ማቴዎስ ምዕራፍ 12 - ኢየሱስ ወንጌሉ ወደ አሕዛብ እንደሚሄድ ተናገረ
We update studies as the Lord Jesus leads us. You can find the latest update of this study at ChurchAges.net
ልክ ዮናስ በነነዌ የነበሩ አሕዛቦችን እንደለወጣቸው ሁሉ ኢየሱስ ወንጌል ከአይሁዶች ወጥቶ ወደ አሕዛብ እንዲሄድ ይፈልጋል።
First published on the 8th of March 2021 — Last updated on the 5th of November 2022በዚህም ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ ሁለት ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተዋል።
እነርሱም የሰንበት እረፍት እና ደቀመዛሙርቱ እሸት መቅጠፋቸው ናቸው።
በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት መጨረሻ ላይ የሚታጨደው መከር ግን ከአሕዛብ ወገን ለሆነቸው ለሙሽራይቱ ነው።
ደግሞም በዘመን መጨረሻ የቤተክርስቲያን መሪዎች የሚቃወሙዋቸው ሁለት ጉዳዮች አሉ።
ማቴዎስ 12፡1 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር።
ሉቃስ 6፡1 በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር።
“እሸት” ማለት እህል ነው በዚያ ዘመን።
አውሮፓውያን በ1500 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ሲገቡ “እሸት” ብለው የሚጠሩት እህል “በቆሎ” ተባለ።
ከመጀመሪያው ሰንበት አልፎ የሚመጣው ሁለተኛ ሰንበት ሶስተኛ ሰንበት ነው።
ይህም እውነት በጨለማው ዘመን ውስጥ ከጠፋ በኋላ ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሶ የሚመጣበትን ሶስተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን ያመለክታል (ሰርዴስ፣ ፊልደልፊያ፣ እና በስተመጨረሻ ሎዶቅያ፤ ራዕይ ምዕራፍ 3 ይመልከቱ)።
ማርቲን ሉተር በሰርዴስ የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ መዳን በእምነት ብቻ የሚለውን እውነት ወደ ቤተክርስቲያን በተሃድሶ አመጣ፤ ሰርዴስ ያመለጡ ሰዎች ማለት ነው።
የሉተር ተሃድሶ መሬት ውስጥ ሞቶ በጨለማ ዘመን ውስጥ በአፈር ተቀብሮ የነበረ ተክል ሲያቆጠቁጥ የሚያወጣውን ቅጠል ይወክላል።
ጆን ዌስሊ በወርቃማው የወንጌል ስብከት ዘመን ቅድስና እና የወንጌል ስርጭት እንደገና እንዲጀመሩ አደረገ፤ ያም ዘመን የፊልደልፊያ ዘመን ሲሆን ትርጉሙ የወንድማማች መዋደድ ነው።
የአበባው ብጫ ዱቄት በሜዳው ላይ ሲበታተን ሕይወት በየስፍራው ተሰራጨ።
በሰባተኛው የሎዶቅያቅ ዘመን (የሕዝቡ መብት ዘመን) የፔንቲኮስታሎች ተሃድሶ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሶ እንዲመጣ አደረገ። ይህም መብቀል የጀመረውን ዘር ከጥፋት የሚከላከል ቅርፊት ነው።
ከዚያ በኋላ ዊልያም ብራንሐም የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መገለጥ ወደ ቤተክርስቲያን አመጣ። ዘር ሆኖ የተተከለው ቃል በተገለጠው መጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ወደ መብሰል ደረሰ። በመከር ጊዜ የሚበስለው ዘር በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ከተዘራው ዘር ጋር ፍጹም አንድ ዓይነት ነው።
ዘሩ በስሎ ከተክሉ ላይ የሚታጨድበት ጊዜ ሙሽራይቱ በኋለኛው ዝናብ ወይም በመከር ወቅት ወደ ሰማይ የምትነጠቅበትን ሰዓት ይወክላል።
እነዚህ ፍጥረታዊ ዘሮች የሐዋርያትን አስተምሕሮ እና በሐዋርያት እጅ ተጽፎ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ የሚሆነውን መልእክት ይወክላሉ። እነዚህ የተጻፉ እውነቶች ቤተክርስቲያን በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን መጨረሻ ላይ ለሚደረገው የመከር አጨዳ እንድትዘጋጅ ያደርጓታል፤ በዚያም ጊዜ የሞቱ ቅዱሳን በትንሳኤ ከመቃብራቸው ይወጣሉ።
እውነተኛው ሰንበት ከሐጥያት ሸክም ማረፍ ነው። እውነተኛው ሰንበት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው።
ኢሳይያስ 28፡11 በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤
ይህ የሆነው እነርሱ በመንፈስ ቅዱስ በተሞሉበት በጴንጤቆስጤ ዕለት ነው።
ኢሳይያስ 28፡12 እርሱም፦ ዕረፍት ይህች ናት፥ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም ማረፊያ ናት አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ።
ንሰሃ ከገባንና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበልን በኋላ ወደ ቀድሞው የሐጥያት ሥራችን መመለስ የለብንም።
እግዚአብሔር ከመፍጠር ሥራው አረፈ፤ ካረፈ በኋላ ተመልሶ ወደ መፍጠር ሥራው አልሄደም።
ዕብራውያን 4፡10 ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።
ዋነኛው ሐጥያት አለማመን ነው።
ኢየሱስ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር መሆኑን እና ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ እንከን የሌለው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን መንፈስ ቅዱስ ካሳመነን በኋላ ተመልሰን ወደ ቀድሞ አለማመናችን መሄድ አንችልም። እግዚአብሔር ለእኛ ባሰበው ሃሳብ ውስጥ ብዙ ስሕተት አለ ብለን ማመን አንችልም። ስለዚህ ስለምንኖርበት የኑሮ ሁኔታ ማጉረምረም እናቆማለን። ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር እጅ ነው ያለው፤ እርሱም ምን ማድረግ እንዳለበት እኛ ሳንነግረው ያውቃል።
ደግሞም ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳችም ስሕተት አለ ብለን ማመን አንችልም።
አስተሳሰባች በኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው እውነት ጋር እንዲገጥም ብለን በአስተሳሰባችን መለሰጥ አለብን።
ዮሐንስ 8፡24 እንግዲህ፦ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው።
በተጻፈው ቃል ስለማናምን ሰባኪዎች በቀላሉ ያታልሉናል።
ማቴዎስ 24፡4 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ዋነኛ ዓላማው እኛ የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራ መረዳት እንችል ዘንድ ወደ እውነት ሁሉ ሊመራን ነው።
ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤
የመጨረሻው ዘመን ላይ ያለችዋ ሙሽራ ወደ ሐዋርያዊ አባቶች እምነት በተመለሰች ጊዜ ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ወደ ላይ ትነጠቃለች።
እሸት ቀጥፎ ሳያበስሉ መብላት በጣም የትሁታን አበላል ነው። ትሕትና የኋለኛው ዝናብ የመከሩ ዝናብ ቁልፍ ነው። ይህ ዝናብ ሐዋርያት የጻፉትን እውነት ብቻ እንድናምን ነው ወደ ቃሉ የሚመልሰን።
ደቀመዛሙርቱ በእርሻ ውስጥ በሚያልፉበት ሰዓት ብዙ እሸት ሊቀጥፉ አይችሉም።
ይህም የተገለጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት ወደ ማወቅ የሚመጡ ሰዎች ብዙ እንደማይሆኑ ያመለክታል።
ሉቃስ 18፡8 እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?
ማቴዎስ 7፡14 ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
ማቴዎስ 12፡2 ፈሪሳውያንም አይተው፦ እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት።
ፈሪሳውያን ምግብ በልተው የጠገቡ ሰዎች ናቸው፤ ልክ እንደ ዛሬዎቹ ፓስተሮች።
ፈሪሳውያኑ ለምን ደቀመዛሙርቱ እሸት በእጃቸው ቀጥፈው ይበላሉ ብለው አጉረመረሙ።
ደቀመዛሙርቱ ኋላ በእጃቸው በአዲስ ኪዳን መጻሐፍት ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ዘር ይጽፋሉ።
ዘመናዊ የቤተክርስቲያን መሪዎች በሐዋርያት የተጻፉትን አስተምሕሮዎች ይቃወማሉ።
ስለዚህ የዘመናችን ቤተክርስቲያን መሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መገለጣቸውም እና ወደ ቤተክርስቲያን መመለሳቸውን ይቃወማሉ። ብቸኛው እንከን የሌለው መጽሐፍ ቅዱስ ከሆነው ከ1769ኙ እትም ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ የተገለጡትን ሚስጥራት በማስተማር ፈንታ የቤተክርስቲያን መሪዎች ከ450 የተለያዩ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች ይሰብካሉ። ከዚህም የተነሳ ፍጹም የሆነ እውነት የለም ይላሉ። ሰዎች ከ450 የተለያዩ ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል መምረጥ የሚኖርባቸው ከሆነ ሐዋርያት ያስተምሩ የነበረውን እውነት ማግኘት አይችሉም። ከዚህም በተጨማሪ 45,000 ዓይነት የተለያዩ ቤተክርስቲያኖች እና ዲኖሚኔሽኖች አሉ። ይህ የዘመናችን ቤተክርስቲያን ሰባኪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራትን ለመስበክ እምቢ በማለታቸው የተፈጠረ መንፈሳዊ ወከባ እና ግርግር ነው።
ማቴዎስ 12፡3 እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥
ዳዊት ለምንድነው በድንኳኑ ቅድስት ስፍራ ያለውን የመስዋእቱን ሕብስት እንዲበላ የተፈቀደለት ብሎ ኢየሱስ ጥያቄ ጠየቃቸው። በእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ ካሕናት ብቻ ነበሩ ህብስቱን መብላት የተፈቀደላቸው።
ማቴዎስ 12፡4 እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን?
ዳዊት የክርስቶስ ጥላ ነበረ። ገና በወጣትነቱ ነበር ንጉስ እንዲሆን የተቀባው፤ ነገር ግን ወደ ንገስናው ዙፋን የወጣው ጠላቱ ሳኦል ከሞተ በኋላ ብቻ ነው።
ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ነበር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ንጉስ እንዲሆን የተቀባው። ነገር ግን ወደ ንግስናው ዙፋን ወጥቶ የሚነግሰው ጠላቱ የሆነው በሮማዊው አውሬ ውስጥ ያለው የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ እና ሐሰተኛው ነብይ (ፖፕ) በአርማጌዶን ጦርነት ውስጥ ከጠፉ በኋላ ነው። ለጊዜው ኢየሱስ የአሕዛብ ቤተክርስቲያንን መዳን የሚያስፈጽም ሊቀካሕናት ነው።
ስለዚህ በመቀባቱ እና ንጉስ በመሆኑ መካከል ዳዊት የክሕነትን ሥራ የመፈጸም ፈቃድም ተሰጥቶት ነበር።
ዳዊትን ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩትም ሰዎች ለካሕናቱ ብቻ የተባለውን ሕብስት እንዲበሉ ተፈቅዶላቸው ነበር።
ዳዊት እና እርሱን የተከተሉ ሰዎች ዳዊት በተቀባው ቅባት አማካኝነት እንደ ካሕናት ማገልገል ከቻሉ ኢየሱስ እና ደቀመዛሙርቱም ይችላሉ ምክንያቱም ደቀመዛሙርቱ የአዲስ ኪዳን ካሕናት ናቸው።
ማቴዎስ 12፡5 ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን?
የብሉይ ኪዳን ካሕናት ቃሉን በመስበክ እና መስዋእቶችን በማቅረብ በሰንበት ተግተው ይሰሩ ነበር።
ስለዚህ የአዲስ ኪዳን ካሕናት ማለትም ሐዋርያትም በሰንበት መስራት እና መከሩን መሰብሰብ ይችላሉ።
በመጨረሻው ሰዓት ጌታን በአየር ላይ ትቀበለው ዘንድ ሙሽራይቱን ከምድር ላይ የሚያነሳት መከር የሚፈጸመው የሐዋርያት እምነት ሙሉ በሙሉ ወደ አማኞች በተመለሰ ጊዜ ነው። በዚያ ጊዜ የዘመናችን ሙሽራ ከቤተክርስቲያን አለማመን ታርፋለች።
ከአለማመን ማረፍ፤ ይህ ነው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል መነጠቅን የሚያስከትለው እውነተኛው ሰንበት።
ማቴዎስ 12፡6 ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
ኢየሱስ የአይሁድ መሪዎችን እያስጠነቀቀ ነው። እርሱ ከቤተመቅደሱ ይበልጣል። ከእርሱ ጋር መጣላታቸው ምን ያህል የማያስተውሉ እና ዕውሮች መሆናቸውን ያሳያል።
ካሕናቱ በሰንበት ዕለት በቤተመቅደሱ ውስጥ አገልግሎታቸውን ሲፈጽሙ ለቤተመቅደሱ ወይም ለድንኳኑ ባገለገሉበት መንገድ ነው ደቀመዛሙርቱም ለኢየሱስ የሚያገለግሉት።
እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ካሕናት በሰንበት መስራት ይፈቀድላቸው ነበር።
በአዲስ ኪዳን እውነተኛውን እረፍት (ሰንበትን) የሚሰጠን የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መግለጥ ነው ምክንያቱም ከቤተክርስቲያኖች አለማመን እና ከትምሕርቶቻቸው እንዲሁም ከልማዶቻቸው ነጻ ያወጣናል።
በዘመኑ መጨረሻ ወንድም ብራንሐም ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ ሲመላለስ ማየት እንድንችል ሚስጥራትን ገልጦ ያሳየናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጠው እውነት የትኛውም የቤተክርስቲያን መሪ ከሚናገረው አመለካከት ይበልጣል።
ማቴዎስ 12፡7 ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር።
የፈሪሳውያን ስሕተት ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ምሕረት እንደሚያስፈልጋቸው አለማሰባቸው ነው።
በዚህም ምክንያት ፈሪሳውያን የአዲስ ኪዳን ካሕናት የሆኑትን ደቀመዛሙርት እየነቀፉ ነበር።
ነገር ግን ከፈሪሳውያን ሐጥያት ሁሉ ትልቁ ሐጥያት ለመሲሁ እውቅና አለመስጠታቸው ነው። በዚህም ድርጊታቸው የብሉይ ኪዳንን ቃልኪዳን ማፍረስ ጀምረው ነበር፤ ለዚህ ነበር አዲስ ኪዳን ያስፈለገው።
ሙሴ ከእርሱ በኋላ ስለሚመጣ ታላቅ ነብይ አስጠንቅቆ ነግሯቸው ነበር።
ኤርምያስ ደግሞ ሊመጣ ስላለው አዲስ ኪዳን ተናግሯል።
ኤርምያስ 31፡31 እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤
ዘዳግም 18፡15 አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ታደምጣለህ።
ሙሴ መሲሁን እንዲያዳምጡት ነበር ያዘዛቸው፤ እርነሱ ግን መሲሁና በማዳመጥ ፈንታ በመሲሁ ላይ አቃቂር ያወጡበት ነበር።
ፈሪሳውያን እግዚአብሔርን በራሳቸው መንገድ ለማገልገል ይሞክሩ ነበር፤ ነገር ግን በዚያው አጋጣሚ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል መፈጸም ቸል እያሉ እና እየተቃወሙ ነበር።
ለሐጥያት ፍቱን የሆነ መስዋእት በሰዎች ጥረት ሊቀርብ አይችልም። በዚህም ምክንያት አይሁዳውያን የሚያቀርቧቸው መስዋእቶች ያለማቋረጥ በየዓመቱ ይደጋገሙ ነበር። ይህም የሰዎች ጥረት እና መስዋእት ውጤት አልባ መሆኑን ያሳያል።
ከቀራንዮ መስቀል በኋላ የአይሁዳውያን መስዋእቶች በሙሉ ተወግደዋል።
ከቤተመቅደሱ መስዋእቶች ውስጥ ብቸኛው ወደ አዲስ ኪዳን የሚዘልቀው ገጽታ በሐጥያተኞች ላይ ምሕረት የሚደረግበት የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው።
ማቴዎስ 12፡8 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።
ኢየሱስ ብቻ ነው በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ፍጹም የሆነውን መስዋእት ማቅረብ የቻለው። ስለዚህ እርሱ ብቻ ነው የሰንበት ጌታ፤ ከሐጥያት እና ከአለማመን ሊያሳርፈን የሚችል ጌታ።
ኢየሱስ ብቻ ነው እኛን በመንፈሱ በመሙላት ከሐጥያት እና ከአለማመን ሊያሳርፈን የሚችለው፤ መንፈሱም እንድናምን እና ቃሉን እንድናስተውል ያስችለናል።
ሐጥያታችን እንዲሰረይልን የሚያስፈልገንን ምሕረት ሊሰጠን የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው።
ከሐጥያት እና ከአለማመን እንድናርፍ የሚያደርገን የሐጥያት ይቅርታ ሙሉ በሙሉ በኢየሱስ መስዋእት እና በምሕረቱ ላይ የተመሰረተ ነው።
ኢሳይያስ 64፡6 ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤
እኛ ሰዎች ሐጥያታችንን በራሳችን ለማስተስረይ አቅም የለንም።
የምናረጋቸው ታላላቅ ጥረቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንደ መርገም ጨርቅ ናቸው።
ዳንኤል ወደ እግዚአብሔር የጸለየው በሰው ጽድቅ ወይም መልካም ሥራዎች ወይም መስዋእቶች በመደገፍ አይደለም።
ዳንኤል 9፡18 አምላኬ ሆይ፥ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት።
በአይሁዶች ዘንድ ከጥፋት በቀር ምንም መልካም ነገር እንደሌለ ዳንኤል ገብቶታል። ሙሉ በሙሉ ወድቀዋል።
ስለዚህ ዳንኤል የጸለየው በእግዚአብሔር ታላቅ ምሕረት በመደገፍ ብቻ ነው።
ማቴዎስ 12፡9 ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ።
ፈሪሳውያን ኢየሱስን ነቀፉ። ስለዚህ ኢየሱስ ከእነርሱ ተለይቶ ሄደ።
በኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጥቅስ እንኳ የምትነቅፉ ከሆነ ኢሱስን መንቀፋችሁ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው።
ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ትቷችሁ ስለሚሄድ መሃይሞች እና የማታምኑ ሰዎች ሆናችሁ ትቀራላችሁ።
ኢየሱስ እና ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ከእኛ ከሰዎች አእምሮ በላይ የሆነ ታላቅ ጥበብና ማስተዋል ይገልጣሉ።
ኢየሱስ ለውጥ እና ሰዎች ያልጠበቁትን ነገር ለማምጣት ነው የመጣው።
የተጻፈውን ማመን እና መረዳት እንችል ዘንድ ደግሞ ማስተዋል እንዲሰጠን መጸለይ አለብን። የተጻፈው እውነት ላይ አንዳችም ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም።
ማቴዎስ 12፡10 እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት።
ይህ እጁ የሰለለች ሰው በሰለለ እጁ ምንም ዓይነት ሥራ መስራት አይችልም ነበር። ስለዚህ ይህ ሰው በሰንበት ምንም ዓይነት ሥራ መስራት ስለማይችል ሕግን ሊተላለፍ አይችልም።
ይህም የሚያሳየን አንዳችም ስራ መስራት የማይችል ሽባ ሰው ብቻ ነው ሰንበትን በትክክል ሊጠብቅ የሚችለው። የፈሪሳውያን አስተሳሰብ ምን ያህል የዘቀጠ መሆኑ በዚህ ተገለጠ።
ማቴዎስ 12፡11 እርሱ ግን፦ ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?
እያንዳንዱ ገበሬ እንስሳቱን በየዕለቱ ውሃ ማጠጣት አለበት። በሰንበት ዕለት ተኩላ እንስሳቱን ሊበላ ቢማ ገበሬው ተነስቶ እንስሳቱን ከተኩላው ይከላከላቸዋል።
እንስሳቱ ማንኛውም ችግር ውስጥ ቢገቡ የትኛውም ገበሬ ተነስቶ ይረዳቸዋል። የተቸገረ እንስሳን መርዳት ማንም ሰው የሚደግፈው ድርጊት ነው።
በሰንበት ቀን ሥራ አትስሩ የተባለው አይሁዳውይን ገንዘብ የሚገኝበትን ሥራ በሰንበት ዕለት ከመስራት ተቆጥበው ቀኑን እግዚአብሔርን ለማምለክ እንዲያውሉት ተብሎ ነው።
ማቴዎስ 12፡12 እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው።
በችግር ውስጥ ያለ ሰውን መርዳት በችግር ውስጥ ያለ እንስሳን ከመርዳትም እንደሚበልጥ ነው ኢየሱስ ግልጽ አድርጎ ያስተማረው።
ማቴዎስ 12፡13 ከዚያም በኋላ ሰውየውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች።
ኢየሱስ ሰው ሊያደርገው የማይችለውን ግን እግዚአብሔር ብቻ ማድረግ የሚችለውን ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል ገለጠ።
እስከ ዛሬ ድረስ ዘመናዊ ሕክምን የሰለለ እጅ መፈወስ አልቻለም። ኢየሱስ ያደረገው ታላቅ ተዓምር ነው።
ማቴዎስ 12፡14 ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት።
ጠግበው የበሉ ፈሪሳውያን ርቧቸው የነበሩ ደቀመዛሙርት ጥቂት እሸት በእጃቸው ቀጥፈው በሉ ብለው ነቀፏቸው።
በእጁ እሸት ቀጥፎ መብላት የማይችል እጁ የሰለለች ሰው ሲያዩ ደስ ይላቸዋል።
ኢየሱስ ግን የማይሰራውን እጅ መከር መሰብሰብ የሚችል ጤናማ እጅ እንዲሆን አድርጎ ፈወሰ።
በቤተክርስቲያን ዘመናት መጨረሻ ላይ የሚሆነው መከር የሚፈጸመው ኢየሱስ የሰለለውን የቤተክርስቲያናችንን እምነት ወደ መጀመሪያው ዘመን ሐዋርያት እምነት ሲመልሰው ነው። የመጨረሻውን መከር የሚያስገኘውን እውነት እነርሱ ብቻ ነበሩ የሚያውቁት። በእጃቸው ያለፈው የቃሉ ዘር በመጨረሻው ዘመን ማብቂያ ላይ በስሎ ለመታጨድ ይደርሳል።
የቤተክርስቲያን መሪዎች ግን ዓለም አቀፍ የቤተክርስቲያኖች ምክር ቤት መስርተው አንድነት በመፍጠር ሥላሴ እና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ እምነቶችን ማስፋፋት መረጡ። ስለተገለጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት የነበራቸውም መረዳት ሰለለ።
መጽሐፍ ቅዱሳዊነት የጎደለው እምነታቸው ውስጥ ያለውን ጉድለት ለማካካስ ብለው ሰዎች በኪንግ ጄምስ ቨርዥን የነበራቸው እምነት እንዲጠፋ አደረጉ። አዳዲስ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞችን ሁል ጊዜ እያዘጋጁ ፍጹም የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት የማይቻል ነገር ነው ይላሉ። ዛሬ እንከን የሌለው መጽሐፍ ቅዱስ አለ ብለው የሚያምኑ ክርስቲያኖች በጣም ጥቂት ናቸው።
ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ችግር አለበት የሚሉ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ ጥርጣሬ እና አለማመን በጣም ተስፋፍቷል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰነዝሩት ትችት በኢየሱስ ላይ ትችት ከመሰንዘር ጋር እኩል ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ለዚህ ነው ኢየሱስ አሁን ከቤተክርስቲያን በር ውጭ የቆመው።
ማቴዎስ 12፡15 ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤
እውነት ኢየሱስ ነው። ፈሪሳውያን እርሱን ሊገድሉ ፈለጉ።
ዛሬ የቤተክርስቲያን ፓስተሮች የተገለጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሊገድሉ ይፈልጋሉ።
ሕዝቡ ኢየሱስን ወደዱት፤ ደግሞም ተከተሉት።
የሐይማኖት መሪዎቻቸው ግን ኢየሱስን አወገዙት።
ዛሬ የቤተክርስቲያን መሪዎች ናቸው መጽሐፍ ቅዱስን በመተቸት ኢየሱስን የሚያወግዙት። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው።
ማቴዎስ 12፡15 እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤
ኢየሱስ ታዋቂነትንም ሆነ ዝናን ፈልጎ አያውቅም።
በሰዎች ልብ ውስጥ ምን እንዳለ ያውቅ ነበር።
ሕዝቡ ኢየሱስን የተከተሉት ፈውስ ፈልገው ነበር፤ ምክንያቱም ፈውስ ከግል ጥቅማቸው ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። በመለኮታዊ ኃይል መገለጥ ይገርማቸው ነበር።
በሆሳእና ዕለት በአህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ያወድሱት የነበሩ ሕዝብ እራሳቸው ናቸው ከአራት ቀናት በኋላ ሐሙስ ዕለት “ስቀለው፤ ስቀለው” ብለው የጮሁት።
ኢየሱስን ሲያመሰግኑ ሲያወድሱ የነበሩትን ሕዝብ ይገደልልን ብለው እንዲጮሁ ለማሳመን የሐይማኖት መሪዎች አራት ቀን ፈጅቶባቸዋል።
መቸም የገቢ ምንጫቸው እንዳይቋረጥባቸው ይሰጉ ከነበሩ የቤተክርስቲያን መሪዎች ምን ይጠበቃል፤ ኢየሱስ በሆሳእና እሁድ ዕለት ሲያወድሱት ነበር፤ በዚያው ሳምንት ሰኞ ዕለት ገንዘብ ለዋጮችን ከቤተመቅደስ አባረራቸው።
ሰዎች ባህርያቸው እንዲህ ነው ቶሎ ቶሎ የሚለዋወጠው።
የቤተክርስቲያን መሪዎች ይህን ያህል ነው ለገቢ ምንጫቸው የሚጋደሉት።
ማቴዎስ 12፡17 በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል፦
ኢየሱስ ትንቢቱን ፈጸመ።
ማቴዎስ 12፡18 እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል።
ኢሳያስ አይሁዶች በስተመጨረሻ ኢየሱስን አንቀበልም እንደሚሉና ኢየሱስም በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ወደ አሕዛብ እንደሚዞር አውቋል።
ማቴዎስ 12፡19 አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም።
ኢየሱስ አይሁዶች እንዲከተሉት ማድረግ አልቻለም ምክንያቱም የሐይማኖች መሪዎቻቸው እርሱን እንዲጠሉት እና እንዲያስገድሉት ይገፋፉዋቸው ነበር።
ማቴዎስ 12፡20 ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም።
ሆኖም ግን ኢየሱስ ማመን ለፈለጉ ሁሉ ምንም ያህል በመንፈስ የተሰቡ ቢሆኑም እኳ ምሕረቱን ይገልጥ ነበር።
ነገር ግን ብዙ ያልተፈለጉ ውጤቶች መከሰታቸው አልቀረም።
አይሁዶች በስግብግ መሪዎቻቸው ተገፋፍተው ኢየሱስን ገፉት።
እርሱም ደግሞ አይሁዶችን ትቶ ቤተክርስቲያንን ለመመስረት ወደ አሕዛብ ዞረ።
ማቴዎስ 12፡21 አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።
ወንጌሉ በዓለም ዙርያ በተሰራጨ ጊዜ የኢየሱስ ስም በአሕዛብ መካከል ታላቅ ሆነ።
ማቴዎስ 12፡22 ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው።
ዕውር ዲዳ። ይህ ቃል አሕዛብ በብሉይ ኪዳን ዘመን የኖሩበትን ሁኔታ ያሳያል።
አሕዛብ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን እውነት አልሰሙም፤ ደግሞም በጣኦት አምልኮ ይመላለሱ ስለነበረ በመንፈስ ዕውሮች ነበሩ። እውነቱን በተመለከተ ዲዳዎች ነበሩ ምክንያም የሥላሴ እምነቶቻቸውና የፀሃይ አምልኮዋቸው ታላላቅ ስሕተቶች ነበሩ።
ዕውርና ዲዳ የነበረውን ሰው በመፈወስ ኢየሱስ ዕውር እና ዲዳ ለነበርነውን ጣኦት አምላኪ አሕዛብ እንደሚደርስልንና ወደ እውነት እንደሚመልሰን አሳየ።
ማቴዎስ 12፡23 ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና፦ እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን? አሉ።
ሕዝቡ በዚህ ተዓምር ተደነቁ። ኢየሱስ ማን መሆኑን አወቁ።
እርሱ የዳዊት ልጅ መሆኑን አወቁ።
ዳዊት የካሕናቱን ሕብስት በልቷል። ከዚህም የተነሳ ዳዊት እንደ ካሕን እንዲያገለግል ተፈቅዶለታል።
ኢየሱስ የዳዊት ልጅ እንደመሆኑ እርሱም እንደ ካሕን ማገልገል ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ በሰንበት ዕለት መስራት እና መፈወስ ይችላል ምክንያቱም ካሕናቱ በሙሉ ሕዝቡን ለማገልገል ብለው በሰንበት ይሰሩ ነበር።
ማቴዎስ 12፡24 ፈሪሳውያን ግን ሰምተው፦ ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ።
የሐይማኖት መሪዎች ኢየሱስን የአጋንንት አለቃ ነው ብለው ስሙን አጠፉ። የሐይማኖት መሪዎች ለእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ያላቸው ጥላቻ ይህን ያህል ነው።
ማቴዎስ 12፡25 ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም።
አስተሳሰባቸው ትልቅ ድክመት ያለበት አስተሳሰብ ነበር።
አጋንንት እርስ በራሳቸው ከተጋደሉ የሰይጣን መንግስት ልትቆም አትችልም።
ማቴዎስ 12፡26 ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?
ማቴዎስ 12፡27 እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።
አይሁዶች አጋንንት ከሰው ውስጥ ቢያስወጡ አይሁዶችም ራሳቸው አጋንንት ናቸው ማለት ነው። ይህ ምንም ትርጉም የለውም። እነርሱ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ነበሩ።
ማቴዎስ 12፡28 እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።
ኢየሱስ በስራው የእግዚአብሔርን ልዕለ ተፈጥሮአዊ መንፈስ እየገለጠ ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔር መንግስት ወደ አይሁዶች መጥታ ነበር።
ማቴዎስ 12፡29 ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።
ጋኔን ጠንካራ መንፈስ ነው፤ ሰውን ማሰር ይችላል።
መንፈስ ቅዱስ መጀመሪያ ያንን ኃይለኛ መንፈስ ማሰር እና ከሰው ውስጥ አውጥቶ መጣል አለበት። ከዚያ በኋላ ነው የሰውየው አካል ወደነበረበት ጤና መመለስ የሚችለው
ማቴዎስ 12፡30 ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል።
መሃል ቤት መሆን አይቻልም። በኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ቃል አንድ በአንድ እናምናለን ወይ ደግሞ እውነትን ለመቀበል እምቢ እንላለን።
ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰኑ ክፍሎችን አምነን ቀሪዎቹን እምቢ ማለት አንችልም። እንደዚያ ካደረግን እንበትናለን እንጂ አናከማችም።
ከውሸቶች ሁሉ የከፋ ውሸት ግማሽ እውነት ነው።
ከሁሉ የከፋ ስሕተት የሰው አመለካከት የተቀላቀለበት መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
ማቴዎስ 12፡31 ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም።
መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ፈውስን ያደርጋል። ፈውስን የሚያደርገው ሰይጣን ነው አትበሉ።
መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል።
ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤
ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር በትክክል የሚገጥሙ የተገለጡ የእግዚአብሔር ቃል ሚስጥራትን አትንቀፉ።
ማቴዎስ 12፡32 በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።
የመንፈስ ቅዱስን ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል መተቸት አይቻልም።
የተገለጡትን ጠለቅ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መተቸት አይፈቀድም።
ማቴዎስ 12፡33 ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ።
ልዕለ ተፈጥሮአዊ ፈውስ እና መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ራዕይ ድረስ ተያይዞ የሚመጣ መገለጥ ከሰይጣን አይገኝም።
ማቴዎስ 12፡34 እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና።
የእባቡ ዘር። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን ኢየሱስን የሚነቅፉ ሰዎች በውስጣቸው ችግር አለባቸው ማለት ነው። በውስጣቸው ያለው ችግር በአፋቸው ወጥቶ ይገለጣል። ኢየሱስን ሲነቅፉ በውስጣቸው በልባቸው እንደሚቃወሙት ተገለጠ።
ማቴዎስ 12፡35 መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።
መልካሞቹ ሰዎች ኢየሱስን ወይም ኪንግ ጄምስ ቨርዥነ መጽሐፍ ቅዱስን አይነቅፉም። የሚያስተምሩት አስተምሕሮ የኢየሱስን እና የኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን ፍጹምነት አጉልተው ያሳያሉ።
ክፉዎቹ ሰዎች ሁልጊዜ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን ይነቅፋሉ፤ ደግሞም የተገለጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይቃወማሉ።
ማቴዎስ 12፡36 እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤
የምንናገረው እያንዳንዱ ቃል በእኛ ላይ ምስክር ሆኖብን ይመጣል። መጽሐፍ ቅዱስን በፍጹም አታክፋፉ። በእግዚአብሔር እቅድ ላይ አታጉረምርሙ። እኛ የተጠራነው እውነቱ ላይ እንድንከራከርበት ሳይሆን እንድናምን ነው።
ማቴዎስ 12፡37 ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ።
ብናጉረመርም ወይም ለሚገጥሙን ፈተናዎች እግዚአብሔርን ተጠያቂ ብናደርግ ከባድ ችግር ውስጥ ነን ማለት ነው።
መልካምም ሆነ ክፉ የሚገጥመን ነገር ሁሉ ለምክንያት ነው የሚገጥመን።
ሕይወታችን በሙሉ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ውስጥ መሆኑን ማመን አለብን።
ከአፋችን የሚወጡ ቀላት እግዚአብሔርን በውዳሴ የሚያመሰግኑ መሆን አለባቸው። እምነታችን ሁልጊዜ ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን አለበት።
ማቴዎስ 12፡38 በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና፦ መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ።
ሰው ይደክማል። እኛ ምልክት ማየት እንፈልጋለን። የምናምነው ምልክት ስናይ ብቻ ነው።
ይህ ግን ጥሩ አካሄድ አይደለም።
ብዙ ጊዜ ሰዎች ምልክት ሲያዩ ዋነኛው ክስተት እራሱ ይመስላቸዋል።
የ1963ቱ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ደመና በሰማይ ላይ የተገለጠ የሰው ልጅ ምልክት ነበረ።
ይህም ሰባቱ ማሕተሞች እንደሚገለጡ የሚያመለክት ምልክት ነው።
የሜሴጅ አማኞች ግን ወዲያው ያሰቡት ደመናው የጌታ ምጻት ነው ብለው ነበር። ያም ካልሆነ ደግሞ የራዕይ ምዕራፍ 10 ብርቱ መልአክ ወደ ምድር መውረድ ነው ብለው ነው ያሰቡት።
ስለዚህ ብዙ ዓይነት የተሳሳቱ አስተምሕሮዎች ተከትለው መጡ፤ ለምሳሌ “ምሕረት አብቅቷል፣” “ሰባቱ ነጎድጓዶች ንግግራቸውን አሰምተዋል”።
ማንም የማያውቀውን የጌታን አዲስ ስም አውቀነዋል ብለው የተለያዩ የሜሴጅ ፓስተሮች የተለያዩ ስሞችን ተናግረዋል።
ምልክቶች ብዙ ሊያሳስቱ ይችላሉ።
ማቴዎስ 12፡39 እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።
ክፉ ሰዎች ምልክት ማየት ይፈልጋሉ። እውነተኛ ሰዎች ግን ምልክት ሳያዩ የተጻፈውን ብቻ ለማመን ፈቃደኞች ናቸው።
ማቴዎስ 12፡40 ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።
ለእኛ አንዱ ዋነኛው ምልክታችን የኢየሱስ ሞት፣ ቀብር፣ እና ትንሳኤ ነው።
ሶስት ሌሊት መቃብር ውስጥ አድሮ ነው እሁድ ጠዋት በሌሊት ከሙታን የተነሳው።
ሐሙስ ማታ፣ አርብ ማታ፣ ቅዳሜ ማታ።
ስለዚህ ኢየሱስ የሞተው ሐሙስ ዕለት ነው።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ግን ኢየሱስ የሞተው “የስቅለት አርብ” ዕለት ነው ብላ ታስተምራለች፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም።
ኢየሱስ የሞተው አርብ ዕለት ከሆነ በመቃብር ውስጥ ሶስት ሌሊት ሊቆይ አይችልም፤ ይህም ሆኖ ግን ፕሮቴስታንቶች አርብ መሞቱን እውነት አድርገው ይቀበላሉ።
ከዚህም የተነሳ የተሰጠንን ዋነኛ እና ታላቅ ምልክት እንጠመዝዘዋለን።
ስለዚህ ምልክቶች እንዲሰጡ የታሰበላቸውን ጥቅም ብዙ ሰዎች አይጠቀሙም።
ማቴዎስ 12፡41 የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
ነነዌ የአሕዛብ ከተማ ነበረች።
አሕዛብ የዮናስን (የዕብራዊውን) ስብከት አመኑ።
ኢየሱስ አሁንም ከሞቱ፣ ከቀብሩ እና ከትንሳኤው በኋላ ወንጌል ወደ አሕዛብ እንደሚሄድ እያሳየ ነው።
ማቴዎስ 12፡42 ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።
የሳባ ንግሥት ከአፍሪካ የመጣች የአሕዛብ ወገን ነበረች፤ እርሷም ስለ ሰሎሞን አምላክ ሰምታ ይበልጥ ለማወቅ ስለትል የሰሃራ በረሃን በታላቅ ችግር አቋርጣ ሄደች። የሰሎሞን ጥበብ ይህን ያህል በምድር ዙርያ አስደናቂ ስለነበረ ሰዎች እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር መሆኑን ሊያውቁ ችለዋል።
ኢየሱስ በድጋሚ አንዲትን ከአሕዛብ ወገን የሆነች የአሕዛብ ቤተክርስቲያንን የምትወክል ሴት በመጥቀስ የመጽሐፍ ቅዱስን ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ለመማር ብዙ ችግር እንደምታልፍ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሃሳብ ይገልጥልናል።
በቀጣዩ ምሳሌ ወደ አይሁድ እንመለሳለን።
ማቴዎስ 12፡43 ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም።
ኢየሱስ እሥራኤል ውስጥ ሰይጣንን አሸነፈ። ሰይጣን ዋና ዓላማው እግዚአብሔርን መተካት እንደመሆኑ ሌላ ዓላማ የለውም።
ማቴዎስ 12፡44 በዚያን ጊዜም፦ ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል።
የኢየሱስ ደም ቤተመቅደሱን አንጽቶታል።
ስለዚህ አይሁዶች አዲስ ኪዳንን እንዳይቀበሉ ለማድረግ ሰይጣን ተመልሶ ወደ እሥራኤል ሄደ።
የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝቦች ቢሆኑም እንኳ ሰይጣን እየመራቸው ነበር፤ ደግሞም በአለማመን አስሯቸው ነበር።
ማቴዎስ 12፡45 ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።
ለሰባት የቤተክርስቲያን ዘመናት ሰይጣን አይሁዳውያን የአዲስ ኪዳን እውነቶችን እንዳይቀበሉ አድርጓል። በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ማለቂያለ ላይ የሰባቱም የቤተክርስቲያን ዘመናት ሁሉ ክፋት ተጠራርጎ ወደ እሥራኤል ይገባል።
በዚያን ጊዜ አሁን እንደሆነው ለአይሁዳውያን እንደ ሕዝብ ወደ ወንጌል እምነት መምጣት ከባድ መስሎ ይታያል።
የሁለቱ ነብያት ማለትም የሙሴ እና የኤልያስ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል እንዲሁም በታላቁ መከራ ውስጥ የሚሆነው የብዙ ሰዎች እልቂት ብቻ ነው ኢየሱስን እንዲቀበሉ የሚያደርጋቸው። አይሁዳውያን ፈጽመው ከመጥፋታቸው በፊት ኢየሱስ ሊታደጋቸው ይመጣል። በዚያ ጊዜ ከእሥራኤል ሕዝብ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑነት ይገደላሉ።
ከዚያ ወዲያ 144,000 አይሁዳውያን ኢየሱስ መሲሁ መሆኑን ይቀበላሉ።
ይህ በታላቁ መከራ ድንጋጤ እና ሰቆቃ የሚጠናቀቀው ምሳሌ ስለ ሰነፎቹ ቆነጃጅት ጭምር ነው የሚናገረው።
የጥንቷ ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጸድታ በሐዋርያት ተተክላለች። ሐዋርያት ከተገደሉ በኋላ ሰይጣን ወደ ቤተክርስቲያን አመራር ውስጥ ሾልኮ በመግባት ጳጳሶች የከተማ ገዥ እንዲሆኑ አደረገ። ይህን ተከትሎ ሥላሴ፣ የአሕዛብ ልማዶች፣ እና ፖለቲካ ወደ ቤተክርስቲያን ውስጥ ገቡ። በገንዘብ ብዛት እና በአጋንንታዊ አሰራር የተቀነባበረው የሰባቱ ዘመናት ክፋት ሰነፎቹን እና የተታለሉትን ቆነጃጅት ይዟቸው ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ያስገባቸዋል። ቆነጃጅት ንጹህ ሴቶች ናቸው። ስለዚህ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የዳኑ ሰዎችን ይወክላሉ።
በታላቁ መከራ ውስጥ የሚከሰት እልቂት እና ዘግናኝ ሰቆቃ ብቻ ነው ከሰነፎቹ ቆነጃጅት ላይ የቤተክርስቲያን ልማዶችን ሊያራግፍ የሚችለው።
ማቴዎስ 12፡46 ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር።
ኢየሱስ አይሁዳዊ ቤተሰብ ነበረው። እነርሱም እናቱ እና አራት ወንድሞቹ ናቸው።
ማቴዎስ 12፡47 አንዱም፦ እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል አለው።
ማቴዎስ 12፡48 እርሱ ግን ለነገረው መልሶ፦ እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው።
ኢየሱስ በዘመድ አያዳላም። በስጋ ቤተሰቦቹ ለሆኑት ሰዎች አድልቶ አያውቅም።
ማቴዎስ 12፡49 እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፦ እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤
ቤተሰቦቹ እነማን እንደሆኑ ለማሳየት ኢየሱስ በስጋ ቤተሰቡ የሆኑትን አይሁዳውያን ትቶ ወደ ደቀመዛሙርቱ አመለከተ።
ኢየሱስ ከአይሁዶች ተለይቶ ወደ አሕዛብ የሚሄድበት ጊዜ እየተቃረበ ነበር።
ደቀመዛሙርቱ እውነተን በአሕዛብ መካከል ለማሰራጨት በዝግጅት ላይ ነበሩ።
ኢየሱስ አንድ ፍላጎት ብቻ ነው የነበረው።
ይኸውም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ፈቃደኛ ማነው? የሚለውን ማወቅ ነው።
የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑት ሰዎች ናቸው የኢየሱስ ሙሽራ ወይም የአሕዛብ ቤተክርስቲያን የሚሆኑት።
እውነተኛ ቤተሰቦቹ እነዚህ ናቸው።
ማቴዎስ 12፡50 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።
የእግዚአብሔር ቤተሰብ መሆን ከፈለግን ለሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ያዘጋጀውን ትልቅ እቅድ ማወቅ ያስፈልገናል።