመን ስሌት ማሽን በዓለም ላይ ካሉ ማሽኖች ሁሉ እጅግ የተሻለ የሚባል ማሽን ነው። ሴትየዋ የሳለቻቸውን ስዕሎች በዚህ ማሽን ሲመረምሩ ስዕሎቹ 1,200 ዓመታት ሆኗቸዋል ተባለ። ስዕሎቹ ግን ከተሳሉ ገና 6 ወራቸው ነበር።

እንግዲህ በእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች እንዳየነው ናሙናዎቹ መች እንደተወሰዱ እናውቃለን፤ እንዲሁም የሬድዮ አክቲቭ የዘመን ስሌት ማሽኖችም የሰጡት ውጤት የተሳሳተ መሆኑን እናውቃለን። ወይዘሮ አሕረንስ የስዕሎቿን ፎቶ ጋዜጣ ላይ አየችና ተክክለኛ አመጣጣቸውን ተናገረች። እንዲህ ባይሆን ኖሮ የታሪክ ምሑራን ዛሬ ስለ ኮይ ሳን ሕዝብ እነርሱ ድንጋይ ላይ የሳሉት ስዕል ነው በተባለው ግኝት ላይ ተመስርተው የተሳሳት ግንዛቤ ይዘው በቀሩ ነበር።

ስለዚህ ስለ ሳይንስ የተማርነው አንድ ትምሕርት ይህ ነው፡- በሬድዮአክቲቭ የዘመን ስሌት የተገኘ ሳይንሳዊ ቀን አትመኑ ምክንያቱም ስሕተት ሊኖርበት ይችላል።

ሁለተኛው ችግር ደግሞ እንደሚከተለው ነው፡- አንዱ ናሙና እራሱ ብዙ ጊዜ ቢመረመር የተለያዩ ውጤቶችን ይሰጣል። ከዚያ ሳይንቲስቱ የራሱን ግምት (ይቅርታ ማለቴ ቲዎሪ) ይበልጥ የሚደግፍለትን ስሌት መርጦ ይጠቀማል።

በ1801 ዓ.ም ሐዋኢ ደሴት ውስጥ ሁዋላላይ የተባለ ቦታ ዕሳተ ገሞራ ፈነዳ። ከዕሳተ ገሞራው ከፈሰሰው የቀለጠ ዓለት የተለያዩ ናሙናዎች ተወስደው ሬድዮአክቲቭ ምርመራ ሲደረግባቸው የተገኙት ውጤቶች ከ160 ሚሊዮን ዓመታት ጀምሮ እስከ 3,000 ሚሊዮን ዓመታት ድረስ ነበሩ። ሰዎች የዕሳተ ገሞራውን ፍንዳት ጽፈው ስላስቀመጡ ክስተቱ ምስክር የሚሆኑ ሰዎች በቦታው ነበሩት። ስለዚህ ከ200 ዓመታት የማይበልጥ ዕድሜ ያለው የዕሳተ ገሞራ ፍንዳታ ላይ የተደረገው የሬድዮአክቲቭ የዘመን ስሌት ውጤቱ በጣም የተሳሳተ ነበረ።

ሐዋኢ ውስጥ እስካሁን ድረስ ከኪላዉያ ከሚፈነዳው ዕሳተ ገሞራ የሚጣው የቀለጠ ዓለት ወደ ባሕር ውስጥ ይፈስሳል። በአንድ ቀን ከፈሰሰው የቀለጠ ዓለት ከባሕር ወለል ላይ የተወሰደ ናሙና በዚያው ቀን በምድር ላይ ከፈሰሰው የቀለጠ ዓለት ላይ ከተወሰደ ናሙና ጋር በሬድዮአክቲቭ ስሌት ሲለካ ከባሕር ወለል ላይ የተወሰደው ናሙና በ22 ሚሊዮን ዓመታት ቅድሚያ አሳየ። ነገር ግን ናሙናው በቅርብ ከፈሰሰ ዓለት ላይ የተወሰደ ነበር። ስለዚህ የውቅያኖሱ ጥልቀት የምርመራውን ውጤት ይቀይረዋል ማለት ነው። ይህ የዘመን ስሌት ብዙ ችግር አለበት።

ሳይንቲስቶች አንዱን ናሙና በዩራንየም ሊድ እና በፖታሲየም አርገን የዘመን ስሌት ዘዴዎች ሲመረምሩ የሚገኙት የዕድሜ ውጤቶች አብዛኛውን ጊዜ የ45% ልዩነት ያሳያሉ።

ይህንን የዕድሜ ምርመራ ቴክኒክ ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርገው ደግሞ ቅሪተ አካላት በዝቃጭ ዓለቶች ውስጥ መገኘታቸውና እነዚህ ዓለቶች ደግሞ በሬድዮአክቲቭ ዘዴ ሊለኩ የማይችሉ መሆናቸው ነው።

ስለዚህ የቅሪተ አካላቱን ዕድሜ በተዘዋዋሪ መንገድ ለመለካት ተጨማሪ የግምት ሥራ መስራት ይጠይቃል።
ቀጥተኛ የሆነው ሬድዮአክቲቭ ስሌት እራሱ ምን ያህል የተሳሳተ ዘዴ መሆኑን አስቀድመን አይተናል። ደግሞ በዚህ ላይ ቀጥተኛ ያልሆኑ ግምቶችና መላ ምቶች ሲጨመሩበት ምን ያህል ብዙ ስሕተት እንደሚፈጠር አስቡ።

ለምሳሌ በ1922 ሃሮልድ ኩክ የተባለ ጂዮሎጂስት ነብራስካ ውስጥ የጥርስ ቅሪተ አካል አገኘ። የአሜሪካ ናቹራል ሒስትሪ ሙዜም ሃላፊ የሆነው ሔንሪ ፌየርፊልድ ኦስቦርን በተገኘው የጥርስ ቅሪተ አካል ውስጥ ሰውንም ጦጣንም የሚመስሉ ገጽታዎችን ተመለከተ። በዚህም “ጠፍቶ የነበረው” የሰውን ዘር ከጦጣዎች ዝርያ ጋር የሚያገናኘው ሰንሰለት ማለትም ሰው-ጦጣ ተገኘ ተባለ።

ነገር ግን ትክክለኛው “የጠፋው አገናኝ” እባቡ ነበረ፤ ምክንያቱም እባቡ አውሬ ነበረ እንጂ በደረቱ የሚሳብ እንስሳ አልነበረም፤ ስለዚህ ከሰው ጋር መነጋገርና መከራከር የሚችል ከእንስሳት ሁሉ በላይ የሆነ እንስሳ ነበረ። ከዚያም እግዚአብሔር እባቡን ረገመውና በደረቱ የሚሳብ ፍጥረት አደረገው። ከዚህም የተነሳ እባቡ መጀመሪያ የነበሩት አጥንቶች ጠፍተው በደረቱ ወደሚሳብ እንስሳ ከተለወጠ በኋላ ያሉት አጥንቶች ብቻ ቀሩ። በዚህም ምክንያት ሳይንስ “የጠፋውን አገናኝ” በተመለከተ መቸም ቢሆን መቸ ማስረጃ አያገኝም።

ሆኖም ከዚህ የጥርስ ቅሪተ አካል ተነስተው ሄስፐሮፒቲከስ የተባለ የሚገርም ስም ያለው ሰው ጦጣ ፈጠሩ። ከጥርሱ ብቻ ተነስተው የፊቱን ቅርጽ፣ ከንፈሮቹ ምን ያህል እንደነበሩ፣ ገላው በሙሉ በፀጉር የተሸፈነ እንደነበረ፣ እንዲሁም ምንም ልብስ የማይለብስ እንደነበረ ሁሉ አወቁ። ያላቸው ብቸኛ ማስረጃ አንድ ያረጀ ጥርስ ብቻ ሆኖ ሳለ ከዚያ ተነስተው ይህንን ሁሉ ማወቅ መቻላቸው እጅግ በጣም አስደናቂ ነው። ሳይንቲስቶች የሚሰሩት ትልቅ ስሕተት ምናባቸውን ካገኙት መረጃ በላይ ለጥጠው መጠቀማቸው ነው። ይህን የሚያደርጉት በተለይ አንድ “ማረጋገጥ” የሚፈልጉት ቲዎሪ ሲኖራቸው ነው።

ይህ ሰው ጦጣ በ1925 ቴነሲ ፍርድ ቤት ውስጥ በቀረበው ክስ ላይ ለኤቮልዩሽን ማስረጃ እንዲሆን ቀርቧል። እስኮፕስ የተባለ ሰውዬ ትምሕርት ቤት ውስጥ ባዮሎጂ አስተማሪ ነበረ፤ ይህ ሰው በሕግ ሳይፈቀድለት ክፍል ውስጥ ስለ ኤቮልዩሽን አስተማረ። ኦስቦርን ትምሕርት ቤቶች ስለ ኤቮልዩሽን እንዲያስተምሩ የተቻለውን ያህል ጥረት እያደረገ ነበር። እነ ኦስቦርን ይዘው የመጡትን አስደናቂ እውቀት ጠበቃዎች ለክርክር ተጠቀሙበትን እስኮፕስ ነጻ ሆኖ ተለቀቀ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ኩክ የመጀመሪያውን የጥርስ ቅሪተ አካል ያገኘበት ቦታ የአሜሪካ ሙዜም ጠለቅ ያለ ቁፋሮ አደረገና እሱኑ የመሳሰሉ ተጨማሪ ጥርሶች አገኘ፤ እነዚህ ጥርሶች ግን ከባለቤታቸው መንጋጭላ ጋር ተያይዘው ነበር የተገኙት፤ እርሱም ዝርያው የጠፋ አሳማ ሆኖ ተገኘ!
እነዚህ ምሳሌዎች ሳይንቲስቶች ስለ ጥንታዊ ግኝቶች የሚሰጧቸው ትርጓሜዎች ሁሌ ትክክል ሊሆኑ እንደማይችሉ ያስረዷችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

 

ስለ ዓለም መፈጠር ስታስቡ በጣም ረጅም ዘመናትን ልትገምቱ ትችላላችሁ።

ነገር ግን ይህንን ግምታችሁን ሕይወት ላለው ፍጡር ልትጠቀሙት አትችሉም ምክንያቱም ሕይወት ያለው ነገር አልተፈረም ነበር።

ሳይንቲስቶች እጅግ በጣም ጥንታዊ የሆኑት ቅሪተ አካላት የሚገኙባቸው ዓለቶች ካምብሪያን ንጣፍ ይባላሉ ይላሉ። ከእነርሱ ቀጥሎ የሚገኘው ሳንድስቶን ኦርዶቪሺያን ንጣፍ ዓለት ሲሆን እርሱም 450 ሚሊዮን ዓመታት ሆኖታል ይላሉ። ቴክሳስ ውስጥ ለንደን የተባለ ከተማ በተደረገ የምርምር ቁፋሮ የኦርዶቪሺያን ሳንድስቶን ስባሪ ውስጡ ከብረት የተሰራ የመዶሻ ጭንቅላት ተቀርቅሮበት ተገኘ። ከሳንድስቶን ዓለቱ ውስጥ ከእንጨት የተሰራ የመዶሻው እጀታም ተገኘ። ከእንጨት የተሰራው እጀታ በከፊል ወደ ድንጋይ ከሰልነት ተለውጦ ነበር። ዛፎች በአዝጋሚ ለውጥ ብዙ ሚሊዮን ዓመታት ካለፉ በኋላ ካርቦኒፈረስ በተባለው ዘመን ከ300 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ነበር ተፈጠሩ ተብሎ የሚታሰበው። በምድር ላይ ከብረት የመዶሻ ጭንቅላት መስራት የሚችለው ብቸኛ ፍጡር ሰው ነው። ስለዚህ ሰዎችና ዛፎች ኦርዶቪሺያን በሚሉት ጥንታዊ ዘመን ውስጥም ነበሩ ማለት ነው።

ይህ የሚያመለክተው ቅሪተ አካላት እንዴት እንደሚፈጠሩ እንደማናውቅ ነው።

የትኛውም ሳይንቲስት ቤተሙከራ ውስጥ ቅሪተ አካል አዘጋጅቶ አያውቅም፤ ምክንያቱም አንድ ሕይወት ያለው ፍጡር ሲሞት ወደ ቅሪተ አካልነት ከመለወጡ በፊት በባክቴሪያ በሌሎች ሕዋሳት አማካኝነት በስብሶ ይጠፋል። ለቅሪተ አካላት የሚሰጧቸው እጅግ ረጃጅም ዕድሜዎች በጣም አሳሳች ናቸው። ሰው ያን በሚያህል ረጅም ዘመን በምድር ላይ አልነበረም። ሳይንቲስቶች ለቅሪተ አካላት የሚሰጡዋቸው ትርጓሜዎች በጣም የተሳሳቱ ናቸው።

ሮሜ 5፡12 ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤

ሞት ወደ ምድር የገባው አዳም ሐጥያት የሰራ ጊዜ ነው። አዳም ሐጥያት ከመስራቱ በፊት ሞት አልነበረም። እጽዋት እና እንስሳት ሐጥያት መስራት አይችሉም፤ ስለዚህ አዳም ሐጥያት ከመስራቱ በፊት እንስሳት እና እጽዋት አይሞቱም ነበር።

በኖኅ የጥፋት ውሃ ዘመን የተፈጠሩ ቅሪተ አካላት አሉ። የአሸዋ፣ የድንጋይና የዓለቶች፣ እንዲሁም የሞቱ እጽዋትና እንስሳት ቅሪተ አካላት ምድርን ባልጥለቀለቃት ጎርፍ ስር በተለያዩ ንጣፎች ተቀምጠው ምድር ላይ ተኝቶባት ተራሮችን ሁሉ ሸፍኖ በነበረው ብዙ ውሃ ክብደት አማካኝነት ተደፍጥጠዋል። ስለዚህ ከምድር ገጽ በላይ በጣም ብዙ ኪሎሚትር ጥልቀት ያለው ውሃ ነበረ።

ዘፍጥረት 7፡19 እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው፥ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።

20 ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ።

ሳይንቲስቶች እንዲህ ዓይነት ነገሮችን አይተው አያውቁም። ዛሬ ቅሪተ አካላትን መፍጠር የማንችልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

የኮዊላካንዝ ዓሳ ቅሪተ አካል ዕድሜው 60 ሚሊዮን ዓመት ነው ይላሉ። ይህ ዓሳ ትንንሽ እግሮች ስለነበሩት ከባሕር ወጥቶ ምድር ላይ መሄድ ይችል ነበር ይላሉ። ሆኖም ግን ልክ ቅሪተ አካሉን የሚመስል አሁን በሕይወት ያለ ኮዊላካንዝ ዓሳ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ኢስት ለንደን የተባለ ቦታ በ1938 ዓ.ም ተጠምዶ ተይዞ ነበር። ሳይንቲስቶቹ በገመቱት 60 ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ አንዳችም ለውጥ አልታየም። ይህም ለኤቮልዩሽን ቲዎሪ ትልቅ ኪሳራ ነው። ዛሬ ኮዊላካንዝ የተባለው ዓሳ በጥልቅ ባሕር ውስጥ ብቻ ነው የሚገኘው። ከባሕር በላይ ከወጣ ይሞታል። ስለዚህ ወደ ምድር ላይ ወጥቶ ሄዶ አያውቅም።

ፍራፍሬዎች ላይ የሚቀመጡ ዝንቦች በሁለት ሳምንት ውስጥ መራባት ይችላሉ። ቤተሙከራዎች ውስጥ ብዙ ሺ የፍራፍሬ ዝንቦች በተለያዩ ዝርያዎች ተራብተዋል። ነገር ግን ሁልጊዜም ቢሆን የፍራፍሬ ዝንቦች ሆነው ቀርተዋል።

ሰው ውሻዎችን አዳቅሎ አዳቅሎ ብዙ ልዩ ልዩ ቀለም፣ መጠን እና ቅርጽ ያላቸው የውሻ ዝርያዎችን አግኝቷል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የውሻ ዓይነቶች ቢባዙም እንኳ ከውሻነት አልፈው መሄድ አልቻሉም።

ኢኮሊ የተባለው ባክቴሪያ 30,000 ትውልዶቹ ተጠንተዋል (ይህ ከሰው የ1 ሚሊዮን ዓመታት ታሪክ ጋር እኩል ነው)፤ ግን እስካሁን ድረስ ኢኮሊ ባክቴሪያ ናቸው ወይም ትንሽ ለውጥ ያላቸው ኢኮሊ ባክቴሪያ ወይም ትንሽ የተጎዲ ኢኮሊ ባክቴሪያ ናቸው፤ እነዚህ ጥቂት ለውጦች የተገኙባቸው አካላቸው የሚገነባበትን አርኤንኤ የማዘጋጀት ችሎታቸውን በመጣላቸው ነው።

ማይክል ቤሂ የተባለ ባዮኬሚስት ይህንን ክስተት ዲቮልዩሽን ይለዋል፤ ማለትም የኤቮልዩሽን ተቃራኒ ነው። ስለዚህ በአንድ ዝርያ ውስጥ ጥቂት ለውጦች ሊገኙ ይችላሉ፤ ነገር ግን የትኛውም ፍጥረት ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ ፍጥረትነት አይቀየርም። ባክቴሪያዎቹ ወደ ፍራፍሬ ዝንብነት አልተለወጡም።

ከነዚህ ምሳሌዎች እንዳየነው የኤቮልዩሽን ሳይንሳዊ ቲዎሪ ፍጹም አይደለም። አንዳንድ በግልጽ አይተን የምናውቃቸው ነገሮች ላይ ትልቅ ስሕተት ይሰራል። ስለዚህ መደ መጽሐፍ ቅዱስ መመለስ ይሻላል።

እግዚአብሔር ፀሃይን፣ ጨረቃን፣ እና ከዋክብትን ፈጠረ፤ እነዚህን በአንድነት ሰማይ ወይም ሕዋ እንላቸዋለን።
ሕዋ እኛ በዓይናችን ማየት የማንችለው በሌላ ቀጠና የሚገኘው የእግዚአብሔር መኖሪያ ሰማይ አይደለም።
ሕዋ የሚያመለክተው በጣም ሰፊ የሆነውን መላእክት የሚኖሩበትንና የዳኑ ሰዎች ሲሞቱ ነፍሳቸው የሚሄድበትን መንፈሳዊ ሰማይ አመልካች ነው።

 

በመጀመሪያ ምንም ነገር አልነበረም።

አንድም ቁስ ወይም ኤነርጂ አልነበረም።

ምንም ነገር ለመጀመር ወይም ለመስራት የሚሆን እንደ ጥሬ እቃ ሊያገለግል የሚችል ነገር እንኳ አልነበረም። ስለዚህ “መፍጠር” የሚለው ቃል ከምንም ነገር አንድ ነገር መስራት ማለት ነው። ይህን ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ፍጥረትን ለማስረዳት ሳይንቲስቶች አንድ ኃይል ወይም ኤነርጂ ነበረ ይላሉ። ኤነርጂ ግን ሊፈጠር አይችልም።

ሳይንቲስቶች ኤነርጂ ምን እንደሆነ እንዲሁም ኤነርጂ ከየት እንደመጣ ሊነግሩን አይችሉም።

እግዚአብሔር ብቻ ነው ኤነርጂንና ቁስን ምንም ነገር እንደ ግብአት ሳይጠቀም መፍጠር የሚችለው። ኢየሱስ አምስት እንደራ እና ሁለት ዓሳ ተጠቅሞ 5,000 ሰዎችን ለማጥገብ የሚበቃ ምግብ ፈጠረ። ይህን ማድረግ የሚችል አንድም ሳይንቲስት የለም። ከፊዚክስ ሕጎች ውጭ መስራት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ደግሞም የፊዚክስ ሕጎችን የሰራው እግዚአብሔር ነው። ጊዜን የፈጠረው እግዚአብሔር ነው፤ ነገር ግን ከጊዜ ገደብ ውጭ መንቀሳቀስም ይችላል። እግዚአብሔር እራሱ በፈጠራቸው የተፈጥሮ ሕጎች አይታሰርም። እኛ ሰዎች ግን እግዚአብሔር ያዘጋጃቸው ሕጎች ይገድቡናል።

በአጭሩ ከዓለም መፈጠር በፊት ስለነበሩ ከስተቶች የሚጠየቁ ጥያቄዎች በአሁኑ ሰዓት ሳይንሳዊ ጥያቄዎች አይደሉም፤ ወደፊትም ብዙ የመሆን ዕድል የላቸውም። ይህ መግለጫ የተሰጠው ከኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ነው (http://curious.astro.cornell.edu/)።

 

እንዲህ ዓይነቱ መግለጫ የእውነተኛ ሳይንስ መታወቂያው ነው፤ እውነተኛ ሳይንስ መረጃዎችን ይተነትናንል እንጂ ባልተጨበጠ ነገር ላይ መላ ምቱ እንደ እውነት አደርጎ አያቀርብም።

 

ዩሮፓ ኦቭ ጁፒተር የተባለችዋ ጨረቃ ሃይድሮጅን እና ኦክስጅን ታመነጫለች

 

 

ዩሮፓ በተባለችዋ የጁፒተር ጨረቃ እና ኢንሴላደስ በተባለችዋ የሳተርን ጨረቃ ዙርያ ያሉ የሃይድሮጅን እና ኦክስጅን ጋዞች ላይ ጥናት ተደርጎባቸዋል።

እነዚህ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ናቸው። ዩሮፓ የተባለችዋ የጁፒተር ጨረቃ በበረዶ የተሸፈነች ናት። ጋሊሌዮ የተባለው መንኩራኩር ወደ ጁፒተር ሄዶ በ1995 በደረሰ ጊዜ ዩሮፓ የተባለችዋን ጨረቃ ከሸፈናት በረዶ ስር ጨዋማ ውሃ መኖሩን አረጋግጧል፤ ይህም ከበረዶው ሽፋን ስር ውቅያኖስ ሊኖር እንደሚችል ያመለክታል። በ2016 ሃብል የተባለው የጠፈር ቴሌስኮፕ ከዩሮፓ ላይ የሚነሱ የኦክስጅን እና ሃይድሮጅን ትነቶች ከመቶ ኪሎሜትር በላይ ወደ ሕዋ ውስጥ እንደሚበተኑ የሚያሳይ ፎቶግራፍ አንስቷል። ሃብል ቴሌስኮፕ የኦክስጅን እና ሃይድሮጅን ትነቶችን መለየት ስለሚችል ሳይንቲስቶች እነዚህ ትነቶች ውሃ ናቸው ብለው አመኑ። ስለዚህ አሁን አንድ የጠፈር መመራመሪያ ማሽን ልከው በትነቱ ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ትነቱ ውሃ መሆኑን ሊያረጋግጡ ይፈልጋሉ። ሕዋ ውስጥ ባለው የፀሃይ አልትራቫዮሌት ጨረር ምክንያት የውሃው ሞሎክዩሎች ወደተሰሩበት ኦክስጅን እና ሃይድሮጅን ጋዝ ሊነጣጠሉ ይችላሉ ብለው ያምናሉ።

ይህ ከጠፈር የተገኘ ማስረጃ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ያደረገውን ስናጠና ካገኘነው እውቀት ጋር ተመሳሳይ ነው፤ እግዚአብሔር መጀመሪያ ከጠፈር በታች ያለውን ውሃ እና ከጠፈር በላይ ያለውን ውሃ በለየ ጊዜ ከውሃ ሞለክዩል ውስጥ ሃይድሮጅን እና ኦክስጅንን በመለያየት በምድር ዙርያ ለምድር ከለላ የሚያደርግና ብርሃን የሚያሳልፍ የውሃ መጋረጃ አዘጋጅቷል።

በተጨማሪ ኢንሴላደስ የተባለችዋ የሳተርን ስድስተኛ ትልቅ ጨረቃ በንጹህ በረዶ የተሸፈነች ናት፤ እንዲሁም በሳተርን ዙርያ ተከትላ የምትሄድበት ምሕዋር (ቶረስ የሚባል) ውስጡ እንደ ቀፎ ባዶ የሆነ ቀለበት ነው፤ ይህም ቀለበት ከሃይድሮጅን እና ከኦክስጅን ጋዝ ነው የተሰራው። ስለዚህ እነዚህ ጋዞች ኢንሴላደስ የተባለችዋን ጨረቃ በርቀት የሚጋርድ ንጣፍ ሰርተዋል።

ስለዚህ ምድር ልክ እስከ አሁን ድረስ የበረዶ ኳሶች እንደሆኑት ዩሮፓ እና ኢንሴላደስ የተባሉ ጨረቃዎች ከመጀመሪያዋ በበረዶ የተሸፈነች ኳስ ከነበረች ከመጀመሪያው ከምድር በላይ በታላቅ ከፍታ የውሃ ግብዓቶች የሆኑት የሃይድሮጅን እና ኦክስጅን ጋዞች መገኘታቸው እንግዳ ነገር አይደለም።

ነገር ግን በምድር ላይ ያለው ከባቢ አየር በምድር ላይ ሕይወትን (ሰዎችን እና ሌሎች እንስሳትን) ለማኖር የተለያዩ ጋዞች በትክክለኛ መጠን ተመጥነው የተከማቹበት መሆን አለበት። ይህ በላይኛው ውሃ እና በታችኛው ውሃ መካከል ያለው ሥፍራ ከባቢ አየር ይባላል፤ እርሱም በትክክለኛ መጠን በተመጠኑ ጋዞች የተሞላ ነው፡- ስንተነፍስ ምግብ በሰውነታችን ሴሎች ውስጥ እንዲቃጠል የሚያደርግ 21% ኦክስጅን። ይህ የምግብ መቃጠል ሰውነታችን በ37 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዲሞቅ ያደርገዋል። ከባቢ አየር በ78% ናይትሮጅን የተሞላ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ኦክስጅንን እና ሌሎችን ነገሮች ሁሉ አረጋግቶ ለመቆጣጠር ነው፤ አለዚያ ኦክስጅን ሁሉን ነገር ከቁጥጥር ውጭ እየነደደ እንዲቃለጠል ያደርጋል። በ1967 አፖሎ 1 የተባለችዋ የጠፈር መንኩራኩር በውስጧ 100% የታመቀ ኦክስጅን ነበራት፤ ከዚህም የተነሳ በድንገት የተነሳ የእሳት ፍንጣሪ ያስከተለው ኃይለኛ እሳት ማንም ሰው ሳይደርስላቸው በውስጧ የነበሩ ሶስት የጠፈር ተመራማሪዎች ተቃጥለው እንዲሞቱ አድርጓል።

 

ከባቢ አየራችን በጣም ያረጀ ቢሆን ኖሮ ብዙ ሂልየም ይገኝበት ነበር

 

 

ከባቢ አየር ውስጥ ያለው ሂልየም በጣም ትንሽ ከመሆኑ የተነሳ ሊያረጅ አይችልም።

ከባቢ አየር ዕድሜው ምን ያህል ነው?

የሬድዮአክቲቭ ካርቦን (ወይም ካርቦን ዴቲንግ) የተባለውን የዕድሜ መለኪያ ማሽን የፈጠረው የኖቤል ተሸላሚ የሆነው ፕሮፌሰር ሊቢ ነው። አንድ የናይትሮጅን አተም ኑክሊየሱ ውስጥ 7 ፕሮቶኖች እና 7 ኒውትሮኖች አሉት። ሕዋ ውስጥ ከሩቅ የመጣ ኒውትሮን እንደ ጨረር ሲመታው ከኑክሊየስ ውስጥ ፕሮቶኑ አየር ላይ ተገፍትሮ ይወጣና ከዚያ ኒውትሮኑ የፕሮቶኑ ቦታ ላይ ይቀመጣል። ከዚህም የተነሳ አተሙ 6 ፕሮቶን ይኖረውና የካርበን አተም ይሆናል። 8ቱ ኒውትሮኖች ለካርበን በጣም ይበዙበታል ምክንያቱም ካርበን ብዙውን ጊዜ 6 ኒውትሮን እና 6 ፕሮቶን ነው የሚይዘው። ይህንን ካርበን-14 እንለዋለን። ከስምንቱ ኒውትሮኖች መካከል አንዱ ውስብስብ በሆነ ሂደት ውስጥ አልፎ ነገቲቭ ቻርጅ ያለውን አንድ ኤሌክትሮን አስፈንጥሮ ያስወጣል፤ ይህንንም በማድረጉ እራሱን ወደ ፕሮቶን ይለውጣል። ከውስጡ ፓርቲክሎችን የሚያስወጣ አተም ሬድዮአክቲብቭ ይባላል። አሁን 7 ፕሮቶን አሉ (ኑክሊየስ ውስጥ ደግሞ 7 ኒውትሮን) ስለዚህ አተሙ ተመልሶ ናይትሮጅን ይሆናል። ስለዚህ ካርበን-14 ይፈራርስና ተመልሶ ናይትሮጅን-14 ይሆናል።

ሊቢ በሰራው ስሌት መሰረት የምድር ከባቢ አየር በተሰራ ጊዜ በቂ ሬድዮአክቲቭ ካርበን-14 ለማዘጋጀት 30,000 ዓመታት ወስዷል፤ ስለዚህ ሬድዮአክቲቭ ካርበኑ ለመፈራረስ የሚወስደው ጊዜ ከሕዋ በሚመጣው የጨረር ግጭት አማካኝነት የከባቢ አየር ናይትሮጅን ለመስራት ከሚወስደው ጊዜ ጋር እኩል በሆነ ፍጥነት ነው የሚከናወነው። ሊቢ ምድር 4,600 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ አላት ብሎ ያምናል፤ ስለዚህ ከባቢ አየር ለረጅም ዘመናት በካርበን-14 አተሞች ሲሞላ ቆይቷል።

የሬድዮአክቲቭ ካርበን ዴቲንግ የተባለው የዘመናት ማስያ ዘዴ ሙሉ በሙሉ በነዚህ ግምቶች ወይም መላ ምቶች ላይ የተመሰረተ ነው።

ሊቢ ሙከራዎችን ባደረገ ጊዜ ግን ያገኘው ውጤት ከባቢ አየር ውስጥ የሚፈጠረው የካርበን-14 መጠን እየፈራረሰ ከነበረው በ25% እንደሚበልጥ ያሳያል። በ1963 ሪቻርድ ሊንገንፌልተር እና ሳዘርን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰራው ሃንስ ሱዌስ ጆርናል ኦቭ ጂኦግራፊካል ሪሰርች በተባለ መጽሔት ውስጥ በ1965 ዓ.ም እንደጻፉት እንዲሁም ቪ.አር. ስዊትዘር ሳይንስ በተባለ መጽሔት ውስጥ በ1967 እንደጻፈው ይህን ውጤት ትክክል መሆኑ ተመስክሮለታል። ስለዚህ ከባቢ አየር እስካሁን ድረስ በካርበን-14 እየተሞላ ነው። ይህም ከባቢ አየር 30,000 ዓመታት እንዳልሞላው ያመለክታል።

ፕሮፌሰር ሊቢ ይህንን ውጤት ለመቀበል እምቢ አለ፤ ስለዚህ የእርሱ ቲዎሪ ስሕተት የሚያሳየውን ማስረጃ የቤተሙራ ስሕተት ነው በማለት ወደጎን ትቶታል።

ዩታ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሰራው ስዊድናዊው የኖቤል ወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ፐሮፌሰር መልቪን ኩክ የሱዌስ እና ሊንገንፌልተርን ምርምር ውጤት ተመልክቶ ካርበን አተም እንደውም ከሚፈራርስበት በ38% በሚበልጥ ፍጥነት እየተሰራ መሆኑን አስልቶ አረጋግጧል። ምድር 30,000 ዓመታት ቢሞላት ኖሮ ካርበን-14 የሚፈራርስበትና የሚፈጠርበት ፍጥነት እኩል ይሆን ነበር።

ከሚፈራርስበት ፍጥነት የሚፈጠርበት ፍጥነት ከበለጠ ከባቢ አየር ገና 30,000 ዓመታት አልሆነውም ማለት ነው።
ከሚፈራርስበት ፍጥነት በ38% የበለጠ ፍጥነት የሚፈጠር ከሆነ ከባቢ አየር ዕድሜው ከ10,000 ዓመታት አይበልጥም ማለት ነው።

ምድር 4,500 ሚሊዮን ዓመት ሞልቷት ቢሆን ኖሮ ዓለቶች ውስጥ ያለው ዩራንየም በሬድዮአክቲቭ ጨረር እየፈራረሰ ከባቢ አየር በሂልየም ጋዝ ይሞላ ነበር። ዩራንየም ሬድዮአክቲች ነው፤ ስለዚህ ደረጃ በደረጃ ወደ ሊድ በሚቀየርበት ጊዜ የሂልየም አተምን ኑክሊየስ ይተፋ ነበር። ነገር ግን አሁን ከዚህ ሂልየም ጋዝ ውስጥ 99.96% የሚሆነው ከባቢ አየር ውስጥ የለም።

ሳይንቲስቶች ሂልየም በጣም ቀላል ስለሆነ ከምድር አምልጦ ወደ ሕዋ ውስጥ ገብቷል ይላሉ። ይህ ሲሆን ግን ማንም አላየም።

ጄምስ ላቭሎክ የተባለ የሕዋ ሳይንቲስት “ጋያ፡ ኤ ኒው ሎክ ኦን ኤርዝ” በተባለው መጽሐፉ ውስጥ የምድር ከባቢ አየር ውጨኛው ጠርዝ በጣም ስስ ከሆነው የፀሃይ ውጨኛ ከባቢ አየር ጋር የተቀላቀለ ነው ብሎ ጽፏል። ፀሃይ ያለማቋረጥ ፕሮቶኖችን እና ሂልየም አተሞችን እየለቀቀች መሆኗን እንራለን (እነዚህ ፕሮቶን ናቸው ሃይድሮጅን ጋዝ የሚፈጥሩት)፤ እነዚህንም ፕሮቶን እና ሂልየም አተሞች ሶላር ዊንድ ወይም የፀሃይ ነፋስ እንላቸዋለን። ፀሃይ ውስጥ ሃይድሮጅን አተሞች ያለማቋረጥ እየተጨመቁ ሂልየም ጋዝ ይሰራሉ። ስለዚህ ፀሃይ በሰፊ እና ስስ በሆነ የሃይድሮጅን እና ሂልየም ጋዝ የተከበበች ናት፤ ይህም ከምድር አልፎ እርቅ ቦታ ይደርሳል።
ከዚህም የተነሳ ምድር በፀሃይ ሃይድሮጅን እና ሂልየም ከባቢ አየር ውስጥ ነው በምሕዋርዋ የምትዞረው።
የፀሃይ ነፋስ ልናብራራ የማንችላቸው እንግዳ የሆኑ ገጽታዎች አሉት። የሃይድሮጅንና ሂልየም ፓርቲክሎች የሚፈጥሩት የፀሃይ ነፋስ ከፀሃይ እየራቀ ሲሄድ ባልታወቁ ምክንያቶች ፍጥነቱ በጣም ይጨምራል።

ከዚያም ከፀሃይ በጣም ርቆ የሚገኘው ፈጣኑ የፀሃይ ነፋስ ይበልጥ ብዙ ሂልየም ይዞ ይገኛል፤ ሂልየምም ክብደቱ ከሃይድሮጅን ይበልጣል። ሂልየም የፀሃይ ነፋስን ፍጥነት ለምን እንደሚጨምር አናውቅም።

የፀሃይ ነፋስ ከፀሃይ ዋልታዎች ላይ ተነስቶ በመጀመሪያው የፀሃይ ከባቢ አየር ራዲየስ ውስጥ የሚሄድበት ፍጥነት ለማብራራት ከምንችለው በላይ እጅግ ፈጣን ነው። ተርማል ኤነርጂ (የሙቀት ኃይል) ብቻውን ይህን ዓይነት ፍጥነት ሊፈጥር አይችልም። ከ2016 ጀምሮ ፓረከር ሶላር ፕሮብ የተባለው የናሰ የጠፈር የምርምር ማሽን ይህንን የፍጥነት ሚስጠር ለመፍታት ሙከራ በማድረግ ላይ ነው።

ላቭሎክ ባደረገው ስሌት አማካኝነት ያገኘው ውጤት ምድር ወደ ሕዋ እየለቀቀች ከምታጣው ሃይድሮጅን ከፀሃይ የምታገኘው አይድሮጅን እንደሚበልጥ ያሳያል።

ሂልየም ከሃይድሮጅን በክብደት ስለሚበልጥ ይህ ውጤት ለሂልየምም ይሰራል ምክንያቱም ምድር ከፀሃይ በምትገኝበት ርቀት ውስጥ ከሃይድሮጅን ይልቅ ብዙ ሂልየም አለ።

ላይኛው ከባቢ አየር በየጊዜው ይለዋወጣል፤ ነገር ግን ከፀሃይ እና ከሌሎች ነገሮች እንቅስቃሴ የተነሳ ለውጡት በትክክል መተንበይ አይቻልም።

የአውሮፓ እስፔስ ኤጀንሲ ክላስተር ሚሽን የላካቸው አራት የተያያዙ ሳተላይቶች የፀሃይ ነፋስ ወደ ምድር ከባቢ ማግኔታዊ ኃይል (ወይም ማግኔቶስፊር) ውስጥ በፊት ከሚታሰበው በላይ በጣም በቀላሉ እንደሚገባ የሚያሳይ ማስረጃ አግኝተዋል።

በየዓመቱ ከፀሃይ የሚለቀቀው ማግኔታዊ ኃይል ያለው ጨረር እጅግ በጣም ብዙ ሃይድሮጅን እና ሂልየም ወደ ምድር በከፍተኛ ፍጥነት እየወረወረ ይልቃል።

ስለዚህ የምድር ሂልየም በሙሉ ወደ ሕዋ እያመለጠ ካልሄደ እዚሁ የእኛ ከባቢ አየር ውስጥ ነው ያለው ማለት ነው። በምድር ከባቢ አየር ውስጥ ያለው የሂልየም መጠን በ4,600 ሚሊዮን ዓመታት ሊከማች የሚችለው 0.035% ያህል ብቻ ነው።

ነገር ግን በከባቢ አየራችን ውስጥ ካለው ሂልየም ውስጥ አብዛኛው የተገኘው ከፀሃይ ነው እንጂ በምድር ላይ ካለው ዩራንየም መፈራረስ ብቻ አይደለም። ስለዚህ ከባቢ አየር ዕድሜው ከ4,600 ሚሊዮን ዓመታት እጅግ በጣም ያነሰ ነው።

 

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23