የዳንኤል 70 ሱባኤዎች
We update studies as the Lord Jesus leads us. You can find the latest update of this study at ChurchAges.net
መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ የጊዜ አቆጣጠር አለው።
በትንቢት ውስጥ አንድ ቀን አንድ ዓመትን ሊወክል ይችላል። (የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት የሚለውን ጥናታችንን ይመልከቱ)
ላባ ለያዕቆብ እንዳለው ያዕቆብ ራሔል የተባለችዋን የላባ ልጅ ማግባት ከፈለገ ተጨማሪ 7 ዓመታት ለላባ ማገልገል አለበት።
ዘፍጥረት 29፡27 ይህችንም ሳምንት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ወር 30 ቀናት ነው።
እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ወር 30 ቀናት መሆኑን እናረጋግጥ።
ራዕይ ምዕራፍ 11 ሁለት ነብያት ወንጌሉን በታላቁ መከራ ዘመን ውስጥ ወደ 144,000 አይሁዳውያን ይዘው የሚሄዱበትን ጊዜ በተመለከተ ነው የሚናገረው።
ራዕይ 11፡2 በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።
3 ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።
ይህ 1,260 ቀን በሌላ አገላለጽ 42 ወራት ይባላል። ስለዚህ በትንቢት ውስጥ እያንዳንዱ ወር 30 ቀናት ነው።
ለዚህ ማረጋገጫ ዘፍጥረት ውስጥ ማግኘት እንችላለን፤ ማለትም የኖህ መርከብ በጥፋት ውሃ ላይ ከተንሳፈፈችበት ቀን ጀምሮ በደረቅ ምድር እስካረፈችበት ቀን ድረስ ያለፉት ቀናት 150 ቀናት ሲሆኑ በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ 5 ወራት ተብለው ተገልጸዋል።
ዘፍጥረት 7፡24 ውኃውም መቶ አምሳ ቀን በምድር ላይ አሸነፈ።
ዘፍጥረት 8፡3 ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እያደር ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ።
ዘፍጥረት 7፡11 በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፥ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ፤
ዘፍጥረት 8፡4 መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች።
ከ2ኛው ወር 17ኛ ቀን ጀምሮ እስከ 7ኛው ወር 17 ቀን ድረስ ያሉት ወራት 5 ወራት ናቸው። ይህ የጊዜ ርዝመት በሌላ መንገድ 150 ቀናት ተብሎ ተገልጾአል። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ አንድ ወር ማለት 30 ቀናት ነው።
ዳንኤል ስለ 70 ሱባኤ የተናገረው ትንቢት የጀመረው መች ነው?
የተጀመረው የፋርስ ንጉስ ትዕዛዝ ባወጣ ጊዜ ነው።
የወጡት ትዕዛዛት ሶስት ነበሩ።
1. መጀመሪያ ቤተመቅደሱ እንዲገነባ።
2. ሁለተኛው ትዕዛዝ ዕዝራ የቤተመቅደሱን እቃዎች ወደ ቤተመቅደሱ እንዲመልሳቸው።
3. ሶስተኛ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ከተማ መልሶ እንዲገነባ እና ከቅጥሯ በሮች ጋር የሚጋጠሙ ጎዳናዎችን እንዲያድስ።
እነዚህ ሁሉ የተከናወኑባቸው ዓመታት የተወሰዱት ከመደበኞቹ ኢንሳይክሎፒዲያዎች ነው። በቤተክርስቲያን የተጻፉ መጽሐፎችን አልተጠቀምንም ምክንያቱም እነርሱ በብዛት የራሳቸውን አመለካከት ለመደገፍ ብለው ቀኖችንና አመታትን ያጠጋጋሉ።
የመጀመሪያው ትዕዛብ በ536 ዓመተ ዓለም ንጉስ ቂሮስ ቤተመቅደሱ እንዲገነባ ያወጣው ትዕዛዝ ነው።
ዕዝራ 1፡1 በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ፦
2 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤
3 ከሕዝቡ ሁሉ በእንናተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤
የታሪክ ምሑራን እንደሚሉት ይህ አዋጅ የታወጀው በ536 ዓመተ ዓለም ነው፤ ብዙ ከዘገየ በኋላ በስተመጨረሻ በነብዩ ሃጌ እና በነብዩ ዘካርያስ አበረታችነት ቤተመቅደሱ በ515 ዓመተ ዓለም ተገነባ።
ዕዝራ 5፡1 ነቢያቱም ሐጌና የአዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁድ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው።
ዕዝራ 6፡15 ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ።
በዚህ ጊዜ ቤተመቅደሱ ተገንብቶ ተጠናቋል።
ሁለተኛው ትዕዛዝ ለዕዝራ የተጻፈ ደብዳቤ ሲሆን ዓላማውም በኢየሩሳሌም ውስጥ የተገነባውን ቤተመቅደስ ለማስዋብ ውድ የሆኑ እቃዎችን ዕዝራ እንዲወስድ ነው።
ዕዝራ 7፡11 ንጉሡም አርጤክስስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዓት ይጽፍ ለነበረው ለጸሐፊው ለካህኑ ለዕዝራ የሰጠው የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው።
ዕዝራ 7፡12 ከንጉሠ ነገሥት ከአርጤክስስ ለሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ለዕዝራ፥ ሙሉ ሰላም ይሁን፤
15 ንጉሡንና አማካሪዎቹም መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው ያቀረቡትን ብርና ወርቅ፥
16 በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ትወስድ ዘንድ በንጉሡና በሰባቱ አማካሪዎች ተልከሃልና
17 ስለዚህ በዚህ ገንዘብ ወደፈኖችንና አውራ በጎችን ጠቦቶችንም የእህላቸውንና የመጠጣቸውን ቍርባን ተግተህ ግዛ፤ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው።
18 ከቀረውም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ ለማድረግ ደስ የሚያሰኛችሁን ነገር እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አድርጉ።
19 ስለ አምላክህም ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አሳልፈህ ስጥ።
20 ከዚህም በላይ ለማውጣት የሚያስፈልግህን ለአምላክህ ቤት የሚያሻውን ነገር ከንጉሡ ቤተ መዛግብት አውጣ።
21 እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ላሉት በጅሮንዶች ሁሉ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። የሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ካህኑ ዕዝራ ከእናንተ የሚፈልገውን ሁሉ አዘጋጁለት፤
22 እስከ መቶ መክሊት ብርም ቢሆን፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት ቢሆን፥ ጨውም ያለ ልክ ቢሆን ስጡ።
ይህ ደብዳቤ የተሰጠው መች ነበር?
ዕዝራ 7፡8 በንጉሡም በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ።
ዘርክሲስ ቀዳማዊ በ465 ዓመተ ዓለም ተገደለ፤ ከዚያም ልጁ አርጤክስስ በእርሱ ቦታ ነገሰ።
ንጉሱ የተገደለበት ዓመት አጨቃጫቂ ነው። ብዙዎቹ ኢንሳይክሎፒዲያዎች በ465 ዓመተ ዓለም ነው ይላሉ። ሁሉም ሳይሆኑ አንዳንድ የክርስቲያን ማጣቀሻ መጻሕፍት ደግሞ ዓመቱ 464 ዓመተ ዓለም ነው ይላሉ። ነገር ግን አንዳንድ ክርስቲያን ምሑራን ሌሎች ሰዎች እንዲበሉዋቸው የሚፈልጉት ጠንካራ አመለካከት አላቸው። እነርሱም ዓመቱን የሚተምኑት የራሳቸውን የትንቢት አተረጓጎም እንዲደግፍላቸው አድርገው ነው። ስለዚህ መደበኛዎቹ ኢንሳይክሎፒዲያ በሚነግሩን መረጃ እንጠቀማለን።
Year BC | 465 | 464 | 463 | 462 | 461 | 460 | 459 |
Year of rule | 1st | 2nd | 3rd | 4th | 5th | 6th | 7th |
ስለዚህ በ459 ዓመተ ዓለም ዕዝራ ትዕዛዝ ተቀብሎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ተነሳ።
ንጉስ ቤተመቅደሱን ለማስዋብ ስለሰጠው ስጦታ ዕዝራ ለእግዚአብሔርን የመጨረሻውን ምስጋና ያቀርባል።
ዕዝራ 7፡27 በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ያሳምር ዘንድ እንደዚህ ያለውን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ … የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ።
የፈረሱትን የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ስለማደስ ምንም የተባለ ነገር አልነበረም። በር የሚያስፈልጋቸውን እና ከቅጥሮቿ ጋር የሚገናኙትን አውራ ጎዳናዎች ስለመስራትም የተባለ ነገር አለነበረም።
የዳንኤል ትንቢት እንዲህ ይላል፡-
ዳንኤል 9፡25 ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።
ስለዚህ በፋርስ ንጉስ የተሰጠው ሶስተኛ ትዕዛዝ ብቻ ነው እነዚህን ሁኔታዎች የሚያሟላው።
ይህም ንጉሱ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንዲሰራ ለነህምያ ፈቃድ የሰጠበት ጊዜ ነው።
ነህምያ 1፡2 እኔ በሱሳ ግንብ ሳለሁ፥ ከወንድሞቼ አንዱ አናኒ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሰዎች ከይሁዳ መጡ፤ እኔም የዳኑትን ከምርኮ የተረፉትን የአይሁድን ነገር የኢየሩሳሌምንም ነገር ጠየቅኋቸው።
3 እርሱም፦ በዚያ ስፍራ ያሉት ከምርኮ የተረፉት ቅሬታዎች በታላቅ መከራና ስድብ አሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈርሶአል፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል አሉኝ።
በሮቹ በከተማይቱ ዙርያ በተሰሩት አጥሮች ውስጥ ጎዳናዎቹ የሚያልፉባቸው ቦታዎች ናቸው።
ነህምያ 2፡1 በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር።
ነህምያ 2፡4 ንጉሡም፦ ምን ትለምነኛለህ? አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ።
5 ንጉሡንም፦ ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፥ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶቼ መቃብር ከተማ ስደደኝ አልሁት።
ነህምያ የፈረሰችውን ከተማ መልሶ መስራት ማደስ ፈለገ።
ዳንኤል 9፡25 … ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ …
ነህምያ 2፡7 ንጉሡንም፦ ንጉሡ ደስ ቢለው፥ እስከ ይሁዳ አገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ ማዶ ላሉት ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤
8 በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ አልሁት። ንጉሡም በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነችው እንደ አምላኬ እጅ ሰጠኝ።
9 በወንዙም ማዶ ወዳሉት አለቆች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤ ሰጠኋቸው፤ ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ሰደደ።
የንጉሱ ደብዳቤዎች ገዥዎች ለኤርምያስ ኢየሩሳሌምን መልሶ ይገነባ ዘንድ እንዲፈቅዱ ትዕዛዝ የሚሰጡ ነበሩ። ዋነኛ ሃሳቡ በከተማይቱ ዙርያ ለሚቆሙት ቅጥሮች ነበር።
ነህምያ 2፡13 በሸለቆውም በር ወጣሁ፥ ወደ ዘንዶውም ምንጭና ወደ ጕድፍ መጣያው በር ሄድሁ፤ የፈረሰውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፥ በእሳትም የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትሁ።
በሃሳቡ ውስጥ ትልቁን ስፍራ የያዙት ቅጥሮች ናቸው። ማንኛይቱም ከተማ ያለ ቅጥር ራሷን መከላከል አትችልም።
ነህምያ 2፡17 እኔም፦ እኛ ያለንበትን ጕስቍልና ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ አልኋቸው።
ዳንኤል እንዲህ ነበር ያለው።
ዳንኤል 9፡25 … እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።
ቅጥሮቿ እና ለጎዳናዎቿ የሚያስፈልጓት በሮች በጭንቅ ወራት ነው የሚሰሩት።
ስለ አስጨናቂዎች መኖር ምን ማስረጃ እናገኛለን? ቅጥሮችን የሚገነቡ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ሰዎች ናቸው።
ነህምያ 4፡16 ከዚያም ቀን ጀምሮ እኵሌቶቹ ብላቴኖቼ ሥራ ይሠሩ ነበር፥ እኵሌቶቹም ጋሻና ጦር ቀስትና ጥሩርም ይዘው ነበር፤ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር።
17 ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር።
18 አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ።
በአንድ እጃቸው ጡብ ይይዛሉ። በሌላ እጃቸው ደግሞ የጦር መሳሪያ ይይዛሉ። ሰይፋቸውንም ወገባቸው ላይ አድርገው ሥራቸውን ይሰራሉ። ድንገት በሌሊት ጥቃት ቢሰነዘርብን ብለው ሲተኙ እንኳ ከነልብሳቸው ይተኙ ነበር። ምክንያቱም ተነስተው ልብሳቸውን የሚለብሱበት ጊዜ አይኖራቸውም።
ነህምያ 4፡23 እኔና ወንድሞቼም ብላቴኖቼም በኋላዬም የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር።
ለነህምያ የተሰጠው ይህ ትዕዛዝ በተፈጸመ ጊዜ ነህምያ የዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱ ሁኔታዎችን በሙሉ አሟልቶ ተገኘ።
መች ነበር ለነህምያ ፈቃድ የተሰጠው? በአርጤክስስ መንገስት በሃየኛው ዓመት።
ነህምያ 2፡1 በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር።
Year BC | 465 | 464 | 463 | 462 | 461 | 460 | 459 |
Year of rule | 1st | 2nd | 3rd | 4th | 5th | 6th | 7th |
Year BC | 458 | 457 | 456 | 455 | 454 | 453 | 452 |
Year of rule | 8th | 9th | 10th | 11th | 12th | 13th | 14th |
Year BC | 451 | 450 | 449 | 448 | 447 | 446 |
Year of rule | 15th | 16th | 17th | 18th | 19th | 20th |
ስለዚህ በ446 ዓ.ም ኢየሩሳሌም ለማደስ እና ለመስራት ትዕዛዝ ወጣ። ስለዚህ ከዚህ ዓመት ነው ቆጠራ መጀመር ያለብን።
የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዓመቶች 360 ቀናት ናቸው
ቀጣዩ ውስብስብ ነገር ደግሞ ይህ ነው፡- የትንቢት ወር 30 ቀናት ከሆነ የትንቢት ዓመት 12 x 30 = 360 ቀናት ነው እንጂ 365.24 ቀናት አይደለም።
ነብዩ ዳንኤል ስለ ክርስቶስ ተቃዋሚው አሰራር ሲናገር እንዲህ አለ፡-
ዳንኤል 7፡25 በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።
ምድር በዛቢያዋ ላይ ቀጥ ብላ ነበር የቆመችው፤ እያንዳንዱ ዓመትም በ360 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቅ ነበር። በኖህ ዘመን በመጣው የጥፋት ውሃ ጊዜ እግዚአብሔር ምድርን ከፀሃይ ለጥቂት ጊዜ ፈቀቅ ስላደረጋት ሕዋ ውስጥ ካለው ከፍተኛ ቅዝቃዜ የተነሳ ከሰማይ የወረደው ውሃ እንዲሁም ከምድር ውስጥ በፈለቀውም ውሃ ወደ በረዶነት ተለወጠ። ይህም የበረዶ ዘመን እንዲጀምር ምክንያት ከመሆኑም በላይ እግዚአብሔር ምድርን አሁን ወዳለችበት ምሕዋር ከመለሳት በኋላ እንኳ ለረጅም ዘመናት እስካሁን ድረስ በዋልታዎች አካባቢ የተጋገረው በረዶ ሳይቀልጥ እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል። ምድር አሁን በፀሃይ ዙርያ የምትሄድበት ምሕዋር መጀመሪያ ትሄድበት ከነበረው ምሕዋር በለጥ ያለ ነው።
በደቡብ ዋልታ ያለው የበረዶ ግግር በሰሜን ዋልታ ካለው የበረዶ ግግር አስር እጥፍ ይበልጣል፤ ምክንያቱም በደቡብ ዋልታ ያለው በረዶ ከስሩ መሬት አለ፤ ይህም ታላቁ የአንታርክቲካ አሕጉር ነው። ሰሜን ዋልታ ላይ ግን ሙሉ በሙሉ ባሕር ነው።
ግግር በሰሜን ዋልታ እና በደቡብ ዋልታ አለመመጣጠኑ ምድር በዛቢያዋ ላይ 23½ ዲግሪ እንድታጋድል አድጓታል።
ምድር የምትዞርበት ምሕዋር ተለቅ በማለቱ ምክንያት የምድር ዓመት ረዘም ብሎ ወደ 365.24 ቀናት ከፍ ሊል ችሏል።
ይህ እግዚአብሔር የወሰደው ጊዜአዊ እርምጃ ነው። በታላቁ መከራ ወቅት እግዚአብሔር ምድርን ወደ ፀሃይ ጠጋ ስለሚያደርጋት በሚፈጠረው ታላቅ ሙቀት በዋልታዎች ላይ የተጠራቀመው የበረዶ ግግር ሲቀልጥ ኢየሱስ የ1,000 መንግስት ሊመሰርት በሚመጣ ጊዜ ምድር በዛቢያዋ ላይ ምንም ሳታጋድል ቀጥ ብላ ትቆማለች።
ራዕይ 16፡8 አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት።
9 ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፥ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፥ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም።
ስለዚህ የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ የዓመትን ርዝመት ከ360 ቀናት ወደ 365.24 ቀናት እንዲለውጥ እግዚአብሔር ፈቀደለት። ይህም የተደረገው ሮም ውስጥ ነው። ሮማዊው አምባገነን ንጉስ ዩልየስ ቄሳር በ46 ዓመተ ዓለም ላይ 67 ቀናትን ጨመረ፤ ከዚህም የተነሳ ያ ዓመት 445 ቀናት ሆነ። ሮማውያን ከፌብሩዋሪ ወር በስተቀር ሌሎች ወራት ሁሉ 30 እና 31 ቀናት እንዲሆኑ አደረጉ። ከዚያ በኋላ በ1582 ፖፕ ግሪጎሪ 13ኛው 10 ቀናትን በመቀነስ ጳጉሜ ስድስት ቀናት የምትሆንበትን በፈረንጆቹ አጠራር ሊፕ ይር የምትባለዋን ዓመት በመጨመር ካላንደርን አስተካከለ፤ ይህም በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የሚመጣው ዓመት ቁጥሩ ሁልጊዜ በ400 ሊካፈል የሚችል ነው (ለምሳሌ 1600 ወይም 2000 ሊሆን ይችላል ግን 1900 አይሆንም)።
ይህም አንድ ከባድ ችግር ያመጣብናል። አይሁዳውያን ብሉይ ኪዳንን ብቻ ነው የሚታዘዙት። መሲሁ ከመወለዱ 45 ዓመታት በፊት የተለወጠውን ካላንደር አይሁዳውያን አይጠቀሙበትም። በተለይም ደግሞ እነርሱ አምርረው የሚጠሏቸው ጠላቶቻቸው ሮማውያን የለወጡትን የዘመን አቆጣጠር አይሁዳውያን አይቀበሉም። ፖምፔይ የተባለው ሮማዊ ጀነራል አይሁዶችን ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረው በ63 ዓ.ም እነርሱ በሰንበት አንዋጋም ባሉበት ቀን ጥቃት በመሰንዘር ነው።
ስለዚህ አይሁዳውያን ዘፍጥረት ውስጥ በተጻፈው መሰረት በኖህ ዘመን አንድ ወር 30 ቀን እንዲሆን በተወሰነው መሰረት መቁጥር ቀጠሉ።
አሁን እኛ የምንጠቀመው ባለ 365.24 ቀናት ዓመት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚታወቀው ባለ 360 ቀናት ዓመት በ5.24 ቀናት ይረዝማል።
ስለዚህ እኛ በ70 ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 70 x 5.24 = 367 ትርፍ ቀናት አሉን፤ ይህም አንድ ተጨማሪ ዓመት ነው። ስለዚህ በቀላሉ ማየት እንደምንችለው እኛ 70 ዓመታት ብለን የምንቆጥረው ከመጽሐፍ ቅዱስ 71 ዓመታት ጋር እኩል ነው።
ስለዚህ “ሰባ ሳምንታት” ማለት 70 x 7 = 490 ወይም 490 የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመታት ማለት ነው።
ነገር ግን በየ70 ዓመታቱ እኛ ከትንቢታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ዓመት በአንድ ዓመት ወደ ኋላ እንጎተታለን። ስለዚህ በ70 x 7 ዓመታት ውስጥ የእኛ ረጃጅም ዓመታት በ 7 ዓመት ወደኋላ ይቀራሉ። በእኛ የዘመን አቆጣጠር ወይም ካላንደር መሰረት “ሰባ ሳምንታት” ማለት 490 ዓመታት - 7 = 483 ዓመታት ማለት ነው።
ከሰባው ዓመታት ውስጥ የመጨረሻው ሳምንት (የመጨረሻዎቹ ሰባት ዓመታት) የመሲሁ አገልግሎት ሳምንት ነው።
ስለዚህ መሲሁ እስኪመጣ ድረስ ስንት ዓመታት ነበሩ የቀሩት? 483 – 7 = 476 ዓመታት።
መሲሁ የሚመጣው መች ነው?
ብዙዎቹ ኢንሳይክሎፒዲያዎች በሚሉት መሰረት እስከ መሲሁ መወለድ ድረስ የቀሩትን ዓመታት መቁጠር የተጀመረው በ446 ዓመተ ዓለም ነው።
ስለዚህ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩት 446 ዓመታት ሲቀነሱ ስንት ዓመታት ይቀራሉ?
476 – 446 = 30 ዓመታት። ይህም ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረበት ዕድሜው ነው።
ሉቃስ 3፡1 ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት …
2 ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ።
ጢባርዮስ ንጉስ ተብሎ የተሾመው የሮማ መንግስት ምክር ቤት በ14 ዓ.ም ከንጉስ አውግስጦስ መሞት በኋላ ነው።
አውግስጦስ ጢባርዮስን እንደ ልጁ አድርጎ በማደጎ አሳደገው። በ12 ዓ.ም አውግስጦስ አብሮት ይገዛ ዘንድ ጢባርዮስን ሾመው፤ ግን ይህን ማድረጉ ኋላ ጥባርዮስ በእርሱ ቦታ እንዲነግስ ዋስትና አልነበረም። አውግስጦስ እንደ ንጉስ ይገዛ ነበር፤ ነገር ግን ንጉስ አይደለሁም እያለ ይቀልድ ስለነበረ በማደጎ ያሳደገው ልጅ እርሱን ተክቶ መንገስ አይችልም። በተጨማሪ ደግሞ አውግስጦስ አግሪጳ ፖሰቱመስ የሚባል የልጅ ልጅ ስለነበረው እርሱም አውግስጦስ ሲሞት መንገስ ይገባኛል ብሎ መፎካከር መብት ነበረው። ስለዚህ በ14 ዓ.ም አውግስጦስ ሲሞት አግሪጳ ፖስቱመስ ወዲያው ተገደለና ምክር ቤቱ ጥባርዮስ እንዲነግስ ጥያቄ አቀረበለት። በመጀመሪያ እያመነታ “እምቢ” አለ ከረጅም ጊዜ በኋላ ግን “እያንገራገረ” እሺ አለ።
ስለዚህ የጥባርዮስ የንግስና አስራ አምስተኛ ዓመት 14 + 15 = 29 ዓ.ም ነበረ። ያም መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎቱን የጀመረበት ዓመት ነው።
ሉቃስ 3፡23 ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር
“30 ያህል” ። 30 ዓመት አናቱ ላይ አይደለም። ይህ የሆነው በ29 ዓ.ም ማለቂያ አካባቢ ነው።
ዮሐንስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ ዕድሜው ይህን ያህል ነበረ፤ በእርሱም ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደበትና ቀባው።
መንፈስ ቅዱስ ወደ ውስጡ አልገባም፤ በእርሱ ላይ አረፈበት እና ኖረበት።
ዮሐንስ 1፡32 ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ።
33 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።
በሕዝብ ፊት በአደባባይ መቀባቱ “የተቀባው” ማለትም (በግሪክ) ክርስቶስ ወይም (በዕብራይስጥ) መሲህ እርሱ መሆኑ መለየት አስችሏል።
ሉቃስ 3፡22 መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።
ማነው የተናገረው? እግዚአብሔር አብ ነው።
ማቴዎስ 1፡20 እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።
በሴት ማሕጸን ውስጥ የሕይወትን ዘር የሚያስቀምጥ ሁሉ የሕጻኑ አባት ነው። የኢየሱስን ሥጋዊ አካል ያዘጋጀው መንፈስ ቅዱስ ነው። ስለዚህ የኢየሱስ አባቱ መንፈስ ቅዱስ ነው።
መንፈስ ቅዱስ ነው ለኢየሱስ አባት እንደመሆኑ “የምወደው ልጄ” ብሎ የተናገረው።
በወልድ ላይ ይህን ያህል ትኩረት መደረጉ እርሱ መሲሁ አለቃው መሆኑን ያሳያል።
ዳንኤል 9፡25 ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።
መሲሁ አለቃው የሚለው መጠሪያ የሚያመለክተው በ29 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ አገልግሎቱን የጀመረበትን ጊዜ ነው።
በአገልግሎቱ ማብቂያ አካባቢ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉስ ተብሎ ተወድሷል። አለቃ ከመሆን አልፎ ንጉስ ሆኗል።
ዘካርያስ 9፡9 አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።
የኢየሱስ አገልግሎት ለምን ያህል ዘመን ነበር?
የአይሁዶች ዓመት ሁለት ሁለት ወራት ተደርጎ በስድስት ክፍለ ዓመት የተከፋፈለ ነበር። እያንዳንዱ ክፍለ ዓመት በወሩ አጋማሽ አካባቢ ይጀምርና ይፈጸማል።
Seed time | Winter | Spring | Harvest | Summer | Extreme heat |
Oct, Nov | Dec, Jan | Feb, March | April, May | June, July | Aug, Sept |
በየዓመቱ የሚከበሩ ሰባት በዓላት ነበሩ።
የመጀመሪያው በዓል ፋሲካ ነበር፤ ሁለተኛው ደግሞ በማርች ወር አጋማሽ (በፈረንጆቹ ፀደይ ወቅት) የሚከበረው የቂጣ በዓል ነበር።
የበኩራት በዓል የሚከበረው ሚያዝያ ወር ውስጥ ሲሆን ይህም መከሩ መታጨድ የሚጀምርበት ወቅት ነው።
በግንቦት ደግሞ የጴንጤቆስጤ በዓል ነው የሚከበረው።
መስከረም ወይም ጥቅምት ውስጥ ሶስት በዓላት ይከበራሉ -- የስርየት በዓል፣ የመለከት በዓል፣ እና የዳስ በዓል ናቸው -- እነዚህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚከበሩ በዓላት ናቸው።
ዮሐንስ 2፡13 የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
ይህ ከኢየሱስ የውሃ ጥምቀት በኋላ የመጀመሪያው ፋሲካ ነው፤ ስለዚህ ቀኑ በ30 ዓ.ም ማርች ወር ውስጥ፤ እርሱ ከተጠመቀ ከጥቂት ወራት በኋላ ነው።
ከላይ ባለው ጥቅስ ውስጥ ከተጠቀሰው ከ30 ዓ.ም ፋሲካ በኋላ ኢየሱስ ሰማርያ ውስጥ በሲካር ከተማ አለፈ።
ከሳምራውያኑ ጋር ሲያወራ የእርሻቸው መከር ሊደርስ አራት ወራት እንደቀሩ ይነግራቸዋል።
ዮሐንስ 4፡5 ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤
ዮሐንስ 4፡35 እናንተ፦ ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን?
በሚያዝያ አጋማሽ ከመከር ወቅት አራት ወራት አስቀድሞ ማለት ታህሳስ አጋማሽ አካባቢ ነው። ስለዚህ ይህ ወቅት የ30 ዓ.ም ማለቂያ አካባቢ ነው። የ30 ዓ.ም በዓለት በሙሉ ተከብረው ተጠናቅቀዋል።
ዮሐንስ 5፡1 ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
ይህ ሊሆን የሚችለው በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ31 ዓ.ም ነው ምክንያቱም በታህሳስ እና በየካቲት መካከል አንዳችም በዓል የለም።
በዮሐንስ ምዕራፍ 5 ውስጥ የተመዘገበው ይህ በዓል የዋለው ኢየሱስ ወደ ሲካር ከመጣ በኋላ ሲሆን ፋሲካ ወይም ከበዓላቱ አንዱ ሊሆን ይችላል። ሌላ በዓል ከሆነ የፋሲካ በዓል ከዚህ በዓል በፊት ቀድሞ ተከብሯል ማለት ነው። የፋሲካ በዓል ሁልጊዜ በዓመቱ ውስጥ የመጀመሪያው በዓል ነው። ስለዚህ በዚያ ዓመት ፋሲካ መከበሩ ግድ ነው።
ስለዚህ ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ (ዮሐንስ 5፡1) የ31 ዓ.ም የፋሲካ በዓል ይሆናል፤ አለዚያም በ31 ዓ.ም ውስጥ ከተከበሩ ሌሎች በዓላት አንዱ ይሆናል። ያም
ሆነ ይህ በ31 ዓ.ም ውስጥ ፋሲካ ሳይከበር አላለፈም።
አሁን ቀጥሎ ወደተከበረው የፋሲካ በዓል ስንመጣ ቀጣዩ ፋሲካ በ32 ዓ.ም ነው የተከበረው። በያንዳንዱ ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ፋሲካ የሚከበረው።
ዮሐንስ 6፡4 የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር።
ከዚህ ቀጥሎ የምናገኘው በአገልግሎት ዘመኑ ማቂያ በ33 ዓ.ም የተከበረውን የመጨረሻውን ፋሲካ ነው።
ዮሐንስ 11፡55 የአይሁድም ፋሲካ ቀርቦ ነበር። ብዙ ሰዎችም ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከፋሲካ በፊት ከአገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።
30 AD 31 AD 32 AD 33 AD
እያንዳንዱ የፋሲካ በዓል በዓመት ያህል ይራራቃል። በአራት ፋሲካዎች መካከል የሶስት ዓመት ሶስት ክፍተቶች አሉ።
ስለዚህ ኢየሱስ ቢያንስ ለሶስት ዓመታት አፈልግሏል።
ከዚያም እርሱ ከተጠመቀ በኋላ 40 የፈተና ቀናት መጡ፤ ከትንሳኤውም በኋላ ደግሞ ለ40 ቀናት ለተለያዩ ሰዎች ተገልጦ ታየ። እነዚህ 80 ቀናት ሲጠጋጉ ሶስት ወር ያህል ይሆናሉ።
ከመጀመሪያው የ30 ዓ.ም ፋሲካ በፊት ጥር፣ የካቲን እና የመጋቢት ግማሽ ሲደመሩ ሁለት ከግማሽ ወራት ይጨምሩለታል። ይህም ተደማምሮ 3 + 2½ = 5½ ወራት ይሰጠናል።
ስለዚህ የአገልግሎት ዘመኑ 3½ ዓመት እንዲሞላለት ከ39 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የአንድ ወር ግማሽ ብቻ ነው መጨረር የሚያስፈልገው።
ስለዚህ የኢየሱስ አገልግሎት ከመጨረሻው ሱባኤ ላይ የመጀመሪያው ግማሽ ነው።
የመጨረሻው የሱባኤ እኩሌታ
ይህ ከመጨረሻው ሰባት ዓመት ውስጥ 3½ ዓመት ነው፤ አይሁዶች ከቀራንዮ ጀምሮ ተገለሉ ምክንያቱም መሲሃቸውን አልቀበልም ብለዋል። ነገር ግን ያልተጠቀሙበት 3½ ዓመት እስካሁን ድረስ አለ።
የአይሁዶች ሊቀካሕናት ሰማያዊ ቀሚስ ነው የሚለብው፤ በአንገቱም ዙርያ ያማረ ስፌት አለው።
የመጀመሪያውም ሊቀካሕናት አሮን ነበረ።
ዘጸአት 28፡30 በፍርዱ በደረት ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል።
31 የኤፉዱንም ቀሚስ ሁሉ ሰማያዊ አድርገው።
32 ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት።
ጥሩር ማለት በአንገት እና በወገብ መካከል የሚለበስ የብረት ልብስ ነው።
ሊቀካሕናቱ ቀያፋ የራሱን ልብስ ከቀደደ በኋላ በኢየሱስ ላይ ፈረደበት።
ማቴዎስ 26፡65 በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ፦
ስለዚህ ሊቀካሕናቱ የራሱን ልብስ በመቅደድ ሕጉን ተላለፈ፤ እግዚአብሔርም የቤተመቅደሱን መጋረጃ በመቅደድ ምላሽ ሰጠ።
ማቴዎስ 27፡51 እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤
በዚህ ሰዓት የመጨረሻዎቹ ሰባት ዓመታት እኩሌታ በደረሰ ጊዜ የአይሁዶች ሕግ ከጥቅም ውጭ ሆነ።
የእንስሳት መስዋእቶችም ከዚያ ወዲያ ወጋቸውን አጡ። ከዚያ ወዲያ ምንም ተቀባይነት አልነበራቸውም። ቢያቀርቧቸውም እንኳ በከንቱ እያስመሰሉ ነበር።
ዳንኤል 9፡27 እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።
“በእርኩሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል” ፡- ቤተመቅደሱ አገልግሎቱ አብቅቷል። መዳን ከዚህ ወዲያ በክርስቶስ መስቀል ብቻ ነው የሚገኘው።
ስለዚህ በ70 ዓ.ም ክርስቶስን የሰቀሉት ሮማውያን ቤተመቅደሱን እና ኢየሩሳሌምን አፈራረሱ። መስዋእት ለማቅረብ ማስመሰል እንኳ ቀረ። ቤተመቅደሱ የነበረበት ቦታ ሙሉ በሙሉ ወደመ። አንድ ድንጋይ እንኳ በሌላ ድንጋይ ላይ አልቀረም።
በ135 ዓ.ም ሃድሪያን የተባለው የሮም ገዥ ባር ኮችባ የተባለውን የአይሁዶች አመጽ ደምስሶ ከተማይቱን በድጋሚ አወደማት፤ አይሁዶችንም ከኢየሩሳሌም አባረራቸውና ትራጃን የሚመለክበትን የጁፒተር ካፒቶሊነስ ቤተመቅደስ በመስራት የመጨረሻውን እርኩሰት ፈጸመ። ከቤተመቅደሱም ፊት ለፊት በፈረስ ላይ ተቀምጦ የሚታይበትን የራሱን ሃውልት አቆመ።
በ325 ዓ.ም ሮማዊው ገዥ ኮንስታንቲን ቤተክርስቲያንን ተቆጣጠራት፤ የጁፒተርን ቤተመቅደስ አፈረሰና ቤተመቅደሱ በነበረበት ተራራ ላይ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ሰራበት። ይህ ዓይነቱም ዲኖሚኔሽናዊ ጥመት ተስፋፍቶ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት ላይ ጥፋትን አድርሷል። ይህ ጥፋት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሳይሆን ቤተክርስቲያን የተናገረችውን እንድታምኑ የሚፈልግ ነው።
በ700 ዓ.ም ሙስሊሞች ቤተመቅደሱ በነበረበት ቦታ ዶም ኦቭ ዘሮክ የተባለውን መስጊድ ሰሩበት። ቁርአንን በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚቃወሙ የመጽሐፍ ቅዱስ እምነት እየጠፋ ይሄዳል።
“እስከ ተቆረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሰፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል” ፡ ዶም ኦቭ ዘሮክ እስከ ዛሬ ድረስ ለ1,300 ዓመታት በቤተመቅደሱ ተራራ ላይ ቆሟል። ይህ ጥፋት ዓለም ሁሉ ወደ ታላቁ መከራ ውስጥ እስኪገባ ድረስ እስከ መጨረሻው ይቀጥላል።
“መቅሰፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል” ፡ አይሁዶች ጥፋት ወርዶባቸዋል። ንጉስ ሃድሪያን ከኢየሩሳሌም አባሯቸዋል። በብዙ ሃገራት ውስጥ ያለማቋረጥ ተሰድደዋል፤ ከብዙ ሃገሮች ተባርረዋል፤ እንደ ለማኝ በቆሻሻ ላስቲክ ቤቶች ውስጥ ለመኖር ተገድደዋል፤ ብዙ ጭፍጨፋዎች ውስጥ ተገድለዋል፤
“በክርስቲያን” የመስቀል ዘማቾች ተዘርፈዋል፤ ተደፍረዋል፤ በ70 ዓ.ም ሮማዊው ጀነራል ታይተስ ኢየሩሳሌምን ባፈረሰ ጊዜ 1.1 ሚሊዮን አይሁዶች ተጨፍጭፈዋል፤ 6 ሚሊዮን አይሁዶች በሒትለር ዘመናዊ የሞት ካምፖች ውስጥ ተገድለዋል።
አይሁዶች እንደምንም ታግለው በ1948 ዓ.ም ወደ ተስፋይቱ ምድራቸው ከተመለሱ በኋላ አራት ታላላቅ ጦርነቶች ውስጥ ተዋግተዋል፤ ከውስጥ እና ከውጭ ብዙ የሽብርተኞችን ጥቃት ተጋፍጠዋል። የአረቦች እና የፍልስጤማውይን ጥላቻ ሁልጊዜ በአይሁዶች ላይ ነው።
ይህ ሁሉ ግፍ እንዲፈስስባቸው እግዚአብሔር አስቀድሞ ወስኖባቸዋል። ነገር ግን እግዚአብሔር በወሰነው መጠን ብቻ ነው። እርሱ ከወሰነው አንዳችም አያልፍም። ስለዚህ አይሁዶች አይጠፉም። በስተመጨረሻ ይህ ሁሉ መከራና ስደት እየነዳ ወደ መሲሁ ያመጣቸዋል።
ትልቁ ሚስጥር መሲሁ ወደ አይሁዶች በመጣበት በመጀመሪያው ምጻቱ መከራ መቀበሉ ነው። ከዚያም አይሁዶች ይገፉታል። ስለዚህ የእሥራኤል ዘመን በዚያ ይቋረጣል።
ከዚያ በኋላ በታላቁ መከራ ዘመን ውስጥ እግዚአብሔር ወደ አይሁዶች ይመለሳል።
የተቋረጠውም የእሥራኤል ዘመን ከዚያ በኋላ ይቀጥልና በመጨረሻዎቹ ሶስት ዓመት ተኩል ውስጥ ይዘልቃል።
ራዕይ 11፡1 በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ፦ ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ።
2 በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።
42 ወራት ማለት 3½ ዓመታት ነው።
ራዕይ 11፡3 ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።
1,260 ቀናት ማለት እያንዳንዳቸው 360 ቀናት ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ 3½ ዓመት ነው።
144,000ዎቹን አይሁዳውያን ወደ መሲሁ ለመምራት ሁለት ነብያት ማለትም ሙሴ እና ኤልያስ ወደ እሥራኤል ይመለሳሉ።
ከዚያ በኋላ ሰባዎቹ ሱባኤዎች ይጠናቀቃሉ።