የቤተክርስቲያን ዘመናት - ሰምርኔስ፤ ሁለተኛው ዘመን፤ ከ170 ዓ.ም. – 312 ዓ.ም.

ሰምርኔስ የሚለው ስም የመጣው “መር” (ከርቤ) ከሚላው ቃል ሲሆን ትርጉሙ መራራነት እና ሞት ማለት ነው።

ይህ ግራ የመጋባትና ያለመረጋጋት ዘመን ነበር። በዚህ የ142 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብዙ ባለስልጣኖች ተገድለዋል፤ ደግሞም ወደ 80 የሚጠጉ ሰዎች በሮማ ግዛት ውስጥ በተለያየ ቦታ እንዲሁም በሮም ከተማ ውስጥ ራሳቸውን ንጉስ ብለው ሾመዋል። በ23 ዓመታት ውስጥ ከ247 ዓ.ም. እስከ 270 ዓ.ም. ሰላሳ ሰዎች ራሳቸውን ንጉስ አድርገው አውጀዋል። በ238 ዓ.ም. ራሳቸውን ንጉስ አድርገው ያወጁ ሰባት ሰዎች ተገድለዋል። የነገሥታትን መተካካት እንደዚህ ፈጽሞ ባልተረጋጋ መንገድ መሆኑ የሮማ ግዛትን ድንበር ጠባቂ ኃይል በእጅጉ አዳከመው፤ ኢኮኖሚውንም አቆረቆዘው። ስልጣን ፈላጊ ሰዎች በዙፋን ላይ ያሉትን ለመግደልና ራሳቸውን በስልጣን ላይ ለማስቀመጥ ብለው የከፈቱዋቸው የእርስ በእርስ ጦርነቶች ብዙ ገንዘብ የፈጁ ሲሆን ድንበር የሚጠብቁ ወታደሮችን ቁጥር በማመንመን ግዛቱ ለተናጣቂ የጀርመን ባርቤሪያን ወራሪዎች እና ኃይላቸውን እየጨመሩ ለመጡት ለፋርስ ነገሥታት እንዲጋለጥ አድርገዋል።

በሮማ ግዛት ውስጥ የተከሰተው የአመራር ቀውስ በቤተክርስቲያን ውስጥ እየበዛ የሄደውን የአመራር ቀውስ የሚያንጸባርቅ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት የመሰረቱዋቸው ቤተክርስቲያኖች በሙሉ መለወጥ እና ለየዘመኑ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እንዲመች ተብሎ መሻሻል በማያስፈልገው በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተዘጋጀው ቋሚ መርህ መሰረት በሽማግሌዎች ሕብረት የሚመሩ ነበሩ። ኢየሱስ እራሱን የእያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ማዕከል እንደማድረጉ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ለቤተክርስቲያናት የማይለወጥ መምሪያ ተደርጎ ተሰጥቷል። ለዚህ ነው ኢየሱስ በመቅረዞቹ መካከል የሚታየው። የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች በስደት፣ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በባርቤሪያውያን እና በፋርሶች ወረራ ምክንያት ብዙ ተበታትነዋል። እውነተኞቹ አማኞች ሳይጠፉ እንዲቆዩ ያደረጋቸው ሕዝቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ መሰባሰባቸው ነው። ሞት ሁልጊዜም አብሮአቸው ነበረ። የስደተኞቹ ክርስቲያኖች መበታተን በሰዎች አምባገነን የቤተክርስቲያን መሪነት አማካኝነት በእውነተኞቹ ክርስቲያኖች ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን አሉታዊ ተጽእኖ ቀነሰው።

ማቴዎስ 18፡20 ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።

የተበታተኑት ትንንሽ ቡድኖች በአንድ ሰው ስር የሚያሰባስባቸው ሐይማኖታዊ ድርጅት አላስፈለጋቸውም።

ነገር ግን በየከተማው ያሉትን ቤተክርስቲያኖች እንዲመሩ በሰው ሃሳብ የተሾሙ ጳጳሳት የሚመሩበት ሥርዓት እያደገ ሲመጣ የቤተክርስቲየን ድርጅትም ቶሎ ቶሎ ማደግ ጀመረ። ይህች ድርጅታዊ የሆነች ቤተክርስቲያን ደግመፐ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ ልባቸው ለሚከተሉ ሰዎች ጠላት መሆን ጀመረች።

በዚህ አለመረጋጋት በነገሰበት ዘመን ውስጥ መረጋጋትን ያመጣ ዘንድ የጳጳሳት በአመራር መተካካት ትክክለኛው መፍትሄ መስሎ ቀረበ። ይህ ዘመን በታሪኮቹ ላይ ታላቅ ጨለማ የሰፈረበት በመሆኑ ስለዘመኑ የማየታወቁ ብዙ ክስተቶች አሉ። በተለይ ከ235 እስከ 284 ዓ.ም. ድረስ ስላለፉት ሃምሳዎቹ ዓመታት ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። በሃምሳ ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት እና በ20 ዓመታት የጀርመን ባርቤሪያውያን ወረራ (ከ245 እስከ 265 ዓ.ም.) የተፈጠረ ነውጥ ይህንን ወቅት የከፍተኛ ቀውስ ዘመን አድርጎታል። ከሃኒባል ቀጥሎ ለሮም እጅግ አስጊ ጠላት የሆነው የፋርስ መሪ ሻፑር በ242 እና በ260 ዓ.ም. መካከል ሦስት ታላላቅ ጥቃቶችን በሮም ላይ ሰንዝሯል። በጥቃቶቹ መካከል በሮማ ግዛት አውራጃዎች ላይ ዓመታዎ ወረራዎችንም ያካሂድ ነበር።

በዚህ አደጋ በተሞላበት ዘመን ውስጥ እነዚህን ሁሉ አስጊ እና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ለመከላከል ቤተክርስቲያኖች በተመረጡ ጥቂት ከተሞች ውስጥ እውነትን ለማስጠበቅና የተረጋጋ አመራር ለመመስረት ብለው “ሐዋርያዊ መተካካት” የሚባል ስርዓት በማበጀት ታላቅ ስሕተት ሰሩ። በሐዋርያት የተጀመሩ ቤተክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ ነው እውነት የሚገኘው አሉ። ይህም በወቅቱ እየደገ የመጣውና ቤተክርስቲያኖችን ሁሉ የወረሰ ውሸት ነበር።

ከ249 እስከ 260 ዓ.ም. የነበረው ጊዜ በክርስቲያኖች ላይ ለአሥራ አንድ ዓመታት ያልተቋረጠ ከባድ ስደት የደረሰበት ጊዜ ነበረ። በዚያኑ ወቅት የበሽታ ወረርሽኝ እና የዋጋ ንረት በመከሰቱ የገንዘብ አቅም የወደቀበት ጊዜ ነበረ። ለእነዚህ ሁሉ አደጋዎች ክርስቲያኖች ተጠያቂ ተደረጉ፤ የሮማ ግዛትም ፈጽሞ ሊያጠፋቸው ተነሳ። በ266 ዓ.ም. ከእርስ በርስ ጦርነት የተነሳ የሮማ ግዛት በሦስት ክፍል ተከፈለ። ብዙ ሐብት እና የብዙ ሰው ሕይወት ከወደመ በኋላ ኦሬሊያን የተባለው ንጉስ በታላቅ ወታደራዊ ብቃት እና ጭካኔ (ጭካኔው በተለይ በክርስቲያኖች ላይ ነበር) በ274 ዓ.ም. ግዛቱን ወደ አንድነት መልሶ እንዳመጣ በቀጣዩ ዓመት በ275 ዓ.ም. ነፍሰ ገዳይ ወግቶ ገደለው። ይህ ዘመን የብዙ ወከባ እና የታላላቅ ነውጦች ዘመን ነበር።

ከ178 ዓ.ም. ጀምሮ በ200 ዓ.ም እስከሚሞት ድረስ (የዚህ ዘመን ታሪክ ውስጥ ቀናት እና ዓመታት እንቅጫቸውን መጥቀስ አስቸጋሪ ነው) የልዮንስ ከተማ ጳጳስ የነበረው አይሬንየስ የዘመኑ ታላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ነበረ። አይሬንየስ ጳጳስ የሆነው በከፊል የአእምሮ ሕመምተኛ እንዲሁም እጅግ ክፉ የነበረው ከ180 ዓ.ም. እስከ 192 ዓ.ም. የነገሰው ንጉስ ኮሞደስ ወደ ሥልጣን ከመውጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። የዚህ ንጉስ መርዛማ ባሕርይ መንስኤው ጭካኔ፣ ከንቱነት፣ የስልጣን ፍቅር እና ፍርሃት ነበር። ተድላ ብቻ ይወድ የነበረው ሰነፍ ንጉስ ኮሞደስ መንግስቱን እንዲያስተዳድርለት አንድ ሰውን ሾመ፤ የታሪክ ምሁራን እንደጻፉት ይህ በሮማ ግዛት ታሪክ ውስጥ እጅግ ብልሹመንግስት ነበረ። አይሬኒየስ የልዮንስ ጳጳስ በሆነበት ጊዜ የነበረው ትርምስ ይህ ያህል ነበር። አይሬንየስ በዘመኑ ደማቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ነበረ፤ ነገር ግን በጣም ጠማማ የፖለቲካ ሥርዓት ሰፈነበት ዘመን ውስጥ ነው የኖረው። የኮሞደስ አባት ማርከስ ኦሬሊየስ በሳል መሪ ተብሎ ይቆጠራል ግን በክርስቲያኖች ላይ ከልክ ያለፈ ጭካኔ የሞላባቸው ስደቶችን አስነስቷል። ክርስሰቲያኖችን ከመግደሉ በፊት በታላቅ ጭካኔ አሰቃይቷቸዋል። በበሳል ፍልስፍናው ከሚታወቅ ሰው ዘንድ ከልክ ያለፈ ጭካኔ መገኘቱ በጣም ግራ ያጋባል። ማርከስ ኦሬሊየስ በ177 ዓ.ም. በተነሳ ስደት ወቅት የልዮንስን ጳጳስ አስገድሏል። በዚህ ጳጳስ ቦታ ነው አይሬንየስ ጳጳስ ሆኖ የተተካው።

ስለዚህ ሁሉም ሰው በቤተክርስቲያን ውስጥ የተረጋጋ አመራር እንዲሰፍን በጣም ይናፍቅ ነበር፤ ይህም መላቅጡ የጠፋው የጊዜው ፖለቲካዊ አመራር የሚያደርስባቸውን ስጋትና ጥቃት ለመታገስ እንዲችሉ ይረዳቸው ዘንድ ነበር። በዚያ የጭንቅ ዘመን የሮማው ንጉስ ኮሞደስ እጅግ ብልሹ አባቱ ማርከስ ኦሬሊየስ ደግሞ ለክርስቲያኖች በጣም ጨካኝ ጠላት ስለነበረ አይሬንየስ የሮምን ጳጳስ ከሁለቱም ነገስታት የተሻለ አሳቢ ሰው ሆኖ ስለገኘው እንደ ምሳሌ ሊከተሉት የሚገባ የእውነት ጠበቃ አድርጎ ቆጠረው። ነገር ግን ሮምን ብቻ እንጂ ሌላ ከተማ አልጠቀሰም። በዚህም ምክንያት ሐይማኖታዊ ስልጣን ለሮማው ጳጳስ ተሰጥቶታል ያለ ይመስላል። እንደዚህ በሚያሳዝን ሁኔታ የዚህ የሁለተኛው ዘመን መልእክተኛ የሮማ ጳጳሳት ስልጣን ቀጥታ ከሐዋርያው ጴጥሮስ “ሲወርድ ሲዋረድ” የመጣ ነው ብሎ እውቅና በመስጠት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምሕርት ፈቀቅ አለ። ይህ ዘመን ስደት እና ግራ መጋባት የበዛበት በዚህም ምክንያት ቤተክርስቲያኖች ሰው መሪ እንዲሆንላቸው ወደመፈለግ ፈቀቅ ያሉበት ጊዜ መሆኑን አስታውሱ፤ ቤተክርስቲያኖቹም በተለያዩ ከተሞች ውስጥ እየተተካኩ ጳጳሳት የሆኑት ሰዎች ብቸኞቹ የእውነት ባለ አደራዎች እንደሆኑ አድርገው አመኑ።

የሚገርመው በዘመኑ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ የበለጠ እውነትን የተረዳ እና የያዘ ሰው አይሬንየስ ነበረ ግን እርሱ የልዮንስ ከተማ ጳጳስ ነበረ፤ የዚህችም ከተማ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መስራች አልነበራትም። የዚህ አስተሳሰብ ሞኝነት ማሳያው የቱርስ ማርቲን፣ የአዮና ደሴት ኮሉምባ፣ የዊተንበርግ ሉተር፣ የእንግሊዙ ዌስሊ፣ እና ከጄፈርሰንቪል አሜሪካ የሆነው ዊልያም ብራንሃም ሁላቸውም አንድም ሐዋርያ ረግጧት ከማያውቅ እና በዘመናት ውስጥ እየተተካኩ የመጡ ጳጳሳት ካልኖሩባት ከተማ ተነስተው የእውነትን ተሃድሶ ለማምጣት መሞከራቸው ነው። አይሬንየስ ሰው ነው፤ በዚህም ሃሳብ ላይ ብዙ ስቷል። ብልህ የሆነ የሰው አመለካከትን አትታመኑ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፈው ቃል ጸንቶ መቆም ይሻላል።

ይህ የሐዋርያት መተካካት የሚለው ሃሳብ ሮም፣ አንጾኪያ፣ ተመልሳ የተገነባቸው ኢየሩሳሌም፣ እና አሌግዛንድሪያ በክርስቲያኖች መካከል እየገነኑ በመጡበት ጊዜ በጣም ጥሩ ሃሳብ እንደሆነ ተቆጥሮ ነበር። በትናንሽ ከተሞች ያሉ ቤተክርስቲያኖች ከእነርሱ መማር ይችላሉ። ከእነዚህ ትልልቅ ቤተክርስቲያኖች አንዳቸው ሌላኛዋን ትልቅ ቤተክርስቲያን እንደ ሚዛን ሆና መጠበቅ ትችላለች። ስለዚህ እነዚህ ጥቂት ትልልቅ ቤተክርስቲያኖች እርስ በራሳቸውን እንደ ሚዛን መጠባበቅ ይችላሉ። ነገር ግን የአረብ ሙስሊሞች ከአረቢያ በረሃ በ634 ዓ.ም. ተነስተው በ641 ዓ.ም. አንጾኪያን፣ ኢየሩሳሌምንና አሌግዛንድሪያን በተቆጣጠሩ ጊዜ ይህንን እቅድ አከሸፉ። ከዚያ ወዲያ እነዚህ ቤተክርስቲያኖች በክርስቲያኖች ዘንድ የነበራቸውን ታላቅነት ሲያጡ የሮም ቤተክርስቲያን ደግሞ በምዕራብ ካሉ ሐዋርያዊ መሰረት ካላቸው ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ብቸኛ በመሆን በክብር ከፍ ከፍ አለች። ግሪክ በሐዋርያት የተጀመሩ ቤተክርስቲያኖች ነበሩዋት ግን ግሪክ ደግሞ የምሥራቃዊው ግዛት አካል ነበረች። ይህ ክስተት ለምን ከመጽሐፍ ቅዱስ መራቅ እንደሌለብን የሚያስተምር ታላቅ ትምሕርት ነው። የወደፊቱን ዘመን መተንበይ አንችልም፤ ቅን ሰዎች በዘመናቸው የነበረውን ችግር ለማቃለል ብለው ያመጡት መፍትሄ መጨረሻው ልክ ያልሆነችዋን ቤተክርስቲያን መደገፍና ሃይለኛ ማድረግ ሆኗል። እውነት “ተከታታይ ጳጳሳት” በአደራ ተላልፏል የተባለው ምን እንደፈጠረ አይተናል። ሃሳቡ ከአጀማመሩ አርቆ አሳቢነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስም የማይስማማ ነበር።

አይሬኒየስ እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር፡- “ያ በዓለም ሁሉ ከታወቀችው እና በሮም ከተማ በሁለቱ የጥንት ታላላቅ ሐዋርያት በጴጥሮስ እና በጳውሎስ ተመስርታ ከተደራጀችው ቤተክርስቲያን የመጣው ልማድ፤ እንዲሁም ለሰዎች ሁሉ የተሰበከው እምነት፤ በጳጳሳት መተካካት ወደኛ ዘመን ደርሷል። ይህች ቤተክርስቲያን ከሁሉ የላቀ ስልጣን ስላላት ሁሉም ቤተክርስቲያኖች ከዚህች ቤተክርስቲያን ጋር መስማማታቸው የግድ አስፈላጊ ነው”።

አይሬንየስ በሮም ያለችውን ቤተክርስቲያን የመሰረታት ጴጥሮስ ነው አለ። ይህ ሙሉ በሙሉ ስሕተት ነው። ጴጥሮስ ሮም ሔዶ አያውቅም።

ከዚያም ደግሞ የሮማ ጳጳሳት መተካካት እውነተኛውን የሐዋርያት እምነት በመከተል የተደረገ ነው ስለዚህ የስልጣናቸውን ታላቅነት ልንቀበል ይገባል አለ።

ነገር ግን ሮም መጽሐፍ ቅዱስ የጋለሞቶች እናት ብሎ የሚጠቅሳት ቤተክርስቲያን ናት።

ይህም ጴጥሮስ ሮም ስለመምጣቱ የተናፈሰው የሃሰት ወሬ ብዙ ጊዜ ከመደጋገሙ የተነሳ ሁሉም ሰው እንዴት አምኖ እንደተቀበለው ያመለክተናል።

እንግዲህ የሰው እውቀትን ምክር ውጤቱ ይህ ነው። ጥሩ የተባሉ መሪዎች እንኳ ሳይቀሩ ይስታሉ። ስለዚህ በፓስተራችሁ እና በአመለካከቱ አትታመኑ፤ ከዚያ ይልቅ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በተጻፈው ላይ ታመኑ።

አይሬንየስ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የተሾሙ ጳጳሳት መነሻቸው ከጥንቶቹ ሐዋርያት እንደሆኑ እና ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ወይም ፍቺ ሊሰጡን የሚችሉት እነርሱ ብቻ እንደሆኑ ይናገራል። የአይሬንየስ ጽሑፍ ከክሌመንት እና ከኢግናሺየስ ጽሑፎች ጋር የሮም ቤተክርስቲያን የሁሉ ታላቅ ናት የሚለውን ትምሕርት ለማጽናት ከተጻፉ የመጀመሪያ ጽሑፎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። የሮማውን ጳጳስ የሌሎቹ ሁሉ ጳጳሳት አለቃ ያደረገ ትምሕርት ዓመታት እንኳ ሳይቆይ መዘዞችን ይዞ መጥቷል።

አይሬንየስ የሮማ ቤተክርስቲያንን ሳይቋረጥ እየተቀጣጣለ የመጣ የስልጣን ሽግግር ምሳሌ አድርጎ ያቀርብልናል። የዚህ ትምሕርት አንድምታው የተወሰኑ ከተሞች ከሌሎች ከተሞች እንደሚበልጡ አድርጎ ማሳየት ነው። አንድን ጳጳስ ትልቅና ለሌሎች የበላይ ሌሎችን ጳጳሳት ደግሞ የበታች ማድረግ የኒቆላዊነት ቁልፍ ነው።

አይሬንየስ በስም ዘርዝሮ ከመዘገባቸው ጳጳሳት ጋር የሐዋርያት የስልጣን ሽግግር አስተምሕሮ በዚያ ዘመን በቤተክርስቲያን ውስጥ ስር ሰዶ ተተከለ። ይህ ሽግግር ወይም መተካካት እነርሱ እውነት ብለው ለተቀበሉት ትምሕርት ተተኪ የባለአደራነት ሰንሰለትን ለማበጀት አስፈላጊ ነበረ። አይሬንየስ ደግሞ ስለ ሽማግሌዎች (ፕሬስቢተርስ) መተካካት መናገርም አስፈላጊ ነው ብሎ አመነ። ነገር ግን ስለ ሽማግሌዎች መተካካት የተናገረው ስለ ጳጳሳት መተካካት የተነገረውን ያህል በቁም ነገር አልተሰማለትም።

በ258 ዓ.ም. የሞተው ተደማጭነት ያለው የቤተክርስቲያን ጸሐፊ ሳይፕራያን የተባለው የካርቴጅ ጳጳስ በቤተክርስቲያን ላይ ጳጳሳት ያላቸው ስልጣን ይጨመር ብሎ ጻፈ፤ እንዲህ ሲል፡-
“ቤተክርስቲያን እናት ያልሆነችለት ማንኛውም ሰው እግዚአብሔር አባት ሊሆንለት አይችልም።”

ቤተክርስቲያን እናትህ መሆን የምትችለው የቤተክርስቲያንን ጳጳስ ከታዘዝክ ብቻ ነው።

አይሬንየስ በተጨማሪ እንዲህ አለ፡- ኒቆላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ በሐዋርያቱ ከተሾሙ ሰባት ዲያቆናት የአንዱ የኒቆላዎስ ተከታዮች ናቸው። እነርሱም ያለምንም ገደብ ደስ ያላቸውን እያደረጉ ይኖራሉ አለ። ይህን በማለቱ ሙሉ በሙሉ ስቷል። ክርስቲያኖች እውነት በሚመስሉ ያልተረጋገጡ ወሬዎች በቀላሉ ለመታለል የተጋለጡ ናቸው።

ጳጳሳት ከጉባኤው በላይ ከፍ ያሉ መሪዎች ሆነው መተካካታቸው የኒቆላውያን መገለጫ ነው። በዚህ መንገድ የሁለተኛው ዘመን ቤተክርስቲያን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሐዋርያት ከመሰረቱት መንገድ ፈቀቅ ብላ መውጣት ጀመረች። የሐዋርያቱ የመጀመሪያ ብርሃን እየደበዘዘ መጣ።

ሁለተኛው መቅረዝ ተለኩሶ ነበር። ግን የዚህኛው ዘመን ብርሃን ከመጀመሪያው ዘመን የተለየ እና ደብዘዝ ያለ ሆነ።

በሮማውያን ነገስታት አማካኝነት የተነሳው ከባድ ስደት በግዛቱ ውስጥ ያሉ ኃይላት ሊያጠፉዋት ከሚችሉት ይበልጥ ቤተክርስቲያንን በአስገራሚ ፍጥነት አሳደጋት። አሳዳጆች እና ክርስቲያኖች መከራ ሲቀበሉ ቆመው ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እየተለወጡ የክርስቲያኖችን ቁጥሩ አበዙ።

በክርስቲያኖች ላይ በ64 ዓ.ም. በኔሮ ተጀምረው እስከ 312 ዓ.ም. የዘለቁ አሥር አሰቃቂ ስደቶች ውስጥ ወደ ሦስት ሚሊዮን ክርስቲያኖች ተገድለዋል።

ብዙዎቹ እነዚህ ጨካኝ የሮማ ገዥዎች የነገሱት በሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ነው። 312 ዓ.ም አካባቢ ሰይጣን አንድ ትምሕርት ሳይወድ በግዱ ተማረ፡- ይህም የትኛውም ምድራዊ ኃይል ቤተክርስቲያንን ከውጭ በማጥቃት ክርስትናን ሊደመስስ አይችልም።

የሮማ ግዛት ቀስ በቀስ ቤተክርስቲያኖችን ለማጥቃት ትጥቆ ወደመነሳት የተሳበ ሲሆን በስተመጨረሻ የንጉስ ኃይል በሙሉ በአንድነት ተሰባስቦ ቤተክርስቲያን ለማጥፋት እስኪሰማራ ድረስ ጥቃቱ እየተባባሰ መጣ፤ በዚህም የተነሳ ቤተክርስቲያን በአስቸኳይ እርዳታና ድጋፍ አስፈለጋት። የሮም ቤተክርስቲያን በዚህ ጊዜ ይሰደዱ ለነበሩ ለብዙ ክርስቲያኖች ድጋፍ የመስጠት አቅም ነበራት፤ እነዚያም ክርስቲያኖች የሮም ቤተክርስቲያንን እንደ ተንከባካቢ እናት ማየት ጀመሩ።

ራዕይ 2፡8 በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል፦

ይህ ዘመን መሞት በጣም ቀላል የሆነበት ዘመን ነበር። የሃምሳ ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የሃያ ዓመታት ወረራ እና ከጀርመን ባርቤሪያኖች ጋር የድንበር ጦርነቶች እንዲሁም ከፋርስ ሰራዊት ጋር ውግያ ሲደረግ ነበር። በሮማውያን ነገስታትም ብዙ ጭካኔ የሞላባቸው ስደተች ተነስተዋል።

ሰምርኔስ መር (ከርቤ) ከሚለው ቃል የመጣ ስም ሲሆን ትርጉሙም አስከሬኖችን ለማድረቅ የሚያገለግል ከዛፍ ግንድ የሚወጣ መራራ ዘይት ማለት ነው።

ስለዚህ ኢየሱስ በዚህ ዘመን ውስጥ የሚገደሉትን ብዙዎችን ከራሱ ሞት በመጀመር ከዚያም እራሱን ሕያው ሆኖ ወዳሳየበት ወደ ትንሳኤው በማመልከት ያጽናናቸዋል። ሞት ለክርስቲያን አስፈሪ መሆን የለበትም ምክንያቱም ሞት ንሰሃ ለገባ ክርስቲያን የሰማይና እና የዘላለም ሕይወትን በር ይከፍትለታል። ኢየሱስ የመጀመሪያም የመጨረሻም ነው፤ ማለትም ስደቶች ሲነሱ አማኞች በሚገደሉበት ቦታ ቀድሞ በመገኘት በሚያልፉበት መከራ ውስጥ የሚበረታቸው እርሱ ነው፤ ከዚያ ቦታ መጨረሻ ላይ የሚሄደውም እርሱ ነው። ስለዚህ ብቻውን የሚሞት ክርስቲያን የለም። ኢየሱስ ለዓለም ሳይታይ አብሮነቱ ግን ሁልጊዜም ከእኛ ጋር ነው።

እርሱ የመጀመሪያም የመጨረሻም ነው። የመጨረሻዎቹ ክርስቲያኖች እንደ መጀመሪያዎቹ እንዲሆኑ ይፈልጋል ምክንያቱም እርሱ አይለወጥም።

ዕብራውያን 13፡8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።

ነገር ግን ይህ ሁለተኛ ዘመን የክርስቲያኖች የመጨረሻ ዘመን አልነበረም፤ ምክንያቱም ክርስቲያኖች ከአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን እየራቁ ነበር።

ራዕይ 2፡9 መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፥ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ የሰይጣንም ማኅበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ፦ አይሁድ ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ።

እነዚህ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ገንዘብ ድሆች ነበሩ ነገር ግን በእምነት ባለጠጎች ነበሩ ምክንያቱም ሞት ቢያስከትልባቸውም እንኳ ለእግዚአብሔር ቃል እውነት ቆመዋል። በዚህ ምድር ለጥቂት ጊዜ መከራ ተቀብለዋል፤ ነገር ግን በሚቀጥለው ሕይወት ለዘላለም የማይቆጠር ሃብት ተቀምጦላቸዋል። ስለዚህ ለጊዜው በምድር ላይ ስለሚያጡዋቸው ነገሮች አንዳችም ጸጸት የላቸውም ምክንያቱም በሰማያት የሚጠብቃቸው ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው። ልክ ለመውለድ እንደምታምጥ ሴት ነገር ግን ልጅዋን አቅፋ ስታየው በምጥ ውስጥ የነበረውን ሕመምና ስቃይ እንደምትረሳው ማለት ነው።

እነዚህ ክርስቲያኖች በጣም አስተዋዮች ነበሩ። በምድር ላይ ሃብት አከማችተው ቢሆን ኖሮ ስግብግቦቹ የሮማ ገዥዎች ንብረታቸውን ይዘርፉዋቸው ነበር፤ እነርሱም በዚያም ሆነ በዚህ ባዶዋቸውን ይቀሩ ነበር። የእምነታቸው ሃብት ግን የሌቦች ነገስታት እጅ ቆፍሮ ማግኘት በማይችለው ቦታ ነበር።

ሲገድሉዋቸው በቀላሉ በሰማያት ለዘላለም ማንም የማይነካው ሃብታቸው ወዳለበት ሊወርሱ ሄዱ። ይህ ዘመን ምስጋናን የሚያውቁ ሰዎች የነበሩበት ዘመን ነው። በጣም ጥቂት ንብረት ብቻ ነበራቸው ነገር ግን የሚረባቸው ምን እንደሆነ የሚያዩበት ብዙ ማስተዋል ነበራቸው።

ድሆች ነበሩ እግዚአብሔር ግን አልነቀፋቸውም። ይህ በጣም ጠቃሚ ትምሕርት ያስተምረናል። በአንጻሩ የመጨረሻው ዘመን ውስጥ ያለችዋ ቤተክርስቲያን ሎዶቂያ ሃብታም ነች እግዚአብሔር ግን አንዳችም አያሞግሳትም። ስለዚህ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ የሳትነው ምንድነው?
ምኩራብ ስብሰባ ወይም የመሰብሰቢያ ቦታ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ በሆነ መንገድ ሰዎች ሲሰባሰቡ የሚሰበስባቸው ሰይጣን ነው።

ኢሳያስ 54፡15 እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤

ስለዚህ ሰይጣን ትኩረቱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ የቤተክርስቲያን ስርዓት መመስረት ላይ አደረገ።

የእውነትን ቃል የተቀበሉት የመጀመሪያዎቹ አሥራ ሁለት ሐዋርያት አይሁድ ነበሩ። አይሁድ ነኝ የሚሉ ሰዎች የመጀመሪያውን እውነት ይዣለሁ ማለታቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ውሸታሞች እንደነበሩ ይናገራል። ውሸት ተናግረህ ለረጅም ጊዜ በተናገርከው ውሸት ጸንተህ ብትቆም በስተመጨረሻ ሰዎች ያምኑሃል። ስለዚህ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በውሸት መሰረት ላይ ታንጻ ወደ ስልጣን ለመውጣት ተዘጋጀች።

የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ሲጠናቀቅ ክርስቲያኖች የኒቆላውያንን ሐሰተኛ ትምሕርት ተቀብለው ነው የተጠናቀቀው፤ ይህም አንድን ሰው ከጉባኤው በላይ ከፍ ማድረግ ማለት ነው። እንደዚህ አይነቱ ሰው የሰው አመለካከትና አመራርን በቤተክርስቲያን ላይ ይጭናል። ይህ ውሸት እያንዳንዱዋ ቤተክርስቲያን ካሕን ወይም አንድ የሚያስተዳድራት ሽማግሌ ያስፈልጋታል የሚል ሲሆን፤ እያንዳንዱ ከተማ ደግሞ በውስጡ ያሉትን ካሕናት የሚያስተዳድር አንድ ጳጳስ ያስፈልገዋል የሚል ነው። እንግዲህ የዘመኑ ታላቅ ሰው አይሬንየስ እንኳ ሳይቀር በ178 ዓ.ም. የልዮንስ ከተማ ጳጳስ እስከመሆን ድረስ ተታለለ። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ማንም ሰው የከተማ ጳጳስ የመሆን ስልጣንን ይዞ አያውቅም። ነገር ግን ይህ ልማድ ሐዋርያው ዮሐንስ በ100 ዓ.ም. አካባቢ እንደሞተ ወዲያው ራሱን የአንጾኪያ ጳጳስ ብሎ በሾመው በኢግናሺየስ ተጀመረ።

ስሕተት ወደ ሁሉ ሥፍራ ተሰራጨ፤ ክርስቲያኖችም ስሕተትን በሌላ በሚበልጥ ስሕተት ለመዋጋት ወሰኑ፤ ይህም “የሐዋርያት መተካካት” ይባላል። ትክክለኛው እምነት የአንድ ከተማ ጳጳስ ዘንድ ነው ያለው ተባለ፤ እርሱም ስልጣኑን ከእርሱ በፊት ከነበሩ ጳጳሳት ነው የወረሰው እነርሱም ወደ ኋላ ታሪካቸው ሲጠና ስልጣናቸውን የተቀበሉት በዚያ ከተማ ውስጥ ቤተክርስቲያንን ከመሰረተ ከመጀመሪያ ሐዋርያ ነው ተባለ። ይህ ሰው ሰራሽ ስርዓት የሚያዋጣ ይመስላል ግን ትልቅ እንከን ነበረው። እንደ ልዮንስ እና ቱርስ የመሳሰሉ ብዙ የፈረንሳይ ከተሞች አንድም ሐዋርያ ጎብኝቷቸው ባያውቅም ለእውነት ጽኑ አቋም እንዳላቸው አሳይተዋል። ሮም ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጥቂት ጊዜ የቆየባት ከተማ ናት ግን ከጊዜ በኋላ የጋለሞቶች እናት ሆናለች። እንደ ኤፌሶን ያሉ አንዳንድ ከተሞች ወደቡ በጭቃ እየተሞላ ስለነበረ በ170 ዓ.ም. አካባቢ ጠፍተዋል።

ይህ የሐዋርያት መተካካት የተባለ አስተምሕሮ የሮም ከተሞችን (ጳውሎስ በስተመጨረሻ የሄደበት)፣ አንጾኪያ፣ ኢየሩሳሌም፣ አሌግዛንድሪያ (ማርቆስ በዚያ ነበረ ይላሉ) በሌሎች በትንንሽ ከተሞች ውስጥ ባሉ ቤተክርስቲያኖች ዘንድ ትልቅ ስፍራ እንዲኖቸው አድርጓል ምክንያቱም እነዚህ ከተሞች ትልልቅና ሃብታሞች ነበሩ። ይህ አንድን ጳጳስ ከሌላ የሚያስበልጡበት አሰራር መጽሐፍ ቅዱሳዊ አልነበረም። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የማይደግፈው ስርዓት ከዚያ ወዲያ የተነሳው ንጉስ ኮንስታንቲን የኮንስታንቲኖፕልን ከተማ ሲሰራ ሊቀጥል ችሏል። የኮንስታንቲኖፕል ከተማ ጳጳስም ከሮም ጳጳስ፣ ከአንጾኪያ፣ ከኢየሩሳሌምና ከአሌግዛንድሪያ ጳጳሳት ጋር እኩል ስልጣን ይኖረዋል። ምክንያቱም ኮንስታንቲኖፕል የምሥራቃዊው የሮማ ግዛት ዋና ከተማ ስትሆን ከምዕራባዊቷ ሮም ይበልጥ ሃብታም ነበረች ከዚያም በላይ ውስጧ የሚኖረው የንጉስ ድጋፍም ነበራት። ነገር ግን አንድም ሐዋርያ ኮንስታንቲኖፕል ሄዶ አያውቅም ምክንያቱም ከተማይቱ ከ330 ዓ.ም. በፊት ገና አልተቆረቆረችም ነበር። ከዚያም በላይ አረቦች በ634 ዓ.ም. ከመሃመድ ሞት በኋላ ከአረቢያ በረሃ ወጥተው ወረራ ሲጀምሩ በፍጥነት የአንጾኪያ፣ ኢየሩሳሌም፣ እና አሌግዛንድሪያ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል። ሙስሊሞች እነዚህን ታላላቅ ከተሞች ሲቆጣጠሩ በውስጣቸው የነበሩ ቤተክርስቲያኖች ጠፉ። ከዚያ ሮም እና ኮንስታነቲኖፕል ብቻ ቀሩ። ስለዚህ በዚህ ጊዜ በምዕራብ ያሉ ሁሉ ዓይናቸው ሮም ላይ ሆነ ምክንያቱም ከሐዋርያዊ ስልጣን አለኝ የምትል ብቸኛ ቤተክርስቲያን ነበረች። በዚያ ቀውጢ ዘመን እውነተኞቹ ቤተክርስቲያኖች አንድ ቦታ ብቅ ብለው ይጠፉና መንፈስ ቅዱስ በግለሰቦች ልብ እንደሚሰራበት አሰራር እንደገና ሌላ ቦታ ብቅ ይሉ ነበር። ነገር ገን ለሐሰተኛው ሐርግ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የማይነጥፍ ምንጭ ሆነችለት። የሮማ ግዛት ሲፈራርስ ሳትፈርስ የቀረችው ብቸኛ ድርጅት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብቻ ነበረች። ሐዋርያዊ የስልጣን ሽግግር በዓለም ዘንድ ለሮም ትልቅ ከበሬታና ተቀባይነትን ሰጣት። በ400 ዓ.ም. አካባቢ ፖፕ የሆነው የሮማ ጳጳስ ገዥነቱን በሌሎች ጳጳሳት ላይ መጫን ጀመረ። በ606 ዓ.ም. ራሱን የዓለም ሁሉ ጳጳስ አድርጎ አወጀ ምክንያቱም በምዕራቡ ግዛት ውስጥ በሮም ያልተቋረጠ የጳጳሳት የስልጣንን ርክክብ ሰንሰለት እንዳለው ማሳየት የሚችል ብቸኛ ጳጳስ እርሱ ነበረ። እነዚህም ስልጣን ለእርሱ ያስረከቡት የሮም ጳጳሳት አንድ በአንድ ወደ ኋላ ሲቆጠሩ አመጣጣቸው ሮም ውስጥ የነበረ ሐዋርያጋ ይደርሳሉ። ስለዚህ በሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን እውነትን እየተነሱ ከነበሩ ብዙ የአስተምሕሮ ስሕተቶች ለመከላከል ተብሎ የተፈጠረው የሐዋርያዊ ስልጣን ሽግግር ወይም መተካካት የተባለ አስተምሕሮ አሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታላቂቱ ጋለሞታ የተባለችዋን አንዲት ታላቅ የቤተክርስቲያን ድርጅትን ወለደ። እንዲህ ነው መፍትሄ ያመጣል ተብሎ የተፈጠረ የሰው ሃሳብ። በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ለመጽናት መለማመድ አለብን። እግዚአብሔርን ለመርዳት ብለን የራሳችንን ጥሩ ሃሳቦች ስናመጣ አብራሃም እስማኤልን ከመውለዱ በምንም የማይሻል ሥራ ውስጥ እንገባለን። ከእስማኤልም የአረብ ሙስሊሞች እንዲሁም ዝሬ ብዙ ግፍ የሚፈጽሙ የሙስሊም ጽንፈኞች ተወለዱ። ስሕተት ሁልጊዜም ይኖራል። ዛሬ እያንዳንዳቸው እኔ ልክ ነኝ የሚሉ ከ45000 በላይ ልዩ ልዩ ቤተክርስቲያኖች በምድር ላይ አሉ። እነዚህ ሁሉ የየራሳቸውን መብራት መድረክ ላይ ሲያበሩ የሚያስከትሉት ውጤት በመብራታቸው ብዛት ዓይናችንን ማሳወር ነው። ስለዚህ እርስ በርሳቸው ከሚጋጩ ብዙ መብራቶችና አመለካከቶች የተነሳ ዓይናችን በርቶልናል ብለን ስናስብ በእርግጥ የጨለማ ዘመን ውስጥ ገብተናል።

እውነትን ማግኘት የምንችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፤ ወይም ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ከኪንግ ጄምስ ባይብል ብቻ ነው። ያላችሁባት ቤተክርስቲያን ትክክለኛ የመሆን እድሏ ከ45000 ውስጥ አንድ እድል ነው። ቤተክርስቲያኖቻችን በሙሉ እውሮች ናቸው ብሎ ማመን ይቀላል ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ስለ ሎዶቂያ ቤተክርስቲያን የሚናገረው እንደዚያ ብሎ ነው።

ራዕይ 3፡14 በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦

17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥

የሮማው ጳጳስ በሌሎች ጳጳሳት ላይ ስልጣን አለኝ ማለቱ ቀስ በቀስ ነው እውቅና እያገኘ የሄደው። ሌሎችን መግዛትና ተቃዋሚዎችን እንደ ብረት ለጠነከረው አገዛዝዋ እስኪንበረከኩ መጨፍለቅ የሮም መንፈስ ነው።

ከ91 እስከ 100 ዓ.ም. ድረስ ክሌመንት ለቆሮንቶስ በሮም ቤተክርስቲያን ስም ጽፎላቸዋል ግን ሲጽፍላቸው በእነርሱ ላይ አንዳችም የሊቀጳጳስነት ስልጣን እንዳለው ሳያመለክት ነው።

የሮም ጳጳስ አኒሴተስ (ከ154 እስከ 168 ዓ.ም.) ፖሊካርፕ የፋሲካን ቀን ሙሉ ጨረቃ ከምትታይበት ከኒሳን 14 ወደ ሌላ ቀን እንዲቀይር ለማደረግ ሊያሳምነው ባደረገው ሙከራ አልተሳካለትም።

ቪክቶር የተባለው የሮም ጳጳስ (190-202 ዓ.ም) የምሥራቅ ቤተክርስቲያኖችን የፋሲካን ቀን ከኒሳን 14 ወደ ሌላ ቀን ካልቀየራችሁ ብሎ ሲዝትባቸው ነበር። የሮም ቤተክርስቲያን አይሁዶችን “የክርስቶስ ገዳዮች” በማለት ፋሲካን አይሁዶች በሚያከብሩበት በኒሳን 14 ቀን ማክበርን እምቢ አለች። የሮም ቤተክርስቲያን ይህንን አቋሟን በሌሎች ቤተክርስቲያኖችም ላይ ልትጭን ፈለገች። (ዛሬም ቢሆን ፋሲካን የምናከብረው ብዙውን ጊዜ በሙሉ ጨረቃ አይደለም።) ነገር ግን የዚያን ጊዜ የልዮንስ ጳጳስ አይሬንየስ ሌሎችን ቤተክርስቲያኖች እንደፈለገ በአምባገነንነት ሊገዛ የፈለገውን ቪክቶርን ገስጾታል።

የሮም ጳጳስ ስቲቨን 1ኛው (253-257) በሰሜን አፍሪካ ውስጥ ጥምቀትን በተመለከተ የተፈጠረ ግጭት ውስጥ ገብቶ ሊፈታ ሞከረ ነገር ግን የካርቴጁ ጳጳስ ሳይፕራያን እያንዳንዱ ጳጳስ በራሱ ከተማ ላሉት ቤተክርስቲያኖች አለቃ ነውና ጣልቃ አትግባ፤ ዞር በል አለው።

ስለዚህ በዚህ በሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የሮማው ጳጳስ ቀጥታ ከጳውሎስ እና ከጴጥሮስ የተረከብኩት ተልእኮ አለኝ በማለት የስልጣኑን መሰረት ለራሱ አጸና። ሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በጀመረ ጊዜ ሰው ሁሉ ጵጥሮስ ሮም ውስጥ ነው የተገደለው የሚለውን የሐሰት ወሬ አምኖ ተቀብሏል።

እንደውም አይሬንየስም ጭምር የሮማው ጳጳስ እውነትን በባለአደራነት ተቀብሎ የያዘ እንደሆነ አምኗል፤ በዚህም አይሬንየስ ትልቅ ስሕተት ሰርቷል።

ስለዚህ በሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የሮማው ጳጳስ በሌሎች ጳጳሶች ላይ ስልጣኑን ሊጭን እየታገለ ነበር።

ግን ከ400 ዓ.ም. በኋላ ወዲያው የባርቤሪያውያን ቫንዳሎች ሰሜን አፍሪካ ውስጥ የምትገኘውን ካርቴጅን ወረሩ፤ በ476 ዓ.ም. ደግሞ የመጨረሻው የምዕራባዊቷ የሮም ግዛት ንጉስ በባርቤሪያውያን አማካኝነት ከስልጣን ወረደ። ከዚያ ተከትሎ በመጣው ብጥብጥና ሁከት ውስጥ ክርስቲያኖች ለአመራር እና ለገንዘብ ድጋፍ ወደ ሮማው ጳጳስ መመልከትን መረጡ። በዚያ ጊዜ ማንኛውንም የሰው አመራር እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለመቀበል ዝግጁ ነበሩ። ቤተክርስቲያን በአጠቃላይ በአዲስ ኪዳን አስተምሕሮዎች ላይ የነበራትን እምነት አጥታለች። በየቦታው የተበታተኑ ትንንሽ የክርስቲያን ቡድኖች በእግዚአብሔር ቃል ዙሪያ ይሰባሰቡ ነበር። ብዙዎቹ ግን ጎልታ ወደምትታየው በሮማው ጳጳስ ስልጣን ስር በማእከላዊነት ወደተደራጀችው ትልቅ የቤተክርስቲያን ድርጅት ይሄዱ ነበር።

ለሮማው ጳጳስ የሮማ ግዛትን ባፈራረሱት በባርቤሪያውያን ነገዶች ላይ ታላቅ ስልጣን ሊያጎናጽፈው የሚችል ሌላም የተጋነነ የሐሰት ወሬ በዚሁ ዘመን እየተቀነባበረ ነበር።

የሮማ ጳጳስ ካሊክስተስ 1ኛ (218-223 ዓ.ም.) የቤተክርስቲያን “ዓለት” ጴጥሮስ ነው ስለዚህ የሮማው ጳጳስም የቤተክርስቲያን ዓለት ነው ብሎ ለማወጅ የመጀመሪያው ሰው ነበር። በዚያን ጊዜም ታዋቂው ክርስቲያን ጸሐፊና የካርቴጅ ጳጳስ ተርቱሊያን ካሊክስተስን ስልጣን ነጣቂ ብሎ ጠራው።

ነገር ግን የሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ሁከት፣ ብዙ ነፍስ ግድያ እና ግርግር ያመጣው የገንዘብ እጥረትና ግራ መጋባት እየተባባሰ ሄዶ በጣም ብዙ ጳጳሳትና ቤተክርስቲያኖች ተቸግረው ከሮም ቤተክርስቲያን ድጋፍ እና እርዳታ እንዲቀበሉ እንዲሁም የሮማውን ጳጳስ እንደ መሪያቸው እንዲመለከቱ አስገደዳቸው።

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የሮም ቤተክርስቲያን እጅግ የተዋጣለትን ታለቁን ውሸቷን ለማጽናት ተሳካላት -- ይህም ውሸት እንዲህ የሚል ነበር፡- “የመንግስተ ሰማያት በር መክፈቻ ቁልፍ ያለው በጴጥሮስ እጅ ነው፤ ጴጥሮስም ይህንን ስልጣን ለሮማ ጳጳሳት አስተላልፏል፤ ከዚህም በኋላ ማን ወደ መንግስተ ሰማያት ይገባ ወይ አይገባ እንደሆን የመቆጣጠር ስልጣን በሮማ ጳጳሳት እጅ ነው።” ይህም ሐሰት ለሮማው ጳጳስ ታላቅ ስልጣን አጎናጸፈው።

የሮማ ቤተክርስቲያን ይህንን ብልጣ ብልጥ ሃሳብ ቀስ በቀስ እየገነባች በመሄድ ዝናዋን እጅግ አሳደገችው፤ በተለይም ክርስቲያን ባልሆኑ ፓጋንስ ወይም አረማውያን ዘንድ።

ፔትር (Petr) በግብጽ ውስጥ ካሕን ለማለት የሚጠቀሙት ቃል ሲሆን ትርጉሙም የአማልክትን ምስጢር የሚተረጉም ሰው ማለት ነው።

ፔትር ሮማ (Petr Roma) የጥንታዊ ግሪኮችን ኤልዩሲናያን ምስጢራት መፍቻ እና ማምለኪያ መጽሐፍ ነው እነዚህም ምስጢራት በብዙ በአረማውያን ዘንድ ትልቅ ስፍራ ነበራቸው። ኤልዩሲስ ከአቴንስ አጠገብ የነበረች ከተማ ናት። ስለዚህ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጴጥሮስ የመጀመሪያው የሮም ጳጳስ ነበረ የሚለውን የሐሰት ወሬ ማሰራጨት ጀመረች።

ይህም የሐሰት ወሬ “የሮማው ጴጥሮስ” የሚለው መጠሪያ “ፔትር ሮማ” ከሚለው ስያሜ ጋር ያለውን ትልቅ የድምጽና የቃላት ተነሳሳይነት በመጠቀም የተመሰረተ ነው። በዚህም ምክንያት አረማውያን ጴጥሮስ ታላቁ የአረማውያን ኤልዩሳያን ምስጢር ፈቺ መስሏቸው በቀላሉ ይቀበሉታል።

ጴጥሮስ ራሱ ግን ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 12 በኋላ አልተጠቀሰም። ከዚያ ወዲያ ጴጥሮስ የአይሁድ ሐዋርያ እንደነበረ እና ከባቢሎን ተቀምጦ ከጻፋቸው ሁለት መልእክቶች በስተቀር በታሪክ ውስጥ ሁለተኛ አናየውም።

ታላቂቱ ባቢሎን የሚለው ስም ከክርስትና በፊት አረማዊ የነበረችዋን ሮም አመላካች ወይም መጠሪያ አልነበረም።

ቀይ ልብስ የተጎናጸፈችዋ ሴት ማለትም ታላቂቱ ባቢሎን የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት፤ እርሷም ጳጳስዋ በሮም ከተማ ያሉትን ክርስቲያኖች መግዛት ይችል ዘንድ መጀመሪያ በቂ የሆነ ስልጣን ማግኘት አስፈልጓታል። ይህም የሚሆነው በ250 ዓ.ም. አካባቢ ነው። ከዚያም ታላቂቱ ባቢሎንን ለመሆን የባቢሎንን ምስጢራት የራሷ ይፋዊ እምነት አድርጋ መቀበል አለባት፤ ይህም በ325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባኤ ነው የተጀመረው። ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዓመታት ውስጥ የክርስትና ቃላትን ከአረማውያን የጣኦት አምልኮ ጋር ማስታረቅ ተጀመረ፤ ለምሳሌ የፀሃይ አምላክ የተወለደበት ቀን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ የተወለደበት ቀን ተደረገ። ከብቶች እንዲወልዱላቸው እና የእርሻቸው ሰብል እንዲያፈራላቸው ኢሽታር ለምትባለዋ አምላክ አምልኮ የሚያደርጉባቸው ጥንቸሎች እና እንቁላሎች የፋሲካ እንቁላሎች እና ጥንቸሎች ሆነው መጡ። ይህ በክርስትና እምነት እና በአረማዊነት መካከል የተፈጸመ ጋብቻ በ450 ዓ.ም. ለፖፕ ሊዮ 1ኛ ፖንቲፍ የሚለውን ማዕረግ ለራሱ እንዲጠቀም አመቸው፤ ፖንቲፍ የባቢሎናውያን የምሥጢር ሥርዓት የሚያገለግል ሊቀካሕን ነው።

ከዚያም በአውሬው ላይ የተቀመተችውን ሴት ለመሆንና በአውሬው ላይ ስልጣንን ለመጎናጸፍ ጳጳሱ በሮም ከተማ ላይ ፖለቲካዊ ስልጣንን ጨምሮ መያዝ አስፈልጎታል፤ ይህም ሊሳካ የሚችለው ምዕራባዊው የሮም ገዥ በ476 ዓ.ም. ከስልጣን ከወረደ በኋላ ነው። ከዚያ በኋላ ብቻ ነው ሮም ታላቂቱ ባቢሎን ሆነች ማለት የሚቻለው።

ኢየሱስ ጴጥሮስ እንደሚገደል ትንቢት መናገሩን እናውቃለን። አፈታሪክ ጴጥሮስ የተገደለው በመስቀል ተሰቅሎ ነው ይላል። አንዳንዶች ጴጥሮስ እራሱ ተዘቅዝቆ እንዲሰቀል ጠይቋል ይላሉ ግን ይህ እውነት እንደሆን የታሪክ ምሑራን ማረጋገጥ አልቻሉም። በጣም የሚያሳዝነው የጴጥሮስን የመጨረሻ እድሜ በተመለከተ ጠጨባጭ ማስረጃዎች የማይገኙ ሲሆን አፈታሪኮች ግን እጅግ ሞልተዋል። “The Popes, a history” በተሰኘው መጽሐፉ የታሪክ ምሑር ጆን ዩልየስ ኖርዊች በገጽ 4 እንዲህ ይላል፡- “አንድ ነገር ብቻ ማለት እንችላለን፤ ይህም በሁለተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ (በ150 ዓ.ም. አካባቢ) ጴጥሮስንና ጳውሎስን በአካል ያወቋቸው ሰዎች የልጅ ልጅ ልጆች በኖሩበት ዘመን ውስጥ ጴጥሮስም ጳውሎስም ሮም ውስጥ እንደተገደሉ እንዲሁ ይታመን ነበር።”

ጴጥሮስ ሮም ውስጥ ነው የተገደለው የሚለውን ንግግር ማረጋገጫ የሚሆን አንድም ታሪካዊ ማስረጃ የለም። ጴጥሮስ ሮም ውስጥ ነው የተገደለው የሚለው ወሬ ሰዎች ለብዙ ዓመታት ያለማቋረጥ ስለደጋገሙት ብቻ እንደ እውነት ተቀባይነትን ያገኘ ውሸት ነው። ዛሬም ክርስቲያኖች ሁልጊዜ ሰብዓ ሰገል ወደ በረት ውስጥ ገቡ የሚለውን ውሸት ያለማቋረጥ ይደጋግሙታል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ሰብዓ ሰገል እቤት ውስጥ ገቡ ነው የሚለው። ሰው ሁሉ በረት ውስጥ ገቡ የሚለውን ወሬ ከመደጋገሙ የተነሳ ይህ ውሸት እንደ እውነት ተቀባይነት አግኝቶ ይኖራል። አንድን ውሸት ብዙ ጊዜ ብትደጋግሙት እንደ እውነት ተቀባይነት እንደሚያገኝ ፕሮፓጋንዲስቶች ሁሉ ያውቃሉ።

ማቴዎስ 2፡11 ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።

ስለዚህ ለምንድነው ጴጥሮስ ሮም ውስጥ ነበር ብለው ለማሳመን ይህን ሁሉ መከራ የሚበሉት? ወሬው ታሪካዊ ማስረጃ የለውም።

ጳውሎስ ለሮሜ በጻፈው መልእክቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ውስጥ ቢያንስ ለ28 ሰዎች ሰላምታ ያቀርባል። ነገር ግን ጴጥሮስን አንዴም እንኳ አይጠቅሰውም። ስለዚህ በግልጽ እንደምንረዳው ጴጥሮስ የሮም ጳጳስ ሊሆን ይቅርና ጭራሽ ሮም ውስጥ እንኳ አልነበረም። ጴጥሮስ ጳጳስ ነበረ የሚል ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም የለም።

ማቴዎስ 8፡14 ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤

ጴጥሮስ ባለትዳር ነበረ። የሮም ጳጳሶች ማግባት አይፈቀድላቸውም። ስለዚህ ጴጥሮስ የመጀመሪያው የሮማ ጳጳስ ወይም ፖፕ ነበር ማለት ስሕተት ነው።
የሮም ጠላቶች በአደባባይ ይገደሉና ራሳቸው በፍጥነት የሚፈሰው ታይበር ወንዝ ውስጥ ይወረወር ነበር። አንድ “ወንጀለኛ” ሐዋርያ በተለይም ከፓለስታይን የመጣ ያልተማረ ዓሣ አጥማጅ ሮም ውስጥ በክብር ሊቀበር አይችልም። ጴጥሮስ ጭራሽም ወደ ሮም መጥቶ ስለማያውቅ ሮም ውስጥ ሊሞት አይችልም።

ስለዚህ ጴጥሮስ ሮም ውስጥ የመጀመሪያው ፖፕ ነበር ብሎ መናገር ማስረጃ የሌለው መሰረተ ቢስ ወሬ ነው።

ነገር ግን ሮም በችግር እና በስደት ወቅት እንዲሁ የመሪነትን ሚና እንድትጫወት የሚያደርጋት የሆነ ልዩ ድባብ ነበራት። በዚህ በሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ሮማውያን ገዥዎች በክርስቲያኖች ላይ ከረር ያለ ስደት አስነሱባቸው። የሮም ቤተክርስቲያን ደግሞ ሰዎችን የምትረዳበት ብዙ ሃብት ስለነበራት ራሷን ለመግለጥ የወቅቱን ችግር እንደ እድል ተጠቀመችበት።

ሐዋርያው ዮሐንስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ መካተት ያለባቸውን መጻሕፍት መርጦ ከጨረሰ በኋላ በ100 ዓ.ም. አካባቢ ሞተ። ከዚያም በኋላ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የነበሩ ቤተክርስቲያኖች የክርስቲያኖችን ቤተክርስቲያኖች የመምራቱን ስልጣን ለመያዝ መፎካከር ጀመሩ። አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች የሚመሩት በሽማግሌዎች ሕብረት ነበር፤ እነዚህም ሽማግሌዎች ቤተክርስቲያኖች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተጻፈው የሐዋርያት መንገድ ፈቀቅ እንዳይሉ ይጠብቋቸው ነበር።

Shepherd of Hermas በሚል ርዕስ ሮም ውስጥ ከ100 ዓ.ም. በኋላ የተጻፈ ጥናታዊ ጽሑፍ ሁልጊዜ “የቤተክርስቲያን መመሪያዎች” ወይም “የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች” እያለ ይናገራል።

የታሪክ ማስረጃዎችን ብንመለከት በዚህ ዘመን ውስጥ ብዙም አስተማማኝ ባይሆኑም እንኳ የመጀመሪያው የሮም ጳጳስ ሆኖ የምናገኘው አኒሴተስ ነው፤ ከ155 እስከ 166 ዓ.ም.። ነገር ግን ሮም ብዙ የቤተክርስቲያናት ሕብረቶች ነበሩዋት፤ ደግሞም አንድን ሰው የሮም ጳጳስ አድርገው በሁሉ ላይ ስልጣን ሰጥተው መሾም ገና እስከ 250 ዓ.ም. ድረስ እንኳ አልተጀመረም።

በ70 ዓ.ም. ብዙዎቹ ሐዋርያት ተገድለዋል አለዚያም ደግሞ ከሮም ግዛት ድንበር ውጭ ተሰደው ሄደዋል፤ ኢየሩሳሌምም ከአንድ ሚሊዮን በላይ አይሁዳውያንን በገደሉት የሮማውያን ሰራዊት አማካኝነት ፈራርሳለች። ከዚያ በኋላ ለክርስትና እምነት ማዕከል ተደርጎ የሚቆጠር ከተማ አልነበረም። ግን ስልጣን የሚፈልጉ የቤተክርስቲያን መሪዎች ቀስ በቀስ ኃይላቸውን እያጠናከሩ ነበር።

የሮም ቤተክርስቲያን የሮማ ግዛት ዋና ከተማ ውስጥ በመገኘትዋ የተነሳ ብቻ በቤተክርስቲያኖች መካከል የታላቅነትን ስፍራ ልታገኝ ችላለች።

ከ180 ዓ.ም በኋላ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ጭንቀትና ስጋት ተስፋፍቶ ነበር። የሮማ መንግስት በአምባገነናዊ ኃይል መግዛትን መረጠ። አይበገሬ የጀርመን ጎሳዎች በዳኑብ ወንዝ ድንበር አካባቢ የሚቀሰቅሱዋቸው ጦርነቶች ሮም ላይ ከባድ ወጪ በማስከተል ሮም በግዛቶችዋ ላይ ከባድና አስጨናቂ ግብር እንድትጥል አስገደዱዋት። በምስራቅ በኩል የነበሩት ፓርሲያን የሮም ቀንደኛ ጠላቶች ከእነርሱ የባሰ አደገኛ በሆኑት በፋርሶች ተተኩ። በዚህ የጭንቅ ዘመን ላይ ደግሞ የ50 ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነትና የበሽታ ወረርሽኝ ተጨመረባቸው። ከ240-260 ዓ.ም. የባርቤሪያን ጀርመኖች ወረራ እየተባባሰ ቀጠለ። የገንዘብ ዋጋ ወደቀ፤ የዋጋ ንረትም እያሻቀበ ሄደ። ይህ ሁሉ መቅሰፍት በክርስቲያኖች ላይ ተሳበበ፤ ስለዚህም ክርስቲያኖች በብዙ መከራ ተቀጡ ደግሞም ብዙዎች ተገደሉ። ከዚያም በእርስ በርስ ጦርነት አማካኝነት የሮማ ግዛት ለአጭር ጊዜ በሦስት ተከፈለ። ከዚያ በኋላ ኦሬሊያን የተባለ የፈረሰኛ ኮማንደር ንጉስ ሆነና ግዛቱን መልሶ አንድ አደረገ። ይህንን ድል በማስመልከት በ274 ዓ.ም. ዲሴምበር 25ን እሱ የሚያመልከው የፀሃይ አምላክ ልደት ቀን ተብሎ እንዲከበር ወሰነ።

የፀሃይ አምላክን ማምለክ አረማዊነት ሮም ውስጥ በይፋ እንዲያንሰራራ አደረገ።

ዲዮክሊቲያን በ284 ዓ.ም. ነገሰ። ከእርሱ በፊት ከተሰሩ ቤተመንግስቶች ሁሉ በዋጋም በውበትም ወደር የሌላቸውን ቤተመንግስቶስ ሰራ፤ የመንግስት ሰራተኞችን ቁጥር ጨመረ የሰራዊቱንም ቁጥር እጥፍ አደረገ። ይህ ሁሉ የሕዝቡን ወገብ የሚሰብር ከባድ ግብር አስከተለ። ዲዮክሊቲያን ፍጹም አምባገነናዊ መንግስት በመመስረት የሕዝቡን ማሕበራዊ ኑሮ፣ ባሕል እና ፖለቲካ በሙሉ በራሱ ቁጥጥር ስር አደረገ። በዚህ ሁሉ ላይ ጨምሮ ክርስቲያኖችን በሙሉ በማጥፋት ሕዝቡን በአረማውያን አማልክት ዙሪያ በማሰባሰብ ሐይማኖታቸውንም መቆጣጠር ፈለገ። በ303 ዓ.ም. አካባቢ ከቀደሙት ሁሉ እጅግ የከፋ ስደት እና በግዛቱ ውስጥ ሁሉ እያንዳንዱን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥፋት ዘመቻ ጀመረ። ከሁለት ዓመታት በኋላ በ305 ዓ.ም. ከስልጣኑ ወረደ፤ ነገር ግን እርሱ የጀመራቸው ከባድ ስደቶች ከእርሱ በኋላ ለስምንት ዓመታት እስከ 312 ዓ.ም. ድረስ ዘለቁ።

በዚህ የግፍና የነፍስ ግድያ ዘመን የሮማ ቤተክርስቲያን በባርቤሪያውያን ወራሪዎች አማካኝነት ወይም በእርስ በርስ ጦርነት ወይም በስደት ምክንያት ጥቃት ይደርስባቸው የነበሩትን ቤተክርስቲያኖች በደግነት ትረዳቸው ነበር። እነዚህ አጋጣሚዎች ብዙዎቹ ቤተክርስቲያኖች በሮም ያለችዋን ቤተክርስቲያን ረዳታቸው እንዲሁም መሪያቸው አድርገው እንዲመለከቱ አደረጋቸው። ማንም ሰው በተቸገርን ጊዜ በገንዘብ ቢረዳን ያንን ሰው አለቃችን አድርገን ለመቀበል ምንም አይከብደንም፤ ደግሞም ያለ አንዳች ቅሬታ ያለምንም ማጉረምረም ልንታዘዘው ፈቃደኛ እንሆናለን።

የግሪክ ፈላስፎች ከአረማውያን ሐይማኖታዊ ልማዶች እና ሥርዓቶች በስተጀርባ ያሉትን “ምስጢሮች” ይመረምሩ ነበር። ክርስቲያኖች ደግሞ የአረማውያንን አስተሳሰቦች ከክርስትና አስተምሕሮ ጋር ለመቀላቀል የግሪክ ፍልስፍናን መጠቀም ጀመሩ። ቤተክርስቲያን ይህንን ስሕተት ለመከላከል ብላ ከሰው የሆነ የአመራር ሥርዓት አበጀች፤ ይህም ቤተክርስቲያን ላይ ሊከላለከሉ ከሚያስቡት ስሕተትም የከፋ አሉታዊ ተጽእኖ አመጣ። የኒቆላውያን ትምሕርት አንድን ቅዱስ ሰው ከጉባኤው በላይ ከፍ የማድረግ ሥርዓት ነው፤ ይህም ስርዓት በቤተክርስቲያን ላይ ያልተፈለገ ለውጥን ይዞ መጣ። ካሕናት እንያንዳንዱን ቤተክርስቲያን እንዲያስተዳድሩ ተሾሙ፤ ጳጳሳት ደግሞ በካሕናቱ ላይ ተሾሙ። የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን በ170 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ አንድ ጳጳስ በአንድ ከተማ እና በዙሪያው ላሉ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ የበላይ ተደርጎ የተሾመበት የስልጣን ተዋረድ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተደራጅቶ ነበር። ይህንንም ተከትሎ እውነት የከተማይቱን ቤተክርስቲያን ከመሰረተው ሐዋርያ ስልጣን እየተረከቡ እየተተካኩ ከመጡ ጳጳሳት ስልጣን ተረክቦ በተሾመ አንድ ጳጳስ ዘንድ ብቻ ነው ያለው የሚል ሃሳብ መጣ።

በ250 ዓ.ም. የሮም ቤተክርስቲያን ሃብት እጅግ አድጎ ነበር። ስለዚህ 1500 ባልቴቶችንና ችግርተኛ ሰዎችን ይረዱ ነበር፤ ይህም መልካም ነው።

የቤተክርስቲያኒቱ ራስ ለሆነው ለጳጰሱ፣ ለ46 ሽማግሌዎች፣ ለሰባት ዲያቆናት፣ ለ42 ረዳት ዲያቆናት፣ ለ52 አጋንንት አስወጪዎች፣ ለአንባቢዎች እና ለበር ጠባቂዎች መተዳደሪያቸውን ይሰጡዋቸው ነበር። በዚህም መንገድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ቅርጽ ያለው ድርጅት ተፈጠረ በፍጥነት እያደገ ሄደ።

በብዙ አደጋዎች ለተሞሉ ጥቂት ዓመታት ብቻ የነገሰው ንጉስ ዴሲየስ በ250 ዓ.ም. በክርስቲያኖች ላይ የመረረ ስደት አስነሳ። ብዙ ስደተኛ ጳጳሳት ከተለያዩ ከተሞች ሸሽተው ወደ ሮም ገቡ፤ በዚህችም ሰፊ ከተማ ውስጥ ለመደበቅና ከሮም ቤተክርስቲያን ድጋፍ ለማግኘት አመቻቸው። በሮም ያለችዋ ቤተክርስቲያን አማኞችን እንዲሁም የማያምኑትንም ሲቸገሩ በብዙ ትረዳቸው ነበር። ይህም የሮም ቤተክርስቲያንን ዝናዋን አገነነው።

በ260 ዓ.ም ንጉስ ጋሌኒየስ ክርስቲያኖችን እንዲቀበሉዋቸውና እንዳያሳድዷቸው አዋጅ አሳወጀ። ሰዎች ሊሞቱ ሲሉ በኑዛዜያቸው ገንዘብና መሬት ለሮም ቤተክርስቲያን ለውረስ መናዘዝ ጀመሩ። የቤተክርስቲያንም ሃብት እየጨመረ ሄደ። በዚህም የተነሳ በሮማ ግዛት ውስጥ ብዙ ቤተክርስቲያኖችን መርዳት ቻሉ፤ ቤተክርስቲያኖችም በተለይም በዚህ አስጊ ዘመን ውስጥ ስደት እና የገንዘብ እጥረት በበዛበት ወቅት በሮም ያለችዋን ቤተክርስቲያን እንደ መሪ መመልከት ጀመሩ።

በዚያኑ ጊዜ የሮም ቤተክርስቲያን ያለችበት ከተማ እና የወቅቱ ሁኔታዎች እንዲሁ እየሰጡዋት የነበረውን የታላቅነት ቦታ እና ክብር የምታጸናበት ምክንያት እየፈለገች ነበር። ደግሞም ጴጥሮስ ሮም ውስጥ እንደነበረ ሰዎችን አታለው ማሳመን ቢሳካላቸው ከዚያ ወዲያ ለዓላማቸው መጠቀም የሚችሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስም ነበረ።

ማቴዎስ 16፡18 እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።

19 የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።

ሮም አረማዊ ከተማ ነበረች። ጴጥሮስ የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻዎች መያዙ በሮም ውስጥ ባሉ አረማውያን መካከል ለብዙ እድሎች በር መክፈት ይችላል። ጴጥሮስ የመንግስተ ሰማያትን በሮች ቢከፍትላቸው አረማውያን ደስ እያላቸው ጴጥሮስን ያገለግሉታል።

እንደ አይሬንየስ ያሉ ታላላቅ ሰዎች የሐዋርያዊ ስልጣን ሽግግር የተባለውን ስሕተት ካጸኑት በኋላ የሮም ጳጳስ በቀላሉ የጴጥሮስ ተተኪ ነኝ ብሎ ማወጅ ቁልፎቹን የመጠቀም ስልጣን አለኝ ማለትም ይችላል። ሌሎች ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያት ቁልፎች አልተሰጣቸውም። ስለዚህ የሮም ጳጳስ የጴጥሮስ ተተኪ እንደመሆኑ ከሌሎች ጳጳሳት ሁሉ ታላቅ ይሆናል። ከዚያም የሰዎች ነፍስ መዳንም የሚወሰነው በኢየሱስ ሳይሆን የመንግስተ ሰማያትን በር መክፈት በሚችለው በሮም ጳጳስ ፈቃድ ይሆናል። ይህ በጣም ድንቅ የሆነ የማጭበርበሪያ ስልት ነው።

ፔትር ሮማ (ሲነበብ “የሮማው ጴጥሮስ” እንደሚል አይነት ድምጽ የሚሰጥ መጠሪያ) የኤልዩሲናያን ምስጢራትን ለማምለክ የሚያገለግል ሐይማኖታዊ መጽሐፍ ነበር፤ መጽሐፉም ከአርጤምስ ጋር ዝምድና ያለው ሲሆን እርሷም ዳያና የምትባለው የአረማውያን አምላክ ናት። እነዚህም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ700 ዓመተ ዓለም ጀምሮ የነበሩ የጥንታዊ ግሪኮች የአምልኮ ስርዓቶች ሲሆኑ ኋላ ወደ ሮም ሄደዋል። እነዚህ ምስጢራት በአረማውያን ዘንድ በስፋት የሚታወቁ ነበሩ፤ ስለዚህ አረማውያን ጴጥሮስ ሮም ውስጥ ነበረ ብለው ካመኑ ጴጥሮስ ፔትር ሮማ ወይም የአረማውያን ምስጢራት ተርጓሚ ነው ስለዚህ የሰማያትን በር ይከፍታል ብለው ይቀበሉታል።

በተጨማሪም የኢየሱስ ንግግር ጴጥሮስን ለክርስቲያኖችም ጭምር የመንግስተ ሰማያትን ደጅ የሚከፍት ሰው አድርጎታል።

ስለዚህ የሮም ቤተክርስቲያን ጴጥሮስን ጠልፋ ወደ ሮም ማምጣት ከተሳካላት ትልቅ ማታለያ ዘዴ ይሆንላታል። በሮም ከተማ ውስጥ የተቀመጠው የአረማውያን ግሪኮች ምስጢራት ተርጓሚ እራሱ ደግሞ የክርስቲያኖች መንግስተ ሰማያትን ቁልፎች የያዘ ሰው ነበር።

የግሪክ ፍልስፍና በብልሃት የተሞላ ነው። ስለዚህ ግሪኮቹ የአረማውያንን ምስጢር አሳምረው ወልውለው ካቀረቡ በኋላ እጅግ ማራኪ እና አሳማኝ ውበት ይሰጡታል። አሁን ሮማውያን እነዚህን ሁሉ የግሪክ ምስጢራት ለአረማውያን የመተርጎም ሥራ አገኙ። ጴጥሮስ ደግሞ በታሪክ ሁሉ የመንግስተ ሰማያትን ቁልፎች የያዘ ብቸኛው ሰው ታላቁ ተርጓሚ ነበር።

ከዚህም ሌላ ከሮማውያን አማልክት ሁሉ ታላቅ አምላክ ጁፒተር ነበር። ስሙም ጁ-ፒተር ስለሆነ አሁንም ከፒተር ወይም ጴጥሮስ ጋር ይመሳሰላል።
ስለዚህ ፕሮፓጋንዳው ተጠናክሮ ተጀመረ። ጴጥሮስ ስለሞተ ተነስቶ ውሸታቸውን ማጋለጥ አይችልም። ጴጥሮስን ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 12 በኋላ የት እንደገባ አናገኘውም። ከሱ በኋላ የተነሳው ትውልድ ስለ ጴጥሮስ ሕይወት ጥርት ያለ መረጃ የለውም። የልጅ ልጆቻቸው ስለ ጴጥሮስ ሕይወት የነበራቸው እውቀት ከአያቶቻቸውም ያነሰ ነበር። የስደቶች ብዛት ቤተክርስቲያኖች ለእርዳታ ወደ ሮም እንዲመለከቱ ሲያደርግ እነዚህ የሮምን እርዳታ ይጠይቁ የነበሩ ክርስቲያኖች የሮም ቤተክርስቲያን ጴጥሮስ ሮም ውስጥ ነው የሞተው ስትላቸው ምንም ተቃውሞ አልነበራቸውም። በ250 ዓ.ም. አካባቢ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስዋ የከተማው ጳጳስ ነው ብላ ለማወጅ የሚበቃ ኃይል ነበራት። እነርሱ የሾሙት ሰው የሮም ከተማ ጳጳስ ከሆነ በኋላ ጴጥሮስ ደግሞ የመጀመሪያው የሮም ጳጳስ እንዲመስል ሮም ውስጥ የኖረበት ዓመት በሐሰት ተስተካክሎ ተመዘገበ። ከ70 ዓ.ም. በፊት ጴጥሮስ በሕይወት እያለ የአንድ ከተማ አስተዳዳሪ ሆኖ የሚያገለግል ጳጳስ አልነበረም። ጳጳስ ወይም አስተዳዳሪ ሽማግሌ ማለት ነበር። በያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሽማግሌዎች ነበሩ፤ እነርሱም ጳጳሳት ተብለው ይጠሩ ነበር። ለምሳሌ በፊልጵስዩስ ከተማ፡-

ፊልጵስዩስ 1፡1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤

ጴጥሮስ የመጀመሪያው የሮም ጳጳስ እንደነበረ ሰዎች ካመኑ በኋላ ከጴጥሮስ ጀምሮ በስልጣን ተዋረድ እና ቅደም ተከተል በጊዜው የነበረውን ጳጳስ ከጴጥሮስ ጋር ለማገናኘት ተብሎ በመሃል የነበሩ ጳጳሳት ስማቸው በፈጠራ ተዘርዝሮ ተመዘገበ። ሐዋርያዊ የስልጣን ሽግግር ይህ ነው። የጥንት ሮማ ጳጳሳት ስም ዝርዝር እርስ በርሳቸው በሚጣረሱ የተለያዩ መዝገቦች ውስጥ ይገኛል፤ ስለዚህ የጳጳሳት መተካካት ከመጀመሪያው ጀምሮ አጠራጣሪ ሰነድ ነው ያለው።

ነገር ግን ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ይህ ከጴጥሮስ የጀመረው የጳጳሳት የስልጣን ቅብብሎሽ ቆይቶ “ሐዋርያዊ መተካካት” የሚባለውን የተዋጣለት ትምሕርት ወለደ። በዚያ ጊዜ የነበረው የሮም ጳጳስ ለጴጥሮስ የተሰጠው የመንግስተ ሰማያትን በር የመክፈት ስልጣን ከጴጥሮስ ቀጥሎ ለተተኩት ለሮም ጳጳሳት ተላልፏል አለ።

ይህም ሃሳብ ወዲያው ለሮም ጳጳስ ታላቅ ስልጣንና ክብር ሰጠው። የመንግስተ ሰማያትን በር ሊከፍትላችሁ የሚችል በምድር ላይ ብቸኛው ሰው ነው። ነገር ግን የእርሱን ትምሕርትና እምነት ካልተቀበላችሁ በስተቀር የመንስተ ሰማያትን በር አይከፍትላችሁም። ከዚያም በላይ እምነታችሁን ወይም እናንተን ከጠላ ደግሞ በሩን ይዘጋባችኋል፤ ከዚያም ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት አትችሉም። ይህ እንዴት ይሆናል? የሮም ጳጳስ በምድር ላይ የጴጥሮስ ተወካይ ነኝ አለ፤ ስለዚህ ጴጥሮስ በምድር ላይ የእርሱ ተወካይ የሆነው የሮማ ጳጳስ ለፈቀደላቸው ሰዎች ብቻ የመንግስተ ሰማያትን በር ይከፍትላቸዋል።

ስለዚህ የሮማው ጳጳስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የታላቅ ስልጣን ባለቤት ሆነ። የዘላለም እጣ ፈንታችሁ በእርሱ እጅ ነው። ይህ በጣም የሚያስፈራ ሃሳብ ነው።

ከ400 ዓ.ም. በኋላ የሮማ ጳጳስ ራሱን ፖፕ ብሎ ለመጥራት የሚበቃ ስልጣንና ኃይል በተጎናጸፈ ጊዜ ፖፕ የሚባለው ማዕረግም በዘመን ወደ ኋላ ተጎትቶ ተወሰደና ጴጥሮስ የመጀመሪያው ፖፕ ነበር ተባለ።

እንግዲህ የሮም ፖፕስ በምድር ታሪክ ውስጥ ከሁሉም በላይ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ የአምባገነን መሪዎች ስርወ መንግስት ናቸው።

ራዕይ 17፡8 ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ።

የዚህ ታላቅና ኃይለኛ የሮማን ካቶሊክ ፖለቲካዊና ሐይማኖታዊ ሥርዓት ወይም ድርጅት ራስ ፖፑ ወይም አውሬው ነው። በታሪክ ውስጥ በማኝኛውም ዘመን አንድ ፖፕ ቤተክርስቲያንን ይመራ ነበረ ከዚያ ይሞታል ስለዚህ የለም ነገር ግን አለ ምክንያቱም አዲስ ፖፕ በቦታው እንዲተካ ተመርጦ ይሾማል። ስለዚህ የፖፕስ መተካካት ይቀጥላል። የስልጣናቸው መሰረት በምድር ላይ የጴጥሮስ ወኪሎች ነን ብለው ማወጃቸው እና የመንግስተ ሰማያትን በር ለመክፈት ወይም ለመዝጋት ቁልፉን ተቀብለናል ማለታቸው ነው።

አስቀድሞ የነበረው፤ አሁንም የሌለው ነገር ግን ያለው አውሬ (የሐዋርያዊ ስልጣን መተካካት)

በሰማያዊ ቀለም የተሳሉት ጳጳሶች ባለፉ ዘመናት የነበሩ ጳጳሳትን ይወክላሉ። ቀዩ ደግሞ አሁን በቅርብ የነበረውን ነገር ግን በመሞቱ የተነሳ የሌለውን ጳጳስ ይወክላሉ። ከፊት የቆመው በጥቁር ቀለም የተሳለው ደግሞ አሁን ያለውን ጳጳስ ይክላል እርሱም በቅርቡ የተመረጠ በመሆኑ አለ።

የጳጳሳቱ መተካካት ረጅም ተምዘግዛጊ እባብ ይመስላል፤ ይህም እባብ ራስ እስኪያገኝ ድረስ እየተጠባበቀ ነው፤ ራሱም በታላቁ መከራ ጊዜ የሚገለጠው ዋነኛው የክርስቶስ ተቃዋሚ ፖፕ ነው። ወደፊት ሲገለጥ ምናልባት ራሱን ፖፕ ጴጥሮስ 2ኛው ብሎ ይጠራ ይሆናል።

ምን ያህል ከመጽሐፍ ቅዱስ እየራቁ እንደሄዱ ልብ በሉ። ኢየሱስ የመንግስተ ሰማያት በር ነው፤ ጴጥሮስ ግን ቁልፎቹ በእጁ ስለሆኑ በሩን የመክፈትም ሆነ የመዝጋት ስልጣን የጴጥሮስ ነው። ጴጥሮስም ፖፑ ያዘዘውን ብቻ ነው የሚያደርገው።

ስለዚህ ሰዎችን ማዳን የኢየሱስ ስልጣን አይደለም። እንደ በር ጠባቂ እጣ ፈንታችሁን በእጁ የያዘው ጴጥሮስ ነው። እንደውም እጣ ፈንታችሁን በእጁ የያዘው የሮማው ጳጳስ ፖፑ ነው ምክንያቱም ለጴጥሮስ ምን እንዲያደርግ የሚነግረው እርሱ ነው። ሰይጣን የኢየሱስን ማዳን ከዓይናቸው በመሰወር በታላቅ ስሕተት አስቷቸዋል።

እንግዲህ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ቁልፎችን እና በሰማያት የማሰር እና የመፍታት ስልጣን ሲሰጠው ምን ማለቱ ነው?

የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
39 የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው።

ንሰሃ የመንግስተ ሰማያትን በር ይከፍታል። ከዚያም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠምቀን የክርስቶስ ሙሽራ አካል እንሆናለን፤ ምክንያቱም ሙሽራ በባሏ ስም ትጠራለች።

ከዚያም ጴጥሮስ የዮሐንስን ጥምቀት በር ቆለፈው ምክያቱም የዮሐንስ ጥምቀት አስፈላጊነቱ አበቅቷል።

ነገር ግን ንሰሃ እና በኢየሱስ ስም መጠመቅ የመንግስተ ሰማያትን በር የሚከፍት ቁል ቁልፍ በመሆኑ ሰይጣን በዚህ ቁልፍ ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ። ከልብ የእውነት ንሰሃ ገብቶ ከሐጥያት መመለስን፤ በዚህም መንገድ በክርስቶስ ዳግመኛ መወለድን፤ ኢየሱስንም ከሐጥያት መንገድ የሚመልስና የአማኙን ሕይወት የሚቆጣጠር የግል አዳኝ አድርጎ መቀበለን የማይሰብኩ ቤተክርስቲያኖች ተነሱ። ንሰሃ የመንግስተ ሰማያትን በር የሚከፍት ቁልፍ ነው።

ነገር ግን አንዲት ሙሽራ እና እንቅልፍ የተኛች ድንግል አሉ፤ ሁለቱም ደግሞ ድነዋል።

ግን ሙሽራዋ ብቻ ናት ለጌታ ዳግም ምጻት የተዘጋጀችው፤ ምክንያቱም በጥምቀት የኢየሱስ ክርስቶስን ስም የተቀበለችው ሙሽራዋ ብቻ ናት። ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጣ በስሙ በመጠመቅ በእርሱ ስም የተጠራችውን ሚስቱን ብቻ ነው ወደ ቤቱ ይዞ የሚሄደው። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቀችውን አይደለም ይዞ የሚሄደው። ስለዚህ ሰይጣን ሆን ብሎ ጥቃት የሚሰነዝረው በእግዚአብሔር ሰብዓዊ ስም ላይ ነው፤ ይህም ስም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሰይጣን የኢየሱስን ክብር ቀንሶ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ አድርጎ ሊያስቀረው ፈለገ። በዚህም መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በውሃ ጥምቀት ጊዜ መጥራት ቀረ፤ ከዚያም በሦስት የማእረግ መጠሪያዎች ተተካ።

ሌላው የሚገርመው ነገር ደግሞ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጴጥሮስ ያዘዘውን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ማጥመቅ እምቢ ብለው ግን የመጀመሪያው ፍጹም የማይሳሳት የሮም ፖፕ ነው ብለው ማወጃቸው ነው።

እውነቱን እንነግራችኋለን አሉ ግን ዋሹ። እውነት የሚነገረው መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ ብቻ ነው እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል እንደወደዱ በመለወጥ አይደለም።

ዮሐንስ 17፡17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።

ራዕይ 2፡10 ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።

ይህ የቤተክርስቲያን ዘመን በእግዚአብሔር ሃሳብ ውስጥ የሚፈጸም ዓላማ ነበረው። ምንም አይነት ግፍና ጭካኔ ቢደርስባቸውም እንኳ በኢየሱስ በማመን መጽናት ነበረባቸው። በምድር ላይ በሕይወት የቆዩት የተድላ ኑሮን ለማጣጣም አልነበረም። ደስታቸውና ተድላቸው በቀጣዩ ሕይወት ነው የሚሆነው። ሞት፣ ጥፋት፣ እና መከራ የክርስትናን እምነት ሊያጠፉ እንደማይችሉ ለሰይጣን ማሳየት ነበረባቸው። ሰይጣን እነርሱን አጠፋለው ብሎ በአንድ ጊዜ የብዙዎችን ደም በማፍሰስ ተጠመደ። ተደጋጋሚ ስደትና መከራ እንደ ማዕበል በላያቸው ላይ አለፈ። ነገር ግን እያንዳንዱ ማዕበል ካለፈ በኋላ እውነተኞቹ አማኞች በእውነተኛው ዓለት ላይ ቆመው ተገኙ፤ ዓለቱም ለእያንዳንዱ አማኝ በግሉ የሚሰጠው የኢየሱስ ማንነት መገለጥ ነው።

በእግዚአብሔር ቃል ላይ የታመነ ልብ ባለው ክርስቲያን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲኖርበት ይህንን ክርስቲያን በማንኛውም አይነት ጥቃት ውስጥ ሳይወድቅ በጽናት ያሳልፈዋል። እያንዳንዱ የማስፈራራት ማእበል ካለፈ በኋላ ሳይጠፉ የሚቀሩት ሰዎች ጥቃቱ ከተጀመረበት ጊዜ ይልቅ በርተተው መገኘታቸውን ሰይጣን ሲያይ ግራ ተጋባ። የሰማእታቱ ደም ቤተክርስቲያን ተመልሳ እንድትበቅል የሚያደርግ የቤተክርስቲያን ዘር ነበር።

እነዚህ ክርስቲያኖች ሞት ማለት በሰማያት ወዳለው የተሻለ ሕይወት የሚሻገሩበት ክፍት በር መሆኑን ተረድተዋል። ሊገደሉ ሲወሰዱ ያለምንም ፍርሃት በአስደናቂ እምነት እና ልበ ሙሉነት ነበር የሚሄዱት፤ የዚህም መሰረቱ ለኢየሱስ እና ለቃሉ ያላቸው ፍቅር ነው።

የአስሩ ቀን መከራ የተባለው ለመጨረሻ ጊዜ በዲዮክሌቲያን አማካኝነት ከ303 እስከ 313 ዓ.ም. ለአስር ዓመታት የተነሳው ስደት ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ቀን አንድ ዓመትን ይወክላል።

ዘፍጥረት 29፡27 ይህችንም ሳምንት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።

አንድ ሳምንት ሰባት ቀን ነው፤ ይህም የሰባት ዓመታት አገልግሎትን ይወክላል።

ያዕቆብ ሰባት ዓመታት አገለገለ እና ታላቅየዋን እሕት አገባ። ከዚያ ወዲያ ታናሽየዋን እሕት ለማግባት ተጨማሪ ሰባት ዓመታት አገልግል ተባለ።
ይህ ምን ያስረዳናል?

በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር አይሁዶችን በሰባት ዘመናት ውስጥ መራቸው፤ ይህም የጀመረው ሚስቱን ሳራን ሌላ ሰው እንዲያገባት አሳልፎ በመስጠት የቀደመ ፍቅሩን በተወው በአብራሃም ነው። ሁለተኛው ዘመን ዮሴፍ በወንድሞቹ የተነሳ መከራ ውስጥ ገብቶ እንደ ባሪያ ተሽጦ በሃሰት ተከስሶ ወደ ወኅኒ የወረደበት ጊዜ ነው። በሕይወት ዘመኑ በደረሰበት መከራና ፈተና ሁሉ ጸንቶ ሲቆም ሁሉም ነገር በእርሱ ላይ ጠላት ሆኖ ተነሳበት።

ከዚያም ሙሴ የሐይማኖት መሪው አሮን የወርቅ ጥጃ በሰራ ጊዜ የገንዘብ ፍቅርን የመቃወም ፈተና ገጠመው (ይህ የሚያስታውሳችሁ ነገር አለ?)።

ከዚያም ደግሞ የአይሁድ ሴቶችን የሚመስሉ ነገር ግን የእውነት አይሁድ ያልሆኑ ሞዓባውያን ሴቶችን (ቤተክርስቲያኖችን ይወክላሉ) በመጠቀም አይሁድን ካሳተው የበለዓም ትምሕርት ጋር ውግያ ገጠመ። በለዓማ ምን ማድረግ እንዳለበት ትዕዛዝ የተቀበለው ከፖለቲከኛ ከንጉስ ባላቅ ነው።

ኮንስታንቲን ወደ ንግስና የመጣ ፖለቲከኛ በ325 በተደረገው የኒቂያ ጉባኤ ላይ ቤተክርስቲያንን አሳተ፤ ከአረማዊነትና ከፖለቲካ ጋር እንዲጋቡ አደረገ። ጴርጋሞን ማለት ሙሉ በሙሉ የተጋባች ማለት ነው።

ከዚያም ኤልያስ በእስራኤል የጨለማ ዘመን ዘመን ውስጥ መጣ፤ በዚያ ዘመን እስራኤል ክፉ በሆነው ንጉስ አሃብ ከእርሱ የባሰ ክፉ በሆነችው ፊቷን በምትቀባው ሚስቱ በኤልዛቤል (በጨለማው ዘመን ትገዛ የነበረችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምሳሌ) አማካኝነት ወደ ጨለማ ጥልቅ ወርዳ ነበር። ትያጥሮን ማለት ጨቋኝ ሴት ማለት ነው።

እዝራ መቅደሱን ያደሰ ጊዜ የመቅደሱን መዝገብ (ሃብት) ሁሉ መለሰ። እውነተኛ ሃብታችን የሆነውን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የመዳንን ወንጌል ወደ እግዚአብሔር መቅደስ ወደ ቤተክርስቲያን መልሶ ያመጣውን ማርቲን ሉተርን ይወክላል። በዚህም ፕሮቴስታንቶች ከሮማ ካቶሊክ እጅ አመለጡ። ሰርዴስ ማለት ያመለጡ ማለት ነው።

ነህምያ ኢየሩሳሌምን የሚያጠናክሩ የከተማዋን ቅጥሮች መልሶ ገነባ። የክርስትና ጥንካሬ በወንድማማች ፍቅር (ፊላደልፊያ) ላይ የተመሰረተ ቅድስና እና ወንጌልን መስበክ ነው። ጆን ዌስሊ ኢንግላንድ ውስጥ ታላቁን የሚሽነሪ ዘመን መሰረት የጣለበትን እንቅስቃሴ ጀመረ።

ከዚያም በሰባተኛው የአይሁድ ዘመን መጥምቁ ዮሐንስ መጣና አይሁዶችን ሊያገባ የመጣውን መሲህ አስተዋወቀ። እነርሱ ግን አንቀበለውም ብለው ገደሉት። አይሁዶች እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ውስጥ እነርሱን ፈልጎ የሰራላቸው ታላቅየው እሕት ናቸው (ሴት ቤተክርስቲያንን ትወክላለች)። አሁን ደግሞ እንደገና ለታናሽየዋ እሕት ወይም ለቤተክርስቲያን ከአሕዛብ ለሆነችዋ ሙሽራ ሲል የሚሰራበት ዘመን ነው። እግዚአብሔር አሁንም የአሕዛብን ቤተክርስቲያን በሰባት የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ በማሳለፍ ወደ መጀመሪው የአዲስ ኪዳን አስተምሕሮ እስኪመልሳት ድረስ ይመራታል።

ራዕይ 2፡11 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም።

እያንዳንዱ ዘመን ቃሉ የሚለውን እንዲያደምጥ ታዟል። አሁን ካለህበት ሁኔታ ጋር እንዲጣጣምልህ ብለህ የእግዚአብሔርን ቃል አትለውጠው፤ ምክንያቱም ከለወጥከው የባሰ ትልቅ ስሕተት ትሰራለህ። በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ብትገባ እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ጸንተህ ቁም። ግፋ ቢል ብንሞት እንጂ ሌላ ምንም አይመጣም። ግን ይህ ሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ታሪክ በሙሉ ስለ ሞት እና ሞትም የእግዚአብሔር እቅድ አካል ስለመሆኑ ነው የሚናገረው። የሞት እና የሲኦል ቁልፍ በኢየሱስ እጅ ነው ያለው። ኢየሱስ ካልፈቀደ በቀር የሚሞት ክርስቲያን የለም። ኢየሱስ ፈቃድ ሲሰጥ የምንሞተው በእርሱ ፈቃድ ውስጥ ሆነን ነው፤ እንደዚህ በሞት ጭምር ስናከብረው የእኛ ራስ ወዳድ ፈቃድ በእርሱ ፈቃድ ተውጦ ፈቃዱ በእኛ ሲፈጸም ለእኛ ከሁሉ በላይ መልካም ነገር የሚሆንበት አንዱ መንገድ ነው።

በእሳት ባሕር ውስጥ የሚሆነው ሁለተኛው ሞት ለማሰብም እንኳ ይጨንቃል። አሁን በሕይወት ኖሬ ኋላ የእሳት ባሕር ውስጥ ከምገባ አሁን ሞቼ ኋላ መንግስተ ሰማያት ብገባ ይሻለኛል። ሁለተኛው ሞት ከሚባለው የእሳት ባሕር ጋር ሲነጻጸር በዚህ ሕይወት ውስጥ ለኢየሱስ መሞት ቀለል ያለ አማራጭ ነው። ለራስህ ብትሞትና ዳግመኛ ብትወለድ ከዚያም በአካል ስትሞት ያንን ሁለተኛ ሞት ብለህ መጥራት ትችላለህ። ስለዚህ ወደ እሳት ባሕር ውስጥ አትገባም ምክንያቱም ለሁለተኛ ጊዜ ሁለተኛውን ሞት መሞት ይሆንብሃል፤ ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።

ሁላችንም ሁለት ጊዜ መሞት አለብን።

ስለዚህ አንዴ ብቻ ከተወለድን ሁለት ጊዜ እንሞታለን። በአካል (የመጀመሪያው ሞት) ደግሞም በእሳት ባሕር (ሁለተኛው ሞት)።

ተወልደን ከዚያ ደግሞ ለራሳችን ብንሞት (የመጀመሪያ ሞት) እና ዳግመኛ ወይም ሁለተኛ ብንወለድ ከዚያ በኋላ በስጋ ስንሞት ሁለተኛ ሞት ይሆንልናል።

በዚህ በሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ሁለተኛው ሞት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ለራሳቸው የሞቱ (የመጀመሪያው ሞት) ከዚያም ዳግመኛ ተወልደው ሁለተኛውን ሞት የተጋፈጡ (በአካል) ሞት ሲመጣባቸው በልበ ሙሉነት ይጋፈጣሉ ምክንቱም ሊጎዳቸው እንደማይችል ያውቃሉ። ሁለተኛው ሞት የመንግስተ ሰማያትን በር ብቻ ይከፍትላቸዋል። ስለዚህ የእሳት ባሕርን አያዩትም፤ እርሱም ለማያምኑ ሰዎች ሁለተኛ ሞት ነው።

ሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የመከራ እና የሞት ዘመን ነው። በስንፍና እና በድሎት የመኖር እድል አልነበረም። ክርስቲያን መሆን በራሱ ከባድ ነበር። በዚያ ዘመን ሁከትና መከራ ውስጥ የግል ፍላጎቶች ፈጽመው ይጠፉ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ይህንን ዘመን በአንዳችም ነገር አለመውቀሱን ልብ ማለት አለብን።

እነዚያ ክርስቲያኖች ልክ እንደ እኛው ድካም ያለባቸው ሰዎች ነበሩ። እነርሱም ስሕተት ሰርተው ያውቃሉ። ነገር ግን አንድ መልካም ነገር በውስጣቸው ነበር፤ እርሱም ለራሳቸው ፈቃድ መሞታቸው ነው። የራስ ፈቃድ የሚያጠነጥነው በምቾትና የቁሳቁስ ሃብት በማከማቸት ላይ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ለኢየሱስ መከራ መቀበል ላይ ነበር ትኩረታቸው። ፈቃዱ የእነርሱን መሞት የሚጠይቅ ቢሆንም እንኳ ወደ ኋላ አይመለሱም ነበር። እርሱ እንዲያደርጉ የፈለገውን ሁሉ አደረጉ እንጂ እራሳቸው የፈለጉትን አይደለም።

ሚሊዮኖች ለእርሱ ሞቱ፤ እርሱም አንዳች እንኳ ስሕተት ሰሩ ብሎ አይጠቅስባቸውም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማስቀደም እግዚብሔርን ለማስደነቅ ዋነኛው ቁልፍ ነው።

ለእግዚአብሔር ፈቃድ እስከተገዛሁ ድረስ በሕይወቴ ምንስ ቢከሰት ምን ያስስበኛል። ይህ ነው የክርስትና ሚስጥር።

ሰይጣን ውጫዊ የሆነ ኃይልን በመጠቀም ቤተክርስቲያንን ማጥፋት አልተሳካለትም።

ከበድ ያለ ትምሕርት ከወሰደ በኋላ ለቀጣዩ ዘመን ዘዴውን ለውጦ እውነቱን በሚመስል ነገር ግን በተጭበረበረ ወንጌል ወደ ቤተክርስቲያን ሾልኮ ለመግባት ወሰነ።