ኢየሱስ እንደ ፍጹም ሰው - በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 6

ሉቃስ ኢየሱስ ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሰው መሆኑ ላይ ነው አጽንኦት ሰጥቶ የጻፈው። ሉቃስ በተጨማሪም ኢየሱስን ለማገልገል ምን አይነት ልብ ሊኖረን እንደሚገባንም ነግሮናል።

7 ሙላትን የሚወክል ቁጥር ነው። በሳምንት ውስጥ 7 ቀኖች አሉ። በተፈጥሮ ውስጥ የሰባት ቀን ኡደት የለም። ዘፍጥረት ውስጥ እግዚአብሔር በምድር ላይ ሕይወትን ፈጥሮ 7 ቀናት ውስጥ እንዳጠናቀቀ ተጽፏል። በአንድ ሳምንት ውስጥ 7 ቀናት የኖሩበት ብቸኛ ምክንያት ይህ ነው። ፈረንሳውያን በ1700ዎቹ ውስጥ እግዚአብሔርን በካዱበት ዘመን አንድ ሳምንት አሥር ቀኖች እንዲኖሩት ሊያደርጉ ሞክረው ነበረ ግን አልተሳካላቸውም። እግዚአብሔር በሳምንት ውስጥ 7 ቀን እንዲኖር ካደረገ በኋላ ይህንን ሊቀይር ሞክሮ ማንም የተሳካለት የለም።

6 የሰው ቁጥር ነው። ሰው የተፈጠረው በስድስተኛው ቀን ነው።

ሰው በሕይወቱ ውስጥ ሐጥያት ስላለበት ከሰባት በአንድ ጎድሏል። በምድር ላይ ያሉ የሕይወት መከራዎችና ውጣ ውረዶች ሁሉ መንስኤያቸው ሐጥያት መኖሩ ነው።

ስለዚህ ሰው በዚህ በሐጥያት በተሞላ ምድር ውስጥ በሰላም መኖር እንዲችል አዲስ አስተሳሰብ ያስፈልገዋል።

ሉቃስ እግዚአብሔር ከአይሁዶች ወደ አሕዛብ ዘወር እንደሚል በመግለጽ አዲስ ሃሳብ ያቀርባል። ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ አሕዛብ ዘወር ባለ ጊዜ አሕዛብ እግዚአብሔር በሚያስብበት መንገድ ማሰብን መማር አለባቸው። እግዚአብሔር ከሐጥያት ሊያነጻንና ይቆጣጠረንም ዘንድ በውስጣችን መኖር ይፈልጋል፤ ይህንንም የሚያደርገው ዓለምን የማዳን ሃሳቡን በእኛ በኩል መፈጸም ስለሚፈልግ ነው፤ ዓለምም ይህንን ሃሳቡን አታውቅም።

ሉቃስ በጻፈው ወንጌል ውስጥ የአሕዛብን ቤተክርስቲያን በተመለከተ ብዙ ፍንጮች በስውር አስቀምጧል።

በሁለት ሺ ዓመታት ውስጥ የሚያልፉት ሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት አይሁድ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያልተረዱት ታላቅ ሚስጥር ነው።

ምዕራፍ ስድስት የሚጀምረው ደቀመዛሙርቱ ርቧቸው በእርሻ መካከል ሲያልፉ እሸት እየቀጠፉ እንደበሉ በማሳየት ነው። ኢየሱስን ይጠሉ የነበሩት ፈሪሳውያን ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ደቀመዛሙርቱ የሙሴን ሕግ አያከብሩም በሰንበት ሥራ ይሰራሉ ብለው ተናገሩ።

ሉቃስ 6፡1 በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር።
ሉቃስ 6፡2 ከፈሪሳውያን ግን አንዳንዶቹ፦ በሰንበት ሊደረግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? አሉአቸው።

ኢየሱስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈ እንግዳ የሆነ ክስተት ጠቀሰላቸው፤ ይህም ዳዊት የራበው ጊዜ መቅደሱ ውስጥ ገብቶ በቅዱስ ስፍራ ለካሕናት ብቻ እንዲበሉ የተፈቀደውን የመሥዋዕት እንጀራ እንደበላ ነበር። እግዚአብሔርም ዳዊት ሕግ ተላልፏል ብሎ አልቀጣውም።

ሉቃስ 6፡3-4 ኢየሱስም ለእነርሱ መልሶ፦ ዳዊት በተራበ ጊዜ እርሱ አብረውት ከነበሩ ጋር ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ከካህናት ብቻ በቀር መብላቱ ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ ይዞ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ደግሞ እንደ ሰጣቸው ይህን አላነበባችሁምን? አለ።

ኢየሱስ ፈሪሳውያንን የሚመልሱት አሳጣቸው። እግዚአብሔር ዳዊትን በዚህ ሥራው ሳይቀጣው ለምን እንዳለፈው ማሰብም ማመንም አይፈልጉም። ከዚያም ሌላ ደግሞ እግዚአብሔር ዳዊት የመሥዋዕቱን እንጀራ እንዲበላ ለምን እንደፈቀደለትም አያውቁም። በዚህም ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ትርጉም አለማወቃቸውን ማመን ሊኖርባቸው ነው። እነርሱ ግን አናውቅም ማለት አይፈልጉም።

ዳዊት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያደረገው ነገር በአዲስ ኪዳን የሚመጣው መሲኅ የሚያንጸባርቅ ነበር።

የብሉይ ኪዳን ነብያት እያንዳንዳቸው ሊመጣ ያለውን የክርስቶስን አገልግሎት በከፊል በድርጊታቸው አሳይተዋል።

ዳዊት ገና ትንሽ ልጅ ሳለ ነው በነብዩ ሳሙኤል እጅ ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው፤ ነገር ግን የእርሱ ተቃዋሚ የነበረው ንጉሥ ሳኦል እስኪገደል ድረስ መንገስ አልቻለም።

ክርስቶስ ከዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በነብዩ መጥምቁ ዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ሲወጣ በእርሱ ላይ በወረደው እና ባረፈበት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቷል። ነገር ግን ንግሥናውን በይፋ የሚጀምረው ጠላቶቹ አውሬው እና ሐሰተኛው ነብይ በታላቁ መከራ መጨረሻ ወደ እሳት ባሕር ሲወረወሩ ነው። ከዚያ በኋላ በሺ ዓመቱ ዘመን ውስጥ ኢየሱስ ይነግሳል።

በእነዚህ ጊዜያት መካከል የእኛን መዳን ለመፈጸም ኢየሱስ በመልከጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካሕናት ሆኖ እያገለገለ ነው።

የመጀመሪያውን ሊቀካሕናት አሮን አጥቦ በዘይት የቀባው ነብዩ ሙሴ ነው።

ዘጸአት 40፡12 አሮንንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አቅርበህ በውኃ ታጥባቸዋለህ።

13 የተቀደሰውንም ልብስ አሮንን ታለብሰዋለህ፤ በክህነትም ያገለግለኝ ዘንድ ቀብተህ ትቀድሰዋለህ።

ዕብራውያን 5፡5 እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤
6 እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል።

ኢየሱስ ደግሞ የታጠበው መጥምቁ ዮሐንስ በተባለ ነብይ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ነው፤ ከዚያም ከውሃው ውስጥ ሲወጣ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል። የሊቀካሕናትነቱ አገልግሎትም የጀመረው ከዚያ ወዲያ ነው።

ዳዊት የክርስቶስን አገልግሎት በድርጊት ስላሳየ ዳዊትም ንጉስ እንዲሆን በተቀባበት እና ከብዙ ዓመታት በኋላ በነገሰበት ጊዜ መካከል የክሕነትን ሥራ እንዲፈጽም ተፈቅዶለታል። ምክንያቱም ዳዊት የክርስቶስን አገልግሎት እያንጸባረቀ ነበር።

ዮሴፍ ኢየሱስን የራሱ ልጅ አድርጎ ተቀብሎ በማሳደጉ ኢየሱስን የዳዊት ንጉሳዊ የዘር ሐረግ ውስጥ አስገብቶታል፤ ከዚህም የተነሳ ኢየሱስ የዳዊት ልጅ ተብሏል፤ ስለዚህ ለዳዊት የተፈቀደለት መብት ሁሉ ለኢየሱስ ተሰጥቶታል።

1ኛ ጴጥሮስ 1፡10 ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤
11 በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር።

የክርስቶስ መንፈስ በእያንዳንዱ የብሉይ ኪዳን ነብይ ውስጥ ነበረ፤ ይህም መንፈስ ለነብያቱ ወደፊት ስለሚሆን ስለ ክርስቶስ አገልግሎት የተለያየ ፍንጭ ይሰጣቸው ነበር። ዳዊት የተወሰኑ ትንቢቶችን በመናገሩ ንጉሥም ነብይም ነበረ።

ሌላ ምሳሌ ደግሞ ዮሴፍ ነው፤ ዮሴፍን አባቱ ይወደዋል ወንድሞቹ ግን ይጠሉታል። ዮሴፍ ግብጽ ውስጥ ከሁለት ወንጀለኞች ጋር ታስሮ ነበር። ዳቦ ጋጋሪው ሲሞት ጠጅ አሳላፊው ግን በሕይወት ኖረ።

ኢየሱስ የተባለው ሰው በአባቱ በእግዚአብሔር የተወደደ ሲሆን ወንድሞቹ አይሁዶች ግን ጠልተውታል። እርሱም በመስቀል ላይ ከሁለት ወንጀለኞች ጋር ታስሮ ነበር፤ ከነዚህ ሁለት ወንጀለኞች አንዱ ሞቶ ወደ ሲኦል ሲወርድ ሌላኛው ግን ወደ ገነት ገብቷል።

ሉቃስ 6፡5 የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው አላቸውም።

ኢየሱስ ሕዝቡ ለማመን የሚከብዳቸውን ትልቅ ነገር ተናገረ። ነብያት ሁሉ እያንዳንዳቸው የክርስቶስን ሕይወት በከፊል ማሳየታቸው ብቻ ሳይሆን እንደውም አይሁድ የተቀደሰ ቀን ብለው የሚያከብሩት ሰንበት እንኳ ሳይቀር የክርስቶስ አገልግሎት መገለጫ አንዱ መንገድ ነበር።

ሰንበት ማለት እረፍት ነው።

ዘፍጥረት 2፡3 እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ ዐርፎአልና።

እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን የባረከው እግዚአብሔር ስላረፈበት ነው እንጂ ቀኑ ሰባተኛ ቀን ስለሆነ አይደለም።

ትኩረቱ በሰባተኛው ቀን (በቅዳሜ) ሳይሆን በእረፍቱ ነበር።

ነገር ግን በእግዚአብሔር ልብ የነበረው ትልቁ ቁምነገር ከሥራ እና ገንዘብ ለማግኘት ስደስት ቀን ከሚያደርጉት ሩጫ በሳምንት አንድ ቀን እንዲያርፉ አልነበረም፤ ምክንያቱም ይህ አይሁዶችን የተሻሉ ሕዝብ አላደረጋቸውም።

የሰንበት እረፍት የታሰበው ከሐጥያት እና ከአለማመን እረፍት እንዲሆን ነበር።

ዕብራውያን 4፡9 እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል።
ዕብራውያን 4፡10 ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።

ስድስት ቀን ከሰሩ በኋላ በሰባተኛው ቀን ማረፍ ከዚያም እንደገና ወደ ሥራ መመለስ ምንም አይጠቅምም።

እግዚአብሔር እንደዚያ አላደረገም። እግዚአብሔር ሰርቶ የፍጥረትን ሥራ አጠናቀቀና አረፈ፤ ከዚያ በኋለ ወደ መፍጠር ሥራ ተመልሶ አያውቅም ምክንያቱም አንድ ጊዜ ፈጥሮ ጨርሷል።

ስድስት ሐጥያትን የሚወክል ቁጥር ነው። 666 የአመጽ ሰው ነው። ለስድስት ቀናት መስራት የሐጥያት ሥራዎቻችንን ይወክላል። ጴጥሮስ ለሕዝቡ የሐጥያትን መድሐኒት አሳይቷቸዋል።

የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ … አላቸው።

የኢየሱስ ደም ከሐጥያት ያነጻናል። ከዚያም መንፈስ ቅዱስ ማለትም በደሙ ውስጥ ያለው ሕይወት ወደ ልባችን ውስጥ ገብቶ ይቆጣጠረንና የሐጥያትን ፍላጎት ከልባችን ውስጥ ያስወግደዋል። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ሕይወታችን በኢየሱስ ቁጥጥር ውስጥ እንዲሆን ያደርገዋል፤ ከዚያም በኋላ በፊት እንመላለስባቸው የነበሩ የሐጥያት ሥራዎችን እንተዋቸዋለን።

ስለዚህ የአይሁድ የሰንበት ቀን (እነርሱን የተሻሉ ሰዎች ሊያደርጋቸው ያልቻለው ቀን) የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጥላ ነበረ፤ ይህም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እኛን የተሻሉ ሰዎች ያደርገናል ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ኢየሱስ የሕይወታችን ጌታ ይሆናል፤ በውስጣችንም በመኖር በአዲስ ኪዳን ውስጥ እርሱ ማድረግ የሚፈልገውን እንድናደርግ ከውስጥ ሆኖ ይመራናል።

ዕብራውያን 10፡1 ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥

ይህንንም የሚያደርገው ሳይወለድ በፊት በመንፈሱ በብሉይ ኪዳን ነብያት ውስጥ ሆኖ ሊመጣ ያለውን አገልግሎቱን በእነርሱ ድርጊት ይገልጥ እንደነበረው ነው።

በዚህም መንገድ የሰንበት ቀን ከሳምንት ውስጥ አንድ ቀን ከመሆን ተለውጦ እግዚአብሔር በሚለዋወጡት የሰባቱ ቤተክርስቲያን ዘመናት ክስተቶች መካከል የአሕዛብ ቤተክርስቲያን የማዳን እቅዱን የምትከተልበት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ሆኗል።

በገዛ ፈቃዳችን ነጻ ፈቃዳችንን ለእርሱ ብቸኛ መስዋዕት አድርገን ስናቀርብና ሕይወታችንን ተረክቦ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲመራን ስንጠይቀው የዛኔ በእውነትም እርሱ የሰንበት ጌታ ይሆናል ማለትም ከሐጥያት እና ከአለማመን እረፍት ይሰጠናል።

ጻፎችና ፈሪሳውያን እንደገና በነገር ሊያጠምዱት ሞከሩ። በሽተኛ ስለፈወሰ ብለው በሰንበት ሥራ ሰራ በማለት ይከሱታል።

አይሁዶች ቁምነገሩ አልገባቸውም። በሰንበት ምንም ስራ አለመስራት ሰው የራሱን የሐጥያት ሥራውን ከመስራት የማረፉ ምሳሌ ነው።

በብሉይ ኪዳን ውስጥ የነበሩ አይሁዶች ሐጥያት የመስራት ፍላጎታቸውን ማስወገድ አልቻሉም። ሐጥያትን የመስራት ፍላጎት ሊወገድ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ልባችን ውስጥ ገብቶ ሲቆጣጠረን ነው፤ ይህም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ይባላል። ከዚያ በኋላ የራሳችንን ስራ አንሰራም፤ ምክንያቱም ሥራዎቻችን ሁሉ በኢየሱስ ቁጥጥር ውስጥ ይሆናሉ። የዛኔ ብቻ ነው እግዚአብሔር ሕይወታችንን ሲመራ ከእግዚአብሔር የማዳን ሚስጥር እቅድ ጋር አብረን ልንሄድ የምንችለው። ይህ ሁሉ የሚሆነው በሰባቱ የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ በሚያልፈው የአዲስ ኪዳን ዘመን ብቻ ነው።

ሉቃስ 6፡6 በሌላው ሰንበትም ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤
7 ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር።
8 እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው፦ ተነሣና በመካከል ቁም አለው፤ ተነሥቶም ቆመ።
9 ኢየሱስም፦ እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው።
10 ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን፦ እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች።

ይህም ፈሪሳውያንን እጅግ አስቆጣቸው። ኢየሱስ በሥራው በለጣቸው። የእርሱን አይነት ኃይል ሊገልጡ አልቻሉም። እርሱ ከሚሰራው አንጻር እነርሱ አቅመቢስና ተራ ሰዎች ሆነው ታዩ፤ ክብራቸውም ስለተነካባቸው ሊበቀሉት ፈለጉ። ሆኖም ኢየሱስ ምንም ነገር አላደረገም ነበር፤ ጥቂት ቃላትን ተናገረ እንጂ።

ፈሪሳውያንን ያስቆጣቸው ሌላ ነገር ደግሞ ቃላት መናገር ካሕናቶቻቸውም ሐይማኖታዊ አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ በየሰንበቱ ያደርጉት የነበረ ነገር መሆኑ ነው። ካሕናቱ ብዙ ንግግር ይናገሩ ነበር። እንዲናገሩ የፈቀደላቸው እግዚአብሔር ነው። ኢየሱስም ካሕናቱ ከሚያደርጉት የተለየ ነገር አላደረገም።

ደግሞም ካሕናቱ ራሳቸው በሰንበት እሳት ሲያነድዱ፣ ለመስዋዕት የሚሆኑትን እንስሳት ሲያርዱ እና እጣን ሲያጨሱ ሥራ ይሰራሉ። የሚወዘወዘውን መስዋዕት ወደ ጎን ወደ ጎን ይወዘውዛሉ፤ የማንሳት ቁርባኑን ወደ ላይ ያነሳሉ፤ ይህም የመስቀሉ ምሳሌ ነው። ከዚያም የእንስሳቱን ሥጋ ይቆራርጡና ከመሰውያው ላይ ያስወግዱዋቸዋል፤ ቦታውንም ያጸዱታል። ይህን ሁሉ በማድረግ ካሕናቱ በሰንበት ቀን ተግተው ይሰራሉ።

ከሕግ አንጻር ፈሪሳውያን ይህንን ሁሉ የካሕናት ሥራ ደግፈው የኢየሱስን ንግግር መቃወማቸው በጣም ተሸንፈዋል።

ሉቃስ 6፡11 እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ።

እውነቱ ግን ፈሪሳውያን ለእግዚአብሔር ሕግ መሟገታቸው ሳይሆን የሰዎችን ትዕዛዝ የሚያከብር የራሳቸው ቡድን መፍጠራቸው ነው።

እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል አይፈልጉትም ነበር ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ከእነርሱ ልማድ ፈጽሞ የተለየ ነው። እነርሱ የሚቀበሉት ቀድመው እራሳቸው ካመኑት ጋር የሚስማማላቸውን ብቻ ነው። ለለውጥ ዝግጁ አልነበሩም። አስቀድመው ከያዙት ነገር የተሻለ ሲመጣ ለመቀበል ፍላጎት አልነበራቸውም።

ስለዚህ እነርሱ ካወቁት በላይ ከሚያውቀው ከኢየሱስ ከመማር ይልቅ እርሱን ለማጥፋት ነው የፈለጉት፤ ምክንያቱም በቃሉም ሆነ በሥራው እነርሱ ከእርሱ በጣም እንደሚያንሱ አሳይቷቸዋል። ይህም በትዕቢት ያበጠ ልቦናቸውን አስተንፍሶባቸዋል።

የእነርሱ ሕይወት ባለህበት ሂድ ነበር። ብዙዎቻችን ለለውጥ ፍላጎት የለንም።

በሰዎች ሐይማኖታዊ ሥርዓት ውስጠ ያለው ትልቅ ስሕተት ለውጥን እምቢ ማለት ነው። ዛሬ የቤተክርስቲያን ወግ ነው የምንፈልገው እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን አይደለም። ለዚህ ሰብዓ ሰገል ወደ በረት ገቡ ብለን የምናምነው፤ እነርሱ ግን ወደ ቤት ውስጥ ነው የገቡት።

በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተጻፈውን ሳይሆን የምንወደው ስጦታ የመለዋወጥ ባሕላችንን ነው።

ሉቃስ 6፡12 በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ።

ኢየሱስ አንድ ቡድን ማቋቋም ፈለገ። መሪ የሚሆኑ ሰዎችን መመልመል በጣም ትልቅ ሥራ ስለሆነ ሌሊቱን በሙሉ በጸሎት አሳለፈ።

በጸሎት ካሳለፈው ሰዓት አንጻር ካደረጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ ይህ በጣም ከባዱ ውሳኔ ነበር፤ እርሱም የቤተክርስቲያን መሪ የሚሆኑ ሰዎችን መምረጥ ይመለከታል። እግዚአብሔር በሰጠው ስኬት ራሱን ከፍ ሳያደርግ እግዚአብሔርን በማገልገል የሚጸና ማነው? ሌሎች ሰዎችን ፍጹም ወደ ሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲመራቸው እግዚአብሔር ሊያምነው የሚችል ሰው ማነው? የእኛ ትልቁ ድክመታችን እግዚአብሔር ሲሰራ አሰራሩ እኛ ከምናስበው መንገድ የተለየ መሆኑን አለማስተዋላችን ነው። ሰዎች እንደመሆናችን በራሳችን አቅም መደገፍ በራሳችን ጥበብ መስራትና አሮን የወርቅ ጥጃውን በሰራ ጊዜ እንዳደረገው ለሕዝብ ፈቃድ የመስገድ ልማድ አለብን ምክንያቱም ይህ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝልናል ብለን እናስባለን። የሰው እኔነትና በራስ ጥበብ መደገፍ ከጥንትም ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ጠላትነት ነው። ብቸኛው መልካም የሆነ የሰው ፈቃድ ለራሱ ምኞት የሞተ ፈቃድ ነው።

የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምናገኝበትም ብቸኛው መንገድ በጸሎትና ለቃሉ በመታዘዝ ነው።

ከእግዚአብሔር የምናገኛቸው መልሶች ግን ከጠበቅነው ፍጹም የተለዩ ነው የሚሆኑት። የራሳችንን ፈቃድ ለመፈጸም እንድንችል ብለን መጸለይ የለብንም። ምክንያቱም የራሳችንን ፈቃድ ስንፈጽም ጥቅሙ የረጅም ጊዜ አይሆንም። ለራሳችን ፈቃድ መሞት አለብን። ዛሬ ሰዎች “ሰልፊ” ፎቶ በመነሳትና በራስ ወዳድነት ተጠምደዋል። ይህም ጥሩ አይደለም።

ሉቃስ 6፡13 በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤

ዛሬ ያለብን ትልቅ ችግር ኢየሱስ ማንን እንደመረጠ አለማወቃችን ነው።

የጥንቷ ቤተክርስቲያን በይሁዳ ቦታ አሳዳጁን ሳውልን አትመርጠውም ነበር። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ሐዋርያት በይሁዳ ቦታ ማቲያስን መረጡ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ማቲያስን ሁለተኛ አይጠቅሰውም። እግዚአብሔር ግን ሳውልን መረጠውና ጳውሎስ ብሎ ጠራው እርሱም በሰባቱ የቤተክርስቲያን ዘመናት ውስጥ ከተነሱት ሁሉ እጅግ ታላቅ ክርስቲያን ሆነ፤ ደግሞም 29 በመቶ የሚሆኑትን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጻፈ፤ ይህም ሌሎቹ ጸሐፊዎች ሁሉ ከጻፉት በላይ ነው። ከዚያም በላይ ከእርሱ በኋላ ባሉት ዘመናት የተነሱ ታላላቅ ክርስቲያኖች ሁሉ ትምሕርታችን ትክክል ነው የሚሉ ከሆኑ የግድ ከጳውሎስ ጋር መስማማት ነበረባቸው።

ስለዚህ ከመጀመሪያው ታላቆቹ ክርስቲያኖች ማለትም ደቀመዛሙርቱ የቤተክርስቲያን መሪ የሚሆን ሰው ሲመርጡ ተሳስተዋል።
ለምን? እግዚአብሔር አስተሳሰቡ ከሰዎች የተለየ ስለሆነ።

ስለዚህ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አመራር ውስጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማያውቁ ሰዎች ሰው መሪ እንዲሆን ካልመረጥን ብለው ሙጭጭ ማለታቸው ነው። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከመካከላቸው ታላቅ መነኩሴ የነበረውን ማርቲን ሉተርን አወገዘችው። እርሱን በጭራሽም መሪያቸው እንዲሆን የመምረጥ ዝንባሌ አልነበራቸውም።

የመሪነትን ጉዳይ ለእግዚአብሔር መተው ያቅተናል። በሰው ሥርዓት ያደራጀናቸውን ቤተክርስቲያኖች ለመጠበቅ ብቻ እንተጋለን።

ለዚህ ነው ቤተክርስቲያን ስኬታማ ያልሆነችው፤ በስተመጨረሻ ደግሞ በሎዶቅያ ቤተክርስቲያን ዘመን እውነተኛው የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው ኢየሱስ ከቤተክርቲያን ውጭ ነው የቆመው። መቸም በቤተክርስቲያን ውስጥ ስላሉት መሪ ሰዎች የቤተክርስቲያን ራስ ነን ስለሚሉ ሰዎች ምን እንደሚያስብ መገመት አያቅተንም። እነዚህ መሪዎች እርሱን ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል አንቀበልም ያሉ ሰዎች ናቸው።

ሉቃስ 6፡14 እነርሱም፥ ጴጥሮስ ብሎ እንደ ገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብም ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥
15 ማቴዎስም ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥
16 የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው።

ይህ ለሁላችንም ማስጠንቀቂያ ነው። የቤተክርስቲያንን ታሪክ ያጎደፈው ትልቁ ከሃዲ የት ነበር? እዚያው በቤተክርስቲያን መሪዎች መካከል ነው የነበረው።

ለውድቀቱ ትልቅ መንስኤ ምን ነበረ? ገንዘብ።

ሃብታም የቤተክርስቲያን መሪዎች። በቤተክርስቲያኖች መካከል ይህ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ከሆነ ቆይቷል። በአንድ በኩል እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች በታማኝነት ስለማገልገላቸው መባረኩ መልካም ይመስላል። ነገር ግን በቤተክርስቲያኖች መካከል ከፍተኛ የሆነ የእምነት መለያየት በመኖሩ የትኞቹ ታማኝ መሪዎች መሆናቸውን ለመወሰን እንኳ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። በትምሕርታቸው የተለያዩ ቢሆኑም እንኳ ሁሉም እየለመለሙ ይመስላሉ። ግን ደግሞ ሌሎች ሐይማኖቶችም ሃብታም መሪዎች አሉዋቸው። ደግሞም እግዚአብሔር የለም የሚሉ ሃብታሞችም አሉ። ስለዚህ ሃብታም መሆን ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለመሆን ማረጋገጫ አይደለም።

ስንት ፓስተሮች ናቸው በጣም ውድ በሆኑ የቅንጦት ቤቶች ውስጥ የሚኖሩት? ስንት የቤተክርስቲያን መሪዎች ናቸው በጣም ውድ የቅንጦት መኪና የሚነዱት? በባንክ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ያከማቹ? ስንቶቹ ደግሞ ይህንን “የቤተሰብ ንግድ” አድርገው ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸው ከወንድሞቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር ረዳት ፓስተር፣ ረዳት አገልጋይ በሚል ሰበብ ትርፉን በቤተሰብ ውስጥ እንደሚከፋፈሉ ታውቃላችሁ? ገንዘቡ ከቤተሰብ እንዳይወጣ ማድረግ ነው ዋናው ዓላማቸው። “ቤተክርስቲያን” ትልቅ ንግድ ሆናለች።

ስለዚህ ባለፉት 2,000 ዓመታት ውስጥ የተለወጠ ነገር የለም። ኢየሱስ እጅግ የተቆጣበት አንድ ጊዜ መቅደሱ ውስጥ ገንዘብ ለዋጮችን ሲያገኝ ብቻ ነው። እነዚያ ሰዎች በሐይማኖት ሰበብ እየነገዱና ገንዘብ እያከማቹ ነበር። ዛሬ ደግሞ ሁሉ ነገር በታላቁ መከራ ሊጠፋ በቀረበበት ሰዓት ስንት ትልልቅ እጅግ ሃብታም ቤተክርስቲያኖች እንዳሉ ተመልከቱ።

ሉቃስ 6፡17 ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤
18 ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤
19 ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር።

ኢየሱስ በሰብዓዊነቱ ሰዎችን ከበሽታ፣ ከአጋንንት እስራት፣ እና ከልዩ ልዩ ደዌ ነጻ ለማውጣት ፈቃደኛ ነበረ።

እነዚህ ሁሉ አስፈላጊ ቢሆኑም ግን ለአጭር ጊዜ የሚሆኑ የጤና መፍትሄዎች ነበሩ። ፈውስ ማግኘት ትልቅ በረከት ቢሆንም በሥጋ ጤናማ መሆን ወደ መንግሥተ ሰማያት አያስገባንም።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ከሥጋ ፈውስም በሚበልጥ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመረ። ይህም እውነትን ማስተማር ነው። እውነትን ማስተማር የእግዚአብሔርን የረጅም ጊዜ እና የማዳን እና የዘላለማዊ ሕይወት እቅድ ስለሚያካትት ከሁሉም የሚበልጥ አገልግሎት ነው።

ከዚህ ቀጥሎ ኢየሱስ የተናገረው ነገር እኛ ሰዎች ለነገሮች ካለን አመለካከት የተለየ ነው።

ኢየሱስ በሰውነቱ ሲናገር እኛ ሰዎች የምንሰማው በጣም የተለየ እና ከእኛ አመለካከት ጋር አብሮ የማይሄድ ነገር ነው።

ሉቃስ 6፡20 እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።

ክርስቲያኖች ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ይጸልያሉ ሁልጊዜ ይጥራሉ። እግዚአብሔር ደግሞ ድሃ መሆን ይሻላል ይላል።

በዚህ ስብከት ውስጥ እግዚአብሔር ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ለድሆች ነው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ሃሳብ ከሃብታሞች ይልቅ ወደ ድሆች ነው። ሰዎች ያላቸው ገንዘብ ባነሰ ቁጥር ይበልት በእግዚአብሔር ላይ ይደገፋሉ፤ ከዚህም የተነሳ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የመውጣት ዝንባሌያቸው ዝቅተኛ ይሆናል። ለጊዜው ድሆች የዚህን ዓለም ገንዘብና ሃብታ ላያገኙ ይችላሉ፤ ደልቷቸው ላይኖሩ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለእነርሱ የረጅም ጊዜ እቅድ አለው። በስተመጨረሻ በመንግስተ ሰማያት ውስጥ ከሃብታሞች ይልቅ ብዙ ድሆች ይኖራሉ። ምክንያቱም ድሆች ድሃነታቸው የተሳሳተ ውሳኔ እንዳያደርጉ ይከለክላቸዋል።

ሉቃስ 6፡21 እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና።
ኢየሱስ ስቆ እንደሆነ የተጻፈ ቃል የለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም አጭር ጥቅስ ተብሎ የሚታወቀው “ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ” የሚለው ቃል ነው።

ይህም ቃል ምድራችን በመከራ፣ በጉስቁልና፣ እና በሐዘን የተሞላች ዓለም መሆኗን ይነግረናል።

ምግብ አስፈላጊ ነው፤ ግን ለጊዜው ብቻ ነው የሚያስፈልገው። በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከሆዳችን ይጠፋል፤ ወዲያው እንደገና መብላት ያስፈልገናል። የሚበሉት በቂ ምግብ ለሌላቸው እናዝናለን፤ ኢየሱስ እነርሱ ብጹአን ወይም የተባረኩ ናቸው ይላል። የእኛ አመለካከት ግን ከዚያ ይለያል። ስለዚህ አመለካከታችንን መቀየር ያስፈልገናል። በዚህ የምድር ሕይወት ውስጥ መከራን መቀበል ዓለማዊ ከሆነ ቁሳቁስ የመሰብሰብ አባዜ ነጻ አውጥቶን ስለ ሰማያዊ ነገር በትኩረት እንድናስብ ይረዳናል።

ስንስቅ ደስተኞች እንደሆንን ይመስለናል ግን ሳቅ የሚገልጠው ደስታ ብዙም ጥልቀት ያለው አይደለም። በግል ስኬት ስናገኝ ሳቅ በቀላሉ ሊመጣልን ይችላል፤ ነገር ግን ሳቅ በኪሳራ እና በአደጋ ጊዜ ሊመጣ አይችልም።

ግን እውነተኛ ደስታ ደግሞ አለ። እውነተኛው ደስታችንን የያዘው ጽዋ ከሃዘን የተሰራ ጽዋ ነው። ያለፍንበት ሃዘን በጣም ጥልቅ በሆነ መጠን ኋላ የምንቀበለውም ደስታ በዚያው መጠን ታላቅ ይሆናል። ሃዘን ባሕሪያችንን ይቀርጸዋል ምክንያቱም ሃዘን ከብዙ ሰዎች ፍላጎትና ችግር ጋር ቅርብ እንድንሆን ያደርገናል። ችግርና ሽንፈት ልክ እንደ ቀጥቃጭ መዶሻ ባሕርያችንን ቀጥቅጦ ትክክለኛ ቅርጽ ያስይዘዋል፤ ባሕርያችንን ያጠነክረዋል። ከዚያ በኋላ ሕይወትም ሆነ ሰይጣን አልፎ አልፎ የሚወረውሩብንን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም ብርቱ እንሆናለን።

ሉቃስ 6፡22 ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ።

መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቃችሁ የምትይዙ ከሆነ ቤተክርስቲያኖች አይፈልጓችሁም። ስሕተት መሆናችሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማሳየት ካቃታቸው ስማችሁን ያጠፋሉ፤ ሰው እንደማይፈልጋችሁ እንዲሰማችሁ ያደርጋሉ። አብረዋችሁ መሆን ይጠላሉ፤ ይገፉዋችኋል፤ ከዚያም ከቤተክርስቲያናቸው እንድትባረሩ ያደርጋሉ።

ሉቃስ 6፡23 እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና።

እንደዚህ ስትገፉ ደስ ይበላችሁ። በቤተክርስቲያኖች ዘንድ መልካም ስም ሲኖራችሁ ጥሩ አይደለም። የሆሳዕና እለት ለኢየሱስ የዘመሩና ያጨበጨቡለት ሰዎች እራሳቸው ናቸው በቀጣዩ አርብ ዕለት ደግሞ የሰቀሉት።

ይህንን አትርሱ። ከቤተክርስቲያን ስትባረሩ በዚህ በሰባተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ኢየሱስን ልታገኙ የምትችሉበት ብቸኛው መንገድ ነው። ምክንያቱም እርሱም ራሱ ከቤተክርስቲያን ውጭ ነው የቆመው።

ቀጣዮቹ ሶስት ቁጥሮች የብልጽግና ወንጌል የተመሰረተበትን ዋነኛ ምሰሶ ደህና አድርገው ያፈራርሱታል። በሰባተኛው ወይም በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን እግዚአብሔር በክርስቲያኖች ሃብታም የመሆን ጉጉት ላይ ጠንከር ያለ ወቀሳ ነው የሚሰነዝረው።

ራዕይ 3፡17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ … የምትል ስለ ሆንህ፥

ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ የሚፈልጉትና የሚጸልዩት ስለ ሃብት ነው።

ሉቃስ 6፡24 ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና።

የይሁዳ ውድቀት መንስኤ ምንድነው - - ገንዘብ። ሃብት ለምቾትና ለተድላ በር ይከፍታል። ይህም ከንቱነትን ብቻ ነው የሚያበዛው። ብዙ ብር በተጠቀምን ቁጥር የበለጠ ብዙ ብር እንፈልጋለን፤ በገንዘባችን በገዛነው ነገር የምናገኘውም ደስታ ይቀንሳል።

የዓለማችን ሃብታሞች ቢልየነሮች እነ አልፍረድ ክሩፕ፣ ጆን ሮክፌለር፣ እና አሪስቶትል ኦናሲሰ የሚተነፍሱት አየር ሳይቀር ገንዘብ ነበር፤ ነገር ግን ሕይታቸው ያበቃው ደስታ በሌለበት እጅግ አሳዛኝ በሆነ ብቸኝነት ነው።

ሉቃስ 6፡25 እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ።

ይህ ተደላድላ የምትኖት ቤተክርስቲያንን አወዳደቅ ያሳያል። የምበላው አለኝ፤ ደስተኛ ነኝ። ምን አይነት ርካሽና ራስ ወዳድ አስተሳሰብ ነው። ዓላማ የሌለው ሕይወት ራስን በማስደሰት ላይ ብቻ ያተኩራል።

ሉቃስ 6፡26 ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።

ዝነኛነትና በሕዝብ ተወዳጅነት። ሰዎች በሌሎች አስተያየትና በሌሎች ምስጋና ውስጥ የራሳቸውን ዋጋ ማግኘት ሲፈልጉ በጣም አሳዛኝ ምስኪኖች እየሆኑ ነው። ማሪዮ ላንዛ የተባለውን ታላቅ ኢጣሊያዊ ዘፋኝ፣ ሜሪሊን ሙንሮ የተባለችውን ታላቅ የፊልም ተዋናይ፣ ኤልቪስ ፕሬስሊ የተባለውን ታዋቂ የሮክ-ኤንድ-ሮል ዘፋኝ ያጠፋቸው የዝና ብዛት ነው። እነዚህ ሰዎች የነበራቸው የዝና ብዛት ያተረፈላቸው ሃዘን፣ ብቸኝነት፣ ተስፋ መቁረጥና ያለ ዕድሜ መሞት ብቻ ነው።

በዚህ ምድር ላይ አንድ ግራ የሚያጋባ ነገር ሰዎች ታዋቂ ለመሆን ብዙ ከለፉ በኋላ ታዋቂነትን ሲያገኙ ደግሞ ማንም እንዳያውቃቸው ጥቁር መነጽር ዓይቸው ላይ አድርገው መዞራቸው ነው።

ከዚህ ቀጥሎ ኢየሱስ ትኩረት የሰጠው ለቆራጥነትና ለሥነ ምግባራዊ ጥንካሬ ነው።

ዓለም እንደምትዋጋችሁ በዚያው መንገድ መልሳችሁ አትዋጉ። መሸነፍ ካስፈለገ ለመሸነፍ ዝግጁ ሁኑ።

እግዚአብሔር ለሕይወታችሁ ሃላፊነትን እስከወሰደ ድረስ በእናንተ ላይ የሚሆን ነገር ሁሉ ለምክንያት ነው የሚሆነው። ጠላቶቻችሁ የሚሰነዝሩባችሁ ጥቃት እንኳ ሳይቀር እግዚአብሔር ለሕይወታችሁ ያለው እቅድ አካል ነው።

ሉቃስ 6፡27 ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥
28 የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ።
29 ጕንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ስጠው፥ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን ደግሞ አትከልክለው።

ጎልያድ ሰይፍ ይዞ በመጣበት ጊዜ ዳዊት ወንጭፍ ይዞ ነው የገጠመው። ጠላትህን ስትዋጋ ጠላትህ የያዘውን አይነት መሳሪያ አትጠቀም።

ጠላትህ ከሚያደርገው ተቃራኒውን አድርግ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግን ማንም አይጠብቅም። ጠላትህ ቢጠላህ ውደደው። ጠላትህ ቢረግምህ ጸልይለት። ቢመታህ መልሰህ አትምታው። አንድ ነገር ቢሰርቅብህ ሌላም ጨምረህ ስጠው። እግዚአብሔር ስለተሰረቀብህ እቃ ብሎ ምንም አይሸልምህም፤ ግን እቃ በተሰረቀብህ ጊዜ ተጨማሪ አውጥተህ በመስጠትህ በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ ነጥብ ታስቆጥራለህ።

እግዚአብሔርን የሚገርመው መስጠት እንጂ መቀበል አይደለም።

ይህ ግን ከሰዎች አስተሳሰብ ጋር አይገጥምም። ይህንን ልታደርጉ የምትችሉት እግዚአብሔር በውስጣችሁ ካለ ብቻ ነው። እነደዚህ አይነቱ ጠንካራ ፈተና ብቻ ነው እግዚአብሔር በውስጣችን መኖሩን ወይም አለመኖሩን የሚገልጠው። የሞተ ሰው ቢደበድቡትም ተነስቶ አይደባደብም። ስለዚህ ሲመቱን መልሰን የምንማታ ከሆነ ለእኔነት አልሞትንም ማለት ነው።

ሉቃስ 6፡30 ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፥ ገንዘብህንም የሚወስድ እንዲመልስ አትጠይቀው።

31 ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።

ለሰዎች ለመስጠት ዝግጁ ሁኑ። ከዚያ በኋላ ለሰዎች የምትሰጡት ነገር ስላላችሁ እግዚአብሔርን ታመሰግናላችሁ።

ሰዎች ንብረታችሁን ቢወስዱ መልሳችሁ ላለመጠየቅ ዝግጁ ሁኑ። መጀመሪያውኑም የእናንተ ንብረት አልበረም። ሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ነው። ንብረት በሙሉ እግዚአብሔር ለጊዜው ለእናንተ ያዋሳችሁ እንጂ ባለንብረት እንድትሆኑ ሰጥቷችሁ አይደለም።

ንብረት ከእጃችሁ ሲወጣ አለመደናገጥ አለማዘን የእወነትም ለእኔነት የመሞታችሁ መፈተኛ ማጣሪያ ነው። እውነቱ ቢገለጥ ከሚያስፈልገን ወይም ልንጠቀም ከምንችለው በላይ ነው በእጃችን ያለው። ስለዚህ ካለን ላይ ስንቀንስ ይሻለናል። በእጃችን ላይ ያለውን ስንቀንሰው የቀረውን በብቃት የመጠቀም አቅም ይኖረናል።

ወርቃማው ሕግ ለራስህ እንዲደረግልህ እንደምትፈልገው ለሌሎች ማድረግ ነው።

መልካም ለሚያደርጉልህ ሰዎች መልካም ማድረግ ምንም ትርጉም የለውም።

ሉቃስ 6፡32 የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና።
33 መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና።
የሚንከባከቡህን ሰዎች መንከባከብ ከፈተና አይቆጠርም።

ክፉ ለሚያደርጉብህ ሰዎች መልካም ልታደርግላቸው ትችላለህን? ሰው ትክክለኛ ባሕርዩ መሆን ያለበት ልክ እንደዚህ ነው።

ሉቃስ 6፡34 እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ።

ሰዎችን የምንረዳቸው እነርሱ ደግሞ ኋላ እንዲረዱን ብለን ከሆነ ልክ እንደ ዓለማውያን እየሆንን ነው።

ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ አንዳችም ነጥብ አያስቆጥርልንም፤ ምክንያቱም በዓለም ያሉ ሰዎችም ይህንኑ ያደርጋሉ። እንዲህ ማድረግ ዋነኛ ዓላማ የግል ጥቅምን ለማስጠበቅ ነው።

ከዚህ ቀጥሎ ያለው ሃሳብ ለሰዎች ለመቀበል በጣም የሚከብድ ፍልስፍና ነው፡-

ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም ሁኑላቸው። ተመልሶ እንዲከፈላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ። የሚደርስባችሁን በደል ሁሉ ይቅር በሉ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለአንድ ምክንያት ብሎ ነው እንዲደርስባችሁ የፈቀደው። ምሕረት ለማይገባቸው ምሕረት አድርጉ።

ከሰው ጋር በሃሳብ ላትስማሙ ትችላላችሁ ግን በሰውየው ላይ አትፍረዱበት። ሰዎች ያደረጉት ማናቸውም ነገር እግዚአብሔር እንዲያደርጉ ፈቅዶ ነው። እኛን ይበልጥ ለማጠንከር እግዚአብሔር እነርሱን እየተጠቀመባቸው ነው። ማደግ ካለብን ተቃዋሚ ያስፈልገናል።

ሁል ጊዜ ደግ ሁኑ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የተባረከ ነው።

ሉቃስ 6፡35 ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥

የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና።

ሉቃስ 6፡36 አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ።

ሰዎች ክፉ ሆውብህ አንተ ግን መልካም ከሆንክላቸው ይህ የተለመደ የሰው ባሕርይ አይደለም፤ ስለዚህ ሕይወትህን እየመራ ያለው እግዚአብሔር መሆኑን ያሳያል። ሰዎች በቀል ይወዳሉ፤ እግዚአብሔር ግን ምሕረት ማድረግን ይወዳል።

ሉቃስ 6፡37 አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ።
ሉቃስ 6፡38 ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።

በሰዎች ላይ አትፍረድ፤ ምክንያቱም ኋላ ሊለወጡ ይችላሉ። ደግሞም ሰዎች ላደረጉት ክፉ ነገር ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አናውቅም። እኛን ለመቅረጽ እግዚአብሔር እየተጠቀመባቸው ሊሆን ይችላል። ወይ ደግሞ እነዚህ ክስተቶች በእግዚአብሔር ትልቅ እቅድ ውስጥ ለሆነ ምክንያት መፈጸም በሚገባቸው ሰዓት ላይ ተገኝተን ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በሐጥያተኛው አትፍረድበት፤ ይልቁን ይቅር ለማለት ተዘጋጅ። ደግሞ እኛ ራሳችን ፍጹም አለመሆናችንን ይቅርታም እንደሚያስፈልገን አስቡ።

ሁልጊዜ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ከዚያ እግዚአብሔር ስጦታዎቹን ለሌሎች ለማዳረስ እናንተን እንደ ማስተላለፊያ ይጠቀማችኋል።

ሉቃስ 6፡39 ምሳሌም አላቸው፦ ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን?

የሰዎችን ምክር ለመከተል አትቸኩሉ። ዛሬ የሚከሰቱ ነገሮች እጅግ ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ ትክክለኛውን ምላሽ መስጠት ቀላል አይደለም።

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መከተል አለብን። ዛሬ በዚህ ዘመን ለምንኖር ሰዎች ጉድጓዱ ከፊታችን የሚመጣው ታላቁ መከራ ነው።

ሉቃስ 6፡40 ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል።

ኢየሱስ ጌታ ሆኖ ሳለ በብዙ መከራ እና እንግልት ውስጥ አልፏል። እኛ ከእርሱ አንበልጥም፤ ስለዚህ እርሱ ስለእኛ ብሎ ካለበት መከራ የምናመልጥበት ምንም መብት የለንም።

ሉቃስ 6፡41 በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?
42 በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን፦ ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።

የራሳችን ድክመትና ጥፋት በሌሎች ሰዎች ውስጥ እንደ መስተዋት ተንጸባርቆ እናያለን። እኛ ራሳችን ስሕተት አድርገን ስሕተታችንን እየደበቅን ሌሎች እሱኑ ስሕተት ሲሰሩ ግን ደስ ብሎን እናጋልጣቸዋለን። በናንተ ላይ አንድ ጣቴን ስጠቁም ሦስት ጣቶቼ ደግሞ እኔው ላይ መልሰው ይጠቁማል።

ሉቃስ 6፡43 ክፉ ፍሬ የሚያደርግ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያደርግ ክፉ ዛፍ የለም።

ሌሎች ሰዎችን መተቸት፣ መንቀፍ፣ እና በሌሎች ላይ መፍረድ ነገር ግን ራስን ደግሞ ማጽደቅ መራራ ፍሬ ነው። እኔ ስለ ራሴ እንደምናገረው ያህል መልካም ከሆንኩ ሌሎችን ክፉዎች ብዬ መንቀፍ የለብኝም።

ሉቃስ 6፡44 ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም።

45 በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል።

ኮሉምባ የተባለው አየርላንዳዊው ሚስዮናዊ ወንጌል ሰባኪ ሁልጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተጻፈው እውነት ትኩረት ይሰጥ ነበር።

ትክክል የሆነውን ነገር ለሰዎች መንገር አስፈላጊ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ተነስተን ከነገርናቸው ብዙ ልንሳሳት አንችልም። ነገር ግን ለሰዎች ሰው ሰራሽ ትምሕርቶችን መንገር የክፋት ሥራ ነው።

ሉቃስ 6፡46 ስለ ምን፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም?

ክርስቲያን ሁሉ ኢየሱስን “ጌታ” ይለዋል። ነገር ግን ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተናገረውን የማይታዘዙ ከሆነ እርሱን ጌታ ብሎ መጥራት ምንም ትርጉም የለውም። “ጌታ” ማለት “ዋነኛ አዛዥ” ነው፤ እርሱንም ሰዎች ያለ አንዳች ጥያቄ ሊታዘዙት ይገባል።

ሉቃስ 6፡47 ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ።
48 ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም።

እምነታችሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መስርቱ። ከዚያ በኋላ ምንም የምትጸጸቱበት ነገር አይኖርም። የተቃውሞ ጎርፍ ቢመጣ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሊነቀንቀው አይችልም። የዓለም ሁኔታ እንዴትም ቢለዋወጥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በፍጹም አይለወጥም። ዘላለማዊ እውነት ስለሆነ ለውጥ እና ማሻሻያዎች አያስፈልጉትም።

ሉቃስ 6፡49 ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።

ብዙ ሳይንቲስቶች እግዚአብሔር የለም ብለው ያምናሉ። የምናየው ዓለም ያለ እግዚአብሔር ኃይል እንዲሁ የመጣ ነው ብለው ለማስረዳት እስታንዳርድ ሞዴል ኦቭ ፊዚክስ (Standard Model of Physics) እና ቢግ ባንግ (Big Bang) የተባሉ ንድፈ ሃሳቦችን አዘጋጅተዋል።

ሃሳባቸው ድንቅ ሃሳብ ነበር ግን ዳርክ ኤነርጂ እና ዳርክ ማተር የሚባል ነገር ባገኙ ጊዜ ይህም ደግሞ የዓለምን 96 በመቶ የሚሸፍን እና የማይታይ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ሃሳባቸው ውድቅ ሆነ። ይህ ዳርክ ነገር ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚሰራ፣ ወይም ከየት እንደሚመጣ አንዳችም አያውቁም። ስለዚህ ያዘጋጁት እስታንዳርድ ሞዴል ወዲያ መግለጽ የሚችለው የዓለማችንን 4 በመቶ ብቻ ሆነ፤ እርሱም አሳማኝ አይደለም። የሚታየውን ዓለምበመጀመሪያዎች ሦስት ደቂቃዎች ውስጥ 98 በመቶ የፈጠረው ቢግ ባንግ ነው አሉ (ነገር ግን የሚታየው ከዓለም ውስጥ 4 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው)። ነገር ግን ይህ የቢግ ባንግ ንድፈ ሃሳባቸው በዓለማች ውስጥ ስላለው 96 በመቶ ስለሚሆነው የማይታይ ክፍል አንዳችም ማብራሪያ የለውም።

ስለዚህ ተራቀቅን ብለው ያመጡት የቢግ ባንግ ንድፈ ሃሳብ ውድቅ ሆኖ ቀርቷል፤ ይህንንም ንድፈ ሃሳብ ያፈለቁት እነ አላን ጉት እና የኖቤል ሽልማት አሸናፊው እስቲቨን ዋይንበርግ ድሮ ያስፋፉት ከነበረው ንድፈ ሃሳባቸው ርቀው ተቀምጠዋል።

ታላላቅ የፊዚክስ ጠበብቶች ለየት ያለ መልስ ለማግኘት መከራቸውን እየበሉ ነው፤ ነገር ግን ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ አንዳችም በሙከራ ሊረጋገጥ የሚችል ፊዚክስ ሕግ ማስረጃ አላገኙም። (ሂግስ የተባለ ሰው በ2013 ያገኛቸው ቦሶን የተባሉ ቅንጣቶች አስቀድሞ በ1960ዎቹ የተሰጡ መላምቶችን የሚያረጋግጡ ነበሩ።) የሳይንስ መሰረቶች ሁልጊዜ በነፋስ ቅርጻቸውን እንደሚለውጡ የአሸዋ ክምር እንጂ እንደማይናወጡ ዓለቶች አይደሉም። ምክንያቱም አዳዲስ ግኝቶች በመጡ ጊዜ ቀድመው የነበሩ ታላላቅ ሃሳቦች ሁል ጊዜ ይሻራሉ። ሳይንቲስቶች አዲስ እስትሪንግ የተባለ ንድፈ ሃሳብ ላይ ሙከራ እያደረጉ ናቸው ግን ምን እንደሆነ እንኳ አያውቁም፤ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥም አንዳች ሙከራ ማድረግ አይችሉም። ስለዚህ ይኸኛው ንድፈ ሃሳባቸው ብዙ “ምናልባቶችን” ብቻ የሚያሰፍሩበት ሃሳብ ሆኖ ቀርቷል።

በአሁኑ ጊዜ ከዓለማችን 96 በመቶ የሚሆነው ክፍል ከዓይናችን የተሰወረ መሆኑ ስለታወቀ ሳይን ዓለማችን ምን ዓይነት እንደሆነ ሊያብራራልን አይችልም። እስታንዳርድ ሞዴሉ ዳርክ ኤነርጂ ወይም ዳርክ ማተር የሚባለው ነገር ይገኛል ብሎ አልጠበቀም ነበር።

ስለዚህ እግዚአብሔር መኖሩን የሚክዱ ሳይንቲስቶች የዓለማችንን አጀማመር ለማብራራት አቅም የላቸውም። ዓለማችን እንዴት እንደተጀመረች የሚገልጥ ንድፈ ሃሳብ የላቸውም። እሱን ይቅርና ስለ ዓለማችን ምንነት እንኳ መግለጽ አቅቷቸዋል።

እውነትን ለማወቅ እግዚአብሔር የለም በሚሉ ሳይንቲስቶች ላይ የምትደገፉ ከሆነ እነርሱ ራሳቸው ምንም እንደማያውቁ የሰማችሁ ቀን በጣም ታዝናላችሁ። በብዙ ጥረት ያመጡዋቸው ንድፈ ሃሳቦችም ከዓለማችን እጅግ ጥቂቱን ክፍል እንኳ ለመግለጽ የሚበቁ አይደሉም።