ኢየሱስ እንደ ፍጹም ሰው - በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2



ግብር ለመክፈል በግዴታ ሩቅ መንገድ ሄደው ከዚያ የሚያድሩበት ቦታ አጡ። በሚሸት ግርግም ውስጥ ተወልዶ የመጀመሪያ ጎብኚዎቹ ላብ ላብ የሚሸቱ እረኞች ናቸው።

First published on the 29th of March 2020 — Last updated on the 5th of November 2022

ሉቃስ ኢየሱስን እንደ ፍጹም ሰው ሊያቀርብ ፈልጓል። ስለዚህ ሉቃስ ከሰው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በትኩረት ይጠቅሳል።

የሰውን ሃሳብ ከሚቆጣጠሩ ትልልቅ ጉዳዮች ዋነኛው ሃብት ነው፤ ሃብት ደግሞ በሰዎች መካከል እኩል አልተከፋፈለም። በ2015 አሜሪካ የዓለምን ሃብር 42 በመቶውን መያዟ ተረጋግጧል፤ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቻይና ደግሞ 11 በመቶውን የዓለም ሃብት ይዛለች። አሥሩ የበለጸጉ ሃገሮች በአንድነት የዓለምን 84 በመቶ ሃብት ተቆጣጥረዋል። በዓለም ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ሃገሮች አሉ።

የመጨረሻ ድሃ የሆኑት 40 ሃገሮች በአንድነት ሃብታቸው ሲደመር 1 በመቶ ብቻ ነው።

ስለዚህ 150 ሃገሮች የዓለምን 15 በመቶ የሚሆን ሃብት ተከፋፍለው ነው የሚጠቀሙት፤ ከዚህ የተነሳ እያንዳንዳቸው የ1 በመቶ አንድ አሥረኛ ይደርሳቸዋል።

ሃብታም በሆነችዋ አሜሪካ ውስጥ ከሕዝቡ 80 በመቶ የሚሆኑት በእጃቸው ያለው የሃገሪቱ 15 በመቶ ሃብት ብቻ ነው። ድሆች የሃገሪቱን ሃብት በሙሉ በተቆጣጠሩትና በድሆች ላይ ማዘዝ በሚችሉት ጥቂት ሃብታሞች አይደነቁም። የ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 7000 ሚሊዮን ዶላር ፈጅቷል። ድሃ ሰው በእንደዚህ አይነት ምርጫ ውስጥ ተወዳድሮ ማሸነፍ አይችልም።

በምድር ላይ ሁል ጊዜ የማይቋረጥ ችግር በጥቂቶች እጅ ብዙ ሃብት በመከማቸቱ የተነሳ የሚፈጠረው ኢፍትሃዊነትና የብዙ ሰዎች ከቦታቸው መፈናቀል ነው።

ሉቃስ በሕዝቡ መካከል ብዙሃን ለሆኑት ለድሆች በቀጥታ ነው የሚናገረው። ኢየሱስ ለድሆች የቆመ ሰው ነው። ኢየሱስን ያሳደገው ዮሴፍ እና ማርያም በሕዝብ መካከል ታዋቂ ሰዎች አልነበሩም። ዮሴፍና ማርያም ሐይማኖተኛ ቢሆኑም እንኳ መሲሁ በቤተልሔም እንደሚወለድ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ስለዚህ እግዚአብሔር አውግስጦስ ቄሳር የተባለውን የሮማ ገዥ አዲስ የግብር አዋጅ እንዲያወጣ በማድረግ ዮሴፍን እና ማርያምን ወደ ቤተልሔም እየነዳ አደረሳቸው።

ሉቃስ 2፡1 በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች።

ድሃ የነበረው ዮሴፍ ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም ለመድረስ 140 ኪሎ ሜትር ሄደ። ሕጻኑ ሊወለድ አንድ ሳምንት ስለቀረው ሚስቱ እርግዝናው በጣም ከብዷት ነበር። እርሷም በአህያ ተቀምጣ ሄደች ግን በአህያ ተቀምጦ መሄድ ምቹ አይደለም። ደግሞም በአህያ መሄድ አያፈጥንም። ከናዝሬት እስከ ቤተልሔም ጉዞው አንድ ሳምነት ይፈጃል። ሕጻኑ ሳይወለድ በፊት ቤተልሔም መድረስ ይችላሉ? መንገዳቸውን ሁሉ እየሄዱ ይህ ሃሳብ ያስጨንቃቸው ነበር። ስለዚህ ይህ ጊዜ ለማርያም መንገድ ለመሄድ ምቹ ጊዜ አልነበረም። አህያው የሚሸከመው ማርያምን ብቻ ሳይሆን የአንድ ሳምንት ምግብ፣ በመንገድ ዳር መሽቶባቸው ሲነኙ የሚለብሱትን ብርድ ልብስ፣ እና የዮሴፍን የአናጺ እቃዎች ሁሉ ነበር (ከሁለት ዓመት በኋላ ሰብዓ ሰገል ወደ ቤተልሔም ሲመጡ ቤተሰቡ እዚያው ነበር፤ ዮሴፍም እነርሱን ለማስተዳደር በአናጺነት ይሰራ ነበር)። ለሕጻን ልብስና ለሕጻን መኝታ የሚሆን ቦታ አልነበረም።

ለምንድነው ይህን አስቸጋሪ መንገድ የሚሄዱት? ግብር ለመክፈል ነው።

ከዚህ የከፋ ምክንያት ለማሰብ እንኳ ያዳግታል። ሁላችንም ግብር መክፈል ያስጠላናል።

ማርያም ምጥ ሊመጣባት ጊዜው እየተቃረበ ስለሆነ በቀስታ መሄድ አለባቸው። ፈጠን ብለው የሚሄዱ ሰዎች ስለሚቀድሟቸው እነርሱ ቤተልሔም ሲደርሱ ማደሪያ ቦታዎችና ሆቴሎች በሙሉ ቅድሚያ ተይዘው ያልቃሉ።

እነርሱ ግን ሲደርሱ በረት ውስጥ ንጽሕና በሌለው በሚሸት ቦታ ማረፊያ ያገኛሉ።

በረቶች በእንስሳት ፋንድያ ምክንያት የሚቆሽሹ ቦታዎች ናቸው። ሽታቸውም ደስ አይልም። ሕጻኑ ተወለደ።

ለሕጻኑ የተገኘለት መኝታ በሬዎችና ላሞች ምግባቸውን ሲበሉበት በለሃጫቸውና ምራቃቸው ያረጠቡት ግርግም ነው። በሕይወቱ መጨረሻ ላይም ሰዎች ምራቃቸውን ይተፉበታል። ለምን? እርሱ የሕይወት እንጀራ ነው። እንጀራን ሳናኝከውና በምራቃችን ሳናርሰው ልንበላው አንችልም።

ሉቃስ 2፡7 የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው።

ማረፊያ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ማንም አልፈለጋቸውም። ኢየሱስ በሕይወቱ መጀመሪያ ከአይሁድ ሐይማኖተኛ ማሕበረሰብ ውጭ ነበር። በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመንም ከክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን በር ውጭ ነው የሚቆመው።

ሕጻኑ የተጠቀለለበት መጠቅለያ ጨርቅ አሮጌ ጆንያ ነበር። በበረት ውስጥ ሊገኝ የሚችለው ብቸኛ የጨርቅ አይነት ቀምበር የበሬዎችን አንገት እንዳያቆስል ተብሎ በቀምበሩ ዙርያ የሚጠቀለለው ጆንያ ብቻ ነው። በሬዎች እርሻ ሲያርሱ አድካሚ ሥራ ስለሚሰሩ ያልባቸዋል። ከእንጨት በተሰራው ቀምበር ላይ የሚጠመጠመው ጆንያ በበሬዎቹ ላብ ተነክሮ ይበሰብሳል። ስለዚህ ኢየሱስ በላብ በተጠመቀ ጨርቅ ነው የተጠቀለለው። ድሃ እረኞች እየሮጡ ወደ በረቱ “ፈጥነው ስለመጡ” እነርሱም ራሳቸው ቆሽሸውና ላብ በላብ ሆነው ነው የደረሱት። ስለዚህ እርሱም ራሱ በላብ በተነከረ ጨርቅ ተጠቅለሎ የከብቶች ሽታ ባለበት በረት ውስጥ ስላገኙት እረኞቹ በፊቱ መቅረብ አልከበዳቸውም። ኢየሱስ ከመጀመሪያው በጣም ዝቅ ብሎ በመምጣቱ ድሆች ወደ እርሱ ለመቅረብ እንዳይከብዳቸው አድርጓል። የማንም ሕጻን ልክ ከዚህ በባሰ ዝቅ ያለ ቦታ አልተወለደም።

በሕይወቱ መጨረሻም ላብ ያልበዋል። ያውም የደም ላብ ነው የሚያልበው። ለምን? አዳም ሐጥያት በሰራ ጊዜ የተወሰነበት ቅጣት ላቡን አንጠፍጥፎ እንጀራ እንዲበላ ነበር። ስለዚህ የሰው ላብ የኢየሱስን ደም በመንካቱ ሰው ከዚህ ቅጣት ስለሚዋጅ አንድ ቀን በአዲሲቱ ምድር ውስጥ ሰዎች መኖር ሲጀምሩ ላብ እያንጠፈጠፉ የሚደክሙበት ሥራ አይኖራቸውም።

ሉቃስ በመልእክቱ ውስጥ እግዚአብሔር እኛ ሰዎች እንደምናስበው እንደማያስብ ግልጽ አድርጎ ያሳያል። ለዚህ ነው እግዚአብሔር በሐይማኖታዊ ልማዶቻችን የማይገረመው።

በሰው ታሪክ ውስጥ ለአንዴ እና ለመጀመሪያ ጊዜ የመላእክት ሰራዊት በምድር ላይ ተገልጠው ለእግዚአብሔር ታላቅ ክብርና ምስጋና አቀረቡ።

ይህ የሆነው የት ነው? በሮማ ግዛት ጥግ ፓለስታይን በሚባለው አካባቢ ነው። ከፓለስታይን ውስጥ ደግሞ የት? በትክክል የትጋ እንደሆነ አይታወቅም። ግን ቤተልሔም ከምትባል ታናሽ ከተማ አካባቢ የሚቀርብ አንድ ትንሽ ሜዳ ላይ ነበር።

የዚሕ ታላቅ ሰማያዊ ክብር የተገለጠበት የምስጋና ድግስ ተጋባዦችን እነማን ነበሩ?

ማንም የማያውቃቸው፣ ያልተማሩ፣ ጥቂት ድሃ እረኞች ናቸው። ከቤት ውጭ ሜዳ ላይ ስለሚውሉ ብዙም ጊዜ ገላቸውን አይታጠቡም። እነርሱ ራሳቸው በግ በግ ነበር የሚሸቱት። ከእነርሱ አንዳቸው እንኳ ማን እንደነበሩ አናውቅም። ስማቸው ለመጠቀስ እንኳ የሚበቃ አልነበረም፤ ማንም የሚያውቃቸው ሰው ስላልነበረ ስማቸው ቢጠቀስም እንኳ ማንም አያስታውሳቸውም። ያ ታላቅ የሰማይ ክብር በተገለጠ ጊዜ ታላቅ ፍርሃት ወደቀባቸው።

ስለዚህ ሉቃስ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ሲገለጥ ምን እንደሚመስል ያሳየናል። እግዚአብሔር ይህንን የሚያሳየን ፍጹም ባልተጠበቀ መንገድ ነው። እግዚአብሔር ዋኖቹን ሰዎች (በመቅደስ እና ምኩራብ ውስጥ የነበሩትን ሐይማኖተኛ አይሁዶች) ትቶ በአስደናቂ ክብርና ግርማ የተገለጠው ማንም ከቁም ነገር ለማይቆጥራቸው ድሃና ምንም አቅም የሌላቸው ገንዘብም ለሌላቸው ሰዎች ነው። በጣም ድሃ ከመሆናቸው የተነሳ ስጦታ ገዝተው የማምጣት አቅም እንኳ አልነበራቸውም፤ እነርሱ ራሳቸው ከከብት ጋር ይውሉ ስለነበረ በበረቱ ውስጥ የነበረው ቆሻሻ እና ሽታ አላስጨነቃቸውም። እግዚአብሔር የሰውን ሥጋ ልብሶ ፍጹም ባልተጠበቀ ትሕትና ራሱን በጣም ዝቅ አድርጎ ሰው የናቃቸው ሰዎች እና ድሆች ብቻ ሊገነዘቡት በሚችል መንገድ መጣ።

ሰይጣን ሙሉ በሙሉ ተታለለ። ስለዚህ በአንድ ታንሽ በረት እና ማንም የማያውቃቸው ዋጋ ቢስ ድሃ እረኞች ላይ ጊዜ ማጥፋት አይጠቅምም ብሎ አሰበ። በሰይጣን አስተሳሰብ እንደ ዮሴፍና ማርያም ያሉ ሁለት ማንም የማያውቃቸው ሰዎች በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ ትልቅ ቦታ አይኖራቸውም። ለሰይጣን እንደመሰለው ሰዎቹ ወደ ቤተልሔም ረጅም መንገድ አቋርጠው መሄዳቸው ከመሲሁ መምጣት ጋር የተያያዘ አልነበረም። መሲሁ ሲመጣ መቅደሱ ውስጥ ወዳሉት ታላላቅ የሐይማኖት መሪዎች ነው የሚመጣው፤ አመጣጡም በታላቅ ድግስና ግርግር የታጀበ ይሆናል። የዛኔ ሰይጣን የአጋንንት ሰራዊቱን አሰልፎ መሲሁን ሊዋጋ መውጣት ይችላል። የእግዚአብሔር ሃሳብ በታላቅ ትሕትና እና ማሕበረሰቡ ከቁም ነገር በማይቆጥራቸው ምስኪን ሰዎች አማካኝነት በመፈጸሙ ሰይጣን ሙሉ በሙሉ ተሸውዷል።

በምድር ከተወለዱ ሕጻናት ሁሉ ታላቅ የሆነው ሕጻን ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ በበረት ውስጥ ሊያዩት የመጡት ከሰው ሁሉ ዝቅ ያሉ ዋጋ የሌላቸው ዜሮ ሰዎች ነበሩ።

በኮምፒውተርና በሞባይል የታገዘው የዲጂታል ኢንፎርሜሽን ዘመን ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። ይህ ዲጂታል ዘመን የሚሰራው በሁለት ቁጥሮች አማካኝነት ነው፤ እነርሱም አንድ እና ዜሮ ናቸው።

የኢየሱስ፣ ማለትም ለእኛ የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ኢንፎርሜሽን ሁሉ የያዘው የእግዚአብሔር ቃል መወለድ ዓለምን ለውጧታል። እርሱ አንድ ቁጥር ነው። ስለዚህ እርሱ በተወለደበት ሰዓት የመጡት ሁሉ ዜሮዎች ነበሩ።
በኢየሱስ እና በሰዎች መካከል የነበረውን ሰብዓዊ ሕብረት ሉቃስ ትኩረት ሰጥቶበት ሰው የሆነው ኢየስ 1 ሌሎቻችን ሰዎች ሁሉ ደግሞ 0 እንደሆንን አሳይቷል።

መጽሐፍ ቅዱስ 0 ያለውን በዙርያችን ያለው ዓለም (እኔነት፣ የቤተክርስቲያን ልማዶች፣ የቤተክርስቲያናችን መሪ፣ ቤተሰባችን፣ ባሕላችን፣ ገንዘብ፣ ዝና፣ ሴቶች) 1 ብለን እንድንጠራ ይፈልጋሉ።

የዚህ ዘመን ሕዝብ፣ ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎችን ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸው ምን ያህል ዝቅተኛ መሆኑን ልብ በሉ።

ሉቃስ 2፡8 በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ።
9 እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ።

ሉቃስ 2፡13 ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦
14 ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።

ሉቃስ ጥበበኞቹን (ሰብዓ ሰገልን) ጭረሽም አይጠቅሳቸውም። እነርሱ ሁለት ዓመት ዘግይተው ነው የመጡት፤ ሲደርሱም ኢየሱስ የሁለት ዓመት ልጅ እንጂ አራስ አልነበረም። ሰብዓ ሰገል ወደ ቤት ነው የገቡት እንጂ ወደ በረት አልነበረም። ሲመጡም ኢየሱስ እና ማርያም ነበሩ፤ ዮሴፍ ግን አልነበረም።

ማቴዎስ 2፡11 ወደ ቤትም ገብተው (ሰብዓ ሰገል) ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥

ጥበበኞቹ ሰብዓ ሰገል የከብት ፋንድያ ያለበት በረት ውስጥ ቢመጡ ኖሮ አይመቻቸውም ነበር። ላብ ላብ የሚሸቱ እረኞች ግን በረት ለእነርሱ እንደ ቤት ነው። ምክንያቱም እነርሱ የከብት ሽታ ለምደዋል።

ስለዚህ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ሲመጣ የምድር ኑሮውን እጅግ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ሁኔታ ጀመረ። ከዚህም የተነሳ ከሕዝብ ሁሉ ከፍተኛውን ቁጥር ለሚወክሉት ድሆች ቅርብ ሆነ።

ሉቃስ አስራ ሁለት ዓመት ሲሞላው ወደ ቤተመቅደስ እንደሄደ ሉቃስ ጠቅሷል። ካሕናቱም በእውቀቱ ተደነቁ።

ዮሴፍና ማርያም ትተውት ሄደው ሦስት ቀን ካለፈ በኋላ እርሱን ፍለጋ ወደ ቤተመቅደስ ተመልሰው መጡ።

ሉቃስ 2፡48 ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም፦ ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው።
49 እርሱም፦ ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው።

ማርያም በድንግልና መውለዷን ሊያምኑ በማይችሉ የአይሁድ ምሁራን መካከል በተገኘች ጊዜ ፈርቷ ዮሴፍን የኢየሱስ አባት አለች።

ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ በጥበብ ሆኖ ግን ስሕተትን የሚያርም እና ጥልቅ የሆነ መረዳትን የሚያካፍል ነበር።

“ስለምን ፈለጋችሁኝ?” ይህ ለስለስ ያለ ተግሳጽ ነው። ቢፈልግ እንዲህ ብሎ መቆጣት ይችል ነበር፡- “የፈለጋችሁኝማ መጀመሪያ ከእናንተ ጋር መኖር አለመኖሬን ለማረጋገጥ እንኳ ስለሰነፋችሁ ነው። ይህ የጥሩ ወላጆች ባህርይ አይደልም።”

እኛ ከዚህ ስለራሳችን የምናየው ነገር የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት በቀላሉ ረስተን ትተነው ኑሮዋችን ውስጥ እንደምንጠመድ ነው።

“በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” የተጠቀመበት ጥበብ ያስደንቃል። “ለምን እነዚህ ሰዎች ፈርታችሁ ያለ ወንድ ዘር መወለዴን ትክዳላችሁ?” ማለት ይችል ነበር።

የተናገረው በሌላ አነጋገር ዮሴፍ አባቱ ቢሆን ኖሮ በዮሴፍ የሥራ ቦታ ሆኖ በአናጺነት ይሰራ ነበር ማለት ነው። ነገር ግን አባቱ እግዚአብሔር ከሆነ የእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሆኖ ከካሕናት እና ከምሁራኑ ጋር ይነጋገራል ማለት ነው።

ሦስት ቀን ሙሉ መቅደሱ ውስጥ ስለቆየ ኢየሱስ በአባቱ ቤት መቆየቱን አውቋል። ስለዚህ በነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ እውነተኛ አባቱ ያልሆነው ዮሴፍ እንደተወው እውነተኛ አባቱ የሆነው እግዚአብሔር ግን አልተወውም።

በዚህ መንገድ ታላላቅ ሰዎች ባሉበት ንግግሩን የማያምኑ ሰዎች ባሉበት ኢየሱስ ያለ ወንድ ዘር መወለዱን በግልጽ መሰከረ። የእነርሱ ሊያስነሱ የሚችሉት ተቃውሞ እና አለማመን ነው ማርያም እውነቱን እንድትደብቅ ያደረጋት።

ስለዚህ የቤተክርስቲያን መሪዎች አጥብቀው ለሚቃወሙዋቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶች ሳንፈራ መመስከር እንዳለብን ከዚህ እንማራለን። ነገር ግን እነርሱ መስማት የማይፈልጉትን ልንነግራቸው የሚበቃ ድፍረት ይኖረናል?
ኢየሱስ በታላቅ ጥንቃቄ በሰጠው ምላሽ የማርያምን ስሕተት እያረመ እንደሆነ ሳያስታውቅበት ስሕተቷን አረመ።

ይህን ያህል ነበር ለማርያም አክብሮት የነበረው። ይህም ወላጆቻቸው ላይ ለሚያምጹ፣ ወላጆቻቸውን ለማያከብሩና ለሚተቹ ልጆች ትልቅ አርአያ ነው።

ሉቃስ 2፡51 ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።

ሉቃስ በዚህ ውስጥ ትልቅ ዋጋ ያለው ትምሕርት አስተላልፎልናል። አንድ ሰው ሌሎች እንዲታዘዙት ከፈለገ እርሱ ቀድሞ ትዕዛዝ ማክበር አለበት። ኢየሱስ በአሥራዎቹ እድሜው ውስጥ በአስቸጋሪ የወጣትነት እድሜ ውስጥ ዮሴፍ እና ማርያም ላይ አንድም ጊዜ ሳያምጽ በፍጹም እያከበራቸውና እየተገዛላቸው አደገ። ይህ ታላቅ ምሳሌነት ነው።

ከዚህም የተነሳ እድሜው በደረሰ ጊዜና የዮሴፍና የማርያምን ቤት ለቆ ሲወጣ የሌሎች አዛዥ ለመሆን ብቁ ሆነ።

ቆላስይስ 3፡20 ልጆች ሆይ፥ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23