የቤተክርስቲያን ዘመናት - ሰርዴስ - አምስተኛው ዘመን - ከ1520 እስከ 1750 ዓ.ም.
We update studies as the Lord Jesus leads us. You can find the latest update of this study at ChurchAges.net
ኒኮላስ 5ኛው (ከ1447 - 55) የአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ ሊቀ ጳጳስ ወይም ፖፕ ነበረ። ይህም ፖፕ የለውጥ ፍላጎት በመላው አውሮፓ እየተሰራጨ እንደነበረ ተረዳ። ስለዚህም የለውጡን እንቅስቃሴ እነዲመራ ከኪዩስ ከተማ የመጣውን ካርዲናል ኒኮላስን ወደ ጀርመኒ ላከው። ነገር ግን በዚያኑ ጊዜ የምሥራወቅ አፍሪካ የባሕር ድንበሮችን እያሰሱ ለነበሩ ፖርቹጋላውያን እጅግ አትራፊ በነበረው የባሪያ ንግድ እንድሰማሩም ፈቅዶላቸዋል። ነውረኛ ረብ ወይም ንጹሕ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ መሰብሰብ ለቤተክርስቲያን የውድቀቷ መጀመሪያ ነው። ነውረኛ ረብ መቀበል እስከዛሬም ለክርስቲያኖች ፈታኝ ችግር ነው።
ሰከኒኮላስ በኋላ የተነሱት ጳጳሶች አውሮፓ ውስጥ በየአካባቢው እየተቀጣጠሉ የነበሩትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ ምንም ጥረት አላደረጉም። ጳጳሳቱ ያለ አንዳች ሃፍረት ትኩረታቸውን የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያንን እና ሌሎች የቫቲካን ሕንጻዎችን ለመገንባት የሚያስፈልግ ገንዘብ መሰብሰብ ላይ አድርገው ነበር። እነዚህን ሕንጻዎችም ለመስራት የተጠቀሙት በሮም ከነበረው ኮሎሲየም ፍርስራሽ ላይ ሁለት ሺ አምስት መቶ ጭነት ድንጋይ በመጠቀም ነበር። ኮሎሲየም የተሰራው ኢየሩሳሌም ከወደቀች በኋላ በግዞት በመጡ ስድሳ ሺ አይሁዳውያን ባርያዎች ጉልበት ነው። ኮሎሲየም ውስጥ ብዙ አንበሳ እንዲበላቸው የተሰጡ የጥንት ክርስቲያኖችን ጨምሮ 400 000 ያህል ሰዎች ተገድለዋል። የቅዱስ ጴጥሮስን ቤተክርስቲያን መስራት ከጀመሩ በኋላ የጳጳሶች አእምሮ ሁሉ ሕንጻውን በዓለም ላይ ካሉ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ትልቅ አድርጎ በመስራት ተጠምዶ ነበር። ሰርቶ ለማጠናቀቅ 120 ዓመታት ፈጅቷል። ስለዚህ በማንኛውም ዘዴ ተጠቅመው ገንዘብ ይሰበስቡ ነበር።
ትልልቅ የሕንጻ ግንባታዎች ያልመሰጡዋቸው አንዳንድ የካቶሊክ ለውጥ ፈላጊዎች ድጋፍ ፍለጋ ወደ ፖለቲካዊ መሪዎች ዘውር አሉ። መካከለኛ ገቢ ባለቸው የከተማ ነዋሪዎች ቀስቃሽነት አንዳንድ ቤተክርስቲያኖች ለውጥን ማስተናገድ ጀመሩ። ከተሞችና ቤተክርስቲያኖችም ተባብረው በመስራት አንድነት ሲፈጥሩ ይህ አንድነታቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ኃይል ሰጣቸው።
ታላላቅ ሃይማኖታዊ ኃይሎች በ1500 ዓ.ም. አካባቢ ድንገት እንቅስቃሴ ጀመሩ። ሕዝቡም ለውጥ ፈለጉ፤ በተለይም ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ፈለጉ። ጳጳሳቱ ሃሳባቸውና ህልማቸው በሙሉ መሬትና ገንዘብ ላይ ስለነበረ የሕዝቡን ጥያቄ ሊመልሱ አልቻሉም። ጳጳሳቱ መሬት ለመያዝ ብለው ደግሞ ካስፈለገ ጦርነት ውስጥ ሁሉ ይገቡ ነበር። ፖፕ ሊዮ 10ኛው (1513 - 1521) የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያንን ለመስራት በጣም ከመፈለጉ የተነሳ የጳጳሳትን፣ የሊቀ ጳጳሳትን፣ የካርዲናሎችን የአገልግሎት ዘርፍ በመሸጥ እንዲሁም ሰዎች ለሰሩት ሐጢያት ይቅርታ የሚቀበሉበትን የስርየት ወረቀቶችን በመሸጥ በሮም ውስጥ የነበረውን አንድ ሦስተኛ ገንዘብ ሊሰበስብ ችሏል። ሕዝቡ ላይ ላዩን ሰላም ቢመስልም ውስጥ ውስጡን ግን ሮም ላይ በቁጣ እየተንተከተከ ነበር። አውሮፓ እነዚህ ሁሉ የሐይማኖት ኃይሎች በአንድነት የሚሄዱበትን መንገድ የሚቀይስና በአንድነት ኃይለኛ አሕጉር እንድትሆን የሚያደርጋት ጠንካራ መሪ አስፈልጓታል።
የታሪክ ምሑራን እንደሚሉት ሉተር የሰበከው ስብከት ውስጥ ብዙም አዲስ ሃሳብ አልነበረም። ጆን ሃስ ከሉተር አንድ መቶ ዓመት ቀድሞ ቦኸሚያ ውስጥ ተመሳሳይ መልዕክት ሰብኳል። ነገር ግን የሉተር እንቅስቃሴ ልዩ ያደረገው በዘመኑ የሚያስፈልገውን ጠንካራ፣ ቆራጥ እና እምነትን ያስቀደመ አመራር ይዞ መነሳቱ ነበር።
ሉተር እና ሌሎቹ የለውጥ መሪዎች የሕትመት ውጤቶችን በመጠቀም ሃሳባቸውን በስፋት ለማሰራጨትና የብዙዎችን ቀልብ ለመግዛት የማተሚያ ማሽንን በመጠቀም የመጀመሪያ ሰዎች ነበሩ። የትኛውም የለውጥ አራማጅ ሃሳቡን ለማሰራጨት የሕትመት መሳሪያን ሉተር የተጠቀመውን ያህል አልተጠቀመም። ከ1518 እስከ 1525 ሉተር አዘውትረው ከሚጽፉ 17 የለውጥ መሪዎች የበለጠ ብዙ ጽሁፎችን አሳትሟል። ሉተር አዲስ ኪዳንን ወደ ጀርመንኛ ተርጉሟል፤ ይህም ሮም በጀርመን ሕዝብ ላይ የነበራት ኃይል እንዲዳከም አድርጓል፤ ምክንያቱም ከዚያ በፊት ቤተክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት የሚከናወነው በላቲን ቋንቋ የነበረ ሲሆን ይህንን ቋንቋ መስማት የሚችል ሰው አልነበረም።
የሉተር የለውጥ እንቅስቃሴ ሦስት ቀላል ደረጃዎች ነበሩት።
1. ሰው በጸጋ አማካኝነት በእምነት ይድናል።
ኤፌሶን 2፡8 ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም
9 ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።
ካቶሊኮች ለመዳን እምነትና መልካም ሥራ ያስፈልገናል ብለው ነው የሚያምኑት።
2. እውነትን የምናረጋግጠው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።
ምሳሌ 30፡5 እግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፤
2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።
2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡2 ቃሉን ስበክ፥
ካቶሊኮች የሚመሩት በመጽሐፍ ቅዱስ እና በቤተክርስቲያን ወግ ነበር።
3. አማኞች ሁሉ ካሕናት ስለሆኑ በእግዚአብሔር እና በሕዝቡ መካከል የሚቆም የክሕነት አገልግሎት የለም።
1ኛ ጴጥሮስ 2፡9 እናንተ ግን … የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ … ናችሁ፤
ካቶሊኮች የሚያምኑት ፖፑ እና ካሕናት በሚፈጽሙዋቸው ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች አማካኝነት ብቻ ነው መዳንን የሚያገኙት። የእግዚአብሔርን ቃል የመተርጎም ስልጣን ያለው ፖፑ ብቻ ነው።
በ1302 ፖፑ ከቤተክርስቲያን ውጭ መዳን የለም ብሎ አወጀ።
ቀስ በቀስ እነዚህ የመሳሰሉ የካቶሊክ እምነቶች ወደ ፕሮቴስታንት ቤተክስቲያኖች ውስጥ ሾልከው ገቡ።
ብዙም ሳይቆይ ዛሬም እንደሚሆነው ብዙ ፕሮቴስታንቶች እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ከመሪዎቻቸው ንግግሮች ውስጥ ማግኘት እንዳለባቸው ማመን ጀመሩ።
ክርስቲያኖች እምነታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ አስደግፈው ማስረዳት በራሳቸው ጥቅሶችን ማገናኘት አይችሉም። ሁልጊዜ የሆነ ሰው የተናገረውን መጥቀስ ይቀናቸዋል።
ብዙ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውጭ ያሉ ሰዎች መዳን የሚገኘው ኢየሱስን እንደ አዳኝ በመቀበል እንደሆነ ያምናሉ፤ ነገር ግን ለመዳን በተጨማሪ አዘውትሮ አንድ ቤተክርስቲያን መሄድ እንደሚያስፈልግም ያምናሉ። በአንድ ቤተክርስቲይን አባል ስንሆን ብቻ ነው መዳናችንን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ብለው ከልብ ያምናሉ፤ ደግሞም ከቤተክርስቲያን መሪዎች ጋር መከራከር አይቻልም።
1963 ሦስተኛው ማሕተም
“ከእኔ ቤተክስቲያን ጋር የተያያዘ ካልሆነ -- ምንም ጥቅም የለውም።”
ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውጭ ያሉ የክርስትና መሪዎች ወይም ፓስተሮች በፊትም አሁንም በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ከፍ ያለ ቦታ ይዘዋል።
በአሁኑ ጊዜ የአምስቱ አገልግሎት ዘርፎች የክሕነት ቡድን ራሱን በእግዚአብሔርና በጉባዔው መካከል አቁሟል።
የጀርመኒ ንጉሳውያን ቤተሰቦች በለውጡ ውስጥ እጃቸው ከመግባቱ በፊት በዘመኑ ከነበረው ጥልቅ ሐይማኖታዊ ስሜት የተነሳ እጅግ ብዙ ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ ሉተርን ተከትለውታል።
የለውጡ መልዕክት በሕትመት እና በስብከት ተሰራጨ። የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የለውጥ እንቅስቃሴው የተቀናጀ አልነበረም፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አማካኝነት መዳን አውሮፓ ውስጥ በታላቅ ፍጥነት ተሰራጭቷል።
በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው ሌብነትና የስነምግባር ጉድለት ብዙዎችን ከእንቅልፍ አንቅቷቸዋል።
የካቶሊክ አጥባቂና የጨለማው ዘመን ታላቅ ባለቅኔ የነበረው ኢጣሊያዊው ዳንቴ “ኢንፌርኖ” በተባለው ግጥሙ ውስጥ ፖፕ ኒኮላስ 3ኛው እና ቦኒፌስ 8ኛው ሲዖል ውስጥ እንደገቡ አድርጎ ጽፏል። የለውጥ እንቅስቃሴ መሪዎች አጥብቀው ይቃወሙ የነበሩት ሥር የሰደደ ብልሹነትንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ አስተምሕሮዎችን ነበር።
ስለዚህ ሉተር፣ ዝዊንግሊ፣ እና ካልቪን የካቶሊክን ጵጵስና ሊያሻሽሉት ሳይሆን ፈጽሞ ሊያጠፉት ነበረ ፍላጎታቸው።
ገዳማት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባለመሆናቸው መጥፋት አለባቸው አሉ። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቋማት ሁሉ ብልሹዎች መሆናቸውን አውቀዋል፤ ከዚያም በላይ ያሳስባቸው የነበረው ግን ካሕናቱ እምነትን መበረዛቸውና ሐሰተኛ አስተማሪዎች መሆናቸው ነበር። የለውጥ እንቅስቃሴው ዋነኛ ዓላማው የጠፋውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና መልሶ ማምጣት ሲሆን ይህም ዓላማ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስተምሕሮዎችና ሥርዓቶች ላይ ታላቅ ጥቃት መሰንዘርን አስከተለ። እንቅስቃሴውም አብዮታዊ ገጽታ ነበረው።
ማቴዎስ 10፡34 በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።
በ1500 አካባቢ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በብልሹነትና በገንዘብ ፍቅር በተጠመደችበት ሁኔታ ለውጡ የመጣው ሊለውጣት ሳይሆን ሊያጠፋት ነበረ።
የሉተር ታላቅ ስኬት በእምነት መጽደቅ የሚለውን ትምሕርት መግለጡ ነው። የሰው መልካም ሥራ ማንንም ማዳን አይችልም። እግዚአብሔር ስለ መልካም ሥራዎቻችን ብሎ አይደለም የሚቀበለን። የሰው አእምሮ የጨለማ እስረኛ በመሆኑ መምረጥ የሚችለው በተለያዩ የሐጥያት አይነቶች መካከል ብቻ ነው። ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስ የሰራውን መልካም ሥራ መቀበል ብቻ ሲሆን ይህንንም እንኳ እንድንቀበል የሚያስችለን የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው። መዳን የሚቻለው በኢየሱስ የቀራንዮ መስዋእትነት ብቻ ነው። እኛ ምንም ብንሰራ እርሱ ከሰራው ጋር ሊወዳደር አይችልም። እኛ ማድረግ የምንችለው ከሐጥያታችን ንሰሐ መግባትና እርሱ ስለ እኛ የተሰዋበትን መስዋእትነት በትሕትና መቀበል ነው። በዚህ መንገድ የግል አዳኛችን አድርገን እንቀበለዋለን። ራሳችንን የምናድንበት ሌላ መንገድ የለም።
ለውጥ ለምንድነው ጀርመኒ ውስጥ የተጀመረው?
ፈረንሳይ እና ስፔይን ውስጥ ንጉሱ በልኡሎቹ ላይ ታላቅ ስልጣን ነበረው።
ጀርመኒ ውስጥ ግን ስልጣን ማዕከላዊ አልነበረም። ሰባት መራጮች ከሰባት ክልሎች ተሰባስበው የጀርመንን ንጉስ ይሾሙታል እርሱም ቅዱስ ሮማዊ ንጉስ ተብሎ ይጠራል። የጀርመን ነገሥታት ያለማቋረጥ የሮማ ጳጳሳትን ተዋግተዋል፤ በዚህም የተነሳ የጀርመኒ ነገስታት ስልጣን ተዳክሟል። ስለዚህ የጀርመን መራጮች የጀርመንን ንጉሥ መጋፈጥ ችለዋል። ቻርለስ 5ኛው በ1519 ቅዱስ ሮማዊ ንጉሥ ወይም የጀርመኒ ንጉስ ተብሎ ተመረጠ። እርሱም በተጨማሪ የኦስትሪያ፣ የስፔይን፣ የኔዘርላንድስ፣ የኢጣሊያ ግማሽ እና በከፊል የፈረንሳይ ንጉሥ ነበረ። ከዚህም የተነሳ ቻርለስ 5ኛው ከአውሮፓ ነገሥታት ሁሉ ይልቅ ኃያል ነበረ።
ቻርለስ ለፖፑ ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ወሰነ።
ስለዚህ ሉተር ከበድ ያለ ተቀናቃኝ ነበር የገጠመው።
ነገር ግን ጀርመኒ የቻርለስ ኃይል የተጠናከረባት ሃገር አልነበረችም፤ ምክንያቱም ጀርመኒ አንድ መንግሥት ሳትሆን በብዙ ትንንሽ ነጻ ክልሎች የተከፋፈለች ሃገር ነበረች። ከመራጮች መካከል የሳክሰኒው ፍሬደሪክ 3ኛው ካቶሊክ ቢሆንም እንኳ ለሉተር ጥበቃ አድርጎለታል ምክንያቱም ታላቁ የደች ሥነ መለኮት ምሑር ኢራስመስ በሉተር ትምሕርት ውስጥ አንድም መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረን ሃሳብ ሊያገኝበት አልቻለም። ስለዚህ ፍሬደሪክ 3ኛው እንደ ሃቀኛ መሪ ሉተርን ማሳደድ ተገቢ ነው ብሎ አላመነም። ይህም አስደናቂ የሐይማኖታዊ መቻቻል ምሳሌ ነው።
ቻርለስ 5ኛው ሌላ ችግርም አጋጥሞታል። ግዛቱ ያለልክ ሰፊ ነበር። በዚያ ዘመን ጉዞ እና የመረጃ ልውውጥ በጣም አዝጋሚ ነበር። ስለዚህ በኦስትሪያ ውስጥ የአናባፕቲስቶች አሳዳጅ የነበረውን ወንድሙን ፈርዲናንድን ኦስትሪያንና ጀርመኒን እንዲያስተዳድር ሾመው። ነገር ግን ኦቶማን ቱርኮች ኦስትሪያ ውስጥ ወደ ቪየና እየመጡ ስለነበረና ፈርዲናንድም ቱርኮችን ለመመከት ከጀርመኒ ድጋፍ ያስፈልገው ስለነበረ የጀርመኒን ፕሮቴስታንቶች ማሳደድ አልፈለገም። ኦቶማን ቱርኮች የቅዱስ ሮማዊ ግዛቱን (ማለትም ጀርመኒና ኦስትሪያ) ወታደራዊ ኃይል የእንቅስቃሴ አቅጣጫ በማስቀየር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ከዚህም የተነሳ የቻርለስ እና የፈርዲናንድ የጦር ኃይል ጀርመኒን ከመውጋት ይልቅ ቱርኮችን ለመከላከል እንዲዘምት ተገዷል።
ካርታው ላይ ቢጫ ቀለም ያለበት ቦታ የኦቶማን ቱርክ ግዛት ተስፋፍቶ በ1580 የደረሰበትን የመጨረሻ ስፋት ያሳያል።
በተጨማሪም ቻርለስ 5ኛው የሮማ ካቶሊክ ተከታይ ቢሆንም ያለማቋረጥ ፈረንሳይን ይወጋ ነበር፤ ግን የፈረንሳይ ንጉሥም ካቶሊክ ነበር። ይህም ጦርነት ያለውን ኃይል ሁሉ ስለሚጠቀምበት የቻርለስ ትኩረት ከጀርመኒ ፈቀቅ እንዲል አድርጎታል።
ቻርለስ 5ኛው በዘመኑ በምድር ላይ ከነበሩ ነገሥታት ሁሉ ይልቅ ኃያል የነበረ ቢሆንም በአንድ በኩል ከቱርኮች በሌላ በኩል ከፈረንሳይ ጋር ጦርነት በመግጠሙ የተነሳ ጀርመኒ ውስጥ በዊተንበርግ ከተማ የቤተክርስቲያን በር ላይ 95 የመከራከሪያ ነጥቦችን በመለጠፍ አገርን ሁሉ ሲያምስ የነበረ አንድ መነኩሴን ጸጥ ማሰኘት አቅቶታል። ሉተር እነዚህን ነጥቦች የጻፈው ሰዎች የሐጢያት ስርየትን እንገዛለን ብለው የተታለሉበትን የስርየት ወረቀት ሽያጭ በመቃወም ነበር።
ይህም የሉተር ድርጊት በአንድ ጊዜ የዓለምን ሁሉ ቀልብ ሊገዛ ችሏል።
አውሮፓም በስተመጨረሻ ሕዝቦቿ ሁሉ ያስቡ የነበረውን በድፍረት የሚናገርላት አንድ ድምጽ አገኘች፤ ይህም የስርየት ወረቀት ሽያጭ ሥርዓት በወንጌል ውስጥ አንዳችም ቦታ ያልነበረው የማጭበርበር ድርጊት መሆኑን በአደባባይ ማጋለጥ ነበር።
ስለዚህ አንድ ምስኪን መነኩሴ ታላቅ ሐይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሥልጣን የነበራትን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለብቻው ሲጋፈጥ ድፍን አውሮፓ ሁሉ በመገረም ይመለከቱ ነበር።
ኦቶማን ቱርኮች በ1453 ኮንስታንቲኖፕልን ከተቆጣጠሩ በኋላ በምሥራቅ አውሮፓ በጣም ሰፊ ግዛቶችን ይዘዋል። ኦቶማን ቱርኮች ወደ ቪየና እየገፉ ሲመጡ ለአውሮፓ ታላቅ ድንጋጤ እና ስጋት ሆኑ። ፈረንሳይ አንዳንዴም ፖፑ እንኳ ሳይቀር የቻርለስ 5ኛውን ኃይል ለመገደብ ብለው ከኦቶማን ቱርኮች ጋር ስምምነት አድርገዋል። ስለዚህ ቻርለስ 5ኛው ከላይ ካርታው ላይ እንደምናየው በሁለት ኃይሎች መካከል ተጠመደ፤ እርሱም ያለውን ጊዜ፣ ኃይል እና ሐብት በሙሉ እነዚህን ሁለት ኃይሎች ለመቋቋም ተጠቀበት።
ካርታው ላይ ያለው ቀይ ቀለም የቻርለስን ሙሉ ግዛት ያሳያል።
ሉተር የሚኖርባት በሰሜን ጀርመኒ ውስጥ ያለችዋ ሳክሰኒ የግዛቱ አካል ብትሆንም እንኳ ሩቅ ከመሆኗ የተነሳ ከቻርለስ ዘንድ ብዙም ስጋት አልነበረባትም። እግዚአብሔር በአስገራሚ መንገድ የፖለቲካዊ ኃይል ሚዛን እንዲጠበቅ አደረገ።
ጀርመኒ ውስጥ ከመራጮቹ የተወሰኑት ቻርለስን ለመቃወም በመተባበራቸው ቻርለስ ጀርመኒ ውስጥ የነበረው ኃይል በእጅጉ ቀነሰ፤ ስለዚህም ቻርለስ ጀርመኒ ውስጥ የፈለገውን ሊያደርግ አልቻለም። በተጨማሪም ከፈረንሳይ ጋር ከገባበት ጦርነት የተነሳ ብዙ ጊዜውን የሚያሳልፈው ከጀርመኒ ውጭ ነበር። ስለዚህም ሉተር የለውጥ እንቅስቃሴውን በነጻነት ሊያራምድ ችሏል።
ሱወቪዎችና ቪሲጎቶች ፖርቹጋላውያን እና ስፔይናውያን በመሆን ከማዕከላዊና ደቡባዊ አሜሪካ ውስጥ ብዙ ወርቅ እና ብር በመዝረፍ ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከማበርከት በተጨማሪ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ግዛት ብዙ ግዛቶችን ጨምረዋል፤ ከዚህም የተነሳ ቻርለስ 5ኛውን በምድር ላይ ኃያል ንጉሥ አድርገውታል። ቻርለስም ቀንደኛው የሉተር ፖለቲካዊ ጠላት ነበረ።
በዚህኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የነበረው ትልቁ ችግር ፖለቲካ እና ሐይማኖት መደባለቃቸው ነበር። ፖለቲካ ደግሞ ሁልጊዜ ትኩረቱ ገንዘብ ነው። ስለዚህ በዚህኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ገንዘብ ትልቁን ሚና ተጫወቷል።
የሮማ ጳጳሳት የቅዱስ ጴጥሮስን ቤተክርስቲያንና የቫቲካንን ከተማ ለመገንባት ገንዘብ ፈልገዋል።
ብዙ የአውሮፓ ሃገራት ወደ ፕሮቴስታንት እየተለወጡ ከሮም በመገንጠላቸው የተነሳ የሮማ ካቶሊክ ያጣችውን የገቢ ምንጭ ከደቡብ አሜሪካ ወርቅና ብር በመዝረፍ አካክሳዋለች።
ድሆች ገዳማትንና የሃብታም ሰዎችን ቤት ለመዝረፍ ስለፈለጉ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን መውጣት አሰቡ።
ልኡሎቹ ደግሞ ውድ የሆኑ የቤተክርስቲያን ንብረቶችን ለመያዝ ስለፈለጉ ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለመውጣት አሰቡ።
የሮማ ቤተክርስቲያን ያከማቸችው የተጋነነ ሃብት ብዙ ፕሮቴስታንቶችን ለዝርፊያ አነሳሳቸው።
ብዙዎች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ፕሮቴስታንት ሆኑ። ይህም ትክክለኛ አቋም አልነበረም።
ፊሊፕ የተባለው በሄሲ ከተማ ከጀርመኒ መሪዎች መካከል ታዋቂ የሆነ ሰው በግዛቱ ውስጥ የነበሩ የወንዶችንም የሴቶችንም ገዳሞች ሁሉ ሕገወጥ ባደረገ ጊዜ ከተሰበሰበው ሃብት 41 በመቶ ብቻ ቢደርሰውም እንኳ በጣም ብዙ ገንዘብ ነበረ ያገኘው። እርሱም “መናፍቃንን” ወይም ሐይማኖታዊ አፈንጋጮችን ለመግደል እምቢ ስለሚል መልካም ስም ነበረው። በግዛቱ ውስጥ የፕሮቴስታንት እምነት እንዲገባ በማድረግ በቤተክርስቲያን ላይ የነበረውን ስልጣን ሊያሳድገው ችሏል። ይህ ትልቅ ስሕተት ነበረ፤ ምክንያቱም ይህ እርምጃ የተለወጠችዋ ቤተክርስቲያን ለጥበቃ እና ለገንዘብ ፍላጎቷ በፖለቲካዊ ኃይል ላይ ጥገኛ እንድትሆን አድርጓታል።
ከሮም በመገንጠል የጀርመኒ ልኡሎች የፖፑንና የጳጳሳቱን ስልጣን የመቀማት ፍላጎታቸውን አሳክተዋል። ልኡሎቹም አንዳንዶቹን የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች መምራት ጀመሩ።
ለውጡ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ከሕዝቡ በላይ ከፍ ያሉ መሪ ሰዎችን በፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍ ባሉ መሪ ሰዎች ተክቷል።
በአንድ ልኡል በሚተዳደሩ ግዛቶች ውስጥ ሕዝቡ የገዥውን ሐይማኖት የመከተል ግዴታ ነበረባቸው።
እኛ ሰዎች ውሳኔያችንን ለማጽደቅ የሚያስችሉ እጅግ ብዙ ምክንያቶችን በመፍጠር ራሳችንን የማታለል ያልተገደበ ችሎታ አለን። ብዙውን ጊዜ የአንድ ሰው የሐይማኖት ምርጫ የሚወሰነው በስልጣን እና በገንዘብ በኩል በሚመጣው የግል ጥቅም ነበር።
በ1534 ንጉስ ሔንሪ 8ኛው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፍቺ አልፈቅድልህ ስትለው ከቤተክርስቲያኒቱ ተገነጠለ፤ ምክንያቱም ሌላ ሊያገባ ሃሳብ ነበረው። በዚህም መንገድ ከሮም ጋር በመለያየት ከዓመታት በኋላ በልጁ በቀዳማዊት ኤልሳቤጥ አማካኝነት እንግሊዝ ወደ ፕሮቴስታንትነት የምትለወጥበትን መንገድ ከፈተ።
እግዚአብሔር የእንግሊዝን ንጉሥ ቁጣ ተጠቅሞበት ሮም በእንግሊዝ ላይ የጫነችውን ቀምበር ሰበረው፤ (ንጉሡ ሚስቱን ለመፍታት ፈልጎ ነበር፣ ይህም በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይፈቀድም)።
ማርቆስ 10፡11 እርሱም፦ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤
12 እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።
ሉተር 95ቱን የክርክር ነጥቦቹን በቤተክርስቲያን በር ላይ በለጠፈበት ሰዓት ቴትዜል ለሜይንዝ እና ለማግዲበርግ ሊቀ ጳጳስ ገንዘብ ለመሰብሰብ የስርየት ወረቀት እየሸጠ ነበር። ሊቀ ጳጳሱ ከአንድ በላይ የጳጳስነት ስለጣን ለመግዛት ብዙ ገንዘብ ተበድሮ ነበር። ስለዚህ እዳውን ለመክፈል ነበር ብዙ የስርየት ወረቀት ሽያጭ ያስፈለገው። በዚህ ሽያጭ ውስጥ የፖፑም እጅ ነበረበት ምክንያቱም ከሽያጩ ገቢ ላይ ግማሹን ፖፑ ወስዶ ሮም ውስጥ የቅዱስ ጴጥሮስን ቤተክርስቲያን እና የቫቲካንን ከተማ ለመስራት ይጠቀምበታል።
ሉተር በ95ቱ ነጥቦች እና በሌሎችም ፖፑን በሚቃወሙ በራሪ ጽሑፎች አማካኝነት ቁጣውን ገለጸ።
በ1521 ቻርለስ 5ኛው ሉተር ትምሕርቱን እንዲያስተባብል እና እንዲመለስ ሲነግረው ሉተር የሚከተለውን መልስ በመስጠት ቤተክርስቲያንን ካናወጧት ነውጦች ሁሉ ትልቁን ነውጥ በማስነሳት በታሪክ ውስጥ ታዋቂ ሰው ሆኗል።
“ሕሊናዬን ሊያሳምን የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ምስክርነት ወይም አጥጋቢ ምክንያት ካልቀረበልኝ በቀር (ፖፑንም ሆነ አማካሪዎቹን ስለማላምናቸውና ደግሞም እርስ በርሳቸው ሲቃረኑም ስላየኋቸው) በጠቀስኳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች ተይዣለው፤ ሕሊናዬም ለእግዚአብሔር ቃል እስረኛ ሆኗል። አንድም የተናገርኩትን አላጥፍም፤ ወደ ኋላም አልመለስም፤ ምክንያቱም ሕሊናን ጥሶ መሄድ ልክ አይደለም ደግሞም አያዋጣም። እግዚአብሔር ይርዳኝ። አሜን።”
ለመቶ ዓመታት የዘለቀው የቤተክርስቲያን አንድነትና ለፖፑ ዝቅ ብሎ የመገዛት ልማድ በአንድ ጊዜ ብትንትኑ ወጣ።
ይህ የሉተር መልስ አዲስ የቤተክርስቲያን ዘመንን ከፈተ፤ አውሮፓንም በሐይማኖታዊ እና በፖለቲካዊ ገጽታዋ ለዘላለም ለወጣት።
ሰሜን አውሮፓ ወደ ፕሮቴስታንት ተለወጠ፤ የደች ካልቪኒስቶች በጀመሩት ታላቅ የንግድ እንቅስቃሴ አማካኝነት ሰሜን አውሮፓ ታላቅ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ኃይል ማዕከል ሆነ።
ማዕከላዊ አውሮፓም ወደ ፕሮቴስታንት ተለወጠ ግን በብዛት ለውጡን ለማክሸፍ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከ1540 ጀምሮ በተደረገው የጸረ ለውጥ እንቅስቃሴ ተሸንፎ ቀረ።
ከ1540 እስከ 1570 ዓ.ም. “ልዩ ልዩ የአውሮፓ ሃገሮች ውስጥ አንድ ሚሊዮን ያህል ፕሮቴስታንቶች በአደባባይ እንደተገደሉ በብሔራዊ እውነተኛ ምስክርነት ተረጋግጧል፤ ይህም በስውር ከተገደሉትና መሞታቸው ካልተመዘገበላቸው ብዙዎች በተጨማሪ ነው” (ጄ. ፒ. ካሌንደር፣ Illustrations of Popery፣ 1838፣ ገጽ 400)።
ደቡባዊ አውሮፓ የካቶሊክ ምሽግ ሆኖ ቀረ።
በተራራማው ስዊትዘርላንድ ውስጥ በመጀመሪያ ዝዊንግሊ ከዚያም ካልቪን የተጀመረውን የለውጥ እሳት አራገቡት። ጆን ኖክስ ወደ ስኮትላንድ ሄዶ ካቶሊክን ከነሥሩ ነቅሎ ጣለው። ሌሎች ሃገሮች ውስጥ ማንም ይህን ያህል ተሳክቶለት አያውቅም። ስኮትላንድ ውስጥ ብዙዎች በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ ተቆጥተው ነበር፤ ምክንያቱም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስኮትላንድ ውስጥ ከግማሽ በላይ መሬት ከመያዟ በተጨማሪ በዓመት የምትሰበስበው ገቢ ከስኮትላንድ ንጉሥ ገቢ በ18 እጥፍ ይበልጥ ነበር። ይህን የሚያህል የገንዘብ ሽልማት እያዩ ፕሮቴስታንቶች ጸጥ ብለው ሊቀመጡ አልቻሉም።
የሉተር ትልቅ ስሕተት ፖለቲካ ውስጥ መግባቱ ነበር።
መነኮሳቱ ስልጣናቸው እየተዳከመ ሲሄድ ሲያዩ በሕዝቡ ላይ ጭቆናቸው ያለልክ እየጠነከረ ሄደ። የፖፑ ባለ ስልጣኖች ይህንን አዲስ እንቅስቃሴ ለመደምሰስ የድሮውን የውግዘት እና የግድያ ስልታቸውን ለመጠቀም ወሰኑ። ሉተር በክርስቶስ ስለሚገኝ ነጻነት ጻፈ፤ ገበሬዎችና ሰራተኞችም ይህንን መልዕክት ከጌቶቻቸውና ከገዥዎቻቸው ነጻ እንደወጡ አድርገው ተረዱት። በእምነት መጽደቅ ክርስቶስን በመምሰል ወደ መኖር እንደሚመራ አልተረዱም። ሉተር ገዳማቱ ወንጌሉን እንደሚያጣምሙ አጋልጦ ስላወገዛቸው ገበሬዎች ገዳማትን መዝረፍና መበዝበዝ የተፈቀደላቸው መሰላቸው። ስለዚህ ሉተር የሰበከው የመንፈሳዊ ነጻነት መልዕክት ለጭቁን ገበሬዎች ሲመኙት ከነበረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ጋር ተቀላቀለባቸው። ከ1524 እስከ 1526 የነጻነት ጥያቄ በማቅረብ 300 000 ገበሬዎች በመሬት ከበርቴዎችና በጨቋኝ ጌቶቻቸው ላይ በዓመጽ ተነሱ፤ ንብረትና ገንዘብ የመያዝ ፍላጎታቸውንም በወንጌል ካባ ሸፍነው ገለጡት። ይህ አዲስ የፕሮቴስታንት ሐይማኖት የሃብታሞችን ቤት ለመዝረፍ እንደሚፈቅድላቸው እና ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን ግብር ከመክፈል ነጻ እንደሚያወጣቸው ተስፋ አደረጉ። የሚያሳዝነው ነገር ሉተር ጨቋኝ ገዥዎችን በመደገፍ ከምስኪኑ ሕዝብ በተቃራኒ አቋም መያዙ ነበር። 100 000 ያህል ገበሬዎች መገደላቸውም በጀርመኒ ውስጥ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ጥቁር ጥላ ጣለበት። ይህም ክስተት ሉተራን ቤተክርስቲያን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በገዥዎች ጥበቃ ስር እንድትጠለል አስገደዳት። ጊዜ እያለፈ ሲሄድም ሉተራን ቤተክርስቲያን ወግ አጥባቂ ሃብታሞችና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚሰበሰቡባት የመንግሥት ቤተክርስቲያን ሆና ቀረች።
ሉተር የሰራው ሌላ ስሕተት ደግሞ አይሁዶችን ማውገዙ ነበር። ከዘመናት በኋላ ሉተር በአይሁዳች ላይ ያወጀውን ውግዘት ሒትለር ተነስቶ በተግባር ፈጽሞታል።
63-0318 የመጀመሪያው ማሕተም
ማርቲን ሉተር አይሁዶች ሁሉ የክርስቶስ ተቃዋሚ ስለሆኑ መባረር እንዳለባቸውና ቤታቸውም መቃጠል እንዳለበት ባወጀ ጊዜ… አያችሁ? ይህንን ቃል ማርቲን ሉተር እራሱ ነበር በጽሁፍ ያሰፈረው።
ሒትለርም ማርቲን ሉተር የተናገረውን ነው ተነስቶ የፈጸመው። ማርቲን ሉተር ለምንድነው እንደዚያ አይነት አዋጅ ያወጀው? ምክንያቱም የለውጥ መሪ እንጂ ነብይ ስላልነበረ ነው። የእግዚአብሔር ነብይ እሥራኤልን ይባርካል። እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል፤- “የሚባርክህ ይባረካል፤ የሚረግምህ ይረገማል”። አንድ ነብይ የተናገረውን እንዴት ሌላ ነብይ ይሽረዋል? ሊሽረው አይችልም። አንድ ነብይ ከሌላ ነብይ ጋር አይጋጭም።
ብዙ መልካም ለውጦችን ካመጣ በኋላ ሉተር የተወሰኑ የካቶሊክ ልማዶችን እንደነበሩ ይዟቸው ቀጠለ።
ሉተር በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጨለማው ዘመን የተጀመረውን ሕጻናትን የማጥመቅ ልማድ እንደነበረ ይዞት ቀጠለ።
ደግሞም አንድ ቄስ ለአንድ አካባቢ ተጠሪ የሚሆንበትን አንድ ጳጳስ ደግሞ የብዙ ቄሶች ተቆጣጣሪ የሚሆንበትን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥርዓትም ወደ ፕሮቴስታንት ውስጥ ይዞ መጣ።
ሉተር የሰራው ሌላው ሰሕተት የሮማ ካቶሊክን የሥላሴ ትምሕርት ይዞ መውጣቱ ነው። ሉተር በመጽሐፍ ቅዱስ መመራት አለብን ይላል፤ ነገር ግን ኢራስመስ እና ቶማስ ሞር ሥላሴን ለመግለጽ የሚያገለግሉት ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለመገኘታቸውን ሲያሳዩት አልሰማችሁም አላቸው። ሁለቱ የስዊትዘርላንድ ለውጥ መሪዎች ዝዊንግሊ እና ካልቪንም ሥላሴን ከመቃወም አፈግፍገዋል። ሰርቬተስ የተባለ ስፔይናዊ ዶክተር የለውጥ መሪዎች ሁሉ ለመናገር ያልደፈሩትን የሥላሴ ትምሕርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ብሎ ደፍሮ የተናገረ ጊዜ የለውጥ መሪው ካልቪን አስይዞ በአደባባይ በእሳት አቃጥሎ ገደለው።
አናባፕቲስቶች ቀርቶ የነበረው የትልቅ ሰዎች ጥምቀት እንዲመለስ ለማድረግ ሞከሩ ግን ዝዊንግሊ በ1525 አናባፕቲስቶች ውሃ ውስጥ ሰጥመው እንዲሞቱ አዘዘ። የለውጥ መሪዎቹ በ565 ዓ.ም. የሞተው የሮማ ገዥ ጀስቲንያን ካጸደቀው ሕግ ውስጥ አንድ አንቀስ ወስደው ተጠቀሙበት፤ አንቀጹም በድጋሚ የተጠመቀ ወይም ሥላሴን የካደ ሰው እንዲገደል ይደነግጋል። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንመለስ በሚል መርሕ የተጀመረው ለውጥ ግስጋሴ በአንዴ ተገታ።
የለውጥ መሪዎቼ የአንዲት ሃገር ፖለቲካዊ ደሕንነቷ የሚጠበቀው ሕዝቦቿ መንግሥት የደነገገውን የሃገሪቱን ሕግ ሲያከብሩና የሃገሪቱ መሪ የሚከተለውን ሐይማኖት ሕግጋት ሲያከብሩ ነው ብለው ያምኑ ነበር። በአንዲት ሃገር ውስጥ ሐይማኖታዊ አንድነት ያስፈልጋል አሉ። የሃገሪቱ መሪ ፕሮቴስታንት ከሆነ ዜጎች ፕሮቴስታንት መሆን አለባቸው፤ ካቶሊክ ከሆነ ደግሞ ካቶሊክ። በዚህ መንገድ ፖለቲካና ሐይማኖት ተቀላቀሉ።
የመንግሥትና የቤተክርስቲያን አንድነት ተጠብቆ ቆየ። ፖለቲካዊ መሪዎች ተቃዋሚዎችን መቅጣት ተፈቀደላቸው።
የአንድ ግዛት ሐይማኖት የሚወሰነው በገዥው ሐይማኖት ሆነ። ሰዎች የነበራቸው ሐይማኖታዊ ነጻነት ሐይማኖታቸውን የሚጋራ ገዥ ወዳለበት ሃገር መሸሽ ብቻ ነበር።
ነገሥታትና ገዥዎች የግዛታቸውን ሐይማኖት የመወሰን ሥልጣን ይዘው መነሳታቸው በወቅቱ ለነበረው ሐይማኖታዊ ትግል አዲስ ፖለቲካዊ ጭካኔ አላበሰው። ከእንግሊዝ በቀር የአውሮፓ ነገሥታት ካቶሊክ ሆኑ። አውራጃዎችና ከተሞች የነገሥታትን ሥልጣን ይቃወሙ ነበር፤ በተለይም ሰሜን አውሮፓ ውስጥ ፖለቲካዊ ነጻነት ከመፈለጋቸው የተነሳ ሕዝቡ ፕሮቴስታንት ሆኑ።
ከዚያም በኋላ ካልቪን የሰዎች መዳን ወይም አለመዳን አስቀድሞ በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ ብቻ የተወሰነ ጉዳይ ነው ብሎ በማስተማር ሰውን የራሱ ነጻ ፈቃድ የሌለው እቃ አደረገው። ይህ ጽንፈኛ አመለካከት የሰውን ነጻነት ሙሉ በሙሉ ደመሰሰው።
ክርስቲያኖች የሰው ነጻ ፈቃድና የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ውሳኔ ጎን ለጎን መሄድ እንደሚችሉ ለመረዳት ብዙ ማወቅ ያለባቸው ነገር አለ። ግን የዚህ ዘመን ችግር እውነትን በከፊል ብቻ ማወቃቸው አልነበረም። እጅግ አስደናቂ በሆነ ወኔ ተነስተው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ገዥነተ እንዲያከትም አድርገው ሰዎች እንዲድኑ በእምነት ስለመጽደቅ በግልጽ አስተምረዋል። ነገር ግን የሚከብዱ እና አጨቃጫቂ የሆኑ ሃሳቦች ላይ እግዚአብሔር በቀጣይ ዓመታት ተጨማሪ የእውነት መገለጥ እስኪሰጥ ድረስ በመጠበቅ ፈንታ በተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ የተመሰረቱ ትረጓሜዎችን በማጽናት በእነዚሁ ርዕሶች ላይ የሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እንዳላዩ ለማለፍ ወሰኑ።
ስለዚህ አውሮፓ ውስጥ የተለያዩ ቡድኖች የራሳቸውን ሃሳብ የሚያራምዱ ቤተክርስቲያኖችን ሲከፍቱ ተጀምሮ የነበረው ለውጥ እየቀዘቀዘ ሄዶ ቀጥ ብሎ ቆመ። ከዚያ ወዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ አዲስ መገለጥ መፈለጋቸውን አቆሙ። እግዚአብሔርም በስተመጨረሻ አልፏቸው ሄደ።
የለውት መሪዎቹ አጀማመራቸው መልካም ነበረ፤ ነገር ግን ወዲያው የጥንቷን ቤተክርስቲያን የእምነት ፈለግ መከተላቸውን አቆሙ። ስለዚህ ለውጡ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም ወንጌሉን ወደ ፊት የማራመድ ሥራ ግን በሌላ ትውልድ ለሚመጡ እንደ ጆን ዌስሊ ላሉ ሰዎችና ለሚሽነሪዎች ተላልፎላቸዋል።
ዌስሊ “ምድር በሙሉ ቤተክርስቲያኔ ናት” በሚለው ንግግሩ ታዋቂነትን አግኝቷል።
ይህም ንግግር ትልልቅ መርከቦች የተሰሩበት የቴክኖሎጂ እድገት ሚሽነሪዎችን በባሕር ላይ ወደ ልዩ ልዩ ሃገሮች ያደረሰበት እንዲሁም የባቡር መንገዶች ደግሞ በየብስ ላይ ሚሽነሪዎችን ያጓጓዙበትን ወርቃማውን የክርስትና የወንጌል ስብከት ዘመን የከፈተ ንግግር ነበር።
በ1500 አካባቢ የፖፑ ስልጣን ትልቅ መንፈሳዊ ኪሳራ ውስጥ ቢገባም የሉተር የለውጥ እንቅስቃሴ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በውስጧ ለውጥ እንድትጀምር አስገድዷታል፤ ይህም በ1540 ጀስዩት የተባሉ ሙሉ በሙሉ ለፖፑ ስለመገዛት የሚሰብኩ ሰባኪዎች እንዲነሱ (የጀስዩቶች መስራች ኢግናሺየስ ሎዮላ “ፖፑ ነጭ ጥቁር ነው ካለ አምነዋለው” ብሉ ተናግሯል) እና ከ1545 እስከ 1563 በዓመት ሦስት ጊዜ የሚሰበሰበው የትሬንት መማክርት ጉባኤ እንዲመሰረት አድርጓል። ጀስዩቶች ከተደራጁ በኋላ የፕሮቴስታንትን ለውጥ የሚቃወም ጠንካራ ዘመቻ በመዝመት በማዕከላዊ አውሮፓ ውስጥ ከካቶሊክ እጅ ወጥተው በፕሮቴስታንቶች እጅ የነበሩ ብዙ ግዛቶችን ወደ ካቶሊክ አስመልሰዋል።
ፕሮቴስታንቶች ፖፑ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው ብለው ሲያውጁ ካቶሊኮች ግን ለወደፊት የተነገሩ ትንቢቶችን ወደ ኋላ መልሰው ንጉሠ ነገስቱ ኔሮ አውሬው እንደነበረና በ70 ዓ.ም. የተከናወነው የኢየሩሳሌም መፍረስ ታላቁ መከራ እንደነበረ ተናገሩ። ይህ አተረጓጎም የተዋጠላቸው ሰዎች ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተመለሱ።
ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊት የሚናገራቸው ትንቢቶች በቀላሉ ዋጋ እንዲያጡ የሚደረግበት ዘዴ ሆነ። ስለዚህ እነርሱ እንደሚሉት መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክን ብቻ የሚዘግብልን እንጂ ስለ ወደፊቱ የሚነግረን መጽሐፍ አይደለም።
ዛሬ የሜሴጅ አማኞች በ1963 በሰሜናዊ አሪዞና ፍላግስታፍ ከተማ አጠገብ የተገለጠውን ታላቅ ደመና የጌታ ምጻት ፍጻሜ ወይም የራዕይ ምዕራፍ 10 ታላቅ መልዓክ መገለጥ ነው ብለው ያምናሉ። ስለዚህ ሰባቱ ምሥጢራዊ ነጎድጓዶች ድምጻቸውን አሰምተው አልፈዋል ይላሉ። የወደፊቱን ያለፈ ነው ብሎ መተርጎም በታሪክ ራሱን የሚደግም የስሕተት ስልት ሆኖ ተገልጧል።
ሮም ውስጥ በ1542 የተጀመረው ኢንክዊዚሺን ፕሮቴስታንቶችን በሙሉ ከኢጣሊያ ውስጥ አንድ በአንድ ለቅሞ ንብረቶቻቸውንና መሬቶቻቸውን ሁሉ በመውረስ እነርሱን ደግሞ በማሰር ወይም በመግደል ፈጽሞ አጥፍቶዋቸዋል። በ1478 የተመሰረተው የስፓኒሽ ኢንክዊዚሽንም የፕሮቴስታንት እምነት ስፔይን ውስጥ እንዳይኖር አድርጓል።
ታላቁ የለውጥ መሪ ካልቪን ከፈረንሳይ ስደት ሸሽቶ ወደ ስዊትዘርላንድ ሄዷል።
በ1560 አካባቢ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንደገና ተጠናክራ የመልስ ምት መስጠት ጀመረች።
ትግሉም እየተካረረ ሄደ። ለመቶ ዓመታት ያህል ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች በብዙ ማሕበራዊና ሐይማኖታዊ ግጭቶች ውስጥ ጎሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀዋል።
ካቶሊካዊ ነገሥታት ሃገሮቻቸውን በሙሉ በማዕከላዊነት የመቆጣጠር ፍላጎታቸው እና የፕሮቴስታንት ከተሞችና አውራጃዎችም የራሳቸውን አካባቢያዊ ነጻነት የማስከበር ጽኑ ፍላጎታቸው ሥር የሰደደ ሐይማኖታዊ ገጽታ ያለው ፖለቲካዊ ትግልን አስከተለ። የእምነት እርግጠኝነት ከፖለቲካዊ ግለት ጋር መነጣጠል በማይችል መልኩ ተቀላቀለ። ትግሉም እየተካረረ ሄዶ እርቅ መቀበል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደረሰ።
ይህ አስጨናቂ ዘመን በማዕከላዊ አውሮፓ ውስጥ ከ1618 እስከ 1648 በተካሄደው የ30 ዓመታት ጦርነት አማካኝነት አበቃ፤ በዚህም ጦርነት ከ6 እስከ 8 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል። ረሃብ፣ ቸነፈር፣ በሽታና ቅጥረኛ ተዋጊዎች እንዲሁም ወታደሮች ሕዝቡን መዝረፋቸውና ማስፈራራታቸው የእለት ተእለት ኑሮ ሆነ። ብዙዎቹ ተዋጊ ሃገሮች ሙሉ በሙሉ በመክሰራቸው የተነሳ ጦርነቱ ቆመ። ብዙዎቹ ሃገሮች አንድ ሦስተኛና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎቻቸውን አጡ። የጀርመኒ ደቡብ ምዕራብ ግዛት ከጦርነቱ በፊት የነበራት ሕዝብ አንድ ሦስተኛው ያህል እንኳ አልተረፈላትም። ጦርነቱን ያስቆመው የሚዋጋ ሁሉ ሞቶ በማለቁ ነበር። አንዳንዶቹ የጀርመኒ ግዛቶች በ1618 የነበራቸውን የሕዝብ ቁጥር ለመተካት እስከ 1750 ድረስ ከ100 ዓመታት በላይ ፈጅቶባቸዋል።
ሕዝብ ያላለቀባት ብቸኛዋ ሃገር የደች ሪፓብሊክ ነበረች።
በ1648 ስፔይኖችን እስከ ደም ጠብታ ሲዋጉ ቆይተው በስተመጨረሻ በስፔይን ላይ መነሳት ትተው በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ በታላቅ ሰላምና ብልጽግና ሊኖሩ ችለዋል። በዓለምም ሁሉ በኢኮኖሚ እና በባሕር ኃይል አንደኛ ሆኑ። የካፒታሊዝም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በፕሮቴስታንት ሃገሮች ውስጥ እየተጸጧጧፈ ነበር። ሰ
ሰርዴስ ጠንካራ የምትመስል ነገር ግን ደካማ የነበረች ቤተክርስቲያን ናት።
ጅማሬያቸው መልካም ነበረ፤ ነገር ግን በዘመኑ በገጠማቸው ሁኔታ ተናወጡ፤ ልክ እንደ ስምዖን ጴጥሮስ የመከራ ማዕበል ሲያስደነግጣቸው ዓይናቸውን ይመለከቱት ከነበረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ዘወር አድርገው መስመጥ ጀመሩ።
ድክመት ቢኖርባቸውም እንኳ በዚህ በአምስተኛው የቤተክርስቲያን ወሳኝ ለውጥ አምጠተዋል።
ከእነርሱ የተነሳ ሰዎች መዳን ጀመሩ። በሮም ላይ ተቃውሞ ያስነሳ የመጀመሪያው ሰው ሉተር ሲሆን እርሱ የጀመረው እንቅስቃሴ ሰዎች ከሮም እንዲያመልጡና ፕሮቴስታንት ሃገሮችን እንዲመሰርቱ አስችሏቸዋል።
በጨለማው ዘመን ከመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ብዙ ርቆ ሄዶ የነበረው ባለ ሰባት ቅርንጫፉ መቅረዝ አሁን በሌላኛው ጫፉ በቁል ተለኮሰ። ጻድቅ በእምነት ይኖራል። ዘመኑ ብዙ ችግሮችና ስሕተቶች ቢኖሩበትም እንኳ በእምነት የመጽደቅ ታላቅ እውነት በሕዝቡ ልብ ውስጥ ታትሞ እንዲቀር አድርጓል።
እንባቆም 2፡4 ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል።
የመጣው ትልቅ መሻሻል የአቅጣጫ ለውጥ ነበረ።
ከሐዋርያት ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተክርስቲያን ወደ ጥንቷ ቤተክርስቲያን የመመለስ እርምጃ መውሰድ ጀመረች። ቤተክርስቲያን ጠፍቶባት የነበረውን በእምነት የመዳንን እውነት መልሳ አገኘች። ብዙ መሻሻል ያለበት ነገር ነበር ግን ሕዝቡ ወደ ጥንቷ ቤተክርስቲያን የሚመራው በትክክለኛው መንገድ ላይ መራመድ ጀምረዋል። ቤተክርስቲያን ሕያው መሆን ጀመረች። ከረጅሙ የጨለማ ዘመን ሌሊት በኋላ ፀሃይዋ ቀስ በቀስ ብርሃንዋን ፈነጠቀች።
ራዕይ 3፡1 በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል፦ ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል።
ሰርዴስ የሚለው ቃል ትርጉሙ “ያመለጡ” ማለት ነው።
የሰርዴስ ዘመን ታላቅ መልአክ ወይም መልእክተኛ ሉተር ከሮም ማምለጥ ችሏል። እግዚአብሔር ግን ሰባት ከዋክብት አሉት፤ እነርሱም እያንዳንዳቸው የሁለት ሺ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሚጠናቀቁት ሰባት የቤተክርስቲያን ዘመናት የተመደቡ ናቸው። ከዚህኛው ዘመን በኋላ ተከትለው የሚመጡ ሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናት አሉ። እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ዘመን የመንፈሱን አንድ ልዩ ገጽታ ይገልጥ ነበር ምክንያቱም እያንዳንዱ ዘመን የተለየ መከራና ፈተና ይጋፈጥ ነበር። እግዚአብሔር በሰባት የተለያዩ ባሕርያት የተገለጠ ይመስላል። ሰባቱንም ዘመናት በተለያዩ ሰባት መንገዶች የሚመሩ ሰባት የተለያዩ ሰዎች ይነሳሉ። በመጀመሪያዎቹ ዘመናት ውስጥ እውነት ደረጃ በደረጃ እየጠፋች እንደሄደች ሁሉ አሁን ደግሞ እውነት ደረጃ በደረጃ እየተመለሰች በመሆኑ እያንዳንዱ ዘመን እና ፈተናዎቹ የተለያዩ ሊሆኑ ችለዋል።
ነገር ግን የለውጥ መሪዎቹን የተከተሉ ሰዎች ትልቅ ስሕተት ሰሩ። ሕዝቡ በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ እንዳሉ መሰላቸው ደግሞም የለውጥ መሪዎች እውነትን ሁሉ ሙሉ በሙሉ የገለጡ መሰላቸው። በለውጥ የተጀመሩት ቤተክርስቲያኖች በዙሪያቸው የአስተምሕሮ አጥር አጠሩ። የለውጥ መሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ሊገልጡ ሞከሩ፤ ነገር ግን እውነት ገና በሙላት እንዳልተገለጠ አላወቁም። የለውጥ መሪዎቹ በኒቂያ ጉባኤ ላይ የተቀበረው የእውነት ዘር ቆይቶ የመብቀሉና የማቆጥቆጡ ምልክት የሚሆኑ ቅጠሎች ናቸው።
እነዚህ የለውጥ መሪዎች የሰሩዋቸው ሥራዎች ታላላቅ ናቸው። የማተሚያ ማሽንን በመጠቀም የመዳንን ወንጌል በስፋት አሰራጭተዋል። ነገር ግን ተከታዮቻቸው ደግሞ ራሳቸውን እንደ ሉተራን፣ ካልቪኒስት፣ አናባፕቲስት በሚሉ ሰው ሰራሽ ስሞች ጠሩ።
ከዚህም የተነሳ ለውጡ ተቋርጦ ሰዎች ማስታወሻ የሚሆኑ ትልልቅ የቤተክርስቲያን ሕንጻዎችን ገነቡ።
በለውጡ ውስጥ የነበረው የሕይወት ኃይል ከሰዎች መካካል ቀስ በቀስ በመጥፋት የለውጡን ዘመን ተከትሎ ወደመጣው የሚሽነሪዎች ዘመን ሄደ። ሲያቆጠቁጡ የነበሩት አረንጓዴ የለውጥ ቅጠሎች ግን በየዓመቱ እየጠወለጉና እየደረቁ ሄዱ። ለጥቂት ጊዜ በውስጣቸው ሕይወት ነበረ ግን ሕይወት ወደ ፊት ሲገሰግስ እነርሱ ግን ተጨማሪ መገለጥ አልቀበል ብለው ከሕይወት ጋር አብረው አለመገስገሳቸው ያሳዝናል።
በመደራጀትና ለራሳቸው ሰው ሰራሽ ስም በማውጣት ሞትን ወደራሳቸው ጋበዙ።
እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ሙሉውን እውነት የያዝነው እኛ ነን ማለት ጀመረ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሌላ የቤተክርስቲያን ዘመን ለማስነሳት ወሰነ፤ ይህም ዘመን በወንጌል የዱላ ቅብብል ውስጥ የለውጥ መሪዎች ያቀበሉዋቸውን ዱላ ተከታዮቻቸው በጣሉ ጊዜ ሚሽነሪዎች አንስተው የሮጡበት ዘመን ነው።
ራዕይ 3፡2 ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና።
በእምነት ስለመጽደቅ ተረድተዋል። መዳን እንደሚያስፈልግ ለሕዝቡ አስተምረዋል። ፕሮቴስታንቶች ከብዙ የካቶሊክ ሐይማኖታዊ ልማዶች ተላቅቀዋል። ነገር ግን በዚያ ክፉ ዘመን ውስጥ በተገለጠላቸው እውነት ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ማለትም በመዳን ላይ ከማተኮር ይልቅ በሃሳባቸው ያልተስማሙ ሰዎችን ማሳደድ ጀመሩ።
ደግሞም ለገንዘብ፣ ለጥበቃ እንዲሁም አስተምሕሮዋቸውን ሕዝብ እንዲቀበል ለማስገደድ በመንግሥት ኃይል መጠቀም ጀመሩ።
መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ ለመተርጎም ባደረጉትም ሙከራ ውስጥ በሒደት ብዙ ስሕተት የሆኑ ትምሕርቶችን አጸኑ። ከእነዚህም ውስጥ ተጠቃሾቹ ሕጻናትን ማጥመቅ፣ ከፓስተሮች በላይ የሆነ የኤጲስቆጶሳትና የሊቀጳጳሳት የስልጣን ተዋረድ፣ እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን በፓስተር ገዥነት ይተዳደር ነበር፣ ቤተክርስቲያኖች ለራሳቸው ሰው ሰራሽ ስሞችን አወጡ። አንግሊካን ቤተክርስቲያን፣ ዝዊንግሊያን ቤተክርስቲያን፣ ሁገኖትስ። የአስተምሕሮ ስሕተቶችም ቦታ ያዙ፤ ለምሳሌ ሥላሴ፣ ሔዋን የአፕል ፍሬ በላች፣ የሰባት ዓመት መከራ።
ለአጥቢያ ቤተክርስቲያን መቅናት የቃሉን መገለጥ ወደ ጎን ገፋው። ይህ ዘመን አጀማመሩ መልካም ነበር ግን ፍጻሜው አላማረም።
አጥቢያ ቤተክርስቲያናቸውን ከሁሉ አስቀደሙ። የቤተክርስቲያናቸው አስተምሕሮ ከመጽሐፍ ቅዱስም ጭምር በለጠባቸው።
ራዕይ 3፡3 እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።
በእምነት ስለመጽደቅ ማስተማር ታላቅ ጅማሬ ነበር። ከዚያ ግን ቤተክርስቲያንን መንግሥት እንዲቆጣጠራትና ሕዝቡ የአካባቢውን ገዥ እምነት እንዲከተሉ ወደ ማስገደድ ውስጥ ገቡ። ይባስ ብለው ፕሮቴስታንቶች አናባፕቲስቶችን ውሃ ውስጥ እያሰጠሙ ገደሉዋቸው ምክንያታቸውም ትልልቅ ሰዎችን ማጥመቅ የለባችሁም ብለው ነበር። ታላቁ የለውጥ መሪ ዝዊንግሊ ዙሪክ ውስጥ በ1519 መስበክ ጀመረ ግን በ1531 ተገደለ፤ ምክንያቱም ስዊትዘርላንድ ውስጥ ላሉ ካቶሊኮች ምግብ እንዳይደርሳቸው ለማገድ ሞክሮ ነበር።
ባልጠበቀው ሰዓት አድብተውበት ገደሉት።
ፕሮቴስታንቶቸ ራሳቸውን ከሮም ጭቆና ማላቀቃቸው መልካም ሆኖ ሳለ ግን እነርሱም ከካቶሊክ ያላነሰ ብዙ ስሕተቶችን ሰሩ። ወንጌልን ከፖለቲካዊ ጭካኔ ጋር ደባለቁት። ብዙ ፕሮቴስታንቶች የሮማን ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ሃብት መውረስ ፈለጉ። ምድራዊ ብልጽግናን በመከታተል እምነታቸውን ላላ አደረጉ።
እግዚአብሔርም ብዙ ለማወቅ የነበራቸውን መንፈሳዊ ጥማት ከላያቸው ላይ አነሳ። ስለዚህ ጥቂት ብቻ ተራምደው ከዚያ ቀጥ ብለው ቆሙ።
ራዕይ 3፡4 ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።
ከፖለቲካዊ ትርምሱ፣ ከነፍስ ግድያው፣ ሃብታም የካቶሊክ ቤተክርስቲያኖችንና ቤቶችን ለመዝረፍ ከነበረው ጉጉት መካከል ከልብ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እግዚአብሔርን ለማገልገልና በቃሉም ለመኖር ፍላጎት ያላቸው ጥቂት ሰዎች ነበሩ። እነርሱም ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ሰጡ፤ ከሐጢያታቸው ንሰሃ ገቡ፤ ኢየሱስንም እንደ አዳኛቸው ተቀበሉ። ብዙዎቹ ተራ ሰዎች ስለነበሩ የታሪክ ምሑራን ትኩረት ውስጥ አልገቡም። የሕይወታቸውም ትኩረት እገዚአብሔርን ማገልገልና ሌሎች ሰዎችን ማዳን ነበረ። የልባቸውም ፍላጎት ገንዘብ ወይም እስከ 1650 ድረስ ዘመኑን ያጥለቀለቀው ደም መፋሰስ አልነበረም። ጠላቶቻቸውንም ለማሳመን ይፈልጉ ነበር እንጂ ለመግደል አስበው አያውቁም፤ እነርሱ ራሳቸው ግን ብዙውን ጊዜ ተገድለዋል። ነገር ግን ከ1650 በኋላ መቻቻል እየሰፈነ መጣ ምክንያቱም ከመቶ ዓመታት ውጊያ በኋላ ካቶሊኮችም ፕሮቴስታንቶችም ጦርነቱ አውሮፓን በሁለት ጎራ በካቶሊክ እና በፕሮቴስታንት እንደከፈላትና እንዳወደማት እንጂ አንዱ ወገን ሌላውን ለማጥፋት በቂ ኃይል እንዳልነበረው ማስተዋል ጀመሩ።
ይህ ሶሪያ ውስጥ ከባድ እልቂት ካስከተለው የ2011 የእርስ በርስ ጦርነት ጋር ሊነጻጸር ይችላል። እስከ 2017 ድረስ 400 000 ሰዎች ሞተዋል፤ 12 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ደግሞ ተፈናቃይ ስደተኞች ሆነዋል። ጦርነት የተካሄደባቸው ከተሞች የድንጋይ ስብርባሪ ሆነው ቀርተዋል። በዚህ አሳዛኝ እልቂት ውስጥ አሸንፌያለው የሚል ወገን አለ? የጥንት ሮማውያን አንድን አካባቢ ወግተው ካወደሙት በኋላ ውድመቱን ሰላም ብለው ይጠሩ ነበር። በ1650 አካባቢ ጀርመኒ ውስጥ ብዙ ከተሞች የዛሬዋን ሶርያ ይመስሉ ነበር። የብዙዎቹም የጀርመኒ ከተሞች የሕዝብ ቁጥራቸው በ1540 ወደ ነበረበት እስኪመለስ ድረስ መቶ ዓመታትን ፈጅቶባቸዋል።
ራዕይ 3፡5 ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ።
መዳን እና በእምነት የመጽደቅን ወንጌል ማሰራጨት የቻሉ ሰዎች በዘመኑ ከነበረው ግፍ እና አሰቃቂ እልቂት የተነሳ ብዙ አሳዛኝ መከራዎችን አሸንፈው ማለፍ ነበረባቸው። ነገር ግን ስለ እምነታቸው ለሞትም እንኳ ቢሆን ያለ ምንም ማመንታት ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የተዘጋጁ ነበሩ። ብዙዎቹም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የለውጡን እንቅስቃሴ ለመቃወም በ1540 በጀመረችው ዘመቻ ውስጥ ተጨፍጭፈዋል። ነጭ ልብስ ስለ ቅንነታቸውና ስለ ጽድቃቸው የሚመሰክር ምልክት ነው። በጨካኝ ጠላቶች እጅ በአካል ቢወገዱም እንኳ እግዚአብሔር በሰማይ ከጻፈው የሕወት መጽሐፍ ውስጥ ስማቸውን ማንም ሊያስወግደው አልቻለም።
የሚያስፈልጋቸውም ይህ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም በትንሳኤ ቀን ሁላቸውም ከሞት ተነስተው በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። እነርሱን የገደሉዋቸው ሰዎች በምድር ላይ ለጥቂት ዓመታት መኖራቸውን ቀጠሉ፤ ነገር ግን መጨረሻቸው በእሳት ባሕር ውስጥ ነው የሚሆነው፤ እርሱም ለመሄድ የሚጓጉለት ቦታ አይደለም።
እግዚአብሔር ስለ ስሙ ለቆሙለት ሰዎች ይቆምላቸዋል። ስለ እግዚአብሔር ስም ብሎ መቆም ማርቲን ሉተር ለዚህ ዘመን ያካፈለው ትልቅ እሴት ነው።
ራዕይ 3፡6 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመን የሚልከው መልእክት ግን ብዙዎች የማይሰሙት መልእክት ይህ ነው፤ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተመለሱ። መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ብቻ ያስተምራችኋል።
ሰዎች ግን ብዙውን ጊዜ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ከተጻፈው እውነት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆነው የመሪዎቻቸው ንግግር ላይ የበለጠ እምነት ይጥላሉ። በመከራ ጊዜ ውስጥ የሰው ጥበብ ሊመራን አይችልም። ዋጋ ቢያስከፍለንም እንኳ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ነው መጣበቅ ያለብን። ይህ ዘመን ብዙ ሰማእታትን አስነስቷል። ሮምን ሳይፈሩ የተጋፈጡ ቆራጥ ፕሮቴስታንቶች ተነስተዋል፤ የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ የፕሮቴስታንት ለውጥ መሪዎች ሌሎች ፕሮቴስታንቶች እንዲገደሉ መስማማታቸው ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተጣብቀው ቢቀሩ ኖሮ ይህ ባልሆነ ነበር።