የቤተክርስቲያን ዘመናት - ሎዶቅያ ክፍል 4 - ራዕይ 3፡14-22፤ እግዚአብሔር የማያውቃት ቤተክርስቲያን
We update studies as the Lord Jesus leads us. You can find the latest update of this study at ChurchAges.net
ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን (በእንግሊዝኛ፡ “ለሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን መልአክ” ይላል) መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
ሎዶቅያውያን የራሳቸውን የቤተክርስቲያን አስተምሕሮ እና ሥርዓት በራሳቸው ያበጃሉ። የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ከእርሷ በፊት እንዳሉት አምስት የቤተክርስቲያን ዘመናት አይደለችም፤ ምክንያቱም የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን በሎዶቅያ ከተማ ውስጥ ያለች ቤተክርስቲያን አይደለችም። ይህ የቤተክርስቲያን ዘመን በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን መሪዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አስተሳሰብ መሰረት የሚመራ የቤተክርስቲያን ዘመን ነው።
“የኤፌሶን ቤተክርስቲያን” የእውነተኛ ክርስትና ምሳሌ ነበረች፤ እርሷም እንደ ሞዴል ሆና ሌሎች የቤተክርስቲያን ዘመናት ሊከተሏት ይገባ ነበር። እምነቷም በአዲስ ኪዳን ሐዋርያት የተከተሉት እምነት ነበር።
ራዕይ 2፡1 በኤፌሶን ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
የመጨረሻው ዘመን የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ወደ መጀመሪያዋ ዘመን የኤፌሶን ቤተክርስቲያን እምነት እንድትመለስ ይጠበቅባታል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ማለትም በሎዶቅያ ከተማ ያለች ቤተክርስቲያን እንድትኖር አላሰበም።
ነገር ግን በመሃል በነበሩት አምስት የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ሁሉ ሰዎች በሰው ሃሳብ ላይ በመደገፋቸው የተነሳ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ሊስቱ ችለዋል። ቤተክርስቲያኖቹ የሐዋርያትን ምሳሌነት ትተው ሄዱ፤ እያንዳንዱ ዘመንም የገዛ ራሱን መንገድ ተከተለ። በእያንዳንዱ ዘመን መሪዎች የየራሳቸውን የተለየ ስሕተት ይዘው መጡ፤ ይህም ስሕተታቸው የተፈጠረው መሪዎች በየራሳቸው ዘመን በታሪክ ላጋጠማቸው ችግር በየግላቸው ከሰጡት የተሳሳተ ምላሽ በመነሳት ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ዘመን በተለያየ መንገድ በከፊል መጽሐፍ ቅዱሳዊ በከፊል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን የማይከተል ነበር። ከዚህም የተነሳ ከመጀመሪያዋ ዘመን ቤተክርስቲያን ተከትለው የመጡት አምስት የቤተክርስቲያን ዘመናት በሙሉ ለመጨረሻዋ ቤተክርስቲያን ጥሩ ምሳሌ መሆን አልቻሉም።
ራዕይ 2፡8 በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ።
ራእይ 2፡12 በጴርጋሞንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
በጴርጋሞን ወዳለው፤ በትያጥሮን ወዳለው እየተባለ ነው የተጻፈው።
ራዕይ 3፡7 በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
የመጨረሻዋ ዘመን ቤተክርስቲያን ግን የምትጠራው “ሎዶቅያ ውስጥ ያለችው ቤተክርስቲያን” ተብላ አይደለም።
የመጨረሻዋ ቤተክርስቲያን ወደ ኤፌሶን ቤተክርስቲያን ማለትም ወደ መጀመሪያዋ ዘመን ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ እምነት መመለስ አለባት። የመጨረሻዋ ቤተክርስቲያን የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ተሃድሶ ነው መሆን ያለባት።
1965 የቤተክርስቲየን ዘመን መጽሐፍ - የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ዘመን
እግዚአብሔር እውነተኛነቱን የመሰከረለት ነብይ ይላካል። እግዚአብሔር ሁለት ሺ ዓመታት ካፉ በኋላ ነብይ ሊልክ ነው። ይህም እግዚአብሔር የሚልከው ነብይ ልክ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ እና እንደ ኤልያስ ከድርጅቶች፣ ከዘመናዊ ትምሕርት፣ ከሐይማኖትም እጅግ የራቀ ሰው ስለሚሆን ከእግዚአብሔር ብቻ ይሰማል፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ብሎ ያውጃል ወይም እግዚአብሔርን ብቻ ወክሎ ይናገራል። የእግዚአብሔር አፍ ይሆናል፤ ደግሞም በሚልክያስ 4፡6 እንደተጻፈው የልጆችን ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል። የመጨረሻውን ዘመን ምርጦች ይመልሳቸዋል እነርሱም እውነተኛነቱ የተመሰከረለት ነብይ ልክ ጳውሎስ እንዳደረገው ትክክለኛውን እውነት እውነት ሲናገር ይሰማሉ። እውነትን እንደ እነርሱ በትክክለኛው ቦታ መልሶ ያስቀምጣታል። እነዚያም ምርጦች ከእርሱ ጋር በዚያን እለት ሆነው በእውነት ጌታን የሚገልጡ ይሆናሉ፤ አካሉ በመሆን ድምጹ በመሆን የእርሱን ሥራ ይሰራሉ።
ነገር ግን የሰባተኛውን ዘመን መልእክተኛ ዊልያም ብራንሐምን በመስማት ወደ አዲስ ኪዳናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እምነት በመመለስ ፈንታ የመጨረሻው ዘመን ቤተክርስቲያን አቅጣጫዋ ጠፍቶባታል ትንከራተታለች። የዳንኤል ራዕይ ውስጥ አሕዛብን የሚወክለው ሐውልት እግሮቹ ወደ አሥር ጣቶች እንደተከፋፈሉት ሆናለች። ይህም ሮም በሜሴጅ ቤተክርስቲያኖች ላይ ያደረገችው ተጽእኖ ነው እነርሱን እርስ በርሳቸው የሚፎካከሩ ብዙ ቡድኖች ሆነው እንዲከፋፈሉ ያደረጋቸው።
ወይ ወደ መጀመሪያይቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ወዳላት እውነተኛ ቤተክርስቲያን እምነት እንመለሳለን አለዚያ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ያፈነገጡ እምነቶችና ልምምዶችን የተከተለችዋ የጋለሞቶች እናት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የወለደቻቸው ጋለሞታ ልጆች ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖችን እንከተላለን።
ምርጫው የናንተ ነው።
ስለዚህ ይህች የመጨረሻው ዘመን ቤተክርስቲየን የተመሰረተችው በሎዶቅያውያን ሰዎች አስተሳሰብና አመለካከት ላይ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አይደለም።
ሎዶቅያውያን የራሳቸውን የቤተክርስቲያን መመሪያ፣ የራሳቸውን አስተምሕሮ እና የራሳቸውን በሙዚቃ የታጀበ የአምልኮ ስርዓት አበጅተዋል። ዛሬ ቤተክርስቲያን ውስጥ ድራም እና የኤልክትሪክ ኪይቦርድ ገብተዋል፤ ነገር ግን ድራም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጭራሽም አልተጠቀሰም።
በዘመናችን ሰው ሰራሽ ሐይማኖት ከፍታ ላይ ወጥቷል። በጣም ጠቢብ የሆንን መስሎናል።
ነገር ግን ስንት አይነት የተለያዩ “ሜሴጅ” ቤተክርስቲያኖች እንዳሉ ልብ በሉ፤ እያንዳንዱ በእስተምሕሮው ከሌላው ይለያል ነገር ግን እያንዳንዱ እኔ ትክክል ነኝ ይላል። ሁሉም ልክ ሊሆኑ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።
በጣም የሚያስደነግጠው ነገር ደግሞ ቃሉን ስናጠና እግዚአብሔር ይህን የመጨረሻውን የሎዶቅያ ዘመን እግዚአብሔር እንደሚቃወመው እና ከሃዲ ብሎ እንደሚጠራ እናገኛለን።
ቢሆንም ግን የተስፋ ጭላንጭል አለ።
እግዚአብሔር በታላቁ መከራ ጌዜ ከሚመጣው ታላቅ ቁጣ የዳኑ ሰዎች እንዲያመልጡ እያዘጋጃቸው ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሰባተኛውን የቤተክርስቲያን መልአክ (መልእክተኛ) አይነቅፈውም።
ይህ መልእክተኛ ግን ስምንት ቢሊዮን ሰዎች ባሉበት ዓለም ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ነው።
ይህም የኖኅን ዘመን ያስታውሰናል፤ በዚያ ዘመን ከዓለም ሁሉ ሕዝብ መካከል ስምንት ሰዎች ብቻ ያሉበት የኖኅ ቤተሰብ ብቻ ነበር ከጥፋት ውሃ የዳነው።
ሉቃስ 17፡26 በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።
የኖኅ ቤተሰብ ታላቁ መከራ ከመምጣቱ በፊት የሚድኑትን ሰነፎቹን ቆነጃጅት ይወክላሉ፤ ነገር ግን ታላቁ መከራ በመጣ ጊዜ በቡድናዊ እና ቤተክርስቲያናዊ ልምምዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይሞታሉ። ቢሆንም ከሲኦል ይድናሉ፤ በስተመጨረሻም በፍርድ ቀንዳ መንግስተ ሰማያት ይገባሉ።
ግን ይህ ቁጥር ማለትም ስምንት ራሱ በጣም ትልቅ ቁጥር ነው።
አንድ ሰው ማለትም ሄኖክ ብቻ ነው ወደ ሰማይ በመነጠቅ ከጥፋት ውሃ ያመለጠው።
ዘፍጥረት 5፡24 ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና።
ይህ ለእኛ ማስጠንቀቂያ ነው።
ጌታን በአይር ላይ ለመገናኘት መነጠቅ ከኢየሱስ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በግላችን የምናደርገው ልምምድ ነው።
መነጠቅ በቤተክርስቲያን፣ በቤተሰብ ወይም በቤተክርስቲያንና በቡድን የምናደርገው ልምምድ አይደለም።
ሄኖክ አንድ የተቀባ ሰውን እየተከተለ አልነበረም። ሄኖክ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ቅርበት ሚስቱን፣ ልጆቹን፣ ወይም ጓደኞቹን ከእርሱ ጋር አብረው እንዲነጠቁ አላደረገም።
በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ዊልያም ብራንሐም አስደናቂ የሆነ መለኮታዊ ኃይል የተገለጠበት አገልግሎት አገልግሏል። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ምስጢራት መግለጥ በጀመረ ጊዜ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይቃወሙታል ወይ ደግሞ ተከታዮቹ የእርሱን ንግግሮች ወስደው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትርጉሞችን ይሰጡዋቸዋል።
ነገር ግን በዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በጣለው ዘመናችን ውስጥ ብቸኛው ያለ ነቀፋ የኖረ ሰው ወንድም ብራንሐም ነው።
በሎዶቅያ ውስጥ ለምንኖር ለሌሎቻችን እግዚአብሔር ጠንከር ያለ ነቀፋ ነው የላከብን። መንፈስ ለሎዶቅያ ዘመን አንድም የሙገሳ ቃል አልተናገረም።
ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦
የዚህን የመጨረሻ ዘመን ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር የሚነቅፍባት ትልቅ ነቀፋ ቤተክርስቲያኒቱ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲየን አለመሆኗን ነው። የራሳችንን የሎዶቅያውያውን ቤተክርስቲያን መስርተናል። የዘመናችን ቤተክርስቲያን “የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን” ናት። ቤተክርስቲያኒቱ የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን እንጂ “የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን” አይደለችም።
ሎዶቅያ ማለት የሕዝቡ መብት ማለት ነው። እኛም ደግሞ ስለምናደርገውም ሆነ ለጥቅሶች ስለምንሰጠው ትርጓሜ መብታችን ካልተከበረልን ብለን እንሟገታለን። በአለባበሳችን እና ለእግዚአብሔር በምናቀርበው አምልኮ የራሳችንን መንገድ ካልተከተልን እንላለን። የግል መረዳታችን ትክክለኛ ነው ለማለት ብለን እውነታን ወደምንፈልገው መንገድ እንጠመዝዛለን።
ክሪስማስ ዲሴምበር 25 ላይ እንዲውል ከፈለግን ዲሴምበር 25 ላይ እናደርገወለን። ይህንንም የምናደርገው መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን ልደት ስለማክበር አናዳችም አለመናገሩን እያወቅን ነው። ደግሞ “ክሪስማስ” የካቶሊኮች “ክራይስትስ ማስ” ነው። ዲሴምበር 25 ክርስቲያኖችን ይገድል በነበረው ሮማዊ ንጉሥ በኦውሬልያን በ274 ዓ.ም የፀሐይ አምላክን ልደት ለማክበር የተቆረጠ ቀን ቢሆንም እንኳ ልናከብረው እንፈልጋለን።
ይህ ሁሉ ልምምድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስላለመሆኑ ሎዶቅያ ውስጥ ማንም ግድ የሚለው የለም። ልጆቻችን ክሪስማስ ደስ ይላቸዋል፤ እኛ ደግሞ ልጆቻችንን ለማስደሰት ብለን ከመጽሐፍ ቅዱስ መርህ ስንወጣ ምንም አይመስለንም።
ክሪስማስን በማክበራችን በጣም ሐይማኖተኞች እና መንፈሳውያን ልንመስል እንችላለን ግን በእውነቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እጅግ ርቀን እየሄድን ነው።
ሰብዓ ሰገል ሲመጡ ወደ ቤት ውስጥ እንጂ ወደ በረት እንዳልገቡ፤ ደግሞም የሁለት ዓመት ልጅ እንጂ ጡት የሚጠባ ሕጻን እንዳላገኙ እንኳ ልብ አንልም። የሰብዓ ሰገል ስጦታ የመጣው በግርግም ውስጥ ተኝቶ ለነበረው ለሕጻኑ ኢየሱስ እንደተሰጠ ማመን እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስን በታማኝነት ለመከተል ምንም ፍላጎት የለንም።
ማቴዎስ 2፡11 ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።
ኤርምያስ የአሕዛብን “የክሪስማስ ዛፍ” እንዳንከተል ቢነግረንም እንኳ አልሰማ ብለናል።
ኤርምያስ 10፡2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሕዛብን መንገድ አትማሩ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፤ አሕዛብ ይፈሩታልና።
3 የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል።
4 በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል።
የአሕዛብ ልማድ ላይ የኢየሱስን ስም በመለጠፋችን እግዚአብሔርን የምናስደስተው ይመስለናል። በእውነቱ ግን እግዚአብሔር እንዲጸየፈን እያደረግን ነው።
እግዚአብሔርን የኢየሱስን ልደት በየዓመቱ በአሥራ ሁለተኛው ወር 25ኛ ቀን ላይ እንድናከብረለት ይፈልጋልን? የክሪስማስ ወቅት የተባለውን ጊዜ እግዚአብሔር ይወደዋልን?
ገላትያ 4፡9 አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን?
10 ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ።
ገላትያ 4፡11 ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ።
ዓመታዊ “የክርስቲያኖች በዓል” የሚባለው አይነት ልማድ ጳውሎስ በነዚህ ክርስቲያኖች ላይ በከንቱ ደክሜ ይሆን ብሎ እንዲጨነቅ አድርጎታል። ዓመታዊ በዓል የማክበር ፍላጎት ስላላቸው ሰዎች ጳውሎስ ጊዜዬን በከንቱ አባከኑ ብሎ ካሰበ እንዲህ አይነቱ ልማድ በእግዚአብሔር ፊት ደግሞ ምን ያህል አጸያፊ እንደሆነ አስቡ። ፀሐይን የሚያመልኩበትን የአሕዛብ አምልኮ ከ274 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሁም የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ይህንን አምልኮ ክራይስትስ ማስ ብላ ካጸደቀችበት ከ360 ዓ.ም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ እግዚአብሔር ታግሷል።
ሁለት ነፍሰ ገዳዮች እነርሱም ፈርኦን እና ሔሮድስ ብቻ ናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልደታቸውን እንዳከበሩ የተጻፈላቸው። እነርሱ ደግሞ እንደ ጥሩ ምሳሌ የምንከተላቸው ሰዎች አይደሉም።
ሉቃስ 2፡8 በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ።
ዲሴምበር 25 የክረምት አጋማሽ ወቅት ነው። ይህም ወቅት ፓለስታይን ውስጥ እንደ በረዶ የሚቀዘቅዝ ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት አንድም እረኛ በሌሊት በጎቹን ይዞ ከቤት አይወጣም።
ስለዚህ ኢየሱስ ዲሴምበር 25 ነው የተወለደው ማለት መጽሐፍ ቅዱስን ፊት ለፊት መቃወም ነው።
ይህን ያህል ነው መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ቸልተኛ ለዘብተኛ የሆንነው።
የቤተክርስቲያናችንን የክሪስማስ ልማድ ከመውደዳችን የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን መቃወማችን ምንም ያህል አይቆረቁረንም።
1965 የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ - የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ዘመን
ከሌላው ዘመን ሰዎች ይልቅ ብዙ መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችሁ አለ፤ ነገር ግን ቃሉን አንብባችሁ በመታዘዝ ፈንታ እንደፈለጋችሁ የሚመቻችሁን ጥቅስ መዛችሁ እየወሰዳችሁ የማይመቻችሁን ደግሞ ቸል ብላችሁ እያለፋችሁ ነው። በቃሉ የመኖር ፍላጎት ሳይሆን የመከራከር ፍላጎት ነው ያላችሁ። ትኩስ ወይ በራድ ብትሆኑ ይሻለኝ ነበር። በራድ ብትሆኑና ቃሉን ሙሉ በሙሉ ብትጥሉት ይህን ልታገስ እችላለው። ትኩስ ብትሆኑና እውነትን ለማወቀቅ እንዲሁም ልትኖሩበት ብትጓጉ አደንቃችኋለው። ነገር ግን ቃሌን ወስዳችሁ ሳታከብሩት ስትቀሩ፤ እኔም ደግሞ ላከብራችሁ አልችልም። ከአፌ እተፋችኋለው ምክንያቱም ታንገሸግሹኛላችሁ።
53-0403 የሃጥያት ክፋትና እኛን ከሃጥያት ለማንጻት የተከፈለው ክፍያ
ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄድ ሰው በሙሉ…
ዛሬ ስለ ትልልቆቹ ካድራሎች ሳስብ ነበር፤ ከነ ደወሎቻቸውና ከነቃጭሎቻቸው፤ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱና ዝግጅት ሲያደርጉ ሴቶችም ለኢስተር (ፋሲካ) ኮፍያ ሲገዙ እና የመሳሰሉ ነገሮችን ሲያደርጉ። ይህ ሁሉ ከየት የመጣ ነው? ለመሆኑ የጥንቸል እንቁላል ከትንሳኤ ጋር ምን ያገናኘዋል? የገና ወይም የክሪስማስ ዛፍስ ከኢየሱስ መወለድ ጋር ምን ያገናኘዋል? ወዳጆች ሆይ ይህ ሁሉ የአሕዛብ ልማድ ነው። የሆነ ቦታ ከመንገድ ስተናል። ነገር ግን ዳግመኛ የተወለደ ሰው በውስጡ እውነትን የሚገልጥለት ሕይወት ስላለው ይህ ሁሉ ልማድ ስሕተት መሆኑን ያስረዳዋል።
56-0311A እውነተኛው የወይን ግንድና ሐሰተኞቹ ግንዶች
ዓለም ራሷ ክሪስማስ፣ እና ፋሲካ ታከብራለች፤ እነዚህም ቀኖች ለዓለም ታላቅ የንግድ ቀኖች ናቸው። በእነዚህ ቀናት እግዚአብሔርን የሚያስብም የለም። ኢስተር ወይም ፋሲካ ከጥንቸል ወይም ከዶሮ ወይም ከቢጫ ዳክዬዎች ጋር ምን ተዛማጅነት አለው? ከአሕዛቦቹ ባልተናነሰ አሕዛብ ሆነናል። ነገር ግን ይህንን ሁሉ እንደ ቀላል ነገር ትታገሱታላችሁ። እንዲ አይነት ነገሮችን እንድንጠላ እግዚአብሔር ይርዳን። የእግዚአብሔር ብርሃን በእነዚህ ነገሮች ላይ ሲያበራ እና ሲያጋልጣቸው ባየን ጊዜ በብርሃን እንመላለስ።
60-1207 የጴርጋሞን ቤተክርስቲያን ዘመን
እንግዲህ በዚያ ጊዜ … ታላቅ ግብዣ አዘጋጅተው ኒቆላውያንን ጠሩዋቸው። አይገርምም? “የበለዓም ትምሕርት በውስጣችሁ አለ።” አያችሁ ለጴርጋሞን ምን እንዳላቸው። ከዚያም እነዚህ ሰዎች እንዲህ ብለው አሰቡ፤ እነዚህ ኒቆላውያን እንዲህ ብለው አሰቡ፤ “መልካም፤ በጣም ጥሩ ነው። ይህ ታላቅ በዓልና ድግስ ዓመታዊ አይደለምን? አዎን።” ከዚያም ለሊቀ ጳጳሱ፤ ወይም ያን ጊዜ ማንም ተብሎ ቢጠራ ግድ የለኝም፤ ሊቀጳጳሱ ከተጋበዘ በኋላ ቋሚ ነገር አድርገውት ቀሩ፤ በዚያም ከግልሙትናቸውና ከመዳራታቸው ብዛት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተመሰረተች። እያንዳንዱ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያንና ድርጅትም ምንጩ ከካቶሊክ ነው። እግዚአብሔር አንድም ድርጅት የለውም። እግዚአብሔር የድርጅት ስም ያስጠላዋል። መጽሐፍ ቅዱስም ይህንኑ ይመሰክርልናል።
ይህንንም ሲያደርጉ ምን ተፈጠረ? ከዚያም ምን አሉ መሰላችሁ … መንፈሳዊነት ሊያላብሱት ሲሞክሩ የእግዚአብሔር ልጅ (የጌታ ኢየሱስን) ልደት ሚያዝያ ወር ውስጥ የነበረውን ወደ ኋላ መልሰው ታሕሳስ 25 አደረጉት (ኢየሱስ የተወለደው ሚያዝያ ውስጥ መሆኑን ብዙ ምሑራን ማንኛውም መንፈሳዊ መረዳት ያለው ሰው ሁሉ የሚያምኑበት እና በተፈጥሮም ሁሉም ነገር የበግ ጠቦቶችም ጭምር የሚወለዱበት ወቅት መሆኑን ብዙዎች ያውቃሉ)። ይህን ሁሉ እያወቁ ግን ክሪስማስን እስካሁን ያመልካሉ፤ አሁን ደግሞ ብዞ ሳንታ ክሎዝ ሆኗል። ከዚህ በኋላ ደግሞ ምን ይጨመርበት ይሆን? ብዙ የአሕዛብ በዓሎች እየተጨመሩበት ይሄዳሉ። አያችሁ አይደል የበለዓም ትምሕርት በመካከላችሁ እንዳለ። ይኸውላችሁ እንግዲህ። (ኦ ጌታ ሆይ እባክህ ግለጥላቸው።) አያችሁ? የልደት ቀኑ ከሚያዝያ…
የታሪክ ምሑሩ እንዲህ ይላል “ማስረጃዎች በሙሉ የሚጠቁሙት ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ በብዛት በሚወለዱበት ወር ኢየሱስ በሚያዝያ ወር መወለዱን ነው።” እነርሱ ግን ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን ዲሴምበት 25 አደረጉት፤ የአሕዛብ አምላክ ከተወለደበት ቀን አምስት ቀናት አልፎ፤ ይህንንም ያደረጉት የአከባበር ሥርዓቶቻቸውን አንድ ላይ ለማድረግ ብለው ነው፤ አረማዊ ልማድና ክርስትናን አንድ ለማድረግ። የካቶሊክ እምነት ማለት ብዙ የአሕዛብ ልማዶችና ጥቂት ክርስቲያናዊ ስርዓቶች ሲጣመሩ የሚፈጥሩት ውሕደት ነው። ይህ እውነት ነው። ይህ ልማድ የሚከተሉ ፕሮቴስታንቶችም የጋለሞታይቱ እናት ካቶሊክ ጋለሞታ ልጆች ናቸው። ይህ ትክክል ነው።
ክፋትንና እርኩሰትን የእውነት የምንቃወም እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን።
61-1217 ክርስትና እና ጣኦት አምልኮ
ክሪስማስን ማክበር የአሕዛብ ልማድ የሰይጣን አምልኮ ነው።
64-0719 የኢዮቤልዩ በዓል
በፊት የነበረው የሮማ ግዛት አሁንም አለ፤ አሁን ግን የሚያስተዳድሩት እነማን ናቸው? የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካሕናት ናቸው። የአሕዛብ መንግስት የነበረችዋ ሮም አሁን የካቶሊክ ሮም የጳጳሳቱ መንግሥት ሆናለች፤ መተዳደሪያዋም ክርስቲያናዊ ወጎችና ልማዶች ሆነዋል። የትኞቹ ክርስቲያናዊ ልማዶች ብንል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ልማዶች በሙሉ፤ ሴቶችን ማምለክ እና የመሳሰሉ ሌሎችም ልማዶች እና ክርስቲያናዊ የበዓል ቀኖች እና ሌላም ሌላም በዓሎች። በእነዚህ ልማዶች ስለታሰሩ ነጻ ሆነው ሊንቀሳቀሱ አይችሉም ምክንያቱም እነዚህ ልማዶች ሁሉ ከክርስቲያናዊ መርሆች ተቃራኒ ናቸው። እስካሁንም በመካከላቸው የሚሰራው የአመጸኝነት መንፈስ ነው። ይህም መንፈስ በሕዝቅኤል ትንቢት መሰረት ወደ ዓለም ሁሉ ተሰራጭቷል።
ክሪስማስ እና ሥላሴ ሁለቱ ታላላቅ የሮማ ካቶሊክ አስተሳሰቦች ሲሆኑ፤ እነዚህም ሁለት ሃሳቦች የተለያዩ የክርስትና አይነቶችን ሰብስበው ወደ አንድነት የማምጣት ኃይል አላቸው።
ባልታወቀ መንገድ ሳንታ ክሎዝ ከክሪስማስ ጋር ተቆራኝቶ ቀረ።
ሰይጣን እንዴት በቀላሉ እንዳሳተነተ ተመልከቱ።
ከዚህም የተነሳ ዛሬ 45¸000 የተለያዩ ቤተክርስቲያኖች አሉን። ይህ የሰዎች መብት ያለ ቅጥ የገነነበት መንፈሳዊ አረንቋ ነው። እግዚአብሔርም እያንዳንዱን ቤተክርስቲያን ከአፉ ይተፋዋል፤ አፉ ማለት ቃሉ ነው።
“አሜን” የሚለው ቃል ሁል ጊዜ መጨረሻ ላይ ነው የሚመጣው። ትርጉሙም “ይሁን” ማለት ነው። አሁን የእኛ ዘመን የመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ነው።
የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛና የታመነ ነው። ቃሉ ለዘላለም አይለወጥም። እኛ ግን ቃሉን ፈጽመን መከተል ብንተው ለቃሉ ታማኝ አይደለንም ማለት ነው።
ራዕይ 17፡14 እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።
በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ከኢየሱስ ጋር የሚሆኑት ሰዎች በእርሱ የተጠሩ መሆን አለባቸው፤ ነገር ግን የተመረጡ ይሆኑ ዘንድ ለጥሪው ታማኝ ሆነው መቆየት አለባቸው።
ለመዳን በእግዚአብሔር መጠራት ከሲኦል ያድነናል።
ግን ደግሞ ከታላቁ መከራ መዳን ከፈለግን የኢየሱስ ሙሽራ ሆነን መመረጥ አለብን።
እርሱ ቃሉ ነው። ስለዚህ ለቃሉ ታማኝ መሆን አለብን።
ቤተክርስቲያን የምትለውን ሳይሆን ቃሉ የሚለውን መምረጥ አለብን።
የመጨረሻው የሕዝብ መውጣት የሚሆነው ከቤተክርስቲያን መውጣትና እንደ ግለሰብ የተገለጠውን መጽሐፍ ቅዱስን መከተል ነው።
ማቴዎስ 20፡16 እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤
በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያንና በመጨረሻዋ ቤተክርስቲያን መካከል ምንም ልዩነት መኖር የለበትም። ስለዚህ ወደ ጥንቷ በሐዋርያት ዘመን ወደነበረችዋ ቤተክርስቲያን አዲስ ኪዳናዊ እምነት መመለስ አለብን።
ማቴዎስ 20፡16 እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።
ብዙዎች ወደ መጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን እምነት የሚመልሰንን የወንድም ብራንሐም መልእክት ያዳምጣሉ። ነገር ግን እምነታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ የሚፈትሹ እና ታማኝ የሚሆኑ ግን ጥቂቶች ናቸው።
ስለዚህ እነዚያ ጥቂቶች ብቻ ናቸው የክርስቶስ ሙሽራ ለመሆን የሚመረጡት።
ማቴዎስ 7፡14 ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
መንገዱ ጠባብ ነው።
ከወንድም ብራንሐም ተወስዶ የተጠቀሰ ማንኛውም ጥቅስ ተቀብላችሁ ከማመናችሁ በፊት መጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ልትመረምሩት ይገባል።
ይህና አይነቱን የእውነት መንገድ የሚያገኙ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው።
ብዙዎች የተመረጡ ጥቅሶችን ወስደው ለግል አመለካከታቸው እንሚያመች አድርገው መተርጎም ይቀናቸዋል።
አዳም የመጀመሪያው ፍጹም ሰው ነበረ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ቃል በማፈንገጥ ምክንያት ወደቀ። ሚስቱን አዳመጠ።
ሴት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነች። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረንን መስማት ትተን ቤተክርስቲያን የምትለንን እንሰማለን። ስለዚህ እኛም በውድቀት ውስጥ ነን።
ኢየሱስ የመጀመሪያው ፍጹም ሰው ነበረ፤ ደግሞም ፍጹም ሆኖ የቆየው እርሱ ብቻ ነው። ከዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ተጠምቆ ሲወጣ መንፈስ ቅዱስ እንደ እርግብ መጥቶ በእርሱ ላይ አረፈበት። የኢየሱስ የዘወትር ስኬት ሚስጥር ሁልጊዜ ለመንፈስ ቅዱስ እና ለእግዚአብሔር ቃል መገዛቱ ነው።
ዮሐንስ 1፡32 ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ።
33 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።
መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ላይ እንደ ቅባት ሆኖ አረፈበት። መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ውስጥ አልገባም ምክንያቱም ኢየሱስ ሁልጊዜም በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነበረ።
እርሱ ሁል ጊዜም ለመለኮታዊው እርግብ የሚታዘዝ የእግዚአብሔር በግ ነበረ። የኢየሱስ በሰብዓዊነቱ ሁልጊዜም በውስጡ ለሚኖረው መለኮት በመገዛት ነው የተመላለሰው።
ቆላስይስ 2፡9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤
ይህ የእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ ነበረ።
እርሱም እግዚአብሔር ዳግመኛ የተወለዱ ፍጥረቶቹን በሙሉ የሚፈጥርበት የመጀመሪያው ፍጹም ሰው ነው። ሁላችንም ኢየሱስን እንድንመስለው ተጠርተናል።
ንሰሐ መግባትና በኢየሱስ ክርቶስ ስም መጠመቅ አለብን። ከውሃ ውስጥ እንወጣና ከዚያ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን መፈለግ አለብን።
የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
39 የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው።
መንፈስ ቅዱስ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ እውነት ይመራናል።
ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና …
ስለ ራሳችን መብትና ፍላጎት እንዲሁም ስለ ፍላጎቶቻችን ግትር ብለን መሟገት የለብንም። እኔነት መሞት አለበት።
1ኛ ቆሮንቶስ 15፡31 … ዕለት ዕለት እሞታለሁ።
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሰው ከራሱ መናገር የለበትም።
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው መናገር ያለበት።
ከዚያም በኋላ በአስተምህሮዋችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን ስንጀምር መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይመራናል። የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ብቸኛ መሪያችን ሲሆን መንፈስ ቅዱስ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ቃል በመጠቀም ይመራናል።
ኤፌሶን 2፡10 እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።
ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆነን ስንፈጠር ነው አዲስ ፍጥረት የምንሆነው።
ራዕይ 3፡15 በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር።
የኛ ዘመን ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን የማገልገል ጥማት አላት። ብዙ መልካም ሥራዎችን እንሰራለን።
ቤተክርስቲያን እንሄዳለን። እግዚአብሔርን እናወድሳለን። ወንጌልን ለመስበክ እንተጋለን። ቤተክርስቲያኖች በዘመናዊ ትምሕርት እና የማሕበረሰብ አገልግሎት ይሳተፋሉ። ድሆችን እና ጎስቋሎችን ለመርዳት ብዙ ጥረት ይደረጋል።
ቤተክርስቲያን ያዘዘችንን ሁሉ እናደርጋለን። ስለዚህ በራሳችን አስተያየት ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ላይ እንገኛለን።
ነገር ግን ሳናውቀው ቀስ በቀስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ ቤተክርስቲያንን እያገለገልን ነን። የመጽሐፍ ቅዱስን መንገድ ሳይሆን የቤተክርስቲያንን መንገድ እንማራለን።
ጥሩ የቤተክርስቲያን አባላት ለመሆን ካለን ትጋት የተነሳ እግዚአብሔር በእኛ እያዘነ መሆኑን እንኳ ልብ አላልንም።
ሙሉ ሃይላችንን ለቤተክርስቲያን የሰጠን አባላት ከመሆናችን እና ሌሎችን ለመርዳት የተሰጠን ከመሆናችን የተነሳ በቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተጠምደን ስላለን እግዚአብሔር በእኛ እንዳልተደሰተ አላስተዋልንም።
ነገር ግን ዛሬ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ የራሳቸውን ቃል ከፍ አድርገዋል።
በብዙ መልካም ሥራዎቻችን እና ከሲኦል በመዳናችን አብዝተን ከመመሰጣችን የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስን ምስጢራት መረዳት እንደሚያስፈልገን ረስተናል። ይህም ሊሆን የቻለው የቤተክርስቲያን መሪዎቻችን የተገለጠውን ቃል ባለማስተማር የመጽሐፍ ቅዱስ መሃይማን አድርገውናል።
ይህም ለራሳችን ማሰብ እንድናቆም አድርጎናል፤ ስለዚህ በቤተክርስቲያን ላይ ጥገኛ ሆነን ቀረን።
65-0218 ዘሩ እና ገለባው አብረው አይወርሱም
እንዴት እንደሚመሳሰሉ ተመልከቱ። ማቴዎስ በማቴዎስ 24፡24 እንደጻፈው በመጨረሻው ዘመን ሁለቱ መናፍስጥ በጣም ተመሳሳይነት ይኖራቸዋል። እነዚህም ቤተክርስቲያን የሚመላለሱት ሰዎች የቤተክርስቲያን መንፈስ እና ሙሽራዋ የሚሆኑን ሕዝብ የሙሽራ መንፈስ ናቸው። ተመሳሳይነታቸውም የተመረጡት እንኳ እስኪስቱ ድረስ ነው። ይህን ያህል ይመሳሰላሉ።
ዮሐንስ 4፡24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።
ሙሽራዋ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ አለባት።
አንዲት ሴትዮ በዝሙት ተከሳ ልትገደል ያመጧት ጊዜ ኢየሱስ ለምን ሁለት ጊዜ ምድር ላይ በጣቱ እንደጻፈ ሲጠየቁ ብዙ ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች የሚሰጡት መልስ የላቸውም፤ ከዚያም በላይ በውስጡ ያለውን ምስጢር ለመረዳት ፍላጎት የላቸውም። ምን ለየት ያለ ትርጉም ወይም ምስጢር የለውም ወይም ከመዳኔን ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም ብለው ያልፋሉ። ይህ ሁሉ ንግግር ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቃቸውን ለመሸፋፈን የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን መማር ትጋት የሚጠይቅ ሥራ ነው።
በዚህ በቸልተኛ እና ሰነፍ ዘመን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት እውነተኛ ትጋት አናሳይም። ይህ ነው እግዚአብሔር በጣም እንዲያዝንብን የሚያደርገው።
እግዚአብሔር ለዳንኤል ትንቢቱ እስከ መጨረሻው ዘመን ድረስ ታትሞ እንደተዘጋ ነግሮታል።
ዳንኤል 12፡4 ዳንኤል ሆይ፥ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል።
ዛሬ በኮምፒዩተሮች እና ከኢንተርኔት የተነሳ እውቀት በታላቅ ፍጥነት ይበዛል።
ሰዎች በፈጣን መኪኖር በባቡርና በአውሮፕላኖች ወዲያ ወዲህ ይሮጣሉ፤ እነዚህም መጓጓዣዎች በዳንኤል ዘመን የማይታወቁ ቢሆኑም እንኳ እንደ ነብይ በመጨረሻው ዘመን እንደሚሆኑ በራዕይ አይቷቸዋል።
ስለዚህ በእርግጥ ወደ ፍጻሜው ዘመን እየተቃረብን ነን።
ፕሬዚደንት ትራምፕ ኢየሩሳሌም የእሥራኤል ከተማ እንደሆነች እውቅና ሰጥቷል። ይህም የትንቢት ፍጻሜ ነው።
እግዚአብሔር ወደ አይሁዶች እየተመለሰ ነው። ስለዚህ የአሕዛብ ዘመን ወደ መጠናቀቂያው እየደረሰ ነው።
ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት የሚያስቸግሩትን ክፍሎች መረዳት እንድንችል በቂ የእግዚአብሔር ቃል መገለጥ ያስፈልገናል።
በዚህ ዘመን መጨረሻ የዳንኤል መጽሐፍ ምስጢር መገለጥ ይጀምራል።
ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች ግን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስጢሮችን አያስተውሉም።
ማቴዎስ እና ማርቆስ ለምንድነው በኢየሱስ መቃብር አጠገብ አንድ መልአክ ቆሞ ነበር ብለው የጻፉት? ሉቃስ እና ዮሐንስ ግን ሁለት መላእክት እንደነበሩ ነው የጻፉት። ምን ሊነግሩን እየሞከሩ ነው?
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ማርያምን እንዳትነኪኝ አላት።
ዮሐንስ 20፡16 ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው።
17 ኢየሱስም፦ … አትንኪኝ፤ … አላት።
ነገር ግን ማቴዎስ ውስጥ መግደላዊት ማርያም እና ሌላኛይቱ ማርያም እግሮቹን ያዙ።
ማቴዎስ 28፡9 እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና፦ ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት።
እነዚህ ክስተቶች ጠለቅ ያለ መንፈሳዊ ምስጢር አላቸው፤ እኛም ልናውቃቸው ይገባናል።
እኛ ግን የማወቅ ፍላጎት የለንም ምክንያቱም ቤተክርስቲያናችን አታውቅም። ስለዚህ በቤተክርስቲያን የመሃይምነት ጥላ ስር ተከልለን እንኖራለን፤ በራሳችንም አእምሮ ለማሰብ እጅግ እንፈራለን። ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን ማለት እንደሆኑ እንደመያውቁ ሲናገሩ ጭራሽ ኩራት ይሰማቸዋል።
የቤተክርስቲያን መሪ አላዋቂ ስለሆነ ብሎ አንድ ሰው ለምን አላዋቂ ሆኖ ይቀራል? ቤተክርስቲያን በዚህ አይነት አቋም ውስጥ መሆኗ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን በጣም እንዲጠላት ያደርገዋል። እውነትን ለማወቅ ፈልገን ብንነሳ ቤተክርስቲያን ታስቆመናለች፤ ምክንያቱም የቤተክርስቲያን መሪዎች መሃይምነታቸው እንዲጋለጥ አይፈልጉም።
ስለዚህ ቤተክርስቲያን እውነት የሚገለጥበትን መንገድ ትዘጋለች።
ቤተክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች ደስ የሚል ኑሮ ይኖራሉ፤ ነገር ግን ለመጽሐፍ ቅዱስ ምስጢራት አንዳችም ፍቅር የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ሲፈልጉ ቸል የሚሉት፣ ሲፈልጉ ደግሞ ጥቅሶቹን በራሳቸው ፍላጎት የሚተረጉሙት መጽሐፍ አድርገው ይቆጥሩታል።
ዮሐንስ 4፡24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።
ቤተክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በመንፈስ ስለማገልገል ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር በእውነት ያመልኩት ዘንድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ መፈለጉን ረስተዋል።
ኢየሱስን የሥላሴ አካል አድርጎ ለማምለክ መሞከር አንዳችም አያስደስተውም።
1ኛ ቆሮንቶስ 2፡16 እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።
ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ልብ አለኝ ትላለች ግን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፎሎችን ማብራራት አቅቷታል። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማብራራት ካልቻላችሁ የክርስቶስ ልብ ሊኖራችሁ አይችልም። ምክንያቱም ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማለቱ እንደሆነ በሙሉ ያውቃል።
የመጽሐፍ ቅዱስን ምስጢራት ሊገልጥ በመጣው በሰባተኛው መልአክ ዘመን እየኖርን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታችን ዝቅተኛ መሆኑ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር እውነተኛ ፍላጎት እንኳ የለንም። ከዚያ ይልቅ የሰዎችን ንግግር እየኮረጅን መናገር እንወዳለን። በመጽሐፍ ቅዱስም ፈንታ የሰው ንግግር የእምነታችን መሰረት ሆኗል።
የሰባተኛው መልአክ ድምጽ የእግዚአብሔር ድምጽ ተደርጎ እስኪቆጠር ድረስ ከፍ ተደርጓል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ድምጽ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደሚሰማ እንኳ ተስፋ አልተሰጠም። ስለዚህ ለራሳችን አስተሳሰብ እንዲመች አድርገን መጽሐፍ ቅዱስን እንጠመዝዛለን፤ ደግሞም ዊልያም ብራንሐም የተባለ ሰውን ወደ አምላክነት ደረጃ ከፍ እናደርገዋለን።
እግዚአብሔር ግን ክብሩን ለሌላ አይሰጥም።
ኢሳያስ 48፡11 … ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም።
ቤተክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚፈልጉትን ይወስዳሉ፤ የማይፈልጉትን ደግሞ ይተዋሉ።
ቤተክርስቲያን ትኩስነቷን ትታለች፤ ለዓለምም የእግዚአብሔር ድምጽ አይደለችም። ቤተክርስቲያን በአሁኑ ዘመን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ግድም አይላትም። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አቋም እንዲኖረን (ትኩስ እንድንሆን) ይፈልጋል። አለዚያ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ጭራሽም ባንነካካው (በራድ ብንሆን) ይመርጣል።
በራድ ብንሆን ቢያንስ ግብዝነት አይኖርብንም ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን እንደምናምን አናስመስልም። ከዚያም ክርስቲያን መሆን የሚፈልግ ሰው አይከተለንም ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን አንቀበልም።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቂቱን በማመን፤ ጥቂቱን ደግሞ እንደማያስፈልግ ንቀን በመተው፤ ወይም በትክክል እንዳልተተረጎመ አርድርገን በመቁጠር ነው እግዚአብሔርን የምናሳዝነው።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተወሰኑትን በማመን “ትኩስ” ስንሆን የተወሰኑትን ደግሞ በመቃረን ወይም ትተን በማለፍ “በራድ” ስንሆን የሁለቱ ድብልቅ ለብ ያልን ክርስቲያኖች ያደርገናል።
መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ማመን አለዚያ ደግሞ ጭራሹኑ ብንተወው ይሻላል።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚመቸንን ክፍል ብቻ እየመረጥን የምንወስድ ከሆነ አደጋ ውስጥ ነን። ሔዋን ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ትንሽ ነገር ቸል በማለቷ ነው የሰው ዘርን ሁሉ መከራ ውስጥ የጣለችው።
ዳነኤል 11፡14 … ከሕዝብህም መካከል የዓመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፤ ነገር ግን ይወድቃሉ።
መሪዎች ራሳቸውን ከፍ ማድረፍ ይወዳሉ፤ ነገር ግን የአማኞች ውድቀት መንስኤው ይህ ነው። ሰውን መከተል ከኢየሱስ ጋር የሚኖርህን የግል ሕብረት ይነጥቅሃል።
ዳንኤል 11፡26 መብሉንም የሚበሉ ሰዎች ይሰብሩታል፤ …
መብል ማለት ትምሕርት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን መብል በከፊል ብቻ መብላት ለጥፋት ያጋልጣል። ሙሉውን መብላት አለዚያም ጭራሽም አለመንካት ይሻላል።
አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ሃሳብ እውነት ነው ብላችሁ ያመናችሁ ጊዜ ከእግዚአብሔር ቃል የሚመጣውን ብርሃን ተዘርፋችኋል።
ራዕይ 3፡16 እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።
እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን እየተናገረ። የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ለራሳቸው በጣም ከፍ ያለ አመለካከት ስላላቸው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን እንደማይቀበላት ማመን ይከብዳቸዋል።
ሁሉም የራሳቸው ቤተክርስቲያን ትክክለኛ እንደሆነች ነገር ግን ሌሎች ቤተክርስቲያኖች ሁሉ እንደተሳሳቱ ያምናሉ። እግዚአብሔር ግን ይህንን ዘመን በሙሉ እንደ አንድ ቤተክርስቲያን ነው የሚያየው። እግዚአብሔርን የእኛን ቤተክርስቲያን ዘመን በሙሉ ከአፉ ይተፋል።
አፉ ማለት ቃሉ ያለበት ነው።
የዘመናችን ቤተክርስቲያን ወደ አዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መመለስን እምቢ ብላለች።
ልብ በሉ።
አንድ ግለሰብን አይደልም ከአፌ እተፋለው ያለው።
መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ አማኝ እስከ መጨረሻው መጽናት አለበት ይላል።
ማቴዎስ 10፡22 በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
“እርሱ” የሚለው ቃል ግለሰብን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው።
“ይድናል” ሲል ከምን ይድናል ማለቱ ነው? ከሲኦል አይደለም። ከሲኦል የዳንነው ኢየሱስን እንደ አዳኝ አምነን ንሰሐ በመግባት ስንቀበለው ነው።
ነገር አንድ ሰው እስከመጨረሻው ቢጸና ከታላቁ መከራ ይድናል።
ከአፉ ተተፍታ የምትወድቀው ቤተክርስቲያን ራሷናት።
1965 የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ - የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ዘመን
ታዲያ እነዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች ያለባቸው ችግር ምንድነው? ከቃሉ ርቀው ሄደዋል። ለቃሉ ትኩስ የሆነ ፍላጎት የላቸውም። ስለቃሉ ያላቸው ስሜት ለብ ያለ ነው…
… በሰባቱም ዘመናት ውስጥ ሰዎች ከቃሌ በላይ የራሳቸውን ቃል ከፍ ሲያደርጉ አይቻለው። ስለዚህ በዚህ ዘመን መጨረሻ ከአፌ እተፋችኋለው። ከዚይ በኋላ ይበቃል።
እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን ሰው ሰራሽ እምነቶችና በአንድ ሰው የሚመራ ድርጅታዊ አሰራሮች አሏት። እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን አባሎችዋን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ሃሳቦች አስራ ትይዛለች። እያንዳንዷ ቤተክርስቲያን አባሎቿ መጽሐፍ ቅዱስን ሳይሆን መሪ አድርጋ የሾመችውን ሰው እንዲከተሉ ታደርጋለች።
እግዚአብሔር የቤተክርስቲያንን “ቡድናዊ አስተሳሰብ” አይወደውም።
1965 የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ - የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ዘመን
ሰዎችን የሚያስቱ ሰዎች ተከታዮቻቸውን ከራሳቸው ጋር እንዴት በፍርሃት አስረው እንደሚይዙ ልብ ብላችኋል? ሰዎቹ እነርሱ የሚያዝዙዋቸውን ባያደርጉ ወይም ቤተክርስቲያኒቱን ለቀው ቢሄዱ ጥፋት እንደሚያገኛቸው ያስተምሯቸዋል። እነዚህ ሐሰተኛ ነብያት ናቸው፤ ምክንያቱም እውነተኛ ነብይ ሁል ጊዜ ሕዝቡን ወደ ቃሉ ነው የሚመራቸው፤ የሚያስተሳስራቸውም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው እንጂ እርሱን ራሱን እንዲፈሩት ወይም እርሱ የሚናገረው እንዲፈሩ አይላቸውም፤ ይልቁንም ቃሉ የሚለውን እንዲፈሩ ያስተምራቸዋል እንጂ።
የእግዚአብሔር ቃል የእግዚአብሔር አፍ ነው፤ ቤተክርስቲያን ግን አሁን ስለ ቃሉ ግድ አይላትም።
መጽሐፍ ቅዱስን በከፊል ማመን በኪፊል ደግሞ አለመቀበል ቤተክርስቲያንን ስለ ቃሉ ለብ ያለች እንድትሆን አድርጓታል።
የቤተክርስቲያን አባል የመሆን ፍላጎታችን ውስጥ እንኳ በሌሎች ሰዎች ተጽእኖ እና ግፊት ነው የምንሆነው።
ባቢሎን የምትለመልመው ከፍ ላለ የሰው አመራር ሰዎችን በግድ በማስገዛት ነው።
64-0629 በፊታችን የተገለጠው ኃያሉ እግዚአብሔር
… እግዚአብሔር ከሥጋዊ መጋረጃ በስተጀርባ ተደብቆ ከሚሰራው፣ የቤተክርስቲያን አካል መሆን ከሚፈልገው ውስጥ እንድንወጣ እየጠራን ነው፤ ከሜተዲስት ወይም ባፕቲስት፣ ወይም ፕሬስቢተሪያን ብቻ አይደለም ነገር ግን ከፔንቲኮስታል ቤተክርስቲያኖችም ጭምር እንድንወጣ እየጠራን ነው።
ይህ የግል ጉዳይ ነው። በአንተ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ጉዳይ ነው። የሚመለከተው ቡድንህን ወይም ቤተክርስቲያንህን ወይም ፓስተርህን አይደለም፣ አንተን በግል ነው የሚመለከትህ።
ይህ ከተነጋገርነው ውስጥ ሁሉ ዋነኛው ሃሳብ ነው።
ወንድም ብራንሐም እያንዳንዳችን በግል የመጽሐፍ ቅዱስን መገለጥ መቀበል እንደሚያስፈልገን ተናግሯል።
የምርጫችን ውጤት የሚያስከትለው ነገር አለ።
ከዚያ በኋላ አስቀድመን ያላየናቸው ውጤቶች በመጡ ጊዜ ልንከላከላቸው ወይም ልናስቀራቸው አንችልም።
የቤተክርስቲያን ልምምዳችን መጀመሪያ የዳንን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር የነበረንን ልምምድ ያጠፋብናል። ነጻ ለመሆን በፈለግን ቁጥር የልምዳችን እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎታችን ባሪያዎች እንሆናለን።
ራዕይ 3፡17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥
ቤተክርስቲያን ከእንግዲህ የእግዚአብሔር አፍ አይደለችም፤ የራሷ አፍ ናት።
በዚህ ለቁሳቁስ ክብር በሰጠ ዘመን ሩጫችን ሁሉ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ሆኗል።
ሰብስበን ሰብስበን አይበቃንም። ሁሌ ገንዘብንና ሃብትን ብቻ እንዳሳደድን ነን።
ሥራው ደስ የማይለን አይነት ቢሆንም እንኳ ደሞዙ ከፍ ያለ ከሆነ እንቀበለዋለን። የምናገኘው ገቢ እና ያካበትነው ሃብት መጠን የእግዚአብሔር በረከት ምልክት እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራለን።
በቤተክርስቲያኖቻችን ውስጥ ግድየለሾች ሆነናል። ሁሉ ሰላም ነው፤ ምንም ችግር የለም ማለት ለምደናል። ምን አያስፈልገንም በተለይም ምንም መስተካከል አያስፈልገንም።
“ራቁት መሆንህን ስለማታውቅ”። እኛ ግን ፈጽሞ ያለንበትን ሁኔታ አናውቅም።
ስለ ራሳችን ልንሰማ የማንፈልገው እውነታ ሲገለጥ የምንሰጠው ምላሽ መካድ፣ መከራከር ወይም እና ምን ይጠበስ ማለት ሆኗል። ምቾት የሚነሳንን እውነት ከመስማት ይልቅ ማንኛውንም ሌላ ነገር ብንሰማ ደስ ይለናል።
መሳሳታችንን ካልተቀበልን በቀር መቸም ቢሆን ልንስተካከል ወይም ልንታረም አንችልም።
ሰዎች በቤተክርስቲያናቸው ውስጥ ሰላም የሆኑና ስለ ጌታ በመንፈስ እየተቃጠሉ ያሉ ይመስላቸዋል። እግዚአብሔር ግን በጣም እያዘነባቸው ነው።
አልመገጣጠም ማለት ይህ ነው።
ሕዝቡ ፈጽመው ለነፍሳቸው ብለው የተጣበቁባትን ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር እንደማይፈልጋት አላወቁም።
“ጎስቋላ”። ይህ ማለት ጽናት በረከት ሳይሆን ፈተና የሚሆንበት ጊዜ ነው። ፈታኝ ጊዜዎች ያስፈሩናል።
የድብርት መድሐኒቶች ሽያጭ አሻቅቧል። የአእምሮ በሽታ እና ያልታወቁ ፍርሃቶች እንዲሁም ማደንዘዣዎች ስማቸው ገኗል። አልኮል መጠጥ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ሰዎች ስለ ራሳቸው እርግጠኝነት የላቸውም።
ሃብት ለመጨመር ካለን ፍላጎት የተነሳ በሥራ ላይ የምናጠፋው ሰዓት ጨምሯል፤ ነገር ግን ካሰብነው መድረስም አልቻልንም። ቆም ብለን ስናስብ አንድ ያጣነው ነገር እንዳለ እናስተውላለን። ስለዚህ የሚሰማንን ባዶነት ለመሙላት እንጥራለን። ነገር ግን ባዶነታችን ሁሌም አብሮን እንዳለ ነው። ሁሌ ያለማቋረጥ ሃሳባችን ውስጥ ይቆጠቁጠናል።
“ምስኪን”። ይህ ቃል ሰዎች አሳዛኝ ችግር ውስጥ እንዳሉ ያመለክታል። ቤተክርስቲያን ውስጥ በመሆን ከችግር እናመልጣለን ብለው ያምናሉ ግን የቤተክርስቲያን ድርጅት ላይ ያለውን እርግማን አያውቁም። የወንድም ብራንሐም ንግግሮችን ከመቀበላቸው በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መፈተሽ ትተዋል። ከዚያም ብሰው
“የሜሴጅ” ሰባኪዎች የሰባቱን ነጎድጓዶች ቃል እንዲሁም ሰባተኛውን ማሕተም እንተረጉማለን ይላሉ፤ ነገር ግን እነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ እንኳ አልተጻፉም። ስለዚህ የእምነት መሰረት በተጻፈው ቃል ላይ መሆኑ ቀርቷል። እንዲሁ ብቻ እንደ መጀመሪያን ቤተክርስቲያን መሆን እንዳለብን እናውቃለን።
ነገር ግን በሥራም ይሁን በእምነታችን የመጀመሪያዋን ቤተክርስቲያን አንመስላትም።
በዚህ በዘመናችን ባለው “የቤተክርስቲያናዊነት” ውድድርና በአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን መካከል እጅግ የሚያሳዝን ልዩነት ነው ያለው። አንዳንዴ ሌሎች ሰዎችን ለማስገረምና እና እንዳልጠፋን ለማሳየት እያስመሰልን እንዳለን ይሰማናል።
ከሁሉ የተሻሉ ሆኖ ለመገኘት መሞከር ሰውን ሁሉ ጎስቋላ ያደርጋል።
“ድሃ”። በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ድሃ። እምነታችን ከመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን እምነት በጣም የራቀ በመሆኑ ምሳሌዋ ልንሆን አንበቃም። የጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረው መንፈሳዊ ኃይል በንጽጽር የኛን ዘመን ቤተክርስቲያን ድሃ ያስመስላታል።
“ዕውር”። ይህ በጣም ከባድ ወቀሳ ነው። የተጻፈውን ቃል ምስጢር ማወቅ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመግለጥ ያበቃናል። ሰዎች ግን ያልተጻፈውን የሰባቱን ነጎድጓዶች እና የሰባተኛውን ማሕተም ቃል ፍለጋ ሄደዋል።
ይህን ያህል ተሳስተው ሳይበቃቸው የሄዱበት ስሕተት መንገድ የተጻፉትን ምስጢራት እንዳይረዱ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
ከሌለው ሰው ላይ ያው ያለው ትንሽ እንኳ ይወሰድበታል። ስሕተትን እየተከተሉ በሮጡበት መጠን ከውስጣቸው እውነት እየጠፋ ይሄዳል።
ማቴዎስ 13፡12 ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
ነገር ግን የወንድም ብራንሐም ንግግሮችን ወስደው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የፈተኑ ሰዎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መፍታት የሚችሉበት ፍንጭ ማግኘት ችለዋል።
“የተራቆትህ”። ልክ አዳም እና ሔዋን ከበለስ ዛፍ ቅጠሎች ራቁትነታቸውን ሊሸፍኑ እንደሞከሩ የዚህ ዘመን ሰዎች መንፈሳዊ ራቁትነታቸውን ሰዎች በሰሩዋቸው ሐይማኖቶችና በሰው አስተሳሰቦች ለመሸፈን ይሞክራሉ።
55-0403 የሐጥያት ክፋት እና ሐጥያትን ከሕይወታችን ለማስወገድ የተከፈለው ከባድ ቅጣት
ከዚያ ወዲያ ስመለከት፤ ወጥተው ሲመጡ እግዚአብሔርም በፊቱ መቆም እንደማይችሉ አወቀ። እነርሱም በቅጠሎች ሊሸሸጉ ፈለጉ፤ ነገር ግን መደበቂያ ብለው የወሰዱት ቅጠል በቂ እንዳልሆነ አውቀዋል።
አዳምና ሔዋን ስሕተታቸውንና ሐጢያታቸውን መሸፈን አልቻሉም።
በጣም ብዙ “የሜሴጅ አማኞች” በራሳቸው ባቆሙት ጽድቅና በተሳሳቱ ትምሕርቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባልተጻፉ የነጎድጓድ ድምጽ መልእክቶቻቸው ተጠምጥመዋል። በሰማያት ላይ የሰው ልጅ ምልክት ሆኖ የተገለጠውን ደመና የራዕይ ምዕራፍ 10 መልአክ መገለጥ ነው ብለው ያጣምማሉ። ደመናው ግን ከምድር በላይ በሚገር የ42 ኪሎሜትር ከፍታ ላይ ነው የቆየው።
65-0718 የእግዚአብሔር ፈቃድ ባልተገለጠበት እግዚአብሔርን ለማገልገል መሞከር
በዚያ የጠፈር መመልከቻ ማዕከል ውስጥ ሆነው ምን እንደተፈጠረ በማሰብ ሲገረሙ ነበር። ታክሰን ውስጥ ያሉ ታላላቅ የጠፈር መመልከቻ ማእከሎች ፎቶ አንስተውታል። ቢሆንም ግን ምን እንደሆነ ሊያውቁ አልቻሉም።
በጋዜጦችም ውስጥ “ይህ ክስተት ምን እንደሆነ ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቅ ሰው ይኖር ይሆን?” እያሉ በመጠየቅ ይጽፉ ነበር። በዚያ ከፍታ ላይ አንዳችም ጉም ሊኖር አይችልም፤ አየርም የለም፣ እርጥበትም የለም። ደመናው የታየው ከምድር በአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ ነበር፤ ይገርማል።
“በላይ በሰማይ ምልክቶች ይሆናሉ። እነዚህም ነገሮች ሲሆኑ፣ በልዩ ልዩ ቦታዎችም የምድር መናወጥ በሚሆንበት ጊዜ በሰማይ ላይ ምልክት የሰው ልጅ ምልክት ይታያል።”
ማቴዎስ 24፡30 በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ …
ደግሞም ለምን ሁለት ደመናዎች እንደተከሰቱ ማብራራት አይችሉም።
ከላይ ያለው ፎቶ የተነሳው ከዊንስሎው ከተማ አቅራቢያ ሲሆን ይህም ከተማ ፌብሩዋሪ 28፣ 1963 ደመናዎቹ ያልፉ በነበረበት መስመር አካባቢ ነበረ።
ከዚህ በታች ደግሞ አንድ ስዕል አለ ግን ፎቶ አይደለም። ይህ ስዕል ሁለቱ ደመናዎች ከሳንሴት ማውተን (ወይም ሳንሴት ፒክ) በ200 ማይልስ ርቀት ላይ ከሚገኘው ከፍላግስታፍ ከተማ በላይ ፀሐይ ልትጠልቅ ስትል ለ28 ደቂቃ ያህል በታዩ ጊዜ ምን ይመስሉ እንደነበር ያሳያል።
ወንድም ብራንሐም ስድስት ቀናት ካለፉ በኋላ ወደ ሳንሴት ፒክ ሄደ፤ ነገር ግን ስለ ደመናዎቹ ምንም ያወቀው ነገር አልነበረም።
ማርች 8 ቀን እርሱን የጎበኙት ሰባት መላእክት ከሰማይ ሲወርዱም ሆነ ተመልሰው ሲወጡ አንዳችም ደመና አልፈጠሩም።
የሜሴጅ ተከታዮች (ልክ “በሜሴጅ ውስጥ” እንደሚባለው አነጋገር መጠሪያቸው ራሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም) የራዕይ ምዕራፍ 10 መልአክ ወንድም ብራንሐም በምድር ላይ ሳለ ወርዷል ይላሉ።
1964-0119 ሻሎም
ነገር ግን አስተውሉ፤ ሞት ቢመጣ እንኳ “ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በመጨረሻውም ቀን አስነሳዋለው” ብሎ የተናገረውን ቃል አስቡ። ከዚያም ታላቁ ጌታ ወደ ምድር ሲረርድና በትሩን በምድር ላይ ሲያሳርፍ በዚያን ጊዜ ፍጻሜ ስለሚሆን “ጊዜ ወይም ዘመን” የሚባል ነገር ከዚያ ወዲያ አይኖርም። በራዕይ ምዕራፍ 10 የተጠቀሰው መልአክ ሲመጣና አንድ እግሩን በምድር አንድ እግሩን በባሕር አድርጎ በቆመ ጊዜ ቀስተ ደመናም ከራሱ በላይ በሆነ ጊዜ “ከእንግዲህ በኋላ አይዘገይም” ብሎ ምሏል። ያ ቀን ሲመጣ ከሙታን መካከል ትነሳላችሁ። ሌሎቹ በመቃብራቸው ተኝተው ሲቀሩ እናንተ ግን ትገባላችሁ።
ደመናው ከታየ አንድ ዓመት ካለፈ በኋላ እንኳ ወንድም ብራንሐም የራዕይ ምዕራፍ 10 መልአክ ይገለጣል ብሎ ይጠባበቅ ነበር። ትንሳኤውን የሚያከናውነው ይህ መልአክ ነው። ስለዚህ ይህ ብርቱ መልአክ የመላእክት አለቃ ነው።
65-1127 መስማትን ሰሜቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየች
እግዚአብሔር ሆይ እንደዚህ አይነት ቀን በመጣ ጊዜ ታላቅ የነጎድጓድ ድምጽ ይሆናል ከዚያም የእግዚአብሔር ልጅ በመላእክት አለቃ ትዕዛዝ በታላቅ ድምጽ በእግዚአብሔር መለከት ይመጣል በክርስቶስ ሆነው ያንቀላፉትም ይነሳሉ።
በሕይወቱ የመጨረሻ ወር ውስጥ እንኳ የመላእክት አለቃውን መምጣት ይጠባበቅ ነበር። ስለዚህ የመላእክት አለቃው ማለትም የራዕይ ምዕራፍ 10 ብርቱ መልአክ ወንድም ብራንሐም በምድር ላይ ሳለ አልመጣም ነበር።
በሕይወቱ የመጨረሻ ወር ውስጥ “ድምጹ” ገና ወደ ፊት እንደሚሆን ነበር የሚጠባበቀው። ነገር ግን “ደምጹ” እርሱ ራሱ ምስጢራትን የገለጠበት መልእክት ነበር።
1965-11-27 መስማትን ሰሜቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየች
እግዚአብሔር ሆይ እንደዚህ አይነት ቀን በመጣ ጊዜ ታላቅ የነጎድጓድ ድምጽ ይሆናል ከዚያም የእግዚአብሔር ልጅ በመላእክት አለቃ ትዕዛዝ በታላቅ ድምጽ በእግዚአብሔር መለከት ይመጣል በክርስቶስ ሆነው የሞቱትም ይነሳሉ።
ስለዚህ እርሱ ከሞተ በኋላ ሙሽራይቱ በድምጽ ተቀርጾ የተቀመጠ መልእክቱን ትሰማለች፤ ቀስ በቀስም የመጽሐፍ ቅዱስን ምስጢራት መገለጥ ለራሳቸው ይቀበላሉ።
ስለዚህ “ድምጹ” ማለት ወንድም ብራንሐም እየሰበከ በነበረበት ሰዓት አይደለም። “ድምጹ” የሚሰማው ሙሽራዋ መገለጡን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በማምጣት እውነትን ለራሷ ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈትና ስትቀበል ነው።
የሜሴጅ ሰባኪዎች መልአኩ ወንድም ብራንሐም በሕይወት ሳለ ነው የወረደው በማለት ውሸት ያስተምራሉ። ጥቅስ ወስደው ሲተረጉሙ አተረጓጎማቸው የእግዚአብሔር ቃል ከሰው አእምሮ ውስጥ እንዲጠፋ በሚያደርግ መንገድ ነው።
ምክንያቱም የዛሬ 50 ዓመት አካባቢ የራዕይ ምዕራፍ 10 መልአክ መጥቶ እንደነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ አትችሉም። ስለዚህ ቃሉ ብቻ ነው ዋስትናችን መሆን የሚችለው።
ወንድም ብራንሐም በምድር ላይ ሳለ መልአኩ ወርዶ ነበር ለማለት የሚጠቀሙት ጥቅስ ይህ ነው። (ይህ ጥቅስ እርሱ በሕይወቱ የመጨረሻ ወር በ1965-11-27 ቀን ከተናገረው ጋር የሚቃረን ቢሆንም እንኳ ይጠቀሙበታል፤ በዚያ ቀን እርሱ የነጎድጓዱን ድምጽ እና የመልአኩን መውረድ ይጠባበቅ ነበረ።)
63-0317 በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናትና በሰባቱ ማሕተሞች መካከል ያለው ክፍተት
ማሕተሞቹ ሲፈቱና ምስጢሩ ሲገለጥ የዛኔ መልአኩ ይወርዳል፤ መልእክተኛው ክርስቶስ ከራሱ በላይ ቀስተ ደመና ከቦት አንድ እግሩን በምድር አንድ እግሩን በባሕር ላይ ያደርጋል። አሁን ልብ በሉ ይህ ሰባተኛ መልአክ በምጽአቱ ሰዓት በምድር ላይ ነው።
ግን በጥንቃቄ አንብቡ።
መልአኩ የሚወርደው “ማሕተሞቹ ከተፈቱና ምስጢሩ ከተገለጠ በኋላ ብቻ ነው”። እርሱ የምስጢሩን መገለጥ ሰጥቶ በታሕሳስ 1965 ጨረሰ በዚያው ወር ሞተ።
ስለዚህ መልአኩ ሊመጣ የሚችለው ከዚያ በኋላ ነው።
አሁን ጥቅሱን ሙሉ በሙሉ አንብቡ።
63-0317 በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናትና በሰባቱ ማሕተሞች መካከል ያለው ክፍተት
... ነገር ግን በስተመጨረሻ ሰባተኛው መልአክ ምስጢሩን መግለጥ ሲጀምር እነዚህ ሰዎች ጀምረው ነካክተው የተዉትን ሁሉ ወደ መቋጫ ያመጣል፤ ምስጢሩም የሚመጣው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ እግዚአብሔር ቃል ሆኖ በመውረድ የእግዚአብሔርን መገለጥ በሙሉ ይገልጣል። ከዚያም የመለኮት ምስጢር በሙሉ ይገለጣል። ሌሎች ምስጢሮች በሙሉ፤ የእባቡ ዘር እና ሎሎችም በሙሉ ይገለጣሉ።
አሁን አያችሁ አይደል፤ አንድም ፈጥሬ ማወራው ነገር የለም። … የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ተብሎ ከሚነገር ትንቢት በምንም አይለይም። ከመጽሐፉ ውስጥ አነብላችኋለው፤ ሰባተኛው መልአክ መለከቱን በነፋ ጊዜ እግዚአብሔር በቅዱሳን ነብያቱ የተናገረው ምስጢር በሙሉ ይፈጸማል። ነብያቱ ማለት ቃሉን የጻፉት ነብያት ማለት ነው። ሰባተኛው መለከት በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ሲነፋ ተጀምረው የቀሩ የእግዚአብሔር ምስጢራት በሙሉ መቋጫቸውን ያገኛሉ። ማሕተሞቹም ሲፈቱና ምስጢሩም ሲገለጥ መልአኩ ማለትም መልእክተኛው እርሱም ክርስቶስ ከሰማይ ይወርዳል፤ ከራሱ በላይ ቀስተ ደመና አድርጎ አንድ እግሩ በምድር አንድ እግሩ ደግሞ በባሕር ላይ ሆኖ ይቆማል። አሁን ልብ በሉ በዚህ ምጽአት ሰዓት ይህ ሰባተኛ መልአክ በምድር ላይ ነው ያለው።
ሁለት ምጽአቶች አሉ።
ምስጢሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መገለጥ ሙሉ በሙሉ ለመግለጥ ነው የሚመጡት። ይህም እርሱ በታሕሳስ 1965 በሞተ ጊዜ ተጠናቅቋል።
ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥር ከተገለጠ በኋላ መልአኩ ወደ ምድር ይወርዳል።
እንግዲህ ሰባተኛው መልአክ ለየትኛው ምጽአት ነው ምድር ላይ መገኘት ያለበት?
ያለ ምንም ጥርጥር ለእግዚአብሔር ምስጢራት ምጽአት ነው።
ይህን ለማረጋገጥ ሦስት አንቀጾች አልፈን እናንብብ።
63-0317 በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናትና በሰባቱ ማሕተሞች መካከል ያለው ክፍተት
ይኸው እዚህ ደግሞ በ10ኛው ምዕራፍ ውስጥ በድጋሚ እናገኘዋለን ይህም ከመምጣቱ ጊዜ በኋላ ነው ምስጢራቱ በሙሉ የሚፈጸሙት፤ መሕተሞቹም የሚፈቱት እና ከዚያ ወዲያም ጊዜ እንደማይኖር የሚታወጀው። እርሱም እንዲህ ይላል “ሰባተኛው መልአክ ድምጹ በሚሰማበት ዘመን ምስጢራቱ ይፈጸማሉ ይህም መልአኩ የሚገለጥበት ሰዓት ይሆናል።” ጊዜው ቀርቧል፤ ከኛ እሩቅ አይደለም።
መልአኩ ምስጢራቱ በሙሉ ከተፈጸሙ በኋላ ነው የሚመጣው።
ይህም ደመናዎቹ ፎቶግራፍ ከተነሱ ከ17 ቀናት በኋላ ነው፤ እርሱ ግን እስከዚያ ቀን ሁሉ መልአኩ ይገለጥ እንደሆን በመጠባበቅ ላይ ነበር። ስለዚህ ደመናው የመልአኩን ወደ ምድር መውረድ የሚያመለክት አልነበረም።
ራስን በሰው ንግግር ጥቅስ መደገፍ ያንኑ ጥቅስ የሚያፋልስ የያዝከውን ሃሳብ ውድቅ የሚያደርግ ሌላ ጥቅስ እያለ ከሆነ ከንቱ ነው። የለበስከው የጥቅስ ሽፋን እንደ ጉም ብንን ይልና በመጽሐፍ ቅዱስ አለመጎናጸፍህን ራቁት መሆንህን ይገልጣል፤ ምክንያቱም አቋምህን የሚደግፍ አንዳችም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አይገኝም።
ቤተክርቲያን መንፈሳዊ የእውነት ልብሷ እንደተፈፈው ሁሉ የዚህ ዘመን ፍጥረታዊ ሴቶችም ገላቸውን እርቃን እያሳዩ መልበስ ጀምረዋል። የዚህ ዘመን ሴቶች ባሕሪያቸው የዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ ይገልጣል።
ራዕይ 3፡18 ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።
የተጻፈውን ቃል ማመን ታላቅ ዋጋ ያስከፍላል።
እውነትን ብዙዎች ገፍተዋታል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት የሚኖሩ ሰዎች በሄዱበት ሁሉ ይወገዛሉ ይገፋሉ። የመከራ እሳት ውስጥ መፈተንን በመፍራት ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መንገድ ይወጣሉ። የኛ ዘመን ደካማ ልፍስፍስና የሚያመቻምች ዘመን ነው። ማንም በቤተክርስቲያን ውስጥ መጠላት አይፈልግም።
ባቢሎን ውስጥ ንጉሥ ላቆመው ምስል መስገድን እምቢ ያሉ ሦስት አይሁዳውያን ሰዎችን አስታውሱ።
የሙሽራዋ አካል መሆን ከፈለጋችሁ የሜሴጅ አስተማሪዎች ወንድም ብራንሐም “የእግዚአብሔር ድምጽ ነው” በማለት ላቆሙት ምስል መስገድን እምቢ ማለት አለባችሁ። ምን ማድረግና ምን ማመን እንዳለብን የሚነግረን ኪንግ ጄምስ ባይብል የሚባለው የመጽሐፍ ቅዱስ እትም ብቻ ነው የእግዚአብሔር ድምጽ።
ከወንድም ብራንሐም ንግግር የተወሰዱ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ከፍ ማድረግ የለባችሁም። ወንድም ብራንሐም መጽሐፍ ቅዱስን ሊገልጥ እንጂ ሊተካ አይደለም የመጣው።
የመለኮት ሙላት በዊልያም ብራንሐም ውስጥ በሰውነት ተገልጦ ኖረ ብለው ቢነግሩዋችሁ ማመን የለባችሁም።
ናቡከደነጾር ስለ ዳንኤል እንደዚሁ ብሎ ነበር የሚያምነው። ያ የተሳሳተ መንፈስ እስከ ዛሬም አልሞተም።
ግን አንዳንድ እምነታቸውን በተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ላይ የሚመሰርቱ ጀግኖች ይኖራሉ።
ከዚህ የተነሳ ቤተክርቲያናት እነዚህን ሰዎች ብዙም አትደግፋቸውም። ቤተክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቀው የሚከተሉ ሰዎችን ያወግዛሉ።
እግዚአብሔር ግን እናንተ ከፈለጋችሁ ዓይናችሁን በመንፈስ ቅዱስ ዘይት ይቀባችኋል፤ ከዚያም እምነታችሁን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፉ ቃሎች ውስጥ ማየት ትችላላችሁ።
የዛኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት “አስቸጋሪ” የሚባሉ ጥቅሶች ሁሉ ምን ማለት እንደሆኑ ይገለጥላችኋል።
ራዕይ 3፡19 እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ።
ዘመናችንን ከባድ የሚያደርገው ይህ ነው። ቤተክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንድናገኝ አለመርዳቷ ሳያንስ በግላችን እውነትን ከእግዚአብሔር ዘንድ አጥብቀን ስንፈልግ እግዚአብሔር ደግሞ ይቀጣናል።
ስለዚህ በቤተክርስቲያንም በእግዚአብሔርም እንኮረኮማለን።
ነገር ግን ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር ምልክት ነው። እግዚአብሔር የሚገስጸን ቤተክርስቲያን ብዙ ስሕተት ስላስተማረችን ስሕተታችንን ለማረም እንድንችል ብሎ ነው። ልናስተካክል የሚገባን ብዙ የተሳሳቱ አስተምሕሮዎች እና ልማዶች አሉን።
ንሰሐ መግባት ብቻ በቂያችን አይደለም።
ስሕተቶቻችን ምን እንደሆኑ ለይተን ማወቅ አለብን። ንሰሐ ለመግባት መቅናት ካለብን ብዙ ንሰሐ የምንገባበት ነገር አለ ማለት ነው። ይህም በአሁኑ ሰዓት ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮች እናደርጋለን ብዙ ስሕተቶችን እንደ እውነት እናምናለን ማለት ነው። ይህ ሁሉ ስሕተት የሜሴጅ ሰባኪዎችን የመስማት ውጤትና አጣመው የሚተረጉሙዋቸውን ጥቅሶች የማዳመጥ መጨረሻ ነው። በጣም ብዙ ንሰሐ ካልገባን በቀር ቀጥታ ወደ ታላቁ መከራ እንገባለን።
ራዕይ 3፡20 እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።
ይህ የቤተክርስቲያን በር ነው።
ይህ የሎዲቅያውያን ቤተክርስቲያን ነው።
እምነታችንን በራሳችን ጥበብ መስርተናል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ማን ግድ ይለዋል?
ለምንድነው ግድየለሽ የሆንነው? ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ገፍትረን ከቤተክርስቲያናችን ስላስወጣን ነው። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መጽሐፈ ቅዱስ ምን እንደሚል መጠየቅ ካቆምን ቆይተናል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ጥቅሶች ሁሉ በጣም አሳዛኝ ጥቅስ ይህ ነው። ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን ውጭ ቆሟል።
ማንኳኳቱ የሕይወት ማንኳኳት ነው። በሕይወት ውስጥ ባሉ መከራዎች እግዚአብሔር ግለሰቦችን ለማናገር እየሞከረ ነው። ቤተክርስቲያን የቡድኖች አስተሳሰብ የሚራመድባት እውነትና ሐሰት ተደባልቀው የሚቀርቡባት የስሕተት ወጥመድ እንደሆነችና ሰዎችን ወደ ታላቁ መከራ ይዛ እንደምትሄድ እያስጠነቀቀ ነው።
“ማንም ድምጼን ቢሰማ”። የእግዚአብሔር ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ድምጽ ነው።
ሰዎች መጀመሪያ በገቡት ንሰሐ አማካኝነት ከሲኦል ሊድኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን የቤተክርስቲያን አባል በመሆን ከታላቁ መከራ ሊድኑ አይችሉም።
ኢየሱስ ግለሰቦችን እየጠራ ነው።
ቤተክርስቲያን ምቹ በሆኑ ሰው ሰራሽ ሐይማኖታዊ ልማዶቿ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ እምነቶችዋ ውስጥ ሞቋት ተመችቷት እየኖረች ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እየተመሩ መኖሩ የሚፈልጉ ግለሰቦች አሉ?
መጽሐፍ ቅዱስን ፍጹም እውነት አድርገው የሚቀበሉ ግለሰቦች እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሙሉ ምን ማለት እንደሆኑ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው የሙሽራይቱ አካል የሚሆኑት።
ስለዚህ ትልቁ ፈተናችን የሚሆነው ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ መንገድ እንዲያፈነግጡ የሚያደርጋቸውን የአለማመን ሞገድ ማሸነፍ ነው።
ይህ “መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን በሙሉ ማወቅ አለብን ” የሚሉ ልባሞቹ ቆነጃጅት ተለይተው የሚወጡበት ጊዜ ነው። ምክንያቱም የቆነጃጅቱ ባል መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
ሰነፎቹ ቆነጃጅት ግን በእንቅልፍ እያፋሸጉ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ ማወቅ አለብን እንዴ?” ይላሉ።
“መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን በሙሉ የማወቅ ፍላጎት የለንም፤ ጥቂት ከዚህ ጥቂት ከዚያ ካወቅን ይበቃናል”።
ራዕይ 3፡21 እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።
ዓለምን በሙሉ እያጥለቀለቀ ያለውን የአለማመን ማእበል እና ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ማጣት ማሸነፍ አለብህ።
ወንድም ብራንሐም የተናገራቸውን ቃሎች በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መፈተሽ አለብህ ምክንያቱም እምነትህን በመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ ያስፈልግሃል።
ሰባቱ ነጎደጓዶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፉም። ስለዚህ ሰባቱ ነጎድጓዶች ምን እንደተናገሩ ማወቅ አንችልም።
62-1230 ይህ የመጨረሻው ምልክት ነውን?
አሁን ተመልከቱ፤ የሰባቱ ድምጾች ጊዜ ሲደርስ። መጽሐፉ በተጠናቀቀ ጊዜ የሰባቱ ድምጾች ጊዜ እና ራዕይ ምዕራፍ 10 የሚገለጥበት ጊዜ ይሆናል።
የሰባቱ ነጎድጓዶች ድምጾች የሚገለጡት የተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምስጢራት ሙሉ በሙሉ ከተገለጡ በኋላ ብቻ ነው።
64-0830 ጥያቄዎችና መልሶች - ክፍል 4
ሰባቱ ነጎድጓዶች በቁጥራቸው ከሰባቱ ምስጢራት ጋር እኩል የሆኑት ከአሁን በፊት ተገልጠዋል? …
አልተገለጡም፤ የተገለጡት በሰባቱ ማሕተሞች ውስጥ ነው፤ ነጎድጓዶቹ ትርጉማቸው ያ ነው።
ይህ ነው ብዙዎች የሳቱት ቁልፍ ነጥብ።
ወንድም ብራንሐም ስለ ሰባቱ ማሕተሞች በሰበከ ሰዓት ሰባቱ ነጎድጓዶች ምን እንደሆኑ ገልጧል፤ ዓላማቸውም ወይም ግባቸው ምን እንደሆነ አስተምሯል። ነገር ግን ነጎድጓዶቹ ምን እንደሆኑ አልተናገረም።
የሰባቱ ነጎደጓዶች ዓለማ ወይም ተግባር የሙሽራዋ አካል የሆኑት ሰዎች ለመነጠቅ የሚያበቃ እምነት ይኖራቸው ዘንድ ወደ ወደ አዳዲስ አካላት እንዲገቡ ማድረግ ነው። በእነዚህ ባረጁ አካቻችን ውስጥ ሆነን ልንነጠቅ አንችልም።
63-0318 የመጀመሪያው ማሕተም
ከዚያ በኋላ ሰባት በዝርዝር ያልተገለጡ ምስጢራዊ ነጎድጓዶች ይመጣሉ። በእነዚህ ሰባት ነጎድጓዶች አማካኝነት በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ሙሽራዋ እንድትነጠቅ የሚያዘጋጁዋት መልእክቶች ይመጣሉ ብዬ አምናለው።
ምክንያቱም አሁን ባለን አካል ልንነጠቅ አንችልም።
ሰባቱ ነጎድጓዶች በተጨማሪ ደግሞ በሚናገሩት ቃል ለሁለቱ ነብያት በተፈጥሮ ላይ ኃይልን እንዲገልጡ ስልጣን ይሰጡዋቸዋል።
63-0321 አራተኛው ማሕተም
እነዚያ ሰባት ነጎድጓዶች ድምጻቸውን በማሰማት ሊቀበሉዋቸው ለሚችሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እስከሚያስተላልፉ ድረስ ጠብቁና ታያላችሁ። ይህ ሊሆን የተቆረጠ ነው። እነዚህ ሁለት ነብያት ሲፈልጉ ሰማያትን መዝጋት ይችላሉ፤ የፈለጉትን ይዘጋሉ ደስ ያላቸውን ያደርጋሉ።
ራዕይ 11፡6 እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥
የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ - የሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ዘመን
እርሱም በራዕይ ምዕራፍ 10 የተጻፉትን የሰባቱን ነጎድጓዶች ምስጢራት ይገልጣል፤ እነዚህ ምስጢራት በሰባቱ ማሕተሞች ውስጥ ያሉት መገለጦች ናቸው።
ስለዚህ የነጎድጓዶቹ ተግባር በሰባቱ ማሕተሞች ውስጥ ተገልጧል ግን ንግግራቸው አልተገለጠም። በሰባተኛው ማሕተም መጨረሻ ላይ የሰባቱ ነጎድጓዶች ቃል ሙሉ በሙሉ ምስጢር ተደርጎ እንዲታተምና እንዳይገለጥ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
63-0324 ሰባተኛው ማሕተም
ዮሐንስ የሰማቸው ሰባቱ ነጎድጓዶች ነገር ግን እንዳይጽፍ የተከለከለው፤ ከነጎድጓዶቹ ድምጽ በስተጀርባ ያለው ሚስጥር ዮሐንስ እንዳይጽፍ የተከለከለው ቃል ውስጥ ነው።
… ይህ ማንም የማያውቀው ሚስጥር ነው። ዮሐንስ እንዳይጽፈው ተከልክሏል፤ ስለ ሰባቱ ነጎድጓዶች ምስጢር ምልክት እንኳ እንዳይጽፍ ተከልክሏል። ለምን? ለዚያ ነው ከዚያ በኋላ በሰማይ ውስጥ አንዳችም እንቅስቃሴ ያልተደረገው፤ ቢደረግ ኖሮ የነጎድጓዶቹን ሚስጥር ያሳውቅ ነበር።
… ሰባት ነጎድጓዶች በተከታታይ፣ ግን ንግግራቸውን አላሰሙም… ሰማያት የነጎድጓዶቹን ቃል ሊጽፉ አልቻሉም።
ሰማያት ሊያውቁ አይችሉም ምክንያቱም እንደ ፍንጭ የሚጠቀሙበት ነገር የለም። የእረፍት ሰዓት ነው። ከመላእክት ሁሉ እንኳ ምስጢር ተደርጎ እስኪጠበቅ ድረስ ታላቅ ነው። ለምን?
ሰይጣን ምስጢሩን ቢያገኘው ብዙ ጥፋቶችን ሊያስከትል ይችል ነበር። ሰይጣን የነጎድጓዶቹን ምስጢር አያውቅም።
አሁን የፈለገውን ነገር መተርጎም ይችላል፤ የፈለገውን አይነት ስጦታ ማስመሰል ይችላል (እያስተዋላችሁ ይመስለኛል) ነገር ግን ስለ ነጎድጓዶቹ ማወቅ አይችልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንኳ አልተጻፈም። ሙሉ በሙሉ በምስጢር ተይዟል።
… ሰባት ነጎድጓዶች ናቸው ቃላቸውን የተናገሩት፤ ይህም ፍጹም ንግግር ነው ምክንያቱም ስለንግግራቸው የሚያውቅ አንዳችም ፍጡር የለም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እንኳ አልተጻፈም።
ሰባቱ ነጎድጓዶች ምን እንደተናገሩ አውቃለው ካልክ እራስህን እና ሌሎችንም እያታለልክ ነህ።
ራዕይ 10፡4 ሰባቱ ነጐድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም፦ ሰባቱ ነጐድጓድ የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው አትጻፈውም የሚል ድምፅ ሰማሁ።
ሰባቱ ነጎድጓዶች ንግግራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም፤ ስለዚህ ምን እንደተናገሩ ማወቅ አትችልም።
እግዚአብሔርን ማገልገል የምንችለው እምነታችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፉት ቃሎች ላይ ስንመሰርት ብቻ ነው።
62-1230 ይህ የመጨረሻው ምልክት ነውን?
ነገር ግን ሰባተኛው መልአክ ነው እንዲህ አይነት መልእክት ያለው። ምን አይነት ነበር መልእክቱ? መልእክቱ ምን አይነት እንደሆነ ልብ በሉ፤ “በመጽሐፉ የተጻፉትን የእግዚአብሔርን ምስጢራት በሙሉ ወደ ፍጻሜ ማምጣት”። ሰባተኛው መልአክ ሳይቋጩ የቀሩ ምስጢራትን ሁሉ እየቋጨ ነው፤ በእነዚህ ድርጅቶችና ቤተክርስቲያኖች ውስጥ ሁሉ። ሰባተኛው መልአክ ይሰበስባቸዋል፤ ከዚያም ምስጢራቱን በሙሉ ይቋጫል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚያ ነው ያለው፤ “በመጽሐፉ የተጻፈውን ምስጡር በሙሉ ይቋጫል።”
ወንድም ብራንሐም የሰባቱን ነጎድጓዶች ንግግር ሚስጥር ሊገልጥ አልመጣም፤ ምክንያቱም እነዚህ ምስጢራት ምን እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም።
ሁለት የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀመዛሙርት የነበሩ ሰዎችን እንመልከት። እነዚህ ደቀመዛሙትት ዮሐንስ ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።
ዮሐንስ 1፡35 በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥
36 ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ፦ እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ።
37 ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።
ከወንድም ብራንሐም ስብከት ውስጥ መገለጥ ብታገኙ የመገለጡን ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አማካኝነት መፈተሽ አለባችሁ።
ነገር ግን አንዳንድ የዮሐንስ ተከታዮች የዮሐንስን ጥቅስ ይዘው ቀሩና ኢየሱስን አልተከተሉትም። ስለዚህ ዮሐንስ ኢየሱስ መሲሁ መሆኑን በመጠራጠር ታላቅ ስሕተት የሰራ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ የዮሐንስን የተሳሳተ ጥቅስ መደጋገማቸውን ቀጠሉ።
ማቴዎስ 11፡2 ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና፦
3 የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው።
ኢየሱስ ዮሐንስን ስለ ስሕተቱ አልወቀሰውም። ግን እነዚያ ሁለት ደቀመዛሙርት ከዚያ ወዲያ ሁለተኛ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሱም። ስለዚህ የዮሐንስ ደቀመዛሙርት መሆንና ከዮሐንስ የተሳሳቱ ጥቅሶች ጋር ተጣብቆ መቅረት እነዚያን ሁለት ደቀመዛሙርት አንዳችም አልጠቀማቸውም።
ከዚህ የምንማረው ታላቅ ሰውን መከተል እንደማያዋጣ ነው።
የዮሐንስን ጥቅስ እንደ ገደል ማሚቶ ሲደጋግሙ ኢየሱስን ምንም አላስደነቁትም። ኢየሱስ እነርሱ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያምኑ ነበር የሚጠብቀው። ስለዚህ እርሱ ራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመጥቀስ አረማቸው። የዮሐንስ ደቀመዛሙርት ለዮሐንስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን በመንገር ዮሐንስን ሊያርሙት ይገባ ነበር። ነገር ግን ዮሐንስ በጣም ዝነኛ ስለነበረ እጅግ ፈሩት።
“ነብይን ማረም አይቻልም” ብለው ነበር የሚያምኑት።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛ አይጠቅሳቸውም።
ታሪክ ዛሬም ራሱን ይደግማል። ዊልያም ብራንሐም ሲናገር ሰምተነው ከሆነ ሃሳቡን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፈው ቃል መሰረት በመፈተሽ መከታተል እንችላለን።
62-0318 የተነገረው ቃል የመጀመሪያው ዘር ነው - ክፍል 2
አሁን የተናገርኳቸው ቃሎች በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር ባይስማሙ ወይም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ባይገጥሙ ስሕተት ናቸው ስሕተት ናቸው።
በሰው ንግግር ጥቅስ ላይ ልንቆም አንችልም። ለምሳሌ ወንድም ብራንሐም አሜሪካ በ1977 እንደምትጠፋ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ግን ያ ትንቢት አልተፈጸመም።
ግን ዛሬ ብዙ የሜሴጅ ሰባኪዎች ኢየሱስ በ1977 እንደሚመጣ ሞቅ አርገው መስበካቸውን ሆን ብለው ረስተዋል።
አንዳንድ ጥቅሶች ተወስደው ሒላሪ ክሊንተን በ2016 አሜሪካ ውስጥ በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደምታሸንፍ ተተርጉመው ነበር። ያም ቢሆን አልተፈጸመም።
ወንድም ብራንሐም ደመናው በተከሰተ ጊዜ ከደመናው በታች ቆሞ እንደነበረ ከልቡ አጥብቆ ያምን ነበር። ነገር ግን ደመናው ከፍላግስታፍ ከተማ በላይ ነበረ የተከሰተው፤ ያውም መላእክቱ እርሱን ሊያናግሩ ወደ ሳንሴት ፒክ ከመምጣታቸው ከስምንት ቀናት በፊት። ሳንሴት ፒክ ከፍላግስታፍ 200 ማይልስ ይርቃል። ስለዚህ ወንድም ብራንሐም ስሕተት መስራቱን በዚህ ማየት እንችላለን። እርሱም እንደ እኛ ሰው ነው።
ልክ በመጥምቁ ዮሐንስ እንዳየነው ሁሉ መሳሳቱ የመጨረሻው ዘመን ነብይ መሆኑን አይሽርም።
ወንድም ብራንሐም የሰራቸው እነዚህ ስሕተቶች የሚያመለክቱን የተናገራቸውን ንግግሮች ሁሉ ትክክል መሆናቸውን ፈትሸን ማረጋገጥ እንዳለብን ነው።
ነገር ግን ስሕተቶቹን ዝም ብለው እንደ ገደል ማሚቶ የሚደጋግሙ የዊልያም ብራንሐም ደቀመዛሙርት እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ሁለት ደቀመዛሙርት የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ወደ ጎን ትተው እየሄዱ ናቸው።
እናነተ ግን ማሸነፍ አለባችሁ። ይህ ትግል ነው።
ብዙዎቹ የሜሴጅ አማኞች በመጽሐፍ ቅዱስ ቦታ የሰውን ጥቅሶች እስኪተኩ ድረስ ተታልለዋል። ሰዎች ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚቃረን መልኩ እንዲተረጉሙ ተታልለዋል።
የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ለመረዳት ቀላል የሆነ መንገድ የለም።
እስቲ የአንድ ቅዱስ ሰውን ምስል ማምለክ ግዴታ ሆኖ የታወጀበትን የመጀመሪያውን የአሕዛብ ባቢሎን መንግሥት እንመልከት።
ባቢሎን ውስጥ ለዳንኤል ብልጣሶር የሚል ስም አወጡለት።
ዳንኤል 1፡7 የጃንደረቦቹም አለቃ ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፥
ዳንኤል 4፡8 በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤
ናቡከደነፆር የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ዳንኤል ውስጥ አለ ብሎ አመነ። ስለዚህ የዳንኤልን ምስል በወርቅ አሰርቶ እንዲመለክ አዘዘ። ለዚህ ነው ዳንኤል የራሱን ምስል እንዲያመልክ ያልተገደደው።
ዳንኤል 3፡5 የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል፤
ናቡከደነፆር ዳንኤልን በአምላኩ በብልጣሶር ስም ጠራው። ስለዚህ የአምላኩ ምስል በእርግጥ የዳንኤል ምስል ነበር፤ ዳንኤልም ለዚህ በምስሉ አካባቢ ያልተገኘው። ምክንያቱም ዳንኤልን ለራሱ ምስል ሊያሰግዱት አይችሉም።
የመጀመሪያው የአሕዛብ የባቢሎን መንግሥት በግዳጅ ለአንድ ቅዱስ ነብይ አምልኮና ስግደት ማቅረብን አስተማረች።
የዛሬዎቹ የመጨረሻ የአሕዛብ መንግሥታት በሜሴጅ አማኞች ዘንድ የከበረውን የአሕዛብ ነብይ እንዲመለክ ማስገደዳቸው አይቀርም።
የሜሴጅ ሰባኪዎች ዊልያም ብራንሐም “የእግዚአብሔር ድምጽ” ነው ይላሉ። ይህም ስሕተታቸው በእነርሱ ዘንድ ብራንሐም ፈጽሞ የማይሳሳት ሰው እንዲሁን በማድረጉ ወደ አምላክነት ደረጃ አስጠግቶታል። ስለዚህ አሁን እርሱ የተናገራቸው ቃላት ሲጠቀሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ አስፈላጊ እንደሆኑ ይታመናል።
1965 የቤተክርስቲያን ዘመን መጽሐፍ - የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ዘመን
ለመጨረሻ ጊዜ በሎዶቅያ ነብይ-መልእክተኛ እና የኢየሱስን የመጀመሪያ ምጽአት ቀድሞ በተገለጠው ነብይ-መልእክተኛ ዮሐንስ መካከል ንጽጽር ማሳየት እፈልጋለው። በዮሐንስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ዮሐንስ መሲሁ መስሏቸው ነበር።
ዮሐንስ 1፡19-20
አይሁድም፦ አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ።
አሁን ይህ የመጨረሻው ዘመን ነብይ-መልእክተኛ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ታላቅ ኃይል ስለሚኖረው አንዳንዶች ኢየሱስን ሊመስላቸው ይችላል።
(በመጨረሻው ጊዜ በዓለም ውስጥ የሚነሳ መንፈስ አለ፤ ይህም መንፈስ አንዳንዶችን ያስትና ይህንን ውሸት እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል። )
ማቴዎስ 24፡23-26
“በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።
እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ።
እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤)
ሰባቱ መላእክት ወደ ወንድም ብራንሐም ሳንሴት ፒክ የሚባል ቦታ መጡ፤ ያም ቦታ የሶኖራ በረሃ ውስጥ ነው። ስለዚያ ያ ክስተት የጌታ ምጻት አልነበረም።
በፍጹም አትመኑ። ዊልያም ብራንሐም ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም። እርሱ ከወንድሞች አንዱ፤ ነብይ ወይም መልእክተኛ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። እርሱም ዮሐንስ “እኔ አይደለሁም ግን ከእኔ በኋላ የሚመጣው ነው” ብሎ በጮኸ ጊዜ ከተቀበለው ክብር የሚበልጥ ክብር አያስፈልገውም።
ልብ በሉ፤ ኢየሱስ የራዕይ ምዕራፍ 10 ብርቱ መልአክ ሆኖ ወደ ምድር የሚወርደው ከብራንሐም አገልግሎት በኋላ ነው።
በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ጅማሬ አካባቢ በ1920ዎቹ ኮምዩኒስቶቹ ሌኒንን የአብዮቱ ነብይ ከመሆን አሳልፈው የሮዲና ማለትም የእናት ሃገር የራሺያ አምላክ ወደ መሆን ከፍ አደረጉት። ይህንንም ያደረጉት ወዲያው ሊኒን በ1924 ከሞተ በኋላ ነበር። እርሱን አምላክ ማድረጋቸው በእስታሊን አመራር ወቅት ከሌኒን ትምሕርት አፈግፍገው ለመሄዳቸው ማካካሻ ይሆናቸው ዘንድ ነው። ከሌሊን ትምሕርት ባፈነገጡ ቁጥር ለሌኒን ይበልጥ እያከበሩ ሄዱ።
እኛ የሰው ልጆች በጣም አስተዋዮች አይደለንም። ሌሎች ከእኛ በፊት የሰሩዋቸውን ስሕተቶች የመደጋገም አባዜ አለብን።
64-0823 ጥያቄዎችና መልሶች - ክፍል 2
አንዳንዶች ወንድም ብራንሐም የሰው ልጅ ነው ይላሉ። እኔ ደግሞ የእሳት አምዱ የሰው ልጅ መስሎኝ ነበር። ተሳሳትኩ?
ጥሩ ጥያቄ ነው፤ በጣም ጥሩ። እኔ ግን የሰው ልጅ አይደለሁም፤ ከሰው ልጆች አንዱ ነኝ እንጂ። በጣም ትልቅ ልዩነት አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ የሰው ልጅ ነው፤ የዳዊት ልጅ ነው።
65-0725 የተቀባውና የዘመኑ መጨረሻ
“የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን።” ራዕይ 10፡1 እስከ 7፤ እቤታችሁ ስትገቡ አንብቡት፤ “የሰባተኛው መልአክ መልእክት፣ የማሕተሞቹ መፈታት።” ምን ማለት ነው?
መልአኩ የሰው ልጅ አይደለም፤
ነገር ግን መልእክተኛው የሰውን ልጅ ይገልጠዋል።
አሁን ልዩነቱን አያችሁ?
በጣም ግር የሚያችሁ ይህ ነው አይደል፤ አሁን ግልጽ ሆኖላችኋል።
የሰው ልጅ ራሱ ሳይሆን፤
ነገር ግን ሰባተኛው መልአክ፣ ሰባተኛው መልእክተኛ የሰው ልጅን ለሕዝብ ይገልጠዋል።
በባቢሎን ዘመን ሕዝቡ ሁሉ በአንድ ሃሳብ ሲቆሙ ሦስት ሰዎች ብቻ ከሕዝቡ ተነጥለው በራሳቸው አቋም ጸኑ፤ ሰውን ማለትም ነብዩ ዳንኤልን ከማምለክ ሐይማኖታዊ ስሕተት ራሳቸውን ጠብቀው ጸንተው ቆሙ። እነዚህ ሦስት ሰዎችም ወደ እቶን እሳት ውስጥ ተወረወሩ።
ከነብያቸው ከሌኒን ሃሳብ ጋር አልስማማም ያሉ ራሺያኖች በእስር ቤት ውስጥ ታሰሩ ብዙዎቹም በጥይት ተገደሉ።
ስለዚህ ዛሬ የዊልያም ብራንሐምን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በላይ ከፍ ማድረግን እምቢ ከሚሉ ጥቂቶች ጋር ትቀላቀላለህ፤ ከዚህም የተነሳ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት የማጣት፣ የመተቸት፣ በሜሴጅ አማኞች ዘንድ የመጠላት የእቶን እሳት ውስጥ ትገባለህ?
ራዕይ 3፡22 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
ልብ በሉ መንፈስ ለዚህ ዘመን አንድም እንኳ የማጽናናት ቃል አልተናገረም።
መንፈስ አሁን “ለሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን” ከቤተክርስቲያን ውጭ ቆሞ ነው የሚናገረው። ስለዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ መሆን ለደህንነታችን አስጊ ነው።
ሁላችንም ብዙ ንሰሐ የምንገባበት ነገር አለ።
መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው ወደ እውነት ሁሉ ሊመራን የሚችለው። መንፈስ ቅዱስ ከተገለጠው ከእግዚአብሔር ቃል ተነስቶ ሲናገርህ ይሰማሃል?