ኢየሱስ እንደ ፍጹም ሰው - በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 7



አንዲት ሐጥያተኛ ሴት የኢየሱስን እግር ሽቶ ቀባች፤ የሐጥያቷንም ስርየት ተቀበለች፤ ይህም ቤተክርስቲያን በ7ቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ምን እንደምትመስል የሚያሳይ ምሳሌ ነው።

First published on the 3rd of April 2020 — Last updated on the 5th of November 2022

ምዕራፍ 7 ምሳሌያዊ ምዕራፍ ነው፤ በዚህም ምዕራፍ ውስጥ ሉቃስ እግዚአብሔር በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ወደ አሕዛብ ዘወር ለማለት ማሰቡን ያሳየናል።

ነገር ግን መጀመሪያ ደግሞ ሉቃስ አይሁዳውያን ኢየሱስን አንቀበልም ብለው እንደገፉት በትኩረት ያሳየናል።

ሉቃስ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አንድ ታላቅ እምነት ስለነበረው ሮማዊ መቶ አለቃ ይጽፍልናል። ይህ ሰው አሕዛብ ነበረ። ሥልጣንም ስለነበረው በንግግሩ ብቻ እንደፈለገ ወታደሮችን ያዝዛቸዋል። ስለዚህ ይህ መቶ አለቃ ለኢየሱስ እንዲህ አለ፡- ባሪያዬን ለመፈወስ እቤቴ ድረስ መምጣት አያስፈልግህም ምክንያቱም አንተ ታላቅ ስልጣን አለህ፤ ስለዚህ ቃል ብቻ ተናገርና ባሪያዬን በሽተኛ ያደረገው ጋኔን ለቆት ይሄዳል። ይህም ልክ ሰውየው እንዳለው ሆነ።

ሉቃስ 7፡9 ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ፦ እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው።

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን ያህል የዚህን አሕዛብ እምነት እንዳደነቀና ምን ያህል ከአይሁዳውያን እምነት እንደበለጠ ሉቃስ በአጽንኦት ይጠቅሳል።

ይህም ስለ ወደፊቱ በአሕዛብ ቤተክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔር እምነት ምን ያህል እንደሚስፋፋ በጨረፍታ የሚያሳይ ምልክት ነው።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ናይን ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከተማ የአንዲት መበለት ልጅ ሞቶ ቀብር እየሄዱ ነበር። ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው፤ ስለዚህ ልክ ጨለማ በብርሃን ፊት ሊቆም እንደማይችል ሁሉ ሞት በኢየሱስ ፊት ሊቆም አይችልም። ስለዚህ የሞተው ሰው ከሞት ተነስቶ ሕያው ሆነ።

አይሁዳውያን የእግዚአብሔር አብ ልጆች ነበሩ፤ ስለዚህ አረማውያን አሕዛቦችን እግዚአብሔር አባታቸው ስላልነበረ አይሁዳውያን የሚያዩዋቸው በመንፈሳዊ ሞት ውስጥ እንዳሉ ሰዎች ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ወደ አንዲት ልጇ ወደ ሞተባት መበለት ሄደ ምክንያቱም ይህ ልጅ አባት አልነበረውም። ኢየሱስ ይህንን ልጅ ከሙታን ማስነሳቱ ኢየሱስ በመንፈሳቸው ሙት የሆኑትን፣ እግዚአብሔር አባት ያልሆናቸውን የአሕዛብ አረማውያን በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ የዘላለም ሕይወትን ያገኙ ዘንድ እንደሚያስነሳቸው ያመለክታል።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ መሲሁ መሆኑን ለመጠየቅ መጥምቁ ዮሐንስ ከራሱ ደቀመዛሙርት መካከል ሁለቱን ላከ። አይሁዳውያን መሲሁ ሮማውያንን በሙሉ ከእሥራኤል ውስጥ እያሳደደ የሚያስወጣ መስሏቸው ነበር፤ ከዚያም ደግሞ መሲሁ በሃገራቸው ይነግሳል ብለው ጠብቀው ነበር። ኢየሱስ ይህን አላደረገም፤ ስለዚህ አይሁዳውያንን ከሮማውያን ነጻ የሚያወጣቸው መስሎ አልታያቸውም። የእኛ ትልቁ ስሕተታችን እግዚአብሔር ምን ሊሰራ እንዳሰበ እናውቃለን ብለን ማሰባችን ነው።

ኢየሱስ ግን ሮማውያንን ከማባረር የሚበልጥ እቅድ ነበረው። ኢየሱስ ሃሳቡ አይሁድን ከሮማውያን ጭቆና ነጻ ለማውጣት አልነበረም።

የእርሱ ፍላጎቱ የሰው ዘርን በሙሉ ከሐጥያት ነጻ ማውጣት ነው፤ ስለዚህ እቅዱ በ2,000 ዓመታት የቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በዓለም ዙርያ ያሉትን አሕዛብ በሙሉ ለመለወጥ ነው።

ኢየሱስ ዮሐንስን ታላቅ ነብይ ስለመሆኑ አደነቀው።

ሉቃስ 7፡26 ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን።
27 እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው።

መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን በማጥመቁ

ሀ) ኢየሱስን ለመስዋእት እንደሚሆን በግ አጥቦታል፤ ልክ ካሕናት መስዋእታቸውን እንደሚያጥቡት

ለ) ልክ ሊቀካሕናቱ እንደሚታጠብ በተጠመቀ ጊዜ በወረደበትና በእርሱ ላይ በኖረበት በመንፈስ ቅዱስ ከመቀባቱ በፊት ኢየሱስን

አጥቦታል። አሮን ሊቀካሕናት በሆነ ጊዜ ሙሴ አሮንን አጥቦት በዘይት ቀብቶታል።

ስለዚህ ዮሐንስ ኢየሱስ አዳኝ እና የሰማያዊቷ ድንኳን ሊቀካሕናት እንዲሆን መንገድ ጠርጎለታል፤ ያችም መቅደስ የተገነባችው ሕያዋን ድንጋዮች ከሆኑ ዳግመኛ ከተወለዱ አማኞች ነው፤ እነዚህም አማኞች በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ቤተክርስቲያን ሆነዋል።

ሉቃስ 7፡29 የሰሙትም ሕዝብ ሁሉ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው እግዚአብሔርን አጸደቁ፤
ተራዎቹ አይሁዳውያንና ሐጥያተኞች (ቀራጮች) የዮሐንስን የንሰሃ ጥምቀት ተቀብለዋል።
ሉቃስ 7፡30 ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ስለ አልተጠመቁ የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው ጣሉ።
የአይሁድ መሪዎች ግን የዮሐንስን ጥምቀት አንቀበልም አሉ።

ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ ነብይ ተቀብለውታል፤ የአይሁድ መሪዎች ግን የዮሐንስን ትምሕርት አንቀበልም ብለዋል። ችግሩ ያለው በሐይማኖት መሪዎች ላይ ነበር ምክንያቱም እነርሱ እውነትን አልፈለጉም፤ እነርሱ የፈለጉት ስልጣናቸውንና ዝናቸውን እንዲሁም ገንዘባቸውን ማስጠበቅ ብቻ ነበር።

በኢየሱስ አገልግሎት መጨረሻ ላይም ልክ እንደዚሁ ነው የሆነው። ተራዎቹ የአይሁድ ሕዝብ በሆሳና እለት በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲገባ ኢየሱስን አመሰገኑት። ነገር ግን በቀጣዩ አርብ የአይሁድ መሪዎች እነዚህኑ ኢየሱስን ያመሰግኑት የነበሩትን ሕዝብ ኢየሱስ ይሰቀል ብለው ጥያቄ እንዲያቀርቡ አሳመኑዋቸው።

ለአይሁድ ሕዝብ ውድቀት ምክንያት የሆኑት የሐይማኖት መሪዎች ናቸው።

መጀመሪያ የዮሐንስን ጥምቀት አንቀበልም አሉ። ከዚያ በኋላ ቆይተው ደግሞ ኢየሱስ ካልተሰቀለ ብለው ጥያቄ አቀረቡ።

ኢየሱስም አይሁድ ስለ ገፉት ወደ አሕዛብ ሊዞር ችሏል።

ሉቃስ 7፡31 እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን አስመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ?
32 በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ፦ እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም ይላል።

ሉቃስም ኢየሱስ እንዴት አይሁዶች እንደሚገፉት በትንቢት መናገሩን ጽፎልናል።

ሰዎች እውነትን ላለመቀበል አንዴ ከቆረጡ እውነት ደስ በሚል ሙዚቃ ታጅቦ ቢቀርብላቸውም፤ ወይም በሐዘን እንጉርጉሮ ታጅቦ ቢቀርብላቸውም ላለመቀበል ከወሰኑ እንደማይቀበሉ ኢየሱስ በምሳሌ ገልጧል። ምንም ቢደረግላቸው አይቀበሉም።

ሉቃስ 7፡33 መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና፦ ጋኔን አለበት አላችሁት።

ሉቃስ 7፡34 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና፦ እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት።

ዮሐንስ ከከተማ ሕዝብ ጋር የማይቀላቀል አክራሪ የበረሃ ሰው ነበር፤ አይሁድም አንቀበልህም አሉት። ኢየሱስ ደግሞ እንደ ዮሐንስ አክራሪ አልነበረም፤ ሰዎችንም ይቀርብ ነበር፤ አይሁዶች ግን እርሱንም አልቀበልህም አሉት።

ሉቃስ አይሁዶች ዮሐንስንም ኢየሱስንም እንዴት እንደገፉዋቸው በአጽንኦት ያሳየናል፤ ይህም ኢየሱስ በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ስትመሰረት ደቀመዛሙርቱ ወደ አሕዛብ እንዲዞሩ እንዲያዝዛቸው ምክንያት እንደሆነ ያሳየናል።

ሉቃስ 7፡35 ጥበብም ለልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች።

አብዛኞቹ አይሁዶች አንቀበልም ብለው የገፉትን የወንጌሉን እቅድ አሕዛብ ደግሞ በደስታ ይቀበሉታል። ለብዙዎቹ አይሁዶች ምንም ትርጉም ያልሰጣቸውን የእግዚአብሔር የማዳን እቅድ አሕዛብ ተረድተውት በሙሉ ልባቸው ተቀበሉት።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ አንድ ፈሪሳዊ ቤት እንጀራ ለመብላት ገባ፤ በዚያን ጊዜም አንዲት ሐጥያተኛ ሴት እግሮቹን አጥባ በዘይት ቀባቻቸው። ልክ ኢየሱስ እንደተጠመቀው ጥምቀት፤ በጥምቀቱ እንደ መስዋእት እንደታጠበውና ለሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት በመልከጼዴቅ ሹመት እንደተሾመ ሊቀካሕናት እንደተቀባው አጠበችው፤ ቀባችውም።

በጴንጤ ቆስጤ እለት ጴጥሮስ ተመሳሳይ ነገር ተናገረ።

የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

የተናገረው በጥምቀት ውሃ ስለመታጠብና በመንፈስ ቅዱስ ስለመቀባት ነው።

ከሲኦል የምንድንበት መንገድ ይህ ነው።

ሉቃስ 7፡37 እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች።
38 በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች።

ይህ ለምንድነው በሴት የተደረገው? ሴቲቱ ለምንድነው እግሮቹን ብቻ ያጠበችውና የቀባችው?

ሴት የምትወክለው ቤተክርስቲያንን ነው። ጳውሎስ ቤተክርስቲያን እንደ ንጹህ ድንግል ለኢየሱስ ባልዋ እንዲሆን እንድትታጭ ይፈልጋል።

2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2 በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤

ስዚህ ሉቃስ ይህችን ሴት ተጠቅሞ በጽሁፉ ውስጥ የወደፊትዋን የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ዘመን ሊያጎላ ፈልጓል። ናቡከደነጾር የአሕዛብ ምስል ያለበትን ራዕይ አይቷል። ራሱ ባቢሎን፣ እጆቹ ሜዶናውያን እና ፋርሶች ነበሩ። ሆዱ እና ጭኖቹ ግሪክ ነበሩ። እግሮቹ ደግሞ የሚወክሉት የሮማ መንግሥትን ነበር። ስዚህ የእግሩ ጣቶች ደግሞ የ2,000 ዓመታት የቤተክርስቲያን ታሪክን ነበር የሚወክሉት፤ በዚያን ጊዜም ጌታ እጅ ያልነካው ድንጋይ ሆኖ በመምጣት ምስሉን በሙሉ ይመታውና ያደቅቀዋል።

ስለዚህ የእግሩ ጣቶች ሰባቱን የቤተክርስቲያን ዘመኖች ይወክላሉ፤ በእነዚህም ዘመናት አሕዛብ በቃሉ ውሃ አማካኝነት ታጥበው በመንፈስ ቅዱስ ይቀባሉ።

ኤፌሶን 5፡25-26 ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤

የሴቲቱ እምባ አሕዛብ ስለ ሐጢያታቸው ንሰሃ በሚገቡ ጊዜ የሚያነቡትን እምባ ያመለክታል። የሴት ረጅም ጸጉት ሴቲቱ ለባሏ መገዛትዋን ያመለክታል። ሴቲቱ ረጅም ጸጉርዋን መጠቀሟ ንሰሃ የገባችዋ ቤተክርስቲያን ለባሏ ለኢየሱስ ክርስቶስ ማለትም ለቃሉ መገዛቷን ያመለክታል።

ክርስቲያን ሴቶች ዛሬ ጸጉራቸውን አሳጥረው ይቆረጣሉ፤ ስለዚህ ይህች ሴት በኢየሱስ የተመሰገነችበት ሥራ መስራት አይችሉም። ደግሞ ሐጥያተኛ ነበረች! የሥነ ምግባር መመዘኛችን ወድቋል? የዚህ ዘመን ጸጉሯን አሳጥራ የምትቆርጥ ሴት ለመጽሐፍ ቅዱስ መገዛትን ያቆመች ቤተክርስቲያንን ትወክል ይሆን?

ሉቃስ 7፡39 የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ፦ ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ።

ራሳቸውን የሚያጸድቁ አይሁዳውያን ለሐጥያተኞች፣ ይልቁንም ለአሕዛብ ሐጥያተኞች ጊዜ አልነበራቸውም።

ሉቃስ 7፡40 ኢየሱስም መልሶ፦ ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። እርሱም፦ መምህር ሆይ፥ ተናገር አለ።
41 ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ።
42 የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?
43 ስምዖንም መልሶ፦ ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም፦ በእውነት ፈረድህ አለው።

አይሁዳውያን ከአረማውያን አሕዛብ ይልቅ ለእግዚአብሔር ቅርብ ነበሩ። ስለዚህ አይሁድ ከአሕዛብ ይልቅ ጻድቃን ነበሩ። ስለዚህ እግዚአብሔር አይሁድን ይቅር የሚልበት ብዙም ሐጥያት አልነበረም፤ ምክንያቱም አይሁድ አብዛኛው የሚያደርጉት ነገር ትክክል ነበር።

አሕዛብ ግን ከእግዚአብሔር እሩቅ ነበሩ፤ ከአይሁድ ይልቅ ብዙ ስሕተት ይሰሩ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር አሕዛብን በብዙ ይቅር የሚልበት ሐጥያት ነበረባቸው።

ስለዚህ በቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ለእግዚአብሔር አይሁድ ከነበራቸው ፍቅር አሕዛብ የሚበልጥ ፍቅር ነበራቸው። ከዚህም የተነሳ የአሕዛብ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ እንድትሆን ተመርጣለች፤ ምክንያቱም አሕዛቦች ስለ ብዙ ጣኦት አምልኮዋቸው ይቅር ስለተባሉ እግዚአብሔርን አብልጠው ይወዱታል።

ሉቃስ 7፡44 ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች።

በሕግ የሚኖሩት አይሁዳውያን ኢየሱስን በፍቅር አልተቀበሉትም። ሐጥያተኛዋ ሴት (ቤተክርስቲያን) ግን ተቀበለችው። ይህም ኢየሱስ የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያንን ለመመስረት ወደ ሐጥያተኞች (ወደ አሕዛብ) እንደሚዞር ግልጽ የሆነ አመላካች ነው።

አንድ ሰው ሚስት ሲፈልግ ከሁሉ በላይ የምትወደውን ሴት ነው የሚፈልገው።

ሉቃስ 7፡45 አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም።

ሐጥያተኛዋ ሴት (ቤተክርስቲያን የሚሆኑት ሐጥያተኛ አሕዛብ) እጅግ በጠለቀ ፍቅር ወደ ኢየሱስ ቀረበች። ብዙ ሐጥያት ይቅር ስለተባለላት አብዝታ ወደደችው።

ከኢየሱስ እግር ስር መሆን ትሕትና እና ለእርሱ መታዘዝን ያመለክታል። እነዚህ ባሕርያት የአሕዛብ የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን መለያዎች ናቸው።

ሉቃስ 7፡46 አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች።

ከሐጥያተኛይቱ ሴት ይልቅ ጻድቅ የነበረው አይሁዳዊ ለኢየሱስ ብዙም አክብሮት አልነበረውም።

ኢየሱስ በቀላሉ ትሑት ሆኖ ነበር የመጣው። አይድም ሲያዩት ብዙ አልተደነቁበትም። እነርሱ የፈለጉት ሮማውያንን የሚያባርርላቸው ኃይለኛ የእሥራኤል መንግሥት ነው። እግዚአብሔር ያሰበው በቀራንዮ ሞቶ ዓለምን ሁሉ የማዳን እቅዱ ለእነርሱ አልተዋጠላቸውም።

አይሁዳዊው የኢየሱስን ራሱን እንኳ አልቀባውም። ሐጥያተኛይቱ ሴት ግን ከእግሩ በታች ራሷን አዋረደች።

ሉቃስ 7፡47 ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።

አይሁዳውያን የተሻለና ከሐጥያት የጸዳ ሕይወት ስለኖሩ ብዙም ይቅር የሚባልላቸው ሐጥያት አልነበራቸውም። ስለዚህ እግዚአብሔርን ብዙም አይወዱትም። እነርሱ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከሚሆነው ዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥር ይልቅ ምርጫቸው ለጊዜያዊ የእሥራኤል መንግሥት ነው።

ሉቃስ 17፡21 ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።

የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በውስጣችን ሲሆን እያንዳንዳችንን በመንፈሳዊ መንግሥቱ ውስጥ ሕያዋን ድንጋዮች ያደርገናል።

ሉቃስ 7፡48 እርስዋንም፦ ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት።

ሴቲቱ የቤተክርስቲያን ወኪል ናት። በኢየሱስ ማለትም በቃሉ ላይ የተጣበቀችው የአሕዛብ ቤተክርስቲያን እንባ እያፈሰሰች ንሰሃ ስለገባች ብዙ ሐጥያቷን ይቅር ተባለች።

ሉቃስ 7፡49 ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው፦ ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው? ይሉ ጀመር።

ኢየሱስ ሐጥያትን ይቅር ሊል እንደሚችል አይሁድ መቀበል አቃታቸው። ነገር ግን ኢየሱስ ወደ አሕዛብ ዘወር ሲልና በመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን መዳንን ሲያቀርብላቸው ደስ ብሏቸው ተቀበሉት።

ሉቃስ 7፡50 ሴቲቱንም፦ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።

ኢየሱስ ይህችን ሴት ወደፊት እንደምትመሰረተው የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ተምሳሌት አድርጎ ነው ያያት። እኛ የዳንነው በእምነት በጸጋው አማካኝነት ነው።

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከሐጥያት ሸክም በውስጣችን የምናገኘው እረፍት ነው። የዚያን ጊዜ ብቻ ነው በእግዚአብሔር ፊት ሰላም እና መጽናናትን የምናገኘው።

ኤፌሶን 2፡8 ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤

ዮሐንስ 14፡26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።

ዮሐንስ 14፡27 ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23