አመራር

በዓለም ዙርያ በቤተክርስቲያናት ዘንድ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ አመራር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ወደሚቀጥለው የእድገት እርከን የሚያሸጋግሯቸውን ወጣትና ጠንካራ አዳዲስ መሪዎችን በማበረታታትና በማሰልጠን መርሀ ግብሮች ተጠምደዋል፡፡ ሰዎች ማበረታታት፣ ማነቃቃትና ማነሳሳት ከሚችሉ ወንዶችና ሴቶች ጐን መሰለፍ ይወዳሉ፡፡ ሰዎች ራሳቸውን በሌሎች ስኬት ውስጥ ማየት ይፈልጋሉ፡፡

በጣም የሚያሳዝነው ነገር በአሁኑ ወቅት በሚገኙት በአብዛኞዎቹ አብያት ክርስቲያናት ውስጥ የሚንጸባረቀው የአመራር ሥርዓት በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጠው አመራር ፍጹም የተለየ ነው፡፡

የብዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የአመራር መዋቅር አንድ ሰው የሁሉ የበላይ ሆኖ ከእርሱ ሥር የሚደግፉት አገልጋዮች ያሉበት የሥልጣን ተዋረድ ነው፡፡ እነዚህ አገልጋዮች ለብቻቸው ተለይተው ወደ ዋነኛው መሪ ቀረብ የሚል ቡድን ይፈጥሩና ቀሪው የቤተክርስቲያን ምእመን ገለልተኛ ሆኖ ይቀራል፡፡ ከመሪው ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚችሉት አብዛኛውን ጊዜ ልዩ አባላት ብቻ ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያን አባል ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ማድረግ የሚችለው ግንኙነትም ጭምር ይቋረጣል። በዚያ ምክንያት አንድ ሰው እግዚአብሔርን ለመስማት ወይም ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚችለው በመሪው ወይም በመሪው አገልግሎት አማካኝነት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡

ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ሃሳብ ቤተክርስቲያኑ በዚህ ዓይነት መንገድ እንድትንቀሳቀስ አይደለም፡፡ የዚህ አይነቱን የአመራር መዋቅር በተመለከተ እግዚአብሔር በንጉስ ሳኦል ታሪክ አማካኝነት አስጠንቀቆናል፡፡ ነገር ግን ሳኦልን ከማየታችን በፊት እውነተኛው መሪ ማን እንደሆነ እንመልከት።

 

ዮሐንስ 14:26  አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።

ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።
ኤፌሶን 5:23 ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና።

 

መፅሐፍ ቅዱስ በግልፅ እንደሚናገረው፤ የቤተክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንርሱም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ቤተክርስቲያንን ይመራታል፡፡ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ከእርሱ ውጭ ሌላ ማንም ሰው፣ ፓስተር፣ ዲያቆን፣ ሽማግሌ ወይም መሪ ይህንን ቦታ ሊወስድ አይችልም፡፡

 

1ኛ ጢሞቴዎስ 2:5 አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤

 

በራዕይ መፅሐፍ ውስጥ በቤተክርስቲያን መካከል ቆሞ የሚገኘው ክርስቶስና ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

 

ራእይ 1:13 በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፥ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።
ራእይ 1:20 በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፥ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

 

ችግሩ የሚጀምረው ሰዎች እግዚአብሔር መሪ እንዲመርጥላቸው ምርጫውን ለእግዚአብሔር ከመተው ይልቅ የራሳቸውን መንፈሳዊ መሪዎች ለመምረጥ ሲፈልጉ ነው፡፡ ደቀመዛሙርት የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ከማግኘታቸው በፊት ይህንኑ ተመሳሳይ ስህተት ፈጽመው ነበር፡፡ ይሁዳ እራሱን አጠፋ፤ ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ደቀመዛሙርት በይሁዳ ቦታ ሌላ ሰው መተካት ፈለጉ፡፡ ጴጥሮስም ከሕዝቡ ጋር ተነጋገረና ከዚያም የተሳሳተ ምርጫ አደረጉ፡፡

 

የሐዋርያት ሥራ 1:21-22 ስለዚህ ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ከእኛ ዘንድ እስካረገበት ቀን ድረስ፥ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በገባበትና በወጣበት ዘመን ሁሉ ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ሰዎች፥ ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል።
23 ኢዮስጦስም የሚሉትን በርስያን የተባለውን ዮሴፍንና ማትያስን ሁለቱን አቆሙ።

24-25 ሲጸልዩም፡- የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ፥ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥኸውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው አሉ።
26 ዕጣም ተጣጣሉላቸው፥ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።

 

የሚያስደንቀው ነገር ማቲያስ ከዚያ በኋላ በድጋሚ መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም፡፡ ይሁን እንጂ በኋላ ይሁዳን ለመተካት የተመረጠው እውነተኛው ሐዋርያ ጳውሎስ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ እርሱ የተመረጠው በሰዎች ሳይሆን በእግዚአብሔር ነበር፡፡

 

ገላትያ 1:1 በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ

 

እግዚአብሔር አንድን ሰው በአንድ የሥራ ወይም የአገልግሎት ክፍል ውስጥ ሲያስቀምጠው ሌሎች ሰዎች መስማማታቸው ወይም አለመስማማታቸው ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ የጠራው እግዚአብሔር እስከሆነ ድረስ ሰዎች ድምጽ ቢሰጡት ባይሰጡት አብሔር ራሱ ሃሳቡን እንኪቀይር ድረስ ሰውየው በአገልግሎቱ ይቆያል፡፡

እንደ ክርስቲያን እውቅና የምንሰጠው ከእግዚአብሔር ለተሰጠ አገልግሎት ወይም ጥሪ ብቻ ነው፡፡

አንድን ሰው ሥልጠና ሰጥተነው ወደ አገልግሎት ልናሰማራው አንችልም፤ እኛ ድምጽ ብንሰጥም ባንሰጥም ማን በየትኛው አገልግሎት ላይ መሰማራት እንዳለበት መወሰን አንችልም፡፡

አሁን ወደ ንጉስ ሳኦል እንመለስና እግዚአብሔር የተሳሳተ አመራርን እንዴት ገልጦ እንደሚያሳየን እንመልከት፤ እንዲሁም ይህ ከዛሬዋ ቤተክርስቲያን ጋር እንዴት እንደሚዛመድ እንመልከት፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 8:1፤ እንዲህም ሆነ፤ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ልጆቹን በእስራኤል ላይ ፈራጆች አደረጋቸው።

2፤ የበኵር ልጁም ስም ኢዮኤል፥ የሁለተኛውም ስም አብያ ነበረ። እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር።

3፤ ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር።

4፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና።

5፤ እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት።

6፤ የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

 

በመጀመሪያ የእስራኤል ሽማግሌዎች ለሳሙኤል ጥያቄ ለማቅረብ ጥሩ ምክንያት ያላቸው ይመስላል፡፡ ከሰው እይታ አንፃር ሲታይ ሁኔታው አሳሳቢ ነበር፡፡ ሳሙኤል አርጅቷል፤ ልጆቹ ደግሞ ክፉዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ እስራኤልን ማን ሊመራው ነው? ልብ በሉ፤ ሌላው ቀርቶ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነብይ የነበረው ሳሙኤል እንኳ ለልጆቹ የማይገባቸውን ስልጣን በመስጠት ስህተት ፈፅሟል፡፡ ስለዚህ እምነታችንን በእግዚአብሔር ላይ መጣልን መለማመድ ያስፈልገናል፡፡ እያንዳንዱ ፍላጐታችንን እርሱ የሚያውቅ ሲሆን ሁልጊዜም የሚያስፈልገንን ያዘጋጅልናል፡፡

 

መዝሙረ ዳዊት 118፡8 በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።

 

እግዚአብሔር ብዙ ይታገሰናል፤ ወደ እርሱ እስክንመለስ ይጠብቀናል፤ ነገር ግን እርሱ እንዲመራን እምነት ካልጣልንበትና ፈቃዱን ከፈቃዳችን ካላስቀደምን ለማይረባው ፈቃዳችን አሳልፎ ይሰጠንና ፈቃዳችንን መከተል የመያስከትልብንን መዘዝ ሁሉ መቀበል የኛ ፋንታ ይሆናል፡፡ የምንፈልገውን ልናገኝ እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለሕይወታችን ያለውን ዓላማና ዕቅድ ሳናገኘው እንቀራለን፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 8፡7፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፡- በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ።

 

እግዚአብሔር ለእሥራኤል የልባቸውን መሻት ፈጽሞላቸው ሰው እንዲነግስላቸው ንጉስ ሰጣቸው፡፡ አሁን በዚህ ውስጥ የሰው የአመራር መዋቅር ምን እንደሚመስል ማየት እንችላለን፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ጥቅሶች ውስጥ የሰው አመራር መገለጫዎች ወይም ባህሪያት በሙሉ ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህን መገለጫዎች ልብ ብለን በመመልከት እኛን እያስተዳደረን ያለውን አመራር መመዘን አለብን፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 8፡11፤ እንዲህም አለ፡ በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥

በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፤(ዋነኛው መሪ በሕዝቡ መካከል ከሕዝቡ ውስጥ መርጦ በአመራር ቦታ ላይ የሾማቸው ሰዎች የሚሉትን ሁሉ ሕዝቡ ያምናሉ። ነገር ግን ዳዊት እራሱ እንኳን ይህንን አሰራር አይደግፈውም፡፡ መዝሙር 20፡7 «እነዚያ በሰረገላ እነዚያም በፈረስ ይታመናሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ክፍ ከፍ እንላለን።)

12፤ ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ።(ጉባኤውን በሥርዓት ለማደራጀት ተብሎ የአገልጋዮች፣ የረዳት መጋቢዎች፣ የዲያቆናትና፣ የወጣት መሪዎች የሥልጣን ተዋረድ ይዋቀራል፡፡)

13፤ ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀማሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል። (በሁሉም ዓይነት የቤተክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ በርካታ ሴቶች የሚሳተፉ ሲሆን ዘወትር ለመስተንግዶ የሚቀርብ በቂ ምግብ ይኖራል)
14፤ ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።(ከማሕበረሰቡ የሚገኘው ንብረት አገልግሎቱን ለማሳደግ ጠቅም ላይ ይውልላል)

15፤ ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።(ለእግዚአብሔር የሚገባው አስራት ቤተክርስቲያኑን ለማሳደግ ይውላል)

16፤ ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል።

17፤ ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ።

 

አዎን፤ የተዋቀረ የሰው አመራር ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ለማስተዳደርና ለማደራጀት ይጠቅም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጥቅሙ የቤተክርስቲያኒቱን ዝግጅቶችና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በትክክል እንዲካሄዱ ለማድረግ ብቻ ነው፡፡ ከአመራሩ የሚተላለፈው መልዕክት በሥርዓትና በትክክል ይደርሳል፡፡ ነገር ግን መልዕክቱ በቤተክርስቲያን ዶግማና በሐሰተኛ አስተምህሮ የተሞላ ነው፡፡ በግለሰብና በእግዚአብሔር መካከል እንደ መካከለኛ ሆኖ የሚሰራ የልሂቃን አገልግሎት አለ፡፡

እውነተኛይቱ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በታሪክ በጣም ትልቅ ሆና አታውቅም፡፡ ከዚህ ይልቅ በርካታ ቁጥር ያላቸው አነስተኛ ሕብረቶች ነበሩ፡፡ ሁልጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል የሚገለጠው ጥቂቶች ብዙሃኑን እያሸነፉ ነው፡፡ ጌዲዮን የነበረው ሠራዊት 300 ሰዎችን ብቻ የያዘ ነበር፡፡ ሳምሶን አንድ ብቻውን ሆኖ ብዙዎችን ይገጥም ነበር፡፡ ከነአናዊው ኢያቡስቴ በእግዚአብሔር ኃይል 800 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ገደለ፡፡ እንደውም ብዙውን ጊዜ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሲዘምቱ እግዚአብሔር ከነርሱ አለመሆኑን ያመለክታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ በተመለከተ ያስጠነቅቀናል፡-

 

ማቴዎስ 7፡13 በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤
14 ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።

 

እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን በሕዝብ ቁጥር ታናሽ ብትሆንም እንኳ እግዚአብሔር በመካከሏ ይገኛል፡፡ ከቁጥሩ ይልቅ ለስሙ የሚያመጣውን ክብር የበለጠ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡

ማቴዎስ 18፡20 ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።

 

ጳውሎስ አብዛኛውን ጊዜ በቤት ውስጥ ስለምትገኝ ቤተክርስቲያን ይናገር ነበር፡፡ በአንድ ቤት ውስጥ ብዙ ሰዎችን ማስተናገድ አይቻልም፡፡ ቤተክርስቲያን የታሰበችው በውስጧ ያሉ ሰዎች እንደቤተሰብ አይነት ትስስር እንዲኖራቸው ነው፡፡

 

ሮሜ 16፡5 በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእስያ ለክርስቶስ በኵራት ለሆነው ለምወደው ለአጤኔጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ።

1ኛ ቆሮንቶስ 1፡11 ወንድሞቼ ሆይ፣ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና።
1ኛ ቆሮንቶስ 16፡19 የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ በቤታቸው ካለች ቤተ ክርስቲያን ጋር በጌታ እጅግ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

 

ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለባት በቻይና ውስጥ የምትገኘው ቤተክርስቲያን ስደትን የተቋቋመችው አነስተኛ የቤት ውስጥ ቤተክርስቲያን ስብስቦችን በመያዝ ነው፡፡

የሰው አመራር የሚያስከትለውን ታላቅ ውድቀት ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ የምርጫቸውን ውጤት ሲያብራራላቸው በመስማት መረዳት እንችላለን፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 8፡18፤ በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አይሰማችሁም።

 

እግዚአብሔርን በጣም በፈለጋችሁት ጊዜ አይሰማችሁም፡፡ በሰው ሕይወት ውስጥ እጅግ ከሚያሳዝኑ ሁኔታዎች መካከል ዋነኛው ይህ ነው፡፡

ብልሹ የሆነው ሐሰተኛ አመራር በበዚህ ታሪክ ውስጥ እንዴት እንደተብራራ እንመልከት፡፡

 

ሳሙኤል 8፡19፤ ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ። እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥

20፤ እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት።

 

በሐሰተኛ አመራር ስር የሚገኙ አብዛኞዎቹ ሰዎች በዚያው አመራር ስር መቆየት እንደሚፈልጉ እንደሆኑ ማወቅ አለብን፡፡ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው ያሉበትን ሁኔታ ተገንዝበው የመንፈስ ቅዱስን ምሪት የሚከተሉት፡፡

 

ኤርምያስ 5፡31 ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?

 

ሰዎች በተፈጥሮአቸው ስንፍና አለባቸው፡፡ ሐይማኖታቸውን ሌላ ሰው እንዲያምንላቸው ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ የሚፈልጉት የቤተክርስቲያን ፕሮግራሞች ላይ መገኘት፣ መነቃቃት እና መበረታታት ብቻ ነው፡፡ ፈፅሞ እግዚአብሔርን በማወቅ አያድጉም፤ የአኗኗር ዘይቤያቸውንና ያሉበትን መንፈሳዊ ደረጃ የሚያነፃፅሩት ከሌሎች ሰዎች ጋር ነው፡፡ ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ አስጠንቅቆናል፡፡

 

2ኛ ቆሮንቶስ 10፡12 ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም።

 

የሰው ልጅ አመራር ስርዓት ቤተክርስቲያንን በሚመራና የቤተክርስቲያንን ማሕበረሰብ በሚያሳድግ ጠንካራ መሪ የሚጀምር አይደለም፡፡ ይልቁን ከታች ጀምሮ ወደ ላይ የሚሄድ ነው፡፡ ሰዎች የሚመራቸውን ሰብአዊ መሪ ይፈልጋሉ፡፡

የሰዎች የዚህ ዓይነት ድርጅቶችን የመመስረት ፍላጐት ቅን እና ያልተወሳሰበ ሊሆን ቢችልም፤ አመሰራረቱ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ግድፈት ያለበት በመሆኑ የስርዓቱ ባህሪ በራሱ ሰዎችንና መሪዎችን ብልሹ ያደርጋቸዋል፡፡ ፖለቲካ በአብዛኛው የሚሰራው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ጥሩ እና ታማኝ ሰዎች በመጨረሻ ላይ ሥልጣናቸውን ለማስከበርና ሕዝቡን ለማስደሰት ብለው በፈጠሩት ሥርዓት ውስጥ ባለው የክፋት መንገድ ተጠምደው ይቀራሉ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ሥርዓቱ የሚያድገው በእግዚአብሔር እንቅስቃሴ ሳይሆን፤ ሰዎች በጋራ የሚያግባባቸው ነጥብ ስላገኙበትና ከሕይወት ዘይቤአቸው ጋር የሚጣጣም እንዲሁም ማሕበረሰባዊ ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚያስችላቸው እና ተቀባይነት ያለው አመለካከትና እይታ ላይ ስለሚያስማማቸው ነው፡፡

በስተመጨረሻ ስርዓቱ በአብላጫው ሕዝብ አስተሳሰብ የሚመራና ሆኖ ይቀራል፡፡ በነዚህ ዓይነት ስርዓት ውስጥ ጥሩ መሪ ሰዎችን ምን እንደሚያስደስታቸው፣ እንደሚያዝናናቸውና እንደሚያስደንቃቸው ለይቶ ለማወቅ ይችላል፡፡ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ እግዚአብሔርን ከፍ ከማድረግ ይልቅ መሪውን ከፍ ያደርጉታል፡፡ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት አያደርጉም፡፡ የመፅሐፍ ቅዱስ፣ የእግዚአብሔር ትዕዛዛትና በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሕይወት እውቀታቸው ደካማ ይሆናል፡፡

ሳኦል ንጉስ ሆነ፤ ከዚያም በኋላ ብዙም ሳይቆይ የእግዚአብሔርን ፍቃድ መከተል ትቶ የራሱን ፍቃድ መከተል ጀመረ፡፡ በተቀመተበት የሥልጣን ሥፍራ ሕዝቡ ከፍ ከፍ አደረጉት፡፡ ይህም ትእቢተኛና ራስ ወዳድ አደረገው፡፡

 

ሳሙኤል 13፡3፤ ዮናታንም በናሲብ ውስጥ የነበረውን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፥ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፤ ሳኦልም፡- ዕብራውያን ይስሙ ብሎ በአገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ።
4፤ እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ተጸየፉ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ።

 

ሳኦል ተገቢውን ክብር ማግኘት ላለበት ለዮናታን ክብር ከመስጠት ይልቅ ክብሩን ለራሱ አደረገ፡፡ ወደ ሥልጣን ያመጡት ሰዎች ስለነበሩ ሰዎቹን የማስደሰት ግዴታ ውስጥ ገብቷል፡፡

 

ሳሙኤል 13፡11 ሳሙኤልም፡- ያደረግኸው ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም፡- ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በቀጠሮው እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማክማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፤

 

አንድን ነገር ሌሎች ሰዎች ስለሚያደርጉት ብቻ ብለህ ምን ያህል ጊዜ አድርገህ ታውቃለህ ? ወይም ለሎች ሰዎች የሚያደርጉብህን ወይም የሚሉህን ፈርተህ ምንአድርገህ ታውቃለህ? ሳኦልን ንጉስ አድረገው የመረጡት ሰዎች በሚያደርጉበት ተፅዕኖ ለሚደርስበት ጫና ተንበረከከ፡፡ ጲላጦስም እንደዚሁ ለሕዝብ ጫና እጅ በመስጠት ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡

 

ማርቆስ 15፡15 ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ።

 

እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነቱን ሥርዓት ይቃወመዋል፤ ፈጽሞ ይጠላዋል፡፡ በቀደመችው ቤተክርስቲያን ይህ አይነት የሰው አመራር ተቀባይነት አልነበረውም፤ ነገር ግን ቀስ በቀስ ወደ ቤተክርስቲያን ሾልኮ በመግባት ዋነኛ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ለመሆን በቅቷል፡፡

 

ራእይ 2፡6 ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና።
ራእይ 2፡15
ቀጥሎም እንዲህ ይላል …….
15 እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ።

 

እግዚአብሔር የኒቆላውያን ተግባርና ትምህርት ብሎ ይጠቅሰዋል፡፡ ኒቆላውያን ማለት «ምእመናንን መግዛት ወይም » ወይም በሌላ አገላለጽ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መቆጣጠር ማለት ነው፡፡ ይህ የሚከናወነው እውነተኛውን የመንፈስ ቅዱስ አመራር በማስወገድና የሰውን አመራር በመተካት ነው፡፡

እውነተኛ የሆነ የቤተክርስቲያን አመራር አለ፤ ይህንንም አመራር ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡-

 

1ኛ ጴጥሮስ 5፡1 እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤
2 በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
3 ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤

 

ይህ የሚያሳየው በቤተክርስቲያን ውስጥ የአንድ ሰው መሪነትን ሳይሆን ለሌሎች ምሳሌ የሆነ ሕይወት መኖርን ነው፡፡ የሚያወራው ስለ አንድ ሰው ብቻ ሳይሆን ስለ ሽማግሌዎች (ብዙ ቁጥር) ነው፡፡ ሽማግሌዎች ምሪት ይሰጣሉ፣ ይመክራሉ እንዲሁም ገና ወደ ብስለት ላላደጉት የ በቤተክርስቲያን አባላት የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምራሉ፡፡ ሕይወታቸው ለአዳዲስ አማኞች ምሳሌ ይሆናል፤ በግላቸው ከጌታ ጋር ሕብረት በማድረግ ስለተመላለሱ መልካም አርአያ መሆን ይችላሉ፡፡ በራሳቸው የግል ተሞክሮና ተፈትነው ባለፉባቸው ፈተናዎች አማካኝነት ለሌሎች የቤተክርስቲያን አባላት የእግዚአብሔር ተስፋ ቃል እንዴት እንደሚፈጸምና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተፃፈው መሠረት እግዚአብሔር ከእኛ ምን እንደሚጠብቅ ማሳየት ይችላሉ፡፡

በአንድ ሰው አመራር ስር የመፅሐፍ ቅዱስ እውቀት ታፍኖ ይቀርና በዶግማ ይተካል፡፡ አሁንም በሳኦል ታሪክ ውስጥ ይህንን እውነት ማየት እንችላለን፡፡ መላው የእስራኤል ሠራዊት ከፍልስጥኤማውያን ጋር ለመዋጋት ወጥቷል፤ ነገር ግን ከሳኦልና ከዮናታን በቀር ማንም ሰይፍ አልታጠቀም፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 13፡22 ስለዚህም በሰልፍ ቀን ሰይፍና ጦር ከሳኦልና ከዮናታን ጋር በነበሩ ሕዝብ ሁሉ እጅ አልተገኘም፤ ብቻ በሳኦልና በልጁ በዮናታን ዘንድ ተገኘ።

 

መፅሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ይህ ታሪክ ጠቶቻቸውን ሊፋለሙ የወጡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል ያልታጠቁ ሰዎችን በምሳሌ ያሳየናል።

 

ኤፌሶን 6፡13 ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።
14-15 እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤
16 በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤
17 የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።

 

ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ካላወቁ ሰዎች ትክክለኛ እምነት ሊኖራቸው አይችልም፡፡

 

ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።

 

የሳኦል ታሪክ እንደሚያሳየን የተሳሳተ አመራር እግዚአብሔርን አያከብርም እንዲሁም የቤተክርስቲያን መሪዎች የተባሉት ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ትክክለኛ ያልሆኑ ሰዎችን በዙሪያቸው ይሰበስባሉ፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 14፡2፤ ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በጊብዓ ዳርቻ ተቀምጦ ነበረ፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ።
3፤ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የፊንሐስ ልጅ የዔሊ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፤ ሕዝቡ ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም።

 

ኢካቦድ ማን ነው? ለምንድነው ስሙ ተለይቶ የተጠቀሰው?

 

1ኛ ሳሙኤል 4፡21፤ እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም፡- ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም ኢካቦድ ብላ ጠራችው።

 

ይህ ጥቅስ የሰው አመራር እግዚአብሔርን የማያከብሩ ሰዎችን በራሱ ዙርያ እንደሚሰበስብ ያሳየናል፡፡ በሰው አመራር የሚተዳደር ቤተክርስቲያን አይነተኛ መገለጫው ዘመድ አዝማድን እየመረጡ መጥቀምና በኃላፊነት ቦታ መሾም ነው፡፡ አንድ መጋቢ ከነልጁ በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲያገለግሉ ስንት ጊዜ አይታችኋል? አኪያ የተከበረው የዔሊ ቤተሰብ ስለነበር ብቻ ነው፡፡ ኤሊ እውነተኛ ነብይ መሆኑ ልጆቹ ወይም ሌሎች የቤተሰቡ አባላትም በግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ እያንዳንዱን ሰው መመዘን ያለብን በሚያፈራው ፍሬ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሳኦል በሚመራው ሰው ሰራሽ ሐይማኖታዊ ስርዓት ውስጥ (እንዲሁም ሌላ ማንኛውም ሐይማኖታዊ ስርዓት ውስጥ) ሰዎች ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የሰዎችን ማንነት እያዩ የመከተል ልማድ አላቸው፡፡ በሰው አመራር የሚካሄድ ሐይማኖታዊ ስርዓት የመጨረሻው መገለጫ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በምድረ ላይ 1.2 ቢሊዮን ያህል ተከታዮች አሏት፡፡ እግዚአብሔርን በዚህ አይደነቅም፤ ደግሞም የዚህች ቤተክርስቲያን ፍርድ በራዕይ 18 ተጽፏል፡፡

በሰይጣን ኃይላት ላይ ድልን ለመቀዳጀት በመንፈስ ቅዱስ መመራት ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር ዓላማ እና ዕቅድ አለው። በውጊያ ሰዓት ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁትም በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ብቻ ናቸው፡፡ ዮሐንስ 16፡13ትን አስታውሱ - እርሱ ወደ እውነት ሁሉ ይመራናል ሊመጣ ያሉውንም ነገር ያሳየናል፡፡ በዚህ መንገድ ሌሎች በውጊያ ቀን ግራ ሲጋቡ እኛ ግን ዝግጁ እንሆናለን፡፡ በዚያን ጊዜ እነርሱ ድንገተኛ ድንጋጤ ያገኛቸዋል፡፡ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት በሄዱበት ሌሎቹ እስራኤላውያን ግን እርሱ መሄዱን እንኳን አላወቁም፡፡ ልክ እንደዚሁ አንዳንዶች ዛሬጠላታቸውን እንዴት በውጊያ ድል እንደሚነሱ ይቅርና የሚዋጋቸውጠላት መኖሩን እንኳ አያውቁም፡፡ መንፈስ በዘመን መጨረሻ ያለችውን ቤተክርስቲያን ሲናገራት አሁን ስላለንበት ዘመን በትክክል ይገልጻል፡፡

 

ራእይ 3፡17 ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥

 

ሳኦል አማንቃውያንን ፈፅሞ እንዲያጠፋቸው ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር፡፡ እርሱ ግን የተሰጠውን ትዕዛዝ ጥሶ የተወሰኑ ከብቶችና በጎችን ለራሱ አደረገ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ሳሙኤልን በሚናገርበት ጊዜ ልክ ምንም እንዳላጠፋ ሰው ነበር የሚናገረው፡፡ በራሱ አስተያየት እርሱ ኃጥያትን ፈጽሞ የማያውቅ ጻድቅ ነው፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 15፡13፤ ሳሙኤልም ወደ ሳኦል መጣ፤ ሳኦልም፡- አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ አለው።
14፤ ሳሙኤልም፡- ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድር ነው? አለ።

 

በሰው አመራር ውስጥ ያለው ሌላኛው ትልቁ ችግር አንድ ሰው (መሪው) ጥፋት በመፈፀም በተሳሳተ መንገድ ሲጓዝ አጠቃላይ ተከታዮቹም በዚያ የስህተት መንገድ ተከትለውት ይሄዳሉ፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ብንቀበል ግን ጌታ እኛን የሚመራባቸው በርካታ መንገዶች ያሉት ሲሆን፤ አንዱን ክርስቲያን ወንድማችንን ተጠቅሞ ስህተታችንን ሊያሳየን ይችላል፡፡ በሐይማኖታዊ ስርዓት ውስጥ በታችኛው የስልጣን ተዋረድ እርከን ላይ የሚገኙ ሰዎች ላይኛው እርከን ላይ ለሚገኙ ሰዎች ስህተታቸውን መንገር አይችሉም፡፡ ይህ ቤተክርስቲያኒቷን እንደመቃወም ወይም እንደቅናት፣ ፈራጅነት ወይም እራስን ማፅደቅ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡

በእግዚአብሔር ስርዓት ውስጥ ግን አንድ ባለሥልጣን ያለ ሲሆን እርሱም ቃሉ ነው፡፡ ታላቅ ይሁን ታናሽ እያንዳንዱ ሰው ለቃሉ መገዛት አለበት፡፡ እግዚአብሔር ይበልጥ የሚገደው ቃሉን መታዘዝህ እንጂ በሰው ሰራሽ የሐይማኖት ስርዓት አማካኝነት ስለምታመጣለት ስኬቶች አይደለም፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 15፡22 ሳሙኤልም፡- በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።

 

ሰው ሰራሽ የሐይማኖት ስርዓቶች አብዛኛውን ጊዜ የምስጋና መዝሙሮች የሚሰውባቸው ድንቅ የሆኑ የአምልኮ አገልግሎቶች አሏቸው፡፡ ሰዎች የተቀቡ መስሎ ይሰማቸዋል፤ ነገር ግን ለቃሉ አይታዘዙም፡፡ በመሆኑም ከሳኦል ጋር ተመሳሳይ የሆነ ዕጣ ይገጥማቸዋል፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 16፡14 የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው።

 

በጥፋታችን የምንቀጥል ከሆነ እግዚአብሔር ከእኛ ይርቅና በሐሰት ማመናችንን እንድንቀጥል ይተወናል፡፡

 

2ኛ ተሰሎንቄ 2፡9-10 ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው።
11-12 ስለዚህም ምክንያት፥ …ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል

 

ይህ ሰው ሰራሽ የሐይማኖት ስርዓት እውነተኛዎቹን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት በማሳደድ የሚያስከትለውን ታላቅ መከራ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቀናል፡፡

 

ማቴዎስ 24፡21 በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።

 

በድጋሚ የሰው ሰራሽ ሐይማኖት መሪ እንዴት በእግዚአብሔር የተቀቡ ሰዎችን እንዴት እንደሚያሳድድ የሳኦል ታሪክ ያሳየናል፡፡

 

1ኛ ሳሙኤል 18፡11፤ ሳኦልም፡ ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ።
12፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው።

 

አንድ ታዋቂ መምህርን ወይም ነብይን የሚከተል ቤተ እምነት ወይም ቡድን አባል ነህን? ምንም እንኳን መምህሩ ወይም ነብዩ ትክክለኛና እውነት ቢሆንም፤ በዙሪያው የተገነባው ሰው ሰራሹ ስርዓት የሐሰት አገልግሎት ነው፡፡ የቤተክርስቲያንህን አመራር ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ፈትሽ፤ እውነቱን እንደሚያሳይህ ቃል ስለገባ በመንፈስ ቅዱስ ስለመመራትህ እርግጠኛ ሁን፡፡

እራስህን የዚህ ዓይነት ስርዓት ውስጥ ካገኘኸው ማድረግ የምትችለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡

 

ራእይ 18:4 ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤