የቤተክርስቲያን ዘመናት - ትያጥሮን - አራተኛው ዘመን - ከ606 እስከ 1520 ዓ.ም.



First published on the 26th of May 2019 — Last updated on the 26th of May 2019

የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ዘመን ካሕናትን ወይም ሌላ አይነት መሪዎችን ይዞ መጣ።

ሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በካሕናቱ ላይ ስልጣን ያለውን ወይም በከተማ ቤተክርስቲያኖች ላይ መሪ በሆኑት ካሕናት ላይ ስልጣን ያለውን ጳጳስ ይዞ መጣ። እያንዳንዷ ከተማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጳጳስ ነበራት።

በሦስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ንጉስ ኮንስታንቲን የቤተክርስቲያን ራስ በሆነበት ጊዜ 318 ጳጳሳት በእርሱ ስር በአንድነት ተደራጁ። ኮንስታንቲን ወደ ምሥራቅ በመሄድ በኮንስታንቲኖፕል ተቀመጠ። ከዚያም ለሮማው ጳጳስ ስለጣንና ሃብት በመስጠት የሮማው ጳጳስ በምዕራቡ ግዛት ላይ ዋነኛው ጳጳስ እንዲሆን መንገድ አመቻቸለት።

በ400 ዓ.ም. ራሱን ፖፕ ወይም ጳጳስ ብሎ ጠራ፤ ትርጓሜውም አባት ማለት ነው።

ማቴዎስ 23፡9 አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ አባት ብላችሁ አትጥሩ።

በ450 ዓ.ም የሮማ መንግሥት ሲወድቅ ጳጳሱ ራሱን ፖንቲፍ ወይም የባቢሎናውያን ሊቀ ካሕናት ብሎ ሰየመ፤ ይህንንም ያደረገው የሮማ ግዛትን እየወረሩ የነበሩ አረማውያን መካከል መግቢያ ለማግኘት ነው።

የሮማ መንግሥት በ476 ዓ.ም. ከወደቀ በኋላ በአራተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ፖፑ የሮማ መንግሥትን ወዳሸነፉት ባርቤሪያውያን ነገዶች ለመዞር ተገደደ። በዚህ በአራተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ፖፑ በአውሮፓ ውስጥ በስልጣን ከፍ እያለ ሄደ ከዚያም ደግሞ የሚቃወሙትን ሁሉ ማሳደድ ጀመረ።

በኃይል ከፍ ማለት የጀመረው ባርቤሪያውያን ነገሥታትን የመቀባትና የመሾም ስልጣን አለኝ ብሎ እንዲሁም ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያት ቁልፎችን በእጁ ይዟል ብሎ በማሳመን ነው። ፖፑ የጴጥሮስ ተተኪ ነኝ ብሎ ስላሳመናቸው ባርቤሪያውያን ለፖፑ ቢታዘዙ ይሻላቸዋል። ለፖፑ አልታዘዝም ቢሉ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ አይከፍትላቸውም።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተቃዋሚዎቿ ላይ ፖለቲካዊ ሥልጣንን ለማግኘት ብላ በ325 ዓ.ም. በኒቂያ በተደረገው ጉባኤ ከሮማ ግዛት ፖለቲካዊ ኃይል ጋር ከተጋባች በኋላ ምዕራባዊው የሮማ ግዛት እየተበታተነ እና በባርቤሪያውያን ወራሪዎችና በእርስ በርስ ጦርነት በሚደረግበት ጫና እንዲሁም በጨካኝ ግን ደካማ ገዢዎች የብቃት ማነስ የተነሳ እየተንኮታኮተ መሆኑን አልተገነዘበችም ነበር።

በኢጣሊያ፣ በግሪክ ቅጥረኛ ወታደሮች እና በኦስትሮጎቶች መካከል ከ535 እስከ 554 የነበረው የሃያ ዓመት ውጊያ በኢጣሊያ ውስጥ ድህነት፣ ረሃብ፣ የበሽታ ወረርሽኝ እና ይህንንም ተከትሎ የጨለማው ዘመን እንዲመጣ ከማድረግ ውጭ ለኢጣሊያ ምንም መላ አላመጣላትም።

የታሪክ ምሑራን በዚህ ወቅት ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተዋል ይላሉ። በወቅቱ በነበሩ ጦርነቶች አማካኝነት በሥላሴ የማያምኑት ኦስትሮጎቶች ሙሉ በሙሉ ከኢጣሊያ ምድር ተወግደዋል። ከዚህም የተነሳ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በአስተምሕሮ የሚሞግታት በሌለበት ያለተቀናቃኝ መግዛት ችላለች።

የሮማ ቤተክርስቲያን ራሷን ያገኘችበትን ያለተጠበቀ አዲስ ሁኔታ በአስገራሚ መንገድ በባርቤሪያውያን ነገዶች ላይ ፖለተካዊ እና ሐይማኖታዊ ሥልጣንን ለመቆናጠጥ ተጠቅማበታለች።

ከ634 እስከ 720 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት ዓመታት ውስጥ የአረብ ሙስሊሞች ሶሪያ፣ ፍልስጤም፣ ሰሜን አፍሪካ እና እስፔይንን ተቆጣጠሩ። በዚህም ምክንያት ሮም በሜዲተራኒያን ባሕር ላይ በመመላለስ በሚነግዱ ነጋዴዎች አማካኝነት ያደጉ ከተሞችዋ ላይ የነበራትን ግዛት አጣች።

ከዚያ በኋላ እስላቮች በደረቅ ምድር (በየብስ) የነበረውን የምሥራቅ የንግድ መስመር ዘጉ።

ከዚህ በታች ባለው ካርታ ላይ በወይን ጠጅ ቀለም የተቀቡ ግዛቶች ሁሉ ሙስሊሞች የተቆጣጠሩዋቸውን አገሮች ያመለክታሉ።

የምዕራቡ ዓለም አውሮፓ ውስጥ ወደ ሰሜን ከመሸሽ በቀር ምንም አማራጭ አልነበረውም። ባርቤሪያውያን ነገዶች የራሳቸው ሕግጋት ነበሩዋቸው ስለዚህ ሁሉን በአንድ ሕግ ያስተዳድር የነበረው የሮማውያን አገዛዝ በብዙ ራሳቸውን በቻሉ የባርቤሪያውያን ግዛቶች ተከፋፈለ። በሜዲተራኒያን ባሕር ላይ ያላቸውን ግዛት በ634 ዓ.ም. እና በ720 ዓ.ም. መካከል በአረብ ሙስሊሞች ሲነጠቁ በባሕር ላይ ንግድ አማካኝነት እያደጉ የነበሩ ከተሞች እየጠፉ ስልጣኔም ከሜዲተራኒያን ባሕር ወደ ሰሜን ሲሸሽ በከተሞቹ ፋንታ የእርሻ መሬት ዋነኛ የሃብት ምንጭ ሆነ። ገዳሞች አብረዋቸው ከሚከፈቱ ሃኪም ቤቶች እና ትምሕርት ቤቶች ጋር የእርሻዎች ማዕከል ሆኑ፤ መንደሮችም በዙሪያቸው እየተስፋፉ ሄዱ። መነኩሴዎቹም ብዙውን ጊዜ ምሑራንና በልዩ ልዩ ሙያዎች እና በሕክምና የሰለጠኑ ሰዎች ነበሩ።

እነርሱም ጫካዎችን እየመነጠሩ እርሻ ማረስ ሲጀምሩ ብዙ ገበሬዎች እንዲከተሉዋቸው ምሳሌ መሆን ችለዋል። የመጀመሪያው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ገዳም የተከፈተው ኢጣሊያ ውስጥ በ529 ዓ.ም. በቅዱስ ቤኔዲክት አማካኝነት ሞንቴ ካሲኖ ውስጥ ነው። የገዳም ሕይወት በቤተክርስቲያን መሪዎች ዘንድ የነበረው ምግባረ ብልሹነትና ሐጢያት እንዲሁም በባርቤሪያውያን ወረራ የተነሳ የተፈጠረው ማሕበራዊ ቀውስ ያንገሸገሻቸውን ብዙ ሰዎችን ሊስባቸው ችሏል።

አንድ ገዳም እያደገ ሲሄድ በውስጡ ከነበሩ መነኩሴዎች መካካል የተወሰኑት ወጥተው ሌላ ቦታ ይሄዱና አዲስ ገዳም ይከፍታሉ። በ754 ዓ.ም. ፖፑ የመጀመሪያውን ባርቤሪያዊ ንጉስ የፍራንኮች ፔፒን የተባለውን ቀብቶ አነገሰ። ይህም ለፖፑ ትልቅ ክብር አስገኘ፤ እንዲሁም በፖፑ ሥር የነበሩ በሰሜን አውሮፓ የተከፈቱ የአንግሎ ሳክሰን ገዳሞች በባርቤሪያውያን ሕዝቦች ዘንድ ክብራቸው ጨመረ።

ኢንግላንድ ውስጥ የሚኖሩ አንግሎ ሳክሰኖች ወደ ሰሜን አውሮፓ እጅግ ብዙ ወንጌል ሰባኪዎችን ይልኩ ነበር። እነርሱ ለፖፑ የሚታዘዙ ብዙ ገዳሞችን እና ቤተክርስቲያኖችን ከፈቱ። ሁለት የአንግሎ ሳክሰን ሰዎች በተለይ ለፖፑ ክብርና በሰሜን አውሮፓ ውስጥ ለሮማ ካቶሊክ እምነት መስፋፋት ልዩ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በ690 እና በ739 ዓ.ም መካከል ወደ ሆላንድ ከዚያም ወደ ዴንማርክ ወንጌል ሰባኪ (ሚሽነሪ) ሆኖ የተላከው ዊሊብሮርድ የሮማ ካቶሊክ እምነትን እንዲሁም በርቀት ሮም ውስጥ ላለው ፖፕ መታዘዝን በአውሮፓ ውስጥ አስፋፍቷል። በዚህ መንገድ የአንግሎ ሳክሰን ሚሽነሪዎች እና መነኩሴዎች በዚያ ዘመን የሮማው ፖፕ በሰሜን አውሮፓ ውስጥ ተቀባይነቱ እንዲጨምር ታላቅ ሚና ተጫውተዋል።

ጀርመኒ ውስጥ ከ710 እስከ 754 ዓ.ም. ሚሽነሪ የነበረው ቦኒፌስ ጀርመኒ ውስጥ በብዙ ልዩ ልዩ ቦታዎች የመጀመሪያውን የተደራጀ ክርስትና መሰረተ። ፖፑም ጀርመኒ ውስጥ የሜይንዝ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ሾመው፤ ጀርመኒ ውስጥ ባሉ ጳጳሳት ሁሉ ላይ የበላይ አደረገው። ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱት የፍራንኮች ቤተክርስቲያኖች ብዙ በእምነት ወደ ኋላ አፈግፍገው ነበር፤ ቦኒፌስም እነርሱን በመመለስ እና ለሮም እንዲታዘዙ በማድረግ ታላቅ ሚና ተጫውቷል። ሮም ውስጥ በርቀት ያለውን ፖፕ ሥልጣን አክብሮ መኖር ባርቤርያውያን ፍራንኮችን በጣም ያስገርማቸዋል። እነርሱም በፈቃደኝነት ለቦኒፌስ እና ይዞላቸው ለመጣው ካቶሊካዊ አስተምሕሮ ይታዘዙ ነበር። ፍራንኮች የሥልጣን ተዋረዱና መዋቅሩ በጣም አስገርሟቸዋል። ፍራንኮች ለመነኩሴዎቹ ይታዘዛሉ፤ መነኩሴዎቹ ለጳጳሳቱ፤ ጳጳሳቱም ቦኒፌስ ለተባለው ሊቀ ጳጳሳት፤ ቦኒፌስም ለፖፑ፤ ፖፑም የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ መክፈቻ በእጆቹ ለያዘው ለቅዱስ ጴጥሮስ ይታዘዛል። ይህም በጣም የተጠናከረ ሥርዓት ነው። ይህ ማዕከላዊ የሆነ የሥልጣን መዋቅር በጨለማው ዘመናት ውስጥ ለገዳሞች ሥርዓት ስኬታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ትዕዛዝ ከላይ ወደታች የሥልጣን ተዋረድን ጠብቆ ይተላለፋል፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የታዘዘውን ይፈጽማል።

ከዚያም በበርገንዲያን ነገድ በተያዘው ግዛት ውስጥ በ910 ዓ.ም ክላኒ ውስጥ በጣም ዝነኛ የሆነው ገዳም በዱክ ዊሊያም አማካኝነት ተሰራ (ፈረንሳይ ውስጥ በርገንዲ የሚባለው አካባቢ ስያሜውን ያገኘው ከዚህ ነገድ ነው)።

በክላኒ ውስጥ ያለው ገዳም የምዕራባውያን የገዳም ሕይወት መሪ በመሆን እውቅናን አግኝቷል (ምስል የተወሰደው ከዊኪፔዲያ ነው)።
ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለፖፑ ብቻ የሆኑት የክላኒ ገዳም መነኮሳት ወደ ሰሜን በመሄድ በአውሮፓ ማዕከላዊ አገሮች ውስጥ ሁሉ እየተስፋፉ ከ950 እስከ 1160 ዓ.ም ድረስ 1200 አዳዲስ ገዳሞችን ከፈቱ፤ በዚህም የተነሳ የክላኒ ገዳም አውሮፓ ውስጥ አንደኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ገዳም ሆነ። በዚሁ ወቅት ከተለያዩ ከበርቴዎች ድጋፍ በሚያገኙ ተፎካካሪ ጳጳሳት ሽኩቻ የተነሳ የፖፑ ስልጣን ተዳክሞ ነበር። የክላኒ መነኮሳት የስኬታቸው ምስጢር የከፈቷቸው ገዳማት በሙሉ በክላኒ ገዳም ሥልጣን ስር መሆነቸው እና የክላኒ ገዳም ደግሞ ተጠሪነተዋ በቀጥታ ለሮማው ፖፕ በመሆኑ ነው። በርቀት የሚኖረው ፖፕ በባርቤሪያውያን ነገሥታት ዘንድ ትልቅ ክብር ነበረው። ፖፑ አንድን ሰው የባርቤሪያውያን ነገድ ንጉሥ አድርጌ የመሾም ስልጣን አለኝ አለ። ስለዚህ ባርቤሪያውያን ሕዝቦች በቀትታ ለፖፑ ይታዘዙ ለነበሩት መነኮሳት እና ጳጳሳት አክብሮት ያሳዩ ነበር። የበርገንዲያን ሕዝብ በክላኒ ከነበረው ገዳም ተጽእኖ የተነሳ በአውሮፓ ውስጥ በብዙ ቦታዎች የሮማ ካቶሊክ እምነት እንዲስፋፋ ሊያደርግ ችሏል።

የመጀመሪያዎቹ የክላኒ ገዳሞች ሁከት ከሞላበት ዓለም ለሚሸሹ ሰዎች መጠለያ ይሰጡ ነበር፤ ኋላ ግን በ1100 ዓ.ም የክላኒ ገዳሞች የቅድስና ሕይወት ወደ ማሕበረሰቡ ውስጥ ዘልቆ ገባ። በዚህ ወቅት ነበር ማእከላዊው የአውሮፓ በሙሉ ወደ ክርስትና የተለወጠው። የሮማ ጳጳሳት በሥነ ምግባር ውድቀት ውስጥ በነበሩበት ወቅት የመነኮሳቱ በስነ ምግባር የታነጸ የኑሪ ዘይቤ የባርቤሪያኖቹን ትኩረት ስቧል። ሮም ውስጥ ያሉት ጳጳሳት የሥነ ምግባር ሚዛናቸው ሲወርድ በርገንዲ ውስጥ ያሉት የክላኒ ገዳም መነኮሳት ግን የሥነ ምግባር ሚዛናቸውን ከፍ በማድረግ የፖፑን ሥልጣን ከውድቀት ሊያድኑት ችለዋል። ባርቤሪያውያን ክላኒ ውስጥ በተከፈቱ ገዳማት ውስጥ የሚኖሩትን መነኮሳት ያዩዋቸዋል። ባዩዋቸውም ጊዜ ባዩት ሁሉ ተገርመዋል። ብዙዎቹ ባርቤሪያውያን ፖፑን አይተውት አያውቁም። በዚህም ምክንያት በፖፑ ምግባረ ብልሹነት የተነሳ ሊሰናከሉ አልቻሉም።

ለዚህ ዘመን የተላከው መልዕክተኛ ኮሉምባ ነበረ፤ እርሱም በአየርላንድ ከነበሩ ታላላቅ የቤተክርስቲያን ሰዎች ሥር ከተማረ በኋላ በሃገሪቱ ውስጥ በርከት ያሉ ገዳማትን ከፍቷል። በ563 ዓ.ም ኮሉምባ እና አብረውት የሚያገለግሉ አሥራ ሁለት አጋሮቹ ወደ እስኮትላንድ ከተሻገሩ በኋላ እስኮትላንድ አጠገብ ያለ አዮና የተባለ ደሰት ላይ ሰፍረዋል። የወንጌል ስብከት ስራዎቹንም በብዛት ያከናወነው አረማውያን እስኮትላንዶች መካከል ነበር። ራሳቸውን የቻሉ ገዳሞች በማቋቋም ሕዝቡ በተቻላቸው መጠን በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተጻፈው የአኗኗር ዘይቤ እና ትምሕርት መሰረት ለመኖር እንዲሞክሩ አበረታቷቸዋል።

ተከታዮቹ ከመሰረቱዋቸው ገዳሞች ሁሉ በጣም ታዋቂ የነበረው የሊንዲስፋርን ደሴት ላይ የተከፈተው ገዳም ነበር።

ኮሉምባ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በግልጽ የሚያበራ ደማቅ ብርሃን ነበረ፤ ነገር ግን ልክ የአራተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን በ606 ዓ.ም ከመጀመሩ በፊት በ597 ዓ.ም ሞተ፤ ምክንያቱም ትያጥሮን የወንጌል ብርሃን ፈጽሞ ሊጨልም የተቃረበበት የቤተክርስቲያን ዘመን ነበረ።

ኮሉምባ ደማቅ ብርሃን ስለነበረ እርሱ በሕይወት እያለ የወንጌል ብርሃን ሊደበዝዝ አልቻለም።

ሦስተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የተጠናቀቀው ፖፕ ግሪጎሪ እንግሊዝ ውስጥ ወደ ኬንት የሮማ ካቶሊክ ሚሽነሪዎችን በመላክ ኮሉምባ በእንግሊዝ ምድር ውስጥ የፈጠረውን ተጽእኖ ደብዛውን ለማጥፋት ትልቅ ሙከራ እያደረገ በነበረበት ወቅት ነው።

በ597 ዓ.ም የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ ኦጋስተን ወደ ኬንት መጣ። አንግሎ ሳክሰኖችን ካቶሊክ አደረጋቸውና በላያቸው ጳጳሳትን ሾመ። ኦጋስተን ካንተርበሪ ውስጥ ተቀምጦ የሶማቸውን ጳጳሳት ሁሉ ይቆጣጠር ነበር። ሮም በእንግሊዝ ውስጥ ስኬት ያገኘችበት ምስጢር ይህ ነው።

የካንተርበሪ ጳጳስ በእንግሊዝ ውስጥ የተደራጁ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ራስ ሲሆን እንግሊዝ ውስጥ ሚሽነሪ እንዲሆኑ ስልጠና ወስደው የሚላኩ ጳጳሳት በሙሉ ለካንተርበሪ ጳጳስ ተጠሪ ይሆናሉ። የካንተርበሪ ሊቀጳጳስ ደግሞ ተጠሪነቱ ለፖፑ ነው።

በሊንዲስፋርን ደሴት ላይ በሰፈሩት ኮሉምባ በመሰረታቸው ነጻ ገዳሞች ውስጥ በሚኖሩት መነኮሳት እና ፖፑ በላካቸው ሚሽነሪዎች መካከል ግልጽ የሆነ ግጭት ነበረ፤ በተለይም በእንግሊዝ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ ባለችው በኖርዘምብሪያ ግዛት ውስጥ።

በተጨማሪ ይህ ክፍለ ዘመን (ከ600 እስከ 700 ዓ.ም) እንግሊዝ ውስጥ የክርስትና ባሕል የጀመረበት ጊዜ ነው፤ ይህም የሆነው በተለይ የእንግሊዝ ውስጥ ኖርዘምብሪያ በሚባልበት ግዛት ውስጥ ነው። ኖርዘምብሪያ በወቅቱ ከእንግሊዝ ግዛቶች ሁሉ ግምባር ቀደም ነበር። ቦታውን ከላይ በሚገኘው ካርታ ማየት ይችላል።

ኮሉምባ የላካቸው ከሰሜን ምዕራብ (ከእስኮትላንድ እና ከአይርላንድ) የመጡ ሴልቲክ ሚሽነሪዎች እንዲሁም ከደቡብ እና ከምሥራቅ (ኬንት) የመጡ ሮማን ሚሽነሪዎች በዚህ ሥፍራ የአራተኛውን የቤተክርስቲያን ዘመን እጣ ፈንታ ለመወሰን ተሰባሰቡ።

ስለዚህ ኢንግላንድ ውስጥ የመነኩሲቶች መሪ ሒልዳ በ663 ዓ.ም በዊትቢ በሚገኘው ገዳም ሲኖዶስ መስርታ የኖርዘምብሪያ ንጉሥ ኦስዊዩ ከሁለታቸው ማን ትክክል መሆኑን እንዲወስን ጠራችው። የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች በጴጥሮስ እጅ ናቸው ያሉት አለ። ስለዚህ በምድር ላይ የጴጥሮስ ወኪል የሆነውን ፖፑን ብትታዘዙ ስትሞቱ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ ይከፍትላችኋል። የኮሉምባ ተከታዮች ኮሉምባ እንዲህ አይነቱ መክፈቻ እንደሌለው አላስተባበሉም። ስለዚህ ንጉሡ ለካቶሊኮቹ ፈረደላቸው ምክንያቱም ንጉሡም ራሱ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ እንዲከፍትለት ፈልጓል። ይህ የብልጠት ዘዴ ነው።

የመንግሥተ ሰማያት በር ኢየሱስ ነው አሉ፤ ነገር ግን ስትሞቱ በሩን ሊከፍትላችሁ ወይም ሊቆልፍባችሁ ስልጣን ያለው ጴጥሮስ ነው።

ጴጥሮስ ደግሞ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ የሚከፍተው ለፖፑ ለሚታዘዙ ሰዎች ብቻ ነው። ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ የመክፈት ሥልጣን ያለው ብቸኛው ሰው ነው የሚለው ሃሳብ በባርቤሪያን ነገዶች ዘንድ ትልቅ ክብደት ያለው የካቶሊኮች መከራከሪያ ነጥብ ሆነ። ይህም ውሸት ባርቤሪያኖች በምድር ላይ የጴጥሮስ ወኪል ለተባለው ለፖፑ እንዲገዙ አደረጋቸው። ስለ ጴጥሮስ የተፈጠረው ይህ አስተምሕሮ የካቶሊክ እምነት በመላው አውሮፓ እንዲስፋፋ አስቻለ። ነገር ግን መዳናችሁን ወይ አለመዳናችሁን የሚወስነው ጴጥሮስ ስለሆን ኢየሱስ ወደ ጎን ተገፋ ጭራሽም አዳኝነቱ እየተረሳ ሄደ፤ በዚህም ምክንያት አውሮፓ ቀስ በቀስ እየተንሸራተተች ወደ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ገባች። ይህንን አስተምሕሮ በተቀበሉበት አካባቢ ሁሉ የወንጌል ብርሃን ጠፋ።

ማን እንደሚድን የሚወስነው ጴጥሮስ ነው የሚለውን ትምሕርት አንቀበለውም ያሉት የሊንዲስፋርን መነኮሳት ከሊንዲስፋርን ተነስተው ወደ አዮና ደሴት ሄደው ሰፈሩ፤ ከአዮና በኋላ ወደ አየርላንድ ሄዱ። የኮሉምባ ተከታዮች ለምሳሌ ኮሉምባነስ እና ካታልድ በመካከለኛው ዘመን ሚሽነሪዎች በመሆን ወደ ፈረንሳይ፣ ጀርመኒ፣ ስዊትዘርላንድ እና ኢጣሊያ ሄደው ነጻ የሆኑ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ገዳሞችን ከፈቱ። ከዚህም የተነሳ የኮሉምባ ተከታዮች የሆኑ ሚሽነሪዎች ሕዝቡን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምሕርት መሰረት እንዲኖሩ እያበረታቱዋቸው የወንጌል ብርሃን በልዩ ልዩ ሥፍራዎች በትናንሽ ቡድኖች መካከል ሳይጠፋ ግን ጭል ጭል እያለ ማብራቱን ቀጠለ።

በአራተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን የቤተክርስቲያን መቅረዝ ይህንን ነበር የሚመስለው። የመቅረዙ መብራት ሊጠፋ እጅግ ተቃርቦ ነበረ። ቤተክርስቲያን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ከጻፉት ከሐዋርያት አስተምሕሮ በጣም ርቃ ሄደች። ይህ ዘመን በእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ፈንታ ትልቅ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ድርጅት በኃይል እና በሥልጣን ያደገችበት ዘመን ነበር። ይህም የእግዘአብሔር ፈቃድ አልነበረም።

ይህ ገዳሞች የሚገነቡበት ዘመን ነበር። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጴጥሮስን ቁልፍ በመጠቀምና ፖፑ እዲሁም ከእርሱ ቀጥሎ የሚተካው ፖፑ የጴጥሮስ ተተኪዎች ናቸው በማለት የባርቤሪያውያንን ልብ ማረከች። የሚገርመው ግን ጴጥሮስ ሮም ሄዶ ወይም ሮም ውስጥ ኖሮ አያውቅም።

መቸም ሐሰት በሰዎች ጆሮ ውስጥ ብዙ ጊዜ ሲደጋገም በአእምሮዋቸው ውስጥ እውነት ወደ መሆን መለወጡ አይቀርም። በዚህም መንገድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪዎች አንግሎ ሳክሰን ሚሽነሪዎቻቸውን ወደ ሰሜን አውሮፓ በመላክ ዓለምን በሙሉ ወደ ጨለማው ዘመን ውስጥ ይዘው ገቡ። ከዚያም ለፖፑ ከልባቸው ይታዘዙ የነበሩት የሮማ ካቶሊክ በርገንዲያኖች አውሮፓ ውስጥ በየቦታው ተስፋፍተው 1200 ገዳሞችን ተከሉ። ይህንንም ተከትሎ መላው አውሮፓ በፖፑ እጅ ውስጥ ወደቀ።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አውሮፓን በሙሉ ስትቆጣጠር የእውነትን ብርሃን ሙሉ በሙሉ አዳፈነችውና አውሮፓ ለዘጠኝ መቶ ዓመታት በጨለማ ዘመን ተዋጠች። የሰዎች ሕይወት በቅዝቃዜ፣ በጨለማ፣ በቆሻሻ እና በአጓጉል እምነቶችና በፍርሃት ተወረረ። ሰዎች ገላቸውን መታጠብ እንኳ አቆሙ። በሽታና ረሃብ ተንሰራፉ። የአብዛኛው ሕዝብ የእድሜ ወሰን ከ45 ዓመት በታች ነበር። ቤተክርስቲያን አውሮፓን በተቆጣጠረችበት ዘመናት ውስጥ የሰዎች ኑሮ ጉስቁልና ብቻ ሆነ። ፖለቲካ እና ሐይማኖት ሲደባለቁ ከባድ መርዝ ይፈጥራሉ።

የሮማ ካቶሊክ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ የገነነችው ለምንድነው?

በመጀመሪያ ሐዋርያት እራሳቸው የመሰረቱዋቸው ቤተክርስቲያኖች አሉባቸው የተባሉ አራት ታላላቅ ከተሞች ነበሩ። ኮንስታንቲኖፕል ታላቅ ከተማ ነበረች ምክንያቱም ንጉሥ ኮንስታንቲን መናገሻውን ያደረገው በዚያች ከተማ ነበረ። ስለዚህ ሮም ከአምስት ታላላቅ ቤተክርስቲያኖች አንዷ ነበረች እንጂ ብቸኛዋ ታላቅ አልነበረችም።

ቀጥሎ ከመሃመድ ሞት ሁለት ዓመታት እንዳለፉ በ634 ዓ.ም የአረብ ሙስሊሞች ከአረቢያ በረሃ ተነስተው አንጾኪያ፣ ኢየሩሳሌም እና አሌግዛንድሪያ የተባሉ ከተሞችን በ641 ዓ.ም ተቆጣጠሩ። ከሰሜን አፍሪካ በኩል አልፈውም በ720 ዓ.ም እስፔይንን ተቆጣጠሩ። ከዚህ በታች ባለው ካርታ ውስጥ ቀይ ቀለም የተቀቡት ቦታዎች ሁሉ ሙስሊሞች የተቆጣጠሩዋቸው ሃገሮች ናቸው።

አንጾኪያ፣ ኢየሩሳሌም እና አልግዛንድሪያ የሙስሊም ከተሞች ሆኑ። ሮም እና ኮንስታንቲኖፕል ብቻ በሙስሊሞች ሳይገዙ ቀሩ። በዚህም የተነሳ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ሮም ብቸኛዋ ታላቅ የቤተክርስቲያን ከተማ ሆነች። ከዚያ በኋላ የአረብ መርከቦች ሜዲተራንያንን ስለተቆጣጠሩ የሮም የባሕር ላይ ንግድ ተቋረጠ። ኮንስታንቲኖፕልም በአረቦች ብዙ ዛቻ ይደርስባት ስለነበረ ሮምን ለመደገፍ ወታደሮችን መላክ አልቻለችም።

የባሕር ላይ ንግዱ ሲቋረጥ ሕዝቡ በግብርና ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት ፊታቸውን በሰሜን አውሮፓ ወዳሉ ሃገሮች መለሱ። ፍራንኮች ከኢጣሊያ በስተ ሰሜን ይኖሩ ነበር፤ እነርሱም ፖፑን ከፍ ከፍ ለማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ሥልጣኔ ከሜዲተራንያን እየሸሸ ወደ ሰሜን ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ሄደ። በ1500ዎቹ ፈረንሳይ፣ ሆላንድ፣ እና ጀርመኒ የአትላንቲክ ውቅያኖስን በመርከብ ማቋረጥ ሲጀምሩ በኢኮኖሚ ኃያላን እየሆኑ ሄዱ።

በሰሜናዊው አውሮፓ ግብርና እና ዘመናዊ ትምሕርት በገዳሞች ውስጥ መበልጸግ ጀመረ።

ከዚያም በሰሜን ኢጣሊያ ይኖሩ የነበሩት ሎምባርዶች (አካባቢው አሁን ሎምባርዲ ተብሎ ይጠራል) ፊታቸውን ወደ ደቡብ አዙረው ወደ ሮም ሄዱ። በሮማ ግዛት መፈራረስ ውስጥ ሎምባርዶች ታላቅ ሚና ተጫውተዋል። በመጀመሪያ በኢጣሊያ ሰሜን የምትገኘውን ሎምባርዲ ተቆጣጠሩ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ እቅድ ውስጥ ዋነኛው ድርሻቸው ወደ ደቡብ ሄደው ሮም ላይ ሥጋት መፍጠር ሲጀምሩ ነበር።

ይህም ሥጋት ፖፑ ድጋፍ እንዲፈልግ አደረገው። ኮንስታንቲኖፕል የአረብ ሙስሊሞችን ወረራ በመከላከል ተጠምዳ ነበር። ስለዚህ ከሎምባርዶች ዘንድ የመጣው ሥጋት ፖፑ የፍራንክ ባርቤሪያኖችን ድጋፍ እንዲጠይቅ አስገደደው።

ይህም በጨለማው ዘመን ውስጥ ፖፑ ካደረጋቸው የፖሊሲ ለውጦች ዋነኛው ነበር።

ፖፑ በኮንስታንቲኖፕል ከተቀመጠው ንጉሥ ፊቱን መልሶ እርዳታን ፍለጋ ወደ ባርቤሪያኖች ዘወር አለ። ፖፑ በትክክለኛው ጊዜ ነበር ስልታዊ ለውጥ ያደረገው። ፔፒን የቤተመንግሥቱ አስተዳዳሪ በነበረ ሰዓት ቺልደሪክ 3ኛው የፍራንኮች ንጉሥ ነበረ፤ እርሱም በጣም የተዳከመ ንጉሥ ነበረ።

በፔፒን እና በፖፑ መካከል ወዳጅነት ተመሰረተ። ፔፒን በሰዓቱ የነበረውን ደካማውን የፍራንኮች ንጉሥ ከዙፋኑ አወረደውና ፔፒን በ751 ዓ.ም ፖፕ ዛካሪ እርሱን በንጉሥነት እንዲቀባው አሳመነው። ከዚያም በ754 ዓ.ም ፖፕ እስቲቨን 2ኛው ወደ ፓሪስ ሄዶ ፕፒንን ንጉሥ አድርጎ ሾመው። ለመጀመሪያ ጊዜ የሮማ ፖፕ አንድ ባርቤሪያዊ ንጉሥን ሾመ። ይህም ፕፒንን ስልጣን ቀምቶ ከነገሰ ሰው በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደተቀባ ንጉሥ ለወጠው። በዚህም ምክንያት ፕፒን እድሜው ሲያልቅ ልጆቹ ብቻ በንግሥና ሊተኩት የሚችሉት ልጆቹ ብቻ ሆኑ።

ፖፑ ከቅዱስ ጴጥሮስ የተላከ የሚል ሐሰተኛ ደብዳቤ ይዞ ሄደ፤ በደብዳቤውም ውስጥ የነበረው መልዕክት ለፔፒን የተጻፈ ሲሆን ፔፒን ተነስቶ ሮምን የከበቡዋትን ሎምባርዶችን እንዲወጋ እንዲሁም ለፖፑ የተወሰነ ግዛት እንዲሰጠው ትዕዛዝ ያስተላልፋል። ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡበት ቁልፍ በጴጥሮስ እጅ ስለሆነ ፔፒን ለፖፑ ድጋፍ ማድረግ ግዴታ ሆነበት። ስለዚህ ፍራንኮች ወደ ኢጣሊያ ሄደው ሎምባርዶችን ተዋግተው አሸነፉ። ከዚያም ፔፒን ለፖፑ የተወሰኑ ግዛቶችን ሰጠው፤ እነዚህም ግዛቶች ፓፓል ስቴትስ ተብለው ተጠሩ። (ለፖፑ የተሰጡ ግዛቶች ከዚህ በታች ያለው ካርታ ውስጥ በቢጫ ቀለም ምልክት የተደረገባቸው ቦታዎች ናቸው።) በስተመጨረሻም የፔፒን ልጅ ሻርለሜይን ሎምባርዶችን ደመሰሰና የፖፑን ግዛቶች አስፋፋ። ከዚያም ፖፕ ሊዮ 3ኛው በ800 ዓ.ም ሻርለሜይንን አነገሰው፤ እርሱም ከባርቤሪያን ነገሥታት ሁሉ ታላቅ ሆነ፤ ከእርሱም የተነሳ ፖፑ በአውሮፓ ውስጥ ያለው ተጽእኖ ጨመረ።

ሻርለሜይን ከሁሉ ታላቅ ክርስቲያን ሆነ።

ነገር ግን በምሥራቅ የባይዛንቲየም (የኮንስታንቲኖፕል) ንጉሥን ዋነኛው የአውሮፓ ገዥ አድርገው ይመለከቱት ስለነበረ በእግዚአብሔር የተሸመ የአውሮፓ ንጉሠ ነገሥት የሚለው ማዕረግ ለሻርለሜይን ሲሰጠው አልተደሰቱም። በዚህም አቋማቸው በመጽናታቸው የተነሳ በምዕራብ እና በምሥራቅ መካከል መገንጠልን አስከትለዋል። ከዚያም ሮም እና ኮንስታንቲኖፕል ተፎካካሪ ቤተክርስቲያኖች ሆኑ። ሁለቱም እየተወዳደሩ አንዱ ሌላውን ለመብለጥ ሽኩቻ ውስጥ ገቡ።

የሮማ ካቶሊክ ሐይማኖት ሰሜን አውሮፓ ውስጥ ተስፋፋ፤ ደግሞም ያለተቀናቃኝ የሚገዛ ብቸኛ ሐይማኖት ሆነ፤ ኮንስታንቲኖፕል ደግሞ በሰሜን አውሮፓ ላይ እምብዛም ተጽእኖ አልነበራትም። በጣም የሚያሳዝነው ነገር ሮም ተቃዋሚዎችዋን በሙሉ ለማጥፋት መነሳቷ ነው።

ሰዎችን መግደል ከተፈለገ ወታደሮች ያሉዋቸው ነገሥታት ያስፈልጋሉ፤ እነዚህም ነገሥታት ለፖፑ በመታዘዝ ፖፑን ጠላቶች ለመግደል ፈቃደኞች መሆን አለባቸው። ፖፑ ሰዎችን በንግሥና ለመሾም ስልጣን ያለኝ እኔ ብቻ ነኝ ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አሳምኗል፤ ይህም በባርቤሪያን ነገዶች ላይ ትልቅ ተጽእኖ ወይም ስልጣን እንዲኖረው አስችሎታል። ፖፑ ውግዘት የተባለ ኃይለኛ መሳሪያ ለራሱ አበጀ። የፖፑ ውግዘት አንድን ንጉሥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከመግባት የመከልከል ኃይል አለው ተብሎ ይታመን ነበር ምክንያቱም ፖፑ አንድን ንጉሥ ካወገዘው ቅዱስ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያትን በር አይከፍትለትም። ከዚህም የተነሳ ነገሥታት ሁሉ ፖፑን ስለፈሩት ሁል ጊዜም ሊታዘዙት ዝግጁ ነበሩ።

በጨለማው ዘመን ውስጥ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሉተር የተጀመረውን ለውጥ ለማዳፈን በወሰደችው እርምጃ የተነሳ ከአሥር ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል። ፖለቲካ እና ሐይማኖት አንድ ላይ ተጋብተው በአውሮፓ ምድር ላይ ታላቅ የሞት ድግስ ይደግሱ ጀመር። በዚህ ጽሑፍ ውስት በሐይማኖት ስም እጅግ ብዙ ሕዝብ የተጨፈጨፈባቸውን ሁለት ቦታዎች ብቻ በጥቂቱ እንዳስሳለን።

በሊዮንስ ከተማ የነበሩት ዋልደንሶች አስተዋዮች ስለነበሩ ልጆቻቸው ሥራፈቶች እንዲሆኑ አይፈቅዱም ነበር። በፊታቸው ብዙ ፈተና እና የመከራ ሕይወት እንደሚገጥማቸውና ከዚያም ባለፈ የሰማዕትነት ሞት እንደሚጠብቃቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከልጅነታቸው ጀምሮ መከራን እንዲቋቋሙ፣ ለበላዮቻቸው እንዲታዘዙ፤ ነገር ግን ራሳቸውን ችለው እንዲያስቡ ተምረዋል።

እያሳደዱ ቢገድሉዋቸውም የፈሰሰው ደማቸው የተዘራውን ዘር እንደ ውሃ እያጠጣ ፍሬ ማፍራቱ አልቀረም። በዚህ መንገድ ሉተር ከመወለዱ ጥቂት መቶ ዓመታት በፊት ዋልደንሶች ለእግዚአብሔር መስክረዋል። በብዙ ሃገሮች ውስጥ በመበታተን በዋይክሊፍ ዘመን የተጀመረውን የለውጡን ዘር ዘርተዋል፤ ይህም ዘር በሉተር ዘመን በጥልቀት እና በስፋት አድጎ ተገለጠ።

ከ1173 እስከ 1560 ዓ.ም በኢጣሊያ የአልፕስ ተራሮች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዋልደንሶች 36 ጊዜ አሰቃቂ ስደቶች ደርሰውባቸዋል። እንደ ሕዝብ የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል፤ የጻፉዋቸው ጽሁፎች በሙሉ ከምድር ላይ ተቃጥለው ጠፍተዋል። ከእነርሱ ጥቂቶች ለመትረፍ ብለው በኢጣሊያ ኮቲያን ወደሚገኘው የአልፕስ ተራሮች አካባቢ ርቀው ሸሹ። ሞት ሁልጊዜ በዙሪያቸው ቢያንዣብብም ብዙ ሚሽነሪዎችን ወደ አውሮፓ ግዛቶች ይልኩ ነበር። ከዚህ በታይ የሚገኘው ካርታ ዋልደንሶች የተስፋፉባቸውን አካባቢዎች ያሳያል። ከእነርሱ መካካል ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በመገደሉ ታላቅ ዋጋ ከፍለዋል።

በጨለማ እና በክህደት ዘመን ውስጥ ሁሉ የሮምን ታላቅነት አሻፈረኝ አልቀበልም ያሉ ዋልደንሶች ነበሩ። በ2015 ዓ.ም በቱሪን ከተማ ውስጥ ፖፕ ፍራንሲን በዋልደንሶች ላይ ስለተፈጸመው ግፍ ይቅርታ ጠይቋል።

ሁለተኛው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጭፍጨፋ የተደረገው በደቡባዊ ፈረንሳይ የሚኖሩት አልቢጀንሶች ላይ ነበር፤ ይህም ጭፍጨፋ (ከ1209 እስከ 1229 ዓ.ም) የተፈጸመው በፖፕ ኢነሰንት 3ኛው፣ ኦኖሪየስ 3ኛው እና ግሪጎሪ 9ኛው አማካኝነት ነበር። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተፈጸሙ አሰቃቂ የደም ማፍሰስ ታሪኮች ውስጥ ሁሉ ይህኛው በአንደኛነት ሊመደብ ይችላል። በሃያ ዓመታት ጦርነት ውስጥ የተገደሉ አልቢጀንሶች ቁጥር ከአንድ እንከ ሁለት ሚሊዮን ይደርሳል። አልቢጀንሶች ይኖሩ የነበረበት ሰላማዊ እና እጅግ የበለጸገ ሃገርም ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

በደቡባዊ ፈረንሳይ የምትገኘው ላንጉዶክ የተባለችው አውራጃ በካቶሊክ ጦረኞች በተወረረች ጊዜ አንድ መቶ ሺ አልቢጀንሶች በአንድ ቀን አልቀዋል።

የአልቫ ገዥ 100000 መናፍቃንን እንደገደለ ይነገራል።

በእስፔይን ውስጥ ይደረግ የነበረው ዘስፓኒሽ ኢንኩዊዚሽን የተባለው ለ350 ብዙ ሰዎች አካላዊ ስቃይ እንዲደርስባቸው የተደረገበት ግፍ በታሪክ ላይ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

ሰማዕታት በሰይፍ፣ በስቅላት፣ ከምድር በታች በተሰሩ ጨለማ እስር ቤቶች ውስጥ እና ንብረቶቻቸው ስለተወረሱባቸው በረሃብ ሞተዋል።

ክርስትና ተቃዋሚዎቹን የማሳደድ ኃይል ካገኘበት ዓመት ጀምሮ ከሁሉ በላይ እጅግ አስቀያሚ ታሪክ አስመዝግቧል።

ክርስትና በኃይልና በፖለቲካዊ ሥልጣን ከፍ ከፍ እያለ በመጣበት ዘመን የሮማ ጳጳሳት ከ493 ዓ.ም በኋላ ሄሩሊዎችን ፈጽመው አጥፍተዋቸዋል፤ ቫንዳሎችን ደግሞ ከ533 ዓ.ም በኋላ፤ ከዚያም ኦስትሮጎቶችን በ554 ዓ.ም አጠፉዋቸው። እነዚህ ሁሉ የተገደሉት ሥላሴን የማይቀበለውን የአሪዮስን አስተምሕሮ ተከትለዋል ተብለው ነው። በሐይማኖት ስም የነፍስ ግድያ መፈጸም ከተጀመረ በኋላ ወንጌሉ መልኩ ተለውጦ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ዘማቾች ወደ ፍልስጤም ሄደው ሙስሊሞችን በመግደል የሐጢያታቸውን ስርየት ማግኘት እንደሚችሉ እስከሚያምኑ ደረሱ። በ1099 ዓ.ም ኢየሩሳሌምን ተቆጣጠሩና በውስጧ የሚኖሩ ሙስሊሞችን፣ አይሁዶችን እና ክርስቲያኖችን በሙሉ ገደሉ። በፖፕ ኢነሰንት የታወጀው ሦስተኛው የመስቀል ዘመቻ ሐይማኖታዊ ቧልት ነበረ። ዘማቾቹ በስግብግብነት በፖፑ ጥበቃ ስር የነበረችውን ዛራ የምትባለዋን ባለጠጋ ከተማ ሙልጭ አድርገው ዘረፉ፤ ይህንንም ሲያደርጉ የግድ ገንዘብ ያስፈልገናል ብለው ነበር። ከዚያም ቤተክርስቲያኖችን ብቻ ትተው ከተማይቱን ሙሉ በሙሉ ደመሰሱዋት።

ከዚያም እነዚህ ጨካኝ ምሕረት የለሽ “ጦረኛ ክርስቲያኖች” መርከቦቻቸውን ተሳፍረው ፖፑ ልኮናል በማለት የኮንስታንቲኖፕልን ከተማ በዝርፊያ፣ በነፍስ ግድያ እና በአስገድዶ መድፈር አስጨነቁዋት። ከተማይቷ የግሪክ ክርስቲያኖች ከተማ ብትሆንም ጦረኞቹ ከተጠናወታቸው ደም የማፍሰስ አመል እና ለገንዘብ ካላቸው ከፍተኛ ፍቅርና ስግብግብነት የተነሳ በከተማይቱ የሚኒሮትን ግሪካውያን ክርስቲያን ወገኖቻቸውን ከመግደል አልተመለሱም።

የመስቀል ጦርነቶች የሚባሉት (ከ1099 እስከ 1254 ዓ.ም) በ150 ዓመታት ውስጥ የተደረጉ ሰባት ዘመቻዎች ናቸው፤ እነዚህም ዘመቻዎች የተደረጉት ቅድስቲቱን ሃገር ከሙስሊሞች እጅ ነጻ ለማውጣት በሚል ሰበብ ነበር።

ገንዘብ፣ የነፍስ ግድያ፣ እና ሥልጣን፤ ይህ ዘመን በምኞትና በስግብግብነት የተነሳ ሐይማኖት የተጣመመበት ዘመን ነበር። ይህ ሁሉ ይደረግ የነበረው ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነበረ። ይህ ሁሉ ድርጊታቸው የሚያሳየው ሰዎቹ ፌዘኞችና አላጋጮች መሆናቸውን እንዲሁም የእግዚአብሔር ፍቅር ከልባቸው ውስጥ መጥፋቱን ነበር።

ጋሻዎቻቸው ላይ በቀይ ቀለም መስቀል ቢስሉም እንኳ በልባቸው የነበረውን ዲያብሎስ ሊደብቀው አልቻለም።

በይፋ ትንቀሳቀስ የነበረችዋ ቤተክርስቲያን ይህንን ያህል ነው የሰላም ንጉስ ይዞ ከመጣው መልካም ወንጌል ርቃ የሄደችው።

ቀጥሎ ያለው መቅረዝ በዚህ ጨለማ ዘመን ውስጥ ቤተክርስቲያን የነበረችበትን ሁኔታ ያሳያል።

ቤተክርስቲያን በዚህ ጊዜ የመጀመሪያው ዘመን ውስጥ ይሰጥ ከነበረው የአዲስ ኪዳን ንጹህ ትምሕርት ብዙ ርቃ ሄዳለች።

የእግዚአብሔር ብርሃን በጣም ደብዝዞ ነበር ግን ፈጽሞ አልጠፋም። በየዘመናቱ ጉልበታቸውን ለሮም ያላንበረከኩ ታማኝ ሰዎች ነበሩ።

በጨለማው ዘመን ውስጥ በየቦታው ትንንሽ የብርሃን ፍንጣቂዎች ነበሩ፤ እነርሱም በለውጡ ዘመን እየደመቁ ታላቅ ወገግታ ለመሆን በቅተዋል።

እስከዚያ ድረስ ግን እንደ በ1384 ዓ.ም እንደሞተው ዋይክሊፍ እና በ1415 ዓ.ም እንደተሰዋው ጆን ሃስ ያሉ ታላላቅ ሰዎች ስለ ንሰሃ እንዲሁም መዳን በጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በማመን እንጂ በራሳችን ሥራ አለመሆኑን በማስተማር የወንጌል እሳት ተዳፍኖ እንዳይጠፋ ተጋድለዋል።

አውሮፓን አንቆ የያዛትን የካቶሊክ ማነቆ እግዚአብሔር በለውጡ ዘመን ከብዙ ሃገሮች ላይ እስከሚያስወግደው ድረስ እነዚህ ሰዎች እና እነርሱን የመሰሉ ሌሎች በዚህ የጨለማ ዘመን ውስጥ ብዙ ታግለዋል ብዙ ለፍተዋል።

የመጀመሪያዎቹን አራት ቤተክርስቲያኖች በተመለከተ በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 2 ውስጥ ተጽፏል፤ በዚህም ምዕራፍ ውስጥ ቤተክርስቲያን እንዴት ከሐዋርያት እውነተኛ ትምሕርት ወደ ስሕተት እንደምትሄ ተገልጧል።

ምዕራፍ 3 ደግሞ በቀሩት ሦስት የቤተክርስቲያን ዘመናት እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ወደ ነበረችበት እውተኛ ትምሕርትና እምነት ሊመልሳት በትጋት የሰራበትን ጊዜ ያሳያል።

በዚህ የመቅረዝ ምስል እንደምናየው ቤተክርስቲያን በመጀመሪያዎቹ ዘመናት እውነትን ትታ ሄዳለች።

ራዕይ 2፡18 በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፦

ትያጥሮን ማለት አምባገነን ሴት ማለት ነው። ቤተክርስቲያን በሴት ትመሰላለች ምክንያቱም ኢየሱስ እውነተኛዋን ቤተክርስቲያን ሙሽራዬ ብሎ ነው የሚጠራት።

አምባገነን ሴት ለምድር ታላቅ እርግማን ናት። ቤተክርስቲያን አውሮፓን በተቆጣጠረች ጊዜ በታሪክ ውስጥ ክርስትና እጅግ የተዳከመበት ዘመን ነበረ። አሁንም አምባገነን ቤተክርስቲያን ስትገለጥ ዓለምን ሁሉ ይዛ ወደ ታላቁ መከራ ታስገባለች፤ በዚህም የተነሳ እንዲህ አይነቷ ቤተክርስቲይ በፍርድ ቀን ለሰዎች ኩነኔ ዋነኛ ምክንያት ትሆናለች። የምድር ሁሉ ዳኛ ይህች ቤተክርስቲያን የሰራቻቸውን ክፉ ሥራዎች በፍርድ ቀን እሳት በተሞሉ ዓይኖች ያያል። እያንዳንዱ የግፍ ሥራ ተመዝግቧል፤ እግዚአብሔርም በጊዜው ይበቀላል።

ናስ የሚወክለው ፍርድን ነው። የነጠረ ናስ ማለት ትንሹ ስሕተት እንኳ ከእይታ አያመልጥም ማለት ነው። ስለዚህ ንሰሃ የማንገባ ከሆነና በኢየሱስ ደም ካልታጠብን ፍርድ ይጠብቀናል።

ዘሌዋውያን 26፡14 ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥
19 የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ።

የጨለማው ዘመን ስሕተት ቤተክርሰቲያናዊነት ነበረ፤ ይህም የሰው አስተምሕሮ ነው።

እነዚህ የሰው ወጎች የተስፋት በጉልበት ነበር። ዳንኤል ስለ አሕዛብ ነገሥታት ባየው ሕልም ውስጥ ከሁሉም በላይ ጠንካራው እቃ ብረት ነው።

ብረት የጥሬ ጉልበት ምሳሌ ነው።

ዳንኤል ባየው ራዕይ ውስጥ ብረት ሮምን የሚወክል ምልክት ነበር። ነገር ግን ጉልበት ሁልጊዜም እርግጠኛ የሆነ አቅጣጫ ስለሌለው ያልታሰቡ ውጤቶችን ያስከትላል።

ሰይጣን በሁለተኛው የቤተክርስቲያን ዘመን ከ170 እስከ 212 ዓ.ም የሰምርኔስ ክርስቲየኖችን ለመጨፍጨፍ የሮማ መንግሥትን በተጠቀመ ጊዜ የነጹ የጠሩ እግዚአብሔር በምንም የማይወቅሳቸው ክርስቲያኖች ተገለጡ።

ራዕይ 2፡19 ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይነበብ በታገደበት እና ብዙ ሰዎችም ፊደል ባልቆጠሩበት ዘመን የእውነተኞቹ ቅዱሳን መልካም ሥራዎች ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ያንጸባርቅ ነበር። “ሥራሕን” የሚለውን ቃል ተከትሎ የሚመጣው “ፍቅርህን” የሚለው ቃል ነው። ሥራዎቻቸው ሁሉ መነሻው ለእግዚአብሔር ቃል ያላቸው ፍቅርና ሰዎችን በመውደድ እግዚአብሔርን ለማገልገል የነበራቸው ፍላጎት ነው።

በመዳናቸው የተነሳ ደስ እያላቸው መልካም ሥራ መሥራት እንደ ተፈጥሮአዊ ባሕርያቸው ሆነ። እንደ ሐሰተኛው የወይን ሐረግ መልካም ሥራ ለመዳን ብለው ወይ ደግሞ ሰው እንዲያደንቃች አልሰሩም።

መልካም ሥራቸው ሁሉ መሰረቱ ፍቅር እና ለጋስነት ነበር።

ሐሰተኛው የወይን ሐረግ መልካም ሥራ የሚሰራው ሐብታም ለመሆን፣ በዚህ ዓለም ገንዘብ ለመበልጸግና ሥልጣን ለማግኘት ነው። በ774 ዓ.ም ፖፕ ሃድሪያን ቀዳማዊ ለታላቁ ባርቤሪያን ንጉሥ ለሻርለሜይን ከኮንስታንቲን የተላከ ስጦታ ብሎ ሐሰተኛ ሰነድ አበረከተለት።

ኮንስታንቲን ከሞተ 400 ዓመታት አልፈዋል ነገር ግን ይህ ሰነድ ኮንስታንቲን ለሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብዙ ንብረቶች እና ሰፋፊ ግዛቶችን እንደውም በምዕራብ ያሉ ሃገሮችን በሙሉ እንደሰጠ ይናገራል። ከዚያ በኋላ የቤተክርስቲያን ሃብት በጣም እየበዛ ሄደ።

እግዚአብሔር የሚመለከተው “እምነትን” እንጂ እየበዛ የሚሄደውን የቤተክርስቲያን ሃብት፣ ንብረት እና ፖለቲካዊ ሥልጣን አይደለም።

ሮሜ 10፡17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።

እግዚአብሔር በቁሳቁስ እና በሃብት ላይ አይደለም ትኩረቱ፤ እግዚአብሔር ማየት የሚፈልገው ሰዎች ምን ያህል ከቃሉ ጋር እንደሚጣበቁ ነው። ሩቅ ቦታ በአልፕስ ተራሮች ውስጥ ተደብቀው የሚኖሩ አማኞች በምድረበዳ ያለችው ቤተክርስቲያን ተብለው የሚጠሩት እነዚህ በፖለቲካዊ ሥልጣን አስገዳጅነት በሕዝቡ ላይ ከተጫነውን የሮም አስተምሕሮ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አጥብቀው ይራመዱ ነበር። እግዚአብሔር ትኩረቱን ሰጥቶ ይመለከት የነበረው እምነት ይህ ነው።

ሮሜ 5፡3-4 ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤

ትዕግሥትን የተማሩት በመከራ ነው። ብዙዎቹ ተገድለዋል፤ ምድራዊ ተስፋቸውም ከንቱ ሆኗል።

እነርሱ አላወቁም እንጂ የጨለማው ዘመን ረጅም ሌሊት ለ900 ዓመታት እንዲዘልቅ ተፈቅዶለታል፤ ከዚያም ወዲያ ለውጥ ይመጣል።

ስለዚህ ከእነርሱ ይጠበቅ የነበረው መታገስ፣ መታገስ እና እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ነው ምክንያቱም የእነርሱ ሰብዓዊ አእምሮ እግዚአብሔር በራሱ ጥበብ ያሰበውን ዓላማ ሊያውቀው አይችልም። የጨለማው ዘመን የሐዋርያቱ የመጀመሪያ ቤተክርስቲያን የዘራችው የእውነት ዘር የተቀበረበት አፈር ነው። ዘር በጨለማ ውስጥ ለመብቀል ጊዜ ይፈጅበታል። በስተመጨረሻ ግን የተቀበረው ዘር ይበሰብስና አዲስ ሕይወት ከአፈሩ ውስጥ ይበቅላል። በጨለማው ዘመን ውስጥ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እውነተኛው ዘር የተቀበረባት አፈር ነበረች። ስለዚህ የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የዘራችው እውነተኛ ዘር ከጨለማው ዘመን አፈር ውስጥ ነው የሚበቅለው።

የኮሉምባ እና የተከታዮቹ ተጽእኖ በዘመናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል። ነገር ግን ከ1300 ዓ.ም በኋላ ትኩረት የሚስቡ እንደ ዋይክሊፍ እና ጆን ሃስ የተባሉ አዳዲስ ስሞች ብቅ አሉ። እነዚህ ሰዎች በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ ያስነሱት ተቃውሞ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንንን ምግባረ ብልሹነት እና ዓለማዊነት ባንገሸገሻቸው ብዙ ሰዎች ዘንድ ጠንካራ እንቅስቃሴ እንዲጀመር አድርጓል።

ከዚያ ብዙ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሳቮናሮላ የተባለ የካቶሊክ መነኩሴ ፍሎረንስ ውስጥ በመነሳት የካሕናቱን ሃብት ማግበስበስ እና ምግባረ ብልሹነት እንዲሁም አምባገነናዊ አመራራቸውን እና ሕዝቡ ላያ የሚያደርጉትን ብዝበዛ አወገዘ። በሮማ ቤተክርስቲያን ላይ ተቃውሞ እየበዛ ሄደ። ሮም ደግሞ እነዚህን በየቦታው የሚለኮሱ የተቃውሞ እሳቶች በማጥፋት ተጠመደች።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሃስን እና ሳቮናሮላን ገደለቻቸው።

ቤተክርስቲያን ጨቋኝ ገዥነቷንና ገናናነቷን ታታቅ ሕንጻዎችን በመገንባት እና የተወሳሰቡ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችን በማብዛት ቀጠለች። ቤተክርስቲያኖች በወርቅ እና በእንቁዎች አሸበረቁ፤ በውብ መጋረጃዎች አጌጡ፤ በእጣን ደመና ታወዱ፤ በሻማ ብርሃን ደመቁ፤ በታላላቅ መሰዊያዎች፣ ውድ በሆኑ ልብሰ ተክሕኖዎች ትልቅ የሙዚቃ መሳሪያዎች ግርግዳዎቻቸው ላይ በተሳሉ ስዕሎችና በብዙ መዘምራን ተዥጎደጎዱ።

ነገር ግን የለውጥ ነፋስ ቤተክርስቲያን ላይ እፍ እያለባት ነበረ። ዋይክሊፍ እና ጆን ሃስ በጊዜያቸው ያጡት ነገር የማተሚያ ማሽንና ርካሽ ወረቀት ነበር።

በግል ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ስለሚገኘው መዳን ብዙ ሰዎች ደስ ብሏቸው መስማት ጀመሩ። ብዙዎቹ ለዘመናት ሲሰበክ የነበረው የቤተክርስቲያን አባል በመሆንና የቤተክርስቲያን ሥርዓቶችን በመፈጸም መዳን የሚለው ትምሕርት አስጠልቷቸው ነበር። የሥርየት ወረቀትን ከቤተክርስቲያን በመግዛት የሐጥያት ሥርየት ማግኘት ይቻላል የሚለው ትምሕርት፤ የመነኮሳት ሥራፈት ሕይወት፣ ጥንታዊ የሐይማኖት ቁሳቁሶች ንግድ እና በሮም ውስጥ የነበረው ምግባረ ብለሹነት በብዙዎች ዘድን ቁጣ ማስነሳት ጀመረ።

ሮም እነዚህን ሁሉ አቤቱታዊች ልታፍን ሞከረች፤ ነገር ግን በሮም ላይ ከተነሳው ተቃውሞ በተጨማሪ የእግዚአብሔር ቃል ፍቅር በሰዎች ልብ ውስጥ እያደገ ነበር፤ ይህም ሁሉ በአንድነት ሊፈነዳ እንደተቃረበ እሳተ ገሞራ እየታመቀ ነበረ።

በ1455 ዓ.ም መጽሐፍ ቅዱስ ጀርመኒ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በጉተንበርግ ከተማ በመጽሐፍ ታተመ።

የሕትመት ሥራ በአውሮፓ ውስጥ ወዲያው በመስፋፋቱ ቴክኖሎጂው በፍጥነት እየተሻሻለ ሄደ። የሕትመት ሥራ በአውሮፓ ውስጥ በታላቅ ፍጥነት ተዛመተ።

በ1453 ዓ.ም ቱርኮች ኮንስታንቲኖፕልን ከተቆጠጠሩ በኋላ ምሑራንና ስደተኞች ጥንታውያን የብራና መጽሐፍ ቅዱሶችን ወደ ምዕራብ አውሮፓ ይዘው መጡ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ ጥንታዊ ሰነዶች ተሰባስቦ መታተም ይችላል። እነዚህ የግሪክ እና የእብራይስጥ ቋንቋ ምሑራን በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ለጥንታዊ ቋንቋዎች ጥናት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

እነዚህ በጥንታዊ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻሕፍት ሕዝቡ ወደሚናገሩቸው ቋንቋዎች ሊተረጎሙ ይችላሉ፤ ስለዚህ ሁልጊዜ እንደ ላቲን ባሉ ሕዝቡ አንብቦ መረዳት በማይችሉዋቸው ቋንቋዎች ተጽፈው አይቀሩም። የሕትመት ማሽን መፈልሰፉ ለሉተር የለውጥ አገልግሎት መሳካት ትልቅ ድጋፍ ሰጥቷል።

ነገር ግን የሮማ ቤተክርስቲያንም ሐብት የመሰብሰብ እና ተቃዋሚዎችዋን የመግደል ሥራዎችዋን በትጋት ቀጠለች።

ፖፕ ኢነሰንት 3ኛው (1198 - 1216) በታሪክ ውስጥ ትልቅ የሚባለውን ሐይማኖታዊ ግድያ እና ጭፍጨፋ አስጀመረ፤ በዚህም ዘመቻው በደቡባዊ ፈረንሳይ ውስጥ የሚኖሩትን አልቢጀንሶች ፈጽሞ አጠፋቸው። በ1204 ዓ.ም በተደረገው አራተኛው የመስቀል ጦርነት ወቅት ገንዘብ ለማሰባሰብ ተብሎ ዛራ የምትባለው ከተማ ሙሉ በሙሉ ተደምስሳለች፤ ከዚያም የክርስቲያኖች ከተማ የሆነችዋ ኮንስታንቲኖፕል ሙልጭ ተደርጋ ተዘርፋለች።

ፖፕ ግሪጎሪ 9ኛው (1227 - 1241) ተቃዋሚ ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች ላይ ከባድ ስቃይ በማድረስ ምርመራ ጀመረ፤ ይህም ምርመራ የሚካሄደው በመናፍቅነት የተጠረጠሩ ሰዎችን አካል በመቆራረጥ እና በእሳት አቃጥሎ በመግደል ነው።

ግፍ እና ግድያ የሐይማኖታዊ ሕይወት አካል ሆኑ።

ከ1200 – 1300 ባሉት ዓመታት ውስጥ ዋልደንሶች በሙሉ ተጨፍጭፈዋል ወይም ከብዙ መኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል። በ1400 ዋልደንሶች ሸሽተው ከስደትና ከግድያ ማምለጥ የቻሉት በአልፕስ ተራሮች ውስጥ ኮቲያን የተባለ ቦታ ተደብቀው ነበር፤ ግን እዚያ ከደረሱ በኋላ ብዙዎቹ በብርድ ሞተዋል።

ሮም ሥልጣንዋን ያገኘችው ከጭካኔ አምላክ ነው እርሱም ሰይጣን ነው።

ሰዎች በ1000 ዓ.ም የዓለም ፍጻሜ የሚመጣ መስሏቸው ነበር፤ በዚህም ምክንያት መሬቶቻቸውን እና ንብረቶቻቸውን በሙሉ ለቤተክርስቲያን ሰጡ። ከዚህም የተነሳ ሮም ሃብቷ እጅግ ጨመረ። ከዚያ በኋላ በፈቃደኝነት የሚሰጡ ስጦታዎችን ቤተክርስቲያን ግዴታ አደረገች። በ1081 ዓ.ም ፖፕ ግሪጎሪ 7ኛው እያንዳንዱ የተጠመቀ ካቶሊክ አማኝ ያለበት ቤት በየዓመቱ ለተባረከው ቅዱስ ጴጥሮስ ግብር እንዲከፍል አደረገ። ግሪጎሪ አሁን በሕይወት ለሌለው ለጴጥሮስ ገንዘብ ሰበሰበለት። በያንዳንዱ ሰው መሬት ላይ 33 ፐርሰንት የሞት ግብር ለቤተክርስቲያን እንዲከፈል ተወሰነበት። በኑፋቄ የተከሰሱ እና የተፈረደባቸው ሃብታሞች ንብረታቸው በቤተክርስቲያን ይወረሳል፤ ከዚያም የተወረሰው ንብረት ለቤተክርስቲያን እና ለመንግሥት ተካፍሎ ይሰጣል። የቤተክርስቲያን እጅግ የተካበተ ሃብት በብዙ ሃገሮች ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ፈጠረ። ንጉሥ ፍራንሲስ ቀዳማዊ ፈረንሳይ ላይ በነገሰበት ጊዜ (1515 – 47 ዓ.ም) 600 መነኩሴዎች፣ ጳጳሶች እና ሊቀ ጳጳሶች በአንድነት ፈረንሳይ ውስጥ በጣም ሰፊ መሬት በመቆጣጠራቸው የተነሳ የሚሰበስቡት ገቢ ንጉሡ ከሚሰበስበው ግብር ጋር እኩል ሆነ።

ከዚያም ፖፑ በገንዘብ የሚሸጥ የሥርየት ወረቀትን አስተዋወቀ። ገንዘብ ለቤተክርስቲያን በመክፈል የሐጥያታችሁን ሥርየት መግዛት ትችላላችሁ ማለት ነው።

ደግሞም ፑርጋቶሪ የሚባል ቦታን ፈጠሩ፤ እርሱም ሙታን ወደ መንግሥተ ሰማያት ከመግባታቸው በፊት ስለ ሐጢያታቸው የሚሰቃዩበት ሥፍራ ነው። ስለዚህ ለቤተክርስቲያን ገንዘብ በመክፈል ሙታን ዘመዶቻችሁ ከፑርጋቶሪ ወጥተው ወዲያው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ ማድረግ ትችላላችሁ። ይህ በቀላሉ ብዙ ገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴ ነው። ቤተክርስቲየን ገንዘብን ከሕያዋንም ከሙታንም ትሰበስብ ነበር። ንግዷም በጣም ተሳካላች።

አሁን ግን ሮም ያላሰበችው ሥጋት መጣባት። የፖለቲካ መሪዎች ቅናተኛ ዓይኖች የሃብቷን ብዛት እያዩ መጎምጀት ጀመሩ። ሃስ ሮምን በተቃወመ ጊዜ የሮምን ምሽግ ለመስበር የሚበቃ ድጋፍ አልነበረውም። ሉተር ሮምን በተቃወመ ጊዜ ግን ብዙ ኃያላን ሰዎች ደግፈውታል ምክንያቱም ሉተርን ከደገፉ ከቤተክርስቲያን ሃብት ላይ ድርሻቸውን ተናጥቀው መውሰድ ያስችላቸዋል። ስለዚህ ቤተክርስቲያን ባላሰበችው መንገድ ለውጡ በተጀመረ ጊዜ ሃብቷ ለውድቀቷ መንገድ አመቻቸ።

መዝሙር 76፡10 ሰው በፈቃዱ ያመሰግንሃልና፥ ከሕሊናቸው ትርፍም በዓልህን ያደርጋሉ

ብዙዎች በሉተር የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች በትክክለኛ ልብ አልነበረም የተሳተፉት፤ ገንዘብ ለማግኘት ብለው ነው። ሆኖም ለሉተር ያደረጉት ድጋፍ ለእግዚአብሔር ተስማሚ ሆኗል ምክንያቱም ያደረጉት ድጋፍ ሉተር ፖፑ የሚሰነዝርበትን ጥቃት እንዲቋቋም አስችሎታል።

ራዕይ 2፡20 ዳሩ ግን፦ ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤

ኤልዛቤል ማለትም የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ኒቆላዊነትን ጀመረች፤ ይህም ከፍ ያለ የሰው መሪ ማለት ነው። ቤተክርስቲያንን ለማሳደግ አመቺ ዘዴ ነው በሚል ሃሳብ ነበር ኒቆላዎነት የተጀመረው፤ ከዚያ በኋላ ግን ማንም እንዲቃወመው የማይፈቀድ አስተምሕሮ ሆነ። ቤተክርስቲያን የመንግሥትን ሥልጣን ተቀበለችና ቀጥላ ደግሞ አረማውነትም አስተናገደች። በዚህ ዘመን የነበረችው የሮማ ቤተክርስቲያን ለሕዝቡ በመሪዋ ማለትም በፖፑ አማካኝነት ዓለምን ሁሉ እንድትገዛ የተላከች አካል መሆኗን የምትነግር ነብይት ሆናለች፤ ምክንያቱም መሪዋ ፖፑ ለወደደው ሰው የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ ለመክፈትና በፈለገው ላይ ለመዝጋት ስልጣን ያለው የጴጥሮስ ተተኪ ነው።
በ1302 ዓ.ም ፖፑ “ኡናም ሳንክታም” (Unam Sanctam) የሚባል አዋጅ አወጀ።
ይህም አዋጅ መዳን የሚቻለው የቤተክርስቲየን አባል ለመሆን ለፖፑ ሥልጣን በመገዛት ብቻ ነው ይላል።
የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሐሰተኛ ትምሕርቶችን የምታስተምር ድርጅት በሆኗ እና ሰዎች ልባቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘወር እንዲል በማድረጓ ሐሰተኛ ነብይ ሆናለች። ጣኦታት ሕይወት የሌላቸው ሐውልቶች ናቸው። በሰው አስተምሕሮ ውስጥ አንዳችም ሕይወት የለም።

ማቴዎስ 15፡9 የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።

ኤልዛቤል የባሏን የአካብን ሥልጣን በመጠቀም የባእድ አምልኮ እና እምነቶችን በአይሁድ ሕዝብ ላይ ጫነችባቸው። በጨለማው ዘመን ውስጥም የአውሮፓ ሕዝብ በግድ፣ በሰይፍ እና በእሳት በማስፈራራት የሮማ ካቶሊክን ሐይማኖት እንዲቀበሉ ጫና ተደርጎባቸዋል።

ሴሰኝነት ወይም ማመንዘር ከጣኦት አምልኮ ጋር ይያያዛል። የካቶሊክ ቤተክርስቲያኖች የክርስቶስ፣ የማርያም፣ የሐዋርያት እና የብዙ ቅዱሳን የተቀረጹ ምስሎች ሞልተውባቸዋል።

ፖፕ ጆን ፖውል ዳግማዊ ብርቱ መሪ ነበር ግን ዘወትር ወደ ማርያም ሐውልት በትጋት ይጸልያል።

ራዕይ 2፡21 ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም።

ይህ ዘመን ለረጅም ጊዜ ቆይቷል ማለትም ለ900 ዓመታት። በዚህ ዘመን ውስጥ በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብዙ አስጸያፊና ገደብ ያለፉ ክፋቶች ተፈጽመዋል፤ ንሰሃ መግባት እንደሚያስፈልጋቸውም በጣም ግልጽ ነበር። እነርሱ ግን ልባቸውን ስላደነደኑ ንሰሃ አልገቡም። ፖፕ ፍራንሲስ እንኳ ኢሰብአዊ ድርጊታቸውን በመጸየፍ በይፋ በ2015 ቱሪን ውስጥ በዋልደንሶች ላይ ስለተፈጸመው ግፍ ይቅርታ ጠይቋል። የጨለማው ዘመን ፖፕ የነበሩት ግን ይቅርታ አልጠየቁም ንሰሃም አልገቡም። በጨለማው ዘመን ስለተፈጸሙ ግድያዎች በሙሉ ንሰሃ በመግባት ፈንታ ለውጡ ሲጀመር የነፍስ ግድያቸው በአውሮፓ ውስጥ በነበሩት ላይ የለውጥ አራማጆች ወይም ፕሮቴስታንቶች ላይ አነጣጠረ። ደግሞም በማዕከላዊ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ የበሩ ኢንዲያኖችም ላይ ግድያቸውን ቀጠሉ፤ የሚገድሏቸው ሰዎችም በጣም በዙ።

ራዕይ 2፡22 እነሆ፥ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፥ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፤

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ራዕይዋ ጠፍቶባት ዓይኖችዋን ምድራዊ ሃብት ላይ፣ ፖለቲካዊ ሸር እና ዓለማዊ ተድላ ላይ አደረገች። ድሎት መንፈሳዊ ቅንአቷን ገደለባት ነገር ግን ቀብሯ ላይ እየሳቀ ሄደባት። ታላቁ መከራ ለሐሰተኛዋ ቤተክርስቲያን መጨረሻዋ ይሆናል። መንፈሳዊ ግልሙትና ሰው ሰራሽ አስተምሕሮን ወደ ልቦና ማሕጸን ውስጥ መቀበልማለት ነው። ሰው ሰራሽ አስተምሕሮ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ስር ከሰደደ በኋላ የሃሳብ ዘር ከመሆን ጀምሮ ያድግና ድርጊቶቻችንን በሙሉ የሚቆጣጠር ተግባር ይሆናል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ተጠናክሮ ልማድ ይሆንና አስተሳሰባችንን በሙሉ የሚገዛ አስተምሕሮ ይሆናል። ይህም የአውሬው ምልክት በሰዎች እጅ ላይ (በሥራዎቻቸው) እና የአውሬው ምልክት እና በግምባራቸው ላይ (የምናስብበት አእምሮ ያለበት ቦታ) ማለት ነው።

ስለዚህ የአውሬው ምልክት ማለት የአእምሮ በሌላ ሃሳብ መወረስ ወይም በአውሬው ትምሕርት መሞላት ማለት ነው። የአውሬውን ምልክት የተቀበለ ሰው የሚባለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምሕርቶችን ሁሉ የሚያምን ሰው ነው። ይህ አይነቱ ሰው ቤተክርስቲያን አድርግ የምትለውን ሁሉ ያደርጋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ ምንም ግድ የለውም።
ነገር ግን የቤተክርስቲያን መሪዎች ብዙውን ጊዜ ሃሳባቸው በዋነኝነት ሃብት መሰብሰብ፤ ስልጣንን ማግኘት እና ንብረት ማግበስበስ እንዲሁም በተድላ ስለመኖር ነበር።

ራዕይ 2፡23 ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።

የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልጆች እነማን ናቸው? የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች የሚወጡት ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲየን ውስጥ ነው። ሮም ጠንካራ የሰዎች አመራር እና በአጥቢያ የመከፋፈል መንፈስ ስለነበራት ፕሮቴስታንቶችም ይህንኑ ልማዷን ለዓመታት ተከትለዋል። ልዩነቱ ፕሮቴስታንቶች ሰዎች የሆኑ መሪዎቻቸውን ፓስተር ብለው መጥራታቸው ነው ማለትም እንደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካሕናት ወይም ቄሶች ብለው አለመጥራታቸው ነው። ከዚያም እያንዳንዱ የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ በሰው ሰራሽ ትምሕርታቸው ዙርያ ተሰባስበው ቤተክርስቲያን ይመሰርታሉ።
መንፈሳዊ ሞት ማለት ከእግዚአብሔር መለየት ነው። የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተጻፈው የሐዋርያት ትምሕርት ርቃ ሄዳለች፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ከቤተክርስቲያኒቱ መንፈሱን አስወገደ። በዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያን አሳፋሪ ብልጽግናን የማሳደድ እና የቤተክርስቲያን መሪዎች የዘቀጡበት አጸያፊ ሕይወት ላይ አንዳችም ገደብ የሚጥል ኃይል አልነበረም። በሥጋ በሕይወት ነበሩ፤ ክርስቲያኖች ነን ይላሉ ነገር ግን በውስጣቸው እግዚአብሔር ትቷቸው ስለሄደ በመንፈስ ሞተዋል።
ሞት ማለት በቀላሉ የተደራጀ ሐይማኖት ነው፤ ይህም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በግል በመተዋወቅ እና ሕብረት በማድረግ ፈንታ የሐይማኖት ሥርዓቶችን መከተል ነው።
የተደራጀ ሐይማኖት በተለያዩ ስሞች በሚጠሩ ቤተክርስቲያኖች ይከፋፈላል። ይህም አይነቱ መከፋፈል በሰዎች መሪነት አማካኝነት ነው የሚስፋፋው፤ የሰዎች መሪነትም ኒቆላዊነት ይባላል።
ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆኑን የመስቀል ጦረኞች ናቸው።
ስለ ኢየሱስ ብለው በስሙ እንደሚገድሉ ይናገራሉ፤ ነገር ግን ከዚያም አልፈው ይዘርፋሉ፣ አስገድደው ይደፍራሉ፤ መሬት እና ብዙ ሃብት ለመሰብሰብ ብለው ብዙ ከተሞችን ያወድማሉ። ለመግደል የነበራቸው ፍላጎት በልባቸው የሞላውን ክፋት የሚያጋልጥ ማስረጃ ነው። “ክርስቲያን ገዳዮች” የሐይማኖት እና የፖለቲካ መርዛማ ቅይጥ ፍሬዎች ናቸው። ሐይማኖት እና ፖለቲካ ሲደባለቁ ምን እንደሚፈጥሩ ለማየት ከእስልምና ሐይማኖት የመጣውን አይሲስን መመልከት በቂ ነው።

ከላይ የተጠቀሰው ቃል ልዩ ልቤተክርስቲያኖችን በተመለከተ ነው የሚናገረው። ከእነዚህ ቤተክርስቲያኖች አንዱ ቅርንጫፍ እውነትን አያውቅም። ይህ ሐሰተኛ የወይን ሐረግ አማኙ ከኢየሱስ ጋር ስለሚኖረው የግል ሕብረት አንዳችም የሚያውቀው ነገር የለም። ኢየሱስ “ልብን” እና “ኩላሊትን” ይመረምራል። ከልባችን ውስጣዊ ስሜታችንን እና ጥልቅ ፍቅራችንን እንገልጻለን። ኩላሊት ደግሞ የልባችንን ስሜት እና ምርጫዎቻችንን የሚመራውን ሃሳባችንን ይወክላል።
ሰዎች ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ቤተክርስቲያናቸውን አብልጠው ወደዱ።
ሰዎች ለገንዘብና ለትርፍ ተንገበገቡ። እግዚአብሔርን ለግል ጥቅምና ለራሳቸው ለሃብት ለማከማቸት ብለው አገለገሉ።
እግዚአብሔር ውስጣዊ ፍላጎታችንን ስለሚያውቅ ለገንዘብ ወይም ለጥቅም ብለን የምናገለግለውን አገልግሎት አይቀበልም። እንድናገለግለው የሚፈልገው ለቃሉ ካለን ንጹሕ ፍቅር የተነሳ ብቻ ነው።
“ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለው።” ይህ አራተኛው ዘመን የጨለማ እና የመሃይምነት ዘመን ነበረ። ክፋት እንደ ልቡ ይሰራ ዘንድ ተፈትቶ የተለቀቀበት ዘመን ነበር። የሰው ሕይወት ርካሽ ነበር። እንደዚህ ሆኖ ግን በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ለመኖር የሞከሩ ሰዎችም ነበሩ። የእነዚህ ሰዎች መልካም ሥራ ውስጣዊ እምነታቸውን ይገልጣል። እነዚህ ሰዎች ከሕዝቡ መካከል ጥቂቶች ሲሆኑ በግልጥ የሚታወቁና ዝነኞች አልነበሩም። ሆኖም ግን ሕይወታቸው ከፍ ያለ የሥነ ምግባርና እና የንጽሕና መለኪያ በመሆኑ የነዚህ ሰዎች ሕይወት በሐጥያትና እግዚአብሔርን ባለመፍራት ለሚመላለሱት ለብዙሃኑ ጠንከር ያለ ተግሳጽ ነበረ።

ራዕይ 2፡24 ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፥

በጨለማው ዘመን የነበረችዋ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የወደቀችበት የክፋት ጉድጓድ እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ሰው ክፋቷን በሙል በዝርዝር ቢያስታውሰው አእምሮውን ሊያረክስ እንደሚችል ሁሉ ይሰማዋል። ታሪክን በሙል ብትመረምሩ በክፋቱና በሥነምግባራዊ ዝቅጠቱ ከቦርጂያው ፖፕ አሌግዛንደር 6ኛው (1492 -1503 ዓ.ም) የሚብስ ሰው ልታገኙ አትችሉም። አሌግዛንደር በስተመጨረሻ የሞተው ድግስ ላይ የጋበዛቸውን እንግዶቹን ሊገድልበት ያዘጋጀውን አርሰኒክ በመጠጥ ውስጥ ቀላቅሎ በመጠጣት ነበር። አስተናጋጆቹ ሳያውቁ መጠጫዎቹን አምታትተው መርዙ ያለበትን መጠጫ ለአሌግዛንደር ሰጡት።
ይህ ዘመን በጣም ረጅም፣ ዘግናኝ እና ብዙ ግፍ የታየበት ዘመን ነበር። ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ እና ለመዳን በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋእትነት ብቻ በግላቸው ቢያምኑ እግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ ይህንን ያመኑ ግን በጣም ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። እነዚህም ሰዎች የትዕግሥትን እና የጽናትን ፈተና ተፈትነው አልፈዋል። እሳቱ ትንሽ ቢሆንም ሳይጠፋ እያበሩት ቆይተዋል። የራሳቸውን ድርሻ ወይም ሃላፊነት በትዕግሥት እና በቆራጥነት ተወጥተዋል።

“የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።” — 1 ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16:23