ማቴዎስ ምዕራፍ 24 የሚተረጎመው በራዕይ ምዕራፍ 6 መሰረት ነው፤ ክፍል 1



ማቴዎስ ምዕራፍ 24 ከራዕይ ምዕራፍ 6 ጋር መስማማት አለበት፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች ሁሉ እርስ በራሳቸው ይስማማሉ።

First published on the 10th of March 2021 — Last updated on the 5th of November 2022

የራዕይ ምዕራፍ 6 የመጀመሪያዎቹ ሰባት ቁጥሮች ባለፉት 2,000 ዓመታት ውስጥ በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት በቤተክርስቲያን ውስጥ ሲደረጉ የነበሩ መንፈሳዊ ጦርነቶችን ይገልጣሉ። እያንዳንዱ ቁጥር አንድ የቤተክርስቲያን ዘመንን ይወክላል።

ቁጥር 8 አዲስ ሥርዓትን ይገልጣል፤ እርሱም ታላቁ መከራ ነው። እኛም ማምለጥ የሚያስፈልገን ከታላቁ መከራ ነው።

ራዕይ ምዕራፍ 4 ውስጥ በእግዚአብሔር ዙፋን ዙርያ አራት እንስሳት ይታያሉ።

 

 

የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ አራት እንስሳት (ኃይላት) ወይም ሕያዋን ፍጥረታት ሆኖ ይገለጣል። እያንዳንዱ እንስሳ የእግዚአብሔርን መንፈስ አንድ ገጽታ ይገልጣል፤ ይህም የእግዚአብሔር መንፈስ ገጽታ እግዚአብሔር በተለያዩት ዘመናት ቤተክርስቲያንን ለመምራትና ለመቆጣጠር የተጠቀመበት ነው። እግዚአብሔር በየጊዘው መልኩን እየቀያየረ ከሚገለጠው በፈረስ ላይ እንደሚጋልብ ሆኖ ከሚገለጠው ከተንኮለኛው የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ጋር ሲዋጋ ቆይቷል።

ይህ ፈረስ ጋላቢ ፈርኦን ሙሴን እንዲቃወም ያደረገው መንፈስ እራሱ ነው።

ዘጸአት 15፡1 በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።

የፈርኦን ወታደሮች በሰረገሎች ይሄዱ ነበር እንጂ ፈረስ አይጋልቡም።

ዘጸአት 14፡25 የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤

“ፈረሱ እና ፈረሰኛው” የሚለው ቃል የሚወክለው ፈርኦን የእግዚአብሔርን ቃል እንዲቃወም (የሚያምኑ ሰዎችንም ባሪያ እንዲያደርግና እንዲገድል) የሚገፋፋውን የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው የሚወክለው፤ በተቃራኒው ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያምን እና የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እንዲጽፍ ይመራው ነበር።

ይህ መንፈሳዊ ውግያ እስካሁንም እንዳለ ማወቅ አለብን። ፈርኦን ሰይጣንን የሚወክል ንጉስ ነበረ።

መዝሙር 136፡15 ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤

ከዚያ ወዲያ ሁሉ ሰላም የሆነ ይመስል ነበር። ግብጻውያኑ ሞቱ፤ ነገር ግን ይመራቸው የነበረው ሰይጣን አልሞተም።

ኋላ ዮሐንስ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ መልኩን ቀይሮ ከባሕር ሲወጣ አይቶታል።

ራዕይ 13፡1 አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ።

በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ በሰዎች ላይ ስልጣን የሚፈልግ አውሬ ሆኖ ነው የተገለጠው። ወደር የሌለው የሮማ መንግስት ጭካኔ፣ ግፍ እና ስግብግብነታቸው፣ ሕዝቦችን ሁሉ በእግራቸው እየረገጡ ግብር ያስገበሩበት ኃይል በ476 ዓ.ም በባርቤርያውያን አማካኝነት ጠፍቷል። ነገር ግን የሮም ግፈኛነት እና ወደር የሌለው ኃይል ከጠፋ በኋላ በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አማካኝነት ተመልሶ ተነስቷል።

 

 

ሰይጣን የመጀመሪያውን ፍልሰት የመራውን ሙሴን ተቃወመው፤ ሰይጣን ሙሴን የተቃወመው ሕዝቡ ሙሴ በአምስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ የጻፈውን ቃል ባመኑ ጊዜ ነበረ።

ከዚያ ደግሞ በመጀመሪያው ማሕተም ውስጥ ሰይጣን ሁለተኛውን ፍልሰት እየተቃወመ ነበር፤ ይህም ክርስቲያኖች ቅዱስ ጳውሎስ እና ሐዋርያት በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጻፉዋቸውን መልእክት በማመን ከይሁዲነት የወጡበት ፍልሰት ነው።

ልክ ፈርኦን አይሁዶችን ሊገድል እንደሞከረ ሁሉ ሰይጣንም ከ64 እስከ 312 ዓ.ም የሮም ነገስታት 3 ሚሊዮን ያህል ክርስቲያኖችን እንዲገድሉ አነሳሳቸው።

ከዚያ በኋላ በሁለተኛው ማሕተም ጊዜ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ትተው የሰውን ልማዶች፣ ፖለቲካ፣ የአሕዛብን እምነቶችና ሥርዓቶች እንዲሁም ሰዎች ስሕተትን ደግፈው በመከራከር ጎበዝ እንዲሆኑ የሚያደርገውን የግሪክ ፍልስፍና አመኑ።

ሶስተኛው ማሕተም እንደ ሉተር እና ዌስሊ የመሳሰሉ የተሃድሶ መሪዎችን ያሳያል፤ እነዚህ መሪዎች ቤተክርስቲያንን በከፊል ወደ ተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል መልሰዋታል፤ ቢሆንም ግን ከእነርሱ አገልግሎት በኋላ ስሕተት ከቤተክርስቲያን ውስጥ ሙሉ በሙሉ አልተወገደም።

አራተኛው ማሕተም ዛሬ እኛን ይመለከተናል፤ ምክንያቱም አሁን ያለንበትን ሰባተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን የሚገልጸው አራተኛው ማሕተም ነው። ኢየሱስም ከሌሎቹ የበለጠ ትኩረት የሚያደርገው በዚህኛው ማሕተም ላይ ነው።

ይህም ሶስተኛው ማሕተም ሲሆን በዚህ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን የምታምነው የክርስቶስ ሙሽራ ዲኖሚኔሽናዊ ከሆኑት የክርስቲያን ቤተክርስቲያኖች ወጥታ ትፈልሳለች፤ ቤተክርስቲያኖች ግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባልተጻፉ በሰው ሰራሽ ልማዶች እና አስተምሕሮዎች ተተብትባ ትቀራለች።

ይህ ዘመን የሚያበቃው ሞት የሐመር ቀለም ባለው ፈረስ ላይ ተቀምጦ በሚመጣበት ጊዜ በታላቁ መከራ ውስጥ ነው።

 

 

እንግዲህ መንፈሳዊው ጎዞ የሚጀምረው በዚህ መልክ ነው። ሁሉም ጦርነት ከባድ ስለሚሆን የእግዚአብሔርን ቃል የሙጥኝ ብለን መያዝ አለብን።

ራዕይ 4፡6 በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ። በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ፥ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ።

7 ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል።

በዙፋኑ ዙርያ አራት እንስሳት አሉ፤ እነዚህም እንስሳት ሥራቸው ሰይጣን በየጊዜው ልክ እንደ ቫይረስ መልኩን እና ባህሪውን እየለዋወጠ በሚመጣበት የተለያየ ዘመን ውስጥ ቤተክርስቲያንን መምራት እና ከክፉ መጠበቅ ነው።

የመጀመሪያው ማሕተም።

ራዕይ 6፡1 በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።

2 አየሁም፥ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት።

 

 

ቁጥር 1 እና 2 የሚወክሉት 1ኛውን እና 2ኛውን የቤተክርስቲያን ዘመኖች ነው፤ እነዚህም ዘመኖች ከ33 ዓ.ም ማለትም ከቀራንዮ ንጉስ ኮንስታንቲን ክርስቲያኖችን መግደል አስቁሞ ክርስትናን የሮማ ግዛት ይፋዊ ሐይማኖት እስካስደረገበት እስከ 312 ዓ.ም ዘልቀዋል።

ይህ ዘመን ከአራቱ እንስሳት በአንበሳው ነው የተወከለው እርሱም የእውነት ተምሳሌት ሲሆን በቅዱስ ጳውሎስ እና በሌሎቹ ሐዋርያት አማካኝነት የይሁዳ አንበሳ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የእውነት ቃል መሰበኩን ያመለክታል።

የእውነት ቃል እግዚአብሔር ለስሕተት የላከው መድሐኒት ነው። እግዚአብሔር የጥንቷን ቤተክርስቲያን በእውነት ቃል አማካኝነት ክትባት ሰጥቷታል።

በመጀመሪያ ክርስቲያኖች ሐዋርያት ባስተማሯቸው የአዲስ ኪዳን አስተምሕሮች ጸንተው ይኖሩ ነበር።

የዚህ መንፈሳዊ ውጊያ አንዱ ገጽታው ብዙ ክርስቲያኖች በአይሁድ መሪዎች መገረማቸው እና በአይሁድ እምነት ሕጎች እና ሥርዓቶች እየኖሩ ለመቀጠል መፈለጋቸው ነው።

ራዕይ 2፡9 መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፥ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ የሰይጣንም ማኅበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ፦ አይሁድ ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ።

ይህ መልእክት የተጻፈው ለሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ለሰምርኔስ ነው፤ ሰምርኔስ የሚለው ቃል በውስጡ ከርቤ የሚል ትርጉም የያዘ ሲሆን እርሱም ሙታን እንዳይሸቱ ለማድረግ የሚቀቡት ቅጠል ነው። ይህም በክርስቲያኖች ላይ በሮማውያን ነገስታት አማካኝነት የደረሰባቸውን ከባድ ስደት ያመለክታል። ይህ ጥቅስ አይሁዳውያን መሪዎች እስከዚያ ጊዜ ድረስ ትልቅ ተጽእኖ እንደነበራቸው ያሳያል። ክርስቲያኖች የአይሁድን ስርዓቶች እና ሕጎች መጠበቅ እስኪያቆሙ ድረስ ብዙ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። ብዙዎች ለመዳን በሕጉ ሥራዎች ላይ ይደገፉ ነበር።

ሰዎች ላይ ራሱን አክብዶ የሚጭን መሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ነገሮችን ቢናገር እንኳ ሕዝቡ በቀላሉ ይሰሙታል።

ስደቶች መብዛታቸው ቤተክርስቲያኖች ከመስመር እንዳይወጡ አድርጓቸው ነበር። በሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን መጨረሻ ግን በ312 ዓ.ም አካባቢ ንጉስ ኮንስታንቲን ክርስቲያኖችን ማሳደድ ባቆመ ጊዜ ክርስቲያኖች ከትክክለኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድ መንሸራተት ጀመሩ።

መከራ እና ስደት ጠንካራ ክርስቲያኖች ያደርጉናል።

ንጉስ ኔሮ ክርስቲያኖችን መግደል ከመጀመበት ከ64 ዓ.ም ጀምሮ 10 ተከታታይ ከባድ ስደቶች ተነስተዋል። የመጀመሪያው ስደት የተነሳው ኔሮ የሮምን ከተማ አቃጥሎ ያቃጠሉት ክርስቲያኖች ናቸው ባለ ጊዜ ነበር። እስከ 312 ዓ.ም ድረስ 3 ሚሊዮን ያህል ክርስቲያኖ ተገድለዋል። ክርስቲያኖችም ኮንስታንቲን በወሰደው እርምጃ ደስ ብሏቸው እርሱን እንደ መሪ ተቀብለው በፖለቲካ የተቃኘ ሐይማኖታዊ ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ ሲከተሉ (እንደ ሥላሴ፣ ክሪስማስ፣ እና ፖንቲፍ የመሳሰሉ ቃላትን በመቀበል) ከመጽሐፍ ቅዱስ ርቀው ሄዱ። ኮንስታንቲን ለሮም ጳጳስ ለሲልቬስተር ብዙ ገንዘብ፣ ሃብት እና የላተራንን ቤተመንግስት በስጦታ ያበረከተለት ጊዜ ሰው በምዕራባውያን ቤተክርስቲያኖች ውስጥ መሪ መሆን ጀመረ። በዚህም መንገድ ጠላት በነጭ (ሐይማኖታዊ) ፈረስ (ኃይል) ላይ ተቀምጦ፤ ደጋን ይዞ ነገር ግን ቀስት ሳይኖረው መጣ። ስለዚህ ሕዝቡን እያታለለ ነበር ማለት ነው። ይህም ስሕተትን የሚያስፋፋ የሐይማኖት አሳች ነው። ቀስተኛው በፍጥረታዊ ቀስት አልነበረም የሚጠቀመው። ይበልጥ ውጤታማ መሆን የቻለው ውሸቶቹን መበጠቀም ነው።

ኤርምያስ 9፡8 ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፤ ሽንገላን ይናገራሉ፤

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የመሰረታት በፈረሱ ላይ ተቀምጦ የሚመጣው የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው፤ እርሱም ክርስትናን በመጨቆን በስተመጨረሻ ፖፕ ኒኮላስ ቀዳማዊ (858 - 867) የተባለውን አምባገነን ሰው ያለ ልክ ከፍ ከፍ አድርጎ የፈላጭ ቆራጭ ስልጣን አጎናጽፎታል።

 

 

የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ቦታውን የያዘው በመጀመሪያዎቹ ሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናት ነው፤ ነገር ግን ሰዎችን ከሰው ሰራሽ ሃሳቦቻቸው ጋር የቤተክርስቲያን ራስ አድርጎ የመቀበሉ ሐይማኖታዊ ስሕተት ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ዘመናት አልፎ በቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ሁሉ ተሰራጭቷል። እንደ ፑርጋቶሪ፣ የስርየት ወረቀት፣ ጸበል፣ ቅዳሴ፣ ሕጻናትን ውሃ በመርጨት ማጥመቅ፣ ወደ ማርያም እና ወደ ሞቱ ቅዱሳን መጸለይ፣ የቅዱሳን ሃውልት፣ ዲኖሚኔሽኖች እና እናት ቤተክርስቲያን የመሳሰሉትን አዳዲስ ሃሳቦች እየጨመረ ብዙ ጊዜ መልኩን ለዋውጧል። እነዚህ ሁሉ የተጨማመሩ ሃሳቦች እስከዛሬ አብረውን አሉ፤ ደግሞም ሌሎች እየተጨመሩባቸው ነው።

ሁለተኛው ማሕተም።

ራዕይ 6፡3 ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።

4 ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፥ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።

 

 

ቁጥር 3 እና 4 የሚወክሉት 3ኛውን እና 4ኛውን የቤተክርስቲያን ዘመናት ሲሆን እነዚህም ዘመናት በ312 ዓ.ም ጀምረው ሉተር ተሃድሶውን እስከጀመረበት እስከ ጨለማው ዘመን መጠናቀቂያ እስከ 1520 ድረስ ዘልቀዋል። ይህም 1,200 ዓመታትን የፈጀ ረጅም ዘመን ነው። ጥጃው ወደ በሬነት የሚያድግበት በቂ ጊዜ አግኝቷል። በሬ ለስራ የሚሆን ብዙ ጉልበት እንጂ የሕይወት ዘር የለውም።

ቤተክርስቲያን በጨለማው ዘመን አልተሻሻለችም፤ ከመሻሻል ይልቅ ወደ አጉል እምነቶች፣ ፖለቲካዊ ሽኩቻዎች፣ እና ክፉ የሆኑ የመስቀል ዘመቻ ጦርነቶች እየዘቀጠች ነው የሄደችው። የመስቀል ዘመቻ ጦርነቶች ሕዝብን በጅምላ መጨፍጨፍ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዝርፊያ አስከትለዋል፤ (ወደ ፓለስታይን የሚያደርሰው መንገድ ላይ የነበሩ አይሁዶች ተዘርፈዋል) በተጨማሪ ፓለስታይን ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሙስሊሞችም ተዘርፈዋል። እነዚህ ዘመቻዎች ያስከተሉት ቁጣ እስከዛሬም ድረስ አለ። በዚያ ጊዜ የተፈጸሙ ግፎች ናቸው የእስልምና ጽንፈኞች እስከ ዛሬ ድረስ በምዕራባውያን ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ እንዲነሳሱ የሚያደርጓቸው።

መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ለመከተሉ የሞከሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን በዚያ በረጅሙ የጨለማ ዘመን ውስጥ ጸንተው ለማለፍ እጅግ በጣም ጠንካራ መሆን ያስፈልጋቸው ነበር፤ ምክንያቱም በዚያ ዘመን ለፖፑ በሚታዘዙ ጦር ሰራዊት አማካኝነት ሁል ጊዜ በተገኙበት ይገደሉ ነበር። ክርስቲያኖች በዚያ ከባድ ዘመን ውስጥ እየታገሉ በእምነታቸው ሲጸኑ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩት እንደ በሬ ይታረዱ ነበር። ማሕተሙ የሮማ ንጉስ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ኃይል ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ሕብረት ሲፈጥር ነበር ያሳየው። ኮንስታንቲን የሐይማኖት አፈንጋጮችን ከባድ ቅጣት ይቀጣቸው ነበር። ለሮም ጳጳስ ድጋፍ ያደርግለት ስለነበረ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ኃይል እና ስልጣን የተጠናከረው በወታደራዊ ኃይል ነበር። ፖፕ ሊዮ ቀዳማዊ (440 - 461) ፖንቲፍ የተባለውን የባቢሎናውያን ካሕናት ማዕረግ ተቀበለ። በተጨማሪም መናፍቃንን የመግደል ስልጣን አለኝ አለ፤ ይህም ፖሊሲ ኋላ 68 ሚሊዮን የሐይማኖት አፈንጋጮች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል፤ ግድያውም የቆመው ጀርመኒ ሙሉ በሙሉ የወደመችበት የሰላሳ ዓመታት ጦርነት በ1648 ዓ.ም ሲያበቃ ነው። ሰዎች በአካል በአሰቃቂና ጭካኔ በሞላበት ሁኔታ የተሰቃዩበት ሐይማኖታዊ ስደት ውስጥ በታኪክ ውስጥ በአስከፊነቱ ጎልቶ የሚታወቀው በእስፔይን ውስጥ የተደረገው ዘእስፓኒሽ ኢንክዊዚሽን የተባለው ግፍ ነው።

ሃያ ዓመታት (533 - 552) የፈጀውና ኢጣልያ በሥላሴ ከማያምኑ ኦስትሮጎቶች በሮማዊስ ንጉስ በጀስቲንያን ሰራዊት አማካኝነት ነጻ የወጣችበት እንዲሁም በሥላሴ የሚያምነውን ፖፕ ሮም ውስጥ ለመሾም የተደረገው ጦርነት የሮምን ከተማ ከማፈራረስ በተጨማሪ ኢጣልያን አውድሟታል። ከዚያ በኋላ በዚህ ሐይማኖታዊ ጦርነት የተነሳ አውሮፓ ወደ ቀዝቃዛው፣ ጨለማው እና ቆሻሻው የጨለማ ዘመን ውስጥ ወደቀች።

ይህ የበሬው ዘመን ነው። በሬ ለሥራ ለልፋት የተፈጠረ እንስሳ ሲሆን በሕይወቱ መጨረሻ ይታረዳል ምክንያቱም ስጋው በጣም ተፈላጊ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች በጨለማው ዘመን ዘመን ውስጥ ብዙ ታግለዋል፤ ብዙ ተሰቃይተዋል፤ ሞተውማል። መንፈስ ቅዱስ የበሬ ዓይነት ብርታት ሰጥቷቸዋል። በዚያ የመሃይምነት ዘመን ውስጥ ሳይታክቱ ለእግዚአብሔር ሰርተዋል፤ ሞትንም በድፍረት ተጋፍጠዋል።

በእነዚያ ሁለት ዘመናት ውስጥ ሐይማኖታዊ ማሳሳት ከፖለቲካ እና ወታደራዊ ኃይል ጋር ተደባልቆ ነበር፤ ይህም በአንድነት የተጣመረ መንፈስ ከሁለቱ ዘመናት አልፎ በሁሉም የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ በፈረሱ ላይ እየጋለበ እስከ ዛሬ ደርሷል። ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ እና ከአረማውያን እምነቶች ጋር ተጋባች። የፋሲካ እንቁላሎችን አስቡ። ዲሴምበር 25ን አስቡ። እንዲሁም ሥላሴ፣ ካርዲናል፣ የመስቀል ምልክት፣ የጸሎት መቁጠሪያ ጨሌ፣ የሁዳዴ ጾም፣ ጸበል፣ የካቶሊክ ጳጳሳት ከ600 ዓመታት በላይ የሚደፉት ባለ ሶስት ድርብ ዘውድ ወዘተ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳቸውም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉም።

ሶስተኛው ማሕተም።

ራዕይ 6፡5 ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ጕራቻ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ።

6 በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ፦ አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ ሲል ሰማሁ።

 

 

ቁጥር 5 እና 6 የሚወክሉት 5ኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን ነው፤ ይህም ዘመን ሉተር መዳን በእምነት ብቻ ነው ብሎ የሰበከበት ዘመን ነው፤ 6ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ደግሞ ዌስሊ ከቤተክርስቲያን ውጭ ላሉ ሰዎች ስለ ቅድስና እና የወንድማማች መዋደድ የሰበከበት ዘመን ነው። ዌስሊ ያመጣው ተጽእኖ ታላቁ የወንጌል ስርጭት ዘመን እንዲጀመር አድርጓል። ሚሽነሪዎች ቤተክርስቲያን አባሎቿ ላልሆኑ ሰዎች ጥቅም የተመሰረተች ማሕበር ናት ብለው በማመናቸው የመዳንን በረከት በዓለም ዙርያ ሁሉ ላሉ ሰዎች ለማዳረስ ሕይወታቸውን ሰጡ። ይህ ዘመን ከአራቱ እንስሳት መካከል በሰው የተወከለው ዘመን ነው። የሰው በትምሕርት መምጠቅ እና ጥበቡ ለተሃድሶ መሪዎች ብዙዎቹን የሮማ ካቶሊክ ስሕተቶች ማየት እንዲችሉ ረድቷቸዋል። ነገር ግን የሰው አእምሮ እድገት እና ዘመናዊ ትምሕርት በመንፈሳዊ መረዳት በኩል በጣም ውስን ነው። ለተሃድሶ መሪዎቹ ያልተገለጡ ብዙ ሚስጥራት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነበሩ። የመጀመሪያው ሐጥያት ምንድነው? የእግዚአብሔር ስም ማነው? አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ የማዕረግ መጠሪያዎች ናቸው። አስቀድሞ መመረጥ እና ነጻ ፈቃድ በአንድነት የሚሰሩት እንዴት ነው? በሉተር ዘመን አስቀድሞ መመረጥ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሰዎች ካልቪኒስት ይሆኑ ነበር፤ በዌስሊ ዘመን ደግሞ ነጻ ፈቃድ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሰዎች አርሚንያን ይሆኑ ነበር።

በተጨማሪ የሰው አእምሮ በእግዚአብሔር መንፈስ አነቃቂነት የኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም ችሏል፤ እርሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል ብቸኛው ስሕተት የሌለበት ትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

በ1769 በጥንቃቄ ተፈትሾ የታተመው ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ድምጽ ነው።

64-0206 እግዚአብሔር ለዚህ ዘመን ያዘጋጀው መንገድ

“በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ፤ ሌላውን አይከተሉትም።” እግዚአብሔር ሆይ ድምጽህ ቃልህ ነው።

63-0630 ሶስተኛው ፍልሰት

እግዚአብሔር በቃሉ በኩል ሲጠራቸው ድምጹን በግልጽ መስማት ይችላሉና

…መጽሐፍ ቅዱስን የእግዚአብሔርን ድምጽ አድምጡ፤ ዛሬም ይጠራችኋል።

ከአራቱ እንስሳት መካከል የሰው በሆነው በዚህ ዘመን የሰው ባሕልም አድጓል፤ ሼክስፒር በስነ ጽሑፍ፣ ማይክልኤንጅሎ እና ሌዎናርዶ ዳቪንቺ በስነ ሥዕልና ቅርጻ ቅርጽ፣ ባክ እና ቢቶቨን በሙዚቃ፣ አይዚክ ኒውተን በሒሳብ እና በፊዚክስ ታልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በዚህ ጊዜ ነው አጋንንታዊ አሰራርን የሚወክለው ጥቁር ፈረስ እየጋለበ የመጣው። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አንድ መስፈሪያ ገብስ ወይም ስንዴ በአንድ ዲናር ማለትም በቀን ሥራ ዋጋ በመሸጥ መንፈሳዊ ረሃብ እንዲፈጠር አደረገች። ይህም ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል መሸጧን ይወክላል። ቤተክርስቲያን በድሎት እየተጨማለቀች ሳለ ካቶሊክ ሃገሮች ድሃ ሆነው ቀሩ። ሕዝቡ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና በክርስቶስ ብቻ አምነው ከመዳን እንዲርቁ ተደረጉ። ሐይማኖትን የገንዘብ ማግኛ ንግድ በማድረግ የሕይወትን እንጀራ ሸጡ፤ ለሐጥያት ስርየት ገንዘብ አስከፈሉ፤ ደግሞም ነፍሳትን ከፑርጋቶሪ ለማስወጣት ብለው ገንዘብ ሰበሰቡ። የሲስቲን ቻፕል እና የቅዱስ ጥሮስ ቤተክርስቲያን ሮም ውስጥ የተሰሩት የስርየት ወረቀቶች በተሸጡበት ገንዘብ ነው። ሐይማኖት ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝ ንግድ ሆነ። ኢየሱስ ቤተመቅደሱ ውስጥ በገንዘብ ለዋጮች የተቆጣው ወዶ አይደለም። በሐይማኖት ተጠቅሞ ገንዘብ መስራት አጋንንታዊ ድርጊት ነው።

የሮም ቤተክርስቲያን ውስጥ መሪዎቿ ትኩረት ያደረጉት ሰው ሰራሽ ሥርዓቶቿ ላይ ነው፤ በዚህም ምክንያት ሕዝቡ እውነተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት እና መዳን እንዳያገኙ ከልክላቸዋለች። አጋንንታዊ አሰራር የእግዚአብሔርን ቃል የሚቃወም መንፈስ ነው። ጸረ ተሃድሶ እንቅስቃሴም የሉተርን ተሃድሶ ለመቃወም በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተደረገ እንቅስቃሴ ነው። ሉተር ነፍሳት የሚድኑት ከሐጥያታቸው ንሰሃ በመግባት እና ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኛቸው አድርገው በመቀበል ነው ብሎ አስተማረ። ተሃድሶውን ለመቃወም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተደረገው እንቅስቃሴ ብዙ ፕሮቴስታንቶች ተገድለዋል። ከ1618 እስከ 1648 ለሰላሳ ዓመታት የተደረገው የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንቶች ጦርነት ጀርመኒ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሶባታል፤ ከጀርመኒ ሕዝብም አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት በዚህ ጦርነት አልቀዋል።

ዛሬም ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ሙሉ በሙሉ ማመንን አስፈላጊ ነው ብለው ስለማያምኑ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ለማመን ብዙም ቦታ አይሰጡም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ቤተክርስቲያን የምትለውን እንድታምኑ ይፈልጋሉ። ፓሰተሩ የተናገረውን እመኑ ይሏችኋል (ፓስተሮች እርስ በርሳቸው ባይስማሙም እንኳ)። እምነታችሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ እንደማያስፈልጋችሁ አድርገው ያስባሉ። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖራቸው የቻለው ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ስለማያውቁ ነው፤ ከዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ በሰዎች ቤት ውስጥ በመገኘት አንደኛ ባለመነበብም አንደኛ መጽሐፍ ሆኗል።

ዛሬ ክርስቲያኖች ከእምነታቸው ውስጥ አብዛኛውን ነገር እውነት መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጥ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ እየተስፋፋ ነው።

አንድን ክርስቲያን እሁድ እሁድ ለምን ቤተክርስቲያን እንደሚሄድ ጠይቁት። ብዙውን ጊዜ መልሳቸው እሁድ የጌታ ቀን ወይም ሰንበት ስለሆነ ነው የሚል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት እነዚህ መልሶች ሁለቱም ትክክል አይደሉም። ስለዚህ ትክክለኛውን ነገር ያደረጉ ይመስላቸዋል ግን በተሳሳተ ምክንያት ነው የሚያደርጉት። ግራ የሚያጋባ ነገር ነው።

ሰርቬተስ የተባለ እስፔይናዊ ዶክተር የሥላሴ ትምሕርትን ተቃወመ ምክንያቱም ስለ ሥላሴ ለማስረዳት ከሚያገለግሉ ቃላት ውስጥ አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሉም። “አንድ አምላክ በሦስት አካላት”። “የሥላሴ ሁለተኛው አካል”። “ኢየሱስ የመለኮት አካል ነው”። “አብ እና ወልድ በባህሪ እኩል ናቸው”። “አብ እና ወልድ አንድ ባህሪ ናቸው” ወዘተ።

በስዊዘርላንድ ውስጥ ታላቅ የፕሮቴስታንት ተሃድሶ መሪ የነበረው ጂን ካልቪን ሰርቬተስ ያቀረበለትን ጥያቄዎች መመለስ አልቻለም፤ ስለዚህ የገጠመውን ችግር የፈታው ሰርቬተስን በአደባባይ በእሳት በማቃጠል ነበረ። ስለዚህ ፕሮቴስታንቶች በሥላሴ ማመናቸውን ቢቀጥሉ ምንም እይገርምም።

አራተኛው ማሕተም።

ራዕይ 6፡7 አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።

8 አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።

 

 

ቁጥር 7 የሚያመለክተው 7ኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን ነው። ይህም የንሥሩ ዘመን ነው። አሜሪካውያኑ ወንድማማቾች ዊልበር እና ኦርቪል ራይት በ1903 የመጀመሪያውን የአውሮፕላን በረራ አደረጉ። ከዚያ በኋላ ሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በ1906 አሚሪካ ውስጥ ሎሳንጀለስ ከተማ በአዙዛ እስትሪት በተደረገው ጴንጤቆስጤያዊ መነቃቃት አማካኝነት ጀመረ። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሶ መጣ ሕዝቡም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት እንደ ንሥር ወደ መንፈሳዊ ከፍታ ወጡ። በዚያ ዘመን ሰዎች አውሮፕላንን በመፍጠር ከምድር ከፍ ብለው መብረር ችለው ነበር። ከዚያ በኋላ በ1947 አንድ መልአክ አሜሪካ ውስጥ ለዊልያም ብራንሐም ተገልጦ የእግዚአብሔርን ቃል ሚስጥራት ይገልጥለት ጀመር። ንሥር አስደናቂ የማየት ችሎታ አለው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን አስደናቂ መገለጥ ሰጣት። ይህም የተሰጣት መገለጥ ከዚያ በፊት ከነበራት የበለጠ እና የጠራ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መረዳት ነው።

አሜሪካ በጴንጤቆስጤያዊ እንቅስቃሴ እና በወንድም ብራንሐም የመጽሐፍ ቅዱስ መገለጦች አማካኝነት መንፈሳዊ መሪነትን ያዘች። በፍጥረታዊው ዓለምም አሜሪካ በአውሮፕላኖቿ እና በሮኬቶቿ እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አቶሚክ ቦምብ በጣሉት ሁለት አውሮፕላኖቿ አማካኝነት በአየር ላይ ገዥ ሆነች። አሜሪካዊው ኒል አርምስትሮንግ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1969 ጨረቃ ላይ የወረደበት መንኩራኩር “ንሥር” ይባል ነበር። እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ ከአሜሪካውያን ሌላ ማንም ጨረቃ ላይ ማረፍ አልቻለም።

ስለዚህ የመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን የንሥሩ በረራ ዘመን ነው። ወደ ላይ ከፍ ብሎ የሚበረው ንሥር እግዚአብሔር ሰዎችን ለማዳን ያዘጋጀውን እቅድ እንዲሁም የሰይጣንንም የተቃውሞ ውጊያዎች በወፍ በረር ቅኝት የማየት ችሎታ አለው።

በምድር ላይ ቆመን ስንመለከት የወንዝ ሙላት አላሻግር የሚለን ይመስለናል።

ከእግዚአብሐየር እይታ አንጻር ግን በሰማይ ላይ የሚበረው ንሥር የወንዝ ሙላትን ለመሻገር ምንም አይቸገርም። ዘመናችንን በእግዚአብሔር ዓይን ማየት ከቻልን ሰው እንደመሆናችን ያሉብን ውስንነቶች እያሉ ተግዳሮቶችን ሁሉ ጥሰን ማለፍ እንደምንችል እንረዳለን።

ዘዳግም 32፡11 ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፥ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፥ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፥ በክንፎቹም አዘላቸው።

እግዚአብሔር እንደ ታላቁ ንስር በክንፎቹ አዝሎ ከተሸከመን ከየትኛውም ቅጥር ወይም ግድግዳ በላይ መዝለል እንችላለን።

አሁን ባለንበት በንሥሩ ዘመን የተሰጠን ተስፋ ይህ ነው። ይህ ዘመን የሚያበቃው ከጊዜ እና ከቦታ ሁሉ ዘልለን ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ስንነጠቅ ነው።

ራዕይ 10፡7 ወደ ፊት አይዘገይም፥ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥ ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል አለ።

ራዕይ 10፡7 ውስጥ አንድ መልእክተኛ የእግዚአብሔርን ሚስጥር ሲገልጥ እናያለን። ሥላሴ እግዚአብሔር አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው። የእግዚአብሔር ስም አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ አይደለም። እነዚህ የእግዚአብሔር ሶስት ማዕረጎች ናቸው። የእግዚአብሔር ስም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

የመጀመሪያው ሐጥያት ሚስጥር፣ የአውሬው ምልክት፣ የእባቡ ዘር፣ ሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት እና ሌሎችም ሚስጥራት ተገልጠዋል።

ቁልፉ የመልእክተኛውን ንግግር ተጠቅሞ መጽሐፍ ቅዱስን መግለጥ ነው።

የመጨረሻው ዘመን ቤተክርስቲያን ወደ መጀመሪያው ዘመን የቅዱስ ጳውሎስ እና ሌሎች ሐዋርያት ወዳስተማሩት ትምሕርት መመለስ አለባት።

አስተምሕሮዎች እና እምነቶች በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን መጻሐፍት መፈተሽ አለባቸው።

እምነታችሁ ትክክለኛ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ፈትሻችሁ አረጋግጡ።

ማንም ሰው ቢሆም የመጨረሻው ዘመን መልእክተኛም ጭምር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማማ ነገር መናገር አይፈቀድለትም። አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አማካኝነት ቢመራን መጽሐፍ ቅዱስን እንጂ ሰውን እየተከተልን አይደለንም።

ሰባት ሙላትን የሚወክል ቁጥር ነው። ሰባት ቀናት የሳምንት ሙላት ናቸው።

ከዚያ ቀጥሎ ቁጥር 8ን እናገኛለን። ስምንት ቁጥር አዲስ ጅማሬን ያመለክታል። ቀጥሎ የሚመጣው ታላቁ መከራ ነው።

ስድስኛው ማሕተም ታላቁን መከራ የሚመለከት ነው። በአራተኛው ማሕተም ሁለተኛ ቁጥር ውስጥ ታላቁ መከራ መጠቀሱ እግዚአብሔር የመጨረሻውን ዘመን መልእክተኛ የላከበት ምክንያት እኛ ከታላቁ መከራ እንድናመልጥ ሊረዳን መሆኑን ያመለክታል። እምነታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የማይመሰርቱ ሰዎች ቅንነት ቢኖራቸውም እንኳ ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ይገባሉ። አራተኛው ማሕተም የሚፈታው በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ነው፤ እርሱም ለሰነፎቹ ቆነጃጅት ቶሎ የሚያበቃ አይደለም ምክንያቱም ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ይቀጥላል እነርሱም በታላቁ መከራ ውስጥ ይሞታሉ።

 

 

በአራተኛው ማሕተም ውስጥ በቁጥር 7 መጨረሻ ላይ ሙሽራይቱ ወደ ሰማይ ትነጠቃለች።

ከዚያ በኋላ የዳኑት ሰነፍ ቆነጃጅት ከተሳሳተ እምነታቸው እንዲላቀቁ ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ይገባሉ።

በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ስለ እምነታቸው የተገደሉ አይሁዶች በአምስተኛው ማሕተም ውስጥ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ።

ጌታ ኢየሱስ ሲመጣ ከምድር ወደ አየር ላይ ተነስተን ልንቀበለው እንድንችል ጥርት ያለው የንሥሩ መንፈስ እይታ ያስፈልገናል።

ለክርስቶስ ሙሽራ ሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የሚጠናቀው ሙሽራይቱ አዲስ የማይሞት አካል ስታገኝ እና ወደ በጉ ሰርግ ግብዣ ለመታደም ይህን ምድር ተሰናብታ ስትሄድ ነው።

1ኛ ቶሰሎንቄ 4፡17 ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።

አራተኛው ማሕተም ለእኛ በጣም ወሳኝ ማሕተም ነው፤ ምክንያቱም ዛሬ ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ብቸኛው ማሕተም አራተኛው ማሕተም ነው።

ምርጫ አለን። ይህም ምርጫ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ እና ወደ ጥንቷ ቤተክርስቲያን መመለስ አለዚያ ደግሞ በታላቁ መከራ ውስጥ መጥፋት ነው።

ንሥሩ ከላይ ሆኖ የሚያሰማው ጩኸት ይህ ነው። የንሥሩ አስደናቂ ዓይኖች የሚያመለክቱት የእግዚአብሔርን ሚስጥራት የምናስተውልበት የጠራ መንፈሳዊ እይታ እንደሚያስፈልገን ነው። ቤተክርስቲያኖች ግን ዓይናቸው ስላልበራ የእግዚአብሔርን ሚስጥራት ቸል ይላሉ።

ለምሳሌ ኢየሱስ አመንዝራለች ተብላ የተከሰሰችዋን ሴት ይቅር ከማለቱ በፊት ለምንድነው በምድር ላይ በጣቱ የጻፈው? በምድር ላይ ለምንድነው ሁለት ጊዜ የጻፈው? ይህን ታሪክ የምናገኛ የዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው። ለምን?

ኢየሱስ ሕዝቡን ያበላ ጊዜ ለምንድነው ሰዎቹ ሳይበሉት የወደቁ ቁርስራሾች ሲሰበሰቡ 12 መሶብ እና 7 መሶብ የሞሉት?

ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ ሕዝቡ ከበሉት እንጀራ ቁርስራሾቹ የተሰበሰቡበትን መሶብ ቁጥር ትርጉሙን ያስተውላሉ ብሎ ጠብቋል።

ማቴዎስ 16፡9 ገና አታስተውሉምን? ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?

10 ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?

ኢየሱስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉ ዝርዝር ጉዳዮችን ሁሉ እንድናስተውል ይጠብቃል። እያንዳንዱ ነገር ጥልቅ ትርጉም አለው።

በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የዳኑ ክርስቲያኖች ግን ሰነፍ ቆነጃጅት ናቸው። ሁላቸውም በደስታ እና በሞቀ እንቅልፍ ውስጥ በመሆናቸው የማንቂያ ጥሪ ወይም ቅስቀሳ ያስፈልጋቸዋል።

ኢየሱስ ቡችላ ወይም ውሻ ይላት በነበረች አንዲት አሕዛብ ሴት ከልጆች እንጀራ ላይ ፍርፋሪ በለመነች ጊዜ ለምንድነው የተገረመባት?

ከአራቱ ወንጌሎች በሁለቱ ውስጥ መቃብሩ አጠገብ ሁለት መላእክት እናያለን። በሌሎቹ ሁለት ወንጌሎች ውስጥ አንድ መልአክ ብቻ እናያለን። ይህ ልዩነት የኖረው ለምንድነው? ሁለት ወንጌሎች ለምንድነው ሁለተኛውን መልአክ ያልጠቀሱት? ምን ሊነግሩን እየሞከሩ ነው?

የእነዚህን ክስተቶች ጥልቅ መረዳት ማግኘት ካልቻልን ወይም ደግሞ ምንም የማይጠቅሙ ጥቃቅን ዝርዝሮች ናቸው ብለን ካለፍናቸው ከአራቱ እንስሳት በሰው የተወከለው እንስሳ መረዳት ብቻ ነው ያለን ማለት ነው፤ እርሱም የሰው ጥበብ ትምሕርት ነው፤ ለመጨረሻው ዘመን ክርስቲያኖች እንዲሰጣቸው ቃል የተገባው የንሥሩ አስደናቂ እይታ ወይም መረዳት የለንም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ለሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን መጨረሻ የሚያስፈልገው እውቀት ጎድሎናል ማለት ነው።

በዚህ ክፍል ውስጥ ዋናው ጉዳይ መዳን አይደለም። መዳን ያስፈልገናል፤ ምንም ጥያቄ የለውም። በዚህ ክፍል ግን የተነሱት ጉዳዮች ቅድስና እና የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አይደሉም። እነዚህ ለሁሉም ክርስቲያኖች አስፈላጊ ናቸው።

አሁን በጣም አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መረዳት ነው።

ስሕተትን እውነት ብለን ካመንን ተታለናል። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት መረዳት ካልቻልን በመሃይምነታቸው ገድበው ባስቀሩን መሪዎቻችን አማካኝነት ተታልለናል።

የቤተክርስቲያን መሪዎች በሕዝቦቻቸው ላይ እንደ ጣሪያ ወይም እንደ ክዳን ይጫናሉ።

የታላቁ መከራ ዘግናኝ ሰቆቃ በድንገት ሲመጣ ይህ መታለል ከላያችን ላይ ተገንጥሎ ይወድቃል።

የትኛውም ክርስቲያን ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ገብቶ በዚያ በሚፈጸመው ዘግናኝ ሞት እና እልቂት ውስጥ ከተገደለ በኋላ ሁለተኛ ሰው እንዲመራው ወይም የራሱ አመለካከትም ቢሆን እንዲመራው አይፈልግም።

ስለዚህ በቁጥር 8 “ሞት” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆነው ሐይማኖታዊ ንግድ እና ፖለቲካ ፈረስ ላይ ተቀምጦ እየጋለበ በታሪክ የትኛውም ጨካኝ መሪ ከገደለው በላይ ብዙ ሚሊዮን ሰዎችን ለማጥፋት ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ይገባል።

የሰው አመራር የፈጠረው ትልቅ ፈጠራ የሞት ፋብሪካ ነው።

ከድሮ ጀምሮ በቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ክፉ መናፍስት ሁሉ በአንድነት ተባብረው ዓለምን የምትገዛ በጣም ታላቅ የሆነች ቤተክርስቲያንን ይመሰርታሉ።

ይህም ሰይጣን ብዙዎችን የሚያጠፋበት የመጨረሻው መሳሪያ ነው።

ክርስቲያኖች ለምንድነው በዚህ የሞት ክልል ውስጥ የሚገኙት? ምክንያቱም እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መርምረው መቀበል ስላቆሙ ነው።

ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ጊዜ አጥተዋል። መጽሐፍ ቅዱስን መማር ብዙ ጥረት ይጠይቃል። ክርስቲያኖች እምነታቸው ትክክል መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ መርምረው ለማረጋገጥ ሰንፈዋል፤ ምክንያቱም ልንሳሳት እንችላለን ብለው እንዳያስቡ ብዙ እናውቃለን በሚል ስሜት በትዕቢት ተሞልተዋል። ሊያርሟቸው የሚሞክሩ ሰዎችን አይሰሙዋቸውም።

በብዙ ሕዝብ መካከል መሆን የደህንነት ስሜት ስለሚሰጣቸው ከፓስተራቸው ጋር መቃረንን ይፈራሉ። በሰው አመራር እና በሰው ልማድ ውስጥ ተመችቷቸው ተኝተዋል። ይህም በራሳቸው አእምሮ እያሰቡ ከመድከም ያድናቸዋል። ስለዚህ በታላቁ መከራ ውስጥ ታላቅ መሪ የሚሆንላቸውን ሰው ያገኛሉ … እርሱም የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።

4ኛውን ማሕተም የሚገልጠው ቁጥር 7 በጣም ወሳኝ ነው።

ራዕይ 6፡7 አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።

ይህ በራዕይ 10፡7 የተጻፈው የሰባተኛው መልአክ ድምጽ ነው።

በዚህ ክፍል ውስጥ በተጨማሪ የአራተኛው እንስሳ ድምጽም አለ።

ሁለቱም የሚገልጹት ከ1947 እስከ 1965 ድረስ በድምጽ የተቀረጹትን የወንድም ብራንሐም ስብከቶች ነው።

በ7ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ነብይ ይላካል፤ እርሱም ስለሚመጣው ፍርድ ያስጠነቅቀናል፤ እንዲሁም ከሚመጣው ቁጣ ማምለጥ እንድንችል የሚረዳንን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያስተምረናል።

እርሱ የሚያስተምረንን ትምሕርቶች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ወስደን እውነት መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን።

የዚያን ጊዜ የምንከተለው እርሱን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን ነው።

አንድም ክርስቲያን ሰውን መከተል የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስን አምነን ስንታዘዝ ክርስቶስን ነው የምንከተለው።

ከዚያም አራተኛው ማሕተም ቤተክርስቲያንን ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ይዟት ይገባል።

ይህም ትኩረት ወደ አይሁዶች እንዲሆን ያደርጋል ምክንያቱም በታላቁ መከራ ወቅት አይሁዶች ወደ ወንጌሉ ይመለሳሉ።

 

 

አምስተኛው ማሕተም በ70 ዓ.ም በሮማውያን አማካኝነት ጀነራል ታይተስ እና ሰራዊቱ ኢየሩሳሌምን ባፈራረሱ ጊዜ የአይሁዶች ስደት የሚጀምርበት ነው። በዚያ ጊዜ ኢየሩሳሌም በሮማውያን ጦር ሰራዊት ስትከበብ 1,110,000 አይሁዳውያን ሞተዋል። ቤተመቅደሱም ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

ይህ አይሁዶች ላይ ብቻ በሃገራቸው የመጣ ስደት ነበረ። ከዚያም አምስተኛው ማሕተም አይሁዳውያን ከየትኛውም ሕዝብ የበለጠ ለረጅም ዘመን ለ2,000 ዓመታት የተሰደዱበትን ታሪክ ያሳየናል። ከዚያ በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ሒትለር ብዙ ሚሊዮን አይሁዳውያንን በአሰቃቂ መንገድ የገደለበት የሞት ካምፕ ዓለም ሁሉ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ለአይሁዳውያን እንዲያዝን ስላደረገ የዓለም መንግስታት አይሁዳውያን በ1947 ፓለስታይን ውስጥ የሚኖሩበት ሃገር እንዲሰጣቸው በትብብር ውሳኔ አድርገዋል። አሁን አይሁዳውያን እግዚአብሔር ጥንት በሰጣቸው ምድር ውስጥ ይኖራሉ፤ በዚያም መሲሁ በታላቁ መከራ ዘመን ወደ እነርሱ ሲመጣ ለመቀበል ይጠባበቃሉ።

በ1947 እግዚአብሔር አይሁዳውያንን ወደ እሥራኤል መመለስ ጀመረ።

በ1947 ወንድም ብራንሐም የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መግለጥ ጀመረ።

 

 

ስድስተኛው ማሕተም ታላቁ መከራ ነው። ታላቁ መከራ የተፈጥቶ ኡደቶች ሁሉ ሙሉ በሙሉ የሚቋረጡበት ጊዜ ነው። በዚያ ጊዜ ለማመን በሚከብድ መጠን ጨካኝ እና ግፈኛ የሆነ የካቶሊክ ፖፕ ዓለምን ይመራል። ያ ጊዜ ለማሰብ እንኳ የሚዘገንን ጊዜ ነው የሚሆነው።

በታላቁ መከራ ወቅት 144,000 አይሁዶች በሁለቱ ነብያት በሙሴ እና በኤልያስ አማካኝነት ወደ መሲሃቸው ወደ ኢየሱስ ይመለሳሉ፤ ሙሴ እና ኤልያስ በታላቁ መከራ ዘመን የማይሞቱት ከተሰጣቸው ልዕለ ተፈጥሮ ኃይል የተነሳ ነው።

አራተኛው ማሕተም በከፊል ከአሕዛብ ወገን ለሆነችው ሙሽራ (ራዕይ 6፡7) በከፊል ደግሞ ለሰነፎቹ ቆነጃጅት እና በታላቁ መከራ ዘመን ለሚኖሩት አይሁዶች ነው (ራዕይ 6፡8)። የፒራሚዱ ቢጫ ቀለም የተቀባ ጎን ታላቁን መከራ ይወክላል። 7ቱ መለከቶች አይሁዶችን ወደ እሥራኤል እንዲመለሱ ይጠሩዋቸዋል፤ ሰባቱ የእግዚአብሔር ቁጣ ጽዋዎች ደግሞ በሐጥያተኛው ዓለም ላይ የሚመጣውን ፍርድ ያመለክታሉ።

 

 

ሰባተኛው ማሕተም የጌታ ምጻት ነው። ስለ ሰባተኛው ማሕተም የምናውቀው ዝምታ ብቻ ነው። ስለዚህ ማንም የማያውቀው ሚስጥር ነው።

እግዚአብሔር ዝም ያለ ጊዜ የእኛም አፍ ዝም ቢል ይሻለናል።

ስለ ሰባተኛው ማሕተም አንዳችም የምናውቀው ነገር የለም ምክንያቱም የጌታ ምጻት ምልክት ነው።

ራዕይ 8፡1 ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኵል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ።

ስለዚህ ማቴዎስ ምዕራፍ 24 ስለ አይሁዳውያን እና በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌም ስትጠፋ መሲሃቸውን አንቀበልም በማለታቸው ምክንያት በሃገራቸው ስለመጣባቸው የስደት መጀመሪያ ይነግረናል። ይህንንም ተከትሎ እጅግ አሳዛኝ የሆነው የ2,000 ዓመታት ስደታቸው መጣ፤ ስደታቸውም የሚያበቃው ወደ መሲሁ በሚመለሱበት በታላቁ መከራ ውስጥ ነው።

 

 

ከዚያ በኋላ ያለው ትዕይንት ወደ ቤተክርስቲያን ይዞራል።

በምዕራፉ መጀመሪያ ላይ ሰዎችን የሚያታልል ስሕተት ወደ ቤተክርስቲያን እንዴት እንደገባ የሚገልጽ አጭር ታሪክም አለ።

ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለ ስሕተት ነው ዓለምን ወደ ታላቁ መከራ ይዞ እየሄደ ያለው።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ በአራተኛው ማሕተም (ራዕይ 6፡7) እና የመጨረሻው ዘመን ውስጥ ያለችው ቤተክርስቲያን ከታላቁ መከራ ለማምለጥ እንዴት መዘጋጀት እንዳለባት በረጅሙ ያብራራል። ዛሬ ዋነኛው ሃሳባችን ከታላቁ መከራ ማምለጥ መሆን አለበት። ከታላቁ መከራ መትረፍ ከፈለግን እምነታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ሲፈተሽ ፍጹም ትክክለኛ ሆኖ መገኘት አለበት።

ሮኬት ወደ ሕዋ የሚወነጨፍ ከሆነ እያንዳንዱ ክፍሎቹ በትክክል መስራት አለባቸው።

ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል የምንነጠቅ ከሆነ እምነቶቻችን በሙሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን አለባቸው።

የመጨረሻው ዘመን ቤተክርስቲያን የተሃድሶ መሪዎች ወደ ቤተክርስቲያን መልሰው ያመጡዋቸው መዳን፣ ቅድስና፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ያስፈልጓታል።

በተጨማሪ ደግሞ አሁን የሰይጣንን ትልቅ ውሸት መዋጋት የምንችልበት የእውነት መረዳት ያስፈልገናል። የሰይጣን ውሸት በቤተክርስቲያኖች መካከል የሚደረግ ፉክክር፣ ዲኖሚኔሽናዊ ቤተክርስቲያናዊነት እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ እምነቶቻቸው ናቸው።

ኢየሱስ ገንዘብ ለዋጮችን እና ነጋዴዎችን ከቤተመቅደሱ ውስጥ እየገረፈ ባስወጣቸው ጊዜ በጣም ተቆጥቶ ነበር፤ ምክንያቱም እነዚያ ሰዎች ሐይማኖትን ንግድ አድርገዋል። ይሁዳ እውነትን በገንዘብ ለወጠ። የገንዘብ ለዋጮቹ ድርጊት ክርስትና ትልቅ ንግድ የሚሆንበትን የመጨረሻውን ዘመን የሚያመለክት ነበር። ሃብታም በሆኑት ታላላቅ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ ክርስቲያኖች ዛሬ የሚፈልጉት የገንዘብ ትርፍ እንጂ ቃል የሚነግራቸውን ነብይ አይደለም።

የዶላር ምልክት $ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የመዳን ምልክት ነበረ፤ ማለትም ሙሴ በእፉኝነት የተነደፉ አይሁዶች እንዲፈወሱ የነሃስ የተሰራ እባብ በዓላማ ላይ የሰቀለበት ምልክት ነበር።

ዛሬ ክርስቲያኖች መዳን የሚገኘው ገንዘብ በማከማቸት ይመስላቸዋል፤ በተለይም በአሜሪካ ዶላር $።

ማቴዎስ ምዕራፍ 24፡1

ማቴዎስ 24፡1 ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ።

የደቀመዛሙርቱ ስሕተት በሰው ሥራ መደነቃቸው ነው። የእኛም ስሕተት በሰራነው ትልቅ ሥራ መደነቃችን ነው።

የደቀመዛሙርቱ ሞኝነት ኢየሱስ ቤተመቅደሱን ትቶ መውጣቱን አለማስተዋላቸው ነው።

ከቤተመቅደሱ ወጥቶ ሄደ። ኢየሱስ ቤመቅደሱን መተዉን ይህ ቃል በአጽንኦት ይናገራል።

ኢየሱስ ቤተመቅደሱን ትቶ ሄደ ማለት ቤተመቅደሱ በአረማውያኑ ሮማውያን ለመውደም ተጋለጠ ማለት ነው።

በሰባተኛው የሎዶቅያውያን የቤተክርስቲያን ዘመን ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን ውጭ ነው የቆመው። ከቤተክርስቲያን ወጥቶ ስለሄደ ቤተክርስቲያን ከዚህ በኋላ የሚጠብቃት ነገር ቢኖር በመጨረሻው ሮማዊ የክርስቶስ ተቃዋሚ ፖፕ አማካኝነት በታላቁ መከራ ውስጥ መጥፋት ነው።

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ቃሉ ወጥቶ ሲሄድ መንፈስ ቅዱስም ወዲያው የቤተመቅደሱን መጋረጃ ቀዶ ሄደ።

ያለ ቃሉ ሰዎች የሰሩት አስደናቂው የቤተመቅደስ ግድግዳ ዕጣ ፈንታው መፍረስ ነው።

የሚገርመው ነገር ቤተመቅደሱ ተመልሶ የቀድሞ ክብሩ እንዲኖረው ተደርጎ የታደሰው ኢየሱስ የ2 ዓመት ሕጻን ሳለ ሊገድለው በሞከረው በጠላቱ በሔሮድስ ነበር።

ከዚያ በኋላ የቤተመቅደሱ መሪዎች በስተመጨረሻ ኢየሱስን በገደሉ ጊዜ የሔሮድስን ዓላማ ነበር ያሳኩት።

ደቀመዛሙርቱ ሲያደንቁ የነበሩት ሕጻናትን የሚገድል ክፉ ሰው የሰራውን ሥራ ነበረ።

በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ልጆች ናቸው ወደ ሐዋርያዊ አባቶች የሚመለሱት፤ የዚህ ዘመን ቤተክርስቲያኖች ግን ሁላቸውም ይህንን ሊያስቆሙ እየሞከሩ ናቸው።

ዛሬ የቅዱስ ጴጥሮስን ውብ የቤተክርስቲያን ሕንጻ እናደንቃለን።

ይህ ቤተክርስቲያን የተሰራው በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ማለትም በአንበሳው ዘመን ውስጥ ክርስቲያኖች በአንበሳ እንዲበሉ ከተደረገበት ከሮም ኮሎሲየም በተጋዘ ሁለት ሺ አምስት መቶ ጋሪ ጭነት ድንጋይ ነው። ኮሎሲየምን የሰሩት ቬስፓሲያን እና ታይተስ ሲሆኑ የሰሩትም ከኢየሩሳሌም ቤተመቅደሱን ባፈረሱ ጊዜ በዘረፉት ሃብት ነው።

ከዚያም ከኢየሩሳሌም 90,000 አይሁዶችን በባርነት ይዘው ወደ ሮም በመውሰድ ኮሎሲየምን እንዲሰሩ አስገደዱዋቸው። በሞኝነታችን የተነሳ የቅዱስ ጴጥሮስን ቤተክርስቲያን ሕንጻ ላይ ላዩን አይተን እናደንቃለን ግን የእግዚአብሔር ቃል ውስጡ እንደማይሰበክ እንረሳለን። አንድ ፖፕ እንኳ በአደባባይ በሕዝብ ፊት ንሰሃ መግባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ አለብን ብሎ ሲናገር ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ 2፡38 የተናገረው ይህንን ነው።

የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

ካቶሊኮች ጴጥሮስ የመጀመሪያው ፖፕ ነው ይላሉ። ፖፕ ሊሳሳት አይችልም ይላሉ። እንዲህ ካሉ ጴጥሮስ አልተሳሳተም ማለት ነው። ታድያ ፖፑ ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረውን ለምንድነው የማያምነው?

ማቴዎስ 24፡2 እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።

ይህ የሰዎችን ሥራ ከንቱነት ይመሰክራል። ሰው የሰራው ነገር ሁሉ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንጂ ለዘላለም አይኖርም። በአካል የምናየውን ማድነቅ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ሃሳብ እንዳልተረዳን ያሳያል። ደቀመዛሙርቱ አንድን ሕንጻ አይተው እያደነቁ ነበር፤ ነገር ግን እያደነቁት የነበረው ሕንጻ መፍረሻው ተቃርቦ እንደ ነበር አላወቁም። ዛሬ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ብዙ ርቀው የሄዱትን የቤተክርስቲያናችንን ሥርዓቶች እናደንቃለን። እነዚህ ሥርዓቶችም ከዚህ በኋላ ለረጅም ጊዜ አይዘልቁም። ለምንድነው በዚህ ዘመን ትልልቅ ሕንጻዎችን የምናደንቀው? ትልልቅ ሕንጻዎች ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር የማይወዳቸውን በምድራዊነት እና በሚጠፋ ገንዘብ ፍቅር የተነደፉ ሥርዓቶችን ሸሽገው የያዙ ቤቶች ናቸው፤ እግዚአብሔርም በታላቁ መከራ ጊዜ በአርማጌዶን ጦርነት ውስጥ እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ያጠፋቸዋል። ስለዚህ መንሳዊው እውነት ላይ ትኩረት ማድረግን መለማመድ አለብን። የእግዚአብሔር ቃል ባለበት ብቻ ነው ለዘላለም ዋጋ ያለው ነገር የሚገኘው። ሌላው ነገር ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ለሚፈነዳው አቶሚክ ቦምብ እራት ሊሆን የተዘጋጀ ነው። በዚህ ዘመን ምድርንም የሰዎችን ሕይወትም ለማጥፋት የሚበቁ አቶሚክ ቦምብ እና ኑክሊየር ቦምብ ሞልተዋል። በምድር ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ ብዙዎቹን ማጥፋት ይችላሉ።

ስለዚህ ምቾት እና ድሎት ሳይሆን እውነትን መፈለግ አለብን።

 

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23