ኢየሱስ እንደ ፍጹም ሰው - በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 8

ኢየሱስ ከብዙ ከተሞች ለተሰበሰቡ ብዙ ሕዝብ የዘሪውን ምሳሌ አስተማረ።

ሉቃስ 8፡5 ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፥ የሰማይ ወፎችም በሉት።
ሉቃስ 8፡11 ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ልብ ውስጥ የሚተከል ከዚያም የሚያድግ ዘር ነው።

ሰይጣን ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን ፍላጎት ሰርቆ ይወስድባቸዋል። ሳይንስም የሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የመማር ፍላጎት በኤቮልዩሽን እና በቢግ ባንግ ቲዎሪ አማካኝነት ይወስድባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ዘመናዊ ትምሕርት ላልተማሩ ኋላ ቀር ሕዝቦች የተጻፈ ተረት ነው እንጂ እውነት አይደለም ይላሉ። ሰዎች ብልህና የተማሩ መስለው መታየት ሲፈልጉ ይህንን ሁሉ ስሕተት ያምናሉ፤ ከእግዚአብሔርም ይርቃሉ። ለጥቂት ሰዓት የተማሩ መስለው ለመታየት ብለው ብዙ ስሕተት ይሰራሉ። ከዚያም ለዘላለም ተታልለው ጠፍተው ይቀራሉ።

ሉቃስ 8፡6 ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፥ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ።

ጥልቀት የሌለው አፈር ውስጥ የበቀለ ተክል ሥር አይኖረውም። ጠለቅ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የሌላቸው ሰዎች ፈተና ሲመጣ መቋቋም ስለማይችሉ ይወድቃሉ። የሰዎች መሰረታዊ ችግር ፡- መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት መስነፋቸው ነው።

ሉቃስ 8፡7 ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው።

ሰዎች በዚህ ዓለም የኑሮ ሃሳብ፣ በገንዘብ ምኞትና በተድላ ይታነቃሉ፤ ስለዚህ የፍጽምና ፍሬ አያፈሩም።

የሰዎች መሰረታዊ ችግር ፡- በራስ ላይ እና በጊዜያዊ ትርፍ ላይ ማተኮር። የረጅም ጊዜ ራዕይ አለማየት።

ሉቃስ 8፡8 ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ። ይህን በተናገረ ጊዜ፦ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብሎ ጮኸ።

ታማኝና መልካም ልብ ያላቸው ሰዎች ቃሉን ሰምተው ይጠብቁታል፤ በትእግስትም ፍሬ ያፈሩበታል።

“የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”

በ2,000 ዓመታት የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ለእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ዘመን የተሰጠ ምክር ይህ ነው። የታሪክ ሁኔታዎች ምንም አይነት ቢሆኑ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ማድመጥ በየትኛውም ዘመን የዘላለም ሕይወት ቁልፍ ነው።

ራዕይ 2፡7 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ

ሉቃስ 8፡9 ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህ ምሳሌ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው ለብዙ ሕዝብ ነው፤ ትርጉሙ ምን እንደሆነ የጠየቁት ግን ደቀመዛሙርቱ ብቻ ናቸው።

ሉቃስ 8፡10 እርሱም እንዲህ አለ፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት አጻጻፍ ለማወቅ የሚጓጉ እና አጥብቀው የሚፈሉጉ ሰዎች ብቻ እንዲያስተውሉት ተደርጎ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተቶች አሉ ብለው የሚያምኑ ሰዎች፤ ወይም ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንዱ ክፍል ጠቃሚ አይደለም ብለው የሚያስቡ ሰዎች ከቸልተኛው ሰው ዓይን እውነትን ከሚሰውረው ከምስጢሩ መጋረጃ በስተጀርባ አልፈው ዘልቀው አይሄዱም።

ሉቃስ 8፡16 መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ።

መጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ነው፤ በውስጡ ያለው ብርሃንም ሁሉ መልካም እና ዋጋ ያለው ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃንን ለመደበቅ አትሞክር። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ባለማወቅህም አትደሰት። በጭራሽ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተት አለ ብለህ በአፍህ አትናገር። የማይጠቅሙ ክፍሎች የሉትም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንተ ከምታምነው ጋር ከተቃረነ የተሳሳትከው አንተው ነህ ማለት ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ምን ማለት እንደሆነ ማብራራት ካቃተህ አለማወቅህን አትሸፋፍን። ሌሎች ሰዎችን ጠይቅ። ደግሞ እውነት ባንተ የቤተክርስቲያን ቡድን ውስጥ ብቻ ነው ያለችው ብለህ አታስብ። ሌሎችም ሊያስተምሩህ ይችላሉ።

ሉቃስ 8፡18 እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።

መጽሐፍ ቅዱስን እመነው፤ አጥናው፤ ተወያየው፤ እግዚአብሔርም አብዝቶ ይገልጥልሃል። ከውስጡ “ስሕተት” ወይም “የማይጠቅም” እያልክ የምትቆራርጥ ከሆነ ግን ያለህን ጥቂት መረዳት እንኳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታጣዋለህ።

ሉቃስ 8፡21 እርሱም መልሶ፦ እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን ቃል መስማት እና ማድረግ ከኢየሱስ ጋር እጅግ የቀረበ ሕብረት የምናደርግበት ብቸኛ መንገድ ነው።

አሁን ሰው ሁሉ የሚፈተንበትን አንድ ትዕይንት እንመልከት። በባሕር ላይ በጀልባ በሰላም እየሄዱ ሳለ ደቀመዛሙርት ኢየሱስን ይረሱታል፤ ስለዚህ እርሱ እንቅልፉን ይተኛል። ነገር ግን ችግር ሲገጥማቸው ወዲያው ይፈልጉታል።

ሉቃስ 8፡22 ከዕለታቱም በአንዱ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ፦ ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር አላቸው፤ ተነሡም።
23 ሲሄዱም አንቀላፋ። ዓውሎ ነፋስም በባሕር ላይ ወረደ፥ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበርና ይጨነቁ ነበር።
24 ቀርበውም፦ አቤቱ፥ አቤቱ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ተዉም፥ ጸጥታም ሆነ።
25 እርሱም፦ እምነታችሁ የት ነው? አላቸው። ፈርተውም ተደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም፦ እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ የሚያዝ ለእርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? አሉ።

ትምሕርት፡ መልካም ዘመን እንዲሆንልን እንጸልያለን፤ ነገር ግን ምንም አይጠቅመንም፤ ምክንያቱም ሁሉ አልጋ በአልጋ የሆነልን ጊዜ ከኢየሱስ ርቀን እንድንሄድ ያደርገናል። ክፉ ጊዜ ከእኛ እንዲርቅ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፤ ነገር ግን ነገሮች የከፉብን ጊዜ በሙሉ ልብ ጌታን እናገለግላለን።

በስኬታችን ወቅት ኢየሱስን ባለመፈለግ ለውድቀታችን የሚሆኑ ዘሮችን እንዘራለን። በውድቀታችን ጊዜ በኢየሱስ ላይ አጥብቀን በመደገፍ ለስኬታችን የሚሆኑ ዘሮችን እንዘራለን።

በጌርጌሴኖን ሃገር ራቁቱን የሚኖር አጋንንት የሞሉበት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም በመቃብሮች መሃል በሙታን መንደር ይኖር ነበር።

አጋንንቱ በአቅራቢያው ወዳሌ አሳማዎች ውስጥ መግባት እንዲፈቀድላቸው ለመኑ። ሰይጣን በኤደን ገነት በእባብ ውስጥ ነበረ። አሁን ደግሞ የእርሱ አጋንንት በአሳማዎች ውስጥ ሊኖሩ ፈለጉ። አጋንንት እንስሳት ውስጥ መኖር ይወዳሉ፤ እግዚአብሔር ግን በሰዎች ልብ ውስጥ ብቻ ነው መኖር የሚፈልገው።

ሉቃስ 8፡32 በዚያም በተራራው የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማሩ ነበር፤ ወደ እነርሱም ሊገቡ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም።
33 አጋንንትም ከሰውዬው ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፥ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና ሰጠሙ።

አሳማዎቹ አጋንንት ሲገቡባቸው ከአጋንንት ጋር መኖርን ጠልተው መሞትን መረጡ።

ሉቃስ 8፡34 እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩት።

እግዚአብሔር ተዓምር አደረገ። ነገር ግን የተደረገው ተዓምር አሳማዎቻቸው እንዲጠፉ ስላደረገ ለሕዝቡ የገንዘብ ኪሳራ አመጣባቸው።

ሰዎች እግዚአብሔር ነገሮችን በሚቆጣጠርበት ሰዓት እንኳ ገንዘብ ሲያጡ ራሳቸውን መቆጣጠር ያቅታቸዋል። ገንዘብ ከሚያጡ ከኢየሱስ ፊት ቢሸሹ ቢርቁ ይመርጣሉ። ሰዎች ለገንዘብ ያለን ፍቅር ይህን ያህል ነው። ብዙዎቻችን ለገንዘብ ያለን ፍቅር ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር ይበልጣል።

ሉቃስ 8፡35 የሆነውን ነገር ሊያዩ ወጥተውም ወደ ኢየሱስ መጡ፥ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ።

አጋንንቱ ልብሱን አስወልቀውት ነበር። ከአጋንንት እሥራት ነጻ እንደወጣ ሰውየው መጀመሪያ የመጣለት ሃሳብ ልብስ መልበስ ነው። ስለዚህ የዛሬ ሴቶችን ገላቸውን ገልጠው እርቃናቸውን የሚያስኬዳቸው ማነው? ይህ በተጨማሪ ራቁታቸውን የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አእምሮዋቸው ጤናማ አለመሆኑን ያመለክታል።

ሉቃስ 8፡37 በዙሪያውም በጌርጌሴኖን አገር ያሉት ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋልና ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት በታንኳም ገብቶ ተመለሰ።

አሳማዎቻቸው ባሕር ውስጥ ሲሰምጡ የገንዘብ ኪሳራ ስለገጠማቸው አይሁድ ኢየሱስን ጠሉት። እነርሱ አንዳችም መስዋእት የማያስከፍል ሐይማኖት ነው የፈለጉት።

ሉቃስ 8፡38 አጋንንት የወጡለት ሰውም ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ለመነው፤
39 ነገር ግን፦ ወደ ቤትህ ተመለስ፥ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረግልህ ንገር ብሎ አሰናበተው። ኢየሱስም እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት በከተማው ሁሉ እየሰበከ ሄደ።

ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ተዓምር ካደረገ በኋላ ሰዎች እንዲያወሩ አይፈልግም። ይህም መንቀሳቀስ በሚፈልግበት ጊዜ የሕዝብ ብዛት መንገድ እንዳይዘጉበት ለማድረግ ይጠቅመዋል። ኢየሱስ ችሎታውን ማንም እንዲያስተዋውቅለት አይፈልግም። እርሱ በአንድ ሥፍራ መገኘቱ በራሱ ብቻውን ትልቅ ማስታወቂያ ነበር። ተዓምራቶቹን ሁልጊዜ በነጻ ነበር የሚያደርጋቸው፤ ይህም ብዙ ሰዎች በራስ ወዳድነት ተዓምራቱን ለራሳቸው ለመጠቀም ብለው እንዲሰበሰቡ አረደጋቸው፤ እነዚህም ሰዎች እውነትን ፈላጊዎች አልነበሩም።

የብልጽግን ወንጌል ሰዎች በራስ ወዳድነት እግዚአብሔርን ተጠቅመው ለራሳቸው ገንዘብ እንዲያካብቱ ያስተምራቸዋል።፤ ነገር ግን እንደዚህ አይነት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የማወቅ ፍላጎት የላቸውም።

ነገር ግን ሕዝቡ በሙሉ እንዲሄድላቸው ስለለመኑት ይህንን የተፈወሰ ሰው ሰባኪ እንዲሆንለት በመተው ሰውየው ሕዝቡ ኢየሱስን ከሰፈራቸው በማባረራቸው ምን እንደቀረባቸው እንዲነግራቸው ላከው።

በተጨማሪም ይህ ተዓምር ሕዝቡን ገንዘብ አሳጥቷቸዋል። ስለዚህ ኢየሱስን መከተል ሁልጊዜ በነጻ ላይሆን ይችላል፤ ዋጋ ወይም መስዋእትነት ያስፈልጋል። ስለዚህ ከወንጌል ለማትረፍ ብቻ ሳይሆን ስለ ወንጌል ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጁ ብቻ ናቸው ኢየሱስን ወደ መንደራቸው በድጋሚ የሚቀበሉት። እንደዚህ አይነት ተከታዮች ከሁሉ የተሻሉ ተከታዮች ናቸው።

ሉቃስ 8፡40 ኢየሱስም በተመለሰ ጊዜ ሁሉ ይጠብቁት ነበርና ሕዝቡ ተቀበሉት።

ሉቃስ ሐኪም እንደመሆኑ ለሐኪሞች ብዙ ገንዘብ ከፍላ ኪሳራ ውስጥ ገብታ ምንም መፍትሄ ያላገኘች ሴትን ታሪክ ይጠቅሳል።

ሉቃስ 8፡43 ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም።

44 በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ።

የልብሱን ጫፍ መንካት ብቻ እርሱ ባያያትም ለፈውሷ በቂ ነበር።

ይህች ሴት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሕብረት በማድረግ መንፈሳዊ ኃይሉን እየሳበች የምትጠቀመዋን ቤተክርስቲያን ትወክላለች።

ከኢየሱስ ኋላ ብንመጣ እና ብንከተለው ልክ ይህችን ሴት እንደረዳት እኛንም ይረዳናል።

ኢያኢሮስ የምኩራብ አለቃ ነበረ፤ እርሱም ኢየሱስ መጥቶ ሴት ልጁን እንዲፈውስለት ለመነው።

ከዚያ በኋላ ልጅቱ ሞታለች የሚል ወሬ ደረሳቸው።

ሉቃስ 8፡50 ኢየሱስ ግን ሰምቶ፦ አትፍራ፤ እመን ብቻ ትድንማለች ብሎ መለሰለት።
51 ወደ ቤትም ሲገባ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ከዮሐንስም ከብላቴናይቱም አባትና እናት በቀር ማንም ከእርሱ ጋር ይገባ ዘንድ አልፈቀደም።
52 ሁሉም እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፦ አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አለ።
53 እንደ ሞተችም አውቀው በጣም ሳቁበት።

የሰዎቹ ለቅሶ ለማስመሰል ነበር፤ ምክንያቱም አንድ ሃዘንተኛ በሐዘኑ ሰዓት ማንም ላይ ሊያሾፍ አይችልም።

ሉቃስ 8፡54 እርሱ ግን እጅዋን ይዞ፦ አንቺ ብላቴና፥ ተነሺ ብሎ ጮኸ።
55 ነፍስዋም ተመለሰች፥ ፈጥናም ቆመች፥ የምትበላውንም እንዲሰጡአት አዘዘ።
56 ወላጆችዋም ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው።

ይህ ከሙታን ትንሳኤ አስደናቂ ነበር፤ ሆኖም ግን ኢየሱስ ተዓምሩን እንደ ማስታወቂያ በሃገሩ ሁሉ አላስነገረም። ሰዎች ስኬታቸውንና ዝናቸውን ለማሳወቅ በጣም ይጓጓሉ።

የአንዲት ሴት ልጅ ከሙታን መነሳት በእሥራኤል ውስጥ ብዙም ትርጉም ላይሰጣቸው ይችላል። የልጅቱ ከሞት መነሳት የአሕዛብ ቤተክርስቲያን በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ሙት ከሆኑ የአረማውያን አስተምሕሮ ወጥታ መነሳቷን ነው የሚያመለክተው። ያች ቤተክርስቲያን ጠንካራ ምግብ ትመገባለች፤ እርሱም የአዲስ ኪዳን አስተምሕሮ ነው።

አይሁዳውያን ግን እግዚአብሔር ወደ አሕዛቦች ዘወር የሚል አልመሰላቸውም።

ስለዚህ ኢየሱስ ይህ ዜና በአይሁዳውያን መካከል እንዲሰራጭ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ትርጉሙን ሊያስተውሉት አይችሉም፤ በተለይም እርሱን አልቀበል ከማለታቸው ጋር ተያይዞ ሊያስተውሉ አይችሉም።