ዮሐንስ ምዕራፍ 10. የሐይማኖት መሪዎች ከንቱነት



First published on the 21st of March 2021 — Last updated on the 21st of March 2021

ኢሳያስ 55፡8 አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር።

9 ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው።

ሰዎች የእግዚአብሔርን ሃሳብ አያስተውሉም።

ስለዚህ ሰዎች ተሰብስበው አንድ ሰውን መሪያቸው አድርገው ሲቀበሉ ያውም ደግሞ ሰውየው የዘመን መጨረሻ ላይ ግራ ስለሚያጋቡ ቀኑች የእግዚአብሔር እቅድ ምን እንደሆነ የማያውቅ ከሆነ እርሱ መሪ አድርገው መቀበላቸው ለጌታ ምጻት ለመዘጋጀት ምንም አይጠቅማቸውም።

እያንዳንዱ ግለሰብ ለራሱ መጽሐፍ ቅዱስብ ለመረዳት እና የእግዚአብሔርን ምሪት ለማግኘት መፈለግ አለበት።

የትኛውም መሪ የእግዚአብሔር ፈቃድ ለሌላኛው ሰው ምን እንደሆነ አያውቅም። እያንዳንዱ ግለሰብ ለሕይወቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ለራሱ ፈልጎ ማግኘት ማወቅ አለበት። ይህንን ሚስጥር ለእያንዳንዱ ሰው ማስተማር የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

 

ፈሪሳውያን የእሥራኤል እረኞች ነን ይላሉ። ግን…

መዝሙር 23፡1 እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም።

ብቸኛው እውነተኛ እረኛ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አይደለም።

የኢየሱስ ክርስቶስ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ኃይል እርሱ የእሥራኤል እረኛ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ፈሪሳውያን ግን ይህ እውነት ስልጣናቸውንና ገንዘባቸውን የሚነጥቃቸው ስለሆነ አጥብቀው ተቃወሙት። እነርሱ ለአይሁዶች መንፈሳዊ ደህንነት ምንም ግድ አልነበራቸውም። ኢየሱስ በፊታቸው እየፈጸመ የነበረውን የመጽሐፍ ቃል ፈትሸው ለማረጋገጥ እንኳ ጊዜ አልወሰዱም። አይሁድን ይመሩ የነበረው ለግል ጥቅማቸው ነበር። ገንዘብ የመሰብሰብ ፍላጎታቸው እነርሱን ቅጥረኛ እረኛ አድርጓቸዋል።

እነርሱ ያዋቀሩት ሐይማኖታዊ ሥርዓት እንደ ብረት በጠነከረ የሰው ተቆጣጣሪነትና መሪነት ውስጥ ነው። በዚህ ስርዓት ውስጥ ግለሰቦች በእግዚአብሔር መንፈስ ለመመራት አይፈቀድላቸውም። በእግዚአብሔር ቃል ቦታ የሰዎችን ወግ ተክተዋል።

ዮሐንስ 10፡1 እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤

የአይሁድ መሪዎች ከአይሁዶች እግዚአብሔርን የማወቅ መብታቸውን ነጥቀዋቸዋል። ሲሰብኩ ከመጽሐፍ ቅዱስ አይሰብኩም፤ ከራሳቸው ሃሳብ እና ከራሳቸው አተረጓጎም ይሰብካሉ እንጂ። በአታላይነታቸው ሕዝቡን የአይሁድ መሪዎችን እንዲከተሉ አደረጉ። ይህም ዓይናቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲርቅ አደረገ።

ዳንኤል 11፡14 … ከሕዝብህም መካከል የዓመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፤ ነገር ግን ይወድቃሉ።

የሐይማኖት መሪዎች ሕዝቡን ለክርስቶስ ምጻት እንዲዘጋጅ እንረዳዋለን በማለት የራሳቸውን ታላቅነት በሕዝብ ላይ መጫን ይፈልጋሉ። የራሳቸውን ዋጋ በሰዎች ላይ ከፍ በማድረግ ሕዝቡ ዓይናቸውን በኢየሱስ እና በተጻፈው ቃል ላይ ሳይሆን በመሪዎች ላይ እንዲያደርግ ያደርጉታል።

ከዚህም የተነሳ ሕዝቡ ከኢየሱስ ጋር የጠለቀ መንፈሳዊ ሕብረት አይኖራቸውም፤ ምክንያቱም የሐይማኖት መሪዎቻቸውን ስለሚፈሩና ለእነርሱም ስለሚታዘዙ ነው።

ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች በቤተክርስቲያን መሪዎቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ይፈልጋሉ፤ “ደህንነትም” የሚሰማቸው በዚህ ነው። የቤተክርስቲያን መሪዎችን እንዲያደንቁ እና እንዲከተሉ ስለተማሩ ሕዝቡ ምንም ጥያቄ የማይጠይቁ ዝም ብለው ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሆነው ይቀራሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው ቃል በጣም ብዙ የማይገባቸው ነገር አለ።

መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ችግር ነው ብለው አያስቡም ምክንያቱም ደህንነታቸው የሚጠበቀው “ቤተክርስቲያን በመሄዳቸው” ይመስላቸዋል። የቤተክርስቲያን መሪዎች እራሳቸው ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን ማለት እንደሆኑ አያውቁም። ከዚያም በላይ መረዳት ያልቻሉትን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ትተው ማለፍ፤ ትርጉሙን መለወጥ ወይም ቃሉን መቃረን ነው ልማዳቸው።

“ቤተክርስቲያን መሄድ” የሚለው አነጋገር እራሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።

ጌታ ወደ አይሁዳውያን በመጣ ጊዜ እነዚሁ የሐይማኖት መሪዎች እራሳቸው ናቸው አንቀበልህም ብለው የገፉት፤ ይህም ሳይበቃቸው ደግሞ ሕዝቡ እንዳይቀበሉትም አድርገዋል። በእኛ ዘመን ለጌታ ዳግም ምጻት እየተጠባበቅን ሳለን ታሪክ እራሱን ይደግማል።

ወደ መንግስተ ሰማይ መግቢያ አንድ በር ብቻ ነው ያለው፤ እርሱም የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የምናደርገውም ሆነ የምናምነው እምነታችንን ለማረጋገጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን በማገናኘት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።

ኢሳይያስ 28፡10 ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው።

እውነትን የምናረጋግጠው በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚናገሩ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማገናኘት እና በአንድ ላይ በማንበብ ነው። ያገኛችሁት መገለጥ ትክክለኛ የሚሆነው አንድም እንኳ የሚቃረነው ጥቅስ ከሌለ ነው።

የሐዋርያት ሥራ 14፡27 በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ።

ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።

እምነት የሚመጣው ከእግዚአብሔር ቃል ነው።

ወደ ሰማይ መድረስ ከፈለግን ልናልፍበት የሚገባን በር የእግዚአብሔር ቃል ነው።

ዮሐንስ 10፡2 በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው።

ኢየሱስ የመጽሐፍን ቃል እየፈጸመ ነበር። ይህም እውነተኛው የእምነት በር ነው።

ሰባኪ ከእግዚአብሔር ቃል መስበክ አለበት ምክንያቱም የሰባኪ አገልግሎት ሕዝብን ወደ እግዚአብሔር ቃል ማመልከት ነው።

አንድ ነገር እውነት ነው ብለን ማመን ያለብን መጽሐፍ ቅዱስ ስለተናገረው ብቻ ነው እንጂ ሰው ተነስቶ እውነት ነው ስላለ አይደለም። የእግዚአብሔርን ቃል ካመንን ኢየሱስን እየተከተልነው ነን ምክንያቱም እርሱ ነው የእግዚአብሔር ቃል።

እግዚአብሔር የዕውሮችን ዓይን በከፈተ ጊዜ አንድ ያልተለመደ ነገር እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።

እግዚአብሔር በሰው ሰራሽ አስተምሕሮዎች በተወረረው የአይሁድ ሐይማኖታዊ ስርዓት ውስጥ መስራቱን ሊያቆም ነው የወሰነው።

ኢሳይያስ 42፡16 ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፥ በማያውቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፥ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውምም።

18 እናንተ ደንቆሮች፥ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች፥ ታዩ ዘንድ ተመልከቱ።

ለዚህ ነው ሰዎችን እንደ መሪ መከተል የማንችለው። እግዚአብሔር ሃሳቡ ከእኛ ሃሳብ የተለየ ነው፤ የሰው መሪዎችም እግዚአብሔር ምን እንደሚያስብ አያውቅም። ስለዚህ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የግል ምሪት ያስፈልገናል።

ኢሳይያስ 55፡8 አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር።

ስለዚህ ማንም ሊመራችሁ አይችልም። ሰው ሊመክራችሁ ይችላል ግን ለሕይወታችሁ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ሊነግራችሁ አይችልም። እኛ ማድረግ የምንችለው ነገር ቢኖር እርስ በራሳችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መካፈል ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር እንዲመራችሁ መፍቀድ የእያንዳንዳችሁ ሃላፊነት ነው።

በጣም የሚያሳዝነው ነገር ሰዎች ብዙ ሕዝብ የሄደበትን መንገድ መምረጣቸው ነው። የመንጋ አስተሳሰብ ማለት በራሳችን አእምሮ ተጠቅመን ማሰብ አቁመናል ማለት ነው። ሌሎች ሰዎችን እየኮረጅን በመኖራችን ሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች እንሆናለን፤ እራሳችንን ሳንሆን እንቀራለን።

ኢየሱስን ከተከተልክ ራስህን የቻልክ ግለ ሰብ ትሆናለህ ምክንያቱም በአንተ እና በእርሱ መካከል ማንም የለም።

ሰዎች መንፈሳዊ እውነትን ማየት ይችሉ ዘንድ ሰው ለሰዎች የእምነትን በር መክፈት አይችሉም። ሰዎች ዕውር ዓይን ማብራትም አይችሉም። ለምን?

በሮችን መክፈት የሚችል በረኛ አለ እርሱም አንድ ብቻ ነው። ይህም በር ከፋች እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የሚሰማው ደግሞ ቃሉን ብቻ ነው።

ዮሐንስ 10፡3 ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል።

እግዚአብሔር የሚናገረን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው።

ኢየሱስ ዕውር ዓይኖችን በማብራት እርሱ በተናገረ ጊዜ በረኛው እግዚአብሔር ሰምቶት ለፍጥረታዊ ዓይኖች ብርሃን የሚበራበትን በር እንደከፈተ ያሳየናል። ይህም ድርጊቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እናስተውል ዘንድ የመንፈሳዊ እይታ በሮችን እንዲከፍትልን ማድረግ እንደሚችልም ያመለክታል።

ኢየሱስ እያንዳንዱን አማኝ በግል ያውቃል።

ኢየሱስ ቤተክርስቲያንን አያድንም። የሚያድነው ግለሰቦችን ነው። እያንዳንዱ ግለሰብ ከእርሱ ጋር ጠለቅ ያለ ሕብረት ማድረግ ያስፈልገዋል። እያንዳንዱ ሰው በመንፈስ ቅዱስ መመራት አለበት።

የክርስቶስ መንፈስ አማኞችን ሲመራቸው ከቤተክርሰቲያን፣ ከቡድናዊ አስተሳሰብ፤ ከሰዎች ልማድና ሃሳብ “አውጥቶ በመውሰድ” ነው የሚመራቸው።

ኢየሱስ ክርስቶስ አማኞችን ወደ ራሱ ይስባል። የትኛውም ሰባኪም ሆነ ቤተክርስቲያን በኢየሱስ እና በአንድ አማኝ መካከል መግባት የለባቸውም።

እውነትን ለመለየት ብቸኛው መለያ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ስሕተት የሌለው መመሪያችን መሆን አለበት።

ዛሬ ግን ክርስትና በቤተክርስቲያን ተመላላሾች እና “በቤተክርስቲያናዊነት” ተተክቷል። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ ማመን አለብን የሚል ጠንካራ አቋም የላቸውም።

ዮሐንስ 10፡4 የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤

“የእግዚአብሔር ድምጽ” መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማድረግ እና ምን ማመን እንዳለብን ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ኢየሱስ ሲናገረን ማለት ነው።

2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።

አስተምሕሮ የስልጣን መሰረት ነው።

ማርቆስ 1፡22 እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ።

ተግሳጽ የሰራነውን ስህተት ይነግረናል። እርማት ደግሞ የተሳሳቱ ትምሕርቶቻችንን እንድናቃና እንድናስተካክል ይረዳናል።

መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ጻድም ለመሆን የሚጠቅመንን መረጃ ይዟል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ መጽሐፍ ነው። ከተፈው ውስጥ ምንም ነገር መለወጥ ወይም መቀነስ ወይም በላዩ ላይ አንዳችም መጨመር የለብንም።

 

 

“በጎቹ እርሱን ይከተሉታል”

በጎቹ የቤተክርስቲያን መሪን አይከተሉም። በጎቹ ከቤተክርስቲን ወጎች እና አመለካከቶች ጋር አይስማሙም።

በጎቹ ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን ውስጥ እየመራ ያስወጣቸው ሰዎች ናቸው፤ ያስወጣቸውም በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እርሱን ብቻ መከተል እንዲችሉ ነው።

ዮሐንስ 10፡5 ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና።

ንግግራችሁ ከእግዚአብሔር ቃል ካልሆነ እውነተኛው አማኝ ይሸሻችኋል።

ሆሴዕ 7፡14 በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዐመፁ።

ወይን በመገለጥ የሚመጣ መነቃቃት ነው።

የእርነሱ የቃል መገለጥ ግን (እህሉ) መጽሐፍ ቅዱስን መለወጥ፤ ቃሉን ቸል ማለት፣ እና በአንዳንድ ቦታዎች ቃሉን መቃረን ነው። ሰዎች በቤተክርስቲያን ውስጥ የራሳቸው የሆነ እምነት ለማበጀት ይሰበሰባሉ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ለመስማት አይደለም። በስተመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚለውን የሚያምኑ ሰዎችን ይቃወሟቸዋል። ስለዚህ በአንድነት መሰብሰባቸው በአለማመናቸው እያጸናቸው ይሄዳል።

አንድ ፓስተር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ነገር በተናገረ ሰዓት እውነተኛ አማኝ ወዲያው ይሸሻል።

መሪያችንን ተከተሉ የሚለው አባባል ለብዙ ዘመን አደጋ ያስከተለ የቤተክርስቲያኖች ልማድ ነው። ይህም ማለት በራስህ እና በእግዚአብሔር መካከል ሰውን ማስገባት ነው። ይህ ስሕተት ነው። ትኩረትህ በቀጥታ በኢየሱስ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መሆን አለበት።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሊቀ ካሕናቱ በስተቀር ማንም ሰው ከካሕኑ በላይ አልነበረም።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ እያንዳንዱ አማኝ ካሕን ነው።

1ኛ ጴጥሮስ 2፡9 እናንተ ግን … የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤

ካሕን እንደመሆንህ መጠን ከአንተ በላይ ያለው ሊቀካሕናቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

ዕብራውያን 6፡20 በዚያም ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው፥ ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ ገባ።

ስለዚህ ከአማኙ በላይ ኢየሱስ ብቻ እንጂ ሌላ ሰው የለም።

መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነው ማመን ያለብን። እያንዳንዱ ሰባኪ ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው መስበክ ያለበት።

ሰዎች ሰባኪውን እንዲከተሉ ማድረግ ከ45,000 በላይ የተለያዩ ቤተክርስቲያኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።

 

እያንዳንዱ ሰባኪ የሚመራትን ቤተክርስቲያን የራሱን መልክ እንድትመስል ይጥራል።

ይህም በስተመጨረሻው ቤተክርስቲያኒቱ የሮማ ካቶሊክን አውሬ እንድትመስል ያደርጋታል፤ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት ሰው የቤተክርስቲያን ራስ ሆኖ ቤተክርስቲያንን መግዛት እንዳለበት ሃሳቡን ያመጣችው። ነገር ግን ከካቶሊክ ትምሕርቶች ውስጥ እውነት መሆናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተመሰከረላቸው ትምሕርቶች ብዙም አይደሉም።

ካቶሊክ ያልሆኑ ቤተክርስቲያኖችም እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተደገፈ አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያምን አማኝ ሰው ሰራሽ ሃሳቦች አይስቡትም፤ ሊከተላቸውም አይፈልግም።

በፍርድ ቀን የሚፈረድብን በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው እንጂ ሰዎች በተናገሩት አይደለም።

ዮሐንስ 10፡6 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደ ሆነ አላስተዋሉም።

የሐይሁድ ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን ማመን እና በክርስቶስ መንፈስ መመራት ምን ማለት እንደሆነ እንኳን አያውቁም።

ዛሬም ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ምን ማለት እንደሆኑ የማያውቋቸው ብዙ ጥቅሶች አሉ።

ልክ አይሁዶች ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃል መረዳት ሲያቅታቸው ቸል እንዳሉ ሁሉ ዛሬም ሰወች ያልገባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ቸል ብሎ ማለፍ በጣም የተለመደ ነገር ሆኗል። አይሁዶች እግዚአብሔርን እናገለግላለን ብለው ከሚያስመስሉ የሐይማኖት ስርዓቶች ውስጥ እግዚአብሔር ሰዎችን ሊያስወጣ ማሰቡን አላወቁም። እግዚአብሔርን በማገልገል ፈንታ የሐይማኖት ተቋማት ሰዎችን ከፍ በማድረግ ነው የተጠመዱት፤ በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ለእነዚህ የሐይማኖት መሪዎች ተገዢ ይሆናል።

ኢየሱስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ከአይሁዶች ጋር የገጠመው ችግር እና ዛሬ ከቤተክርስቲያኖች ጋር የገጠመው ችግር ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሆኑት ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን የዛሬዎቹ “የቤተክርስቲያን አባላትም” ማስጠንቀቂያ እንዲሆኑ ነው (“የቤተክርስቲያን አባላት” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል አይደለም)።

 

ዮሐንስ 10፡7 ኢየሱስም ደግሞ አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ።

“አሥር” እና “ሰባት” ሚስጥር ያላቸው ቁጥሮች ናቸው። እነዚህ ቁጥሮች የስርየት ቀንን ይወክላሉ።

ሌዋውያን 16፡29-30 ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ፤ በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተስረያ ይሆንላችኋልና በሰባተኛው ወር ከወሩም በአስረኛው ቀን ራሳችሁን አስጨንቋት፥ የአገር ልጅም በእናንተ መካከል የተቀመጠም እንግዳ ሥራን ሁሉ አትሥሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ።

ሐጥያታችን ማስተስረይ የሚችለው ኢየሱስ ብቻ እንደመሆኑ በእርሱ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ራዕይ 1፡6 ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥

የኢዮቤልዩ መለከት የሚነፋው ሰዎችን ከሌላ ሰው ባርነት ነጻ ለማውጣት ነበር።

ሌዋውያን 25፡9 ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ።

10 አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ።

ኢየሱስ ከሐጥያት ሊያድነን የመጣው በሰዎች ከመመራት ነጻ ሆነን እርሱን ብቻ መከተል እንድንችል ነው። ሰዎች ሊመክሩን እና መረጃ ሊሰጡን ይችላሉ ግን እንድንከተላቸው መጠበቅ አይችሉም። ሰባኪ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ወደ ቃሉ ማመልከት አለበት፤ እርሱ ራሱ ኢየሱስን ተክቶ እንዳይቆም መጠንቀቅ አለበት። ሰዎችን የራሳቸው ተከታይ ማድረግ የሚፈልጉ ፓስተሮች ተልዕኮዋቸውን ሙሉ በሙሉ ዘንግተዋል።

ዮሐንስ 10፡8 ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም።

ሰባኪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተው ማረጋገጥ የሚችሉትን ብቻ ነው መስበክ ያለባቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አንዳች እንኳ የሚቃረን ስብከት ሐሰተኛ እምነት ነው።

ከመረጥነው ቤተክርስቲያን መሃይምነት ጋር ተጣብቀን እንቀራለን። ተስፋችን እራሱ እያነሰ ይሄዳል፤ ቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ስለማታውቀው እኛም መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ እናስተውላለን ብለን ተስፋ አናደርግም። ከዚህም የተነሳ ሰዎች የራሳቸውን መረዳት ለመደገፍ ብለው እውነትን ይጠመዝዛሉ።

እውነተኛ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈ ነገርን ሁሉ አይቀበሉም።

 

 

ዮሐንስ 10፡9 በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል።

መውጣትና መግባት ተቃራኒዎች ናቸው።

አንድ ችግር ይዘን ወደ ጸሎት ክፍላችን ብንገባ የገጠመን ችግር ለእኛ ብርታትና ጥቅም ሆኖ ይወጣል።

ሐዘን በመጀመሪያ ጠቆር ያለ ጨርቅ ለብሶ ይመጣል፤ ከዚያ በኋላ ግን ልባችን ለስለስ ያለ እና ሩህሩህ እንዲሆን ያደርጋል።

ሐዘን ደስታችንን የያዘውን ጽዋ ቆርጦ የሚያወጣ ቢላዋ ነው።

ኢየሱስ በሩ ነው። መጀመሪያ በበሩ መግባት አለብን፤ ከእርሱ ጋርም የግል ልምምድና ሕብረት ማድረግ አለብን፤ ይህን ካደረግን ሃሳባችንን የሚቆጣጠረው የእግዚአብሔር ቃል ነው። እምነታችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፉት የተለያዩ ጥቅሶች አማካኝነት በማረጋገጥ ኢየሱስን መከተል አለብን። እኔነትና የራስ ፈቃድ ባዶ ናቸው። ከዚያ በኋላ በበሩ እንወጣና ከውጭ ላሉ ሰዎች ኢየሱስን አጉልተን በመግለጥ እናሳያለን።

ዝቅ ለማለት ወደ ውስጥ እንገባለን፤ ከዚያ የእርሱን ከፍ ማለትና መጨመር ለማሳየት እንወጣለን። ትኩረት የሚደረገው በቤተክርስቲያን ወይም በቤተክርስቲያን መሪ ላይ አይደለም። ትኩረት መደረግ ያለበት በኢሱስ ላይ ነው።

ሰባኪው መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ፍጹም እውነት የማያየው ከሆነ እና እራሱን የማይሰዋ ከሆነ በበሩ በኢየሱስ በኩል ማለፍ አይችልም።

ማንም ሰው በጎችን መምራት አይችልም። ሰው ማድረግ የሚችለው በጎችን ወደ እግዚአብሔር ቃል ማለትም ወደ ኢየሱስ መጠቆም ብቻ ነው።

 

ዮሐንስ 10፡10 ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።

መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ቁልፉ መጽሐፍ ቅዱስን ማመን ነው፤ መንፈስ ቅዱስም የዘላለም ሕይወት ነው።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ሃሳብን ማመን ወደ ሞት ብቻ ነው የሚመራው።

ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።

መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰወሩ እውነቶችን ይገልጣል።

ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ ነገር ሁሉ ሞት ልብሱን ቀይሮ ሲመጣ ማለት ነው።

ዮሐንስ 10፡11 መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።

ኢየሱስ ብቻ ነው መልካሙ እረኛ። ሌላ ሰው እረኛ አይደለም። ኢየሱስ መልካም እረኛነቱን ለሕዝብ በመሞት አሳይቷል።

ዮሐንስ 10፡12 ረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።

ቅጥረኛ ሰባኪዎች ግን የሚሰማሩት ለግል ጥቅማቸው ብለው ነው። ችግር ሲመጣ ቀድመው ይሸሻሉ። ሰባኪነት ለእነርሱ ጥሩ ክፍያ የሚያገኙበት ሙያ ነው እንጂ ጥሪ አይደለም። አደጋ ሲመጣ ሲያዩ ጥለው ይፈረጥጣሉ። የበጎቹ ደህንነት ዋነኛ ጉዳያቸው አይደለም።

ዮሐንስ 10፡13 ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል።

ቅጥረኛ ችሎታውን ከፍተኛ ገንዘብ ለሚከፍለው ተጫራች ይሸጠዋል። ቅጥረኛ ድሃ ከሆኑ መሰማሪያዎች ሃብታም ወደሆኑ መሰማሪያዎች ይሄዳል፤ አደገኛ ከሆኑ ቦታዎች እየለቀቀ ሰላም ወደ ሆኑ ምንም አደጋ ወደሌለባቸው ቦታዎች ይሄዳል።

እራሳቸውን ለበጎቹ የበላይ አድርገው ይቆጥራሉ፤ በጎቹንም የእነርሱ አገልጋይ አድርገው ነው የሚያዩት። የሚያሳዝነው ነገር እራሳቸው ምንም የማያውቁ መሆናቸው ነው።

ከሰባተኛው መልእክትኛ በቀር መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ በመጨረሻው ዘመን ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ይነቅፋል።

ማቴዎስ 23፡13 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።

የሐይማኖት መሪዎች ሕዝቡ በተጻፈው ቃል በር ውስጥ እንዳይልፉ ከለከሉዋቸው። መረዳት ያልቻሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደማይጠቅም አድርገው ቸል አሉት።

የቤተክርስቲያን ሰባኪዎች ዛሬ ከእነርሱ ሃሳብ ጋር የማይስማማ የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲያጋጥማቸው ይቃወሙታል፤ ከዚያም ሕዝቡም እውነትን እንዳያገኙ ሕዝቡን የራሳቸው እስረኛ ያደርጉታል።

ዮሐንስ 10፡14 መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ … የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤

አንድ መልካም እረኛ ብቻ ነው ያለው፤ እርሱም ኢያሱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ፍጹም “ትክክለኛ” መሪያቸው አድርገው የሚቀበሉ ግለሰቦችን ያውቃቸዋል። ለእያንዳንዱ ግለሰብ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ የሚያውቀው ኢየሱስ ብቻ ነው። እነዚህ ግለሰቦችም ምሪታቸውን ከተጻፈው ቃል ውስጥ ያገኛሉ እንጂ ከየትኛውም የቤተክርስቲያን መሪ አስተሳሰብ አይደለም የሚያገኙት።

እውነት አድርገው የሚቀበሉት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉትን ቃሎች ብቻ ነው።

የቤተክርስቲያን መሪዎች ሰዎችን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እንጂ ወደራሳቸው አስተሳሰብ መምራት የለባቸውም።

ዮሐንስ 10፡15 አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው … ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆኑ በውስጡ የሚኖረውን እግዚአብሔርን ያውቀዋል። እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ የተባለውን ሰው ሥራዎች ሁሉ ይመራል።

ኢየሱስ ከፊት ለፊቱ አደጋ ሲመጣ ተመለከተና ይህንን ጥቃት በቀራንዮ ፊት ለፊት ተጋፈጠው። ከመስቀሉ አደጋ ሸሽቶ መሮጥን እምቢ አለ። በጎቹን ሊመታ የመጣውን የሐጥያት ሞት ፍርድ በራሱ ላይ ተቀበለው። ከአደጋ ሸሽቶ በመሮጥ ፈንታ እራሱን በመሰዋት በጎቹን አዳናቸው።

ቆላስይስ 2፡9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤

ኢየሱስ ማለት እግዚአብሔር እራሱን በሰው መልክ ሲገልጥ ነው።

 

ዮሐንስ 10፡16 ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።

ይህ በጠማ ጠለቅ ያለ እውነት ያለው ጥቅስ ነው። ማለትም ኢየሱስ የገጠሙትን ችግሮች ለመፍታት የወሰደው እርምጃ በ2,000 ዓመታት የቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለምንኖረው ለእኛም በዘመናችን ይጠቅመናል። በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ በእያንዳንዱ ዘመን ኢየሱስ ሕዝቡን ለዚያ ዘመን በተገለጠው እውነት አማካኝነት ይመራቸዋል። በየትኛውም ዘመን ውስጥ ሰውን መከተል ዋጋ የለውም ምክንያቱም ያ ሰው በቀጣዩ የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ አይኖርም። ስለዚህ ሰባኪዎች በሙሉ የተላኩት ሰዎችን ወደ ኢየሱስ እንዲመሩ ነው፤ በሁሉም የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ሊገኝ የሚችለው እርሱ ብቻ ነውና።

በእያንዳንዱ ዘመን ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች ኢየሱስን በግል ልምምድ ቢከተሉት ኢየሱስን መከተላቸው በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ከኖሩት ከሁሉም ዘመናት ክርስቲያኖች ጋር አንድ ያደርጋቸዋል።

ኢየሱስን መከተል ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠውን እውነት ማመን ነው።

ዮሐንስ 10፡17 ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል።

ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር ዓላማ መከራን ለመቀበልና ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑ በውስጡ የሚኖረውን እግዚአብሔርን አስደነቀው።

ዘር በአዲስ ሕይወት ከመብቀሉ በፊት መሞት እና በአፈር ውስጥ መቀበር አለበት። ስለዚህ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ዘር እንደመሆኑ የዘላለም ሕይወትን በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ በእርሱ ለሚያምኑት ከማካፈሉ በፊት መሞትና መነሳት ነበረበት።

ዮሐንስ 10፡18 እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።

ኢየሱስ በክፉ አጋጣሚዎች ምክንያት አይደለም የተገደለው። ለሐጥያታችን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት መርጦ ነው የሞተው። ደግሞም ሮማውያን መቃብሩን ቢያሽጉትና በዘበኛ ቢያስጠብቁትም እንኳ ከሙታን ለመነሳትም መርጧል።

መዝሙር 16፡10 ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም።

እግዚአብሔር ይህንን የተስፋ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ትንቢት ነው የጻፈው።

ስለዚህ ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ ከሶስት ቀናት በላይ እንደማይቆይ አውቋል። (ሰው ከሞተ ሶስት ቀን ሲያልፈው መበስበስ ይጀምራል)።

የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል መፈጸም መቻላችን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ለመሆኑ እውነተኛ ዋስትና ነው።

 

ዮሐንስ 10፡19 እንግዲህ ከዚህ ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ሆነ።

አይሁዳውያን ተከፋፈሉ። አንዳንዶቹ ከልባቸው የፈሪሳውያን ተከታዮች በመሆን ኢየሱስን ማውገዝ ላይ ብቻ ነበር ትኩረታቸው።

ሌሎች ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ተዓምራትና በትምሕርቶቹ ተገርመው ነበር። ከእርሱ ጋር ሊወዳደር የሚችል አንድም ሰው አልነበረም።

ዮሐንስ 10፡20 ከእነርሱም ብዙዎች፦ ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ? አሉ።

የአይሁድ ሐይማኖት መሪዎች ሰው በሌላ ሰው በተበለጠ ጊዜ የሚያደርገውን ነገር ነበር የሚያደርጉት። ኢየሱስ ስለበለጣቸው ብቻ እርሱን ዲያብሎስ ነው አሉት። ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን መሪዎች ጋር አለመስማማቱ በጣም አበሳጭቷቸዋል።

ነገር ግን በእርሱ ላይ የሚለጥፉት ክስ በሙሉ የራሳቸውን ጉድለት የሚያጋልጥ ነበረ።

ሮሜ 2፡1 ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና።

የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን በሚከስሱበት ክስ እራሳቸው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተውበታል። ለዘመናቸው የተሰጣቸውን ቃል አንቀበልም ማለታቸው በውስጣቸው ያለውን ዲያብሎስ የሚያጋልጥ ድርጊት ነው።

ብቸኛው ፍላጎታቸው ኢየሱስን ለመግደል ስለሆነ የቃየንን የነፍሰ ገዳይነት ምሳሌ እየተከተሉ ነበረ።

ዮሐንስ 10፡21 ሌሎችም፦ ይህ ጋኔን ያለበት ሰው ቃል አይደለም፤ ጋኔን የዕውሮችን ዓይኖች ሊከፍት ይችላልን? አሉ።

የሐይማኖት መሪዎችን ያልፈሩ አይሁዶች ጻድቅ ሰዎች ዕውሮችን ማብራት ካልቻሉ እንግዲያውስ ዲያብሎስ ዕውሮችን ሊያበራ እንደማይችል ገልጠው እየተናገሩ ነበር።

በሰዎች ላይ መከራን መጨመር ብቻ የሚፈልገው ዲያብሎስ ሰዎችን በመፈወስ ከመከራ ሊገላግላችን ፍላጎት ይኖረዋልን?

 

ዮሐንስ 10፡22 በኢየሩሳሌምም የመቅደስ መታደስ በዓል ሆነ፤

በየዓመቱ ኪስሌቭ (ታህሳስ) በሚባለው ወር ከ25ኛ ቀን ጀምሮ ለስምንት ቀናት የሚከበረው በዓል ይሁዳ መቃዕብዮስ በሚባል ሰው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ164 ዓመት የተደነገገ ሲሆን በዓሉ የሚከበርበት ዓላማ አንቲዮከስ አፒፋነስ የተባለ ግሪካዊ የሶርያ መሪ ቤተመቅደሱን ካረከሰው በኋላ ቤተመቅደሱ የነጻበትን ቀን ለማሰብ ነው።

በዓሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አልበረም። ስለዚህ በዓል በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ አንዳችም አልተጻፈም።

ይሁዳ መቃዕብዮስ ፖለቲካዊ መሪ ነበረ። የሱ ሐሳቦችም ከእግዚአብሔር የመጡ ያህል ተቀባይነት ነበራቸው፤ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አልተናገረም። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ400 ዓመት አካባቢ የመጨረሻው ነብይ ሚልክያስ ትንቢት ከተናገረ በኋላ እግዚአብሔር ለእሥራኤል መናገር አቁሞ ነበር።

ይህ በዓል መከበር የጀመረው አይሁዳውያን እየሳቱ እና ከእግዚአብሔር እየራቁ በነበረበት ጊዜ ነው።

ይህ በዓል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ላልሆነው በዓል “ለክሪስማስ” ጥላ ነው። ክሪስማስ ዲሴምበር 25 ላይ መከበር የጀመረው በ350 አካባቢ ዓ.ም በካሊክ ቤተክርስቲያን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ልደት እንድናከብር አልተናገረንም። ክሪስማስ የሮማ ካቶሊክ ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ ካስገባቻቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆኑ ልማዶች መካከል አንዱ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ጳጳስ ቤተክርስቲያንን እንዲመራ የተደረገው በ100 ዓ.ም በአንጾኪያ ነው። ይህም ሃሳብ በፍጥነት ወደ ሌሎች ቤተክርስቲያኖች ተዛመተ። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ሰዎችቸ ሲሰሙ ሊገባቸው ወደማይችል የፈላስፎች “ሥላሴ” ተለወጠ።

በ325 ዓ.ም ከተደረገው ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ እንደ “እግዚአብሔር ወልድ፣” “የመለኮት ሁለተኛው አካል፣” እና “አንድ አምላክ በሦስት አካላት” ያሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ቃላት የቤተክርስቲያን እምነቶች ሆኑ። በስተመጨረሻ በወደቀው በምዕራባዊው የሮማ ግዛት ክፍል በ606 ዓ.ም የሮማው ጳጳስ በሌሎች ጳጳሳት ሁሉ ላይ የበላይ ሆነ።

ኢየሱስ ግን ቤተክርስቲያን ወደ ፊት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ እምነቶችን እንደምታስፋፋ አስቀድሞ አውቋል። በዚህ መንገድ ሰዎች ዓይናቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ (መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ኢየሱስ በጽሑፍ መልክ ነው) ላይ አንስተው የቤተክርስቲያን መሪን ሃሳብ ለመከተል መረጡ። የሰዎችም አመራር ቤተክርስቲያንን ወደ ጨለማው ዘመን ይዟት ገባ።

ዮሐንስ 10፡23 ክረምትም ነበረ። ኢየሱስም በመቅደስ በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ይመላለስ ነበር።

ከዚህ በታች ያለው ስዕል በቀይ ቀለም ቤተመቅደሱን እና በዙርያው የካሕናትን አደባባይ ያሳያል። ከዚያ ቀጥሎ ያለው የእሥራኤል አደባባይ ሲሆን እርሱም የአይሁዳውያን ወንዶች መቆሚያ ቦታ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የአይሁዳውያን ሴቶች መቆሚያ ቦታ ነው ያለው።

 

 

ከዚያ ቀጥሎ አሕዛብ መግባት የማይፈቀድላቸው ውስጠኛ አደባባይ አለ። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የአሕዛብ አደባባይ ከውስጠኛው አደባባይ ውጭ ነበረ። የሰሎሞን በረንዳ በቤተመቅደሱ ዙርያ ከሁሉም ዳር ያለው ውጨኛው ቦታ ነው። ከቤተመቅደሱ ሕንጻ ውጭ እና ከአሕዛብ አደባባይም ውጭ ነገር ግን በቤተመቅደሱ ዙርያ ባለው ትልቅ አጥር ውስጥ ነበረ።

ስለዚህ ኢየሱስ እንደ ቃሉ በቤተመቅደሱ ሕዝጻ ውስጥ አልነበረም። ከቤተ መቅደሱ ሕንጻ በጣም ርቆ ነበር ያለው፤ ነገር ግን በቤተመቅደሱ ዙርያ ከተሰራው ትልቅ አጥር ውስጥ ነበረ።

ይህም የአይሁድ ሐይማኖት መሪዎች እንዴት የእግዚአብሔርን ቃል (ኢየሱስን) እየገፉት እንደነበረ የሚያመለክት ነው፤ ደግሞም የተቻላቸውን ያህል ከእነርሱ እንዲርቅ እየገፉት ነበረ። ነገር ግን እርሱ ደግሞ መሲሃቸው ነበር። ስለዚህ ፈጽመው ሊያስወግዱት ቢፈልጉም እንኳ አልቻሉም።

ሌላው ምልክት ደግሞ በክረምት ቤተመቅደሱ በክረምት የሚመረቅበት በዓል ነበር፤ ይህም ቢሆን በብሉይ ኪዳን ምንም አልተጻፈለትም። ሰዎች መሪ ነን ብለው በእግዚአብሔር ቃል ላይ የራሳቸውን ሃሳብ ማጨመር ስለጀመሩ የእግዚአብሔርን ቃል አንቀበልም እያሉ ነበር።

ሰው ሰራሽ ትዕዛዞች ቦታ ሲይዙ ቃሉ ወደ ጎን እየተገፋ ነበረ።

ኢየሱስ ቃሉ ሆኖ ከቤተመቅደሱ በረንዳ ውጭ ይመላለስ ነበር። በቀራንዮ በሞተ ጊዜ እግዚአብሔር ቤተመቅደሱን ሙሉ በሙሉ ትቶ መውጣቱን ለማመልከት እግዚአብሔር የቤተመቅደሱን መጋረጃ ሙሉ በሙሉ ከላይ ወደ ታች ቀደደው።

ዮሐንስ 10፡24 አይሁድም እርሱን ከበው፦ እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት።

ኢየሱስ እኔ መሲሁ ነኝ ብሎ እንዲናገር ፈለጉ። ይህን የፈለጉት “ተሳደበ” ብለው እርሱን የሚገድሉበት ምክንያት ለማግኘት ነው። ነገር ግን እርሱ የፈጸማቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች እንዳያዩ ታውረው ነበር።

በተጨማሪም ደግሞ ከሮማውያን የፖለቲካ ባርነት ነጻ በመውጣት ሃሳብም ተጠምደው ነበረ። እነርሱ ሰራዊት አስከትሎ መጥቶ ሮማውያንን የሚወጋ መሲህ ነው የፈለጉት። ሐይማኖት እና ፖለቲካ ሲቀላቀሉ ሁልጊዜ ውጤቱ ስሕተት ነው።

ብዙ ተራ ሰዎች ግን ኢየሱስ በሚሰራቸው ተዓምራት ይደነቁ ነበር። የሐይማኖት መሪዎች ግን ስጋታቸው ክብራቸውን እንዳያጡ ነበር። ሰው ሰራሽ በሆነው ሐይማኖታዊ ስርዓታቸው ውስጥ ተመችቷቸው እየኖሩ ስለነበረ ኢየሱስን ከተቀበሉ ብዙ የሚያጡት ነገር እንዳለ አውቀው ስጋር ይዟቸዋል። መስዋዕትነትን አይፈልጉም ነበር።

ዮሐንስ 10፡25 ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤

ኢየሱስ በአገልግሎቱ ዘመን ውስጥ 42 ተዓምራትን አድርጓል። የሐይማኖት መሪዎች ደግሞ አንድም ተዓምር አላደረጉም። ነገር ግን ኢየሱስ ያደረገውን እያዩ ማመን አልቻሉም። እነዚያን ተዓምራት ሊያደርግ የሚችለው መሲሁ ብቻ ነው። ቢቀበሉት ደግሞ ክብራቸውን እና የገቢ ምንጫቸውን ያጣሉ።

ዮሐንስ 10፡26 እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።

ኢየሱስ ሲናገር ቀጥተኛ ነው። የእርሱ በጎች የመጽሐፍ ቃል ሲፈጸም አይተው ያስተውላሉ።

ዮሐንስ 10፡27 በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤

የኢየሱስ በጎች ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን እየፈጸመ መሆኑን ያውቃሉ። ኢየሱስ የራሱን ሕዝብ አንድ በአንድ ያውቃቸዋል፤ ለእያንዳንዳቸውም የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቃል። በጎቹ ይከተሉታል፤ ምክንያቱም መሲሁ ምን እንደሚያደርግ የተጻፈውን እየፈጸመ የነበረ ብቸኛው ሰው እርሱ ነው።

ዮሐንስ 10፡28 እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።

ሕይወትህን ለኢየሱስ ብትሰጠው ከእርሱ ጥበቃ ውስጥ ሊያስወጣህ የሚችል ማንም የለም። ዲያብሎስ አንዳንዴ እንድትወድቅ ሊያደርግህ ይችላል ነገር ግን በወደቅህበት ሊያስቀርህ አይችልም። ችግሮች አማኝን እንዲያድግ ያደርጉታል እንጂ ተስፋ አያስቆርጡትም። ለአጭር ጊዜ ከመጣው ስቃይ አሻግረው በማየት ለረጅም ጊዜ የሚመጣውን ጥቅም ይመለከታሉ።

መፈክራቸው ይህ ነው፡- “የምታልፉበት መከራ ዓላማው እግዚአብሔር እናንተን በሚፈልግበት ቅርጽ ለመቅረጽ ነው።”

በዚህ ዓለም ውስጥ መሞት አዲስ ነገር አይደለም ምክንያቱም ኢየሱስን መከተል ማለት ወደ ሰማይ የምትሻገርበት በር ይከፈትልሃል ማለት ነው።

ዮሐንስ 10፡29 የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።

ኢየሱስን መከተል የሚያስለምደን አስተሳሰብ እያንዳንዱን ማዕበል እንደ ትምሕርት ቤት እንድንቆጥር የሚያደርግ ነው፤ ስለዚህ እያንዳንዱ ፈተና አስተማሪ እና እያንዳንዱ ልምምድ ትምሕርት ነው። እያንዳንዱ ተግዳሮት የሚገጥምህ ለአንተ እድገት ነው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ዓላማ ካንተ መከራ ይበልጣል።

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ኃይል አብሮት አለ። እግዚአብሔር ከየትኛውም ሰው፣ ከየትኛውም መንፈስ፣ ከየትኛውም ሰይጣን ይበልጣል። ስለዚህ አንድ ሰውን ከእግዚአብሔር እጅ ማንም ሊያስወጣው አይችልም።

ዮሐንስ 10፡30 እኔና አብ አንድ ነን።

ኢየሱስ በውጭ የሚታየው ሰው ነው። እግዚአብሔር ደግሞ በውስጡ ያለው መንፈስ ነው።

በኢየሱስ ውስጥ ፍጥረታዊውን እና ከተፈጥሮ በላይ የሆነውን መንፈስ በአንድነት እናገኛለን።

ቆላስይስ 2፡9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤

ኢየሱስ እና እግዚአብሔር አንድ ናቸው። እግዚአብሔር ሰው ሆነና አማኑኤል ተባለ።

ዮሐንስ 10፡31 አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ።

መሲሃቸው በስጋ ተገልጦ ፊትለፊታቸው ሲያዩት ለአይሁድ ሕዝብ በጣም ከበዳቸው። ቢገድሉት እንደሚሻላቸው አሰቡ። ከገደሉት በኋላ በማሕበረሰቡ ውስጥ የከበረ ሥፍራቸውን ይዘው መቀጠል ይችላሉ። የሐይማኖት መሪዎች ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ፊት ለፊት ሲጋፈጡ ምርጫቸው እውነትን አለመቀበል ነው።

ዮሐንስ 10፡32 ኢየሱስ፦ ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው።

በኢየሱስ ውስጥ የነበረው የእግዚአብሔር መንፈስ ብዙ አስደናቂ ተዓምራትን አድርጓል። በጣም ብዙ በበሽታ የሚሰቃዩ ሰዎች በተሰበሰቡበትና ብዙዎች በክፉ መናፍስት እስራት በሚሰቃዩበት ቦታ ብዙ የፈውስ ተዓምራት ተደርገዋል። ኢየሱስ ከሰራቸው ታላላቅ ተዓምራት ስለየትኛው ነው የሞት ፍርድ ሊፈረድበት የሚገባው?

ዮሐንስ 10፡33 አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት።

አሁን አይሁዳውያን አጋንንታዊ ጥላቻቸውን ገለጡ። መሲሁ እግዚአብሔር በሰው መልክ ሲገለጥ ነው። ነገር ግን ማንኛውም እራሱን እግዚአብሔር ብሎ የሚጠራ ሰው ሁሉ ስለ ተሳዳቢነቱ በእነርሱ ዘንድ ይገደላል። ስለዚህ እነርሱ ደግሞ መሲሃቸውን ሊገድሉ ነው።

ዮሐንስ 10፡34 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?

መዝሙር 82፡6

ኢሳይያስ 41፡23 አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ እንደነግጥም ዘንድ በአንድነትም እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ።

ስለ ወደፊቱ ትንቢት ይናገሩ የነበሩ ነብያት አማልክት ይባሉ ነበር።

ዮሐንስ 10፡35 መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥

ኢየሱስ ከየትኛውም ነብይ ይበልጥ ቅዱስ የሆነ ሕይወት ኖሯል። የትኛውም ነብይ ያላደረጋቸውን ተዓምራት አድርጓል፤ ለምሳሌ በውሃ ላይ ተራምዷል፤ አንድ ልጅ የያዘውን ምሳ ተቀብሎ 5,000 ሰዎችን አብልቶበታል።

ዮሐንስ 10፡36 የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?

ኢየሱስ ሰው እንደመሆኑ እነዚያን ተዓምራት ሊያደርግ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ውስጥ በመኖሩ ነው።

ዮሐንስ 10፡37 እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤

ኢየሱስ ከተፈጥሮ ኃይል በላይ የሆኑትን የእግዚአብሔር ሥራዎች መስራት ባይችል ኖሮ በእርሱ ማመን ባላስፈለጋቸው ነበር።

ዮሐንስ 10፡38 ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።

ኢየሱስን ባይወዱትም እንኳ እንዲሁ በሕሊናቸው ከእግዚአብሔር በቀር እነዚያን ተዓምራት ማንም ሊያደርግ እንደማይችል ማወቅ ነበረባቸው።

የእግዚአብሔር መንፈስ በኢየሱስ ውስጥ ነበረ። ኢየሱስ ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ነበረ ምክንያቱም ስለ መሲሁ የሚናገሩ ቃሎችን በሙሉ ፈጽሟል።

ዮሐንስ 10፡39 እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ።

በጣም በተበሳጩ ጊዜ ሊይዙት ፈለጉ። ነገር ግን ከፍ ካለ መንፈሳዊ ቀጠና ከመጣ ሰው ጋር እየተጣሉ መሆናቸውን አላወቁም። እነርሱ በማያውቋቸው መንፈሳዊ ቀጠናዎች ውስጥ መመላለስ ይችላል።

ወደ ከፍተኛ መንፈሳዊ ቀጠና ውስጥ ገብቶ በመሰወር ኢየሱሰ አሁንም በውስጡ የነበረውን የእግዚአብሔር ኃይል አሳየ።

 

ዮሐንስ 10፡40 ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ።

ያም ቦታ በዮርዳኖስ ወንዝ ምሥራቅ ያለው ቤተራባ ነው።

ዮሐንስ 1፡28 ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ።

ዮርዳኖስ ወደ ሙት ባሕር ውስጥ የሚፈስስ ወንዝ ነው። ኢየሱስ ለሞት እየተዘጋጀ ነበር። በአገልግሎቱ መጨረሻ ኢየሱስ መጀመሪያ ወደተጠመቀበት ቦታ ተመልሶ መጣ።

እርሱ አልፋ እና ኦሜጋ፣ መጀመሪያና መጨረሻ ነው።

ከዚህ በታች ያለው ካርታ የዮርዳኖስ ወንዝ የገሊላ ባሕርን አቋርጦ ወደ ሙት ባሕር ሲገባ ያሳያል።

 

 

ቤተራባ የዮርዳኖስ ወንዝ “መሻገሪያ ቦታ” ነው። ይህ ቦታ ኢያሱ ወደ ተስፋይቱ ምድር በገባ ጊዜ ዮርዳኖስን የተሻገረበት ቦታ ነው።

መጥምቁ ዮሐንስ እዚህ ቦታ ያጠመቀበት ምክንያት መሲሁ በመጣ ጊዜ የብሉይ ኪዳን ሕግ ወደ አዲስ ኪዳን ጸጋ “እንደሚሻገር” ስለገባው ነው።

ሙሴ ሕጉን ነው የሚወክለው። ሙሴ አገልግሎቱን ወደ ኢያሱ አስተላለፈ፤ ኢያሱ መንፈስ ቅዱስን ነው የሚወክለው።

ኢየሱስ ወደዚህ ቦታ የተመለሰው በቀራንዮ መስቀል ከአይሁድ ወደ አሕዛብ የሚሻገርበት ጊዜ ስለደረሰ ነው። ይህም የሚሆነው አይሁድ ለመጨረሻ ጊዜ መሲሃቸውን ኢየሱስን አንቀበልህም ብለው ስለሚገፉ ነው።

ዮሐንስ 10፡41 ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ።

ኢየሱስ ያደረጋቸው ተዓምራት እርሱ መሲሁ ስለመሆኑ ሰዎችን ሁሉ ሊያሳምኑ ይገባ ነበር።

ነገር ግን በዮሐንስ ምስክርነት ምክንያት ያመኑ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ፤ ዮሐንስ እራሱ ግን አንዳችም ተዓምር አላደረገም። ተዓምር በሌለበት ማመን መቻል የእውነተኛ እምነት መመዘኛ ነው።

ዮሐንስ 20፡29 ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው።

ተዓምራት ያዩት የአይሁድ ሐይማኖት መሪዎች ግን አላመኑም፤ ስለዚህ እርሱ የሐይማኖት መሪዎች የሚወድቁበትን የአለማመን ጉድጓድ ጥልቀት ያሳያሉ።

ዮሐንስ 10፡42 በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

ኢየሱስ በቤተራባ አንዳችም ተዓምራት እንዳደረገ አልተጻፈም። ነገር ግን በዚያ ስፍራ ብዙ ሰዎች በእርሱ አምነዋል። በኢየሩሳሌም ውስጥ በሐይማኖት መሪዎች ከተበከለው አየር ርቀው የሚኖሩት የቤተራባ አይሁዶች በኢየሱስ ለማመን አልከበዳቸውም።

ይህም የሐይማኖት መሪዎቻቸው ማሰናከያ ዓለት ከመሆን በቀር ምንም እንደማይጠቅሙዋቸው ያመለክታል።

ታሪክ ደግሞ እራሱን ይደግማል።

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23