ኢየሱስ እንደ ፍጹም ሰው - በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 14



የዳኑ ሰዎች የቤተክርስቲያናቸውን ልማዶች ይወዳሉ፤ በዚህም ምክንያት ንጥቀት ያመልጣቸዋል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሚታዘዙ ሰዎችን ከሌላ ቦታ ያገኛል።

First published on the 12th of April 2020 — Last updated on the 5th of November 2022

ኢየሱስ አንዳንድ ፈሪሳውያንን በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶ እንደሆን ጠየቃቸው።

ሉቃስ 14፡5 ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጕድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው? አላቸው።
6 ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም።

አንድ እንስሳ በሰንበት ቀን ችግር ቢገጥመው አይሁዳውያን ከችግር ያወጡታል። እና ሰውን በሰንበት መፈወስ ስሕተቱ ምን ላይ ነው?

ከዚያ በኋላ የሐይማኖት መሪዎች ራሳቸውን በጣም ታላቅና አስፈላጊ አድርገው ስለማሳየታቸው ይወቅሳቸው ጀመር።

ሉቃስ 14፡7 የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል፦

ፈሪሳውያን የምኩራብ መሪዎች እንደመሆናቸው ሁል ጊዜ ከሁሉም በላይ የከበረ ሥፍራ ነው ለመቀመጥ የሚመርጡት።

ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ መከራቸው፡- … ከሁሉ ከፍ ባለው ቦታ አትቀመጡ፤… ዝቅተኛውን ሥፍራ መርጣችሁ ተቀመጡ።

ሉቃስ 14፡11 ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።

እግዚአብሔር የሚያደርገው እኛ ከምናደርገው ተቃራኒውን ነው።

የሮማ ካቶሊክ ፖፕ ሁልጊዜ በስብሰባዎች ላይ በክብር ከሁሉ በሚበልጠው ቦታ ነው የሚቀመጠው። የካቶሊክም ሆነ የፕሮቴስታንት የሐይማኖት መሪዎች በስብሰባዎች ውስጥ ከፍ ያሉ ቦታዎችን መርጠው መቀመጥ ይወዳሉ።

ኢየሱስ ድግስ ስንደግስ ጓደኞቻችንን መጋበዝ እንደሌለብን ተናግሯል፤ ደግሞም ወንድሞቻችንን፣ ዘመዶቻችንን ወይም ሃብታም ጎረቤቶቻችንንም መጋበዝ የለብንም። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች መልሰው ይጋብዙንና ውለታችንን ይመልሱልናል።

ሉቃስ 14፡13 ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤

እነዚህ ሰዎች ውለታህን ሊመልሱልህ አይችሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እራሱ ነው የሚመልስልህ።

ሉቃስ ስለ እራት ግብዣ አንድ ምሳሌ ጠቅሶልናል፤ ይህም በኢየሱስ ዳግም ምጻት ጊዜ ለሚደረገው የሰርግ ግብዣ ምሳሌ ነው።
(ማቴዎስ ኢየሱስን ንጉሥ አድርጎ ነው የጻፈው። ማቴዎስ ይህንኑ ምሳሌ ጽፏል ግን የድግሱ አዘጋጅ ለልጁ ሰርግ የሚያደርግ ንጉሥ ነው ብሎ ነው የጻፈው።)

ከዚህ ምሳሌ የምንማረው ሁሉም ነገር እኛ ከምንጠብቀው ተቃራኒ እንደሚሆን ነው።

ሉቃስ 14፡16 እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤
17 በእራትም ሰዓት የታደሙትን፦ አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ።
18 ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው፦ መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።
19 ሌላውም፦ አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።
20 ሌላውም፦ ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም አለው።
21 ባሪያውም ደርሶ ይህን ለጌታው ነገረው፦ በዚያን ጊዜ ባለቤቱ ተቆጥቶ ባሪያውን፦ ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች ፈጥነህ ውጣ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንና ዕውሮችንም ወደዚህ አግባ አለው።
22 ባሪያውም፦ ጌታ ሆይ፥ እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፥ ገናም ስፍራ አለ አለው።
23 ጌታውም ባሪያውን፦ ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው፤
24 እላችኋለሁና፥ ከታደሙት ከእነዚያ ሰዎች አንድ ስንኳ እራቴን አይቀምስም አለው።

በመጨረሻው የቤተክርስቲያን ዘመን ማብቂያ ላይ መጀመሪያ ወደ ሰርጉ ግብዣ የሚጠሩት የዳኑ ክርስቲያኖች ናቸው። ነገር ግን አንዳቸውም ፍላጎት አላሳዩም። ሁላቸውም ገንዘባቸውን መጠቀምና ኑሮዋቸውን በማጣጣም ተጠምደው ነበር። ሴት ወይም ሚስት የምትወክለው ቤተክርስቲያንን ነው። ክርስቲያኖች በቤተክርስቲያናቸው እምነትና አገልግሎት አብዝተው ይጠመዳሉ። ስለዚህ ወደ አዲስ ኪዳን የሐዋርያት አስተምሕሮ እና ትምሕርት ለመመለስ ጊዜውም ሆነ ፍለጎቱም የላቸውም።

በሬዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ትርጉም አላቸው። በእግዚአብሔር ዙፋን ዙርያ አራት እንስሳት አሉ፤ እነርሱም፡- አንበሳ፣ በሬ ወይም ጥጃ፣ ሰው፣ እና ንሥር ናቸው። አንበሳው ኢየሱስ የይሁዳ አንበሳ ተብሎ የተሰበከበትን የመጀመሪያዎቹን ሁለት የቤተክርስቲያን ዘመናት ይወክላል። በሬው ደግሞ የቤተክርስቲያን ልማዶች ከተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ርቀው የሄዱበትንና እውነት የጠፋበትን የጨለማውን ዘመን ይወክላል። በሬው የሚወክለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈ ነገርን ማመን ትክክል ነው ብሎ ለማስረዳት የሚሞክር ክርስቲያንን ነው። ስለዚህ ዛሬ ክርስቲያኖች ስሕተትን ትክክል ነው ብሎ በመከራከርና በማሳመን ችሎታ ተክነዋል። በዚህም ችሎታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጻፈ ሃሳብን እውነት ነው ብለው ያስረዳሉ።

ስለዚህ የመጀመሪያ ተወዳጅ የሆኑት የዳኑ ክርስቲያኖች ለዳግም ምጻት እንዲዘጋጁ የተባሉት ሳይዘጋጁ ይቀራሉ። ሒላሪ ክሊንተን ለሁላችንም ማስጠንቀቂያ ናት። ሴት እንደመሆኗ የቤተክርስቲያንን ምሳሌ ናት። የአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውስጥ ተወዳጇ ተፎካካሪ እርሷነበረች፤ ግን በምርጫው አልተመረጠችም። እግዚአብሔር ዘመናችንን የሚያሳይ ምልክት እየሰጠን ነው። ከሁሉ በፊት ተወዳጅ የነበሩ ወደ ኋላ ይቀራሉ። ሒላሪ ከትራምፕ ይልቅ ተወዳጅ ነበረች ብዙ ድምጽ ሰጭዎችም ነበሩዋት። ነገር ግን በተወዳጅነቱ ከእርሷ በጣም የሚያንሰው ትራምፕ ፕሬዚደንታዊ ምርጫውን አሸነፈ። በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ መሆን አስተማማኝ የማሸነፊያ መንገድ አይደለም።

ከዚያ በኋላ ቡድናዊ ቤተክርስቲያን “የገፋቻቸው” አይጥቅሙም ተስፋ የላቸውም ብላ የጣለቻቸው ሰዎች ወደ ላይ ይጠራሉ፤ ምክንያቱም እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማመንና የአዲስ ኪዳን አስተምሕሮዎችን ለመከተል ዝገጁ ናቸው። በየትኛውም ቡድናዊ ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል አለመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን በሙሉ እንዲያምኑ ነጻነት ይሰጣቸዋል። በቡድናዊ ቤተክርስቲያን ስሕተቶች አእምሮህ ቀድሞ ያልተበረዘ ከሆነ እውነትን ለማመን በጣም ቀላል ነው።

ዶናልድ ትራምፕ በጠበብቶች ዘንድ ተስፋ የለውም ተብሎ ቸል የተባለ ሰው ነበረ። በስተመጨረሻ ግን አሸነፈ።

ያልተጠበቁ ነገሮች እንደሚሆኑ ጠብቁ። ለጌታ ዳግም ምጻት ተዘጋጅቻለው ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ እንደገና አስቡ። ሒላሪ እንደሚሳካላት በጣም እርግጠኛ ነበረች። ሴት እንደመሆኗ የዘመናችን ቤተክርስቲያን ምሳሌ ነች። ግን አልተሳካላትም፤ አላሸነፈችም።

የዘመናችን ታላቅ ሚስጥር ምን መሰላችሁ፤ የቤተክርስቲያን የተሳሳቱ ትምሕርቶች ተቀባብተው እውነት መስለው በመቅረብ ክርስቲያኖችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው እውነት እንዲርቁ ማድረጋቸው ነው።

እጅግ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን ተከትለውት ነበር ግን እርሱ ለእኛ ለሰዎች በጣም የሚከብዱ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጠ። ኢየሱስ በሕዝብ ብዛት አይገረምም ምክንያቱም በስተመጨረሻ ጸንተው የሚከተሉት በጣም ጥቂቶች እንደሚሆኑ ያውቃል።

ሉቃስ ሁልጊዜ የኢየሱስን ንግግሮች ሲጽፍ አንድ ሰው ብለው የሚጀምሩ ንግግሮችን ነው የሚጽፈው። ይህም እኛ ኢየሱስን እንከተለዋለን የምንል ከሆንን በየግላችን ያለብንን ሃላፊነት የሚያሳይ ነው።

ሉቃስ 14፡25 ብዙም ሕዝብ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር፥ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው፦
26 ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
27 ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።

የቤተሰባችንን ጉዳይ ከእግዚአብሔር ማስቀደም አንችልም። ባሎች ሰላም ለማግኘት ብለው ሚስቶቻቸው እንዲጨቁኗቸው ይፈቅዳሉ።

አግብተው ከቤታቸው የወጡ ክርስቲያኖች ካገቡና ከቤት ከወጡ በኋላ እንኳላጆቻቸው እንዲገዙዋቸው ይፈቅዳሉ። ወላጆች አመጸኛ ልጆቻቸውን ለማግባባት ብለው መጽሐፍ ቅዱስ ካዘዘው መንገድ ይወጣሉ። ሕይወታችንን ከእግዚአብሔር ማስቀደም አንችልም።

ክርስቶስን መከተሌ ቤተሰቤ ሁሉ እንዲቃወመኝ ካደረገ መክፈል የሚያስፈልገኝ ዋጋ ይኸው ነው። መስቀሉ ትርጉሙ መከራ ነው።

ኢየሱስ እርሱን ለመከተል ከመወሰናችን በፊት ዋጋችንን ማስላት እንዳለብን ተናግሯል። እውነተኛ ክርስቲያን ትልቅ ዋጋ ይከፍላል።

ጠንቃቃ ካልሆንን በመንገድ ዳር ወድቀን እንቀራለን።

ሉቃስ 14፡30 ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።

መዳን እና የክርስትና ሕይወትን መጀመር ቀላል ነው። እስከ ፍጻሜው ድረስ መጽናት ግን በጣም ከባድ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ በመጨረሻው አሳሳች የቤተክርስቲያን ዘመን ውስጥ ማለቂያ የሌለው የሰዎች አመለካከት፣ ልማድ እና ስሜትን የሚኮረኩር ለስሕተት መከላከያ የሚሆን ክርክር ቡድናዊ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ በሞላበት ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስን እውት ማግኘት ከባድ ነው።

እነዚህ ሁኔታዎች በጣም ከባድ ናቸው። ግን ጠንካራ ሰዎች ተግዳሮት ይስባቸዋል። እግዚአብሔር ሰዎች እርሱን የሚከተሉበትን መስፈርት ዝቅ ቢያደርገው ወደ እርሱ የሚመጡ ሰዎች በሙሉ ተግዳሮትን ለመጋፈጥ ወኔ የሌላቸው ሰዎች ነው የሚሆኑት።

የጨለማው ዘመን የጨለመው መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ተከልክሎ ስለነበረና ሰዎች የሚከተሉት ብርሃን ስላጡ ነው።

የእኛ ዘመን ደግሞ የሚያሳውረን እጅግ ብዙ አይን የሚያጠፉ የሚያንጸባርቁ በብልጣ ብልጥ መንገድ ስሕተትን እውነት አስመስለው የሚያቀርቡ ትምሕርቶች ስለበዙ ነው፤ እነዚህም በመድረኮቻችን ላይ ደምቀው ሲቀርቡ ግራ ያጋቡናል። የዛሬ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸው እጅግ በጣም በሚያሳዝን ደረጃ አነስተኛ ነው።

እውነትን የሚቀበሉ ሰዎች በጣም ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ እነዚህ እውነትን ያመኑ ሰዎች በብዙሃኑ ዘንድ መገፋት ይገጥማቸዋል።

ሉቃስ 18፡8 … ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?

ለዚህ ጥያቄ ግልጽ የሆነው መልስ “የለም” ወይም “አያገኝም” ነው።

ቤተክርስቲያኖች ዛሬ ሊቆጠሩ የማይችሉ ብዙ ሚሊዮን የዳኑ ክርስቲያኖች አሉ ብለው ያወራሉ። ይህም እውነት ሊሆን ይችላል። ግን ምንድነው የጎደለው ነገር? ጌታ ለምንድነው በጣም ትንሽ ብቻ የመጽሐፍ ቅዱስ እምነት ይኖራል ብሎ የተናገረው? በመጨረሻው ዘመን ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን የማንበብ ፍላጎት አይኖራቸውም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን የማመን ብቃትም አይኖራቸውም።

እምነት የሚመጣው የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት ነው። ስለዚህ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናረውን አያምኑም፤ የዳኑ ቢሆኑም እንኳ አያምኑም።

ክርስቲያን ሁሉ በመንፈሳዊ ጦርነት ውስጥ ነው ያለው፤ ዲያብሎስ ደግሞ ጠንካራ ጠላት ነው፤ ስለዚህ ከዲያብሎስ ጋር ለመደራደር ተዘጋጅተህ ካልሆነ በቀር ሕይወት ቀላል ነው ብለህ አትጠብቅ። ስሕተትን በደገፍክ ቁጥር ሰይጣን አንተን አያስጨንቅህም፤ በሰላም እንድትኖር ይተውሃል።

ሉቃስ 14፡33 እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።

ጓደኞቻችንን፣ ቤተሰባችንን፣ የቤተክርስቲያን ቡድናችንን፣ እንዲሁም የቤተክርስቲያን መሪዎቻችንን ሁሉ ለመቃወም ዝግጁ መሆን አለብን። ቤተክርስቲያኖቻችን ያስተማሩንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ አስተምሕሮዎች ለመርሳት የተማርናቸውን ትምሕርቶች በሙሉ ከአእምሮዋችን አውልቀን ለመጣል መዘጋጀት አለብን፤ አለዚያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈውን እውነት አጥርተን መማር አንችልም።

ሉቃስ 14፡34 ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፈጣል?

ክርስቲያኖች ነን እያልን ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቀን ካልተከተልን ለእግዚአብሔር አንዳችም አንጠቅመውም።

ሉቃስ 14፡35 ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም፤ ወደ ውጭ ይጥሉታል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።

“የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ይህ ትዕዛዝ ለሰባቱም የቤተክርስቲያን ዘመናት ተደጋግሞ ተነግሯል። ይህ ትዕዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምሕርት መጽናት እንዳለብን የሚናገር ማስጠንቀቂያ ነው። ይህ የዛሬው ዓለም እኛ መጽሐፍ ቅዱስን ለመካድ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተት አለ ለማለት ማመካኛ የምንፈልግ ሰዎች እንደሆንን ለማየት የምንፈተንበት የፈተና መድረክ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈ ቃል ጋር አንስማማም ወይም አንቀበለውም ያልን ጊዜ ወዲያው ለእግዚአብሔር የዘመን መጨረሻ እቅድ የማንጠቅም ሰዎች እንሆናለን።

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23