የውሃ ጥምቀት

”ባፕቲዝ” የሚለው የግሪክ ቃል መንከር ወይም ማስመጥ ማለት ነው፡፡

ጥምቀት የመሞት፣ የመቀበርና የመነሳት ምሳሌ ነው፡፡ ሰው ውሃ ውስጥ በሚቀበርበት ጊዜ ውሃው ሬሳ የሚቀበርበትን የመሬት መቃብር ይወክላል፡፡
ወደ ሮሜ ሰዎች 6፣3 ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?

4 እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።
5 ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤
በውሃ መጠመቅ በሃጢአት የተሞላው አሮጌ ማንነት በአፈር የተሸፈነ መቃብር ውስጥ መቀበሩን የሚያመለክት ሲሆን፤ አዲሱ ሰውም ውስጡ በክርስቶስ መንፈስ ተሞልቶ አዲስ ሕይወትን ለመጀመር ከተቀበረበት ውሃማ መቃብር ውስጥ ተነስቶ ይወጣል።ይህም አዲስ ሕይወት በሥጋዊ እና በዓለማዊ ኑሮ ላያ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ እና በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ሕይወት ነው።

የተለያዩ አይነት ጥምቀቶች ያሉ ሲሆን አብዛኞቹ ሙሉ በሙሉ ውሃ ውስጥ መነከር ከሚፈጥረው እርጥበትና መዝረክረክ ለማምለጥ ከመፈለግ የሚደረጉ ዓይነቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በርጭት ወይም በከፊል በመንከር የሚደረግ “ጥምቀት” በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አለው፡፡ ነገር ግን በሰውነታቸው ላይ አፈር በመርጨት ወይም ደግሞ ሰውነታቸውን በከፊል መቃብር ውስጥ በመክተት ብቻ ሰዎችን መቅበር አንችልም፡፡
ብዙዎቹ ያልዳኑ ሰዎችን ያጠምቃሉ፤ ነገር ግን ኃዋርያው ጴጥሮስ ይህንን አላደረገም፡፡
የሐዋርያት ሥራ 2 ፡ 38 ጴጥሮስም፡- ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ
ቅደም ተከተሉን አስተውሉ፤ በመጀመሪያ ንሰሃ በመቀጠልም በጥምቀት መቀበር።
እውነተኛ ንሰሃ ማለት ለራስ ወይም ለእኔነት መሞት ማለት ነው፡፡ መቅበር የምንችለውም የሞተ ሰውን ብቻ ነው፡፡
እውነተኛ ንሰሃ ስትገቡና ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችሁ ስትቀበሉ፣ አዲሱ እምነታችሁ ወዲያውኑ ከበድ ባለ ፈተና ይፈተናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተገለጸውን አይነት መጽሃፍ ቅዱሳዊ ጥምቀት በአሁኑ ወቅት ባሉ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ ሲከናወን አይታችሁ ታውቃላችሁ? ይህ ለማለፍ የሚከብድ ፈተና ነው፡፡
እስቲ አንዳንድ አማራጭ የጥምቀት ሥርዓቶችን እንመልከት፡፡
1. ጭራሽም በውሃ አለማጥመቅ፡፡ ይህ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የነበረውንና ሳይጠመቅ ወደ ገነት የገባው ወንበዴ ላይ በመመስረት ነው፡፡
ወንበዴው እኮ በመስቀል ላይ በመቸንከሩ የመጠመቅ እድል አልነበረውም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው የማጥመቅ ተልዕኮ የተሰጠው ከትንሳኤው በኋላ ነበር፡፡
ማቴዎስ 28፡19 እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥
20 ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።
“እያስተማራችኋቸው”፡፡ ማስተማር የሚለው ሃሳብ ሁለት ጊዜ ተደግሟል፡፡ መማር የሚያስፈልገን ከሆነ ያለ ትምሕርት ልንረዳ የማንችለው ነገር አለ ማለት ነው። ይህ ቀላል ሊመስለን ይችላለን እንጂ ቀላል አይደለም፡፡
በመጀመሪያ፣ ጥምቀት ውሃን በመሬት ፋንታ በመጠቀም የሚደረግ ቀብርን ይወክላል።
በመቀጠልም የእግዚአብሔርን ስም መማር ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር ብቻ ነው አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ በሚሉት ማዕረጎች ሊጠራ የሚችለው።
ከእነዚህ መጠሪያዎች ውስጥ ግን የትኛውም ስም አይደለም፡፡ ታዲያ የአብ፣ የወልድ፣ እና የመንፈስ ቅዱስ ስም ማነው? በሌላ አገላለጽ የእግዚአብሔር ስም ማነው?
የሚገርማችሁ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ይህንን ቀላል ጥያቄ ለመመለስ አይችሉም፡፡
ምክንያቱም ልክ እንደ ባቢሎን እና እንደ ግብጽ ቀሳውስት ሁሉ ብዙ ክርስቲያኖችም በሥላሴ ያምናሉ፤ በዚህም ምክንያት ለሦስቱ ሦስት ስሞችን መስጠት ይፈልጋሉ፡፡
«ሥላሴ» የሚለው ቃል በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ስለሚያምኑበት መፅሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነው «ሥላሴ» የሚለው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለውን የእግዚአብሔርን እውነተኛ ስም እንዳያዩ ያደርጋቸዋል፡፡
ያህዌ የሚለው ስም በብሉይ ኪዳን ላይ በጣም በርካታ ጊዜያት የተጠቀሰ ሲሆን ኢየሱስ የሚለው ስም ግን በብሉይ ኪዳን ውስጥ አንዴም እንኳ አልተጠቀሰም፡፡
ኢየሱስ የሚለው ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ በብዛት የተጠቀሰ ሲሆን ያህዌ የሚለው ስም ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንዴም እንኳ አልተጠቀሰም፡፡
በመሆኑም የብሉይ ኪዳኑ ያህዌ (መንፈስ) የአዲስ ኪዳኑን ሰው ኢየሱስን ሆነ።
ቆላስይስ 2፡9 በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።
በአሁኑ ወቅት ክርስትናን የሚወክሉ 40,000 የተለያዩ ዓይነት ቤተእምነቶች በአብዛኛው የሚለማመዱዋቸውን ሌሎች የጥምቀት አይነቶች በአጭሩ እንመልከት። የተለየ አመለካከት ያላቸው አዳዲስ ቤተእምነቶችም ደግሞ እየተበራከቱ ነው።
2. ሕፃናትን በጭንቅላታቸው ላይ ማንኛውንም አይነት ውሃ በመርጨት ማጥመቅ፡፡
ነገር ግን በግሪክ ባፕታይዝ የሚለው ቃል ማስጠም ማለት ነው፡፡
3. ሕፃናትን በጭንቅላታቸው ላይ ፀበል (የተቀደሰ ውሃ) በመርጨት ማጥመቅ።
ለመሆኑ የተቀደሰ ውሃ (ፀበል) የሚባል ነገር አለን?
አንድ ዝንብ የተቀደሰ ውሃ (ፀበል) ውስጥ ብትወድቅ ውሃው ይረክሳል ወይስ ዝንቧ ትቀደሳለች?

ይህ ክርክር ከጨለማው ዘመን ጀምሮ እንደተቀጠለ ነው፡፡ ፀበል እንደ ማንኛውም ውሃ ተራ ውሃ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ሳይጠቀሙት ቢቆዩ ፀበልም ልክ እንደ ማንኛውም ውሃ ይበላሻል፡፡ የፀበል መያዣ ዕቃም እንደ ሌሎች የውሃ ማስቀመጫዎች በየጊዜውመታጠብ አለበት፡፡
እግዚአብሔር ብቻ ነው ቅዱስ።
እግዚአብሔር የተገኘበት ቦታ ከእርሱ መገኘት የተነሳ የተቀደሰ ቦታ ይሆናል፡፡
በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በአይሁድ ቤተመቅደስ ውስጥ ከመኖሩ የተነሳ ቤተመቅደሱን ቅዱስ ሥፍራ አደረገው፡፡ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ያለው መቅደስ ውስጥ መኖሩ ኢየሩሳሌምን ቅድስት ከተማ አድርጓታል። እርሱ በእሥራኤል ዋና ከተማ በኢየሩሳልም መገኘቱ እስራኤልን ቅድስት ሃገር አድርጓታል፡፡
በ70 ዓ.ም. በጀነራል ታይተስ የሚመራው የሮማ ሠራዊት መቅደሱን አወደመው፡፡ ስለዚህ ከዚያ ወዲያ መቅደሱ የእግዚአብሔር ማደሪያ መሆኑ አብቅቷል፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እግዚአብሔር እንዴት በጴንጤቆስጤ ዕለት በወንዶች እና በሴቶች ልጆቹ ልብ ውስጥ ለመኖር በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካኝነት እንደመጣ ይገልጻል። በዚህም አሰራሩ እግዚአብሔር በሰው እጅ ያልተሰራ የራሱ መቅደስ ውስጥ ልጆቹን የማደሪያው መስሪያ ሕያዋን ድንጋዮች አድርጎ ለውጧቸዋል።
1ኛ ጴጥሮስ 2፡5 እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።
ዕብራውያን 9፡11 ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥
የሮም ወታደሮች የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ እንዳፈረሱ ሁሉ የሮማ ነገስታትም እግዚአብሔር በውስጣቸው በሚኖርባቸው ወንዶች እና ሴቶች የተሰራውን የእግዚአብሔርን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ማፍረስ የሚቻለው መስሏቸው ሦስት ሚሊዮን ክርስቲያኖችን ገድለዋል፡፡
ስለዚህ ዛሬ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣቸው የሚያድርባቸውን የተቀደሱ ወንዶች እና ሴቶች ማግኘት ይቻላል፤ ነገር ግን የተቀደሰ ውሃ ማግኘት አይቻልም ምክንያቱም እግዚአብሔር በውሃ ውስጥ አያድርም።
4. አንድ ሰው አውራ ጣቱን ውሃ ውስጥ ነክሮ በማውጣት የሕፃኑ ግንባር ላይ የውሃ መስመር በማስመር ሕፃናትን ማጥመቅ።

ይህ ሒንዱዎች በአመድ ከሚያደርጉት የተኮረጀ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ አደራረግ ማስመጥን አያካትትም።
5. ሕፃኑን ከጭንቅላቱ በቀር ሌላው የሰውነቱ ክፍል በሙሉ ውሃ ውስጥ እንዲገባ አንድርጎ በአነስተኛ የውሃ መያዣ ውስጥ ማጥለቅ፡፡ እንደዚህ አይነቶቹ ሰዎች ሕጻኑ ውሃ ውስጥ ሰምጦ እንዳይታፈን የሚፈሩ ይመስላሉ።
ነገር ግን ማጥመቅ ማለት ሙሉ በሙሉ መስመጥ ማለት ነው፡፡ እሬሳን ስንቀብር ጭንቅላቱን ከአፈር ውጭ አድርገን አንቀብርም፡፡
6. በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንደሚፈፀመው ሕፃኑን በአነስተኛ የውሃ መያዣ ዕቃ ውስጥ በፍጥነት ነክሮ ወይም አጥልቆ ማውጣት፡፡ ምክንያቱም « ባፕታይዝ » የሚለው ቃል በግሪክ «ማጥለቅ» ማለት ነው፡፡
በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 38 ላይ ጴጥሮስ በመጀመሪያ ንስሐ መግባት ከዚያ በኋላ መጠመቅ እንዳለብን ተናግሯል፡፡ ሕጻናት ንሰሃ መግባት አይችሉም ስለዚህ መጠመቅ የለባቸውም።
7. በአዋቂዎች ራስ ላይ ውሃ በመርጨት ማጥመቅ፡፡
ይህ ማጥመቅ ወይም ማስመት አይባልም፡፡
8. ውሃን ከአነስተኛ መያዣ ውስጥ በአዋቂዎች እራስ ላይ ማንቆርቆር ወይም ማፍሰስ፡፡
ይህም ማስመጥ አይደለም፡፡
9. አዋቂ ሰዎችን በተደጋጋሚ ጊዜ የወንዝ ውሃ ውስጥ ማስመጥ፡፡
ሰው የሚቀበረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
10. ሰዎችን ወደኋላቸው በማጋደም ፊታቸውን ወደ ላይ አድርጎ ውሃ ውስጥ ሦስት ጊዜ ማስጠም፡፡ በአብ (በያህዌ) ስም ማስመጥ፡፡ ሰውየውን ከውሃው በላይ እውጥቶ በወልድ (በኢየሱስ) ስም ማስመጥ፡፡ አሁንም ሰውየውን ከውሃው በላይ አውጥቶ በመንፈስ ቅዱስ ስም ማስመጥ (መንፈስ ቅዱስ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ስም የለውም)።
በመጀመሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ “በአብ ስም፣ በወልድ ስም እና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ” አላለም፡፡ ይህ ሦስት ስሞችን የሚያሳይ ነው፡፡
ማቴዎስ 28፡19 እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤
ኢየሱስ ስለ አብ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አንድ ስም ተናግሯል፡፡
በመሆኑም ሦስት መጠሪያዎች ያሉት እግዚአብሔር ስሙ ማን እንደሆነ ለመገንዘብ ትምህርት ያስፈልገናል፡፡
ሦስት ስሞች ቢኖሩ ኖሮ ትምህርትም አያስፈልግም ነበር፡፡ ለሁላችንም ግልፅ እንደሆነው ሦስት አካላት ሦስት ስሞች ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡
በመቀጠልም፤ አንድ ሰውን አንድ ጊዜ እንቀብረዋለን እንጂ ሦስት ጊዜ አንቀብረውም፡፡
የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ማን ነው? አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ማዕረጐች እንጂ ስሞች አይደሉም፡፡
(ያህዌ የአብ ስም ሲሆን፤ ኢየሱስ ደግሞ የወልድ ስም ነው፡፡ ነገር ግን መፅሐፍ ቅዱስ ላይ ለመንፈስ ቅዱስ የተሰጠ ስም የለም)፡፡ በስላሴ የሚያምኑ ክርስቲያኖች ለሦስት አካላት ሁለት ስሞች አሏቸው፡፡ ይህ ብዙም አሳማኝ አይደለም፡፡ በጥምቀት ወቅት «አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ» የሚለው የማጥመቂያ ቀመር የእግዚአብሔርን ስም አይገልፅም፡፡ ምክንያቱም እንድናጠምቅ የታዘዝነው በስሞች (ማለትም ብዙ ቁጥር) ሳይሆን በአንድ ስም ብቻ ነው፡፡ ለሦስት አካለት ሁለት ስሞች፡፡ ለችግሩ አስደሳች መፍትሄ የሚሰጥ አይደለም፡፡
አብ እና መንፈስ ቅዱስ አልሞቱም፤ አልተቀበሩም እንዲሁም ከሞት አልተነሱም፡፡ በመሆኑም የውሃ ጥምቀት እነርሱ ያደረጉትን የሚገልጽ አይደለም፡፡
ሌላ ትልቁ ችግር በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም ቦታ የመንፈስ ቅዱስ ስም ማን እንደሆነ ያልተጠገለጠልን መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ስሙ ማን እንደሆነ ሳናውቅ (በተለይም መንፈስ ቅዱስ በመለኮት ውስጥ እራሱን የቻለ አካል ነው ብለን አጥብቀን የምናምን ከሆነ) «በመንፈስ ቅዱስ ስም» ማለቱ ምን ትርጉም ይኖረዋል ?
11. ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሚሞትበት ጊዜ ወደፊት ለፊት በማዘንበሉ በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ ጊዜ ወደፊት በደረት በኩል ማስመጥ።
ሰዎችን የምንቀብራቸው ፊት ለፊት ደፍተን ሳይሆን በጀርባቸው አንጋልለን ነው፡፡
ይህም ዘዴ ቢሆን የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ማን እንደሆነ አይነግረንም፡፡ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ስም ከሦስቱ ማዕረጐቹ ጋር በመደባለቅ ስሙን የሚመለከቱ ጉዳዮችን አድበስብሰው ያልፋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሦስቱ ማዕረጐች ስም እንደሆኑ መቁጠር ነው፡፡ «አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ» ስም ነው ማለት ብዥታ ያለበት አስተሳሰብ ነው፡፡
12. ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ ጊዜ ወደኋላ አንጋሎ መንከር፡፡ ይህ አጠማመቅ የመቀበርን ፅንሰ ሐሳብ በትክክል ይገልጻል፤ ነገር ግን የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስም ማን እንደሆነ አይገልፅም፡፡ ሦስት ማዕረጐች ማለትም አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ አንድን ስም መተካት አይችሉም፡፡
መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚህ መንገድ የተጠመቀ አንድም ሰው የለም፡፡
13. ለኃጥያት ስርየት «በኢየሱስ ስም» ብቻ አንድ ጊዜ ወደኋላ አንጋሎ ውሃ ውስጥ ማስጠም፡፡
ሐጢአታችን የታጠበው በጥምቀት ውሃ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡
ራእይ 1፡5 ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥
ልብ ይበሉ፤ በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች ወላጆቻቸው ኢየሱስ (ጂሰስ) የሚል ስም አውጥተውላቸዋል፡፡ በመሆኑም የትኛውን ኢየሱስ እንደሆነ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስን ወይም ጌታ ኢየሱስን እንደሆነ በተለይ መጥቀስ ያስፈልገናል፡፡ አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አለ፡፡
14 በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በጀርባ አንጋሎ አንድ ጊዜ ውሃ ውስጥ ማስመጥ፡፡

ይህ በክርስቲያኖች መካከል በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያጣ አጠማመቅ ነው፡፡
እያንዳንዱ ክርስቲያን ለራሱ ደስ የሚለውን ዓይነት የአጠማመቅ ሁኔታ ይመርጣል። ምንም እንኳን ከመረጡት አጠማመቅ ውጭ ሌላ ዓይነት አጠማመቆችን የማይቀበሉ ቢሆንም ግን በመቻቻል ዓይነት ያልፏቸዋል፡፡
ነገር ግን ብቸኛው የሚያበሳጫቸው የአጠማመቅ ዓይነት በመጨረሻ የተጠቀሰው ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚደረገው ነው፡፡ እግዚአብሔር ሥላሴ ነው የሚለውንና አጥብቀው የሚሟገቱለትን እምነታቸውን ዝቅ ስለሚያደርግ ብቸኛው የማይቀበሉት አጠማመቅ ይህ ነው፡፡ በሥላሴ ማመን በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን (የባቢሎን ምስጢር) አማካኝነት ወደ ክርስትና ውስጥ የገባ ዋነኛ የባቢሎን ምስጢር እምነት ሲሆን፤ ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የወጡት የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያናትም በብዙ ነገር ከሮማ ካቶሊክ ቢለዩም ሥር ከሰደደው የሥላሴ አስተምህሮ ግን መላቀቅ አልቻሉም፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ጊቦን የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን «ክርስትና የተነሳ አረማዊነት» ብሎ ይገልጻታል፡፡
በመሆኑም ጥምቀት የመታዘዝ እርምጃ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ጥምቀት ማለት ምን እንደሆነና በተለይ ደግሞ የእግዚአብሔር ስም ማን እንደሆነ ያለንን ግንዛቤ የሚለካ መመዘኛ ወይም ፈተና ነው ?
የእግዚአብሔር ስምን ታውቃላችሁ? የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስን ስም ታውቃላችሁ?
ማቴዎስ 3፡6 ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።
የምንድነው ኃጥያችንን ስንናዘዝና ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችን ስንቀበል ነው፡፡
እዚህ ላይ ጥምቀት ኃጥያትን ከመናዘዝ ጋር የተያያዘ ሲሆን ኃጥያትን መናዘዝም ለመዳን አስፈላጊ ነው።
ይህ ሕፃናትን አይመለከትም፡፡
ማቴዎስ 3፡11 እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ (ክርስትና ቀላል ሕይወት ወይም ቀልድ አይደለም)
በድጋሚ ጥምቀት ከንስሐ ጋር ይያያዛል፡፡ ዮሐንስ ሲናገር የነበረው ለአዋቂዎች እንጂ ለሕፃናት አይደለም።
ማቴዎስ 3፡13 ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።
14 ዮሐንስ ግን፡- እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር።
15 ኢየሱስም መልሶ፡- አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት።
« ጽድቅ» - ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት በትክክል መጓዝ እችላለሁ?
የእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛ ነው፡፡
አብራሐም እግዚአብሔርን አመነ - ይህም ፅድቅ ሆኖ ተቆጠረለት፡፡
ዘፍጥረት 15፡6 አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት።
«መፈጸም» የቀድሞውን ትንቢት ወይም የሕጉን ጥላ መፈጸም
ኢሳይያስ 42፡21 እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ ወደደ።
ሮሜ 10፡4 ሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።
ሕጉ በውስጡ የተሰጡትን ተስፋዎች ወደ ፍጻሜ የሚያመጣቸውን ክርስቶስን ይጠቁም ስለነበረ ሕጉ ፃድቅ ነበር። ሕጉ ሊመጣ ላለው ጥላ ስለነበረ ነገሮች በሕጉ ዝርዝር ውስጥ በተፈፀሙበት መንገድ በክርስቶስም ላይ መፈፀም ነበረባቸው፡፡
ከቀድሞው ሐይማኖት (የአይሁድ እምነት) ጋር የሚጣጣምና በዚያ ውስጥ የነበሩትን ጥላዎች ሁሉ በትክክል አካል የሚያለብሳቸው እምነት ክርስትና ብቻ ነው፡፡
ቆላስይስ 2፡16 እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ።
17 እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።
ዕብራውያን 8፡4 እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤
5 እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና።
ዕብራውያን 10፡1 ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።
በመሆኑም ልክ ነብዩ ሙሴ ሊቀ ካህናቱን አሮንን በዘይት ከመቀባቱ በፊት እንደአጠበው ሁሉ ሊቀካህናቱ ክርስቶስም በተመሳሳይ መንገድ በነብይ መታጠብ ነበረበት፡፡
ዘሌዋውያን 8፡5 ሙሴም ማኅበሩን፡- እግዚአብሔር ይደረግ ዘንድ ያዘዘው ነገር ይህ ነው አላቸው።
6፤ ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው።
የአሮን ልጆች ከአሮን በኋላ ሊቀ ካህናት እንዲሆኑ ተጠርተዋል፡፡
ዘሌዋውያን 8፡12 ከቅብዓቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ ይቀድሰውም ዘንድ ቀባው።
ዮሐንስ 1፡32 ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፡- መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ።
በመሆኑም ሊቀ ካህችን ኢየሱስ ሕጉን ሁሉ ለመፈጸም ሲል በነብዩ በዮሐንስ ከታጠበ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል፡፡
ስለ እኛ የኃጥያት መስዋእት ሆኖ ለመቅብም ስለሆነ ታጥቧል፤ በእኛ ፈንታ የሲኦልን ስቃይ በመቀበልም ስለ እኛ የሚቃጠል መስዋእት ሆኖ የኃጥያታችንን ዋጋ ከፍሏል።
2ኛ ዜና 4፡6 ደግሞም አሥር የመታጠቢያ ሰኖች ሠራ፥ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው ነገር ሁሉ ይታጠብባቸው ዘንድ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ኵሬው ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር።
ኢየሱስ የእኛ የመስዋዕት በግ ነበር፡፡ እርሱ የሚቃጠል መስዋዕታችን ነው፡፡ በመሆኑም በውሃ መታጠብ ነበረበት፡፡ ይህም በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ተፈፀመ፡፡
ዘጸአት 12፡8 በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል።
9 ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት።
10 ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት።
በቀራንዮ የተሰቀለው “የመስዋእታችን በግ” የሞትንና የሲኦልን ቁልፎች ከሰይጣን ላይ ለመንጠቅ እና የተናዘዝናቸውን ኃጥያቶቻችንን በዲያብሎስ ላይ ለማራገፍ በሲኦል እሳት ላይ በመረማመዱ “የሚቃጠል መስዋዕታችንም” ሆኗል፡፡
በእሳት መጥበስ፡፡ ይህ የሚወክለው የሲኦልን እሳት ነው፡፡ ምንም ዓይነት ውሃ የለም፡፡ እሳት ከፈላ ውሃ የበለጠ ያቃጥላል፡፡ ኢየሱስ በተቀበለው መከራ ውስጥ አንዳችም ምሕረት አላገኘም።
ከበሉት ሥጋ ላይ የተረፈ ሁሉ በእሳት ይቃጠላል እንጂ በኋላ ለመብላት ተብሎ አይቀመጥም። የተወሰነው ይበላል የቀረው ተቃጥሎ አመድ ይሆናል። ኢየሱስ ለእኛ የፋሲካ በግ ሲሆን በሞተበትም ጊዜ መበስበስን አላየም፤ ምክንያቱም የሞተ ጊዜ መበስበስ ከመጀመሩ በፊት በሦስት ቀናት ውስጥ ተነስቷል፡፡
መስዋዕት ጥቅም ላይ የሚውለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን የሚተርፈው በሙሉ ይቃጠላል፡፡ ይቃጠላል ሲባል የሚያገለግለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው ማለትም ነው፡፡ ለኃጥያት አንድ መስዋእት ብቻ፤ እርሱም አንድ ጊዜ ብቻ፡፡
ራእይ 1፡15 እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር…
የዮሐንስ ራእይ 1፡18 ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።
ኃጥያታችንን የኃጥያት ምንጭ በሆነው በዲያቢሎስ ላይ ሊያራግፍ የእኛን ኃጥያት ተሸክሞ በሲዖል እሳት ውስጥ አለፈ፡፡
ሐጢአት የለሽና ፍፁም ስለነበረ የሲኦል እሳት እርሱን ሊያቃጥለውና ሊያጠፋው አልቻለም፡፡
ነብዩ መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን እንደ ሊቀካህናት አጠበው፡፡ በመቀጠልም መንፈስ ቅዱስ በላዩ ላይ በወረደበት ጊዜ ኢየሱስ ተቀባ፡፡
ወንጌል 3፡16 ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤
መቀባት ማለት ዘይቱን በመጠጣት ወደ ሰውነት ውስጥ ማስገባት ሳይሆን በሰውየው ሥጋ ላይ ማፍሰስ ማለት ነው፡፡
በመሆኑም መንፈስ ወደ ውስጡ አልገባም፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያም በመንፈሱ ስለተፀነሰ መንፈስ በውስጡ ነበረ።
ማቴዎስ 1፡20 እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፡- የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።
በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ አባቱ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም አባቱ ነበር፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ አንድ መንፈስ ነው።
ኤፌሶን 4፡4 በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤
ኢሳይያስ 43፡11 እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።
እንደ ሁለተኛ አካልና እንደአዳኝ ከእግዚአብሔር ዙፋን አጠገብ የሚቆም ኢየሱስ የለም፡፡
ዮሐንስ 1፡33 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፡- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።
ኢየሱስ በእርሱ ላይ በወረደበትና ባረፈበት መንፈስ ቅዱስ ተቀባ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ ውስጡ አልገባም፡፡ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ አልተጠመቀም፡፡ እርሱ ሌሎችን በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ ነው እንጂ፡፡
ማቴዎስ 4፡1 ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥
2 አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ።
3 ፈታኝም ቀርቦ፡- የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው።
4 እርሱም መልሶ፡- ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው።
5 ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ።
6 መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።
ሰይጣን አንድ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስን ወስዶ ከሌላው ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር እንዲጋጭ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡
የማቴዎስ ወንጌል 4፡7 ኢየሱስም፡- ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው።
ኢየሱስ ደግሞ ሌላ የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል ጠቅሰለት፡፡ የሰይጣን ስህተት አንደ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይዞ ከሌሎቹ ጋር እንዲጣረስ ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡
በአንድ ጥቅስ (ማቴ 28፡19) ላይ በመመስረት ከሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጋር እንዲጋጭ አታድርግ።
ማቴዎስ 28፡19 እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤
ኢየሱስ ይህንን ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል፡፡
ሂዱ እና አጥምቁ የባሉትን ትዕዛዝ እንዴት እንደፈጸሙ ተመልከቱ፡፡
የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፡- ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤አላቸው።

የሐዋርያት ሥራ 8፡16 በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና።
የፊሊጶስ አገልግሎት ይህ ነበር፡፡
የሐዋርያት ሥራ 8፡38 ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም።

ሁለቱም ወደ ውሃው ውስጥ ገቡ፡፡ ፊሊጶስ ያጠመቀው በደረቅ መሬት ላይ ቆሞ ውሃ በመርጨት አልነበረም፡፡
የሐዋርያት ሥራ 10፡46 በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና።
47 ፤ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፡- እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ።
መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ቢሆንም የግድ በውሃ መጠመቅ ነበረባቸው፡፡
የጌታ ስም ማነው ?
ፊልጵስዩስ 2፡11 መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ኤፌሶን 4፡5 አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤
የሐዋርያት ሥራ 19፡5 ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤
ይህ የጳውሎስ አገልግሎት ነበር፡፡
ሮሜ 6፡3 ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?
እግዚአብሔር አብ እና መንፈስ ቅዱስ አልሞቱም፡፡ በመሆኑም በእነርሱ ሞት ልንጠመቅ አንችልም፡፡
1ኛ ቆሮንቶስ 10፡2 ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤
አይሁድ በተከፈለው የኤርትራ ባሕር ውስጥ ውሃው በግራ እና በቀኛቸው እንደ ግድግዳ ቆሞ በመሃከሉ ተሻገሩ፡፡ ሙሴ የሚለው ስም ትርጉሙ ከውሃ ውስጥ የተገኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነርሱ በሙሴ ስም ተጠምቀው ከውሃ ውስጥ በሕይወት ወጥተዋል፡፡
የፈርኦን ሠራዊትም (ፈርኦን የማዕረግ መጠሪያ ነው) ወደ ባህሩ ገብተው ነበር ነገር ግን ሞተዋል፡፡ በሙሴ ስም መጠመቅ አይሁድን አድኗቸዋል፡፡ በፈርኦን ስም (በማዕረግ) መጠመቅ ግብፃዊያንን ገደላቸው፡፡
በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ለዳግም ምፅአቱ ያዘጋጀናል፡፡
አብ፣ ወልድ፣ እና መንፈስ ቅዱስ በሚባሉ ማዕረጎች መጠመቅ ምንም እንኳን ኢየሱስን እንደ አዳኝ ብንቀበለውም ወደ ምንሞትበት ወደታላቁ መከራ ለመግባት ነው የሚያዘጋጀን፡፡
የፈርኦንን ስም ማንም አያውቀውም፡፡
የትኛውም የሥላሴ እምነት ተከታይ የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን ስም አያውቅም፡፡
1ኛ ቆሮንቶስ 15፡29 እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው?
አንዳንድ ሰዎች ሳይጠመቁ ለሞቱ የቤተሰብ አባላት ብለው መጠመቅ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡ ሰው ከጥምቀት በፊት ንሰሃ መግባት አለበት፡፡ ሙታን ደግሞ ንሰሃ መግባት አይችሉም፡፡ ጥምቀት የሚገልጸው መቀበርን ነው፡፡ ሞቶ የተቀበረን ሰው ድጋሚ መቅበር አይቻልም፡፡ በመሆኑም አስተሳሰባቸው ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ አሁንም የሚያሳየን ጥምቀት ከሞት፣ ከቀብርና ከትንሳኤ ጋር እንደሚያያዝ ነው፡፡
ገላትያ 3፡27 ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።
በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም እንድንወስድ ይረዳናል፡፡
ሚስት የባልዋን ስም ትወስዳለች፡፡ ልክ እንደዚሁ የክርስቶስ፣ ሙሽራ ማለትም እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን፣ ስሙን መውሰድ አለባት፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው ወይዘሮ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን ለመውሰድ አይደለም።

ማቴዎስ 4፡10 ያን ጊዜ ኢየሱስ፡- ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።
11 ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር።
ከመጠመቅ በኋላ ተከትሎ መምጣት ያለበት በቃሉ ውስጥ የተፃፈውን ሁሉ ማመን ነው፡፡ ቃሉን ማመን ጠላት በሕይወታችን ላይ ተፅዕኖ እንዳያደርግ ለመከላከል ተመራጩ መንገድ ነው፡፡
እንዴት አድርገን ነው ማቴዎስ 28፡19ን ስለ ጥምቀት ከሚገልፁት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር ልናስታርቀው የምንችለው?
በቀላሉ የአብ፣ የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስ ስም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ በመገንዘብ ነው።
ኤፌሶን 4፡5 አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤
እንደዚህ ብቻ ነው አንድ ጥምቀት ብቻ ልንጠመቅ የምንችለው።
ማቴዎስ 28፡18 ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፡- ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ።
19 እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥
20 ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።
መማር ያስፈልገናል፡፡ ስም አንድ ወይም ነጠላ ቃል ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ስም ነው፡፡ እግዚአብሔር ሦስት የማዕረግ መጠሪያዎች አሉት፤ እንዚህም ማዕረጎች «አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ» ይባላሉ። ስሙ ግን ማን እንደሆነ መማር ያስፈልገናል፡፡
ጥምቀት የእግዚአብሔርን ስም ማወቅ አለማወቃችሁን ማጋገጫ ፈተና ነው፡፡
«እግዚአብሔር አብ» የሚለው መጠሪያ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ሲሆን በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 16 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፡፡
ዮሐንስ 6፡27 ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።
«እግዚአብሔር ወልድ» የሚለው አጠራር መፅሐፍ ቅዱሳዊ ባለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጊዜ እንኳ አይገኝም፡፡
ነገር ግን «የእግዚአብሔር ልጅ» የሚለው መጠሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ በመሆኑ 52 ጊዜ ያህል ይገኛል፡፡
እንደዚህ አይነት ልዩነት ለምን ተፈጠረ?
ዮሐንስ 4፡24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሥጋና ደም አይደለም፡፡ ልጅ የሚለው ቃል የክርስቶስን ሰብዓዊነት የሚያሳይ ሲሆን አብ የሚለው ቃል ልዕለ ተፈጥሮ የሆነውን መለኮታዊ ባህሪ የሚያሳይ ነው፡፡
እግዚአብሔር ወልድ የሚል መጠሪያ እግዚአብሔር ስጋ እና ደም እንደሆነ አድርጐ የሚያሳይ በመሆኑ ስህተት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ልጅ የሚለው ቃል ሰው የሆነው ኢየሱስ በውስጡ ለሚኖረው የመለኮት መንፈስ እንደሚገዛ የሚያሳይ ነው፡፡
ዮሐንስ 14፡10 … ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሰራል።
«እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ» የሚለው አጠራር መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ ይህ አገላለጽ መጽፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጊዜ እንኳ አይገኝም፡፡ ለምን ?

እግዚአብሔር አብ ከአይሁድ ሕዝብ በላይ የረበበ ልዕለ ተፈጥሮ መንፈስ ነበር፡፡ ይህም መንፈስ የእግዚአብሔር ሙላት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ምሉዕነት ለመግለፅ ሌላ ምንም ተጨማሪ ነገር አላስፈለገም፡፡ «እግዚአብሔር አብ» እግዚአብሔርን በሙላት የሚገልጽ መጠሪያ ነው፡፡

አሁን የእግዚአብሔር ልዕለ ተፈጥሮ መንፈስ የሚኖረው ስለ ኃጢያታችን መስዋዕት ሆኖ በምሕረት ዙፋኑ ላይ በተቀመጠው በኢየሱስ ሥጋ ውስጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ወሰን የሌለው ሲሆን እኛን ሊመራንና ሊጠብቀን መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ከምህረቱ ዙፋን ይመነጫል፡፡ በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ልዕለ ተፈጥሮአዊነት ሙሉ በሙሉ የሚገልፅ ሲሆን እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ለመግለጽ ግን በምህረት ዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን ሰው የሆነውን የኢየሱስን ሰብዓዊ ባህርይም መጥቀስ ያስፈልገናል፡፡ ኢየሱስ የማይቻለውን ችሏል፤ ማለትም በአንድ ጊዜ ሰውም እግዚአብሔርም ሆኗል፡፡ የኢየሱስ ልዕለ ተፈጥሮአዊ መገለጫው መንፈስ ቅዱስ ሲሆን ሰብአዊ ወይም የሰውነት መገለጫው ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ነው፤ እርሱም ስለ ኃጢያታችን የሞተውና አሁን በምሕረት ዙፋን ላይ የተቀመጠውነው፡፡ እነዚህ ሁለት መገለጫዎች አንዳቸው ከሌላው ተነጥለው ከተቀመጡ እግዚአብሔርን በሙላት አይገልጹትም፡፡ በመሆኑም «እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ» ወይም «እግዚአብሔር ወልድ» ማለት አንችልም፡፡
ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚገልፁት ሰብአዊና ልዕለ ተፈጥሮአዊ መገለጫዎች በአንድ ላይ ተጣምረው እግዚአብሔርን በሙላት ይገልጹታል፡፡
ኢየሱስ ለዲያቢሎስ ምን እንዳለው ታስታውሳላችሁ? እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ስለዚህ ለቃሉ ታማኝ መሆንን መለማመድ ያስፈልገናል፡፡
ማቴዎስ 16፡15 እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።
16 ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።
17 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።
18 እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።
19 የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።
አለቱ የሚወክለው የኢየሱስ ማንነት መገለጥ ነው፡፡
አለቱ ክርስቶስ ነው፡፡
1ኛ ቆሮንቶስ 10፡4 ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።
አለቱ ጴጥሮስ አይደለም፡፡ ጴጥሮስ ከአራት ቁጥሮች ወዲያ ሰይጣን ተብሎ ተጠርቷል፡፡
ማቴዎስ 16፡23 ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤
ከዚያ በኋላ እንደውም ጴጥሮስ ኢየሱስን ከመሰቀሉ በፊት ሦስት ጊዜ ክዶታል፡፡
ማቴዎስ 7፡24 ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።
25 ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።
ሉቃስ 3፡7 ስለዚህ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር፡- እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?
8 እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፡- አብርሃም አባት አለን ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል እላችኋለሁና።
ንስሐችን እውነተኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ከሌለ በስተቀር መጠመቅ አይኖርብንም፡፡ ከልባችን ያልሆኑ ቃላትን በትክክል ልንናገር እንችላለን ግን እንደዚህ አይነቱ ንሰሐ ዋጋ የለውም፡፡
ሉቃስ 7፡29 የሰሙትም ሕዝብ ሁሉ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው እግዚአብሔርን አጸደቁ፤
30 ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ስለ አልተጠመቁ የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው ጣሉ።
በአግባቡ ካልተጠመቅን የእግዚአብሔርን ምክር አልያዝንም ማለት ነው፡፡
እግዚአብሔር ማን እንደሆነ በትክክል ካላወቅን ስሙንም ስለማናውቀው በተሳሳተ መንገድ እንጠመቃለን፡፡
ማቴዎስ 16፡19 የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።
ጴጥሮስ ምን አሰረ?
ጴጥሮስ ምን ፈታ?
ዮሐንስ 1፡33 እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፡ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ።
የውሃ ጥምቀትን ተከትሎ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መምጣት አለበት፡፡
ዮሐንስ 16፡13 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።
የመንፈስ ቅዱስ መገኘት ማረጋገጫ ሁሉንም የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል እንድታምኑ ማስቻሉ ነው፡፡
ጴጥሮስ የመጥምቁ ዮሐንስን ጥምቀት አሰረና በኢየሱስ ስም ሚሆን አዲስ ጥምቀትን ፈትቶ ለቀቀ።
የሐዋርያት ሥራ 2፡36 እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።
ጴጥሮስ ለሕዝቡ መጀመሪያ የኢየሱስን ማዕረጎች ነገራቸው። እነዚህም ማዕረጎች ጌታ እና ክርስቶስ መሆናቸውን ካስተማራቸው በኋላ የእግዚአብሔር ስም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ገልጦላቸዋል፡፡
የሐዋርያት ሥራ 2፡38 ጴጥሮስም፡- ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
ከኃጥያት የምንፈታበትን ሒደት በማሳየት ከኃጥያታችን ፈታን፤ ይህም ሒደት፡- ንስሐ መግባት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ እና የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት መቀበልነው፡፡
የሐዋርያት ሥራ 8፡12 ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ።
13 ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ።

14 በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው።
15 እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤
16 በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና።
የሐዋርያት ሥራ 8፡38 ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም።
(በመርጨት ሊያጠምቀው ቢፈልግ ሁለቱም ወርደው ወደ ውሃ ውስጥ እንዲገቡ ባላስፈለጋቸው ነበር።)
የሐዋርያት ሥራ 19፡1 አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ።
2 ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም፡- አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት።
3 እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም፡- በዮሐንስ ጥምቀት አሉት።
(ጴጥሮስ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የሚገኝበትን ቁልፍ ከፍቷል፤ መንፈስ ቅዱስም ወደ እውነት ሁሉ ይመራቸዋል፤ ይህም እውነት ንስሐ መግባትና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ነው።)
4 ጳውሎስም፡- ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው።
(ጳውሎስ የጴጥሮስ ጥምቀት የዮሐንስን ጥምቀት እንዳሰረ ነገራቸው። የዮሐንስ ጥምቀት ጴጥሮስ በቀራንዮ መስቀል ላይ የተሰዋልንን የአዳኛችንን ስም በገለጠ ጊዜ ጠለቅ ያለ ምስጢር ላለው ሌላ ጥምቀት ሥፍራውን ለቋል።
ስለዚህም በጌታ በኢየሱስ ስም ካልተጠመቅክ በድጋሚ መጠመቅ ያስፈልግሃል፡፡)
5 ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤
የሐዋርያት ሥራ 10፡44 ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።
የሐዋርያት ሥራ 10፡47 እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?
48 በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀን እንዲቀመጥ ለመኑት።
(መንፈስ ቅዱስን ብትቀበሉም እንኳ በጌታ ስም መጠመቅ አለባችሁ።)
ፊልጵስዩስ 2፡11 መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ዘዳግም 6፡4 እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤
ዘካርያስ 14፡9 እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል።
ማርቆስ 12፡29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፡- እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥
1ኛ ቆሮንቶስ 8፡6 ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።
ኤፌሶን 4፡5 አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤
ቆላስይስ 3፡17 እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
ጥምቀት ተግባር ነው፤ የእምነት ቃልም ነው፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ስም መደረግ አለበት፡፡
ሮሜ 6፣3 ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?
4 እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።
5 ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤
ጥምቀት የመሞትና የመቀበር ምሳሌ ነው፡፡
በጀርባችን ተኝነት ለመተንፈስ በማንችልበት ሁኔታ በአፈር ተሸፍነን የምንቀበረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
በውሃ ውስጥ በጀርባችን በምንንጋለልበት ጊዜም መተንፈስ አንችልም፡፡ ይህ ቀጥተኛ የሆነ የመሞትና የመቀበር ተምሳሌት ነው፡፡
የትኛውም ደቀመዝሙር በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳልተጠመቀ ልብ በሉ፡፡
ለምን? ምክንያቱም እግዚአብሔር ስለ ኃጢያታችን ለመሞት ሰው ሆኖ እንደመጣ ያውቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ሰብአዊ ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ይህ የኢየሱስን መሞት፣ መቀበርና ከሙታን መነሳት ለሚወክለው የውሃ ጥምቀት ቁልፍ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡
ኤፌሶን 3፡14-15 ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤

የኢየሱስ ክርስቶስን ስም መውሰድ መላበስ አለብን፡፡
2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2 በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤
ሙሽራይቱ የኢየሱስ ክርስቶስን ስም መውሰድ አለባት፡፡ ይህ የሚሆነው መች ነው? በጥምቀት ሰዓት ካልሆነ መች ሊሆን ነው?
የጥፋት ውሃ የመጣ ጊዜ ምድር በውሃ ተሸፍና አንድ ጊዜ ተጠምቃለች፡፡
እያንዳንዳችን ጭብጥ ትቢያ ወይም አፈር ነን፡፡ ስለዚህ እኛም የባላችንን የኢየሱስን ስም እንወስድ ዘንድበውሃ መጠመቅ አለብን፡፡