የቤተክርስቲያን ዘመናት - ጴርጋሞን - ሦስተኛው ዘመን - ከ312 ዓ.ም. እስከ 606 ዓ.ም.

ከ64 ዓ.ም. እስከ 312 ዓ.ም. ሰይጣን በጨካኙ የሮማ ግዛት መንግሥት አማካኝነት አሥር አሰቃቂና ደም አፍሳሽ ስደቶችን በቤተክርስቲያን ላይ አስነሳ። ቤተክርስቲያን ግን ሦስት ሚሊዮን ቅዱሳን ቢሞቱባትም እድገቷ ከበፊቱ ፍጥነቱ ጨመረ። ከውጭ የሚሰነዘር ኃይል ቤተክርስቲያንን ሊያጠፋት እንደማይችል በመረዳት ሰይጣን ቀጥሎ ያመጣው ዘዴ ንጉሥ ኮንስታንቲን በ312 ዓ.ም. ቤተክርስቲያንን ማሳደድ እንዲያቆም ማድረግ እና በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባኤ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ለማያውቅ ሰው ለመለየት አስቸጋሪ የሆነች እውነተኛዋን የምትመስል ነገር ግን አስመሳይ የሆነች ቤተክርስቲያን በመመስረት እውነተኛዋን በመጽሐፍ ቅዱስ የምታምነዋን ቤተክርስቲያን ማፈን እና ማዳከም ነበር።

የሮማ ግዛት ውስጥ የተገለጠው የጭካኔ ብዛት ዳንኤል በራዕይ አይቶ የጻፈው አውሬ ነው፤ እርሱም አንድ ራስ ያለው ታላቅ አውሬ ሆኖ አሥር ቀንዶች እና ከመካከላቸውም አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ ነበሩት።

ሌሎችን ሃገሮች ካጠፋ በኋላ ይህ ኃይለኛ የሮም አውሬ እራሱ በአሥር ባርቤሪያውያን ቀንዶች ወይም መንግሥታት ይከፋፈልና እነዚሁ አሥር መንግስታት አንድ ቀንድ ማለትም መንፈሳዊ የቤተክርስቲያን መንግስት ከመካከላቸው እንዲበቅል ያደርጋሉ።

ዳንኤል 7፡7 ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት።

ዳንኤል 7፡20 በራስዋም ላይ ስለ ነበሩ ስለ አሥር ቀንዶች፥
(አንድ ራስ ብቻ ነው ያለው)

ዳንኤል 7፡8 ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፥ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፥ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ እነሆም፥ በዚያ ቀንድ እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት።

ዓይኖች የሚገልጹት ማስተዋልን ነው። “የሰው ዓይኖች” ላይ የተመሰረተ መንፈሳዊ ኃይል ብቅ እያለ ነበር፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን በሰው ጥበብ ላይ የተመሰረተ ሃይማኖት ነው።

ይህ ሮማዊ አውሬ ሁሉን ከእግሩ በታች እየረረገጠ ለአንድ አምባ ገነን ገዥ ሰው እያንበረከከ ለሮማ መንግሥት ሕግና ለአንዲት ሮማዊት ሃይማኖት እንዲታዘዙ እያደረገ የሚገዛውን ጨካኝ አረማዊ መንፈስ ይወክላል። ይህችም ሮማዊት ሐይማኖት የሮማ መንግሥት ያንበረከካቸውን የአረማውያን ሕዝብ አማልክት በሙሉ ያቀፈች ናት። ይህም ብዙሃኑ ሕዝብ በተሳሳተ እምነታቸው ሳይቆረቁራቸው እንዲኖሩ አስቻላቸው፤ እነርሱን መቆጣጠርም ቀላል ሆነ።

የመሪዎቹ ዓላማ ሐማኖታዊ እውነት ሳይሆን ሐይማኖታዊ አንድነት ነበር። ሕዝቡ መንግሥት ያጸደቀውን ሐይማኖት እንዲከተሉ አሳምኑዋቸው፤ አለዚያም አስገድዱዋቸው። ተቃዋሚ ካለ ርገጡት። በይፋ የታወጀው ሐይማኖት ያዘዘውን ጸሎት ባታምኑበትም ድገሙት።

ስለዚህ ፖለቲካ እና የአረማውያን ሐይማኖት ተዳቅለው ይህንን አስቀያሚ ጭራቅ ወለዱ።

ቀንድ ኃይልን ነው የሚወክለው፤ ልክ የበሬ ወይም የጎሽን ቀንድ እንደምንፈራው። ቀንድ ትልቅ ጉዳት ማድረስ ይችላል። በሮማ መንግሥት መፍረስ ውስጥ ብዙ ባርቤሪያኖች ተሳትፈውበታል። አሥሩ ቀንዶች የሚወክሉዋቸው አሥሩ የባርቤሪያን ነገዶች የተሳተፉት የሮማ መንግሥትን በማፍረስ ብቻ ሳይሆን የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በመትከልም ጭምር ነበር፤ ቤተክርስቲያኒቱም በሮማ መንግሥት ፍርስራሽ ላይ ተመስርታ በኃይል በመጠናከር ወደ ዓለም ሁሉ ተስፋፋች። የሮማ ግዛት መንግሥት ሲፈራርስ ብቸኛዋ ሳትፈርስ የጸናችዋ ድርጅት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት።

ከእስያ የመጡት ሃንስ ከባርቤሪያውያን መካከል እጅግ ኃይለኞች እና ከሁሉ ይልቅ አስፈሪዎች ነበሩ። እነርሱም ከምሥራቅ መጥተው ጀርመኖችን ወደ ሮማ ግዛት ድንበር ውስጥ ገፉዋቸው።

ይህ በሆነበት ጊዜ የሮማ ግዛት መፈራረስ የጀመረው በስደተኞች ብዛት በመጨናነቅ ነበር።

ከባርቤሪያኖች ውስጥ ጥቂቶቹ በውትድርና ተቀጥረው ለሮማ መንግሥት ለመዋጋት እሺ ካሉ ወደ ሮማ ግዛት መቀላቀል ይችላሉ።

ነገር ግን እጅግ ብዙ ስደተኞች በጨካኞቹ ሃንስ እየተገፉ ወደ ግዛቱ ውስጥ ከጎረፉ ይህ ለሮማ መንግሥት ከአቅም በላይ ነው የሚሆንበት። ይህ ከእስያ የተነሳው የሃንስ ወረራ መንስኤው ምን እንደሆነ የታሪክ ምሑራን አያውቁም። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰዎችን ማንቀሳቀስ ሲፈልግ እምቢ ማለት የሚችል ሰው የለም። ብዙ ክስተቶችም ከቁጥጥራችን ውጭ ይወጣሉ። ክፉውም ይሁን መልካሙ ሁሉ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ውስጥ ነው።

የባርቤሪያኖች ወረራ የተጀመረው በሮማ መንግሥት ድንበር አካባቢ የነበሩ የጎቲክ መንግሥታት በሃንስ አማካኝነት በ372-375 ዓ.ም. ሲፈራርሱ ነው። ሃንሶች ብዙ የሮማ ከተሞችን ወረሩ ደግሞ ዘረፉ። ፖፕ ሊዮ ቀዳማዊ የሃንስ መሪ የነበረውን አቲላ አናገረው እርሱም ሮምን ከማጥቃት ተመለሰ። ይህም ፖፑ የሮም ጠባቂ ተብሎ ተወዳጅነትን እንዲያገኝ አደረገ ምክንያቱም ምዕራባዊው ገዥ ለሮም ጥበቃ አላደርግም ብሎ ነበር። በ476 ዓ.ም. ከሄሩሊ ነገድ የሆነው ባርቤሪያዊ ጄነራል ኦዶዋሰር ምዕራባዊውን የሮማ ገዥ ከስልጣን አወረደው።

በሥላሴ የማያምነው ኦዶዋሰር ለጥቂት ዓመታት ኢጣሊያን ሲገዛ ቆየ፤ ከዚያም በኮንስታንቲኖፕል ከተማ የነበረው ምሥራቃዊው ገዥ ኦስትሮጎቶችን ልኮ የሄሩሊዎችን ግዛት ከኢጣሊያ ላይ አስወገደ። ነገር ግን ኦስትሮጎቶችም በሥላሴ አያምኑም ነበር በዚህም ፖፑ ደስተኛ አልነበረም።

ይህ ካርታ በዚህ ጥናት ውስጥ የምንከታተላቸውን አስሩን ነገዶች ያሳያል።

አቲላ በ453 ዓ.ም. ሲሞት ሃንስ ተበታተኑ። ግን ከመበታተናቸው በፊት ሌሎቹን ነገዶች ገፍተው ገፍተው ወደ ሮማ ግዛት ውስጥ አስገብተዋል። ሊዮን ካናገሩት በኋላ ከሮም አፈገፈጉ፤ ይህም ፖፕ ሊዮን ዝነኛ አደረገው። ሕዝቡም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፖፑን የሮም መሪ አድርገው ተመለከቱት። ሄሩሊዎች ከጄነራል ኦዶዋሰር (ጥቁሩ ነጥብ) መሪነት በ476 ዓ.ም. ወደ ኢጣሊያ ገብተው ምዕራባዊውን የሮማ ገዥ ከስልጣን አስወረዱት። እነርሱም ኦስትሮጎቶች በ493 ዓ.ም. እስከሚያስወግዱዋቸው ድረስ ኢጣሊያን ገዙ፤ ከዚያም ኦስትሮጎቶች ኢጣሊያን ገዙ። ከዚያም በኮንስታንቲኖፕል የተቀመጠው ምሥራቃዊው ገዥ ጀስቲንያን ኢጣሊያን ለማንበርከክ ወሰነ። መጀመሪያም በጠንካራው የባሕር ኃይላቸው እንዳያጠቁት ሰሜን አፍሪካ ውስጥ የነበሩት ቫንዳሎች ላይ በ534 ዓ.ም. ጦርነት አውጆ አሸነፋቸው።

ቫንዳሎች ተደመሰሱ። እንዳጋጣሚ እነርሱም በሥላሴ የማያምኑ ነበሩ።

ከዚያም የጀስቲንያን ጦር ሰራዊት በኢጣሊያ ላይ ጦርነት ከፈተ። ሃያ ዓመታት የፈጀው አሰቃቂ ጦርነት የኢጣሊያን ሕዝብ ፈጀ፤ ሃገሪቱን አወደመ፤ ረሃብና የበሽታ ወረርሽኝን አስከተለ። በ553 ዓ.ም. ኦስትሮጎቶች ከኢጣሊያ ተወገዱ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብና በበሽታ አለቁ፤ ረሃቡ እና የበሽታ ወረርሽኙም ከኢጣሊያ አልፎ አውሮፓን እስከ ጨለማው ዘመን ደረስ አጥለቀለቀ። በዚህም መንገድ በሥላሴ የማያምኑት ሄሩሊዎች፣ ቫንዳሎች፣ እና ኦስትሮጎቶች ሲወገዱ በሥላሴ የሚያምነው ፖፕ የሮም ገዥ ሆኖ ተቀመጠ።

ሦስት ቀንዶች ከሥራቸው ተነቃቀሉ።

ሦስቱ በሥላሴ የማያምኑ ነገዶች ፈጽመው ከታሪክ ተወገዱ፤ ስለዚህ የሥላሴን አስተምሕሮ የሚቃወም ጠፋ። የሉተር ተሃድሶ ከዚያ 1000 ዓመታት ካለፉ በኋላ ነበር የመጣው። ስለዚህ የሮማ ጳጳሳት ለ1000 ዓመታት ያህል የሥላሴ ትምሕርትነ አስተማሩ፤ ሊከራቸውም አቅም ያለው ሰው አልነበረም። በዚያ አንድ ሺ ዓመት ውስጥ የሥላሴ ትምሕርት ያለማቋረጥ ከመደጋገሙ የተነሳ ሥር ሰደደ። ስለዚህ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ ያመጡ ሰዎች ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወጡ ነገር ግን ሲወጡ የሥላሴን አስተምሕሮ ይዘው ሄዱ። ዛሬ በመጨረሻው የሎዶቂያ ቤተክርስቲያን ዘመን ብዙዎቹን ቤተክርስቲያኖች ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ከሚያስተሳስራቸው ጥቂት አስተምሕሮዎች አንዱ የሥላሴ አስተምሕሮ ነው።

ከዚያም በ568 ዓ.ም. ሎምባርዶች ኢጣሊያን ወረሩ። ወዲያውም ፖፑ ከባርቤሪያኖች ጋር ሲመሳጠር አዲስ የቤተክርስቲያን ዘመን ተጀመረ። ቀስ በቀስ ሎምባርዶች ለፖፑ ስጋት እየሆኑ መጡ።

በ634 ዓ.ም. ሙስሊም አረቦች ከአረቢያ በረሃ ተነስተው መካከለኛው ምሥራቅን እና ሰሜን አፍሪካ እንዲሁም እስፔይንን አሸንፈው ገዙ። በኮንስታንቲኖፕል ተቀምጦ የነበረው ምሥራቃዊው ገዥ የሙስሊም አረቦችን መንገድ በመዝጋት ተጠምዶ ስለነበረ ሮምን ሊጠብቃት አልቻለም፤ በዚህም የተነሳ ፖፑ ባርቤሪያውያን ወራሪዎችን ለመከላከል ሲል ፖለቲካዊ ሴራ ውስጥ መግባት ግድ ሆነበት። ፖፑ ሰውን ንጉስ አድርጌ የመቀባት ስልጣን አለኝ ብሎ አወጀ። ይህም በታሪክ መለኮታዊ የንጉስ ስልጣን ተብሎ ተጠራ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነገሥታት የነገሥነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ማለት ቻሉ። ፖፑ አንድን ሰው ንጉሥ አድርጎ ይቀባል፤ በዚህም ምክንያት የንጉሡ ቤተሰቦች ብቻ እርሱን ተክተው መንገሥ ይችላሉ፤ በአጸፋውም ንጉሡ የሮምን ከተማ ከሌሎች ባርቤሪያውያን ነገዶች ጥቃት እንዳይሰነዘርባት ይከላከላል። ፖፑም ለዚህ ብሎ ከባርቤሪያውያን ነገዶች መካከል እጅግ ጠንካራ የሆኑትን በፈረንሳይ እና በሰሜን ጀርመኒ የነበሩትን ፍራንኮችን መረጠ።

የፍራንኮች አስተዳዳሪ የነበረው ፔፒን የፍራንኮች ንጉስ የነበረውን ቺልደሪክ ወደ ገዳም ካሳደደው በኋላ በ751 ዓ.ም. በፖፕ ዛካሪ ድጋፍ ራሱን የፍራንኮች ንጉስ ብሎ አወጀ።

በአጸፋውም ንጉስ ፔፒን ወደ ኢጣሊያ መጥቶ ሮምን ሊያጠቁ የነበሩትን ሎምባርዶችን ወግቶ አባረራቸው።

ፔፒን ከዚያ በኋላ ብዙ የኢጣሊያ ግዛቶችን ለፖፑ ሰጠ፤ እነዚህም ፓፓል ስቴትስ ወይም የፖፑ ግዛቶች ተባሉ። እነዚህን ግዛቶች ለማየት ከታች ያለው ካርታ ውስጥ በሽሮማ ቀለም የተለየውን ክፍል ይመልከቱ።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ፖፑ በባርቤሪያውያን መካከል ንጉሥ አንጋሽ እና የመሬት ባለቤት ሆነ። ይህም ትልቅ ክብር እና ፖለቲካዊ ኃይል ሰጠው። የፍራንኮቹ ወታደራዊ ኃይል ተቃዋሚዎቹን ለመምታት አስቻለው።

ሦስት ቀንዶች ተነቅለው ጠፉ፤ ከዚያም የፖፑ ታናሽ ቀንድ ማደግ ጀመረ።

የዚህ ዘመን ታላቅ ስሕተት በጊዜው ለማሕበረሰብ ሕልውና ስጋቶች የነበሩ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ለማለፍ ተብለው የተፈጠሩ አስተምሕሮዎች ናቸው።

አምባ ገነኖቹ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች ቶሎ ቶሎ የሚለዋወጡትን ሁኔታዎች ለመቋቋምና በጊዜው የሚገጥማቸውን ተገዳሮት ለመመከት ብለው የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በራሳቸው ፍላጎት መለዋወጥና በቃሉ ላይ የራሳቸውን ሃሳብ መጨመር ቀጠሉ። ብዙውን ጊዜ ጊዜያዊ የሆኑ መፍትሄዎችን ያገኙ ነበር ግን በስልጣናቸውና በሌሎች ቤተክርስቲያኖችና ሕዝቡ ላይ የነበራቸውን የበላይነት እንደያዙ ለመቆየት ሲሉ ከሐዋርያት አስተምሕሮ እየራቁ በሄዱ ቁጥር የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ጥፋት እያደረሱ ነበር።

ነገር ግን ሁልጊዜ በየዘመናቱ በልዩ ልዩ ቦታዎች ታዋቂ ያልሆኑ ከኢየሱስ ጋር ባላቸው የጠበቀ ሕበረት ላይ የሚደገፉና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን የቤተክርስቲያን መመሪያ አድርገው ለመከተል የሚጠነቀቁ ክርስቲያኖች ነበሩ። ከዚህ መመሪያ ማፈንገጥ በጣም አደገኛ ውጤቶች ያስከትላል። የዚህች የእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ጥንካሬ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተቀመጡትን መርሆች አጥብቃ መያዝዋ እና መከተሏ ነበር። እነዚህ ቤተክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ ይፈርሳሉ ደግሞም ይበታተናሉ፤ ግን ልክ እነርሱን የመሰሉ ደግሞ በሌላ ሥፍራ ብቅ ይላሉ። ስለዚህ ለኢየሱስ የማዳን ኃይል እውነተኛ ምስክር ሁሌም የሆነ ቦታ መገኘቱ አይቀርም ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ቤተክርስቲያን ሌሎችን ቤተክርስቲያኖች እንድትገዛ የሚል ትዕዛዝ ስለሌለው እነዚህ እውነተኛ ቤተክርስቲያኖች የተደራጀ ሕብረት አልነበራቸውም። እነዚህ ቤተክርስቲያኖች ሕብረታቸው ያልተደራጀ መሆኑ በቀላሉ መንቀሳቀስና ስደትን መቋቋም እንዲችሉ ረድቷቸዋል። ሕዝቡን በተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ዙሪያ መሰብሰብና መጽሐፉን እንደማይለወጥ መመሪያ መከተል የእግዚአብሔር ቃል እውነት በሆነ ጊዜ አንድ አካባቢ ላይ ቢጠፋም የእግዚአብሔር መንፈስ አዳዲስ አማኞችን ባነቃቃበት ወቅት በሌላ ጊዜ ሌላ ቦታ ተመልሶ እንዲበቅል አስችሏል።

ለእነዚህ ቤተክርስቲያኖች በሕዝብ ቁጥር ትልቅ መሆን ቁም ነገር አልነበረም።

ማቴዎስ 18፡20 ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ግን ትኩረቷን ከሁሉም የሚበልጥ ትልቅ ቤተክርስቲያን በመስራትና የሁሉ የበላይ በመሆን ላይ አደረገች። ለመጀመሪያ ጊዜ ፖፕ የሚለውን ማዕረግ የተቀበለ የሮማ ጳጳስ አቡነ ሲሪሺየስ (384-399 ዓ.ም.) ነበር፤ ፖፕ በኢጣሊኛ እና በላቲን “ፓፓ” በግሪክ ደግሞ “ጳጳስ” ሲሆን በሁሉም ቋንቋ ትርጉሙ “አባት” ማለት ነው። ኢየሱስ ግን ማንንም “አባት” ብለን መጥራት እንደሌለብን ተናግሯል።

ማቴዎስ 23፡9 አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ አባት ብላችሁ አትጥሩ።

በ400 ዓ.ም. ይህ ጳጳስ በሮም ቤተክርስቲያን ከሚሰበሰበው ገንዘብ አንድ አራተኛውን ለራሱ ይወስድ ነበር።

በሊዮ ቀዳማዊ ጊዜ (440 – 461 ዓ.ም.) የሮም ጳጳስ የአረማውያን ሊቀ ካሕንን የማዕረግ ስም ፖንቲፌክስ ማክሲመስ (ወይም ፖንቲፍ) የራሱ መጠሪያ አድርጎ ተቀበለ። ሊዮ የሮም ጳጳስ (ፖፕ ተብሎ የተጠራውን) የቤተክርስቲያኖች ሁሉ የበላይ ጳጳስ እንዲሆን ፈለገ። ሊዮ የጳጳስ ስልጣን የቅዱስ ጴጥሮስ ስልጣን ነው ብሎ አመነ። ፖፕ ስለሆንኩ የጴጥሮስ ተወካይና ቃል አቀባይ ነኝ ብሎ አወጀ። የእውነተኛዋ ሐይማኖት የበላይ ጠባቂ እኔ ብቻ ነኝ አለ።

በ451 እንደምንም ብሎ የሃንስ መሪ አቲላ ሮም ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝር አሳምኖ መለሰው። ስለዚህ ሃንስ ሮምን ከማጥቃት መመለሳቸው ለፖፑ ትልቅ ተቀባይነትን ሰጠው፤ ሮምን ከጨካኞቹ ሃንስ መታደግ የቻለ ብቸኛው ሰው በመሆን ታወቀ።

ነገር ግን ከሦስት ዓመታት በኋላ የቫንዳሉ ጋይዘሪክ ለ14 ቀናት ሮም ሙልጭ አድርጎ ዘረፋት። አረማዊቷ ሮም እየወደቀች እየተዳከመች ስትሄድ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ግን እያንሰራራች ነበር። ከምዕራባዊው የሮማ ገዥ ምንም እርዳታ ባለመምጣቱ ፖፑ አብዛኛው ጊዜውን የሮምን ከተማ በማስተዳደር ተጠመደ።

ኦጋስተን (354 – 430 ዓ.ም.) በዘመኑ አንደኛ ተሰሚነት ያለው ክርስቲያን ደራሲ ነበረ። እርሱንም በ395 ዓ.ም. በሰሜን አፍሪካ የሂፖ ከተማ ጳጳስ አድርገው ሾሙት። ሮም በ410 ዓ.ም. አላሪክ በተባሉ የጎት ወራሪ እጅ መውደቋና ጎቶችም ከተማይቱን ሙልጭ አድርገው መዝረፋቸው ኦጋስተንን አስደነገጠው፤ እርሱም በዚህ ምክንያት “The City of God” ወይም “የእግዚአብሔር ከተማ” የሚል መጽሐፍ በመጻፍ ምላሽ ሰጠ። ከምድር ከተሞች ሁሉ ታላቋ ከተማ (ሮም) ልትወድቅ ከቻለች ኦጋስተን በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ሳትወድቅ የምትጸና ሰዎችም ተጠግተው ሊተርፉ የሚችሉባትን ሌላ ምድራዊ ድርጅት ለሕዝብ መጠቆም እንዳለበት ተሰማው፤ ይህችም ኦጋስተን ለሰዎች መጠጊያ ብሎ የመረጣት ድርጅት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ነበረች። የኦጋስተን ምርጫ የሚያዋጣ ይመስል ነበር ምክንያቱም የሮማ መንግሥት በፈራረሰ ጊዜ ሳትፈራርስ ጸንታ የቆመች ሮማዊ ድርጅት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብቻ ነበረች። ለምሳሌ የሮማውያን ሕይወት ማዕከልና መዝናኛ ቦታ ኮሎሲየም ነበረ፤ እርሱም ከ70 – 80 ዓ.ም. የተሰራው የዓለም ሁሉ ትልቅ አምፊቲያትር ሲሆን እስከዛሬ ድረስ ግን ፍርስራሹ ብቻ ነው ያለው። በኮሎሲየም ውስጥ ሮማውያንን ለማዝናናት ተብሎ 400 000 ሰዎች እና አንድ ሚሊዮን እንስሳት ሞተዋል፤ ኮሎሲየም የሮማውያንን አሳዛኝ ታሪክና የግንባታ ጥበብ አንድ ላይ የሚያስታውስ ቅርስ ነው። ሕዝቡን ለማዝናናት ተብሎ የሚፈሰው የብዙ ሰውና የእንስሳት ደም ዳንኤል የሮማን መንግሥት ጨካኝ አውሬ ብሎ ከገለጸበት አገላለጽ ጋር በትክክል አብሮ ይሄዳል። በ312 ዓ.ም. ለሮማ ጳጳስ የተሰጠው የላተራን ቤተመንግሥት እስከ ዛሬ ድረስ የፖፑ መኖሪያ ቤት ሆኖ ቀርቷል።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የዓለም ሁሉ ታላቅ ቤተክርስቲያን መሆንዋን ለማስረዳት ኦጋስተን መዳን በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አማካኝነት ብቻ ነው የሚል አስተምሕሮ አዘጋጀ። የሰዎች ነፍስ የሚድንበትን ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች መፈጸም የምትችለው የሮማ ቤተክርስቲያን ብቻ ናት።

ኦጋስተን መዳንን ከአዳኛችን ከኢየሱስ እጅ ነጥቆ በሮማ ካቶሊክ ካሕናትና በጳጳሳቱ እጅ እንዲገባ አደረገ።

በሐጢያተኛው እና ሐጢያተኛውን በሚያድነው በኢየሱስ መካከል የሐይማኖት መሪዎችን አስገብቶ ከፍ አደረጋቸው። ይህም ውጤታማ ሳይሆን ወደቀረው የብሉይ ኪዳን ክሕነት መመለስ ነው።

ኒቆላዊነት ወይም አንድን ቅዱስ ሰው በጉባኤው ላይ ከፍ የማድረግ ሥርዓት በኦጋስተን አማካኝነት አስተምሕሮ ሆኖ መጣ።
ከዚያም በቤተክርስቲያን ውስጥ ጣኦታትን አስገቡ፤ የኑዛዜ ሳጥን ውስጥ ተቀምጦ ሐጢያታችሁን ስትናዘዙ የሚያዳምጥ ካሕን መደቡ፤ ደግሞም ፖፑን የክርስትና ሁሉ ራስ አድርገው ሾሙ። ይህ የይሁዳ ወንጌል ነው። ከዚያም ትምሕርት ቤቶችን ከፍተው ሰባኪዎች በእግዚአብሔር መንፈስ በመመራት ፈንታ በትምሕርት እንዲሰለጥኑ አደረጉ። ከዚያ ዶክተሬት ወይም ፒኤችዲ ሰጡዋቸው።

የጥንቶቹ ሐዋርያት አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምሕርት ቤት አልከፈቱም።

ለቤተክርስቲያን አንድነት ከነበረው ቅንዓት የተነሳ ኦጋስተን በየቤተክርስቲያኑ በሚሰጡ አስተምሕሮዎችና በሚፈጸሙ ሥርዓቶች መካከል አንድም ልዩነት መኖር የለበትም አለ። በኦጋስተን አመለካከት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሰዎችን ማዳን የምትችል ብቸኛዋ ምድራዊ ድርጅት ነበረች።

በዚህም ሌሎች ሐይማኖቶች ሁሉ ሕገወጥ ተብለው እንዲታገዱ አደረገ።

ማስፈራሪያ፣ ቅጣትና፤ ስቃይን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ሁሉ የቤተክርስቲያን አባላት እንዲሆኑ የማድረጉን ዘዴ በደስታ ሥራ ላይ እንዲውል ሃሳብ አቀረበ።

ዓላማው መልካም ሆኖ ሳለ ዘዴዎቹ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ያፈነገጡ በመሆናቸው ኦጋስተን ያመጣው ሃሳብ በጭካኔ የተደራጀ የማሳደድ፣ የማሰቃየትና የነፍስ ግድያ ሥርዓት እንዲቋቋም መሰረት ጣለ። አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ኦጋስተንን የስደት ሐዋርያ ይሉታል። ኦጋስተን በትምሕርቱ ያስተላለፈው ስሕተት አስከፊ ውጤቱ ከሰው አእምሮ በላይ የሆኑ ስቃዮችንና ጭካኔዎችን ወለደ።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የተቃወሙ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሰዎች አውሮፓ ውስጥ በጭካኔ ተገደሉ፤ የስፔይን ገዥዎች በደቡብ አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ኩባ በሄዱበት ከ15 ሚሊዮን በላይ ኢንዲያኖች ያለ ምንም ርህራሄ በግፍ ተጨፈጨፉ።

በ321 ዓ.ም. የሮማ ገዥ ኮንስታንቲን ሰዎች በኑዛዜያቸው ውስጥ መሬታቸውን ለቤተክርስቲያን በስጦታ እንዲያበረክቱ ሕጋዊ ፈቃድ ሰጠ። ቤተክርስቲያንም ወዲያ የብዙ መሬት ባለ ሃብት ሆነች።

ኮንስታንቲኖፕልን (ከ225 እስከ 330 የተመሰረተችዋን) የክርስቲያን ከተማ ለማድረግ በመፈለግ ኮንስታንቲን ፖንቲፌክስ ማክሲመስ (ፖንቲፍ ወይም የባቢሎናውያን ምስጢር ሊቀ ካሕናት) የተባለውን አረማዊ ማዕረግ በአረማዊቷ ሮም ውስጥ ብቻ እንዲያገለግል ወሰነ። በስተመጨረሻም ይህ የማዕረግ መጠሪያ በ450 ዓ.ም. ለፖፕ ሊዮ ቀዳማዊ ተላለፈ።

ኮንስታንቲን በቤተክርስቲያን ውስጥ አንዳች እንኳ መከፋፈል ቢኖርና የቤተክርስቲያን አንድነት ቢረበሽ እግዚአብሔር ይቀጣኛል ብሎ አመነ። ስለዚህ ፖለቲካዊ ስልጣኑን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን መቅጣትና የእግዚአብሔር ሕግ ብሎ እርሱ ላመነበት ትዕዛዝ ሰዎች ሁሉ እንዲታዘዙ ማስገደድ እንዳለበት ተሰማው። ቤተክርስቲያን እና መንግሥት ባለተቀደሰ ጋብቻ አንድነት ውስጥ ገቡ። ንጉሱ ራሱ መንግሥት የትኛውን አስተምሕሮ ትክክለኛ ሐይማኖት አድርጎ መደገፍ እንዳለበት ወሰነ፤ ይህንንም ሲያደርግ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል መለወጥ ቢያስፈልግም እንኳ ምንም ግድ አልነበረውም። ከዚያም የሮማ መንግሥት ኃይል የጦር መሳሪያዎቹን በመጠቀምም ቢሆን እነዚህን እምነቶች ሕዝቡ እንዲቀበሉ ያስገድዳቸዋል፤ ሕዝቡም አንድ ምርጫ ብቻ ነበራቸው እርሱም ለሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መገዛት ነው። ኮንስታንቲን በካየሊያን ኮረብታ ላይ ያለውን የላተራን ቤተመንግሥት ለሮም ጳጳስ መኖሪያ ሰጠ፤ በተጨማሪ ብዙ ገንዘብ ለገሰ፤ ይህም የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የመንግሥት እውቅና እና የመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ያላት ቤተክርስቲያን ሲያደርጋት የቤተክርስቲያኒቱም ራስ ንጉሱ ሆነ።

ቀጣዩ ትልቅ ስሕተት ይህ ነበር፤ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል የቤተክርስቲያን ራስ ወይም የቤተክርስቲየን ጌታ መሆኑ ቀረ።

ፖለቲከኛው ኮንስታንቲን የሮማ ቤተክርስቲያን ራስ ሆነ፤ የሮማ ካቶሊክም በሮማ ግዛት ውስጥ የመንግሥት ሐይማኖት ሆነች።

የቤተክርስቲያን ሰዎችን አብላጫ ድምጽ በማግኘት የሮማ ቤተክርስቲያንን የሚቃወሙ ሰዎችን የመቅጣትና ከግዛቱ የማባረር ስልጣንን ለራሱ ወሰደ። ይህ ቁልፍ ውሳኔ ነበር። ከዚያ በፊት ለሁለት መቶ ሃምሳ ዓመታት ስትሰደድ የነበረች ቤተክርስቲያን በተራዋ አሳዳጅ ለመሆን የመጀመሪያውን እርምጃ ጀመረች።

በ325 ዓ.ም. ከተደረገው የኒቂያ ጉባኤ በኋላ በመጀመሪያው ወር በ14ኛው ቀን ጨረቃ ሙሉ ስትሆን የክርስቲያኖችን ፋሲካ የሚያከብሩ ሰዎች ላይ ከባድ ስደት እንዲነሳ አዘዘ። እስከ ዛሬም ድረስ ፋሲካ ሙሉ ጨረቃ ስትሆን አይከበርም።

ኮንስታንቲን በኒቂያ ጉባኤ ላይ በተደረገው ውሳኔ የማይስማሙ ሰዎችን ሁሉ አሳደደ ደግሞም ከግዛቱ አባረረ።

ሰዎች ሌሎችን ሰዎች ለማሳደድ አሳማኝ ሃሳቦችን መፍጠር ጀመሩ።

በ378 ዓ.ም. ቴዎዶሲየስ ገዥ ሲሆን አረማውያንን ለማሳደድ አዲስ ሕግ ደነገገ። ከዚያ በኋላ በዚህ ሕግ አማካኝነት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የተቃወመ ሁሉ ወንጀለኛ ተባለ። ከመቶ ዓመታት በፊት ስደተኛ የነበረችዋ አሁን ደግሞ የመንግሥትን እውቅና ያገኘችው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ኃይለኛ አሳዳጅ ሆነች። ይህም ቤተክርስቲያን ከፖለቲካ ጋር በመጋባቷ ያፈራችው ፍሬ ነው።

ቅዱስ ኦጋስተን (354 – 430 ዓ.ም.) ስሕተት በፍጹም በትዕግስት መታየት የለበትም። እንደ ኦጋስተን አባባል ግፍን በመጠቀም ማስገደድ ተገቢ ነው።

ኦጋስተን ማሳደድ በሁለት ይከፈላል አለ፤ ይህም በጥላቻ ተነሳስተው የሚያሳድዱ የማያምኑ ሰዎች እና ከፍቅር ተነሳስተው የሚያሳድዱ ክርስቲያኖች። ክርስቲያኖችን እስከ ወደድካቸው ድረስ እነርሱን መግደል እና ማሰቃየት ትችላለህ።

ደግሞም የቤተክርስቲያን ሰዎች እጃቸው በደም የማይነካካበትን መንገድም አዘጋጀ፡- ቤተክርስቲያንን መቃወም መንግሥትን መቃወም ተብሎ እንዲተረጎም አደረገ፤ ስለዚህ ቤተክርስቲያን የፈረደችበት ሰው በመንግሥት እጅ መቀጣት አለበት።

በ385 ዓ.ም. ስፔይናዊው ጳጳስ ፕሪሲሊያን ኑፋቄ አስተምሯል ተብሎ በስፔይን ጳጳሳት ጥያቄ በንጉስ ማክሲመስ አማካኝነት በሞት ተቀጥቷል። ይህም ከዚያ ወዲያ እጅግ ብዙ ሰዎች እንዲገደሉ በር ከፈተ።

ፖፕ ሊዮ ቀዳማዊ (440 – 461 ዓ.ም.) መንግሥት ስለ ቤተክርስቲያን ብሎ መናፍቃንን ስላሰቃየና ስለገደለ ንጉሱን አመሰገነ።

ክርስቲያኑ ንጉስ ጀስቲኒያን በ527 እና በ528 ዓ.ም. በመናፍቃን ላይ ጨካኝ እርምጃ የሚወስድ ሕግ አወጣ።

ከኦጋስተን ጀምሮ ለአንድ ሺ ዓመታት ያህል ክርስቲያን ቲዎሎጂያኖች በሙሉ መናፍቃን ሊሰደዱ እንደሚገባቸው አምነውበታል፤ ብዙዎቹም ደግሞ መገደል አለባቸው ብለው ተስማምተዋል።

ቅዱስ ቶማስ አክዊናስ (1225-1274) መናፍቃንን በእሳት ማቃጠል ጽድቅ ነው ብሎ ያስብ ነበር፤ ደግሞም ከነነፍሳቸው ሳሉ በእሳት ማቃጠል ይመረጣል ብሏል።

ደግሞም እንዲህ ብሎ ጽፏል፡-
“መናፍቃንን በተመለከተ ሁለት ነጥቦቦችን ማየት አለብን፡- አንደኛበራሳቸው በመናፍቃን በኩል ሁለተኛ ደግሞ በቤተክርስቲያን በኩል። በራሳቸው በኩል ሐጥያት አለባቸው ስለዚህ በውግዘት ከቤተክርስቲያን መወገድ ብቻ ሳይሆን ከዓለምም በሞት መለየት አለባቸው። ምክንያቱም ነፍስን የሚያነቃውን እምነት ማርከስ ጊዜያዊ ኑሮን ለማሸነፍ ብሎ የሐሰት ገንዘብ ከማምረት የሚብስ ሐጢያት ነው። እንግዲህ ሐሰተኛ ገንዘብ የሚሰሩ ሰዎች እና ወንጀለኞች በዓለማዊ መንግሥት በኩል የሚፈረድባቸው ከሆነ መናፍቃን ደግሞ ኑፋቄ ሲገኝባቸው ለማውገዝ ብቻ ሳይሆን በሞት ለመቅጣትም ጭምር በቂ ምክንያት አለን።” ቅዱስ ቶማስ አክዊናስ
ነፍስ ግድያ በፍጥነት እውቅና እያገኘ ሄደ።

ስለዚህ ኮንስታንቲን የተከለው የስደት ዘር ፖፕ ሊዮ ውሃ እያጠጣው አድጎ በጨለማው ዘመን ውስጥ ለብዙዎች ሞት ምክንያት ከመሆን አልፎ በማርቲን ሉተር አማካኝነት የመጣውን ለውጥ ለመቃወምም አገልግሏል።

ከአስርኛው ክፍለ ዘመን ማለቂያ ጀምሮ መናፍቃንን በሞት መቅጣት እጅግ እየተለመደ መጣ፤ የሚገደሉባቸው ምክንያቶች ለሞት የማያበቁ ነበሩ። ለምሳሌ በ1051 ዓ.ም. ጀርመኒ ውስጥ ጎስላር የሚባል ቦታ ዶሮ ለማረድ እምቢ ያሉ ክርስቲያኖች ኑፋቄ አስተምረዋል ተብለው በሞት ተቀጥተዋል።

ኮንስታንቲን “አረማውያንን በሙሉ ወደ ክርስትና ስላመጣ” ሰዎች ሁሉ ኮንስታንቲን ጥሩ ሰው ነው ብለው ያስቡ ነበር። ነገር ግን ኮንስታንቲን ሊሞት እያጣጣረ ሳለ የተጠመቀ የፀሃይ አምላኪ ነበር፤ አረማውያንንም “ክርስቲያን ያደረጋቸው” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ላልሆኑ ስርዓቶቻቸውና ልምምዶቻቸው ክርስቲያናዊ ስም በመስጠት ብቻ ነው።

ቤተክርስቲያን ማለት ከዓለም ተለይታ ተጠርታ የወጣች ማለት ነው የምትለየውም ለክርስቶስ ብቻ እንድትሆን ነው።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ሕብረት ውስጥ መግባቷ ለቤተክርስቲያኒቱ ፖለቲካዊ ስልጣን ሰጣት።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለጌታ መገዛት ስላቆመች ከኢየሱስ ዘንድ የነበራትን መንፈሳዊ ስልጣን በምድራዊ ስልጣን ለወጠችው። ጊዜያዊ ጥቅሞችዋ ብዙ ነበሩ፤ የሮማ ቤተክርስቲያን ሕዝባዊና ፖለቲካዊ ስልጣን እና እንዲሁም ሐይማኖታዊ ተቃዋሚዎችዋን የምታሳድድበት ኃይል አገኘች። ቤተክርስቲያን ነፍሷን የሸጠችለት የሮማ ግዛት ግን እየበሰበሰ እየፈራረሰ ሄዶ በስተመጨረሻ በ476 ዓ.ም. በታላቅ አወዳደቅ ወደቀ።

ተርቱሊያን (160-225 ዓ.ም.) አንድ የጋራ “ሕልውና” ያላቸውን ሦስት ግለሰቦች ለመግለጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥላሴ ወይም ትሪኒቲ (በላቲን “ትሪኒታስ”) የሚለውን ቃል ተጠቀመ። ግን ተርቱሊያን ያመነው አግዚአብሔር አብ ብቻ ነው አምላክ ሊባል የሚችለው። የይሆዋ ምሥክሮችም ስለ እግዚአብሔር መለኮት ያላቸው ትምሕርት ልክ እንደዚሁ አይነት ነው።

ቤተክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር ያላትን አመለካከት አንድ ወጥ ለማድረግ እንዲቻል ኮንስታንቲን በኒቂያ ከተማ (ከጴርጋሞን በስተ ሰሜን) ጉባኤ እንዲደረግ አዘዘ። ቤተክርስቲያንም በመለኮት ውስጥ ያሉትን ሦስቱንም አካላት እኩል እግዚአብሔር እንደሆኑ አድርጋ ለማየት እየሞከረች ነበር። ኮንስታንቲን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ “ኤሰንስ” የሚባል ቃል ከግሪክ ፍልስፍና ተውሶ አመጣ። ይህም ግልጽ የሆነ ቁርጥ ያለ ትርጉም የማይሰጥ አሪፍ ቃል ነው። ሦስቱ አካላት እያንዳንዱ አምላክ ናቸው ምክንያቱም አንድ አይነት ኤሰንስ አላቸው (ኤሰንስ ምን እንደሆነ ባናውቅም)። በጉባኤው የተገኙ 318 ጳጳሳት በዓይን የማይታየውን መንፈስ በሰው አእምሮ አቅም ለመግለጽ እየሞከሩ ነበር። ይህም የሚቻል አልነበረም ምክንያቱም “መንፈስ” ምን እንደሆነ ማንም አያውቅም። ሁላችንም በውስጣችን የሕይወት መንፈስ አለን ግን ምን እንደሆነ ወይም እንዴት እንደሚሰራ ማናችንም አናውቅም። ይህም የማናውቀው የሕይወት መንፈስ ለያንዳንዳችን ስብዕና ይሰጠናል፤ ግን ስብዕና በእርግጥ ምን እንደሆነ ማናችንም አናውቅም።

የመንፈስን ታላቅነት በሰዎች ቋንቋ ተጠቅመን ልንገልጽ አንችልም ምክንያቱም ቋንቋችን መንፈስን ለመግለጥ ብቁ የሆኑ ቃላት የሉትም።

2ቆሮንቶስ 12፡4 ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።

1ቆሮንቶስ 2፡9 ነገር ግን፦ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።

ስለዚህ ሰማይ ምን አይነት እንደሆነ መገመት እንኳ አንችልም። እግዚአብሐር ምን እንሚመስልማ ከምን ተነስተን እንገምታለን?
እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል ለመግለጽ መሞከር ከሰው ሁሉ አቅም በላይ ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ እኛ ደግሞ መንፈስ ምን እንደሆነ እንዴት እንደሚሰራም አናውቅም።

ኮንስታንቲን በሰይጣን አነሳሽነት እግዚአብሔር ምን አይነት እንደሆነ ለመግለጥ እንዲሞክሩ በማድረግ ቤተክርስቲያን ጥልቅ ሚስጥር ውስጥ እንድትገባ አስገደዳት። እራሳቸውን እንደ ጠቢብ በመቁጠር ጳጳሳቱ እንችላለን ብለው አሰቡ። አንዳንድ ሚስጥሮች የሚገለጡት ከተምሳሌት ጀርባ በመሰረው ነው። ሴት የቤተክርስቲያን ተምሳሌት ናት። ስለዚህ ራዕይ 17 ውስጥ ያለችው ሴት ቤተክርስቲያን ናት።

የተምሳሌቱን ትክክለኛ ፍቺ ካገኘን ምስጢሩን መግለጥ እንችላለን።

ነገር ግን ሌሎች ምስጢራት በእኛ ሊፈቱ አይችሉም። በራዕይ ምዕራፍ 10 ውስጥ ሰባቱ ነጎድጓዶች የተናገሩት ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም። ስለዚህ የምንተረጉመው ተምሳሌት የለምና ይህንን ምስጢር ልንፈታ አንችልም ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም።

ስለዚህ ከምስጢራት መካከል ሰው እንዲፈታ እድል የተሰጠው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉትን ብቻ ነው።

ሰይጣን ካሰባቸው ማታለያዎች ሁሉ እጅግ የረቀቀና በጣም የተሳካለት ኮንስታንቲንን በመጠቀም የቤተክርስቲያን ጳጳሳት የማይታየውን እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ እና ከግሪክ ፍልስፍና በተውሶ በመጡ ቃላት እንዲገልጹ ባስገደደበት ጊዜ ነው።

ይህንን ሃሳብ ግልጽ ለማድረግ ስለ ኃይል ወይም ኤነርጂ እንወያይ፤ ኤነርጂ በዓይን አይታይም። ሳይንቲስቶች ኤነርጂ ምን እንደሆነ አንዳችም አያውቁም። ስለ ኤነርጂ መናገር የሚችሉት ከተለያዩ ስሌቶች ውስጥ የሚገኝ ቁጥር ብቻ ነው። ኤነርጂን ማስላት እንችላለን። ምን ያህል ኤነርጂ ስለመኖሩ ፎርሙላ ወይም ቀመር አዘጋጅተን መለካት እንችላለን። ግን ኤነርጂ ራሱ ምንድነው? ምንም አናውቅም።

በዓይን የማይታየውን ለመግለጽ መሞከር ለሰው የማይቻል ሥራ ነው፤ መሞከሩም ለስሕተት ያጋልጣል። የኤነርጂ “መገለጫዎች” እያልን ልናወራ እንችላለን ግን “መገለጫዎች” የሚለው ቃል የሚታዩ ነገሮችን ነው የሚወክለው። ኤነርጂ ራሱ ግን የሚታይ ቅርጽ የለውም። ስለዚህ የኤነርጂ ቅርጽ ብሎ ማውራት ልክ አይደለም። ኤነርጂ ቅርጽ የሌለው ኤነርጂ ነው። ኤነርጂን ሊገልጸው የሚችል ሌላ ቃል የለም።

እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ መንፈስ ምን እንደነ ማወቅ አንችልም። መንፈስን ማየት አንችልም። ስለዚህ ስለ እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ሰምተን ብቻ ብናርፍ ይሻለናል።

ግን የማይታየውን እግዚአብሔር ለመግለጽ ሲሞክሩ ጳጳሳቱ ሃሳብ ለማግኘት ከሰዎች ሁሉ ብልጥ የሆኑትን የግሪክ ፈላስፎች ማዳመጥ ጀመሩ። የግሪክ ፈላስፎች አረማውያን እንደመሆናቸው ከሁለት ጥንታውያን አረማዊ ስልጣኔዎች ብዙ ሃሳብ ቀድተዋል፤ እነርሱም ግብጽና ባቢሎን ሲሆኑ ሃሳባቸው በብዙ አረማውያን ስልጣኔዎች ላይ ተጽእኖ አድርጓል። ግሪኮች ብዙ ብልህ ሃሳብ ያላቸው ብልህ ሕዝብ ናቸው። ብልህ መሆን ግን አንድ ሃሳብ ጥሩ ወይም መልካም እንዲሆን ዋስትና አይሰጥም። ብልህ ሰዎች አቶሚክ ቦምብ ፈጠሩ፤ ግን አቶሚክ ቦምብ ጥሩ ፈጠራ አይደለም፤ ያለ አቶሚክ ቦምብ ሰዎች የተሻለ ኑሮ መኖር ይችላሉ።

መለኮታዊ ሦስትነት በጥንታዊ አውሮፓ፣ ግብጽ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና በእስያ ሐይማኖታዊ ጽሑፎችና የሥነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ በብዛት ይገኛል። እነዚህ ሦስትነቶች ልዩ ልዩ ገጽታዎች አሉዋቸው፡ ወንድ አማልክት፣ ሴት አማልክት፣ አባት እናትና ልጅ፤ ወይም ሦስት ራሶች ያሉት አንድ አካል፤ አለዚያም ሦስት ፊቶች ያሉት አንድ ራስ።

ባቢሎንና አሦር በአንድ አካባቢ ስለሆኑ ብዙ የሚጋሩዋቸው እምነቶች ነበሩዋቸው። ባቢሎን ልክ ናቡከደነፆር ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት አሦርን አሸንፋ ገዛች፤ ናቡከደነፆር ዳንኤል በተረጎመው የአሕዛብ መንግሥት ምስል ውስጥ የወርቁ ራስ ነው። ስለዚህ አሦር እስከነ አረማዊ ሐሳቦችዋ የባቢሎን አካል ሆነች። ራስ የምናስብበት የሰውነት ክፍል ነው። ናቡከደነፆር የባቢሎናውያንንና የአሦራውያንን አስተሳሰብ አንድ ላይ በማዋሃድ አንድ ሐይማኖታዊ ሥረዓት ፈጠረ።

ከዚህ በታች ያለው ካርታ አሦርና ባቢሎን ምን ያህል እንደሚቀራረቡ ያሳያል። ካርታው ላይ አረንጓዴው ቀለም የባቢሎንን ግዛት ያሳያል።

የአማልክትን ሥላሴነት የሚያሳይ ቀደምት የቅርጻ ቅርጽ ሥራ የሚገኘው አሦር ውስጥ ነው። እርሱም አንድ ታላቅ ራስ አብ እንደሆነ እና ሁለት ሌሎች ራሶች በመለኮት ውስጥ ያሉ ሁለት ሌሎች አካላት እንደሆኑ ያሳያል። መለኮት እራሱ የተወከለው በወፍ ቅርጽ ነው።

ናቡከደነፆር ካስተዳደራት ባቢሎን በፊት የሚቀድሙ ብዙ መንግሥታት ነበሩ።

የዳንኤል ምስል ለምንድነው ከናቡከደነፆር የባቢሎን መንግሥት የሚጀምረው? ምክንያቱም የባቢሎን ሥርዓተ ክሕነት የአሦርን ሥላሴ ስለተቀበለ እና የባቢሎናውያን ምሥጢር በዚህ የአረማውያን ሐይማኖታዊ ቫይረስ ስለተበከለ ነው። ዳንኤል በብሉይ ኪዳን ዘመን ውስጥ ከተፈጠሩ አደገኛ ሃሳቦች ውስጥ አንዱ የአሕዛብ የሥላሴ እምነት እንደሆነ ተረድቷል፤ ስለዚህም እንደ ጥሩ የሕክምና ባለሙያ የዚህን በሽታ ሥርጭት ከሥላሴ ትምሕርት አካሄድ ጋር በጥንቃቄ ለመከታተል ወስኗል። በዚያን ሰዓት የሥላሴ ትምሕርት በደምብ ስላልዳበረ ወደየሃገሩው ለመሰራጨት ገና አልተዘጋጀም ነበር። ጊዜው ገና ነበር፤ ግሪኮችም ገዥ ሊሆኑ ገና ጥቂት መቶ ዓመታት ይቀራቸው ነበር፤ ነገር ግን ግሪኮች ወደ ሥልጣን ሲመጡ የሥላሴን ሃሳብ ወልውለው አሰማምረው ለክርስቲያኖች በቀላሉ እንዲዋጥላቸው አድርገው ያቀርቡታል።

እስከዚያ ድረስ ግን የባቢሎናውያንን ምስጢራት የሚያራምደው ፖንቲፍ ወይም ሊቀ ካሕን ፋርስ ባቢሎንን ባሸነፈች ጊዜ ተደብቆ የሚቆይበት ቦታ ያስፈልገው ነበር። ስለዚህ ሊቀ ካሕኑ አታለስ ወደ ጴርጋሞን ሸሸ። በዚህም ምክንያት ይህ ሦስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በጴርጋሞን ስም ሊጠራ ችሏል። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ323 ዓመተ ዓለም አሌግዛንደር (ታላቁ እስክንድር) ፋርሶችን አሸንፎ ገዛና ራሱን አምላክ ብሎ ጠራ። ከዚያም ጴርጋሞንን ከአሌግዛንደር ጀነራሎች አንዱ ላይሲማከስ የሚባለው ሲይዛት እርሱም ራሱን አምላክና ንጉስ ብሎ ሰየመ። ጴርጋሞን ውስጥ እርሱን የተኩት በጌጠኛ ልብሳቸውና በባቢሎናዊ ሥርዓቶቻቸው የሚታወቁት ሊቀ ካሕናት ሲሆኑ እነርሱም ራሳቸውን አማልክትና ነገሥታት ብለው ሰየሙ።

የጴርጋሞን የመጨረሻው አምላክ-ንጉሥ-ሊቀ ካሕን አታለስ 3ኛው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ133 ዓመተ ዓለም መንግሥቱን ለሮም አስረከበ። ከዚያ በኋላ ፖፕ ሊዪ ቀዳማዊ በ450 ዓ.ም. አካባቢ ፖንቲፍ ወይም የባቢሎናውያን ምስጢራት ሊቀ ካሕን ተብሎ ሲሾም ነው ምስጢራቱ ወደ ቤተክርስቲያን ሾልከው መግባት የቻሉት።

የዳንኤል ራዕይ ውስጥ የተገለጠው ሐውልት በብሉይ ኪዳን ዘመን ውስጥ የባቢሎንን ምስጢራት ከመነሻ እስከ መድረሻቸው ያሳያል።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፍ እንዴት ወደ ቤተክርስቲያን ሾልከው እንደሚገቡ ያሳያል። የገቡባት ቤተክርስቲያንም ጋለሞታይቱ ባቢሎን ትባላለች ልጆችዋም ጋለሞታዎቹ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች ናቸው።

እውቁ የግሪክ ፈላስፋ ፕሌቶ ትራያድ (Triad) የሚባለውን ቃል ፈለሰፈ። ከዚያም ተፈጥሮ ውስጥ የሦስትነት ባሕርይ አለ ብሎ ተናገረ።

ሰማይ፣ ምድር፣ ውሃ። ፀሃይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት። መፍጠር፣ ማኖር፣ ማጥፋት።

በዚህም መንገድ ፕሌቶ አሕዛብ ስለ አምላክ ያለቸውን አመለካከት ትራያድ በማለት በሦስትነት ለመግለጥ ሞከረ። ተርቱሊያንም (ከ155 – 240 አካባቢ) ካርቴጅ ውስጥ ይህንን ተቀብሎ ወደ ላቲን በመተርጎም “ትሪኒታስ” አለ።

የግሪክ ፈላስፎች ያመጡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አባባል “አንድነት በሦስትነት” እና “ሦስትነት በአንድነት” ኋላ “አንድ አምላክ በሦስት አካላት” የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አባባልን ወለደ። ኮንስታንቲንም ከግሪክ ፈላስፎች በመኮረጅ “ኤሰንስ” ወይም ባሕርይ የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ቃል አመጣ። አብ እና ወለድ በኤሰንስ (በባሕርይ) አንድ ናቸው። ይህ ምንም ትርጉም አይሰጥም ምክንያቱም መንፈስ ምን እንደሆነ አናውቅም። ኤሰንስ ራሱ ምን እንደሆነ በትክክል መግለጽ አንችልም። ከዚያም ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለተጻፈ መልኩ “የመለኮት ሁለተኛው አካል ሆነ”። ጳጳሳቱ የማይታየውን እግዚአብሔርን ለመግለጽ ሲሞክሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ቃላትን መጠቀም ባበዙ ቁጥር መጽሐፍ ቅዱስን ከነጭራሹ መጠቀም አቆሙ። የሮማ ካቶሊክ ጳጳሳት የሥላሴን አስተምሕሮ በየክፍለዘመናቱ እያዳበሩ በሄዱ ቁጥር አስተምሕሮው ለብዙ ጊዜ ተሻሽሏል።

ነገር ግን ከአረማውያን ዘንድ ብዙ የሥላሴ ስዕላዊ መግለጫዎችን ማግኘት ችለዋል።

ግብጽ ብዙ ሥላሴዎች ያሏት ሲሆን እነርሱም በስዕሎቻቸው በአንድ ዙፋን የሚቀመጡ ሦስት ሰዎች ናቸው። ሦስት ሰዎች በአንድ አምላክ።

አይሲስ፣ ኦረስ (ወይም ኦሲሪስ) እና ሴብ (ወይም ሴት) አንዱ የግብጽ ሥላሴ ነው።

አሞን ራ ወይም አሙን ራ፣ ራምሲስ፣ እና ሙት ደግሞ ሌላኛው የግብጽ ሥላሴ ነው።

ይህ ለክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባቸው ሞዴል ወይም መልካም አርአያ አይደለም። ዙፋን ላይ የተቀመጠ እግዚአብሔር በአእምሮዋችን ደግሞም አዳኙ (ኢየሱስ) ከጎኑ ቆሞ ወይም ተቀምጦ በአእምሮዋችን መሳል የለብንም።

ኢሳያስ 43፡11 እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።

ከዚህ በታች ያለው ስዕል ሥላሴን የሚወክል የቤተክርስቲያን ስዕል ነው። ቀጥታ ከግብጾች ስዕል ተኮርጆ ነው የተሳለው። ሆኖም ግን ብዙ ክርስቲያኖች ዛሬ እግዚአብሔርን እንደዚህ ነው የሚያስቡት።

በአንድ አካል ላይ ሦስት ራሶች ደግሞ አንድ አምላክ በሦስት አካላት የሚለውን ሃሳብ ለመግለጽ የተደረገ ሌላ ሙከራ ነው፤ ለምሳሌ ከዚህ በታች ሒንዱዎች የቀረጹት ምስል።

ባቢሎን፡- አኑ ኢንሊል ኢያ
ሒንዱ፡- ቪሽኑ ብራሕማ ሲቫ

ስለዚህ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይህንኑ አረማዊ ሃሳብ በክርስቲያናዊ ቋንቋ ቀባብታ ነው እውነት ብላ ያስተማረችው። ይህም ክርስትና የተነሳ አረማዊነት ነው።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም የተጠመቀች ክርስትና የተነሳች አረማዊነት ናት።

ዮሐንስ 1፡18 መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤

ስለዚህ እግዚአብሔርን በስዕል ለመግለጥ መሞከር ከንቱ ድካም ነው።

አንድ ታዋቂ የሆነ ሰዓሊ በትራክቶች ላይ እግዚአብሔርን በዚህ መልኩ ይገልጻል፡-

የአሦራውያንን ሥላሴ ሲስሉ የወፍ ምስል እንደተጠቀሙ ሁሉ በዚህ ስዕል ውስጥ መንፈስ ቅዱስን ለመወከል የእርግብ ምስል እንደተጠቀሙ ልብ በሉ።

በዚህ ስዕል ውስጥ እግዚአብሔር አብ ፊት የለውም፤ አካል ሆኖ ሳል ፊት ላይኖረው መቻሉ በጣም እንግዳ ነገር ነው።
እርግብ ስብዕናን አይወክልም። ይህ ስዕል የሁለት ሰዎች ምስል ይመስላል። ስለዚህ ሥላሴን በዚህ ስዕል ለመግለጥ የተደረገው ሙከራ አጥጋቢ አይደለም።

ዮሐንስ 5፡37 የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል፡፡ ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፥ መልኩንም አላያችሁም፤

መንፈስ የሆነውን እግዚአብሔርን የሆነ መልክ ወይም ቅርጽ እንዳለው አድርጎ ማሰብ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚቃረን ልማድ ነው። በፍጹም ይህን ማድረግ የለብንም።

ከዚያም ትራክቱ ትንሽ የተሻለ ዘዴ ሲያመጣ መለኮትን ለመወከል ሦስት ብርሃናትን ይጠቀማል። ከጀርባቸውም አንድ መልዓክ ይቆማል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር ብርሃን ነው እንጂ ሦስት ብርሃናት ነው አይልም። ስለዚህ ሥላሴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አብሮ አይሄድም።

1ኛ ዮሐንስ 1፡5 ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው … የምትል ይህች ናት።

ይህ ሦስት ብርሃናትን የሚያሳየው ስዕል አንድ ሆኖ ግን ዳር ዳሩ ድብዝዝ ያለ ወይም ጥርት ያላለ ብርሃን ነው። ጥርት ያለ ብርሃን ከሚያበራው፣ እግዚአብሔር ሦስት ብርሃናት ነው ከማይለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይገጥምም።

ስለዚህ ሥላሴን እንዴትም አድርገህ ብትስል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መቼም አይገጥምም። ስለዚህ በኒቂያ ጉባኤ ላይ ሥላሴ እጅግ ማራኪ የሆነ ምስጢር ሆኖ ወደ ቤተክርስቲያን ገባ። ያን ጊዜ ሥላሴን ማብራራት የሚችል አልነበረም፤ ዛሬም ሊያብራራ የሚችል የለም ምክንያቱም በትምሕርቱ ውስጥ ያሉ እንደ “እግዚአብሔር ወልድ” እና “እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ” የመሳሰሉ ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉም፤ “እግዚአብሔር አብ” ግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ። ይህም ለምን እንደሆነ በሥላሴ የሚያምኑት ሊነግሩን አይችሉም።

በዚያ ዘመን ጳጳሳት አብና ወልድ ሁለት የተለያዩ አካላት ነገር ግን አንድ አምላክ እንደሆኑ ይከራከሩ ነበር። ይህ ሃሳብ እስከ ዛሬ ደረስ ለማንም ግልጽ ያልሆነ ሃሳብና እስከ ዛሬ ድረስ ያልተፈታ ምስጢር ሆኖ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት የባቢሎን ምስጢር የሚለው ስም የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስም ሆኗል።

ጊቦን የተባለ ታላቅ የታሪክ ምሑር እንዲህ አለ፡- “ክርስትና አረማዊነትን አንበረከከ፤ ከዚያ በኋላ ግን አረማዊነት ክርስትናን በረዘ”።
የሥላሴን አስተምሕሮ ለማብራራት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የራሷን ቃላት መፈልሰፍና ምንጫቸው ከፍልስፍና የሆኑ ቃላትን በተውሶ መጠቀም አስፈልጓታል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካተኪዝም

በሥላሴ አስተምሕሮ መሰረት አብ እና ወልድ በሥላሴ ውስጥ እኩል ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ ሃሳብ ጋር ይቃረናል።

ዮሐንስ 14፡28 … ከእኔ አብ ይበልጣልና …

በሥላሴ አስተምሕሮ መሰረት እግዚአብሔር አብ ከመንፈስ ቅዱስ የተለየ አካል ነው።

ማቴዎስ 1፡20 እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።

የወንድን ዘር በሴት ማሕጸን ውስጥ የሚያኖር የሕጻኑ አባት ነው።

ስለዚህ በማርያም ማሕጸን ውስጥ ዘር የፈጠረ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ መሆን አለበት። ሕጻኑ ኢየሱስ እንደ ሰው ሁለት አባቶች ሊኖሩት አይችልም።

የሥላሴ አስተምሕሮ ክርስቶስ በመለኮት ውስጥ ሁለተኛው የመለኮት አካል ሆኖ ይኖራል ይላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ ሃሳብ ጋር ይጋጫል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው የእግዚአብሔር ሙላት ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ ውስጥ ነው።

ቆላስይስ 2፡8 እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።

9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤

ጳውሎስ በፍልስፍና እንዳንማረክ ያስጠነቅቀናል፤ ምክንያቱም የግሪክ ፍልስፍና አማኞችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አርቆ በመውሰድ በክርስትና አስተሳሰብ ላይ ምን ያህል ከባድ ጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል አስቀድሞ ተረድቷል።

እግዚአብሔር ሦስት የተለያዩ አካላት ከሆነ ታዲያ የእግዚአብሔር ስም ማን ነው?

በሌላ አነጋገር የአብ፣ የወልድ፣ እና የመንፈስ ቅዱስ አንድ ስም ማን ነው?

አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ሦስት የተለያዩ አካላት ናቸው ብለህ ካመንክ ለሦስታቸውም የሚሆን አንድ ስም ማግኘት አትችልም። በዚህም ምክንያት ለክርስቲያኖች አምላክ መጠሪያ የሚሆን ስም የለህም።

መሃመድ ክርስትናን ያልተቀበለበት ምክንያት ይህ ነው፤ እርሱም የሙስሊሞች አምላክ ስሙ አላህ ነው ብሎ አጥብቆ አስተማረ።

የመሃመድ አስተሳሰቡ ግልጽ ነው፤ ማለት የፈለገው አምላክ ስም አለው ነው።

እስካሁን 1700 ዓመታት አልፈዋል ግን ቤተክርስቲያን እስከ ዛሬ ለእግዚአብሔር ስም አላገኘችለትም።

“የመለኮት ሁለተኛው አካል” የሚለው አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የለውም።

“የሥላሴ ሦስተኛው አካል” የሚለውም አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም። ይህ ሦስተኛ አካል መንፈስ ቅዱስ ነው፤ እርሱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስም የለውም። ሦስት አካላት ሆነው ሳለ ሁለት ስም ብቻ ካላቸው ማለትም ያህዌህ እና ኢየሱስ ይህ ትክክል አይመጣም።

ነገር ግን ለሦስታቸውም የሚሆን አንድ ስም ደግሞ የለም። እድሜ ለትምሕርተ ሥላሴ የክርስቲያኖች አምላክ ስም የለውም።
የባቢሎን ምስጢራት ወደ ቤተክርስቲያን ሲገቡ ከገቡት መካከል ታላቁ ምስጢር ይህ ነው። ከ1700 ዓመታት በኋላ እንኳ ታላቅ ምስጢር ሆኖ ቀረቷል።

ፈረንሳይ ውስጥ ያለ የሥላሴ ምስል። ለዚህ ሦስት አካላት ላሉት የክርስቲያኖች አምላክ አንድ ስም የለውም። በስዕሉ ውስጥ እግዚአብሔር አብ ያደረገውን ባለ ሦስት ተደራራቢውን የፓፑ ቆብ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ።

ሩበንስ (1577 - 1640) የተባለ ታላቅ ሰዓሊ የሥላሴ ስዕል ስሏል። በስዕሉም ውስጥ እግዚአብሔር አብ ሽማግሌ ይመስላል። የእርጅና ምልክቶች የሚታዩበት ከሆነ ምን ያህል ዘመን ሊኖር ነው?

ይህ ስዕል ካሉበት ችግሮች አንዱ ሁለት ሰዎችን ብቻ ማሳየቱ ነው ምክንያቱም እርግብ ሰውን ወይም ስብዕናን አይወክልም። መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሚመስል መጽሐፍ ቅዱስ አንዳችም አይነግረንም። ስሙ ማን እንደሆነም አይነግረንም። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን ለማሳየት ተብሎ የሚሳል ስዕል ሁሉ ጭፍን የሆነ ግምት ነው። እርሱን እርግብ አድርጎ መሳል ደግሞ ራሱን የቻለ ስብዕናውን ማሳጣት ነው። ስለዚህ የሥላሴ ምስጢር ሰውን ሁሉ ግራ እንዳጋባ ይኖራል። ግሪኮች መከራከር ይወዳሉ ግን ክርክራቸው እውነትን ለመደገፍ ይሁን ወይ ስሕተትን ለመደገፍ እንደሆን ግድ የላቸውም። ብቻ የሚከራከሩበት ርዕስ ካገኙ ደስ ይላቸዋል። ስለዚህ የሥላሴ ክርክር ለአሥራ ሰባት መቶ ዓመታት ቀጥሏል፤ ምስጢር መሆኑንም ይቀጥላል፤ እነርሱ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለተጻፉ ሐሳቦችን እንዲያምኑ በማድረግ ተሳክቶላቸዋል። ከእነዚህ ሃሳቦች መካከል ብቸኛውና ሰይጣንም የብዙ ሰዎችን አእምሮ ለመማረክ ስኬት ያገኘበት ትምሕርት ሥላሴ ነው። መሰረቱም የግሪክ ፍልስፍና ሲሆን የግሪክ ፍልስፍና የባቢሎናውያንና የግብጻውያንን አማልክት ወደ ክርስትና አስተሳሰብ ውስጥ በቀላሉ ሰተት ብለው መግባት እንዲችሉ ወልውሎ አሰማምሮ አቀረባቸው።

በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ከተሰሩ ስሕተቶች ሁሉ ትልቁ ስሕተት የኒቂያ ጉባኤ ነው።

በአረማውያን የጣኦት አምልኮ እምነቶች ላይ የተመሰረተውን ሥላሴ እውነተኛ አምላክ አድርገው አጸደቁ (ለምሳሌ አይሲስ፣ ኦረስ፣ እና ሴብ የግብጻውያን ሥላሴ ነበሩ)።

ፖለቲከኛው ኮንስታንቲን ጉባኤ በመሰብሰብና በጉባኤውም ላይ አለቃ እንዲሆን በመፍቀድ የቤተክርስቲያንን መሪነት ለእርሱ አሳልፈው ሰጡ።

ይህ ፖለቶከኛ የእግዚአብሔርን መለኮትነት ለመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌሉ ቃላትን ለምሳሌ ከግሪክ ፍልስፍና የተገኘውን “ኤሰንስ” እንዲጠቀም ፈቀዱ።

የግሪክ ፍልስፍና የቤተክርስቲያን እውነት መሰረት ሆነ።

ይህም ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ቃላት ከግሪክ ፍልስፍና ወደ ቤተክርስቲያን እንዲገቡ በር ከፈተ፤ ለምሳሌ የፕሌቶ ትራያድ፣ ሦስት በአንድ፣ አንድ አምላክ በሦስት አካላት፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ የመለኮት ሁለተኛው አካል፣ ወዘተ። ኮንስታንቲን የላቲን ቋንቋ ይችል ነበር፤ ስለዚህ ትራያድ የሚለውን የግሪክ ቃል ትሪኒታስ በማለት ወደ ላቲን ተረጎመው፤ ይህም ቃል ዛሬ በእንግሊዝኛ ትሪኒቲ በአማርኛ ደግሞ ሥላሴ ይባላል። ምዕራባዊው የሮማ ግዛት ቋንቋው ላቲን ስለነበረ ትሪኒቲ የሚለው ቃል በስፋት ተሰራጨ።

እግዚአብሔር ሦስት አካላት ነው ብለው ከወሰኑ በኋላ ለሦስቱም የእግዚአብሔር አካላት የሚሆን አንድ ስም ማግኘት አልተቻለም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ስም በሦስት የማዕረግ መጠሪያዎች ተተካና በቀስታ እንዲረሳ ተደረገ፤ እነዚህም የማዕረግ መጠሪያዎች አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ። ነገር ግን የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ አንድ ስም ማን እንደሆና የትኛውም የሥላሴ አማኝ ሊነግረን አይችልም።

በዚህም መንገድ ሥላሴ የሆነው አምላክ ስሙን አጣ።

ብዙ ቤተክርስቲያኖችም ጴጥሮስ እንደነገረን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የማያጠምቁት በዚህ ምክንያት ነው። የመንግስተ ሰማያት ቁልፍ የነበረው ጴጥሮስ እንጂ እኛ አይደለንም።

የእግዚአብሔርን ስም መሳደብ ማለት ስሙን በከንቱ መጥራት እና ስሙን በመሃላ እንዲሁም በቀልድና በስድብ ውስጥ መጠቀምነ ነው። አንድም ሐጥያተኛ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አይሳደብም አይምልም። በየዕለቱ በከንቱ ሲጠራ የምንሰማው ስም የኢየሱስ ስም ነው። ሙስሊም እንኳ በኢየሱስ ስም ሲምል ሰምቻለው። ስለዚህ ሐጥያተኞች ኢየሱስ እግዚአብሔር ሰው በሆነ ጊዜ የተሰጠው ስሙ እንደሆነ ያውቃሉ። ክርስቲያኖች ግን ይህንን እውነት አያውቁም።

የኒቂያ ጉባኤ ላይ የተፈጸመው ሌላ ትልቅ ስሕተት መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብቸኛው የእውነት ምንጭ ሆኖ አለመቀጠሉ ነው። ቤተክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ተጨማሪ ሃሳቦችን ለመጠቀም ነጻነት አገኘች። ዛሬም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌሉ ትምሕርቶችን ያስተምራሉ። ለምን ተብለው ቢጠየቁ የሥላሴ ትምሕርት እውነት መሆኑን ይጠይቃሉ። የዛሬ ክርስቲያኖች 99 በመቶ “አዎ እውነት ነው” ብለው ይመልሳሉ። ከዚያም አስተማሪው ሥላሴ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም ግን እውነት መሆኑን ታምናላችሁ፤ ስለዚህ ሌሎችም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፉ ትምሕርቶችን መቀበል አለባችሁ ይላል። አንድ ስሕተት ለብዙ ሌሎች ስሕተቶች በር ከፈተ።

ጳውሎስ ከቃሉ ውጭ የሚያስተምር የተረገመ ይሁን ብሏል።

ገላቲያ 1፡8 ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።

መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወሙ የባቢሎን ምስጢራት ወደ ቤተክርስቲያን መግባት ጀመሩ። ሰዎች ስለ ሥላሴ ለብዙ መቶ ዓመታት ተከራክረው ሲያበቁ በመረዳት አንዳችም አላደጉም። ትልቁ ኪሳራ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ አስተምሕሮ ለመቀበል መጋለጣቸው ነው። ይህም ብዙ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፉ አስተምሕሮዎች ተቀባይነት እንዲያገኙ በር ከፍቷል።

ብዙ የአረማውያን ትምሕርት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲገባ በር ተከፍቷል። አረማውያንን ለመሳብ ተብሎ ቤተክርስቲያን የአሕዛብ ልማዶችን ክርስቲያናዊ ቀለም ቀብታ ተቀበለች። ከለዳውያን በ40 ቀን ጾም ያምኑ ነበር፤ ይህም ጾም ከፀደይ ወቅት በፊት ኢሽታር የምትባለዋን አምላክ ለማክበር ለ40 ቀን ከሚወዷቸው ምግቦች የሚታቀቡበት ጊዜ ነበር። ቤተክርስቲያንም ይህንን ኮርጃ ወደ ኢስተር (በእንግሊዝኛEaster) ወይም ፋሲካ ለወጠችው። የአሕዛብን ልማድ በክርስቲያናዊ ስም ብትለማመዱ ችግር የለውም ተባለ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እስከ ዛሬ እንደዚሁ ብለው ያምናሉ።

አሕዛብ በቤተ መቅደሳቸው ውስጥ እጣንና አበቦች ያስቀምጣሉ። ቤተክርስቲያን ይህንንም ልማድ ኮረጀች። በጣም ስለሚያምር እግዚአብሔርም ደስ ሳይለው አይቀርም። ነገር ግን በቤተክርስቲያን ውስጥ አበባ ይደረግ እንደነበረ ከአዲስ ኪዳን አንድ ጥቅስ እንኳ ለማስረጃነት ማቅረብ አልቻሉም። እንደውም እስቲ አዲስ ኪዳን ውስጥ ክርስቲያኖች የሰሩትን አንድ የቤተክርስቲያን ሕንጻ እንኳን አሳዩን ካገኛችሁ። በየሰው ቤት ነበር የሚሰበሰቡት። ቤተ መቅደስ ከአዲስ ኪዳን ዘመን በፊት ጥንት ነበር የተሰራው።

ኮንስታንቲን በክርስቲያኖች ላይ የሚደረገውን ስደት ባስቆመ ጊዜ ብዙ ሕንጻዎችን እና የአሕዛብ ቤተመቅደሶችን ለክርስቲያኖች ሰጠ። አሕዛብ ስለ ቤተመቅደስ አሰራር ምሳሌ አድርገው የሚከተሉት ናምሩድንና እርሱ የሰራውን የባቢሎን ግምብ ስለሆነ ቤተመቅደስ ሲሰሩ ጫፉ ሰማይ ጠቀስ የሆነ ጉልላት ያኖሩበታል፤ ይህም አምላካቸው በሰማይ ውስጥ እንዳለ በማመናቸው ነው።

ከአሕዛብ የወረሱዋቸው ቤተመቅደሶች ረጅም ጉልላት ስለነበራቸው ክርስቲያኖች የራሳቸውን ቤተክርስቲያነ ሲሰሩ ጉልላቶችን ከአሕዛብ ቤተመቅደስ ኮርጀው ወሰዱ።

ክርስቲያኖች ለአሕዛብ በዓላት ክርስቲያናዊ ስሞችን በመስጠት ከአሕዛብ ጋር ድርድር ለማድረግ ወሰኑ።

ከላይ ያለው ስዕል የሚያሳየው በፀደይ ወቅት የሚከበረውን የኢሽታር በዓል ነው፤ እርሷም በትልቅ እንቁላል ውስጥ ሆና የኤፍራጥስ ወንዝ ላይ እንደወረደችና ከእንቁላሉ ውስጥ እንደወጣች ይታመናል። አሕዛብ እንቁላል ይቀቅሉና ቅርፊቱ ላይ ስዕል ይስሉበታል።

የግልሙትና ድግሳቸውን ለመግለጽ የጥንቸል ስዕል ይጠቀማሉ፤ ምክንያቱም ጥንቸሎች ከእንስሳት ሁሉ በላይ በፍጥነት በመራባት ይታወቃሉ። ይህ ልማድ በቀላሉ የኢስተር ወይም ፋሲካ እንቁላልና ጥንቸል ሆኖ ወደ ክርስትና ውስጥ ገባ።

እነዚህ የአሕዛብ ምልክቶች ማለትም ጥንቸል እና እንቁላል በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከዛሬ ድረስ የፋሲካ በዓል ምልክቶች ሆነው ያገለግላሉ።

እናትና ልጅን ማምለክ ከባቢሎናዊቷ እናት የናምሩድ ሚስት ከሰሚራሚስ እና ከልጇ ከታሙዝ ነው የተኮረጀው።

ይህም ግብጽ ወደ ግብጽ ሲመጣ አይሲስ እና ኦሲሪስ ወይም አይሲስ እና ኦረስ ሆነ። ሕንድ ውስጥ አይሲ እና ኢስዋራ። ሮም ውስጥ ደግሞ ቪነስ እና ጁፒተር ሆነ።

እናትና ልጅ የሚያሳዩ የማርያምና የኢየሱስ ሐውልቶች በዓለም ዙሪያ በብዛት ይገኛሉ።

ይህ ሐውልት ማርያም በራሷ ላይ ዘውድ ጭና የጠፈሯ ንግሥት እንደሆነች ያሳያል፤ ይህም ለአረማውያን አምላክ የሚሆን አረማዊዊ ስም ነው።

የመጀመሪያዋ የጠፈሯ ንግሥት ሰሚራሚስ ናት። ቤተክርስቲያን ያለማቋረጥ አሕዛብን ትኮርጃለች።

ሰሚራሚስ የጠፈሯ ንግሥት የጨረቃ አምላክ እንደሆነች ስለሚታመን የምትመለከው ሙልሙል ዳቦ በመጋገር ነበር።
በሙልሙሉ መሃል በክሬም ተ ፊደልን ወይም “+” የሚመስል ቅርጽ ይሰራል፤ ይህም የልጇን የታሙዝን ስም የመጀመሪያ ፊደል ይወክላል። የሮም ቤተክርስቲያን የ“መስቀልን” ምልክት መረጠች ይህም የክርስቲያን ባለ መስቀል ሙልሙል ዳቦ ሆነ።

በዲሴምበር 25 የሚከበረው የፀሃይ አምላክ ልደት (በ274 ዓ.ም. በሮማዊው ገዥ በኦሬሊያን የተጀመረው) የእግዚአብሔር ልጅ ልደት ሆኖ ወደ ክርስትና ተቀላቀለ። በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ በዓላት ሲከበሩ ማስ ተብለው ነበር የሚጠሩት፤ ስለዚህ ይህ ቀን ሲከበር ክራይስትስ-ማስ ተባለ። አጠር ሲደረግ ደግሞ ክሪስማስ ሆነ። ከጊዜ በኋላ ሰዎች ይህ በዓል ከክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ሲረዱ ስሙን በትልቅ “X” ሰርዘር ዛሬ እንደምናውቀም Xmas ኤክስ-ማስ አሉት።

ቀጥሎ ደግሞ በጌጣጌጥ ያሸበረቀውን የክሪስማስ ዛፍ እዩ።

ኤርምያስ 10፡2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሕዛብን መንገድ አትማሩ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፤ አሕዛብ ይፈሩታልና።

3 የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል።

4 በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል።

5 እንደ ተቀረጸ ዓምድ ናቸው እነርሱም አይናገሩም፤ መራመድም አይቻላቸውማን ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፥ ደግምም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው።

የአሕዛብን ልማድ አትማሩ ተብለናል። ክሪስማስ የሚከበርበት ቀን እና ያጌጠው ዛፍ ግን የመጡት ከአሕዛብ ልማድ ነው።

ገላቲያ 4፡10 ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ።

11 ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ።

በየዓመቱ የክሪስማስ ወቅት በ12ኛው ወር በ25ኛው ቀን ይከበራል። ይህን ከ350 ዓ.ም. በኋላ ወደ ሮም ቤተክርስቲያን የገባውን በዓል ጳውሎስ ቢያየው ምንም አይደንቀውም ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ የልደት ቀኖችን እንድናከብር አላዘዘንም። ሁለት ልደቶች ብቻ ናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት እነርሱም የፈርኦንና የሔሮድስ ናቸው። ሁለቱም በልደት ቀናቸው የነፍስ ግድያ ፈጽመዋል። እኛ ደግሞ የክርስቶስ ልደት ቀን ያልሆነውን ቀን በግምት ነው ብለን እናከብራለን፤ በክረምት አጋማሽ በረዶ በሚዘንብበት ጊዜ እሥራኤል ውስጥ ካለው ከባድ ብርድ የተነሳ እረኞች በምሽት በጎቻቸውን ይዘው ከቤት አይወጡም። የእውነት እግዚአብሔር የሚደሰት ይመስላችኋል?

ነገር ግን ይህ የአሕዛብ የልደት ቀን በቤተክርስቲያን ውስጥ ከሚከበሩ በዓላት ሁሉ ታላቁና ዋነኛው በዓል ነው። ክርስቲያኖችም ከዚህ በዓል ጋር ከያዛቸው ከባድ ፍቅር የተነሳ ሊተዉት አይፈልጉም። እንደውም መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ለውጠው ሰብዓ ሰገል ለኢየሱስ ስጦታ ለመስጠት ወደ በረት መጡ ይላሉ። ብዙ ስጦታ ለመግዛትም ማመካኛው ይህ ነው።

ሰብዓ ሰገል ኢየሱስ ተወልዶ ሁለት ዓመት ከሆነው በኋላ መጥተው እቤት ውስጥ ነው የገቡት እንጂ አራስ እያለ አልደረሱም። ነገር ግን ብዙ ክርስቲያኖች ይህንን እውነት ይቃወማሉ ምክንያቱም በኢየሱስ ልደት በማሳበብ ብዙ ስጦታ የመግዛት ልማዳቸውን ያስቀርባቸውል።

ማቴዎስ 2፡11 ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።

በኒቂያ ጉባኤ በ325 ዓ.ም. ወደ ቤተክርስቲያን የገቡት የባቢሎናውያን ምስጢራት ወደ ክርስትና ውስጥ ሰርገው በመግባት እስከዛሬ ደረስ አብረውን አሉ።
መቅረዙ ቤተክርስቲያን በሦስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ የነበረችበትን ሁኔታ ይገልጻል። እውነተኛው ብርሃን እየደበዘዘ ነው። ሃሰተኛው ቤተክርስቲያን ከፖለቲካ እና ከአረማዊነት ጋር በፈጸመችው ጋብቻ አማካኝነት ሐዋርያት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከመሰረቷት ቤተክርስቲያን ፍጹም ርቃ ሄዳለች። ሰዎች የቤተክርስቲያን መሪ ወይም ራስ ሆኑ።

ራዕይ 2፡12 በጴርጋሞንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል፦

አንድ ሰይፍ በሁለት ወገን ስለት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ኪዳንና ብሉይ ኪዳንን በአንድ ላይ ይዟል። ፍጥረታዊ ብርሃን የሞገድና የቅንጣትን ተቃራኒ ባሕርያት በውስጡ ይይዛል። ኢየሱስ በሥጋ ሰው ነው፤ ነገር ግን በውስጡ የሚኖረው ልዕለ ተፈጥሮዋዊው መንፈስ እግዚአብሔር ነው።

በእስያ ያሉት ሰባት ቤተክርስቲያናት ኤፌሶን፣ ሰምርኔስ፣ ፔርጋሞን፣ ትያጥሮን፣ ሰርዴስ፣ ፊልድልፊያ፣ እና ሎዶቅያ ናቸው።

ስድስት ከተሞች በተለመደው ስማቸው ተጠቅሰዋል። ጴርጋሞን ግን በግሪክኛ ነው ስሟ የተጠቀሰው። የመጀመሪያ ስሟ ጴርጋመም ነው። በ1850 አካባቢ የአየርላንድ ጳጳስ ለምን ጴርጋሞን ብቻ ብቻ ተለይታ ግሪክኛ ስም እንደተጠቀሰች ጠየቆ ነበር። መልሱም ይህ ነው፡- በሦስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን (312-606 ዓ.ም.) የግሪክ ፍልስፍና በ325 ዓ.ም. በኒቂያ በተደረገው ጉባኤ አማካኝነት የቤተክርስቲያን አስተሳሰብ ውስጥ ሰተት ብሎ ገብቶ ለ200 ዓመታት ያህል ያልተቋረጠ ክርክር እና ማስተካከያ ማሻሻያ ከተደረገበት በኋላ አንድ ታላቅ ባቢሎናዊ ምስጢር እርሱም የሥላሴ አስተምሕሮ ቤተክርስቲያንን ከመጽሐፍ ቅዱስ አስወጥቶ ስላስቀራት ነው።

ቆላስይስ 2፡8 እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።

9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤

ከንቱ መታለል። የግሪክ ፍልስፍናን በመጠቀም የማይታየውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ልንፈታ እንችላለን በሚለው በከንቱ አስተሳሰባችን እንታለላለን። “ከንቱ” ማለት አእምሮዋችን ማስተዋል ከሚችለው በላይ እናውቃለን ብለን በግብዝነት መመካታችን ነው።

1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥

እግዚአብሔር ራሱን በሰው መልክ አበጀ እና እግዚአብሔር የማይታይ መለኮታዊ መንፈስ እንደመሆኑ በዚያ ፍጹም ሰው ውስጥ አደረ።

ዮሐንስ 14፡10 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።

ሰው ውሃ ላይ መራመድ አይችልም። ኢየሱስ ግን ውሃ ላይ ተራመደ፤ ይህም ከሰው በላይ መሆኑን ያረጋግጣል። በእርሱ ውስጥ የሚኖረው የእግዚአብሔር ሙላት እርሱን የእግዚአብሔር ልጅ አደረገው።

የእግዚአብሔር ልጅ - ሰው                   እግዚአብሔር አብ - በውስጥ የሚኖረው መለኮታዊ መንፈስ

የእግዚአብሔር ሕይወት በተወሰነ መጠን በውስጥህ መኖሩ ነው የእግዚአብሔር ልጅ የምትሆንበት ብቸኛው መንገድ።

በዓይን የሚታየው አካላዊው ኢየሱስ በውስጡ ካለው የሰው መንፈስ ጋር (ሁለቱ በአንድነት ሆነው ነው ሥጋው የተዘጋጀው) ሙሉ በሙሉ አምላክ አይደለም፤ ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ልጅ የተባለውና እግዚአብሔር ወልድ ያልተባለው።

ራዕይ 2፡13 የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም።

ቂሮስ ባቢሎንን በገዛ ጊዜ የባቢሎናውያን ምስጢራት ሊቀካሕን ወይም ፖንቲፍ ሥርዓተ ክሕነቱንና መዝገቡን ሁሉ ይዞ ወደ ጴርጋሞን ሸሸ። በምሥራቁ ዓለም ንጉስ እንደ አምላክ ይመለክ ነበር፤ በምዕራቡ ዓለም ግን እንዲህ አይነት ልማድ አይታወቅም። ታላቁ እስክንድር ፋርስን አሸንፎ ሲገዛ በግሪኮች ዘንድ ወዲያው ባይዋጥላቸውም እንደ አምላክ መታየት ጀመረ። እርሱም በጦር ሜዳ የውጊያ ስልቶቹ እና ድሎቹ የተነሳ እንደ ንጉስና አምላክ ተደርጎ ይመለክ ነበር። እርሱም ሲሞት ጀነራሉ ላይሲማከስ የጴርጋሞንን መንግሥት ተረከበና ላይሲማከስም ንጉሥና አምላክ ነኝ አለ። ላይሲማከስ ሲሞት ባቢሎናዊው ፖንቲፍ በቦታው ተተክቶ ንጉሥና አምላክ ሆነ።

ወደ ጴርጋሞን የመጣው የመጀመሪያው ፖንቲፍ ባቢሎን ውስጥ ብልጣሶር ከአይሁድ ቤተመቅደስ የመጡትን እቃዎች አቅርቦ ባረከሰበት ድግስ ላይ ተገኝቶ ስለነበረ ይህ ባቢሎናዊ ሊቀካሕን በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ ከአረማውያን ሊቀካሕናት ሁሉ ታለቅ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። የጴርጋሞን አማልክት-ነገሥታት ወይም ፖንቲፎች ብቻ ነበሩ ትክክለኛ ፖንቲፍ ተደርገው የሚቆጠሩት ምክንያቱም እነርሱ ብቻ ናቸው በዘር ከመጨረሻው የባቢሎን ሊቀካሕን የተወለዱት። የመጨረሻው የጴርጋሞን ንጉሥ-አምላክ አታለሥ ሳልሳዊ በ133 ዓመተ ዓለም መንግሥቱን ለሮም አስረከቦ ሞተ። በዚህ መንገድ ጴርጋሞን ለ400 ዓመታት የሰይጣን ባቢሎናዊ ምስጢራትና የስልጣኑ ዙፋን ሆና ቆይታለች። የባቢሎናውያን ምስጢራት ወደ ጴርጋሞን የመጡት ከፋርሶች ለማምለጥ ነበር፤ ነገር ግን ግሪኮች ፋርሶችን አሸንፈው እስከሚገዙ ባለው ጊዜ ውስጥ የባቢሎናውያን ምሥጢራት በግሪኮች ጥበብና ፍልስፍና አማካኝነት ረቀቅ ብሎ ተሻሻሎ ቆየ። ከዚያም እነዚህ ተሻሽለው የቀረቡ የባቢሎን ምስጢራት ወደ ሮማውያን እጅ ተላለፉ። ነገር ግን የፖንቲፍነትን ሥልጣን የያዘ ማንኛውም ሮማዊ ዩልየስ ቄሳር በ63 ዓመተ ዓለም ጉቦ ከፍሎ እንደ አዲስ ፖንቲፍ እስኪሰየም ድረስ ትልቅ ስልጣን እንዳለው አይቆጠርም ነበር። ጌጣ ጌጥ የበዛባቸው የባቢሎን ልብሰ ተክሕኖዎች እና የባቢሎናውያን ውስብስብ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች ለቄሳር ከበሬታን ጨመሩለት። የቄሳርም ወታደራዊ ዝና እርሱ ደርቦ የያዘው ባቢሎናዊ ክሕነት ክብር እንዲኖረው አደረገ።

ነገር ግን በጴርጋሞን ከዚያ ወዲያ ሥር ሰዶ የቀረው ልማድ ሰውን እንደ አምላክ የማምለክ ዝንባሌ ነው።

በሰዎች ውስጥ አንድ ዝነኛ ሰውን ወይም ጀግናን የማምለክ ፍላጎትና ይህንንም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነው ብሎ ከፍ ከፍ ማድረግ እንዲሁም እርሱ “የእግዚአብሔር ድምጽ” ነው ወይም “የእግዚአብሔር አፍ” ነው ማለት ሰይጣን በሰዎች ላይ የተቀመጠበት ዋነኛ የስልጣኑ ዚፋን ነበር። ከሰው ንግግር የተወሰደ ጥቅስ የእግዚአብሔርን ቃል ተክቶ ይቀርባል። ይህ ሰውን የማምለክ ዝንባሌ በምሥራቅ የተለመደ ሲሆን በምዕራብ አይታወቅም ነበር።

የሐዋርያት ሥራ 12፡21 በተቀጠረ ቀንም ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋን ተቀመጠ እነርሱንም ተናገራቸው፤
22 ሕዝቡም፦ የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም ብለው ጮኹ።
23 ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ።

1ኛ ተሰሎንቄ 4፡16 ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤

በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን የዊልያም ብራንሃም መልዕክት የተኙትን ቆነጃጅት የሚያነቃ ድምጽ ነው። ተከታዮቹም ይህንን ድምጽ የሰባተኛው መልአክ ወይም መልእክተኛ ድምጽ መሆኑን በማስተዋል ፈንታ “የእግዚአብሔር ድምጽ” ነው ብለው ይተረጉማሉ (ልክ የሔሮድስ ቃል “የእግዚአብሔር ድምጽ” ነው እንደተባለው)። የዊልያም ብራንሃም ተከታዮች ዊልያም ብራንሃም አይሳሳትም ብለው ያምናሉ።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ደግሞ ፖፑ ወይም ጳጳሱ ፍጹም የማይሳሳት የእግዚአብሔር ድምጽ ነው ይላሉ።

እውነተኛዋ ሙሽራ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብላ ታምናለች።

ቄሳር በ44 ዓመተ ዓለም ሲሞት ጴርጋሞን በ29 ዓመተ ዓለም ቄሳርን እንደ አምላክ እንድታመልክ ፈቃድ አገኘች። ስለዚህ ሮም ውስጥ የመጀመሪያው እንደ አምላክ የተመለከ ሰው ቄሳር ነበር። ቀጣዩ ፖንቲፍ የነበረው ሮማዊው ንጉስ አውግስጦስ በሕይወት ሳለ እንደ አምላክ እንድታመልከው ለጴርጋሞን ከተማ ፈቃድ ሰጠ።

ፖንቲፍ የሚለውን ማዕረግ መጠቀም ያቆመው የሮም ገዥ ግራቲያን ነው (እርሱም ከ375 እስከ 383 ዓ.ም. በሮም ላይ ነገሰ)።
ከሮማ ጳጳስ ከሊዮ ቀዳማዊ ጊዜ ጀምሮ (440-461 ዓ.ም.) ፖንቲፍ ወይም የባቢሎናውያን ምሥጢር ሊቀካሕን የሚለው ማዕረግ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ንብረት ሆኖ ቀረ።

“ስሜን ትጠብቃለህ”። እውነተኛዎቹ አማኞች በኒቂያ ጉባኤ አንሳተፍም አሉ ከመካከላቸው ተሳትፈው የነበሩትም ኋላ ራሳቸውን አገለሉ። በጉባኤው ላይ ይነገሩ የነበሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ቃላት በሙሉ እውነትን የማግኛ መንገዶች እንዳልሆኑ ተገንዝበዋል። የሐዋርያትን ምሳሌ በመከተል በጌታ በኢየሱስ ስም አጠመቁ እንጂ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በሚባሉ ሦስት ማዕረጎች አይደለም ያጠመቁት።

“የታመነው ምሥክሬ”። ሐሰተኛው የወይን ሐረግ ማለትም የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከእርሷ ጋር ያልተስማሙትን እውነተኛ አማኞች ሁሉ ማሳደድ ጀመረች። ፖፕ ሊዮ ቀዳማዊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የተቃወሙ ሰዎችን ንጉሡ ስለገደላቸው አመስግኖታል። ሥላሴን የካዱ ሰዎችም አንድ በአንድ እየተገደሉ ነበር።

“አንቲጳስ” የሚለው ስም አንቲ ጳጳስ ከሚሉ ቃላት የመጣ ይመስላል። ይህም ጸረ ጳጳስ ማለት ነው፤ ምክንያቱም ፖፑ ቅዱስ አባት ተብሎ ይጠራል። ጳጳስ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ አባት ማለት ነው።

ማቴዎስ 23፡9 አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ አባት ብላችሁ አትጥሩ።

ፖፑን መቃወም በጣም አደገኛ ነው። አባት የቤቱ ራስ ነው። ስለዚህ ፖፑ አባት ተብሎ እንደመጠራቱ የቤተክርስቲያን ራስ ነኝ ማለቱ ነው። የቤተክርስቲያን ራስ ግን ክርስቶስ ነው።

ኤፌሶን 5፡23 ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና።

ራዕይ 2፡14 ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ።

ጣኦታት ወይም የተቀረጹ ምስሎችና ሐውልቶች ወደ ቤተክርስቲያን መግባት ጀመሩ። ጣኦት ይመለክባቸው የነበሩ ቤተመቅደሶች ቤተክርስቲያን ተደረጉ፤ ነገር ግን ከጣኦት አምልኮ መንፈስ ስላልተላቀቁ ክርስትናን በጣኦት አምልኮ በረዙት። የሐሰተኛ አማልክት ሐውልቶች በክርስቲያን ቅዱሳን ስም ተሰየሙ። በጥቁር እምነ በረድ የተሰራ የጁፒተር ሐውልጥ የጴጥሮስ ሐውልት ሆነ።

ቤተክርስቲያን በሴት ትመሰላለች። መሴሰን ያላገባች ሴት የምትፈጽመው ሐጢያት ነው። ዝሙት የሚባለው ደግሞ ካገባች በኋላ ሐጥያት ስትሰራ ነው። ስለዚህ መሴሰን ማለት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር አልተጋባችም ማለት ነው። ባል የላትም።

መንፈሳዊ ሴሰኝነት ማለት በአእምሮዋ (በመንፈሳዊ ማሕጸን) ውስጥ የሃሳብን ዘር በሚተክሉ የሰው ሃሳቦች ተጠምዳለች ማለት ነው።

ይህም ዘር በጨለማው ዘመን ግዙፍና አስፈሪ የሆነ የቤተክርስቲያን ድርጅት እስከሚሆን ድረስ ያድግ ነበር። የባቢሎናውያን አረማዊ ምስጢሮች በግሪኮች ጥበብ ወይም ፍልስፍና ተወልውለው ተቀባብተው መጡ። ታላቁ የአረማውያንና የክርስቲያኖች የጋራ ድግስ በ325 ዓ.ም. የተደረገው የኒቂያ ጉባኤ ሲሆን በዚህም ድግስ ላይ ቤተክርስቲያን የጣኦት አምላኪዎችን ሃሳብ ክርስቲያናዊ ቅርጽና ክርስቲያናዊ ስም በመስጠት ተቀበለቻቸው። ይህም ሂደት በዘመናት ውስጥ በመዝለቁ ተንኮለኛ ሰዎች ክርስትናን አረማዊ ማድረጋቸውን ቀጠሉ፤ ስለዚህም ሥላሴ፣ ክሪስማስ፣ የክሪስማስ ዛፍ፣ የዲሴምበር 25 የኢየሱስ ልደት፣ የፋሲካ እንቁላሎች፣ የፋሲካ ጥንቸሎች፣ የባቢሎን ካሕናት ያጌጡ ልብሰ ተክሕኖዎች፣ ራሳቸው ላይ የዳጎን ምልክት የሆነውን የዓሣ ቅርጽ ያለውን ቆብ ራሳቸው ላይ የሚደፉ ጳጳሳት እና የመሳሰሉ የጣኦት አምላኪዎች ልማዶች ወደ ቤተክስቲያን ገቡ።

ፖፕ፣ ፖንቲፍ፣ ባለ ሦስት ድርብ ዘውድ፣ የቤተክርስቲያን ረጅም ጉልላቶች፣ ካርዲናሎች፣ ሊቀ ጳጳሳት፣ የከተማ ገዢዎች፣ ሰዎች የሐጥያት ሥርየትን በገንዘብ የሚገዙበት ሥርዓት፣ ለሙታን መጸለይ፣ ሕጻናትን ማጥመቅ፣ የእግዚአብሔር ስም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ መለወጡ እና ሌሎችም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሃሳቦችና ልማዶች ተዘርዝረው አያልቁም።

ባላቅ ንጉሥና ፖለቲከኛ ነው። እርሱም በለዓም የእሥራኤል ወንዶች ከሞዓባውያን ሴቶች ጋር በመተባበር ለብኤልፌጎር ይሰግዱ ዘንድ እንዲያስታቸው ጠየቀ። ሞዓባውያን እሥራኤላውያን አይደሉም ስለዚህ የእሥራኤል ወንዶች ከሞዓባውያን ሴቶች ጋር በማይመች አካሄድ መጠመድ አልነበረባቸውም። ነውር ነው። በዚህም ሐጥያት የተነሳ እግዚአብሔር ሃያ አራት ሺ ሰዎችን ገደለ።

በለዓም ትንቢት የመናገር ስጦታውን ለገንዘብ ሽጦ ብዙ ሺዎችን አስገደለ። ፖለቲካዊ መሪ የሆነው ኮንስታንቲን ባፈሰሰው የገንዘብ ስጦታ ብዛት የሮም ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመሆን እድል ፈንታዋን ለገንዘብ ሽጣ ሰው ሰራሽ በሆኑ ሃሳቦች ውስጥ ስትንከባለል ቆየች። በነዚህም የተሳሳቱ እምነቶች ምክንያት የብዙ ሚሊዮኖችን ነፍስ ጠፍቷል።

በኒቂያ ጉባኤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ሥላሴ የሚባል አስተምሕሮ ተፈጠረ። የሥላሴ ትምሕርት ትክክለኛ እንደሆነ ለማስረዳት ብዙ ሰው ሰራሽ አገላለጾችን ይጠቀማል። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያምኑ ክርስቲያኖች ከዚህ አስተምሕሮ መራቅ አለባቸው።

ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈ አስተምሕሮ ሲማሩና ሲያምኑ ቤተክርስቲያን ላይ መንፈሳዊ ሞት ይመጣል። ጳውሎስ ሥላሴ የሚለውን ቃል ተጠቅሞ አያውቅም። እርሱ ካስተማረው ትምሕርት የተለየ አንዳች ብናስተምር እንደምንረገም ተናግሯል።

በኒቂያ ጉባኤ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወደ ጨለማው ዘመን የመጀመሪያ እርምጃዋን ጀመረች። ብርሃንን በአግባቡ በጥንቃቄ ካልያዝከው ብርሃኑ ይጠፋል። በኒቂያ ጉባኤ የተሰበሰቡ ሁሉ በገሃድ መጽሐፍ ቅዱስን ማራከስ ጀመሩ።

ራዕይ 2፡15 እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ።

ኒቆላዊነት አንድ ቅዱስ ሰውን ከፍ የማድረግ ልማድ ነው። አንድ ካሕን፣ ቄስ ወይም ፓስተር ከፍ ይደረግና የቤተክርስቲያን ሃላፊ ይሆናል። ከዚያም ጳጳስ ደግሞ ከፓስተሮችና ከካሕናት በላይ ከፍ ይደረጋል። የሮማው ሊቀጳጳስ ደግሞ ከሌሎች ጳጳሳት ሁሉ በላይ ከፍ ያለ ሹመት ይሰጠዋል። በዚህም መንገድ ድርጅት ተፈጠረና እያደገ መጣ።

አዲስ ኪዳናዊ የአሮን ክሕነትን ለመመስረት ተብሎ አምስቱ የአገልግሎት ዘርፎች ከጉባኤው በላይ ከፍ ተደረጉ። ሰው እንዲህ ከፍ መደረጉን እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ይጠላዋል። ይህ ልማድ ሰውን “የእግዚአብሔር ድምጽ” ወይም “የእግዚአብሔር አፍ” በማለት ከፍ ያደርጋል፤ በዚህ የተነሳ ሰው ሲናገር ከአፉ የተወሰደ ጥቅስ ከእግዚአብሔር ቃል እኩል ወይም በላይ ተደርጎ ይቆጠራል።

ኮንስታንቲን በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ ትልልቅ ሕንጻዎችና ብዙ የገንዘብ ስጦታዎች ስላፈሰሰባት ቤተክርስቲያኒቱ የእርሱ አሽከር ሆነች። የሮማው ጳጳስ በበላይነት የሚመራው ሐይማኖታዊ ድርጅት ተመሰረተ። ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ ይህ የሮማ ጳጳስ የባቢሎናውያን ምስጢራት ፖንቲፍና ፖፕ ተባለ። ደግሞም የቤተክርስቲያኒቱ አለቃ እንደመሆኑ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የሚቃወሙዋትን ሁሉ ስደት እና ግድያ እንዲፈጸምባቸው ፈቃድ ሰጠ።

እውነተኞቹ አማኞች የዚህ በሁሉ ላይ ገዥነትን እና ዝናን የሚፈልግ የኒቆላዊነት ሥርዓት አካል መሆን አልፈለጉም። እውነተኛ አማኞች በየቦታው በማሕበረሰቡ መካከል በተበታተኑበት እንዳሉ የታሪክ ምሑራንም ትኩረት ሳይሰጡዋቸው እግዚአብሔርን ማገልገል ብቻ ነው የፈለጉት። አንዳንዴ በቱርስ እንደነበረው እንደ ማርቲን ያለ ታላቅ ሰው ሕዝቡን ወደ አዲስ ኪዳናዊ የቤተክርስቲያን ቅንነት ለመመለስ ባደረገው ሙከራ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል፤ በዚህም የተነሳ ራሱን የሰዋበት አገልግሎቱ እና ያመጣቸው ውጤቶች በዚህ ዘመን ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድረዋል። ሰይጣን ማዕከላዊ የሆነና የተደራጀ ጭካኔ የሞላበት ጨቋኝ የቤተክርስቲያን ድርጅት እየመሰረተ ነበር፤ ነገር ግን በዚያኑ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሕይወታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይመሩ በነበሩ ግለሰቦች ውስጥ በነጻነት ሥራውን እየሰራ ነበረ።

ራዕይ 2፡16 እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።

ኒቆላዊነት በንጉሱ ድጋፍ በፍጥነት ሐሰተኛ ቤተክርስቲያን ማቋቋም ጀመረ። አማኞች በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለመቆየት ቢሞክሩ በሰዓቱ እውነትን እያሰጠመ በነበረው የሐሰት ጎርፍ ተጠርገው ይወሰዳሉ። ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣው ሰይፍ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን እና አዲስ ኪዳንን በአንድነት ስለሚይዝ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሁልጊዜ የሰዎችን ሃሳብ ይቃወማል። ኢየሱስ ደጋግሞ “ተጽፏል” እያለ በመጥቀስ ነው ሰይጣንን ያሸነፈው። በዚህኛው ዘመን የኒቂያ ጉባኤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሃሳቦችን በማቅረብ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ቃል አርቆ ወሰዳቸው። እግዚአብሔርን ለማስደሰት ብቸኛው መንገድ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመለስ ነው። ቤተክርስቲያን እንደ ገንዘብና ስልጣን የመሳሰሉ ዓለማዊ ጥቅሞችን ለማግኘት ብላ ፖለቲካ ውስጥ ገባች። በዚህም የተነሳ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊነቷን አጣች። ይህም ከባድ ኪሳራ ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ሰይፍ ነው። እግዚአብሔር መንፈሳዊ እውነትን ከማንኛውም ዓይነት ምድራዊ ጥቅም የሚበልጥ ዋጋ ይሰጠዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ጸንቶ መኖር የብልሃተኛ ሰውን ጥበብ ከመከተል እጅግ ይበልጣል።

እውነተኛ አማኞች በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊነትና የእግዚአብሔር ቃል እንደሌለ ሲያዩ ቤተክርስቲያኒቱን ለቀው ወጡ። ታሪክም ብዙዎቹን ረሳቸው እግዚአብሔር ግን አልረሳቸውም። እውነተኛ አማኞች ብዙውን ጊዜ ዝነኛ አይሆኑም ምክንያቱም ዓላማቸው የሕዝብ ዓይን ውስጥ ለመግባት ሳይሆን ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ሆኖ ለመኖር ነው።

ራዕይ 2፡17 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፥ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፥ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል።

ለየዘመናቱ የተሰጠ አንድ አይነት ትዕዛዝ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ታድምጥ የሚል ነው። ቤተክርስቲያን በየዘመናቱ የሚፈጠሩ አዳዲስ ችግሮችን ለመቋቋም ብላ የተለያዩ ሃሳቦችን ማመንጨት የለባትም። እግዚአብሔር አንዴ የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ እንደነበረ ሆኖ ሳይሻሻል በየዘመናቱ የሚመጡ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ብቁ መሆኑን ሊያሳየን ይፈልጋል። ድንጋይ ጠንካራ ስለሆነ በሕንጻዎች ውስጥ በመንገዶችና በድልድዮች ውስጥ ሳይለወጥ ለረጅም ዘመን ይኖራል። ድንጋዮች ጽኑ ናቸው። ስለዚህ ድንጋይ የማይለወጥ ጽናትና የማይናወጥ እምነት ምሳሌ ነው።

ለእያንዳንዱ ድል ነሺ እግዚአብሔር ያዘጋጀለት አዲስ ስም አለው። እነዚህ ክርስቲያኖች በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲየን ተገፍተዋል።

ተገፍተ፤ ብዙውንም ጊዜ ተሰድደው፣ ንብረታቸው ተወርሶ ከቤትና ከሃገራቸው ተፈናቅለው አስቸጋሪ ሕይወት አሳለፉ። ብዙዎቹ መንግሥት እውቅና በሰጣት በቤተክርስቲያን አማካኝነት ተገደሉ። ብዙውን ጊዜ ዝቅ ብለው በትሕትና የኖሩትን ሕይወት ታሪክ አልመዘገበላቸውም፤ ብዙውንም ጊዜ ምድራዊ ተስፋቸውን ስልጣን ወዳድ በሆኑ የቤተክርስቲያን አለቃዎች አማካኝነት ስለተነጠቁ ሕይወታቸውን በከንቱ ያሳለፉ ይመስል ነበር። ነገር ግን በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር ዓይኖቹ በእነርሱ ላይ እንደነበረ ተረድተዋል። ዓለም ስማቸውን ራሳች፤ እነርሱ ግን እያንዳንዳቸው የድላቸው ምልክት የሆነውን ነጩን ድንጋይ እንደ ሽልማት ሲቀበሉ አዲስ ስም ተሰጣቸው። አዲሱ ስማቸው በዙሪያቸው ሁሉ ቤተክርስቲያን ወደ አረማዊነት እየሰጠመች ስትሄድ እነርሱ ለመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ሆነው ለመጽናታቸው የሚቀበሉት የክብር ሽልማታቸው ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለሚደረገው ጥምቀት ታማኝ ሆነው ጸንተዋል። አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ስም መስሏቸው ተታለው የሄዱትን ሕዝብ አልተከተሉም። የተሰወረውን መና ማለትም የእግዚአብሔርን ታላቅ ምስጢር በልተዋል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ መንፈስ የነበረው ሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር ራሱን ፍጹም በሆነ የሰው ሥጋ ውስጥ አድርጎ ማለትም ኢየሱስ በተባለ ሰው ውስጥ አድሮ ወደ ምድር እንደመጣ አውቀዋል።

ዮሐንስ 14፡10 … በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ሰብዓዊ ስሙ ነው። ሰው እግዚአብሔር ሊሆን መቻሉ የተሰወረ ምስጢር ነበረ። አይንስታይን ብርሃን ሞገድ ሊሆን እንደሚችል አስተምሮናል (ኩሬ ውስጥ ድንጋይ ብትጥሉ በሁሉም አቅጣጫ እየሰፋ እንደሚሄድ ሞገድ)፤ ደግሞም ብርሃን በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚጓዝ ቀስትም ሊሆን ይችላል (እንደ ጥይት)። ይህ ታላቅ የፍጥረት ምስጢር ነው።

ኢየሱስ የዓለም ብርሃን ነው፤ እርሱ ብቻ ለዓለም ሁሉ ያበራል (እንደ ሰው በአንድ ቦታ ተወስኖ)፤ ነገር ግን በሌላ በኩል ደግሞ በእርሱ አካል ውስጥ የእግዚአብሔር የመለኮት ሙላት ልዕለ ተፈጥሮ የሆነ መንፈስ በሰውነቱ ውስጥ አደሮበታል (በዚህም የተነሳ ኢየሱስ በሥፍራም ሆነ በጊዜ ያልተገደበ ሆኖ ይኖራል)።

ስለዚህ እርሱ በእውነት ዘላለማዊ ብርሃን ነው።