ማቴዎስ ምዕራፍ 10
We update studies as the Lord Jesus leads us. You can find the latest update of this study at ChurchAges.net
ደቀመዛሙርቱ በእግዚአብሔር አቅርቦት ላይ ብቻ በመተማመን እንዲሄዱ ተላኩ። የመጣ ይምጣ እንጂ እግዚአብሔርን ማስቀደም አለባቸው።
First published on the 7th of March 2021 — Last updated on the 5th of November 2022ማቴዎስ 10፡1 አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው።
ደቀመዛሙርቱ በሙሉ በአጋንንት እና በበሽታዎች ላይ ስልጣን ተሰጥቷቸው ነበር።
ይህም የአስቆሮቱ ይሁዳን ይጨምራል።
ስለዚህ በመለኮታዊ ኃይል ማገልገል አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በመልካም ሕብረት ውስጥ መሆኑን ማስረጃ አይደለም።
ማቴዎስ 7፡21 በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።
መዳን እና ኢየሱስን “ጌታ” ብሎ መጥራት አስፈላጊ የሆነ የመጀመሪያ እርምጃ ነው።
በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ የመሆን ማረጋገጫ አይሆንም።
ከሲኦል እናመልጥ ዘንድ እግዚአብሔር እንድንድን ይፈልጋል፤ እግዚአብሔር ከታላቁ መከራ ስሕተት ሊያድነን የተገለጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንድናውቅ ይፈልጋል።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዳናውቅ የሚያደናቅፈን ትልቁ እንቅፋት “አንድ እግዚአብሔር በሶስት አካላት” እያለ የሚናገረው የሥላሴ አስተምሕሮ ነው።
ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ ማለት ሁለት አካላትን ይወክላል።
ይህም አነጋገር አብ እና ወልድን ሁለት የተለያዩ አካላት አድርጎ በማየት ነው። ይህም እንዲህ የሚያምኑ ሰዎች እግዚአብሔርን የሚጠሩበት ስም እንደሌላቸው ያሳያል። ለሁለት ሰዎች አንድ ስም መስጠት አይቻልም።
ከዚያ ቀጥለው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌሉ ቃላት ይናገራሉ፤ ለምሳሌ፡- “እግዚአብሔር ወልድ” እና “እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ”። “የመለኮት የመጀመሪያው አካል” እና “የመለኮት ሁለተኛው አካል” ይላሉ።
“አብ እና ወልድ አንድ ባህሪ ናቸው” (ምን ማለት እንደሆነ አናውቅም) እንዲሁም “ዘላለማዊ ልጅነት” የሚለውም አነጋገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።
ማቴዎስ 7፡22 በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።
45,000 ዓይነት የተለያዩ ቤተክርስቲያኖች እና ዲኖሚኔሽኖች አሉ፤ እነዚህም ሁሉ የየራሳቸው የተለያየ ሃሳብ አላቸው። አብዛኞቹ እምነታቸው የተለያየ ቢሆንም እንኳ አስደናቂ መለኮታዊ ኃይል ይገለጥባቸዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ ተመሳሳይ እና አስደናቂ ተዓምራዊ ኃይል ማሳየት ቢችሉም እምነታቸውና አመለካከታቸው እጅግ በጣም እንደሚለያይ መደበቅ አይቻልም።
ስለዚህ የሚያደርጓቸው ተዓምራት እውነትን በማመናቸው ላይ የተመሰረቱ አይደሉም።
እግዚአብሔር መኖሩን የማያምኑ ሰዎች እንኳ ከልባቸው ጥያቄ ሲጠይቁ አስደናቂ መልሶችን ተቀብለው ያውቃሉ። በዓመጽ የሚኖረው ሊቀካሕናቱ ቀያፋ ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ ትንቢት ተናግሯል። በሐጥያት የሚመላለሰው ነብይ በለዓም ኮከብ አያለው ብሎ ትንቢት ተናገረ፤ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ከምሥራቅ ኮከብ እየተከተሉ የመጡ ጠቢባን ሰዎች በኮከብ እየተመሩ ክርስቶስን አግኝተዋል።
ሐሰተኛ መንፈስ በእግዚአብሔር ተልኮ አካብን እየመራው ወደ ሞት አድርሶታል። እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጸም ማንኛውንም ሰው መጠቀም ይችላል፤ ካስፈለገ አህያንም ይጠቀማል።
ሮሜ 11፡29 እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና።
ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል እና ክብር ሲገለጥ የሰዎችን ትኩረት ይስባል። እግዚአብሔር ግን የሚፈልገው የግል ጥቅማቸውን የሚፈልጉ ሰዎችን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መከተል የሚፈልጉትን ነው።
ማቴዎስ 6፡33 ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማግኘት በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። የእግዚአብሔር ፈቃድ ከእኛ የግል ፈቃድ በጣም ይለያል።
ስለዚህ ያልተጠበቀውን ለመቀበል ተዘጋጁ። እግዚአብሔርም ለእኛ ያስፈልጋል ብሎ ያመነበትን እንዲጨምር ሁሉን ለእርሱ ተዉለት።
እነዚህ ሰዎች ስማቸውን በሕዝብ ዘንድ ያገነነ ትልልቅ ተዓምራትን በሰዎች መካከል አደረጉ። እግዚአብሔር ግን እይታው ከሰው ይለያል። እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው ምን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት እንደተረዱ በማየት ነው። በዚህም መስፈርት እነርሱ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ወደቁ ምክንያቱም ከበድ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን መረዳት ብዙም አስፈላጊ ያልሆነ ዝርዝር ውስጥ መግባት ነው ብለው ቆጥረዋል። ከበድ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልችን ትርጉም ባለማወቃቸው ሰዎችን በሚያስደንቅ ተዓምራዊ አገልግሎቶች ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ። እግዚአብሔርም አልተቀበላቸውም።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ማለት ተዓምራዊ ኃይልን ከመግለጥም ይበልጣል።
ማቴዎስ 7፡23 የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።
ዓመጽ ማለት ስሕተት መሆኑን እያወቅህ ማድረግ ማለት ነው።
በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር ተሰውሮ የነበረውን የተጻፈውን ቃል ሚስጥር እየገለጠ ነው። ከዚህ የበለጠ አስፈላጊ ነገር ምንም የለም።
እግዚአብሔር የክርስቶስ ተቃዋሚውን ሐይማኖታዊ ፈረሰኛ ስሕተቶች እያጋለጠ ነው።
ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ዘመን ሲጠይቁት መጀመሪያ የተናገረው ስል ስሕተት ማስጠንቀቂያ ነው።
ማቴዎስ 24፡4 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
ስሕተትን እውነት ነው ብላችሁ ብታምኑ የክርስቶስ ተቃዋሚ አስቷችኋል ማለት ነው። መንፈሳዊ ልምምዳችሁ ምንም ያህል አስደናቂ ቢሆን እንኳ ስታችኋል።
ሙሴ 12 ሰላዮችን ወደ ተስፋይቱ ምድር ልኮ ነበር። ኢየሱስን 12 የተመረጡ ደቀመዛሙርትን ወይም ሐዋርያትን ወደ ተስፋይቱ ምድር የላከው የሙሴ ሕግ በጸጋ ዘመን ውስጥ ወደ ፍጻሜ ስለ ማምጣቱ ምልክት ይሆን ዘንድ ነው።
ይሁዳ ብቻ ሲቀር ሌሎቹ አሥራ አንድ ደቀመዛሙርት በልዕለ ተፈጥሮአዊ የኃይል ስጦታቸው አማካኝነት በአይሁድ ሕዝብ ላይ ታላቅ ተጽእኖ አምጥተዋል። ሰይጣንም ኃይለኛ ተቃዋሚ እንደተነሳበት አወቀ።
ከዚህም የተነሳ ሰይጣን የአይሁድ ሐይማኖት መሪዎችን ያለማቋረጥ በመጠቀም ኢየሱስን ለማጥመድና ለመግደል ሙከራውን ቀጠለ።
የአይሁድ ሐይማኖት መሪዎች አንድ ዓላማ ብቻ ነበራቸው። እርሱም በሕዝቡ ላይ የነበራቸውን ስልጣን እና የገቢ ምንጫቸውን ለማስጠበቅ ሕዝቡ በኢየሱስ ላይ እንዲነሱበት ማድረግ ነው።
በመጨረሻው ዘመን የቤተክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ዝንባሌ ይኖራቸዋል። የሎዶቅያውያን ቤተክርስቲያን ሃብታም ናት።
ክርስትና ትልቅ ንግድ ሆኗል። መጽሐፍ ቀዱስ ፓስተሩ የቤተክርስቲያን ራስ ነው አይልም፤ ነገር ግን ፓስተሮች ለገንዘብ ብለው የቤተክርስቲያን ራስ ነን ይላሉ። ከዚያ በኋላ አገልግሎታቸው የቤተሰብ ንግድ ይሆንና አባትየው ፓስተር ሆኖ ብዙ ዓመት ከቆየ በኋላ ልጅየው ፓስተር ይሆናል። በዚህም መንገድ ገንዘቡ በቤተሰባቸው ውስጥ ይቆያል።
ሐዋርያ የነበረው ይሁዳ ለገንዘብ ብሎ ነው የሐዋርያነት ክብሩን የጣለው። የዚህ ዘመን ፓስተሮች ትልቁ ችግራቸውም ይህ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ በትልክክል ባለማስተማራቸው ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ቃል እንዲርቁ ያደርጋሉ። የሚመቻቸውን ጥቅስ በመምረጥ እና የማይፈልጉትን ደግሞ ቸል በማለት ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን ትተው በሰው አመለካከት እየተመሩ ይኖራሉ። በሜሴጅ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ እንደ ቫይረስ ተሰራጭቷል።
ማቴዎስ 10፡2 የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን ወንድሙ እንድርያስም፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብም ወንድሙ ዮሐንስም፥
መጀመሪያ የተጠቀሰው ሐዋርያ ጴጥሮስ ነበር፤ እንደዚያም ሆኖ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሐዋርያት አለቃ አልተባለም፤ የሮማ ካቶሊኮች ግን የሐዋርያት አለቃ ነው ይላሉ።
ማንም ሰው የቤተክርስቲያን አለቃ ተብሎ አያውቅም። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ማዕረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ላልሆኑት ካርዲናሎች ተብሎ የተፈጠረ ነው።
ማቴዎስ 10፡3 ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ቶማስም ቀራጩ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ታዴዎስም የተባለው ልብድዮስ፥
ልብድዮስ ታዴዎስ ወይም ይሁዳ የተባለው ሰው የእልፍዮስ ልጅ የያዕቆብ ወንድም ነው።
ሉቃስ 6፡16 የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው።
ማቴዎስ 10፡4 ቀነናዊውም ስምዖን ደግሞም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
ሉቃስ 6፡15 … ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥
ቀናተኛ የሚባሉት ሰዎች ጽንፈኛ ወይም አክራሪ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ሰዎች ናቸው። ሮማውያን እነርሱን እንደ አሸባሪዎች ይቆጥሯቸዋል።
ስለዚህ ከደቀመዛሙርት መካከል ከሶስት ቤተሰብ ወንድማማች የሆኑ ሰዎች አሉ።
በደቀመዛሙርት መካከል ወንድማማችነት ትልቅ ቦታ የተሰጠው ጉዳይ ነው። ወንድማማች እኩል ናቸው። የትኛውም ወንድም ከየትኛውም ወንድም አይበልጥም።
አንድ ደቀመዝሙር ከሌላ ደቀመዝሙር የበለጠ ስጦታ ሊኖረው ይችላል ግን ሁላቸውም በስልጣን እኩል ናቸው ምክንያቱም ሁላቸውም ለመጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚገዙት።
1ኛ ጴጥሮስ 2፡9 እናንተ ግን … የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ … ናችሁ፤
ክርስቲያኖች ሁሉ ካሕናት ናቸው። ካሕናት ሁሉ በስልጣናቸው እኩል ናቸው። የትኛውም ካሕን ከየትኛውም ካሕን አይበልጥም። ከካሕን የሚበልጠው ሊቀካሕናቱ ብቻ ነው፤ እርሱም ኢየሱስ ነው።
ማቴዎስ 10፡5 እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ፦ በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤
ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ የመጀመሪያው ምጻቱ ለአይሁድ ሕዝብ ብቻ ነበር። ኢየሱስ የዛኔ የመጣው ለአሕዛብም አይደለም፤ ለሳምራውያንም አይደለም። አይሁዶች ግን አንቀበልህም አሉት፤ ስለዚህ ወደ አሕዛብ ዞረ።
ስለዚህ ዳግም ምጻቱ ወደ አሕዛብ ቤተክርስቲያን ነው የሚሆነው እንጂ ወደ አይሁዶች አይደለም። አብዛኞቹ አሕዛቦች ስለገፉት ጥቂቶች የሆኑት የሙሽራይቱን አካላት ወደ ሰማይ ይዟቸው ይሄድና ከዚያ በኋላ ወደ አይሁዶች ይመለሳል።
ማቴዎስ 10፡6 ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ።
አይሁዶች የሙሴን ሕግ እንታዘዛለን ይሉ ነበር፤ ነገር ግን በሮማውያን ላይ ባላቸው ጥላቻ የተነሳ የሙሴን ሕግ የሚጠብቁበት መንገድ ጠፍቶባቸዋል። ከዚያም በተጨማሪ ቤተመቅደሱም ተበላሽቶ የንግድ ቤት ሆኗል።
ፖለቲካ እና ገንዘብ ወደ ሐይማኖት ውስጥ ሲገቡ የሁለቱ ድብልቅ የሚፈጥረው ውጤት መርዛማ ነው።
አንድ ሰው በግል ጉዳዩ ሲጠመድ ያ ሰው በራሱ ዙርያ ትንሽዬ ጥቅል ሆኖ ይቀራል።
ማቴዎስ 10፡7 ሄዳችሁም፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ።
ዳንኤል በጻፈው ትንቢት መሰረት ከሰባዎቹ ሱባኤዎች ውስጥ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ለአይሁዶች አንድ ሱባኤ (ወይም ሰባት ዓመታት) ብቻ ቀርቷቸው ነበር።
ላባ ለያዕቆብ እንዲህ አለ፡-
ዘፍጥረት 29፡27 ይህችንም ሳምንት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።
ስለዚህ የትንቢት ቃል ውስጥ አንድ ቀን አንድ ዓመትን ይወክላል።
ማቴዎስ 10፡8 ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ።
ወንጌሉ ነጻ አገልግሎት እንዲሆን ነው የተወሰነው። እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው የቤተክርስቲያን አባላት ላልሆኑ ሰዎች በረከት እንድትሆን ነው።
ደቀመዛሙርት ለአይሁድ እየሰበኩ በዞሩ ሰዓት ታላቅ ተዓምራዊ ኃይል በእጃቸው ተገልጧል።
ሆኖም ይህ ሁሉ አይሁዶች እንዲያምኑ ሊያደርጋቸው አልቻለም። ለጊዜው ብቻ አስደንቋቸው ነው ያለፈው።
በስተመጨረሻ የሐይማኖት መሪዎቻቸው ኢየሱስን እንዲገድሉ አነሳሷቸው፤ እነርሱም ገደሉት። ብዙ ተዓምራት በስሙ ሲደረግ ቢያዩም እንኳ እርሱን ከመግደል ወደ ኋላ አላሉም።
ልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል የሰዎችን ትኩረት ይስባል፤ ነገር ግን ሰዎችን በእምነት ሊያጸናቸው አይችልም።
ማቴዎስ 10፡9 ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥
ደቀመዛሙርቱ በራሳቸው ገንዘብ ሳይሆን በእግዚአብሔር አቅራቢነት ማመን ነበረባቸው።
ገንዘብ የድርጅቶች ሕይወት ነው። በቂ ገንዘብ ከተገኘ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሌለበትን የቤተክርስቲያን ድርጅት ማዋቀር ይቻላል።
ናቡከደነጾር ከተለያዩ ብረቶች የተሰራ የአሕዛብ ምስል አየ።
የባቢሎን ራስ ወርቅ ነበር፤ ምሳሌነቱም በሃብት ላይ የተመሰረተ ሐሰተኛ ሐይማኖት ወይም አሳሳችነት ነው።
ክንዶች እና ደረት ከብር የተሰሩ መሆናቸው ደግሞ ሁሉን በክንዱ ማድቀቅ የሚችለውን ማዕከላዊ የፋርስ እና የሜዶንን አምባገነን መንግስት ጉልበት ያመለክታል። ጠንካራ በሆነ አወቃቀር የተደራጁ በመሆናቸው ፋርስ እና ሜዶን ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉ ለንጉስ እንዲታዘዙ የተደረገበትን ዓለም አቀፍ መንግስት መመስረት ችለዋል።
ቤተክርስቲያናዊ ወይም ሐይማኖታዊ ድርጅቶች ሕዝቡ ለቤተክርስቲያን እምነቶች እንዲታዘዙ በቀላሉ ማስገደድ ይችላሉ። አንድ ግለሰብ ብቻውን አንድን ድርጅት ለመቃወም ይከብደዋል።
የሕይወት መውጫ ያለበት ወገቡ የተሰራው ከነሃስ ነው። ይህም ለክርስቶስ ተቃዋሚ ሥርዓት ኃይል የሚሰጠውን ጸረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የቤተክርስቲያኖች ስርዓት የሚያስፋፋውን የግሪክ ፍልስፍና ይወክላል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሃሳቦችን ሰዎች በቀላሉ ይማራሉ፤ ከዚያ በኋላ ከአእምሮዋቸው ለማውጣት በጣም ከባድ ይሆናባቸዋል። ለምሳሌ ሥላሴ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ አምላክ በሶስት አካላት፤ ክሪስማስ፣ ዲሴምበር 25፣ የስቅለት አርብ፣ እሁድ ሰንበት ነው፣ ፓስተሩ የቤተክርስቲያን ራስ ነው እና የመሳሰሉት።
ከእነዚህ ሃሳቦች አንዳቸውንም አትቀበሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ብቻ እመኑ።
ማቴዎስ 10፡10 ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።
እግዚአብሔር ደቀመዛሙርቱ ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ አልፈለገም። የፈለገው ሙሉ በሙሉ በእርሱ እንዲደገፉ ነው።
ከረጢት እረኞች የሚይዙት ትንሽዬ ቦርሳ ነው።
ሁላችንም ቤተክርስቲያኖች ያስተማሩንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሃሳቦች የሞሉበትን ትንሽ ቦርሳ ይዘን ዞረናል።
በፍጹም የራሳችሁን ሃሳብ ተሸክማችሁ አትዙሩ። መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውን ብቻ ብታምኑ ይበቃችኋል።
1ኛ ሳሙኤል 17፡40 በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ።
ማቴዎስ 10፡11 በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ።
በዚያ አንድ ስፍራ ተቀምጣችሁ ቆዩ። የተሻለ መስተንግዶ ለማግኙት ብላችሁ ከአንድ ቤት ወደ ሌላ ቤት አትዘዋወሩ። ነገር ግን መጀመሪያ የምትገቡበት ቤት ሰዎች መልካም ስም ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን አረጋግጡ። በክፉ ሰዎች ቤት ውስጥ ማረፍ የወንጌሉን ስም ያጠፋል።
የሚገባው ማለት የሚቀበሉዋችሁ ቤተሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥር መረዳት የሚችሉ ማለት ነው፤ ከዚህም የተነሳ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ጥቅሶች ተገጣጥመው አንድ ወጥ የሆነ መልእክትን በመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ያስተላልፋሉ።
ራዕይ 5፡4 መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ።
የትኛውም የሰው ጥበብ የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት ለመረዳት እገዛ አያደርግም። የሰባቱን ማሕተሞች መገለጥ ሰባት መላእክት ናቸው ለወንድም ብራንሐም በመጋቢት ወር 1963 ይዘው ያመጡለት። እርሱ ካስተማረን ትምሕርት በመነሳት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር መረዳት አለብን።
ራዕይ 3፡4 ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።
ነጭ ቀለም በቀስተ ደመና ውስጥ ያሉ ሰባት ዋና ዋና ቀለሞች ሲደባለቁ ነው የሚፈጠረው።
የመጨረሻው ዘመን ውስጥ ያለችዋ ቤተክርስቲያን ስለ ሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት እውነቱን መማር አለባት። ይህም እውቀት ቤተክርስቲያኖች በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የሰበሰቧቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ስሕተቶችን በሙሉ አውጥተው እንዲጥሉ ያስችላቸዋል።
ከዚያ በኋላ የተለያዩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንድ ላይ አገጣጥመን የተሰወረውን እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሙሉ ተከታትለን ማየት እንችላለን።
እያንዳንዱ አስተምሕሮ ዘፍጥረት ውስጥ ጀምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁሉ ይገኝና በራዕይ ውስጥ መጠናቀቅ አለበት። እነዚህ የመጀመሪያው እና የመጨረሻው መጻሕፍት ናቸው።
ከዚያ በኋላ ብቻ ነው ሙሽራይቱ ወደ መጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን እምነት መመለስ የምትችለው።
ክርስቲያን በሚለው ስም ለመጠራት ብቁ ሆነን እንድንገኝ በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እያንዳንዱ ስሕተት የሌለበት ፍጹሙ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ማመን አለብን።
ያዕቆብ 2፡9 ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል።
ፓስተሮች የቤተክርስቲያን ራስ ነን ብለው ራሳቸውን ከፍ ማድረግ የለባቸውም። ይህ ዓይነቱ ልማድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም።
63-0707 ክሱ
የት ነው የተሰቀለው? ፓስተሮች ባሉበት ነዋ። እናንተ ግብዞች
በቃሉ ፈንታ የሰዎችን ትምሕርት በማስተማራቸው የሕይወት ራስ የሆነው ሰቅለዋል።
ወንድም ብራንሐም የሰው ልጅ ነው ወይም የእግዚአብሔር ድምጽ ነው ብለን ከፍ ልናደርገው አይገባም። ይህ ዓይነቱ ክብር የኢየሱስ ብቻ ነው።
60-0804 ንስር ጎጆዋን ታናውጣለች
እነግራችኋለው፤ የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ይጠቅማችኋል፤ በልባችሁ የሚናገራችሁን ትንሽዬ የዝምታ ድምጽ መስማት ይጠቅማችኋል። የሕዝቡን ትኩረት ይስባል።
… ሙሽራይቱ ትክክል መሆኗን እናውቃለን፤ ይህ የእኔ ድምጽ አይደለም፤ የሚናገራችሁ የእግዚአብሔር ድምጽ ነው
64-0823 ጥያቄዎችና መልሶች - 1
ሰዎች ሁሉ በስሜ እንዲጠመቁ ብፈልግ እኔ የክርስቶስ ተቃዋሚ ሆኛለው ማለት ነው። ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚ ያደርገኛል።
62-1007 የበሩ መክፈቻ
… አንዳንድ ወንድሞች እኔ እንደላኳቸው እያወሩ ሰዎች ሚስታቸውን ትተው ትክክለኛዋን አጥንታቸውን ፍለጋ መውጣት አለባቸው እያሉ ይሰብካሉ፤ በተጨማሪ ደግሞ እኔ ልሳሳት እንደማልችል አድርገው ያወራሉ። … ከዚህም የባሱ አንዳንድ አስደንጋጭ ነገሮችን ይናገራሉ።
ወንድም ብራንሐም የማልሳሳት ሰው ነኝ አላለም።
63-1110 በእናንተ ዘንድ ያለው
መልእክቱን በሙሉ እመኑ። እመኑ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካልተጻፈ ግን አትመኑት።
ወንድም ብራንሐም መጽሐፍ ቅዱስን አብራርቶልናል። እኛም ደግሞ የምናምነው እርሱ ያስተማረንን እውነት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አግኝተን ስለምናነበው ነው።
64-0823 ጥያቄዎች እና መልሶች - 1
ቃሉን በሙላት መቀበል የሚችሉ ግን እኔ ስለሰበክሁ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ስለተናገረ ይቀበላሉ። የሚቀበሉ ሁሉ ለመቀበል ነጻ ናቸው ምክንያቱም ቃሉ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል።
ወንድም ብራንሐም ያስተማረው ነገር በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መገኘት አለበት።
62-0318 የተነገረው ቃል እውነተኛው ዘር ነው - 2
አሁን እነዚህ የተናገርኳቸው ነገሮች በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይስማሙ ከሆኑ ወይም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይገጥሙ ከሆኑ በሙሉ ስሕተት ናቸው።
56-0902 በግድግዳው ላይ የመጣው የእጅ ጽሐፈት
አሕዛብ በዘመናቸው መጀመሪያ ላይ እግዚአብሔር እየመዘናቸው ሳለ በልባቸው ታበዩ፤ እያንዳንዱ ሰው የቅዱስ ሰውን ምስል እንዲያመልክ አስገደዱ።
የአሕዛብ ዘመን በዚህ ነው የጀመረው፤ በዚሁ ይጠናቀቃል።
ትኩረታችንን ሁሉ ዊልያም ብራንሐም በሚባለው ሰው ላይ ማድረግ፤ ይህን ቅዱስ ሰው ከሌሎች ሁሉ በላይ ከፍ ማድረር፤ ይህ ትልቅ ስሕተት ነው።
ማቴዎስ 10፡12 ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤
ማቴዎስ 10፡13 ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ።
ሰላማችሁ ከሚገባቸው ሰዎች ጋር ይቆይ። ሰላማችሁን አንቀበልም ቢሉ ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ።
ሰዎች እውነትን የማይፈልጉ ከሆነ እነርሱ እምቢ ያሉትን እውነት እናንተ ጸንታችሁ ያዙት።
በሙሽራይቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤት አካላት ናቸው። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ለ2,000 ዓመታት የገነባው መንፈሳዊ ቤት አካል ናቸው።
ዕብራውያን 3፡6 እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን።
እያንዳንዱ አማኝ በእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቤት ውስጥ የተጨመረ ሕያው ድንጋይ ነው፤ ይህንንም መንፈሳዊ ቤት ሙሽራይቱ ናት።
ማቴዎስ 10፡14 ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።
እነዚህ ሐዋርያት የገንዘብ ትርፍ አልፈለጉም። ከማያምኑ ሰዎች እግራቸው ላይ ያለውን አፈር ወይም ትቢያ እንኳ አይፈልጉም።
ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማመን የሚቸገሩት በተማሩት የቤተክርስቲያን ልማዳዊ ትምሕርቶች የተነሳ ነው።
ሰዎች በአንድ ፓስተር አገዛዝ ስር ለመቆየት ብለው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያሻሽላሉ ወይም ይለውጣሉ። የሚያምኑትም ፓስተሩ የሚለውን ብቻ ነው።
65-0220 እግዚአብሔር ለአምልኮ የመረጠው ስፍራ
ወደዚያ እነርሱ ወደሚሉት ቤተክርስቲያን ካልሄዳችሁ መንግስተ ሰማያት የማትገቡ ይመስላቸዋል። ይህ ስሕተት ነው። እንደዚህ ብሎ ማመን የክርስቶስ ተቃዋሚ መሆን ነው። እኔም እንዲህ እላለው፡- እንዲህ ዓይነቱን መንፈስ ካመናችሁ ጠፍታችኋል።
ዕብራውያን 3፡15 እየተባለ፦ ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ።
አለማመን። ትልቁ ሐጥያታችን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን እውነት አለማመናችን ነው።
ዕብራውያን 3፡18 ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ?
መንፈሳዊው እረፍት ከሐጥያት ሸክም ማረፍ ነው፤ ይህም እረፍት የሚመጣው ዓይናችን ለእውነት እንዲከፈት በሚያደርገው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካኝነት ነው።
ወደ ቀድሞው አለማመን ተመልሰን እንዳንሄድ ወደ እውነት ሊመራን የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።
ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።
ዕብራውያን 3፡19 ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን።
ዕብራውያን 4፡1 እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት ተስፋ ገና ቀርቶልን ከሆነ፥ ምናልባት ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንፍራ።
በስተመጨረሻ የእግዚአብሔር ሚስጥር እንደሚፈጸም ቃል ተገብቶልናል።
ራዕይ 10፡7 ወደ ፊት አይዘገይም፥ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥ ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል አለ።
የኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የእግዚአብሔርን ሃሳብ ይዟል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው።
እግዚአብሔርን ከእግዚአብሔር ሃሳብ ለይቶ ማየት አይቻልም።
የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መረዳት ካልቻለን የእግዚአብሔርን አስተሳሰብ መረዳት አንችልም ማለት ነው። ይህም የክርስቶስ ልብ እንደሌለን ያመለክታል።
1ኛ ቆሮንቶስ 2፡16 እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።
የመጨረሻው ዘመን ሙሽራ ወደ መጀመሪያው ዘመን ሙሽራ እምነት መመለስ አለባት።
እነርሱ የክርስቶስ ልብ ነበራቸው። ስለዚህ እኛም የክርስቶስ ልብ ሊኖረን ይገባል።
ከዚህም የተነሳ የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት መረዳት መቻል አለብን።
ዕብራውያን 4፡2 ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም።
እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ቃል እውነት መሆኑን ከልባችን ማመን አለብን።
ምሳሌ 30፡5 የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፤
ሙሽራይቱ እረፍቷ በተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ነው። ከተጻፈው አልፋ አትሄድም።
ዕብራውያን 4፡3 ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም፦ እንዲህ፦ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ እንዳለ፥ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን።
ማቴዎስ 10፡15 እውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል።
ከሐጥያት የመጨረሻው እረፍት የሚገኘው የሙሽራይቱ አካላት አዲሱን የማይሞተውን አካላቸውን ሲለብሱ ነው። ከዚያ በኋላ ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ወደ ላይ ይነጠቃሉ። በዚያ ጊዜ በጭራሽ ሐጥያት የማይነካቸው ሰዎች ይሆናሉ።
የተታለሉት ቤተክርስቲያኖች ማለትም ሰነፎቹ ቆነጃጅት ግን ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ ይገባሉ። ታላቁ መከራ ዓለም እስከ ዛሬ አይቶ ከሚያቀው ሰቆቃ የሚበልጥ አስጨናቂ የሆነ ጊዜ ነው።
ዳንኤል 12፡1 በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።
ሚካኤል እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ሆኖ ሲገለጥ የሚጠራበት ስም ነው።
55-0109 የአሕዛብ ዘመን መጀመሪያ እና ማለቂያ
“በዚያ ጊዜ ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል።” ሚካኤል ክርስቶስ ነው፤ እርሱም በሰማያት ውስጥ ከዲያብሎስ ጋር የነበረውን ጦርነት ተዋግቷል።
ይህ የስደት ወቅት የታላቁ መከራ ዘመን ነው።
በዚያ ጊዜ የሚድኑት የዳንኤል ሕዝብ ብቻ ማለትም አይሁዶች ናቸው።
ሰነፎቹ ቆነጃጅት የአሕዛብ ቤተክርስቲያኖች ከታላቁ መከራ አይድኑም። የአሕዛብ ቤተክርስቲያኖች በመከራ ውስጥ ይጠፋሉ፤ ምክንያቱም በዚህ መንገድ ነው ቤተክርስቲያናዊ ስሕተት እና አለማመን ከውስጣቸው ተነቅሎ የሚወጣው።
1ኛ ተሰሎንቄ 2፡12 ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ
ለእግዚአብሔር እንደሚገባ የምንመላለሰው የተገለጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሚስጥራት ስናምን ነው። ለእግዚአብሔር እንደሚገባ የምንመላለሰው ኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹሙ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ስንቀበል ነው።
በምቾት መኖር ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ለመኖር አያበቃንም። እግዚአብሔር የለም የሚሉ ብዙ ሰዎች እንዲሁም በሌሎች ሐይማኖቶች ውስጥ ያሉ ሰዎችም በምቾት ይኖራሉ።
ጥሩ ኑሮ እንድንኖር ይጠበቅብናል።
ለእግዚአብሔር እንደሚገባ የምንመላለሰው እርሱ እንዲጠራን ስንፈቅድና የተገለጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች ስንከተል ነው።
እግዚአብሔር ወደ መንግስቱ ሊጠራን ይፈልጋል። እግዚአብሔር የራሳችንን ፈቃድ ወይም የቤተክርስቲያናችንን ፍላጎት እንድንከተል አይፈልግም።
1ኛ ተሰሎንቄ 2፡13 ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ስናምን መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ በእርግጥ መስራት ይችላል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ካመንን እርሱን ብቻ ነው ለሰዎች የምንነግራቸው እንጂ የራሳችንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አመለካከት ወይም የቤተክርስቲያን ልማድ አናስተላልፍም።
ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማመን አብሮት የሚመጣ መከራ አለ። የሚከፈል ዋጋ አለ - ይህም ዋጋ ከቤተክርስቲያኖች ዘንድ የሚመጣ ተቃውሞ እና ተቀባይነት ማጣት ነው።
1ኛ ተሰሎንቄ 2፡14 እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና።
ማቴዎስ 10፡16 እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።
ጥበብ ሊኖረን ይገባል። ይህ ነውጠኛ እና የተደበላለቀ ዘመን ነው። በዚህ ዘመን ውስጥ በጣም ብዙ ስሕተት እና ብዙ ግራ የሚያጋባ ነገር አለ። ሙሽራይቱ ግን ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የላትም።
ማቴዎስ 10፡17 ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤
የቤተክርስቲያን ሰዎች ሙሽራይቱን ያወግዛሉ።
ስማችንን ሲያጠፉ፤ ሲነቅፉን እና ሲሰድቡን በምንሰማ ጊዜ መልመድ አለብን።
ማቴዎስ 10፡18 ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።
በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ እውነተኛ ክርስቲያኖች በነገስታት ፊት፣ በገዥዎች ፊት እና ዳኞች ፊት ተከስሰው ቀርበዋል።
ማቴዎስ 10፡19 አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤
እነዚህ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው ስለነበረ እግዚአብሔር እነርሱ እንዲናገሩ የፈለገውን ጥቅስ ወደ አእምሮዋቸው ያመጣላቸው ነበር።
ማቴዎስ 10፡20 በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።
እግዚአብሔር ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ብቻ ነው የሚናገረው። ስለዚህ ቃሉ ውስጥ የተጻፈውን በተናገራችሁ ጊዜ እግዚአብሔረ በእናንተ ውስጥ ሆኖ እንደተናገረ ይቆጠራል።
ማቴዎስ 10፡21 ወንድምም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል።
በቤተሰብ ውስጥ መከፋፈል ይመጣል። እውነትን አጥብቀን መያዝ ተወዳጅ አያደርገንም። ጥል፣ የቤተሰብ ክፍፍል፣ ጭንቀት እና ስደት የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች የሚፈተኑባቸው ፈተናዎች ናቸው።
እግዚአብሔር ሁልጊዜ የሚጠይቀን ጥያቄ የሚከተለው ነው፡- በእውነት ታምናላችሁን?
በመከራ ውስጥ ማለፍ ቢያስፈልጋችሁም ጭምር ማለት ነው?
ማቴዎስ 10፡22 በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
አንድ ሰው ኢየሱስ የሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር ስም ነው ብሎ ቢናገር በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሁሉ ይጠሉታል።
ቤተክርስቲያኖች በጣም ከመታለላቸው የተነሳ “በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም” ብሎ መናገር የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ይመስላቸዋል። ያ ስም ማን ነው ተብለው ሲጠየቁ ለስላሴያዊው አምላካቸው ስም እንደሌላቸው ይገነዘባሉ። ለሶስት አካላት የሚሆን አንድ ስም ማግኘት አይችሉም።
እነደዚያም ሆኖ ሥላሴ የሚሉትን እምነታቸውን መተው ያቅታቸዋል፤ የስላሴ ትምሕርት ከ325 ዓ.ም ከተደረገው ከኒቅያ ጉባኤ ጀምሮ በቤተክርስቲያኖች ውስጥ ሲሰጥ የቆየ ትምሕርት ነው። የሥላሴ ትምሕርት ላይ ጥያቄ ብታነሱ ብዙ የቤተክርስቲያን ሰዎች ከቤተክርስቲያን እንዳይባረሩ ብለው የሥላሴ ትምሕርትን የሙጥኝ ብለው ስለሚይዙ ጥያቄ በማንሳታችሁ ብቻ ይጠሉዋችኋል።
በሥላሴ ላይ የሚያደርጉት ትኩረት እስከ ታላቁ መከራ ድረስ ይቀጥላል።
“እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።”
ይህ መዳን ከሲኦል አይደለም። ንሰሃ ገብታችሁ ኢየሱስን የግል አዳኝ አድርጋችሁ የተቀበላችሁ ዕለት ከሲኦል ድናችኋል።
ይህ ቃል የሚናገረው መዳን ጌታ በዳግም ምጻቱ ሲመለስ እርሱን ለመገናኘት በአየር ላይ በመነጠቅ ከታላቁ መከራ ሰቆቃ ስለ ማምለጥ ነው።
ታላቁ መከራው በሚጀምርበት ጊዜ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ተቃዋሚው ፖፕ እጅ በድንገት እን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲጠፉ የዛሬ ክርስቲያኒች በፓስተሮቻቸው ላይ ያላቸው እምነት ሙሉ በሙሉ ይጠፋል። በጣም ከረፈደባቸው በኋላ ወደ ሞት ወጥመድ ውስጥ ተጎትተው መግባታቸውን ይገነዘባሉ። ይህ የሚያመጣባቸው ድንጋጤ በተጨማሪ በሥላሴ ትምሕርት ላይ የነበራቸውን ትምክሕት ይነቀንቅባቸዋል።
በታላቁ መከራ ውስጥ የቤተክርስቲያን ጀግና የሚባል ሰው አይኖርም ምክንያቱም ሕዝቡ መሪዎቻቸው እንዳሳቷቸው ይገነዘባሉ።
ነገር ግን በተፈጥሮ ላይ እንደፈለጉ የማዘዝ ስልጣን ያላቸው ሁለት አይሁዳዊ ነብያት የሰነፎቹን ቆነጃጅት ትኩረት ይስባሉ።
በታላቁ መከራ ጊዜ ከሙሴ አፍ ምን ዓይነት ስብከት እንደሚሰሙ ተመልከቱ።
የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ፤ መዝሙሩም በጉ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ነው የሚል ነው።
ራዕይ 15፡3-4 ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፥ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፥ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ እያሉ የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ።
በጉ ብቻ ነው ቅዱስ።
ስለዚህ በመለኮት ውስጥ ተጨማሪ ሁለት ቅዱሳን አካላት የሉም።
የታላቁ መከራ ዘመን ቤተክርስቲያኖች ሥላሴ የሚባል ነገር አለመኖሩን እስከሚያውቁ ድረስ እርማት ይሰጣቸዋል።
ኢየሱስ አብ ሆኖ በመገለጥ በብሉይ ኪዳን ዘመን ውስጥ ከአይሁድ ሕዝብ በላይ ነበረ።
ልጅ ወይም ወልድ ሆኖ በመገለጥ ኢየሱስ አማኑኤል የሚለውን ስም ይዞ ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ነበረ። አማኑኤል፡- እግዚአብሔር ከእኛ ጋር።
ማቴዎስ 1፡23 እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።
በኢየሱስ በውጭ በኩል የሚታየው የእግዚአብሔር ልጅ የሚባለው ነው።
1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።
ልዕለ ተፈጥሮአዊው የእግዚአብሔር አብ መንፈስ በኢየሱስ ውስጥ በአካል አድሯል።
ቆላስይስ 2፡9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤
እግዚአብሔር እንደ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ በሙሽራይቱ ውስጥ ይኖራል።
እያንዳንዱ የሙሽራይቱ አባል በተወሰነ መጠን መንፈስ ቅዱስን ተካፍሏል።
አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ ሶስቱ የእግዚአብሔር መገለጦች ናቸው፤ ማለትም እግዚአብሔር ከሕዝቡ በላይ፣ ከዚያም ሕዝቡ ጋር፣ ቀጥሎም በሕዝቡ ውስጥ ሲሆን።
ስለዚህ ኢየሱስ የአብ፣ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ ስም ነው።
ጌታ የማዕረግ መጠሪያ ነው።
ክርስቶስ ማለት “የተቀባው” የሚል ትርጉም ያለው የማዕረግ መጠሪያ ነው።
ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም ሶስቱንም የእግዚአብሔር መገለጦች የሚገልጽ ስም ነው።
ማቴዎስ 10፡23 በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።
ክርስቲያኖች መሰደድን እና መበታተንን ይለምዱታል። ወንጌሉም የተሰራጨበት መንገድ ይህ ነው።
ማቴዎስ 10፡24 ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም።
ዊልያም ብራንሐም የመለኮት አካል ነው እያላችሁ ያለቦታው ከፍ አታድርጉት። የእርሱ ንግግር ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በላይ ከፍ ሊደረግ አይችልም። እርሱን የሰው ልጅ ልታደርጉት አትችሉም።
እርሱ የመጣው የሰውን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ውስጥ ሲመላለስ ሊገልጥ ነው። እርሱ ራሱ ሰው ልጅ ለሆን አልመጣም።
ማቴዎስ 10፡25 ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው!
ኢየሱስን የአጋንንት አለቃ አሉት።
እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ብታምኑ እናንተንም ሰዎቸ አጋንንት ሊሉዋችሁ ይችላሉ። እንደ አድናቆት ቆጥራችሁ ተቀበሉት። ኢየሱስ የተቀበለውን ዓይነት መከራ መቀበል ማለት ሰይጣን በእናንት ምክንያት እየተጨነቀ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው።
ማቴዎስ 10፡26 እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና።
ሰዎች ከጀርባችሁ ያሾከሽካሉ፤ ያወግዟችኋል። ነገር ግን አንድ ቀን የፍርድ ቀን ንግግራቸውና ተንኮላቸው በሰው ሁሉ ፊት በአደባባይ ይገለጣል።
ማቴዎስ 10፡27 በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ።
ኢየሱስ የገለጠላችሁን ውሰዱ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች ተናገሩ።
ማቴዎስ 10፡28 ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።
አረማውያን እና እግዚአብሔር መኖሩን የማያምኑ ሰዎች አካላችሁን ሊያጠፉ ይዝቱ ይሆናል፤ ነገር ግን በነፍሳችሁ ውስጥ ያለውን እምነት ሊለውጡ አይችሉም።
ቤተክርስቲያኖች ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል በሰው ሰራሽ ጥቅሶች በመተካት ነፍሳችሁ ላይ አደጋ ለመጣል ይሞክራሉ።
ማቴዎስ 10፡29 ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም።
እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚሆኑ ጥቃቅን ነገሮች ሁሉ ያስተውላል።
ማቴዎስ 10፡30 የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል።
እግዚአብሔር በግል ሕይወታችሁ ውስጥ እንኳ ጥቃቅን ነገሮችን በትኩረት ይመለከታል።
ማቴዎስ 10፡31 እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።
“አትፍሩ” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 365 ጊዜ ያህል ተጽፏል። ይህም በዓመት ውስጥ ለእያንዳንዱ ቀን አንድ ጊዜ ማለት ነው።
ስለዚህ በሚገጥመን ነገር ምንም መፍራት የለብንም። በዚህ ችግር በሞላበት ዓለም ውስጥ እግዚአብሔር ትንንሹንም ነገር እንኳ ሳይቀር ያውቃል
እግዚአብሔርም የራሱ ሙሽራ እንደሆንን አድርጎ ነው የሚወደን። ስለዚህ በመከራችሁ ጊዜ ጥሏችሁ አይሄድም።
ድንቢጦች ትንንሽ ወፎች ናቸው። ይህም ማለት እግዚአብሔር በሕይወታችሁ ለምትፈልጉት ትንንሽ ነገር እንኳ ሳይቀር ያስብላችኋል ማለት ነው።
ማቴዎስ 10፡32 ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤
ለእግዚአብሔር የመቆም ድፍረትን ልናዳብር ይገባናል።
ማቴዎስ 10፡33 በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።
በጭንቅ ሰዓት እግዚአብሔርን መካድ ለረጅም ጊዜ የምንጸጸትበት ውሳኔ ነው።
ማቴዎስ 10፡34 በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።
እውነት ሰላማዊ ሕይወት ከመኖር ጋር አይያያዝም። የእግዚአብሔር ቃል አለማመንን እና ሐጥያትን የሚቆራርጥ ሰይፍ ነው። በዚህም የተነሳ ሁልጊዜ ክርክር ያስነሳል።
ማቴዎስ 10፡35 ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤
አንድ ሰው እውነተን ማመን ሲጀምር በቤተሰቡ ውስጥ የነበረው ሕብረት በቀላሉ ይናጋል።
ማቴዎስ 10፡36 ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።
ሰይጣን አንድን አማኝ ለማጥቃት የቤተሰቡን አባላት መጠቀም ይችላል።
ማቴዎስ 10፡37 ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤
ለትኛውም የቤተሰብ አባል ለእግዚአብሔር ከምትሰጠው የሚበልጥ ቦታ አትስጥ።
በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለኢየሱስ ነው።
በሕይወታችን ውስጥ በሁሉም ነገር ላይ እርሱ ጌታ ካልሆነ በምንም ነገር ላይ ጌታ አልሆነም።
ማቴዎስ 10፡38 መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።
መሸከም የሚገባን መስቀል አለ - የምንከፍለው ዋጋ አለ።
የእግዚአብሔርን ፈቃድ መከተል አለብን እንጂ የራሳችንን ፈቃድ መከተል የለብንም?
ማቴዎስ 10፡39 ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።
በግል ዓላማዎችህ ሁሉ ስኬታማ በሆንክ ጊዜ እግዚአብሔርን ከልብህ ሙሉ በሙሉ አስወጥተህ በር ዘግተህበታል ማለት ነው።
ቤተክርስቲያንህን ከሌሎች ቤተክርስቲያኖች ሁሉ የተሻለች ናት ብለህ ባስተዋወቅህ ጊዜ ኢየሱስ ከቤተክርስቲያን በር ውጭ መቆሙን ትገነዘባለህ።
ኢየሱስን ለመከተል በምታደርገው ጥረት የተነሳ ምድራዊ ጥቅሞች ሲቀሩብህ በሰማያት መዝገብ እያከማቸህ ነው ማለት ነው።
እምነትህ ሕይወትህን እንድትሰዋ ሲጠይቅህ በዚያን ጊዜ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ትሻገራለህ።
ሰማይ በሄድን ጊዜ ሁሌ ሰማእታትን ማለትም ስለ እምነታቸው ሕይወታቸውን የሰዉ ሰዎችን እያደነቅን እንኖራለን።
ማቴዎስ 10፡40 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።
አንተ ወይም አንቺ በምድር ላይ የኢየሱስ አምባሳደር ሆናችሁ እርሱን ትወክሉታላችሁ።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ስትናገሩዋቸው የሚሰሙዋችሁ ሰዎች በእርግጥ የሰሙትና የተቀበሉት ኢየሱስን ነው። የመለኮት ሙላት በእርሱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በአካል ስለሚኖር የሚሰሙዋችሁ ሰዎች በተጨማሪ እግዚአብሔር አብንም ጭምር እየተቀበሉ ነው።
ኢየሱስ በውጭው በኩል ሰው ነው፤ በውስጡ ግን ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ነው።
እግዚአብሔር በስጋ ተገለጠ።
እግዚአብሔር ሰው ሆነ። ትክክለኛው ሰው።
ማቴዎስ 10፡41 ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።
ወንድም ብራንሐም የመጨረሻው ዘመን ነብይ ነው ብለህ ብትቀበለው የምታገኘው ዋጋ ከአገልግሎቱ መጠቀም ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን የመረዳት አቅም ታገኛለህ፤ በዚህም ምክንያት ለጌታ ምጻት ዝግጁ ትሆናለህ።
63-0318 የመጀመሪያው ማሕተም
የመጀመሪያውን ማሕተም ይፈታውና ሰባተኛውን መልአክ ይገልጠዋል፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ሚስጥራት ወደ ፍጻሜ ማምጣት ብቻ ነው የሰባተኛው መልአክ አገልግሎት። አሁን ይህንን ለማረጋገጥ በቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ አልፈን መጥተናል። አያችሁ? ይህም የመልአኩ የሰባተኛ ቤተክርስቲያን መልእክት ነው።
የወንድም ብራንሐም አገልግሎት ዋነኛ ዓላማው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉትን የተሰወሩ ሚስጥራት መግለጥ ነው።
63-0318 የመጀመሪያው ማሕተም
እሺ ይህ በፊት የነበሩትን ሚስጥራት ሁሉ ይገልጣል ከዚህ ቀደም የነበሩ ነገሮችን በሙሉ፡ ራዕይ 10፡1-7 ይህ ነው የሚሆነው።
ሚስጥራቱ በተገለጠው የእግዚአብሔር ቃል መልክ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወረዱ።
ሙሽራይቱ እነዚህን ሚስጥራት ከመጽሐፍ ቅዱስ አይታ ባረጋገጠች ጊዜ የራዕይ ምዕራፍ 10 ብርቱ መልአክ ወደ ምድር ይወርድና ሙታንን ያስነሳል።
ወንድም ብራንሐም የመጨረሻው ዘመን ነብይ ነው ብለን በመቀበላችን የምናገኘው ሽልማት ወይም ጥቅም የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥረት የመረዳት አቅም ማግኘት ነው። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ ቃሎችንና ሚስጥራትን አብራርቷል፤ በዚህም የእውነተኛዋን ቤተክርስቲያን እንዲሁም የክርስቶስ ተቃዋሚውን መንፈስ ታሪክ ገልጦ አሳይቷል።
ወንድም ብራንሐም ራዕይ ምዕራፍ 10 የሚናገረው ወደፊት በብርቱው መልአክ ድምጽ አማካኝነት ስለሚሆነው የሙታን ትንሳኤ መሆኑን ገልጧል።
64-0119 ሻሎም
ያ የራዕይ ምዕራፍ 10 መልአክ አንድ እግሩን በምድር አንድ እግሩን በባሕር ሲያደርገውና በራሱ ላይ ቀስተደመና ሲወጣ እንዲህ ብሎ ምሏል፡- “ወደፊት አይዘገይም”። ያ ጊዜ ሲደርስ ከሙታን መካከል ትነሳላችሁ። ሌሎቹ እዚያው ሲቀሩ እናንተ ግን ትገባላችሁ።
ራዕይ 10፡1 ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፥
“እግሮቹም እንደ እሳት አምዶች”።
የእሳት አምድ ታላቅ መንፈሳዊ ኃይልን ይወክላል። አንድ ታላቅ ነገር ሊሆን ነው።
“ቀስተ ደመናው” በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የሞቱ ጻድቃንን ይወክላል።
“ፊቱም እንደ ፀሃይ”። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መገለጥ የሚበራ ደማቅ ብርሃን ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ ለመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን የተላከ ነብይ ነው።
ዊልያም ብራንሐም ለመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን የተላከ ነብይ ነው።
ሌሎቹ መልእክተኞች በሙሉ ጻድቅ ሰዎች ነበሩ።
ስለዚህ ለዘመናቸው የተላከላቸውን መልእክተኛ ትምሕርት የተቀበሉ አማኞች የሙሽራይቱ ትንሳኤ አካል በመሆን ሽልማታቸውን ይቀበላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ጠለቅ ያሉ ሚስጥራት መረዳት ባይችሉም እንኳ ይህ ሽልማት ይሰጣቸዋል።
የመጀመሪያው ዘመን እና የመጨረሻው ዘመን አማኞች ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት መረዳት በመቻላቸው ተጨማሪ የነብይ ዋጋ ያገኛሉ።
ሙሽራይቱ የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት እንድታውቅ እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚፈልግ ምን የሚያህል ዋጋ እንደሚሰጠው ማወቅ አንችልም።
የ7ኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ሙሽራ የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት በተረዳችና የመጀመሪያው ዘመን ቤተክርስቲያን ያመነቸውን ባመነች ጊዜ ትንሳኤው እንዲጀምር ምክንያት ትሆናለች።
65-1127 ሰምቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየችህ
እግዚአብሔር ሆይ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ልክ እንደዚህ ዓይነት ሰዓት ይመጣል የነጎድጓድ ድምጽ የሚሰማበት ሰዓት፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ልጅ በታላቅ ድምጽ ከሰማያት ይወርዳል፤ በመላእክት አለቃ ድምጽ፣ በእግዚአብሔር መለከት ይመጣል፤ በክርስቶስም ሆነው የሞቱት ይነሳሉ።
ከመሞቱ አንድ ወር በፊት እንኳ ወንድም ብራንሐም የመላእክት አለቃውን “ድምጽ” ለመስማት እየተጠባበቀ ነበር።
“ድምጹ” የወንድም ብራንሐም የመጽሐፍ ቅዱስን ሚስጥራት የመግለጥ አገልግሎት አልነበረም።
“ድምጹ” የሚፈጸመው ሙሽራይቱ ወንድም ብራንሐም ያስተማረውን ሚስጥር ተረድታ ለራሷ ከመጽሐፍ ቅዱስ መርምራ ማረጋገጥ የቻለች ጊዜ ነው። ሰው የተናገረውን ቃል እየጠቀሱ ሳያስተውሉ እንደ ገደል ማሚቶ መድገም የቻሉ ጊዜ አይደለም።
[የምታስታውሱ ከሆነ የሜሴጅ ፓስተሮች ሒላሪ ክሊንተን የ2016ቱን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደምታሸንፍ የሚተነብይ ጥቅስ አግኝተናል ሲሉ ነበር። ከእነዚሁ ፓስተሮች ብዙዎቹ ጌታ በ1977 ይመለሳል የሚል ጥቅስ አለን ይሉ ነበር።]
ጥቅስ ሲጠቀስ እውነተኛ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ አይተን ማረጋገጥ አለብን።
ሌላው ነገር ደግሞ ወንድም ብራንሐም ሲጠባበቀው የነበረው ያ የመጀመሪያ ሚስጥራዊ ነጎድጓድ አለ። ይህም በሚፈጸምበት ጊዜ ምን እንደሚመስል አናውቅም።
ነገር ግን ሙሽራይቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የተጻፉት ሚስጥራት ምን እንደሆኑ መረዳት በቻለች ጊዜ መረዳት መቻሏ “ድምጹ” እንዲሰማ ያደርጋል፤ ይህም ድምጽ ክርስቶስ የትንሳኤውን “ድምጽ” ለማሰማት እንደ መላእክት አለቃ ሆኖ እንዲወርድ ያደርገዋል።
ስለዚህ ተስፋ የተሰጠን ቀጣይ ታላቅ ክስተት “የመላእክት አለቃ ድምጽ” ነው።
1ኛ ተሰሎንቄ 4፡16 ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤
በፍጹም አትሳቱ፤ በዘመን መጨረሻ የእግዚአብሔርን ድምጽ እንደምንሰማ ቃል አልተገባልንም።
የእግዚአብሔር “መለከት”። የፕሬዚዳንት ትራምፕ ስም በእንግሊዝኛ መለከት የሚል ትርጉም የሚሰጥ እንደመሆኑ መጠን ስለ ዘመኑ የሚናገር ምልክት ነው። ወደ ፍጻሜው እየተቃረብን ነን።
ትራምፕ ኢየሩሳሌም የእሥራኤል ዋና ከተማ መሆኗን እውቅና በመስጠቱ በእርሱ ትንቢት ተፈጽሟል።
እግዚአብሔር ወደ አይሁዶች እየተመለሰ ነው፤ ይህም የአሕዛብ ዘመን እያበቃ መሆኑን ያመለክታል።
ራዕይ 10፡2 የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥ እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።
“የተከፈተች ታናሽ መጽሐፍ”።
የወንድም ብራንሐም መገለጦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉትን ሚስጥራት ግልጽ ስላደረጉልን ሙሽራይቱ መጽሐፍ ቅዱስን በመረዳት ማንበብ ትችላለች።
ባሕር እና ምድር በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የሞቱ ቅዱሳን የተቀበሩባቸው ቦታዎች ናቸው።
ራዕይ 10፡3 እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ።
ኢየሱሰ አላዛርን ከሙታን ባስነሳ ጊዜ “በታላቅ ድምጽ ጮሆ” ነው ያስነሳው።
ዮሐንስ 11፡43 ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፦ አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።
ይህ ድምጽ ሙታንን የሚያስነሳው የመላእክት አለቃ ድምጽ ነው።
ራዕይ 10፡3 እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ።
የይሁዳ ነገድ አንበሳ ድል የመንሳት ግሳት ያገሳል፤ በሰባት የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ስትዘጋጅ የቆየችዋን ሙሽራም ከሙታን ያስነሳታል፤ በባሕር እና በምድር ካሉ መቃብሮቿ ሁሉ ያወጣታል። ሰይጣን በማይሞት አካላቸው ውስጥ ያሉትን የሙሽራይቱ አካላት በአንዳችም ነገር ሊጎዳቸው አይችልም።
ራዕይ 10፡3 እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ።
“በጮኸም ጊዜ”። ይህ የሞቱ የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን የሚነሱበተን ጊዜ ያመለክታል።
ማቴዎስ 27፡50 ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ።
የምድር መናወጥ ሆነ፤ ከዚያም የብሉይ ኪዳን ዘመን ቅዱሳን ከሙታን ተነሱ።
ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ከትንሳኤው ጋር ይሆናል - ያም ጊዜ ታላቅ የነውጥ ጊዜ ይሆናል።
ማቴዎስ 27፡51 እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤
52 መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤
53 ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።
ከሙታን የተነሱትን ቅዱሳን ከሰዎች መካከል ለይቶ ማወቅ ቀላል አይሆንም።
የኢየሱስ እናት ማርያም ኢየሱስ ከሙታን በተነሳ ጊዜ አላወቀችውም። አትክልተኛ መስሏት ነበር።
51-0509 ምስክር
አሁን ደግሞ እርሱ ከሙዋችነት ወዳለመሞት ስለተሻገረበት ስለ ታላቁ የትንሳኤ ማለዳ እያሰብኩ ነኝ። ከመቃብር ተነስቶ ወጣ። ምስኪኖቹ ደቀመዛሙርቱ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተበታተኑ… እናቱም በመቃብሩ አጠገብ ቆማ ታለቅስ ነበር። ማለዳ ሲነጋ የፀሃይ ብርሃን ጮራ እየፈነጠቀ ነበር፤ እርግቦችም በአካባቢው ወዲያና ወዲህ ይበርሩ ነበር። እርሱም “ማርያም” ብሎ ጠራት። ወዲያውም አወቀችው።
61-0424 በታሪክ ውስጥ የተሰማ ታላቅ ሰበር ዜና
አሁን መልእክቱ ይህ ነው፤ እርሱ በፊታችን ሄዷል፤ ቀድሞን ሄዷል። እርሱ ከኋላችን መቃብር ውስጥ አይደለም። እርሱን ቀድሞን በመሄድ መንገድ እያዘጋጀልን ነው። እኛም ወደ ኋላ ወደ መቃብሩ መመልከት የለብንም፤ እርሱ ወደሚመራን ወደ ፊት ነው እንጂ፤ ምክንያቱም መሪያችን እርሱ ነው። እርሱን መከተል አለብን እንጂ ወደ ኋላ ወደ መቃብሩ ማየት የለብንም።
ማርያም በዚያ ማለዳ ግራ የተጋባችውን ቤተክርስቲያን ትወክላለች። በትክክል ወክላለች ምክንያቱም እርሷም ልክ ዛሬ ቤተክርስቲያን ባለችበት ሁኔታ ውስጥ ነበረች። ሲናገር በሰማችው ጊዜ ምን አለች? “ማርያም፤ አንች ሴት ስለምን ታለቅሺያለሽ?”
እርሷም እንዲህ አለች ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም።”
ማርያም ግራ ተጋብታ ነበር፤ ስለዚህ በትንሳኤው ዘመን ግራ የምትጋባውን ቤተክርስቲያን በደምብ ትወክላለች።
የራሷ ልጅ ከሞት በተነሳ ጊዜ አላወቀችውም።
ስለዚህ የትንሳኤው ጊዜ በጣም ግራ የሚያጋባ ጊዜ ነው የሚሆነው።
ዮሐንስ 20፡14 ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም።
15 ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው።
16 ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው።
ራዕይ 10፡3 እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ።
ከአዲስ ኪዳን ትንሳኤ በኋላ ሰባት ሚስጥራዊ ነጎድጓዶች ድምጻቸውን ያሰማሉ።
እነዚህ ነጎድጓዶች ያልተጠበቁ እና ያልተለመዱ ስለሚሆኑ የዚያን ጊዜ በሚሆነው ነገር ሙሽራይቱ ትንገዳገዳለች። ሆኖም ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍንጮችን ማስተዋል አለብን።
ወደማናውቀው ነገር ውስጥ መግባት ትዕግስት፣ ጥንቃቄ እና ላልጠበቅነው ነገር ዝግጁ መሆን ይጠይቃል።
በኢየሱስ የመጀመሪያ ምጻት ጊዜ በትንሳኤውና ወደ ሰማይ ባረገበት ቀን መካከል የ40 ቀናት ክፍተት ነበረ።
ይህ ዓይነቱ ክስተት በዳግም ምጻቱ ከተደገመ በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ትንሳኤ እና ተነጥቀው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል በሚሄዱበት ቀን መካከል 40 ቀናት ሊያልፉ ይችላሉ ብለን ማሰብ እንችላለን።
የዚያን ጊዜ ነው ከ7ቱ ሚስጥራዊ ነጎድጓዶች ምሪት የምንቀበልበት ጊዜ።
እነዚህ ሚስጥራዊ ነጎድጓዶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዝርዝር ሳይጻፉ ተሰውረዋል።
7ቱ ነጎድጓዶች ቃላቸውን በሚናገሩ ጊዜ የሚሉትን መረዳት እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት መቻል አለብን።
63-0318 የመጀመሪያው ማሕተም
ያየውን ሁሉ እንዲጽፍ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። ነገር ግን እነዚህ ሰባት ነጎድጓዶች ራዕይ ምዕራፍ 10 ውስጥ በተናገሩ ጊዜ “እንዳትጽፍ” ተብሎ ተነገረው። ሚስጥሮች ናቸው።
… እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡- “ቆይ። አትጻፈው። አትመህ ዝጋው። እኔ በዚያ ቀን እገልጠዋለው። በጭራሽ አትጻፈው ዮሐንስ፤ ምክንያቱም ይንገዳገዱበታል።” ሚስጥራቱን ለመፍታት አትጨነቅ። (አያችሁ?) እኔ ግን በዚያ ቀን ሊገለጥ ሲያስፈልግ እገልጠዋለው።
ስለዚህ እነዚህ ሰባት ነጎድጓዶች ምን ማለት እንደሆኑ አስቀድመን ልናውቅ የምንችልበት አንዳችም መንገድ የለም።
መልአኩ “ታናሽ መጽሐፍ” በእጁ ይዟል። ይህም ማለት በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ እውነት የሚያምኑት።
ራዕይ 10፡10 ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፤ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ።
መጽሐፉ በሆዱ ውስጥ መረረው። መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ስንችል 7ቱ ነጎድጓዶች ትክክለኛውን እውነት መቀበል ያስችሉናል። እነዚህ ነጎድጓዶች አካላችን እንድንለውጥ ምሪት ይሰጡናል። ስለዚህ ምንም ማስተዋል እንደማይችል በቀቀን ወፍ የሰማነውን የሰው ንግግር ጥቅስ አንደግምም። ይህ የመጨረሻ እውነት እኛ ከምንጠብቀው በጣም የተለየ ነው የሚሆነው፤ ደግሞም በጣም መራራ እና ብዙ ሰዎች ሊቀበሉት የማይፈልጉት እውነት ስለሚሆን ብዙ ሰዎች ቦታ አይሰጡትም። አንድ ጊዜ አዲሱን የማይሞተውን አካላችንን ከለበስን በኋላ ለመነጠቅ የሚያስፈልገንን እምነት ማግኘት እንችላለን። አሁን የለበስነው አሮጌ አካል አይነጠቅም።
ብርታት የሚገኘው ከጌታ ዘንድ ነው፤ ተለውጠን አዲሱ አካላችንን ከለበስን በኋላ ምስጋናውም በአፋችን ውስጥ ጣፋጭ ይሆናል። እኛም ዮሐንስ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ካመነውና ከጻፈው እምነት ጋር አንድ ዓይነት የሆነ ትምሕርት እናምናለን።
62-1230 ይህ የመጨረሻው ምልክት ነውን
እንደው ለመነጠቅ ወደሚያበቃው እምነት ውስጥ እንዴት አድርገን እንደምንገባ የሚያሳውቀን ነገር ቢሆንስ? ነውን? እንሮጣለንን፤ ከግድግዳዎቹ በላይ እንዘላለንን? አንድ ነገር ሊሆንና እነዚህ ያረጁ የተበላሹ ስጋዎቻችን ሊለወጡ ጊዜው ቀርቦ ይሆን? ጌታ ሆይ ይህ እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት ታኖረኝ ይሆን? እኔ በሕይወት ሳለው አየው ዘንድ ቀርቧልን? በዚህ ትውልድ ይፈጸማልን? ወንድሞች ሆይ ሰዓቱ ስንት ነው? የት ነው ያለነው?
… በእውነቱ እነዚህ ሰባቱ ነጎድጓዶች ናቸውን፤ ቃላቸውን ሊናገሩ ተዘጋጅተው ይሆን፤ በሕብረት የተሰበሰበው ታናሽ ወገን ለመነጠቅ የሚያበቃውን እምነት ሊቀበል ይሆን፤ እርሱ ሲመጣ ተነጥቀው ለመሄድ?
63-0724 እግዚአብሔር ሰውን አስቀድሞ ሳያስጠነቅቀው ወደ ፍርድ አያቀርበውም
በፍጥረታዊው እና በልዕለ ተፈጥሮአዊው መካከል ካለው “ግድግዳ” በላይ ዝለሉ እና ወደ እግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ ግቡ፤ ወደዚያ ዘላለማዊ ታላቅነት ውስጥ ግቡ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ስለዚህ እናመሰግንሃለን። ጊዜው እየቀረበ መሆኑን እናውቃለን።
2ኛ ሳሙኤል 22፡30 … በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁና።
ናቡከደነጾር አራት የአሕዛብ መንግስታትን የሚወክል ምስል በሕልሙ አየ።
እግሮቹ ሰባቱን የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላሉ።
ከዚያም አንድ ድንጋይ እግሩ ላይ መታውና ምስሉን ሰባበረው። ይህ ድንጋይ የጌታን መምጣት ይወክላል።
ይህ ድንጋይ የሚመጣው ብርቱው መልአክ በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የሞቱትን ከሙታን ስለሚያስነሳቸው ነው።
61-0806 የዳንኤል ሰባተኛ ሳምንት
ያ ድንጋይ ምስሉን በሚመታ ጊዜ ቤተክርስቲያን ሸሽታ ወደ ድንጋዩ ትሮጣለች።
ምስሉን የሚመታው ድንጋይ የአሕዛብ ምስሉን ይሰባብረዋል።
ሙሽራይቱን የሚያድናት ድንጋይ ቤተክርስቲያንን እና ዓለማዊ ስርዓቶችን ያጠፋቸዋል። ከዚህም የተነሳ ሙሽራይቱ በዓለም ውስጥ ተቀባይነት ታጣለች።
አይሁዶች ከአሕዛብ ምስሉ ውጭ ናቸው። በታላቁ መከራ ውስጥ የአሕዛብ ቤተክርስቲያኖች እና ሕዝቦች ይጠፋሉ። ከዚያ በኋላ 144,000 አይሁዶችን ለማውጣት ወንጌሉ ወደ እሥራኤል ይሄዳል።
ማቴዎስ 10፡42 ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።
57-0806 እግዚአብሔር ፍቅሩን ሲገልጽ
ኢየሱስ እንደ ሌሎች ሰዎች አይደለም። ትልቅም ይሁን ትንሽ ነገር በስሙ የምታደርጉትን ሁሉ ያውቀዋል። በሰዎች ፊት ትንሽ ነገር ይመስል ይሆናል፤ ነገር ግን ያደረጋችሁት በእርሱ ስም እስከሆነ ድረስ አንድ ጊዜ እንዲህ ብሎ ተናግሯል፡- “ከእነዚህ ከደቀመዛሙርቶቼ ለአንዳቸው እንኳ በደቀመዝሙር ስም ቀዝቃዛ ውሃ ብትሰጡ እውነት እላችኋለው ዋጋችሁን አታጡም።” ስለዚህ የምታደርጉት ነገር በጣም ትንሽ ቢሆንም ምንም ችግር የለውም፤ ክርስቶስ ሁልጊዜ የምናደርጋቸውን ትንንሽ ነገሮች ያያል። እኔስ እርሱ ሁሉንም ነገር በማየቱ ደስ ይለኛል (እናንተስ ደስ አይላችሁም?) ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክዱስ ክፍል በትክክል ብንቀበለው እርሱ ደስ ይለዋል።
ስለዚህ ደግነት በትንሹም ቢሆን እግዚአብሔርን ያስደስተዋል።
ደግሞም ሌላ ጠለቅ ያለ መንፈሳዊ ትርጉም አለ። ሕይወት የሚሰጥ ውሃ የቃሉ ምሳሌ ነው።
ስለዚህ አንድ ደቀመዝሙር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጻፈውን ትምሕርት በትንሹ እንኳ ብናካፍል ያንን ሰው እየረዳነው ነን።
ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ አለብን - ደቀመዛሙርቱ የጻፉትን መጽሐፍ ቅዱስ።
ሰዎችን ለመርዳት ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደቀመዛሙርቱ የጻፉትን እየተከተልን እንኑር።